Netsanet: ፍኖት – ሐብታሙን ይህ ይገልጸው ይሆን ?

Donnerstag, 10. Juli 2014

ፍኖት – ሐብታሙን ይህ ይገልጸው ይሆን ?

በምረቃ መጽሔቱ ፎቶ ስር‹‹የፈራ ይመለስ››ብሎ ነበር
********************************************
ሐብታሙ አያሌው ራሱን ለፈጣሪው ያስገዛ ሐይማኖተኛ ሆኖ ያገኙት ኢህአዴጎች በአነጋገሩና ነገሮችን ለመግለጽ ያለውን ውስጣዊ ድፍረት ተገንዝበው ከቤተክርስቲያን ጠለፉት ፡፡አባላቸው አደረጉት፡፡ሐብታሙ አባል የሆነበት ኢህአዴግ ጭንቅ ውስጥ ነበርና በልጁ የመናገርና የማሳመን ችሎታ ለመጠቀም ከወጣቶች አደረጃጀት አንስቶ እስከ ወጣቶች ፌደሬሽን ፕሬዘዳንትነት አድርሶታል፡፡
በቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ቀጥተኛ ውክልና ሐብታሙ በአፍሪካ የመገማገሚያ መድረክ መንግስትን በመወከል እንዲሳተፍ ተደርጎም ነበር፡፡በዚህ ወቅት አሁን በስልጣን ላይ ከሚገኙ ሰዎች መካከል አንደኛው ሚኒስትርና ሐብታሙ በግምገማው ላይ በመገኘታቸው አንድ አንድ ሺህ ዶላር ሊሰጣቸው ሲል ሐብታሙ ገንዘቡን አልቀበልም በማለቱ ሁለተኛው ሰው ቂም ቋጥረውበት እንደነበርም ይነገራል፡፡

ኢህአዴግ በአላጌ በከፈተው የካድሬ ማሰልጠኛ ተቋም ሐብታሙ በሰልጣኞች ‹‹ምርጡ አሰልጣኝ››እስከመሰኘትም ደርሶ ነበር፡፡አቶ መለስ በአንድ ስብሰባ ላይም‹‹እንደ ሐብታሙ ያሉ ወጣቶች እኔን የመተካት አቅም አላቸው››በማለት በኩራት ተናግረውለትም ነበር፡፡

በወጣትነቱ በወንበር ላይ ወንበር እየተደረበለት ቤተ መንግስቱን የመኖሪያ ቤቱ ያህል እንዲመላለስበት የተፈቀደለት ሐብታሙ በአጭር ጊዜ ልዮነት የስልጣን ኮርቻውን በመፈናጠጥ ከሚኒስትሮች ያላነሰ ቦታ ላይ ሊመደብ እንደሚችል ሲጠበቅ ‹‹የወጣቶችን ፎረም ስንመሰርት ከየትኛውም የፖለቲካ ድርጅት ገለልተኛ እንደሚሆን ተነግሮን ነበር አሁን ግን ፎረሙ በቀጥታ የኢህአዴግ ክንፍ እስኪመስል ድረስ ለድርጅቱ እየታዘዘ ነው ፡፡ይህም ከፎረሙ ተፈጥሮ ጋር አይገናኝም››በማለት በግልጽ ተቃውሞውን ማሰማት ጀመረ፡፡

ሐብታሙ የ2010 የዓለም ዋንጫን በደቡብ አፍሪካ ለመመልከት የተፈጠረለትን ዕድል በመጠቀም ወደ ሳውዝ ማምራቱን ተከትሎ በአገር ውስጥ ‹‹ሀብታሙ ገንዘብ ይዞ ተሰወረ››የሚል ወሬ በተማይቱ መናፈስ ጀመረ፡፡ወሬውም ደቡብ አፍሪካ የከተመው ሐብታሙ ጋር እንደደረሰም ‹‹ንጽህነቴን ለማሳየት አገሬ መግባት ይኖርብኛል፡፡››በማለት በመወሰኑ ሁሉንም ለመጋፈጥ አገሩ ገባ፡፡በዚህ ውሳኔው አብደሃል ያላለው ወዳጅ ዘመድና ቤተሰብ አልነበረም፡፡

