Netsanet: März 2017

Samstag, 25. März 2017

የቀድሞው የአንድነት  ፓርቲ ወጣቶች ጉዳይ ምክትል ኃላፊን ጨምሮ ዘጠኝ ሰዎች የሽብር ክስ ተመሰረተባቸው

ነገረ ኢትዮጵያ 

የቀድሞው የአንድነት  ፓርቲ ወጣቶች ጉዳይ ምክትል ኃላፊን ጨምሮ ዘጠኝ ሰዎች የሽብር ክስ ተመሰረተባቸው

(በሰማያዊ ፓርቲ ብሄራዊ ሸንጎ የህዝብ ግንኙነት ንዑስ ኮሚቴ)

የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ በ1996 ዓ/ም የወጣውን የወንጀል ሕግ አንቀጽ 35 ፣ 32/1/ሀ  እና የፀረ-ሽብርተኝነት አዋጅ ቁጥር 652/2001 አንቀፅ 4 ሥር ተላልፈዋል በሚል   ክስ የመመረተባቸው ሲሆን አቃቢ ህግ በክሱ ላይ የአርበኞች ግንቦት 7 ድርጅት ውስጥ አባል በመሆን ከሀገር ውጭ ከሚገኙ የሽብር ቡድኑ ከፍተኛ አመራሮች ጋር ግንኙነት በመፍጠርና ተልዕኮ በመቀበል በሀገር ውስጥ አባላትን በመመልመልና በማደራጀት የኢትዬጵያ መንግስት በትጥቅ ትግል በሀይል የመለወጥ የፖለቲካ ዓላማ በመያዝ የሀገሪቱን ሕገ- መንግስታዊ ፣ ፖለቲካዊ ፣ኢኮኖሚያዊ ና ማህበራዊ ተቋማትን ለመናድና ለማፈራረስ በአዲስ አበባ ከተማ በተለያዩ ቦታዎች ላይ አባላትን በመመልመልና በማደራጀት የሽብር ተግባር እንዲፈፀም ተልዕኮ በመስጠትና በመቀበል  የሽብር ድርጅቱን አላማ ለመፈፀም ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ናቸው በማለት በክስ ዝርዝሩ ላይ ገልፀዋል። 

በአቃቤ ህግ እንደተገለፀው ተከሳሾቹ  አድራሻቸው አዲስ አበባ ሲሆን 
1. ክንዱ መሐመድ አስፋው 

2. መሐመድ ካሳ እብሬ 

3. ደረጄ አያሌው ህብስቴ 

4. ኤፍሬም ሰለሞን ለማ (የቀድሞው አንድነት የወጣቶች ጉዳይ ምክትል ኃላፊ (ከታች በምስል የሚታየው ))

5. አብርሃም ሰለሞን ከበደ ( የቀድሞው አንድነት አባል)

6. ጴጥሮስ ጉግሳ ለማ 

7. ዘሪሁን አግዜ ካሳዬ 

8. ተመስገን አልማው በላይ

9. ግሩም መርቅነህ ተገኑ  ናቸው። 

የአቃቤ ህግ ክስ እንደሚያሳየው ዳዊት ከሚባል የሽብር ቡድኑ አመራር ጋር በስልክና በዋትስ አፕ ግንኙነት በመፍጠር በአዲስ አበባ ከተማ በተለያዩ አካባቢዎች የነዳጅ ማደያዎችን ለማቃጠል ሲንቀሳቀሱ ተይዘዋል የሚል ነው።ተከሳሾቹ ከአምስት ወራት በላይ በማዕከላዊ በእስር ላይ የቆዩ መሆናቸው ይታወቃል።

http://wp.me/p5L3EG-fu

Sonntag, 12. März 2017

ጨለማውን ከማውገዝ አንድ ሻማ ማብራት መስቀሉ አየለ

​ጨለማውን ከማውገዝ አንድ ሻማ ማብራት
መስቀሉ አየለ

  ሞት በቆሸው ሰፈረ የሚል ዜና በአለም አቀፍ የዜና ማሰራጫዎች ጭምር ይናኛል፤ ወትሮስ በዚያ መንደር ህይወት ያለ ይመስል፤ ሞቶ በማለፍና እየሞቱ በመኖር መካከል ልዩነት በማይታይበት፤ ሞትና ህይወት ድንበር ከመጋራት ባለፈ ተወራራሽ ትርጉም በያዙበት የዚህ ክፉ ስርዓት መገለጫ በሆነ በዚህ መንደር;ድሆች የመኖር ተስፋችን ብለው የተደገፉት ሃብታም በልቶ ያስታወከው- አላምጦ የተፋው ቅርሻት ለነርሱ ግን የዕለት እስታንፋሻቸው ሆኖ እንዳልኖረ ዛሬ ሸክሙ በዝቶበት እርሱም ከስሩ የተኮለኮሉትን እኒህን የምድር ጎስቋሎች እስከ ወዲያኛው ይዞዋቸው ሄደ፤ ወያኔ የእንጨት ለቃሚዎቹን ልጅ በጥይት አረር ሲቆላ አንድ ነገር የማይተነፍሰው ቢቢሲ ሳይቀር ዜናውን የዘገበው "Many people had been scavenging at the site to make a living, and some even resided there permanently" ብሎ ነበር። የጥንብ አንሳ ኑሮ የሚኖሩ ማለቱ ነው። ጥንባንሳ ለማለት ፈልጎ ነው።
አዲስ አበባ እንግዲህ ዛሬም መቀነቷን አጥብቃ እንደተለመደው አስከሬን ስትቆጥር ትውላለች። የትንሽ ቀን ጉምጉምታ ከመሆን የማያልፍ ዜና፤

በአንድ ወቅት እግር ጥሎኝ አዲስ አበባ ጎራ ብየ ነበር፤ ፕላዛ ሆቴል ገባ ብሎ በመናኛ ክፍል ተከራይቶ የሚኖር አብሮ አደጌ ጋር ነበር ያረፍኩት። ወደ መንደሩ የሚያስገባው መንገድ ላይ ውሻ ሞቶ ተጥሎ ኖሮ ሰው ሁሉ አፍንጫውን እያፈነ ያልፋል፤ መኪና ያለው መስኮቱን ዘግቶ ይሄዳል። ይህን ማድረግ የማይችሉ ወይንም የማይገባቸው ህጻናት ግን ከመከራው ይቋደሳሉ። ማዘጋጃ ቤት የሚባል መሬት ከመቸብቸብ ውጭ ሌላ ስራ የሌለው ጋንግሪን ተስፋ በማይደረግበት በዚህ ስርአት አልባ ከተማ የውሻውን ባለቤቶች ጨምሮ ሃላፊነት የሚሰማው ጠፍቶ መንደሩ እንዲህ ሲታመስ መፍትሄ ለመፈለግ ቆም ብሎ ማሰብ የሚችል ሰው እንደሌለ ግልጽ በመሆኑ ምንም እንግዳ ብሆንም የቤቱን አከራይ ባዶ የናፍጣ ጠርሙስ እንዳላቸው ጠየኳቸውና ሰጡኝ። ከዚያም በሰፈሩ ውስጥ ከሚገኝ አንድ ሱቅ ጎራ ብዬ  አንድ ሊትር ናፍታ ገዛሁና በውሻው እሬሳ ላይ አፍስሸ ክብሪት ብለኩስበት ጸሃይ አቀርንቶት ኖሮ በጥቂት ደቂቃወች ውስጥ እንደ ችቦ ነደደ፤ በአንድ ሊትር ናፍታ ትንሽዬ አቢዮት ተካሄደ ማለት ነው።

