Netsanet: August 2017

Freitag, 18. August 2017

የእነ አቶ በቀለ ገርባ መከላከያ የመስማት ሂደት አቃቤ ህጉ እርቦኛል በማለቱ ምክንያት ተቋርጧል። በ ( ጌታቸው ሽፈራው)

የእነ አቶ በቀለ ገርባ መከላከያ የመስማት ሂደት አቃቤ ህጉ እርቦኛል በማለቱ ምክንያት ተቋርጧል።

አቃቤ ህግ ለሚያቀርበው ጥያቄ ተደጋጋሚ መቃወሚያ የቀረበበት ሲሆን መሃል ላይ "አርብ እንደመሆኑ እኛ ለምሳ  መውጣት ያለብን 5:30 ላይ ነው። የምሳ ሰዓታችን ይከበር" ብሎ ባቀረበው ጥያቄ  መሰረት መጠነኛ ክርክር ተደርጓል። ሌላ አቃቤ ህግ ስለነበር ፍርድ ቤቱ ሌላኛው አቃቤ ህግ ራበኝ ያለውን ተክቶ የሚሰራበት አጋጣሚ ስለመኖሩ ቢጠይቅም ራበኝ ያለው አቶ  አንተነህ  የተሰየመው እሱ ብቻ መሆኑን ገልፆአል።

 " እኔም ከጤናዬ አንፃር ሊታሰብልኝ ይገባል።ጨጓራ አለብኝ። መብላት አለብኝ" ብሏል አቶ አንተነህ።

የቀኝ ዳኛው አቃቤ ህጉ ያነሱት ጥያቄ መስቀለኛ ጥያቄ ሳይጀመር ቢሆን ኖሮ ተገቢ ይሆን እንደነበር  ገልፀው መታገስ እንደሚገባ በመጠቆማቸው  አቃቤ ህጉ " ትክክል ነው። ታግሼ መስራት እንዳለብኝ አውቃለሁ። እዚህ ቦታ ላይ ቆሜ የምሰራው ጤና ሲኖረኝ ነው። ህመሜን እያዳመጥኩ ልጠይቅ አልችልም።" ብሎ የምሳ ሰዓቴ ይከበር የሚለውን ጥያቄ ገፍቶበታል።

አቶ በቀለ ገርባ በበኩሉ "  ይህ ከዚህ ትልቅ  ተቋም የሚጠበቅ አይደለም።  እኛ እየተራብን፣ ብዙ መከራ እያየን ነው ያለነው። ህዝቡም የፍትህ ሂደቱን እንዲያይ ነው። አቃቤ ህግ ከተለየ አካል ትዕዛዝ ሊቀበል ካልሆነ በስተቀር ይህ በምክንያትነት ሊቀርብ አይገባም" ብሏል።

 መሃል ዳኛው" ከዚህ ወንበር ተቀምጠን ትዕዛዝ መስጠት አለብን። ሁለት አቃቤ ህጎች ስላሉ አንዱ ተክቶ ሊሰራ እንደሚችል እንረዳለን። ይህ የትዕዛዝ ጉዳይ አይደለም።" ቢልም ሂደቱ ተቋርጦ ለምሳ ተወጥቷል።
 ይህ የምሳ ሰዓት ይከበር ጥያቄና ክርክር በታዳሚውና ተከሳሾች  ሳቅ የታጀበ ነበር።

Mittwoch, 9. August 2017

እነ መቶ አለቃ ማስረሻ ሰጤ በሀሰት እየተመሰከረባቸው እንደሆነ ገለፁ • (በጌታቸው ሺፈራው)

