Netsanet: März 2014

Montag, 31. März 2014

የአድባራት አስተዳዳሪዎች ማኅበረ ቅዱሳንን በአሸባሪነት መፈረጃቸው ሊቃነ ጳጳሳቱን አስቆጣ ::

ቅሬታቸውን ለፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር ሓላፊዎች ገልጸዋል:
ቅሬታቸውን ለፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር ሓላፊዎች ገልጸዋል:


(አዲስ አድማስ መጋቢት 20 2006 ዓ.ም)

የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት ተከታይ በኾኑ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች የቤተ ክርስቲያኒቱን እምነትና ሥርዐት እንዲማሩ፣ ዕውቀታቸውንና ገንዘባቸውን በማቀናጀት ሞያዊ ድጋፍ እንዲያበረክቱ በማስተባበር ላይ የሚገኘውን ማኅበረ ቅዱሳንን በአሸባሪነት በመፈረጅ፣ በቅዱስ ሲኖዶስ አማካይነት ጠቅላላ ሀብቱና ንብረቱ የሚታገድበት ውሳኔ እንዲተላለፍ በመንግሥትም በኩል እርምትና ርምጃ እንዲወሰድበት የአዲስ አበባ ሀ/ስብከት የአድባራት አስተዳዳሪዎች መግለጫ አውጥተውበታል በተባለው ስብሰባ ጉዳይ ኹለት የቅ/ሲኖዶስ አባላት ለከፍተኛ የመንግሥት ሓላፊዎች ቅሬታቸውን ማሰማታቸው ተገለጸ፡፡

የቅ/ሲኖዶሱን ዋና ጸሐፊ ብፁዕ አቡነ ሉቃስንና በአዲስ አበባ ሀ/ስብከት የፓትርያርኩ ረዳት ሊቀ ጳጳስና የጅማ ሀ/ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስን በስም የጠቀሱት የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ምንጮች፣ ሊቃነ ጳጳሳቱ ቅሬታቸውን ያቀረቡት ለፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር ሓላፊዎች እንደኾነ ቢገልጹም የሓላፊዎቹን ስም ከማሳወቅ ተቆጥበዋል።

ቤተ ክርስቲያኒቱ በፀረ ሙስናና በመልካም አስተዳደር ዙሪያ ከመንግሥት ጋራ የተጠናከረ ሥራ ለመሥራት በቅ/ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ መወሰኗን ሊቃነ ጳጳሳቱ አስታውሰው፣ በዚህም መሠረት ለሙስናና ብክነት የተጋለጡ አሠራሮችን ለማረምና ለማስተካከል ጥረት እያደረገች ቢኾንም ባለሥልጣናቱ ከማን ጋር መሥራት እንዳለባቸው በትክክል አለመለየታቸውንና ግንኙነቱም ሙሰኞችን በአይዟችኹ ባይነት የሚያበረታታ እንደኾነ መናገራቸው ተጠቅሷል፡፡

ሊቃነ ጳጳሳቱ ቅሬታቸውን በዚህ መልኩ ለባለሥልጣናቱ ለማቅረብ ያስገደዳቸው የአድባራት አስተዳዳሪዎቹ፣ ‹‹ከመንበረ ፓትርያርክ እስከ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ምእመናንንና የሰንበት ት/ቤት ወጣቶችን ለአድማ ያነሣሣል፤ በሀገርና በቤተ ክርስቲያን ላይ ሁከትና ሽብር እንዲፈጠርና ሰላም እንዲደፈርስ ያደርጋል›› ባሉት በማኅበረ ቅዱሳን ላይ የሚወሰደው አስተዳደራዊ ርምጃ በፀረ ሽብር ሕጉ መሠረት ተጠናክሮ እንዲቀጥል የጠየቁበት መግለጫቸው ነው፡፡

የመንግሥት የተለመደ እገዛ እንዳላቸው በአጽንዖት የጠቀሱት አስተዳዳሪዎቹ በዚሁ መግለጫቸው፣ መንግሥት በፀረ ሽብር ሕጉ ታሳቢነት ገለልተኛ ኦዲተር መድቦ በማኅበሩ ላይ የሀብትና ንብረት ቁጥጥር የማካሔድ ድጋፉ እንዳይለያቸው ያስተላለፉት ጥሪ በሌላቸው ሕጋዊነትና ውክልና የቀረበ፣ ቤተ ክርስቲያኒቱ በራስዋ መንገድ ማከናወን በሚገባት ተግባር ላይ አላስፈላጊ ጣልቃ ገብነትን የሚጋብዝና ለውጭ ተጽዕኖ አሳልፎ የሚሰጥ እንደኾነ ተመልክቷል፡፡

በመንበረ ፓትርያርኩ ከተገኙት የመንግሥት ሓላፊዎች ጋራ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ እንደተካሔደ በተገለጸው የኹለትዮሽ ውይይት፣ ማኅበረ ቅዱሳንን በመቃወም ሰበብ የወጣው የአስተዳዳሪዎቹ መግለጫ ዋነኛ ዓላማ፣ ቤተ ክርስቲያኒቱ በቅዱስ ሲኖዶስ ደረጃ ወስና የምታካሒደውን የአደረጃጀትና የአሠራር ለውጥ ሒደት መጋፋት ነው ተብሏል፡፡ መላውን የሀገረ ስብከቱን አድባራት አገልጋዮች ለመወከል የማይበቁ ጥቂት ግለሰቦችን በመያዝ ይደረጋል የተባለው ይኸው እንቅስቃሴም ‹‹የት እንደሚያደርስ እናየዋለን›› የሚሉ ንግግሮች ጭምር ከሊቃነ ጳጳሳቱ የተሰሙበት እንደነበር ምንጮቹ አስታውቀዋል፤ ጉዳዩም በመጪው ግንቦት በሚካሔደው የቅ/ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ዓቢይ መነጋገርያ መኾኑ እንደማይቀር ተጠቁሟል፡፡

ከሀገረ ስብከቱ አድባራት የተውጣጡ ናቸው የተባሉ አስተዳዳሪዎች ያደረጉት ስብሰባ፣ አስተባባሪዎቹ ከፓትርያርኩ ተሰጥቶናል ከሚሉት ፈቃድ በቀር በሀገረ ስብከቱ የፓትርያርኩ ረዳት ሊቀ ጳጳስና በሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት ዘንድ በይፋ የታወቀና የተፈቀደ እንዳልነበረ ምንጮቹ ለአዲስ አድማስ ገልጸዋል፡፡


