ታሪክ (ጋዜጠኛ ፋሲል የኔዓለም)
የአንድ ጀግና ወታደር ታሪክ
የዛሬ 5 አመት ገደማ ነው፤ አንድ መረጃ ያቀብለን የነበረ መኮንን ደጋግሞ ስልክ ይደውልልኛል፤ ስራ እንደጨረስኩ ደወልኩለት። ሰላም ነው አንበሳው። “ምን ሰላም አለ፤ ስልኩን አላነሳ ስትል ሳልሰናበተው ልቀር ነው እያልኩ ቆጭቶኝ ነበር፣ ስልክህ ሲጠራ እንዴት እንደተደስትኩ አትጠይቀኝ” አለኝ። ይቅርታ ስራ በዝቶብኝ ነው፣ ልትዛወር ነው እንዴ አልኩት። “ እረዳሃለሁ ፋሲሎ፣ ለማንኛውም ጠፍቼ እየሄድኩ ነው፣ የት እንደምሄድ ግን አላውቅም፤ ዛሬ ያየሁትን ነገር ህሊናዬ ሊሸከመው አልቻለም” ። ቆይ ምን ተፈጠረ? “ምን ያልተፈጠረ ነገር አለ፣ እናቶችንና ህጻናትን በጠራራ ጸሃይ ጨረሷቸው፣ እናቶችን ሳይ እናቴ ትዝ አለችኝ”፣ ድምጹ ተቆራረጠ። ወታደር የሚያለቅስ አይመስለኝም ነበር፤ አይዞህ አይዞህ እያልኩ አጽናናሁት። ምንድነው የሆነው እስኪ ተረጋግተህ ንገረኝ አልኩት። “ዛሬ ጠዋት ኦብነግ አንድ መንደር ውስጥ ገብቷል ተብለን ግዳጅ ወጥተን ነበር፤ የክልሉ ልዩ ሃይል አባላት እኛን እየመሩ ወሰዱንና ቦታው ስንደርስ ኦብነጎች ማምለጣቸውን ሰማን፤ ከዚያ በሁዋላ ህዝቡን ማሸበር ተጀመረ፣ እናቶች አትግደሉን እያሉ ተገደሉ፣ ህጻናት መሸሸጊያ ፍለጋ ሲራወጡ ፊት የተገኙት ሁሉ ተገደሉ፣ ወጣት የሚባል የለም፣ አሮጊቶችና ሴቶች ናቸው ታጨዱ፣ ምን ልበልህ፣ መፈጠርክን ትጠላለህ፤ ያየሁትን ለመግለጽ አልችልም፤ ከእንግዲህ ወዲያ ከዚህ ሰራዊት ጋር መቀጠል አልፈልግም ፣ እነሱ ወደ ፊት ሲሄዱ እኔ ጠፍቼ መንገድ ጀምሬያለሁ።” መኮንኑ በስሜት ውስጥ ሆኖ ሲገልጸው የነበረው እና እኔ ከአመታት በሁዋላ ስጽፈው ያለውን ልዩነት እያስተዋልኩ ተናደድኩ። እንደ ዛሬ የደራሲነት ተሰጥዖ እንዲኖረኝ ተመኝቼ አላውቅም።
ስሜትን ዋጥ አደርኩና፣ ለመሆኑ የት ነው የምትሄደው አልኩት። “አላውቅም ኦጋዴንን ታውቀዋለህ፣ ምደረበዳ ነው፤ ከተሳካላኝ ጅቡቲ ወይም ሶማሊያ ልገባ እችላለሁ፤ ምናልባትም በኦብነግ ወይም አልሸባብ እጅ ልወድቅ እችላለሁ፣ የእኛ መከላከያዎች ካሉበት በተቀራኒ አቅጣጫ ነው የምጓዘው። እነሱ እንዲይዙኝ አልፈግልም፤ ከተያዝኩም ምን እንደሚያደርጉኝ አውቃለሁ፣ በእነዚህ ዘረኞች እጅ ላይ ከምወድቅ ኦብነግ ወይም አልሸባብ ቢገድለኝ እመርጣለሁ፤ አሁንማ አያተርፉኝም፤ የሚይዙኝ ከሆነ ግን እራሴን አጠፋለሁ።” ወንድሜ ስማኝ፣ “ አሁን ወደ ቦታህ ተመለስ፣ አሞኝ ነው ወደ ሁዋላ የቀረሁት በላቸው፣ ሌላ ጊዜ አዘናግተህ ትጠፋለህ፣ እኔ ራሴ መንገድህን አመቻችልሃለሁ፣ በፍጹም ወደማታውቀው ቦታ አትሂድ…” እያልኩ ላሳምነው ሞከርኩ። “አላደርገውም፣ የእኔ ነፍስ ካለቁት እናቶችና ህጻናት ነፍስ አይበልጥም። አሁን ባትሪዬን አትጨርሰው፤ የሆነ ቦታ ላይ በሰላም ከደረስኩ ቁጥርህን በቃሌ ስለያዝኩት እደውልልሃለሁ፤ መንገድ ላይ ከቀረሁም ቻው፤ በርታ፣ በጣም አከብርሃለሁ፤ ኦጋዴን ውስጥ የተፈጸመውን ታሪክ በዝርዝር የምናገርበት እድሜ እንዲሰጠኝ ጸልይለኝ ” ብሎኝ፣ እኔም እንደምንም ስሜቴን ዋጥ አድርጌ መልካሙን ሁሉ ተመኝቼ ስልኩን ዘጋሁት። ዛሬም ድረስ ያ ጀግና ወታደር ይደውል ይሆን እያልኩ ስልኩን በጉጉት እጠብቃለሁ። ከተለያየን ከ3 ዓመታት በሁዋላ ቁጥሬን የቀየርኩ በመሆኔ አዲሱ ቁጥሬ ላይኖረው ቢችልም፤ በ3 ዓመታት ውስጥ ለእሱ በሰጠሁት ቁጥር ደውሎልኝ አያውቅም።
ወዳጄ፣ በአንድ ወቅት በብሄራቸው የሚያስቡ አዛዦች የሞሉበት ሰራዊት ተቀይሮ ህዝባዊነትን ሲላበስ ቢያይ ኖሮ፣ ምንኛ ደስ ባለኝ፤ እሱና መሰሎቹ ይህ ቀን እንዲመጣ ስንትና ስንት መስዋትነት መክፈላቸውን አፍ ቢኖረው ኖሮ የውቅሮ እስር ቤት በዝርዝር ያጫውተን ነበር።
https://netsanetlegna.wordpress.com/2018/08/07/%e1%8b%a8%e1%8a%a0%e1%8a%95%e1%8b%b5-%e1%8c%80%e1%8c%8d%e1%8a%93-%e1%8b%88%e1%89%b3%e1%8b%b0%e1%88%ad-%e1%89%b3%e1%88%aa%e1%8a%ad-%e1%8c%8b%e1%8b%9c%e1%8c%a0%e1%8a%9b-%e1%8d%8b%e1%88%b2%e1%88%8d/
Keine Kommentare:
Kommentar veröffentlichen