እነ መቶ አለቃ ማስረሻ ሰጤ በሀሰት እየተመሰከረባቸው እንደሆነ ገለፁ • ‹‹ህዝብ እውነታውን እንዲረዳልን እንፈልጋለን›› መቶ አለቃ ማስረሻ ሰጤ (በጌታቸው ሺፈራው) ቂሊንጦ እስር ቤትን አቃጥላችኋል፣ ንብረት አውድማችኋል እንዲሁም የሰው ህይወት አጥፍታችኋል በሚል የሽብር ክስ የተመሰረተባቸው እነ ማስረሻ ሰጤ ነሃሴ 2/2009 ዓ.ም ለፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 19ኛ ወንጀል ችሎት በሀሰት እየተመሰከረባቸው መሆኑን ገልፀዋል፡፡ በትናንትናው ዕለት ሁለት ምስክሮች የቀረቡ ሲሆን አንደኛው ምስክር በ13 ተከሳሾች ላይ ምስክርነት ሰጥቷል፡፡ ምስክሩ እነ ማስረሻ ሰጤ፣ ሰይፈ ግርማ እና ፍቅረማርያም አስማማው የአማራ ብሄር ተወላጆችን እየሰበሰቡ ለግንቦት ሰባት በአባልነት ይመለምሉ እንደነበር ሲገልፅ፣ ወልዴ ሞቱማ፣ አበበ ኡርጌሳና ሌሎች ተከሳሾች የኦሮሞ ብሄር ተወላጆችን በመሰብሰብ ለኦነግ ይመለምሉ ነበር ብሎ መስክሯል፡፡ ሆኖም ምስክሮቹ የአማራና የኦሮሞ ብሄር ተወላጆችን ለግንቦት ሰባትና ኦነግ ይመለምሉ ነበር የተባሉት ተከሳሾች ከየትኛው ብሄር እንደሆኑ ሲጠየቁ አናውቅም ብለዋል፡፡ ምስክሮቹ የቂሊንጦ ማረሚያ ቤት በቃጠሎው ወቅት የሞቱትን እስረኞች ፎቶ ቀድሞ በማሳየት ለምስክርነት ያዘጋጃቸው መሆኑን ለችሎቱ የገለፁ ሲሆን ተከሳሾቹም በሀሰት እየተመሰከረባቸው እንደሆነ ለፍርድ ቤቱ አስታውቀዋል፡፡ 1ኛ ተከሳሽ ማስረሻ ሰጤ በበኩሉ በሀሰት እየተመሰከረባቸው መሆኑን በመግለፅ ‹‹በተቋም ደረጃ የሀሰት ምስክርነት እየተሰጠ ነው፡፡ ህዝብ እውነታውን እንዲረዳልን እንፈልጋለን›› ብሏል፡፡ ሌሎች ተከሳሾችም በሀሰት እየተመሰከረባቸው መሆኑን ገልፀዋል፡፡ ዛሬ ነሃሴ 3/2009 ዓ.ም ሁለት ተጨማሪ የአቃቤ ህግ ምስክሮች የተሰሙ ሲሆን የምስክር መስማት ሂደቱ እስከ ነሃሴ 12/2009 ዓ.ም ይቀጥላል ተብሏል፡፡ ምስክሮቹ ነሃሴ 28/ 2008 ዓ.ም ተኩስ እንደነበር፣ በጥይት የተገደሉና የቆሰሉ እስረኞች እንዳዩ እንዲሁም ወደ እስረኛው የጭስ ቦንብ እንደተወረወረ ገልፀዋል፡፡ ለቃጠሎው መንስኤ የአስተዳደር ችግር፣ ምግብ መከልከሉና በመታሰር የተፈጠረ ብሶትም እንዳለበትም ተገልጾአል፡፡ ቶፊቅ ሽኩር፣ ሸቡዲን ነስረዲን፣ ኡመር ሁሴን፣ ሸምሱ ሰይድ፣ ከድር ታደለ፣ ተመስገን ማርቆስ፣ አሸናፊ መለስ፣ ሚስባህ ከድር፣ አግባው ሰጠኝ፣ ምትኩ ደበላ፣ ካሳ መሃመድ፣ ከበደ ጨመዳ፣ ጌታቸር እሸቴና ፍጹም ጌታቸው በሁለቱ ቀን የፍርድ ቤት ውሎ ምስክር ተሰምቶባቸዋል፡፡

https://netsanetlegna.wordpress.com/2017/08/09/%e1%8a%a5%e1%8a%90-%e1%88%98%e1%89%b6-%e1%8a%a0%e1%88%88%e1%89%83-%e1%88%9b%e1%88%b5%e1%88%a8%e1%88%bb-%e1%88%b0%e1%8c%a4-%e1%89%a0%e1%88%80%e1%88%b0%e1%89%b5-%e1%8a%a5%e1%8b%a8%e1%89%b0%e1%88%98/