ማኅበረ ቅዱሳንን በሁከትና ሽብር ለሚከሱ በቂ ሕጋዊነትና ውክልና የላቸውም ለተባሉ አካላት ፓትርያርኩ የሰጡትን የስብሰባ ፈቃድ፣ በቅርቡ ማኀበሩ አገር አቀፍ የአብነት መምህራን የምክክር ጉባኤ እንዳያካሒድ ከተጣለበት እገዳ ጋር ያነፃፀሩ ታዛቢዎች፣ ሁኔታው የፓትርያርኩን ርምጃዎች መርሕ አልባነት የሚያጋልጥ ነው ይላሉ፡፡ ከዚህም ባሻገር መተዳደርያ ደንብ ያለውና ግልጽ ተልእኮ ይዞ የሚንቀሳቀሰው ማኅበር፣ህልውናና አገልግሎት በግልጽ አስተዳደራዊ ጫና ውስጥ መግባቱን እንደሚያመለክት ታዛቢዎቹ ያምናሉ፡፡

ከመዋቅር፣ ከሀብትና ንብረት ቁጥጥር ጋራ በተያያዘ በማኅበሩ ላይ የሚቀርቡት ውንጀላዎች፣ በፀረ አክራሪነት ስም የሚናፈስበትን ፕሮፓጋንዳ በማጠናከር ፖሊቲካዊ ርምጃ እንዲወሰድበት ፍላጎት ያላቸውን አካላት ምኞት በጉልሕ እንደሚያሳይ አስረድተዋል፡፡ ማኅበሩ ሃይማኖቱን የሚጠብቅ፣ ቤተ ክርስቲያኑን የሚከባከብና ሀገሩን የሚወድ ብቁ ዜጋ ለማፍራት ያለውን ዓላማ የሚረዱ ሊቃነ ጳጳሳት፣ ካህናት፣ ምእመናንና የመንግሥት አካላትም የተቃዋሚዎቹን አቋምና መግለጫ በጥንቃቄ እንዲመለከቱትም አሳስበዋል፡፡

በሌላ በኩል፣ በቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቀኖናና ትውፊት ውጭ ነው በተባለ የሌላ እምነት አስተምህሮ የተነሳ በኮሌጁ ደቀ መዛሙርት መካከልና በደቀ መዛሙርቱ ምክር ቤት አባላት ውስጥ ያለው ግንኙነት ውጥረት ውስጥ እንደገባ እየተገለጸ ነው፡፡


ከኮሌጁ ውጭ ከሚገኙና በቅ/ሲኖዶስ ከተወገዙ ግለሰቦችና ቡድኖች ጋር የዓላማና የጥቅም ግንኙነት መሥርተዋል በተባሉ ጥቂት ደቀ መዛሙርት አማካይነት በኮሌጁ ውስጥ ከመንጸባረቅ አልፎ እንደ ሰደድ እሳት እየተቀጣጠለ ነው የተባለው ይኸው አስተምህሮ፣ አስተዳደራዊ መፍትሔ እንዲበጅለት የደቀ መዛሙርቱ ምክር ቤት ጥር 5 ቀን 2006 ዓ.ም. ለኮሌጁ አስተዳደር ያቀረበው ጥያቄ እስከ አሁን ምላሽ አለማግኘቱ ውጥረቱን የበለጠ እንዳባባሰው ለአዲስ አድማስ የደረሰው መረጃ አመልክቷል፡፡

የአስተምህሮው ውዝግብ አፋጣኝ መፍትሔ አለማግኘቱ ከደቀ መዛሙርቱ አልፎ የምክር ቤት አባላትን ለሁለት እንደከፈለ ተገልጧል፡፡ ኮሌጁንና ደቀ መዛሙርቱን በቅንነትና በትጋት ለማገልገል በደቀ መዛሙርቱ ጠቅላላ ጉባኤ የተመረጠውና ከፍተኛ ሓላፊነት የተጣለበት የደቀ መዛሙርቱ ምክር ቤት፣ ‹‹ከልማቱ ጥፋቱ አመዝኗል›› ያሉት ጸሐፊውና አንድ የአመራር አባሉም ራሳቸውን ማግለላቸው ታውቋል፡፡


‹‹ከቤተ ክርስቲያኒቱ ቀኖናና ትውፊት ውጭ የኾነ የኑፋቄ ትምህርት ሲዘራ ድምፀ ተዓቅቦ ከማድረግ ባሻገር ችግር አለባቸው ከሚባሉት ደቀ መዛሙርት ጎን ተሰልፈው ኮሌጁንም ኾነ ሓላፊነት የሰጠንን ደቀ መዝሙር በቅንነት እንዳናገለግል የአንዳንድ መማክርት አባላት ተግባር አውኮናል›› ያሉት ሁለቱ አባላት፤ በዚህ ሳምንት ለኮሌጁ ዋና ዲን ጽ/ቤት በጻፉት ደብዳቤ፣ ምክር ቤቱ የችግሩ ተባባሪ በመኾኑ ከሓላፊነቱ ታግዶ ጉዳዩ እንዲጣራና እምነታቸውና ሥነ ምግባራቸው በተመሰከረላቸው ደቀ መዛሙርት እንዲተካ ጠይቀዋል፡፡


‹‹የቤተ ክርስቲያንን እንጀራ እየበሉ፣ በጀቷን አውጥታ እያስተማረቻቸው የሌላ እምነት የሚያራምዱ›› ያሏቸውን ወገኖች አጥብቀው እንደሚቃወሙ የገለጹ የደቀ መዛሙርት ተወካዮች በበኩላቸው፣ ኮሌጁ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ዶግማ፣ ቀኖናና ትውፊት ለመጠበቅና ለማስፋፋት የቆመ በመኾኑ አስተዳደሩ፣ በቃል፣ በድምፅና በጽሑፍ የሚቀርቡለትን ማስረጃዎች መርምሮ አስቸኳይ መፍትሔ እንዲሰጣቸው አሳስበዋል፡፡



 minilik salsawi

ጉዳዩ:- የሰላማዊ ሰልፍ ጥያቄአችሁን ይመለከታል::



በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የከንቲባ ጽ/ቤ 17/07/06

ለአንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ (አንድነት)
አዲስ አበባ
ጉዳዩ:- የሰላማዊ ሰልፍ ጥያቄአችሁን ይመለከታል::