ዛሬ ድፍን አዲስ አበባን የሞላት ይኽ የሞት ዜና የሁልግዜ ውርደታችን ሆኖ በአለማቀፍ ደረጃ አንገታችንን ሲያስደፋን በችግሩ ላይ ከማላዘን የችግሩን ምንጭ ማደረቁ ነበር እንባችንን ለዘላለሙ የሚያብስልን። ይህን ዜና በምሰማበት በዚህ ቅጽበት አጠገቤ ያለው ወዳጀ አንድ የመንግስት ቢሮ ውስጥ ስለሚደረግ ስብሰባ የሚያሳይ ፎቶ እያሳየኝ ነበር። ከሰዎቹ ጀርባ የዞምቢውን ፎቶ ገጭ አድርገውታል፨ ሰውየው ከሞተ ከአራት አመት ቦሃላም ዛሬም በሙት መንፈስ መገዛቱን ስራዬ ብለው የያዙት  ከተራ የመዝገብ ቤት ሰራተኛ እስከ ኃይለማርያም ደሳለኝ ቢሮ በየመንግስት ቢሮው ፎቶውን መለጠፍ የስራ ዋስትና ማረጋገጫ ብሎም የዜግነት ፓስፖርት ሆኖ መኖሩን መቀጠሉ ነው። በአንድ ወቅት የኢራቅ ህዝብ ብዛት ስንት ነው ሲባል ሰላሳ አራት ሚሊዮን ነው አስራ ሰባት ሚሊዮኑ ግን የሳዳም ሁሴን ፎቶ ግራፍ ነው ይባል ነበር። ዛሬሳዳምም ፎቶዎቹም ኢራቅ ውስጥ ባላመኖራቸው የህዝብ ብዛቱ በግማሽ ቀንሷል ማለት ነው። የኛም አገር የቆሻሻ ምንጭ የጣእራችን መንስኤ ሰዎቹ ተንደግፈውት የሚኖሩት  በየቢሮው የተሰቀለው እነርሱ ራእያችን የሚሉት ለእኛ ግን የተጫነብን መርገምት ነው። የሞት ዜና ከሰለቸን፣ውርደታችንን እንደ ኒሻን አጎንብሶ መቀበሉ ከበቃን ዘቻውና ውግዘቱ ቆሸ ሰፈር ላይ ሳይሆን በየቢሮው ከተሰቀለው እውነተኛው የቆሻሻ መፈልፈያ ማህጸን ላይ መሆን አለበት።እርሱ ከላያችን ሲወገድ ያኔ ክብራችን ይመለሰል። ያኔ በአለማቀፍ መገናኛ ብዙሃን ጥንባንሳ (ስካቬንጀር) ከመባል እንድናለን።
http://wp.me/p5L3EG-fo

Mittwoch, 1. März 2017

ሐተታ አድዋ #BattleOfAdwa #Ethiopia /በዕወቀቱ ስዩም (ደራሲና ገጣሚ) ፍትህ የካቲት 23 2004 ዓ.ም

ሐተታ  አድዋ  #BattleOfAdwa #Ethiopia
(ከጦማሪ አቤል ዋበላ ፌስቡክ ገፅ ላይ የተገኘ )

የአድዋ ድልን ከድንበር ሉአላዊነት ጋር አያይዞ መተንተን የተለመደ ነው፡፡ ድሉ አነሠ በዛ የሚለው ጭቅጭቅ ከዚህ መሠረት jይፈልቃል፡፡ በኔ ግምት የአድዋ ድል ትልቅ ጭብጥ ‹‹የሰውነት ክብር›› ይሰኛል፡፡ ቀደምቶቻችን ወደ አድዋ የጋለቡት በግፍ የተነጠቁትን የሰውነት መታወቂያ ለማስመለስ ነው፡፡ እንዲያውም ሰው መሆናቸውን በማያዳግም መንገድ ያረጋገጡት አድዋ ላይ ነው ማለት ይቻላል፡፡
ወገኖቼ!! ሰው መሆንን ማረጋገጥ ቀላል ነገር አይምሰላችሁ፡፡