Dienstag, 1. August 2017

ግብር በአምባገነን አገዛዝ (በዶ/ር ታደሰ ብሩ ኬርሰሞ)

(የአርበኞች ግንቦት 7 ድምፅ ሬዲዮ)
*******************************
ግብር በአምባገነን አገዛዝ
-------------------------
በዶ/ር ታደሰ ብሩ ኬርሰሞ
 ስለ አምባገነን አገዛዝና ግብር ሲነሳ መጥቀስ የምወደው የእውቁ ኢኮኖክስ ማንኩር ኦልሰን  Dictatorship, Democracy, and Development ነው።  ከዚህ ጽሁፍ በዛ አድርጌ ልጥቀስ።
===
ዘላን ወንበዴዎች /roving bandits/ ነጥቀው ይሮጣሉ፤ መቼ እንደሚመለሱ አይታወቅም። እነዚህ ወንበዴዎች ነጥቀው በሮጡ ቁጥር የማኅበረሰቡ ሀብት የማፍራት ፍላጎት ስለሚዳከም በሚቀጥለው ዙር የሚዘርፉት ነገር እያነሰባቸው ይመጣል። ቀን ባለፈ መጠን ነጥቆ መሮጥ ራሳቸውን እንደሚጎዳቸው ይገነዘቡና ከተዘዋዋሪ ወንበዴነት ወደ ቋሚ ወንበዴነት /stationary bandit/  ይቀየራሉ። ለንጥቂያቸውም ሥርዓትና ልክ ያበጁለታል፤ ስሙን “ግብር” ይሉታል። ማኅበረሰቡንም፣ ራሳቸውንም ከሌሎች ተዘዋዋሪ ወንበዴዎች ይከላከላሉ። ይህ ሥርዓት ከሥርዓተ አልበኝነት የተሻለ፣ የቅሚያውም መጠንም አስቀድሞ የሚታወቅ ከመሆኑ ጋር ማኅበረሰቡ ለሚከፍለው ተመጣጣኝ ባይሆንም የሚያገኘው ጥቅም (ሰላምና ሌሎችም ማኅበራዊ ምርቶች) ስላሉ ምርት ይጨምራል፣  ዕድገትም ይኖራል።
 ይሁን እንጂ አምባገነን ሰፋሪዎች በተደላደሉ መጠን ፍጆታቸው እየናረ መሄዱ ፈጽሞ የማይቀር ነው። ለጦር ሠራዊቱ፣ ለቤተመንግሥቱ፣ ለማሰልጠኛው፣ ለመታሰቢያ ሀውልቶች ግንባታ፣ ለአዳራሾች ግንባታ፣ ለአምባገነኖች፣ ለተከታዮቻቸውና ቤተሰቦቻቸው የክብር ልብሶችና ጌጣጌጦች፣ “ለመጠባበቂያ“፣ .....  የሚያስፈልገው ወጪ በጨመረ ቁጥር ሕዝቡ በግብር አሊያም በሌላ መንገድ እንዲከፍል ስለሚገደድ ሥርዓት በመስፈኑ ምክንያት አንሰራርቶ የነበረው የሥራ ፍላጎት እንደገና ያሽቆለቁላል። የሰፋሪ ወንበዴዎችን የሀብት ማጋበስ፣ ምቾትና እዩልኝ ፍላጎቶችን ማርካት አይቻልም።
==
 በማንኩር ኦልሰን ላይ የምጨምረው የለኝም፤ ሁሉንም ብሎታል።
 ወንበዴዎች ሕዝብን ለማስገበር ሁለት ነገሮች ያስፈልጓቸዋል።  አንዱ ጉልበት ነው። ሞኝ ሽፍታ ዘርፎ ይሮጣል፤ ብልጣብልጥ ሽፍታ ደግሞ ቁጭ ብሎ መዝረፍ ያምረዋል።  ብልጣ ብልጥ ሽፍታ ራሱን በመንግሥትነት ሰይሞ ለዘረፋው “የመንግሥት ግብር “ የሚል ስያሜ ሰጥቶ ተዘራፊን አሰልፎ ደረሰኝ እየሰጠ ይዘርፋል።