ፓርቲያችሁ መጋቢት 15 ቀን 2006 ዓ.ም በቁጥር አንድነት/861/2006 የፃፈው ደብዳቤ መጋቢት 28 ቀን 2006 ዓ.ም ከጠዋቱ 4:00 ስዓት ጀምሮ ከፓርቲው ጽ/ቤት በመነሳት ወደ 4 ኪሎ በመሄድ አደባባዩን ዞሮ ወደ ጠቅላይ ሚኒስቴር ጽ/ቤት የሚያመራ ሰላማዊ ሰልፍ ለማካሄድ እውቅና መጠየቃችሁ ይታወሳል ::

ሆኖም ግን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሰብሰባና የሰላማዊ ሰልፍ አስራር ሥነ ሥርዓት በርካታ ትምህርት ቤቶች የዩንቨርስቲና የመንግስት ተቋማት በሚገኙበት አካባቢ ሰላማዊ ሰልፍ ለማካሄድ የማይቻል መሆኑን የተጠየቀውን የሰላማዊ ሰልፍ ዕውቅና ጥያቄ ተቀባይነት ያላገኙ መሆኑን እንገልፃለን::

ግልባጭ

. በብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ለውስጥ ደህንነት ዋና መምሪያ
. የፌድራል መምሪያ ኮምሽን
. ለአዲስ አበባ ፍትህ ቢሮ
. ለአዲስ ከተማ አስተዳደር ፕሊስ ኮሚሽን አዲስ አበባ

የማሕበረ ቅዱሳን የመጨረሻዎቹ ቀናት – ከተመስገን ደሳለኝ


በኮሎኔል መንግስቱ ኃይለማርያም የሚመራው መንግስት ከናቅፋ እስከ ጉና ተራራ ያሉ ምሽጎቻቸውን ከሰማይ በጦር አይሮፕላን፣ ከምድር እሳት በሚያዘንቡ ቢ.ኤሞችና መድፎች ሳያቋርጥ ደበድብም፤ በሀገሪቱ ሰሜናዊ አካባቢ ከቀን ወደ ቀን ግዛታቸውን እያሰፉ የተጠናከሩት ‹‹ወንበዴዎች›› ራስ ምታት ሆነውበታል፡፡ የኤርትራ ‹‹ነጻ አውጪ›› ቤዝ-አምባው በተወሰነ መልኩም ቢሆን ለጥቃት የመጋለጥ እድሉ አናሳ በሆነው የሳህል በረሃ በመሆኑ አብዛኛው የአመራር አባል መሸሸጊያው አድርጎታል፡፡

በተመሳሳይ መልኩ በትግራይ አካባቢ የሚንቀሳቀሱት የወያኔ መሪዎች ምሽጋቸው እንደ ሳህል ምቹ ባለመሆኑ፤ በርካታ ክፉ ቀናትን ያሳለፉት በተራራማ አካባቢዎች በሚገኙ የኦርቶዶክስ ክርስትና እምነት ገዳማት ውስጥ ተደብቀው እንደሆነና ከቦታ ቦታ መዘዋወር ሲፈልጉም የመነኮሳቱን አልባሳት ይጠቀሙ እንደነበረ በትግሉ ዙሪያ የተዘጋጁ ድርሳናት ያወሳሉ፡፡ በተለይም ታጋይ መለስ ዜናዊ፣ አባይ ፀሀዬ፣ ግደይ ዘርአፅዮን፣ ስዩም መስፍን፣ ስብሐት ነጋን…. የመሳሰሉ የአመራር አባላት የገዳማቱ ቤተኛ ነበሩ፡፡ ከዚሁ ጋ ተያይዞ የሚነገርም አንድ ታሪክ አለ፤ የመንግስት ፀጥታ ሰራተኞች ሁለት የ‹‹ወንበዴ›› መሪዎች በትግራይ በሚገኝ አንድ ገዳም ውስጥ ከመነኮሳቱ ጋር ተመሳስለው መሸሸጋቸው መረጃ ይደርሳቸውና በጥቂት ሰዓታት ውስጥ እስከ አፍንጫቸው የታጠቁ ወታደሮችን በመላክ ዙሪያ ከበባ ያደርጋሉ፡፡ ይሁንና መደበቂያ በመስጠት የረዷቸው መነኮሳት ሁለቱን ታጋዮች ‹‹ወይባ›› በመባል የሚታወቀውን ረጅሙን ቀሚሳቸውን አልብሰው እና ቆብ አስደፍተው ከአካባቢው በማሸሽ ይታደጉዋቸዋል፡፡ የታሪኩ ባለቤት መለስ ዜናዊ እና አባይ ፀሀዬ ነበሩ፡፡ በርግጥ እነዚህ የ‹‹ወንበዴ›› መሪዎች ‹በእንዲህ አይነቱ ከመርፌ አይን እጅግ በጠበበ ዕድል ህይወታችን ከሞት መንጋጋ ተርፎ ኮለኔል መንግሥቱን በጓሮ በር ወደ ዜምባብዌ ሸኝተን በትረ-መንግሥቱን ለመጨበጥና ለሃያ ምናምን ዓመታት ኢትዮጵያን ታህል ታላቅ ሀገር አንቀጥቅጠን ለመግዛት እንበቃለን› የሚል ጠንካራ እምነትና የእርግጠኝነት ስሜት በወቅቱ ነበራቸው ብሎ ማሰብ ለእነርሱም ቢሆን እጅግ አዳጋች ይመስለኛል፤ የሆነው ግን ይህ ነበር፡፡

‹‹ማሕበረ-ቅዱሳን››


መለስ ዜናዊና ጓዶቹ በለስ ቀንቷቸው ባልጠበቁት ፍጥነት የመንግሥት ‹‹ጠንካራ ይዞታ›› የሚባሉ ከተሞችን ሳይቀር እየተቆጣጠሩ ወደ አዲስ አበባ የሚያደርጉትን ግስጋሴ ሲያፋጥኑ፤ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ደግሞ በመንግሥቱ ኃይለማርያም ሰብሳቢበት፣ በደህንነት ሠራተኞች እና የኢሠፓ ካድሬዎች ገፋፊነት ትምህርታቸውን አቋርጠው ለወታደራዊ ስልጠና ደቡብ ኢትዮጵያ ወደሚገኘው ብላቴና የጦር ማሰልጠኛ ከተቱ፤ ዩኒቨርሲቲውም ተዘጋ፡፡

