ከበፈቃዱ ዘ-ኃይሉ | በፌስቡክ ገጹ ካሰፈረው የተወሰደ
አዋሽ ሰባት በነበረኝ “የተሀድሶ” ቆይታዬ ተዋውቄያቸው ከወደድኳቸው ሰዎች መካከል ሁለት ዳዊት በሚል ሥም የሚጠሩ ወጣቶች ነበሩበት። አሁን የማጫውታችሁ ግን ስለ ዲያቆኑ ዳዊት ነው። ዲያቆን ዳዊት ተወልዶ ያደገው ትግራይ ውስጥ ነው። የሚያገለግለው ሥላሴ ካቴድራል ነው። የፖለቲካ ተሳትፏቸው እምብዛም እንደሆኑትና በአዲስ አበባ እንደሚኖሩት አብዛኛዎቹ የትግራይ ተወላጆች የሚያውቀውም፣ የሚያምነውም፣ የሚወደውም ኢሕአዴግን ብቻ ነበር።
“ነበር” ያልኩት ያለምክንያት አይደለም። እንዳጋጣሚ ሆኖ፣ ዲያቆን ዳዊት የተመደበው ኢያስጴድ እና እኔ የነበርንበት (20 ምናምን ሰው የነበረበት) የውይይት ቡድን ውስጥ ነበር። ቡድናችን በፍርሐት ታዝቦ የሚያልፈው ነገር አልነበረውም። በውጤቱ ደግሞ የውይይቱ አባላት በሙሉ የተሰላ ምላጭ ሆነዋል ማለት ይቻላል። ታዲያ ዲያቆን ዳዊት አንድ ቀን ግምገማ ላይ “ከዚህ በፊት የነበራችሁ ዕውቀት ምን ይመስላል? አሁንስ ምን ተማራችሁ?” የሚል ጥያቄ ሲነሳ፣ “እኔ እዚህ ከመምጣቴ በፊት ኢሕአዴግን ብቻ ነበር የማውቀው፤ ቅዱስም ይመስለኝ ነበር። አሁን ግን ብዙ ነገር ሰምቻለሁ። ብዙ በደል እንደሚፈፅም አውቄያለሁ። ሰነዶቹን የሚያዘጋጁት ሰዎች ዕውቀትም እዚህ ከሚታደሱት ሰዎች ዕውቀት ያነሰ መሆኑን ተምሬያለሁ” ብሎ እርፍ አለ።
ዳዊት በጣም ጥሩ ሰው እንደሆነ ከቀረቤታው ያስታውቃል። ኢሕአዴግንም ሲመለከተው የኖረው በየዋህነት ይመስላል። “እንዴት ታሰርክ?” ብዬ ስጠይቀው፣ “እኔ ራሴ ላይ ቀለም አብዮት ታውጆብኛል” አለኝ። አከአዲስ አበባ የተጋዙት ብዙዎቹ የሆነ ፀበኛዬ ቂም በቀል መወጫ ሆኜ ነው የመጣሁት ብለው ያምናሉ – በጥቆማ። ዲያቆን ዳዊትም የሚያምነው እንዲያው ነው። ምናልባት ቤተክርስቲያን ውስጥ ባለ ፉክክር መጥቶ ይሆናል ብዬ ገምቼ፣ “እንዴት ነው ቤተክርስቲያኖቹ የአማራ እና የትግሬ ተብለው ተከፋፍለዋል የሚባለው እውነት ነው?” ብዬ ጠየቅኩት። “ከፖለቲካው አይብስም ብለህ ነው?” አለኝ።
ዲያቆን ዳዊት እኔና ኢያስጴድን ትግራይ ወስዶ ሊያስጎበኘን ቃል ገብቷል። ምክንያቱ ደግሞ ‘የአንድ ብሔር የበላይነት’ የሚል ነገር ስንናገር በመስማቱ ነው። ጉዳዩ ግን በተሐድሶው ወቅት ተፈርቶ በደንብ ያልተወራ ጉዳይ ነው።
ኮማንደር አበበ፣ ራሳቸው የትግራይ ተወላጅ የሆኑ፣ ከስድስቱ ለመጨረሻዎቹ ሦስት የሥልጠና ሰነዶች የኃይል (አማርኛ ተናጋሪዎች ሁሉ የተሰበሰብንበት) መድረክ መሪ (መዝጊያ ንግግር አድራጊ) ነበሩ። አንድ ቀን፣ በግምገማ ወቅት ተጠይቀው መልስ ያላገኙ ጉዳዮችን ሰብስበው መጡ። ከጉዳዮቹ አንዱ “በኢትዮጵያ የአንድ ብሔር የበላይነት አለ” የሚለው ነበር። ኮማንደሩ “መልስ ለመስጠት ጥያቄው ቢብራራልኝ፣ የቱ ብሔር ነው በየቱ ላይ የበላይ የሆነው?” አሉና ጠየቁ። ዝምታ።