 ቁጭ ብሎ ደረሰኝ እየሰጡ ለመዝረፍ ግን ከጉልበት በተጨማሪ ለዘረፋ ሰበብ የሚሆኑ ማኅበራዊ ምርቶች (public goods) ማምረት ያስፈልጋል። ካድሬዎች ሕዝቡን “ግብር የምትከፍለው ለመንገድ፣ ለጤና  አገልግሎት፣ ለትምህርት  ...” ብለው መቀስቀስ አለባቸው። ግብር ግዴታ መሆኑ ቢታወቅም ምክንያታዊ እንደሆነ ማብራራት መቻል አለባቸው። በአምባገነን ሥርዓት ውስጥ ከተሰበሰበው ግብር ምን ያህሉ ወደ ማኅበራዊ ምርት፤ ምን ያህሉ ደግሞ ወደ ባለሥልጣናቱ ኪስ እንደሄደ የሚጠይቅ የለም።  መንገዱም ሆነ ሕንፃው ቢሰራ ለማን፣ ለምን ብሎ የሚሞግት የለም። ሕዝቡ አምፆ እስካላስቀረው ድረስ ደረሰኝ እየተቀበለ ይዘረፋል።
 በህወሓት/ኢሕአዴግ አገዛዝ አገራችን የምትገኝበት ሁኔታ ይህ ነው። የህወሓት ሠፋሪ ወንበዴዎች በግብር ስም እያስራቆቱን ነው። ህወሓት የዘረጋው የግብር ሥርዓት ወንበዴው ቁጭ ብሎ ለፍቶ አዳሪውን የሚመጥበት፤ ድሀው ሀብታሙን የሚደጉምበት ነው። እንዲህ እንዳሁኑ አንዳንዴ የሙስና ዜና  ሲኖር ነው በግብር የተሰበሰበው ገንዘብ የት እንደተከማቸ በወሬ ወሬ የምንሰማው።
 ሌላም ላነሳው የምሻ ጉዳይ አለ:  “ግንዛቤ ማስጨበጥ” የሚሉት።
 አገራችን ውስጥ የወር ደመወዝ ተከፋይ ምንም ከግብር ማምለጫ ቀዳዳ የሌለው በመሆኑ ከሁሉ በላይ ተበዳይ እንደሆነ ስለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ መጠነኛ እውቀት ያለው ሁሉ የሚያውቀው ሀቅ ነው። የግብር ዕዳን ለማስተካከል ሲባል “ነጋዴ ላይ ግብር መጫን የወር ደመወዝተኛው ኑሮ ያሻሽላል” የሚል “ግንዛቤ ማስጨበጥ”  “እኔ ብጎዳም ያንተ ከኔ ይበልጥ መሰቃየት ያስደስተኛል” ዓይነት ሰይጣናዊ አመክኖ ነው። በነጋዴ ላይ የሚጫን ግብር ውሎ አድሮ በሙሉ ወይም በከፊል ወደ ሸቀጦች ዋጋ መተላለፉ አይቀርም።  ይህንን ሽግግር የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅም አያስቀረውም። እናም የወር ደመወዝ ተከፋዩ  የሚጠቀመው በለፍቶ አዳሪው ላይ የግብር ዕዳ በመጫኑ አይደለም። የወር ደመወዝተኛው የሚጠቀመው በለፍቶ አዳሪው ብቻ ሳይሆን በሱም ላይ የተጫነው የግብር ዕዳ  ሲቀንስ ነው።
 ላጠቃለው።
ወገኞቼ፤ ለህወሓት/ኢሕአዴግ አገዛዝ ግብር አልከፍልም ማለት ተገቢ ነው። ለአንባገነን ሥርዓት አልገብርም ማለት ከሥነ ምግባር አንፃር ተቀባይነት ያለው የጽድቅ ሥራ ነው። ለህወሓት አንገብርም ማለት የሚኖርባቸው ነጋዴዎች ብቻ ሳይሆኑ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ነው።