…ከመላው ዘማቾቹ አስራ ሁለት የሚሆኑ ተማሪዎች ተሰባስበው ሲያበቁ፣ በየቀኑ ካምፓቸው አቅራቢያ ወደሚገኘው ‹ሚካኤል ቤተ-ክርስቲያን› በመሄድ፣ ከመዓቱ ይታደጋቸው ዘንድ ፈጣሪያቸውን በፀሎት መማፀን የህይወታቸው አካል አደረጉት፤ ከቀናት በኋላም በአንዱ ዕለት አንድም ለመታሰቢያና ለበረከት፣ ሁለትም ስብስቡ ሳይበተን ወደፊት እንዲቀጥል በሚል ዕሳቤ ‹ማህበረ ሚካኤል› ብለው የሰየሙትን የፅዋ ማህበር መሠረቱ፡፡ …ይሁንና ከመካከላቸው አንዳቸውም እንኳ በ1977 ዓ.ም በ‹ፓዊ መተከል› ዞን የተደረገውን ‹የመልሶ ማቋቋም› ፕሮግራም እንዲያመቻቹ በዘመቱ ተማሪዎች ከተመሠረተውና ከተለያዩ የፅዋ ማህበራት ጋር በመዋሀድ የዛሬውን ‹ማህበረ-ቅዱሳን› እንደሚፈጥሩ መገመት የሚችሉበት የነብይነት ፀጋ አልነበራቸውም፤ የሆነው ግን እንዲያ ነበር፡፡

ኃይማኖትን ጠቅልሎ የመያዝ ዕቅድ

በትጥቅ ትግሉ ወቅት የህወሓት አመራር ገዳማትን ለመሸሸጊያነት ብቻ ሳይሆን ለእርካብ መወጣጫነትም ጭምር ተጠቅሞባቸዋል፡፡ ከድርጅቱ መስራቾች አንዱ የነበረው አረጋዊ በርሄ ለዶክትሬት ዲግሪ ማሟያ ‹‹A Political History of the Tigray People’s Liberation Front (1975-1991): Revolt, Ideology and Mobilisation in Ethiopi›› በሚል ርዕስ ጽፎት፤ ኋላም ወደ መጽሐፍ በቀየረው የጥናት ጽሁፉ ላይ፣ ‹‹የቤተ-ክርስቲያኗን ሥልጣን (በትግራይ የነበረውን) ለማድቀቅ ሲባል በስብሀት ነጋ የሚመራ የስለላ ቡድን ተቋቋመ፡፡ ይህ ቡድንም ደብረ-ዳሞን ጨምሮ በትግራይ ውስጥ ባሉ ገዳማት አባላቱን መነኮሳት በማስመሰል፣ የገዳማቱን እንቅስቃሴ በህወሓት ፍላጎት ስር የማስገዛት ስራ ሰርቷል›› ሲል በገፅ 317 ላይ ገልጿል፡፡ ድርጅቱ ሙሉ በሙሉ ሐይማኖትን ጠቅልሎ ለመያዝ የተነሳበትን ገፊ-ምክንያትም እንዲህ በማለት አብራርቶታል፡-

‹‹ቤተ-ክርስቲያኗ ተከታዮቿን፣ ለነበረው የኢትዮጵያ መንግስት እንዲገዙ ከማስተማር በዘለለ የብሔራዊ ንቃት (ማንነት) ማስተማሪያም ነበረች፡፡ …ለህወሓት እንቅስቃሴ እንቅፋት እንደነበረች ግልፅ ነው፡፡ ስለዚህም ቤተ-ክርስቲያኒቱን በህወሓት ዓላማ ስር ለማሳደር ፍላጎት ነበር፤ በዚህ የተነሳም የእርሷን ተፅእኖ ለማግለል ጥልቅ እርምጃዎች ተወስደዋል፡፡›› (ገፅ 315-316) ዶ/ር አረጋዊ ‹‹ጥልቅ እርምጃዎች›› ብሎ ከጠቀሳቸው መካከል አንደኛው ‹‹ለአጥቢያ ቀሳውስቱ ኮንፍረንስ በማዘጋጀት፣ በትግራይ ውስጥ ያሉትን ቤተ-ክርስቲያናት ለብቻ ነጥሎ ህወሓት በሚያራምደው የትግራይ ብሔርተኝነት ስር ማካተት›› እንደነበረ በዚሁ መጽሐፍ ጠቅሷል፡፡ ይሁንና አስገምጋሚ መብረቅ የወረደብን ያህል የምንደነግጠው፣ ዶ/ሩ ከዚሁ ጋ አያይዞ ‹‹የተጨቆነው የትግራይ ብሔርተኝነት የተነሳሳውም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ-ክርስቲያንን ተፅእኖ ለመገዳደር ነው›› በማለት መመስከሩን ስናነብ ነው፡፡ የአረጋዊ መረጃ የሰሚ-ሰሚ ወይም በቢሆን ሃሳብ የተቀኘ አይደለም፤ ይልቁንም ራሱም በመሪነትና ሃሳብ በማዋጣት ከተሳተፈበት ከድርጅቱ የፖለቲካ ፕሮግራም የተቀዳ እንጂ፡፡

የሆነው ሆኖ ህወሓት ከ1970-72 ዓ.ም ድረስ ባሰለጠናቸው ካድሬ ‹‹ካህናት›› አማካኝነት ‹‹ነፃ በወጡ›› መሬቶች ላይ ራሱን የቻለ የቤተ-ክህነት አስተዳደር (ከሲኖዶሱ የተገነጠለ) መመስረቱ ይታወሳል፡፡ ድርጅቱ ለእነዚህ ቤተ-ክርስቲያናት መተዳደሪያ ደንብ ከመቅረፅ አልፎ ዓላማውንም እንደ አስርቱ ትዕዛዛት በፍፁም ልባቸው የተቀበሉ ‹‹መንፈሳዊ ክንፍ›› አድርጓቸው እንደነበረ፣ አረጋዊ በርሄ ተንትኖ አስረድቷል፡፡ እንዲህ አይነቱ ሰርጎ ገብነት በእስልምናም ላይ መተግበሩ አይዘነጋም፡፡ በተለይም የእምነቱ ተከታዮች በሚበዙበት አካባቢዎች ወላጆቻቸው ሙስሊም የሆኑ ታጋዮችን እየመረጠ እና ከክርስቲያን ቤተሰብ የወጡ ካድሬዎችንም ሀሰተኛ የሙስሊም ስም እየሰጠ ‹የትግሉ ዓላማ እስልምናን ማስፋፋት› እንደሆነ በመግለፅ የፕሮፓጋንዳ ስራ ይሰራ ነበር፡፡ በዚህ ስልቱ በተወሰነ ደረጃም ቢሆን የአንዳንድ ዓረብ ሀገራትን ቀልብ ማግኘት ችሏል፡፡ ይህ ደግሞ ከዓረቦች በገፍ ዕርዳታ ያጎረፈለት ሲሆን፣ ወደ መሀል ሀገር የሚያደርገውን ጉዞም አፋጥኖለታል፡፡