አባቶቻችን ከአውሮፓውያን ጋር የሚጋሩትን ግን ደግሞ ከአውሮፓውያን ቀድመው የሚያውቁትን  ቅዱስ መጽሐፍ ጠቅሰው ሁላችንም ያዳም ልጆች  ነነ ይሉ ነበር፡፡ እና ያዳም ልጆች ነነ ብለው የሚያምኑ ፈረንጆች ቢቸገሩ የሚደርሱላቸው፣ ቢጠቁ የሚታደጓቸው ወንድሞቻቸው እንደሆኑ ያስቡ ነበር፡፡ በርግጥም የሃይማኖት አንድነት የቀለም ልዩነትን ደምስሶ አዳማዊ ወንድማማችነትን ያስገኘበት የዘመን ምዕራፍ ነበር፡፡ ክርስቶፈር ደጋማ የተባለ የፖርቹጋል ነፍጠኛ ለኢትዮጵያ  ደሙን ያፈሰሰው  የማተብ  አንድነት ስለገፋፋው ነው፡፡
ይሁን እንጂ ባንድ ወቅት የሚያገለግል የኑሮ ዋስትና በሌላው ዘመን አያገለግልም፡፡ ሁላችንም ያዳም ልጆ ነነ የሚለው የዝምድና ውል ከእለታት አንድ ቀን ያገልግሎት ዘመኑ አለቀ፡፡ በ1548 ተወልዶ በ1600 እንደጧፍ የተቃጠለው ዦርዳኖ  ቡርኖ  የተባለ  የጣልያን  መናፍቅ ‹‹ኢትዮጵያውያን ያዳም ልጆች አይደሉም፤ ቅድመ- አዳማዊያን ናቸው እንጂ›› ብሎ ፃፈ፡፡ በቡርኖ  ዘመን ኢትዮጵያ  የጥቁር ዘር ሁሉ  የወል ስሙ ነው፡፡ ቅድመ አዳማዊ ማለት ደሞ  በአዳምነት  ማዕረግ ያልደረሠ  ጅምር ፍጡር ማለት ነው፡፡ ይህ አስተሳሰብ ጥቁሮች በእግዜር አምሳል የተፈጠሩ አይደሉም የሚል ድምዳሜ ላይ ያደርሳል፡፡ ያለማለዘቢያ ለመግለፅ፣ ጥቁሮች  ከእንሥሣትና  ከእፅዋት ይመደባሉ ማለት ነው፡፡ ነገሩ ይበልጥ የሚያስገርመን ይህንን አመለካከት ከጥንታዊያን ግሪኮች  ነባይ  አመለካከት ጋር ስናመዛዝነው ነው፡፡ ጥንታውያኑ ግሪኮች ጥቁሮችን ከአማልክት ጋር ያወዳድሯቸው እንደነበር ለመገንዘብ የሆመርን ውዳሴ መስማት ይበቃል፡፡ ሆመር እንዲህ ይዘምራል፡፡
እናንት ኢትዮጵያውያን ከሰው ዘሮች ሁሉ እንከን የሌላችሁ
ከተንኮል ከክፋት ከሰው ድክመት ሁሉ ነፃ የሆናችሁ
ከቶ ከምን ይሆን የተፈጠራችሁ? ምንድነው ባህሪያችሁ?
እግዜሮች ትሆኑ ወይስ ሰዎች ናችሁ? (ከሀዲስ አለማየሁ ትርጉም የተጠቀሰ)