‹‹በፎረሙ የአዲስ አበባን ወጣቶች ልብ እሸምታለሁ›› የሚል ተስፋ ሰንቆ የነበረው አውራ ፓርቲም በሐብታሙ ቂም መቋጠር ጀመረ፡፡ሐብታሙ በፎረሙ አካሄድ ደስተኛ ያልሆኑ ወጣቶችን በመያዝ ‹‹ባለ ራዕይ››ማህበርን መሰረተ፡፡የማህበሩ ዋነኛ ግብም ‹‹አንድነታችን ከልዩነታችን በላይ ነው፡፡››የምትልና ኢትዮጵያዊ አንድነትን የምታቀነቅን መሆኗ ‹‹አንድነት››ሲባል ፊታቸው ላይ ነፍጠኞች፣የቀድሞው ስርዓት ናፋቂዎች ድቅን የሚሉባቸው ወገኖች በሐብታሙና በባለራዕይ ማህበሩ ደስተኞች አልሆኑም፡፡

ሐብታሙ ለሚፈልገው ስብሰባ የመንግስት ሆቴሎች፣የግል አዳራሾች፣ለታሸገ ውሃ፣ለኩኪስ፣ ለአበል የሚሆኑ ወጪዎችን ያለምንም ድካም ሲያገኝ እንዳልቆየ ለባለራዕይ ማህበር መሰብሰቢያ አዳራሽ በገንዘብ የሚያከራየው አጣ፡፡ቢሮ ማግኘት የማይታሰብ ሆነ፡፡በዚህና በሌሎች ውጫዊና ውስጣዊ ደባዎች ማህበሩ የለም የሚሰኝበት ደረጃ ላይ እንዲደርስ ተደረገ፡፡

ሐብታሙ በአንድነት በተናጠል የሚያደርገው ትግል የትም እንደማያደርሰው በመረዳቱ ሐብታሙ በአገሪቱ ያሉ ፓርቲዎችን ጊዜ ወስዶ በማጥናት አንድነትን ለመቀላቀል ወሰነ፡፡ከኢህአዴግ ቤት እንደመምጣቱ በመጀመሪያዎቹ ወራቶች የመታመን ችግር እንዳጋጠመው በቅርቡ መናገሩ አይዘነጋም፡፡ፓርቲው ያደረጋቸውን ህዝባዊ ስብሰባዎች፣ሰላማዊ ሰልፎችና የቴሌቭዥን ላይ ክርክሮች በመገኘት ሐብታሙ የብዙ ሺህ ኢትዮጵያዊያንን ልብ ለማግኘት በፓርቲው ውስጥም በጥርጣሬ ይመለከቱት የነበሩትን ለማሸነፍ በቅቷል፡፡

አንድነት ከመኢአድ ለመዋሀድ የጀመረው ጉዞ በስኬት እንዲጠናቀቅም ሐብታሙ የተዋቀረው ኮሚቴ አባል በመሆን ሰርቷል፡፡

በቅርቡ ሐገርና ፖለቲካ በሚል ርዕስ የመጀመሪያውን የመጽሐፍ ክፍል በማሳተም የአገሪቱን ታሪክ በንቃት ይከታተል እንደነበር ያሳየው ሐብታሙ የመጽሐፉን ቀጣይ መድብል የማሳተም እቅድ አለው፡፡ ባሳለፍነው ሳምንት እንደወላጅ አባቱ ይመለከታቸው የነበሩ የባለቤቱን ወላጅ አባት በሞት መነጠቁ ሐዘን የፈጠረበት ሐብታሙ ከቅድስት ስላሴ የነገረ መለኮት መንፈሳዊ ኮሌጅ በዚያው ሳምንት ተመራቂም ነበር፡፡

የኮሌጁ ተመራቂ ተማሪዎች የምረቃ ኮሚቴ ሲመርጡ ሐብታሙ በከፍተኛ ድምጽ ቢመረጥም የኮሚቴው አባል በመሆኑ ደስተኛ ያልሆኑ አካላት የተለያዩ ሰበቦችን በመፍጠር ከምረቃ ኮሚቴው እንዲወጣ አድርገውታል፡፡ሐብታሙ ኮሌጁ ባዘጋጀው የምረቃ መጽሔት ላይ ከፎቶው ግርጌ ‹‹የፈራ ይመለስ››የሚል ጽሑፍ አስፍሮ ነበር፡፡

ይህን መንገድ በመምረጡ ብዙ መስዋዕትነት እየከፈለ የቆየው ሐብታሙ ከትዳሩ ‹‹ኤማንዳ››የሚል ስያሜ ያወጣላትን ሴት ልጅ አግኝቷል፡፡አባቷ ወጥቶ እስኪገባ በር በሩን የምትመለከተው ኤማንዳ አንደኛ የልደት ሻማዋን የለኮሰችው በቅርቡ ነበር፡፡

Keine Kommentare:

Kommentar veröffentlichen