ከመንግስት ለውጥ በኋላም ሁለቱን ሐይማኖቶች የተቆጣጠረው በታጋይ ‹‹ካህናት›› እና ‹‹ሼሆች›› ለመሆኑ በርካታ ማሳያዎች አሉ፡፡ ዛሬም በኦርቶዶክስ ክርስትና እምነት የበላይ በሆነው ጠቅላይ ቤተ-ክህነት ውስጥ ከሚገኙት አስራ ስምንት መምሪያዎች፣ አስራ ስድስቱ በህወሓት ሰዎች የመያዛቸው ኩነት ስልቱ በተሳካ ሁኔታ መተግበሩን ያስረግጣል፡፡ በተለይ ዋነኛው ሰው አቡነ ማቲያስ ሲኖዶሱን ብቻ በሚመለከት ጉዳይ ላይ ጭምር ውሳኔ ከመተላለፉ በፊት ‹‹የመንግስት ባለሥልጣናትን ላማክር›› ሲሉ በተደጋጋሚ መደመጣቸው እና አንዳንድ ጳጳሳት ተቃውሞ በሰነዘሩባቸው ቁጥር በአፃፋው ‹‹መንግስት ያግዘኛል ብዬ ነው እዚህ መንበር ላይ የተቀመጥኩት፤ ባያግዘኝ ሥልጣኑን አልቀበልም ነበር›› በማለት በግላጭ ሲመልሱ መስተዋላቸው ለስርዓቱ ጣልቃ-ገብነት እንደማሳያ ሊቆጠር ይችላል፡፡ ከዚህ ቀደም ለሶስት ወር የቋሚ ሲኖዶሱ አባል ሆነው የሰሩ አንድ ጳጳስም ‹‹ሁልጊዜም ቋሚ ሲኖዶሱ ሲሰበሰብ እርሳቸው (ፓትርያርኩ) ‹መንግስት እንዲህ አለ›፣ ‹መንግስት ሳይፈቅድ›… የሚል ንግግር ይጠቀማሉ›› በማለት ለፋክት አስተያየት ሰጥተዋል (በነገራችን ላይ ፓትርያርኩ የመዘንጋት፣ ለውሳኔ የመቸገር፣ እንቅልፍ የማብዛትና መሰል ችግሮች ስራቸውን እያስተጓጎሉባቸው እንደሆነ ይነገራል፤ ራሳቸውም ‹‹ሲጨንቀኝ እተኛለሁ፤ ስተኛ ደግሞ እረሰዋለሁ›› በማለት ችግሩን አምነው ተቀብለዋል)

በእስልምና እምነት ውስጥም የመንግስት ጣልቃ-ገብነት ከቀድሞውም መጅሊስ የባሰ እንደሆነ በርካታ መዕምናን የሚያውቁት እውነታ ነው፡፡ ይህ መጅሊስ የሚዘወረው እንደተለመደው በምክትል ፕሬዚዳንቶች ሲሆን፤ ይች አይነቷ ጨዋታ ደግሞ ህወሓት ጥርሱን የነቀለበት ስለመሆኑ ነጋሪ አያሻም፡፡ ምክትል ፕሬዚዳንቱ ሼህ ከድር ለ17 ዓመታት የትግራይ ክልል መጅሊስና የሸሪአ ፍ/ቤቱን ደርበው በመያዝ መእምናኑን ቀጥቅጠው ሲገዙ ከመቆየታቸውም በላይ ታጋይ እንደነበሩ በኩራት ለመናገር የሚደፍሩ እንደሆነ የቅርብ ሰዎቻቸው ይመሰክራሉ፡፡ በአናቱም ከታማኝ የመረጃ ምንጭ ባይረጋገጥም የመጅሊሱ ፕሬዚዳንት ሼህ ኪያር መሀመድ ከእኚሁ ‹‹ታጋይ›› ምክትላቸው ጋር በአንዳንድ ጉዳዮች መስማማት ባለመቻላቸው እና ‹‹መንግስት የሚያዘውን ሁሉ ለመስራት ለምን እንገደዳለን?›› የሚል ተቃውሞ እስከማሰማት በመድረሳቸው በቅርቡ ከኃላፊነታቸው ሊነሱ እንደሚችሉ ተወርቷል፡፡

ኢህአዴግ እና ‹‹መንፈሳዊ›› ገበያው


ግንባሩ የእምነት ተቋማትን በአብዮታዊ ዲሞክራሲ አስተሳሰብ ጠርንፎ መያዝን እንደ ዋነኛ ዓላማ አድርጎ የመንቀሳቀሱ መግፍኤን ከሶስት ጉዳዮች አንፃር በአዲስ መስመር ለመተንተን እሞክራለሁ፡-
የመጀመሪያው ቤተ-ክህነት በነገስታቶቹ ዘመን የነበራትን ፖለቲካዊ ተሰሚነት (ምንም እንኳን ራሱ ኢህአዴግም በአፋዊነት ከማውገዝ ቸል ባይልም) ለቅቡልነት መጠቀሚያ የማድረግ ፍላጎቱ ነው፡፡ በገቢር እንደታየውም በኃይል በተቆጣጠራቸውም ሆነ ካድሬዎቹ ሊደርሱባቸው በማይችሉ የገጠር ቀበሌዎች ተቀባይነት ለማግኘት ማህበራዊ አክብሮት ባላቸው ሼሆች፣ ቀሳውስት፣ ዲያቆናት… ሲቀሰቅስ ተደጋጋሚ ጊዜ ተስተውሏል፡፡ እንዲሁም የእስልምና እምነት በታሪክ ያሳለፈውን አገዛዛዊ ጭቆናንም ሆነ የደርጉን ሁሉንም ሐይማኖት ማግለልን በማጎን ለፕሮፓጋንዳ ተጠቅሞበታል (በወቅቱ የድርጅቱ አመራር አባል የነበረው አቶ ገብሩ አስራት፣ እንደ ሼሆች በመልበስና በመጠምጠም ከፍተኛ አስተዋፆ ማበርከቱን ብዙሀኑ ታጋዮች አይዘነጉትም) በዚህ ዘመንም በቤተ-እምነቶች ካድሬ-ጳጳሳትንና ካድሬ-n ሼሆችን አሰርጎ የማስገባቱ ምስጢር ይኸው ነው፡፡