ታዲያ በጥንታዊ ግሪኮች ሰው  ናቸው አማልክት? ተብለው የተጠረጠሩ ጥቁሮች፣ በአስራ ሰባተኛው ክፍለ ዘመን ሰው ናቸው እንስሳ? ተብለው ለምን ተጠረጠሩ? የጥቁሮችን ሰውነት መካድ ለምን አስፈለገ? መልሱ ብዙም የተወሳሰበ አይደለም፡፡ የቅኝ ግዛት ዳርዳርታው ለቅኝ  የታጩ ህዝቦችን የሰውነት  መታወቂያ መንጠቅ  ነው፡፡ ሰው በድንግል ተፈጥሮው መሠሉን ለማጥፋት ልቡና እጁ በቀላሉ አይታዘዙለትም፡ ፡ ይህንን ለማድረግ ባፍራሽ ንድፈ ሀሳብ መታገዝ ይኖርብታል፡፡ ሰው፣ በጎች ነፍስ የላቸውም ብሎ ራሱን ካሳመነ ጀምሮ በጎችን ወደ ቀይወጥ ለመለወጥ የህሊና ወቀሳ የለበትም፡፡ አውሮፓዊውም ጥቁሮችን ጨፍጭፎ አገራቸውን ለመቀማት ከሰው ተራ አውጥቶ ከዋርካና በጥድ ተራ ማሰለፍ አስፈላጊ ሆኖ አግኝቶታል፡፡ ባድዋ ድባቅ የተመታው የጣልያን ቅኝ ወራሪ ኃይል ኢትዮጵያውያኑን ከማይገባቸው ማሣ ላይ የተሰማሩ ገመሬዎች አድርጎ ሳይቆጥራቸው አልቀረም፡፡ የጣልያኑ ጄኔራል (ባሪያቴሪ መሰለኝ) በጦርነቱ ዋዜማ ‹‹…ምኒልክን በቀፎ አስገብቼ አበረክትላችኋለሁ›› ብሎ ለሮማውያን ወንድሞቹ መጐረሩ በአእምሮው ውስጥ የነበረው ምስል ምን እንደነበር ፍንጭ ይሰጠናል፡፡
‹‹መትረየስ ጠመዱ አሉ በርከክ በርከክ አውሬ መስያቸው
ከሰው መወለዴን ማን በነገራቸው?›› አለ አቅራሪ፡፡
ታዲያ አባቶቻችን እንዲህ በአደባባይ የተነጠቁትን  የሰውነት ክብር ለማስመለስ ከፍልሚያ ውጭ ምን አማራጭ ነበራቸው?? ፓትሪክ ሄነሪ የተባለው የአሜሪካ አርበኛ ‹‹ነፃነቴን ወይም ሞቴን ወዲህ በሉ!›› ብሎ በአሜሪካ ተራራዎች ላይ ከመጮኹ አንድ መቶ አመት አስቀድሞ ኢትዮጵያውያን  ‹‹…ይኄይስ መዊት በክብር እምሐይው በኃሣር (በውርደት ከመኖር በክብር መሞት ይሻላል) የሚለውን መፈክር ያውቁት ነበር፡፡ (የሰርፀ ድንግልን ዜና መዋዕል ተመልከት)