ፈራ ተባ እያልኩ እጄን አውጥቼ “የሚባለው የትግራይ የበላይነት እንደሆነ፣ ነገር ግን አባባሉ የትግራይ ገበሬ የኦሮሞን ወይም የአማራን ገበሬ ይጨቁናል፣ ወይም የበላዩ ይሆናል ማለት ሳይሆን፣ የልሒቃኑ የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካ አመራር እና በማበብ ላይ ያሉ ቢዝነሶች ላይ ያለውን የበላይነት እንደሚመለከት” አስረዳሁ። ከዚያ በኋላም ብዙ አስተያየቶች ተከተሉ። ለምሳሌ አንድ የገረመኝ አስተያየት ሰጪ (በሙያው መምህር የሆነ ወጣት) በእናቱ ትግሬ መሆኑን ገልጦ፣ “ምናልባት የሚፈቱኝ ከሆነ ብዬ የተያዝኩ ዕለት ጣቢያ ብሔር ስጠየቅ ‘ትግሬ’ ልል ነበር፤ አፍሬ ተውኩት” ብሎ አማረረ። በመቀጠልም፣ “እንዲያውም፣ እዚህ ከመጣነው ውስጥ በናቱም ባባቱም ትግሬ የሆነ ሰው የመጣ አይመስለኝም፤ ያውም አምስት የምንሞላ አይመስለኝም” አለ። ነገር ግን ይህ አካሔድ የትግራይን ተወላጅ ሁሉ እየጠቀመ አለመሆኑን ሲያስረዳ “እናቴ የጋራ ኩሽናችንን ተጠቅማ በሌሊት እንጀራ ስትጋግር በመቀደሟ የተናደደችው ጎረቤታችን ‘ምን ይደረግ እሷ የዘመኑ ሰው ናት’ ስትል ሰምቼ በጣም ነበር ያዘንኩት” በማለት አስረዳ።
ኮማንደር አበበ “እውነቱን ልንገራችሁ” አሉን፣ “ለዚህ ሁሉ ‘ሁከትና ብጥብጥ’ መንስኤ የሆነው ይሄ አስተሳሰብ ነው። ጠላቶቻችን ለዓመታት በኢሳት እና ኦኤምኤን እንዲሁም በፌስቡክ ሲያራግቡት የነበረው የጥላቻ ፕሮፓጋንዳ ውጤት ነው ይሄ” አሉ። “የትግራይ ሕዝብ፣ እንዲያውም ሕወሓት ለራሱ ትልቅ ቆርሶ ወሰደ እንዳይባል በይሉኝታ እየተበደለ ያለ ሕዝብ ነው” በቁጭት ስሜት ሊያስረዱን ሞከሩ። “በርግጥ፣” አሉ “የትግራይ ተወላጅ ሆነው ሙሰኞች አሉ፣ ሌቦች አሉ፤ ነገር ግን የኦሮሞ ተወላጅ ሌቦችም አሉ፣ የአማራ ተወላጅ ሌቦችም አሉ። በጥቂት ሰዎች ሥም የአንድ ብሔር ሕዝብ መወቀስ የለበትም”።
በማግስቱ ዲያቆን ዳዊት ከኮማንደሩ የተሻለ የነገሩን ውስብስበነት አስረዳኝ። ዳዊት “እኔ በጦርነቱ ጊዜ አባቴን አጥቻለሁ፤ አሁን ደግሞ የትግራይ ተወላጅ ስለሆንኩ ብቻ በሕወሓት ጥፋት አብሬ እወቀሳለሁ። ያገኘሁት ጥቅም ምንድን ነው?” ነበር ያለኝ።
ዲያቆን ዳዊት ግቢው ውስጥ ከብዙዎቻችን የተሻለ የመንቀሳቀስ ነጻነት ነበረው። ማታም ግቢው ውስጥ አምሽቶ እንደሚገባ የክፍሉ ልጆች ነግረውኛል። ይህንን ነጻነት ጠይቆ አላመጣውም። የአነጋገር ዘዬው ላይ የትግርኛ ቅላፄ መኖሩ ያጎናፀፈው ዕድል ነው። በጊቢው ውስጥ ካሉ ጥበቃዎች ውስጥ በጣም ቁጡ የሚባሉት የትግራይ ተወላጆች መሆናቸው አነጋጋሪ ነበር። እነሱ ዲያቆን ዳዊት ላይ ቁጣቸው ይበርዳል። እኛ ክፍል ከነበረው ሌላኛው ዳዊት ጋር ስናወራ “የነሱ ክፋት የግላቸው እንጂ የወጡበት ማኅበረሰብ በውክልና የሰጣቸው ስላልሆነ የነርሱን ለነርሱ እንተወዋለን” እንባባል ነበር። ለምሳሌ ኃይሌ የሚባለው የኛ ክፍል ኃላፊ የአዲስ አበባዎቹ ‘ሠልጣኞች’ ከሔድን በኋላ መምታት በኮማንድ ፖስቱ ልዑካን ቡድን በመከልከሉ የተቆጨ ይመስላል። የውይይት ተሐድሶው የሚለውጠን ስላልመሰለው ማታ ማታ እየመጣ ይቆጣንና ይመክረን ነበር። አንዴ እንዲያውም፣ ዘላችሁ ዘላችሁ ያው የምታርፉት መሬት ነው ለማለት የእንግሊዝኛ ተረት ተርቶ በሳቅ ገድሎናል፤ “ራቢት ጃምፒያ ጃምፒያ ቱ ኧርዝ” ነበር ያለን ቃል በቃል። የእነ ኢያስጴድ ክፍል ኃላፊ ደግሞ አብርሃም ነበር። ኃይሌም አብርሃምም በጣም ከሌሎቹ ጠባቂዎች ሁሉ በጥላቻ እና በክፋት ነበር የሚያዩን።
አንድ ቀን ማታ ሜዳ ላይ ተኮልኩለን ቲቪ ስናይ ጥቂቶች ወንበር እያመጡ ሲቀመጡ እኔም ወንበር አምጥቼ ተቀመጥኩ። ሌሎቹ ምንም አይሉም፤ አብርሃም ግን “ወንበሩን መልሱ” እያለ መጥቶ አንዴ ዠለጠኝ። በጣም ተናድጄ ቻልኩት። ስመለስ ዲያቆን ዳዊት እና ሌላ አንድ ተመሳሳይ ሰው ከወንበራቸው አልተነሱም። የባሰ ተናደድኩ እና የማይገባ ቃል ተናገርኩ። ዲያቆን ዳዊት “ወንበሩን ካልለቀቅኩልህ” አለኝ፤ እምቢ አልኩት። በማግስቱ መጥቶ ሲያናግረኝ፣ በቋንቋ ላይ ተመሥርቶ አብርሃም እንደበደለኝ ነገርኩት። “የምርቃታችን” ዕለት አብርሃም ጠራኝና ይቅርታ ጠየቀኝ። ነገሩን ያደረገው “በሆነ ብስጭት” ተነሳስቶ እንደሆነና “ቂም ይዤ እንዳልሔድ” ጠየቀኝ። ይቅርታ መጠ‘የቅ ደስ ይላል። ቂም ይዤበት ነበር ለማለት ግን ይከብዳል። ነገር ግን ክፉው አብርሃም ይቅርታን ኬት አመጣው ብዬ ዳዊትን ጠየቅኩት። “አናግሬው ነበር” አለኝ። “የሠራው ሥራ ጥፋት እንደሆነ ይቅርታ መጠየቅ እንዳለበት አሳምኜዋለሁ” አለኝ። አሪፍ ነው።
ዳዊት ወደትግራይ ሊወስደኝ ቃል የገባው የሕዝቡን ድህነት እና ሰው ወዳድነት ሊያሳየኝ ፈልጎ ነው። እኔም ይሄንን አልክድም። ምናልባት እሱ ያልገባው፣ እሱ በአነጋገር ዘዬው ብቻ ያገኘውን ተቃራኒው ለኔ መሰሎቹ እየተሰጠን እንደሆነ ነው። እሱ እንደልቡ ጊቢው ውስጥ መንቀሳቀስ ሲፈቀድለት የኔብጤዎቹ ለምነንም ማግኘት አልቻልንም ነበር። እሱም እዚያ የነበረው በግፍ ነው። ይሁን እንጂ ሌሎቻችንም በተመሳሳይ ሁኔታ ከመያዛችን አንፃር እሱ ቢያንስ ግቢው ውስጥ ሲኖር በፍርሐት ተሸማቆ አልነበረም። ይሄን ችሮታ (entitlement) ዲያቆን ዳዊት ከነበፍቃዱ ተነጥቆ ይሰጠኝ አላለም፤ ነገር ግን ለሱ ችግር ስላልነበር አልታየውም። በተጨማሪም ይሄን መሰል አድሎ የትግራይ ሕዝብ ባርኮ አላፀደቀውም። ነገር ግን ተመልካች ይሄን ያመዛዝናል? የማመዛዘን ግዴታስ አለበት?
ሕወሓት/ኢሕአዴግ እታደሳለሁ ካለ መጀመሪያ ይህን ዓመሉን ይሻር እና በአዲስ የተሻለ አመል ይተካው። መልካም አስተዳደር ለማግኘት የአነጋገር ዘዬ የሚያደርገው ያልተጻፈ አዎንታዊም አሉታዊ አስተዋፅዖ ይቀረፍ።
Keine Kommentare:
Kommentar veröffentlichen