በሁለተኛነት እንደምክንያት ሊጠቀስ የሚችለው የታገለለትን ዘውግ ተኮር ፖለቲካ ያለአንዳች ተግዳሮት ማሳለጥን ታሳቢ ማድረጉ ይመስለኛል፡፡ ምክንያቱም የሁሉም ሐይማኖቶች ‹‹የሰው ልጅ በሙሉ የአንድ አምላክ ፍጡሮች ናቸው›› በሚል አስተምህሮ የሚመሩ ከመሆናቸው አኳያ፣ በዘውግ ከፋፍሎ ማስተዳደርን ቀላል አያደርገውምና ነው፡፡ ስለዚህም መፍትሔው አክራሪ ብሔርተኛ ‹‹መንፈሳውያን›› በየእምነት ተቋማቱ እንዲፈለፈሉ እና ከፍተኛውን የሥልጣን እርከን መቆጣጠር እንዲችሉ በማብቃት ላይ የተመሰረተ ብቻ መሆኑን የህወሓት መሪዎች ያውቃሉ፡፡ ይህ ‹‹እውቀታቸው››ም ይመስለኛል ሀገራዊ ስሜት የሌላቸው፣ በችሎታ ማነስ እና በስነ-ምግባር ጉድለት የሚታወቁ፤ እንዲሁም በእምነቱ ተከታዮች ዘንድ ቅቡል ያልሆኑ ሰዎች ቦታውን እንዲይዙ እስከማድረግ ያደረሳቸው፡፡

የራሳቸው የስለላ መዋቅርም በጥቅምት 2 ቀን 1995 ዓ.ም ‹‹ለዋናው መ/ቤት፣ አዲስ አበባ፤ ከ-ል.ዮ፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ አቡነ ጳውሎስን ጉዳይ ይመለከታል›› በሚል ርዕስ ለደህንነቱ ዋና መስሪያ ቤት በላከው ጥናታዊ ዘገባ ላይ እውነታውን እንዲህ ሲል ገልፆታል፡- ‹‹…ለፓትርያርኩ ወዳጅነት አላቸው የሚባሉ ሊቃነ ጳጳሳት ከሦስትና አራት ብዙም ያልበለጡ ናቸው፡፡ ፓትርያርኩ ምንም ዓይነት ተቀባይነትና ከበሬታ ያጡ በመሆናቸው ህልውናቸውን የአንዳንድ መሪዎችን ስም በመጥራትና እንደማስፈራሪያ በመጠቀም ላይ የተንጠላጠለ ሆኗል››፡፡ ከዚህ ሪፖርት በኋላም እንኳ ለማስተካከል አለመሞከሩ መከራከሪያውን አምነን እንድንቀበል ያስገድደናል፡፡

አገዛዙ መንፈሳዊ ተቋማትን ጠቅልሎ ለመያዝ ለሚያደርገው እንቅስቃሴ በሶስተኛነት ሊጠቀስ የሚችለው ምክንያት፣ ምንም እንኳ ‹‹ተሳክቷል›› ሊባል ባይቻልም፤ በስነ-ምግባር መታነፅ፣ በሀገር አንድነት ማመን፣ ለሕዝብ ጥቅም መቆም፣ የትኛውንም ህገ-ወጥነት ‹ለምን› ብሎ መጠየቅና መሰል መንፈሳዊ አስተምህሮዎችን መርሁ አድርጎ የሚነሳ ትውልድ እንዳይፈጠር መከላከልን ታሳቢ በማድረግ እየሰራ ያለውን ሴራ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ ምክንያቱም የስርዓቱ ሰዎች በዚህ መልኩ የሚቀረፅ ትውልድን ዛሬ ባነበሩት አይነት የጭቆና ቀንበር ለተራዘሙ ዓመታት መግዛት ከባድ እንደሆነ ለመረዳት አይሳናቸውምና ነው፡፡ ከዚሁ ጋር አንስተን ማለፍ ያለብን ጭብጥ፤ መቃብር ከሚቆፈርለት የኢትዮጵያዊ ብሔርተኝነት ጋር የሚያያዝ ነው፤ የሐይማኖቱና የማዕከላዊ መንግስቱ የቅድመ-አብዮቱ ጋብቻ (በምንም አይነት መከራከሪያ ትክክለኛነቱን ልንሟገትለት ባንችልም)፣ ቤተ-ክርስቲያኗ ለኢትዮጵያዊ ብሔርተኝነቱ የታሪክ ብያኔ ከፍተኛ አስተዋፆ ማድረጓን አያስክደንም፡፡ ይህም ‹የሐይማኖቱን ተቋም የብሔርተኝነቱ ወካይ ሆኖ እንዲታሰብ ይገፋዋል› ብሎ ለሚያምነው ህወሓት፣ ሐይማኖቱ ተቋማዊ ነፃነት እንዳይኖረው የሚቻለውን ሁሉ ሲያደርግ፤ ሐይማኖቱን በማዳከም የብሔርተኝነት መንፈሱንም ማላላት ይቻላል ከሚል መነሾ ነው ብሎ መደምደም ተምኔታዊ አያስብልም፡፡

ገደል አፋፍ የቆመው ማሕበረ ቅዱሳን…


ስርዓቱ የሐይማኖት ተቋማትንና መንፈሳዊ መሪዎቹን ለመቆጣጠር ገፊ-ምክንያቶች ሆነውታል ብዬ ከላይ ለማብራራት የሞከርኳቸውን ሶስት ምክንያቶች ሙሉ ለሙሉ መተግበርን አስቸጋሪ ያደረገበት፣ ቀጥታ በምዕምናኑ የተመሰረቱ ማሕበራት መሆናቸውን መገመት ይቻላል፡፡ ለማስረጃም ያህል ከኦርቶዶክስ ክርስትና-ማሕበረ ቅዱሳን፤ ከእስልምና ያለፉትን ሁለት ዓመታት የእምነቱ ተከታዮች ወካይ ሆኖ የተመረጠው ኮሚቴ አባላት መንግስትንም ሆነ መጅሊሱን በመገዳደር ያደረጉትን አበርክቶ መጥቀስ ይቻላል፡፡ ይሁንና የሙስሊሙን ተወካዮች በገፍ ሰብስቦ እስር ቤት ካጎረ በኋላ፣ ከሲኖዶሱም ሆነ መሰል ማሕበራት ጠንካራ እንደሆነ የሚነገርለትን ማሕበረ ቅዱሳንን ዋነኛ ኢላማው አድርጎ ለመደፍጠጥ የቆረጠ ይመስላል፡፡ የማሕበሩ አባላት በዓለማዊ እውቀት የተራቀቁ፣ በሀገር አንድነት በፍፁም የማይደራደሩ፣ በጥቅመኝነት የማይደለሉ… የመሆናቸው ጉዳይ አገዛዙ ከኃይል አማራጭ የቀለለ መፍትሔ የለም ብሎ እንዲያምን አድርጎታል ብዬ እገምታለሁ፡፡