አባቶቻችን  አይን ያጠፋውን  አይኑን በለው የሚለው ኦሪታዊ ሕግ ለአድዋ ዋዜማ ተስማሚ ሆኖ አግኝተውታል፡፡ እንደ ሰው ያልቆጠራቸውን ጠላት እንደ ሰው ሊቆጥሩት አልፈለጉም፡፡  አፄ ምኒልክ በጦርነት አዋጃቸው  ‹‹…እኔም ያገሬን ከብት ማለቅ፣ የሰውን መድከም አይቼ ዝም ብለው ደግሞ እያለፈ እንደፍልፈል መሬት ይቆፍር ጀመር›› አሉ፡፡  በዚህ ንግግር ውስጥ ያለው ትልቅ ነገር ጣልያኑ እንደ ፍልፈል መታየቱ ነው፡፡ አጤ ምኒልክ ያገራቸው ወታደር ለወራሪው ሰብዓዊ ዝምድና ተሰምቶት እንዲሳሳለት አልፈለጉም፡፡ በጦርነቱ ወቅት በተመሳሳይ መልኩ ወራሪን ወደ አውሬ የመለወጥ የስነ ልቦና  ቅኝት የነበረ ይመስለኛል፡፡ ለምሳሌ በመቀሌ ጦርነት ዋዜማ ራስ አሉላ በተገኙበት ጉባኤ ቀኛዝማች በሻህ ጣልያኑን በዜግነት ስሙ መጥራት ሳያስፈልጋቸው  ‹‹…በሾተል እየቀነጠሰን በግንቡ ውስጥ እንደ አይጥ እንፈጀዋለን›› ሲሉ መስማቱን በጅሮንድ ተክለሐዋርያት በግለ-ታሪኩ ይዘግባል፡፡ ታሪክ በሠፈሩት ቁና ይሠፍራል፡፡ ጣልያኖች ከሰው ተራ ወጥተው በፍልፈልና በአይጥ ሰልፍ ውስጥ ገብተው ለእልቂት ተመቻቹ፡፡ አዎ፣ ውርደት እንደ ተስቦ ነው፡፡ ወደ አዋራጁም ይጋባል፡፡ ወታደር ባለመሆኔ የጦርነቱን ውሎ ማተት አያምርብኝም፡ ፡ ያም ሆኖ የአድዋ ድል   ዛሬ   ብርቅ በሆኑብን  ሁለት እሴቶች ረድኤት የተገኜ ይመስለኛል፡፡እኒህ  ሁለት እሴቶች መተባበርና መደማመጥ ናቸው፡፡ ጣልያኖቹ በጊዜው ወደ  ጦርነት ሲገቡ  ተስፋቸውን የጣሉት  በመድፍና በጠመንጃቸው ሳይሆን ኢትዮጵያውያን ዝነኛ በነበሩበት የውስጥ መቆራቆስ ላይ ነው፡፡ የትግራይ ቅልጥም ሲመታ ሸዋ ያነክሳል ብለው አላሰቡም፡፡ በርግጥም በክፍለ ሀገሮች ውስጥ የተለያዩ ሽኩቻዎች ነበሩ፡፡ እኒህን ሽኩቻዎች አስረስቶ ኢትዮጵያውያንን ሁሉ ለአንድ አላማ ማሠለፍ ምኒልክነትን ይጠይቃል፡፡ መደማመጥ ያልሁትን ላሳይ፡፡ አባ ዳኘው ከዛሬው የይስሙላ ፓርላማችን በተሻለ ሁኔታ ለልዩነቶች ቦታ የሚሰጥ ተንቀሳቃሽ ምክር ቤት በጦርነቱ ወቅት መፍጠር ችለዋል፡፡ ፀሐፌ ትእዛዝ ገብረሥላሴ በውጊያው ዋዜማ የነበረውን ሁኔታ እንዲህ ይገልፁታል
‹‹…አፄ ሚኒልክም በበነጋው ሰራዊቱን የቀኙን በቀኝ፣ የግራውን በግራ አሰልፈው ነጋሪትዋን እያስመቱ ወደሱ ተጓዙ፡፡ ኢጣሊያኖችም ዘበኛው ሲመጣ ባዩ ጊዜ ተመልሰው ወደ እርዳቸው ገብተው ተኙ፡፡
ከዚህ በኋላ ሰራዊቱም እንደ ኤሊ ስንመጣበት ከድንጋይ ይገባል፤ ስንመለስ ይወጣል፤ እንዲህ አርጐ ሊጫወትብን ነውን? ብሎ እጅግ አጥብቆ ተናደደ፡፡ መኳንንቶቹም ተሰብስበው ከዚህ ሰፍረን አድረን በማለዳ እዚያው ካሉበት ከርዱ ድረስ ሄደን እንዋጋለን ብለው መከሩ፡፡ ንጉሠ ነገሥቱም እሺ ብለው ድንኳኑን ለማስመጣት አዘዙ፡፡
ይህ ምክር ካለቀ በኋላ የትግሬው ገዢ ራስ መንገሻ ተሰልፎ በፈረስ ሆኖ  መጣ፡፡ እሱም ይህ ምክር እንዳለቀ ባዬ ጊዜ አንድ ነገር ልናገር ይፍቀዱልኝ ብሎ ወደ ንጉሠ ነገሥቱ ቀርቦ እንዲህ አለ፡፡ እንደ ተርታ ነገር ካልሆነ ስፍራ ሄደን ልናስፈጀው ነውን? አለ፡፡  ይህ ምክር የተስማማ ምክር ሆነ፡፡ አፄ ምኒልክም ተመልሰው ከድንኳንዋ ከገቡ በኋላ እንዲህ አሉ፡፡ እንግዲህ ከሰፈሬ ወጥቶ ተኩስ አልጀመረ ባይኔ ካላየሁት ተሰልፌ አልወጣም፡፡››

