የሀብታሙ አያሌው መልዕክት ከቂሊንጦ ማረሚያ ቤት
በሞት ጥላ መካከል ብሄድ እንኳን ክፉን አልፈራም !!!
********************************************************
የልቤን ምጥ ልፃፈው ብዬ ደጋግሜ ብዕሬን ይዤ ወረቀቱ ላይ ብፅፍም እንደተራበው ወገኔ ሆድ ብዕሬ ባዶ ሆኖ ቀለም አልነጥበው አለ፡፡ በቅሊንጦ ማጎሪያ ቤት ሰማይ ስር ነፍሴ ሀዘን አቆርዝዛ በማይገፉ ቀንና ሌሊቶች ውስጥ ባዘነች፡፡ ለወትሮው ወገኔ እንደከፋው ስሰማ እንደወፍ በርሬ ችግሩን ልጋራው ከመሃሉ እደርስ ነበር፡፡ ዛሬ ግን የህዝቤ ስቃይ ወደ ሰማይ ጉኖ በጠኔ ሲንበረከክ እንደ ጅብራ ተገትረው በማያንቀሳቅሱኝ ወታደሮች ተከብቤ በጭንቀት እየባዘንኩ ከመጠውለግ በቀር አደርገው ነገር አጣሁ ፡፡ ወይ ሀገሬ!!! ወይ ወገኔ!!! ….. እመነኝ እንዳልኩህ አሁንም እመነኝ … አሁንም እመነኝ !!! እመነኝ ደርግ ወድቋል ኢህአዴግ ይወድቃል፡፡ ዛሬ በአሳሪዎቼ ጡጫ ተደቁሼ፤ ድምፄ በኢትዮዮጵያ ሰማይ ስር ባይሰማም የታገልኩለት እውነት ወደ አደባባይ ወጥቶ ህዝቤ የነፃነት ሻማ እሚጎናፀፍበት ቀን እንደሚመጣ ግን ጥርጥር የለኝም፡፡ የልጄ ናፍቆት የሚስቴ ስቃይና እንግልት የእህቶቼ መባከን እና መሳቀቅ አቅሜን ሲፈታተኑት በማዕከላዊ የስቃይ ማማ ስር ጉዳት ያተረፉት ሁለቱ ኩላሊቶቼ የቀን ከሌት ስቃዬን ሲያረዝሙት የነከስኩት ጥርሴ ጉልበቴ አበርትቶ የነፍሴን መዛል ብሸሽግም… ዛሬ ግን በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ሆኖ የታገልኩለት ህዝብ በረሃብ ጠኔ እየተመታ በሞት ጥላ መንበርከኩን ስሰማ ነፍሴ በውስጤ አለቀች እናም የልቤን ሀዘን እፅፍ ዘንድ ሞከርኩ… ሞከርኩ ግን አቃተኝ…. ጃርት እንደ በላው ዱባ በየቦታው የተፈረካከሰው ፓለቲካችን ዛሬም እርስ በእርስ እየተሸነቋቆጠ ይቀጥላል ወይስ ወገኑን ለመታደግ እንኳ አንድ ይሆናል? ነፍሴ በየእለቱ የምትሟግተኝ ጥያቄ ነው ፡፡ ሳንተባበር ጉልበት አንድ ሳንሆን ኃይል ከወዴት እናገኝ ይሆን ? የአምባገነኖች ጡጫ እየደቆሰን ረሃብ በየዘመኑ የሚቆላንስ እስከመቼ ነው? በእውነቱ በሀሳብ ብዙ ባከንኩ አገኝለት ዘንድ ግን መልስ አጣሁ፡፡ ነገር ግን እግዚአብሄር እና የኢትዮጵያ ህዝብ መልስ አጥተው አያውቁም እና ተስፋዬ ፈፅሞ አይመክንም፡፡ እናም ያገባናል ለሚሉ ሁሉ እላለሁ የኢትዮጵያ ገፅታ የሚገነባው በየሰርጡ በጠኔ የሚሞቱ የወገኖችን እሬሳ በመደበቅ እንዳልሆነ ካሳለፍናቸው ክፉ ጊዜያት ተምረን ባለን አቅም ተረባርበን ወገኖቻችንን ለመታደግ እንበርታ እላለሁ…!!! በአዲስ አበባ፤ በባህር ዳር፤በአርባ ምንጭ፤ በጎንደር፤ በደሴ፤ በአዳማ፤ በአዋሳ፤ በወላይታ ህዝብ በሚንቀለቀል የለውጥ ፍላጎት ድምፁን ባሰማባቸው ሰላማዊ ሰልፎች… ‹‹ኢህአዴግ ከታሪክ ይማር፤›› ‹‹አምባገነኖች ባሉበት ሀገር የጀግና ሞቱ እስር ቤት ነው ፤›› ‹‹ታጋይ ይታሰራል ትግሉ ይቀጥላል፤ ›› ‹‹ እጃችን ባዶ ነው እነዚህ አምባገነኖች ነገ አሸባሪ ይሉናል›› ፤ ‹‹እመነኝ ደርግ ይወድቃል ኢህአዴግም ይወድቃል›› ማለታችንን ….. በእርግጥም ልክ ነበርን፡፡ ዛሬ አሸባሪ ተብለን ከትግል አጋሮቼ ከዳንኤል ሺበሺ ፤አብርሃ ደስታ ፤ የሺዋስ አሰፋ ፤አንዷለም አራጌ፤ ተመስገን ደሳለኝ ፤እስክንድር ነጋ ፤ ወዘተ…. ስፍር ቁጥር ከሌላቸው ውድ የኢትዮጵያ ልጆች ጋር የነፃነት ቀንን እየናፈቅን በእስር ቤት አለን ፡፡ የፍርድ ቤት ድራማውም ተጠናክሮ ቀጥሏል ፍርድ ቤቶችን ከጀርባ ቆመው የሚዘውሩ በቀጭን ትዕዛዝ ማረሚያ ቤቶችን የሚያሽቆጠቁጡ፤ በፍትህ ስም የሚቀልዱ ፓርቲዬን ያፈረሱ፤ የህዝቤን ተስፋ ለማምከን ቀን ከሌት የሚደክሙ የካዛንቺሱ መንግስቶች እጃቸው የሚያጥርበትን ቀን አብዝተን እንናፍቃለን ፡፡ በእውነት እላለሁ በሞት ጥላ መካከል እንኳ ብሄድ ክፉን አልፈራም !!!
OPPOSITION PARTIES
Sonntag, 22. November 2015
የሀብታሙ አያሌው መልዕክት ከቂሊንጦ ማረሚያ ቤት በሞት ጥላ መካከል ብሄድ እንኳን ክፉን አልፈራም !!!
Abonnieren
Kommentare zum Post (Atom)
Keine Kommentare:
Kommentar veröffentlichen