በርግጥ በአቶ መለስ ዜናዊ ይዘጋጅ እንደነበረ ከህልፈቱ በኋላ በተነገረለት የኢህአዴግ የንድፈ ሃሳብ መጽሔት ‹‹አዲስ ራዕይ›› ከተወሰኑ ዓመታት በፊት አብዛኛውን ጊዜ ‹‹የከሰሩ ፖለቲከኞች ‹ኢትዮጵያ የክርስቲያን ደሴት ናት፣ አንድ ሐይማኖት አንድ ሀገር› እና ‹ሙስሊሙ ማሕበረሰብ ቀደም ሲል ሲደርስበት የነበረውን በደል በማራገብና በመቀስቀስ፤ ከዚህም አልፎ ተገቢነት የሌላቸው አዳዲስ ጥያቄዎችን በማቅረብ ለማነሳሳትና ለማተረማመስ ሲሰሩ ማየት የተለመደ ሆኗል›› በማለት ከሚያቀርበው የሾላ-በድፍን ፍረጃ ዘልሎ ብዙም መንፈሳዊ ማሕበራትን በስም ጠቅሶ ሲያወግዝ አይሰማም ነበር፡፡ ዛሬ ዛሬ ግን ማንኛውንም ሐይማኖታዊ የመብት ጥያቄን ‹‹ወሃቢያም ይሁን ማሕበረ ቅዱሳን…›› በማለት ማውገዙ የተለመደ ሆኗል፡፡ ከውግዘትም ተሻግሮ ጥያቄያቸውን በሕጋዊ መንገድ ወደ አደባባይ ያወጡትን የሙስሊሙን ተወካዮች ሰብስቦ አስሯል፤ በተለያየ ጊዜ የተደረጉ ሰላማዊ ተቃውሞዎችንም በማስታከክ በበርካታ የእምነቱ ተከታዮች ላይ ግድያና ስቀየትን ጨምሮ ብዙ ግፍ በመፈፀም ጉዳዩን በጠብ-መንጃ ብቻ የሚፈታ አድርጎ ካወሳሰበው ሰነባብቷል፡፡

‹‹ቀጣዩ የኢህአዴግ ኢላማ ማሕበረ ቅዱሳን ይሆን?›› በሚል ርዕስ ከስድስት ወር በፊት በዚሁ መጽሔት ላይ ለማተት እንደሞከርኩት ሁሉ፤ ከላይ በተዘረዘሩ የፖለቲካ አጀንዳዎች እና በሚቀጥለው ዓመት የሚካሄደውን አገር አቀፍ ምርጫ በለመደው የማጭበርበር መንገድ አሸንፎ ያለኮሽታ የሥልጣን እድሜውን ለማራዘም ዓለማዊም ሆነ መንፈሳዊ ነፃ ተቋማት እንዳይኖሩ በይፋ ኢ-ሕገ መንግስታዊ ድርጊቶችን እየፈፀመ ያለው የእነ አባይ-በረከት መንግስት፣ በአሁኑ ወቅት ሙሉ ትኩረቱን ማሕበረ ቅዱሳን ላይ ማድረጉን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡
ይህንን አፈና ለማሳካትም ፓትርያርኩ አቡነ ማትያስ በፍፁም ልባቸው ከመተባበር ለአፍታም እንደማያመነቱ በርካታ ማሳያዎች አሉ፡፡
ለምሳሌ ያህልም አንዱን በአዲስ መስመር ላቅርብ፡-

ከወራት በፊት የአዲስ አበባ ሀገረ-ስብከት አስተዳደርን ወደ ዘመናዊነት ለማሻገር ሲኖዶሱ ጥናት ተደርጎ እንዲቀርብለት ውሳኔ አሳልፎ ነበር፡፡ እናም ጥናቱ ተጠናቆ ይፋ መደረጉን ተከትሎ ከአንዳንድ የደብር አስተዳዳሪዎች ብርቱ ተቃውሞ ስለገጠመው፣ በሀገረ-ስብከቱ ሥራ-አስኪያጅ አቡነ እስጢፋኖስ አማካኝነት በጠቅላይ ቤተ-ክህነት አዳራሽ ከሁሉም አድባራትና ገዳማት የተወጣጡ 2700 ሰዎች የሚሳተፉበትና አስራ አራት ቀን የሚፈጅ የውይይት ፕሮግራም ይዘጋጃል፡፡ ይሁንና ውይይቱ በተጀመረ በሁለተኛው ቀን ጠዋት ፓትርያርኩ፣ ከአቡነ እስጢፋኖስ ጋር በስልክ ከሞላ ጎደል እንደሚከተለው መወዛገባቸውን ሰምቻለሁ፡-

‹‹ጥናቱን የሚሰሩት ባለሙያዎች ናቸው ብለውኝ አልነበረም ወይ?››
‹‹አዎ! ታዲያስ ባለሙያዎች ናቸው የሰሩት፡፡››
‹‹አይደለም! የማሕበረ ቅዱሳን አባላት ናቸው፤ እርስዎ አታለውኛል!››
‹‹የጥናት ኮሚቴው አባላት በቤተ-ክርስቲያን ልጅነታቸውና በየአጥቢያው ባላቸው ተሳትፎ ተጠርተው የመጡ ሙያቸውን ‹አስራት› ያደረጉ ናቸው፡፡››
‹‹በፍፁም! ጥናቱ የማሕበረ ቅዱሳን ነው!››
‹‹ቅዱስ አባታችን ቢሆንስ? ከጠቀመን ችግሩ ምንድን ነው?››
‹‹በቃ! ውይይቱ ከመንግስት ይቋረጥ ተብሏል፡፡››
‹‹ለምን ይቋረጣል?››
‹‹የጥናቱ ተቃዋሚዎች ረብሻ ያስነሳሉና የፀጥታ ስጋት አለ፡፡››
‹‹ለምንድን ነው ረብሻ የሚያስነሱት? ከፈለጉ መጥተው መሳተፍ ይችላሉ፤ እኛ እየተወያየን አይደለም እንዴ! ተቃውሞ ያለው መጥቶ ሃሳቡን ይግለፅ እንጂ ማቋረጥ እንዴት መፍትሄ ይሆናል? ደግሞስ ሲኖዶሱ አይደለም ወይ ‹ሰነዱ ወደታች ወርዶ ይተችበት› ብሎ የወሰነው?››
‹‹የለም! ይቁም ተብሏል፤ ይቁም!››
‹‹እንግዲያውስ የከለከለው አካል ራሱ መጥቶ ይንገረን፡፡››