ፀሐፌ ትእዛዝ ያቀረቡትን ዘገባ ወደ ዘመናዊ አማርኛ አሳጥሬ ሳዛውረው የሚከተለውን ይመስላል፡፡ርዕሰ-ብሔር ምኒልክ ሰራዊታቸውን እየመሩ ወደፊት ሲገሰግሱ የጣልያን ሰራዊት ስልታዊ ማፈግፈግ አድርጎ ወደ ምሽጉ ገባ፡፡ ምኒልክ በቀጣዩ ስትራቴጂ ላይ ለመወያየት አስቸኳይ ስብሰባ ጠሩ፡፡ በስብሰባው ላይ ወደ ጠላት ምሽግ ሄደን እንዋጋ የሚል ሐሳብ ቀርቦ ባብላጫ ድምፅ ፀደቀ፡፡ ምኒልክም በብዙሃኑ ተሰብሳቢ የቀረበውን ሐሳብ ለማስፈፀም ተዘጋጁ፡፡ ይሁን እንጂ ጄኔራል መንገሻ ዮሐንስ ዘግይቶ ስብሰባውን ከተቀላቀለ በኋላ ‹‹ምሽግ ድረስ ሄዶ መዋጋት በወገን ጦር ላይ ጉዳት ያስከትላል›› ብሎ መከራከር ጀመረ፡፡ ምኒልክም ‹‹እኔ አንዴ ወስኛለሁ፤ ውሳኔዬ ካልጣመህ በሊማሊሞ በኩል ማቋረጥ ትችላለህ›› ብለው ሳያሸማቅቁት ሐሳቡ እንዲጤን አደረጉለት፡፡ ሐሳቡ በድምፅ ብልጫ ፀደቀ፡፡ በድምፅ ብልጫ ያልሁት ‹‹ይህ ምክር የተስማማ ምክር ሆነ›› የሚለውን የፅሐፌ ትዕዛዙን አማርኛ ተርጉሜ ነው፡፡
እንደተመለከተው አጤ ምኒልክ ልዩ ልዩ ሐሳቦችን ለማዳመጥና አወዳድረው የነጠረውን ሐሳብ ለማስፈፀም ዝግጁ ነበሩ፡፡ በአራት ነጥብ የታጠረ ግትርነት አልነበረባቸውም፡፡ ሾፐናወር የተባለ የጀርመን አገር ፈላስፋ ከአድዋ ሠላሳ አምስት አመት አስቀድሞ ‹‹ከጥንት ግብፃውያንና ከህንዶች ውጭ ያለው ታላቅ የስልጣኔ ፍሬ ሁሉ በነጮች ጥረት ውጤት ነው፡፡ ከጥቁር ህዝቦች መካከል እንኳ የገዢነትን ስልጣን የሚይዙት በቀለም ፈካ ያሉት ናቸው›› ብሎ ነበር፡፡ ያጤ ምኒልክ ፊት ይህንን ንድፈ ሐሳብ በይፋ ለማስተባበል የተፈጠረ አይመስልም?

በዕወቀቱ ስዩም (ደራሲና ገጣሚ)
ፍትህ የካቲት 23 2004 ዓ.ም