…የስልክ ምልልሱ ከተጠናቀቀ ከሰዓታት በኋላ አንድ ባለሥልጣን አቡነ እስጢፋኖስ ቢሮ ድረስ መጥቶ ትእዛዙን ያስተላለፈው እርሱ እንደሆነ ገልፆ ውይይቱ እንዲቋረጥ አሳሰባቸው፤ እርሳቸውም ‹‹እናቋርጣለን፤ ነገር ግን እናንተ ‹የፀጥታ ስጋት አለ› ብላችሁ በደብዳቤ ኃላፊነቱን ውሰዱ፡፡ እኛም ለካህናቱም ሆነ ለመዕምናኑ ሁኔታውን ዘርዝረን እንገልፃለን›› የሚል ምላሽ ሰጥተው ይሸኙታል፡፡ ከዚህ በኋላ ነው እንግዲህ ለጊዜው ግልፅ ባልሆነ አንድ ምክንያት መንግስት ‹‹ይቋረጥ›› የሚለውን ማስፈራሪያ ሊያነሳ የቻለው፡፡ ኩነቱ ግን ፓትርያርኩ ማሕበሩን በጥርጣሬ ማየታቸውንና አገዛዙ ለሚወስድበት ማንኛውም አይነት እርምጃ ተባባሪ መሆናቸውን የሚያሳይ ይመስለኛል፡፡

ሌላው መንግስትና ፓትርያርኩ፣ ማሕበረ ቅዱሳንን ለማፍረስ በሰምና ወርቅነት እየሰሩ መሆናቸውን የሚያመላክተው የዛሬ ሳምንት በጠቅላይ ቤተ-ክህነት የማሕበሩ ተቃዋሚዎች ያደረጉትን ውይይትና የአቋም መግለጫ ስናስተውል ነው፡፡ ለመጽሔቱ ዝግጅት ክፍል የደረሰው በድምፅ የተቀረፀ የውይይቱ ሙሉ ክፍል እንደሚያስረዳው፣ ተሰብሳቢዎቹ ማሕበሩን በተመለከተ ባወጡት የአቋም መግለጫ የሚከተሉትን ነጥቦች ዘርዝረዋል፡- ‹‹የዋነኛ አመራሮቹ የባንክ አካውንት ይመርመር፣ የማሕበሩ ሒሳብ መንግስት በሚመድበው የውጪ ኦዲተር ይመርመር፣ ቋሚና ተንቀሳቃሽ ንብረቶቹ (ከቀረጥ ነፃ ያስገባቸው ቀላልና ከባድ መኪናዎቹ ሳይቀሩ) ወደ ቤተ-ክህነት ይግቡ፣ የንግድ ተቋማቱ (ትምህርት ቤት፣ ሬስቶራንቶቹን፣ ንዋየ ቅድሳት ማምረቻና ማከፋፈያውን) ያስረክብ፣ ከምዕምናን በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የሚቀበለው አስራት እየፈረጠመበት ስለሆነ እንዳይቀበል ይከልከል፣ የግቢ ጉባኤ (በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት) እርሱ በሚቀርፀው እንዳይወሰዱ መስራት፣ ተጠሪነቱ ከዋና ሥራ-አስኪያጁ ተነስቶ፣ በሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ ስር አንዱ ንዑስ ክፍል ይሁን…›› የሚሉና የመሳሰሉት ይገኙበታል፡፡

ከዚህ ሴራ ጀርባ ፓትርያርኩና መንግስት በትብብር መቆማቸውን የሚያሳየው በተቀረፀው ድምፅ ላይ፣ የውይይቱ መሪ አዳራሹን መጠቀም የቻሉት በአቡኑ መልካም ፍቃድ እንደሆነና እርሳቸው በዛሬው ውይይት ያልተገኙት የሕዳሴው ግድብ ምክር ቤት አባል በመሆናቸው ግዮን ሆቴል ስብሰባ ስላለባቸው መሆኑን ከመግለፅም በዘለለ፤ ‹‹ቅዱስ አባታችን በዚህ የተቃውሞ ምክንያት ከሥራ የሚባረር የለም አይዟችሁ አትፍሩ ብለውናል›› በማለት ሲናገሩ መደመጣቸው ነው፡፡ በተጨማሪም ‹‹ከዚህ ግቢ አቅም ኖሮት የሚያስወጣን የለም፤ ካስወጡን ግን መንግስታችን ስለሚተባበረን (ቸር ስለሆነ) ከእርሱ ሌላ መሬት ተቀብለን የራሳችንን ቤተ-ክርስቲያን እናቋቁማለን›› እና ‹‹የኦርቶዶክስ እምነት አገልጋዮች የሚል ማሕበር እንመሰርታለን›› እስከማለት መድረሳቸው ከአገዛዙ ጋር ያላቸውን የጠበቀ ቁርኝት ያመላክታል፡፡ በነገራችን ላይ በስብሰባው እንዲሳተፉ ከተጠሩት ከመቶ ስልሳ ዘጠኙ አድባራትና ገዳማት፣ እንዲሁም ከ10 ሺህ በላይ ሠራተኞቻቸው መካከል የተገኙት የስምንት አድባራት አስተዳዳሪዎችና 150 ሠራተኞች ብቻ እንደነበሩ ከመረጃ ምንጮቼ አረጋግጫለሁ፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ በተለይም በፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር ምኒስትር ዶ/ር ሽፈራው ተክለማሪያም አዝማችነት ማሕበሩ ላይ የደቦ ዘመቻ ከተከፈተ ሰነባብቷል፡፡ በተከታታይ በ‹‹ጥናት›› ስም የሚወጡ ወረቀቶች ማሕበሩን ከአክራሪነትም አሻግረው ‹‹የግንቦት ሰባት መንፈሳዊ ክንፍ›› ሲሉ ይወነጅሉታል፡፡ በጥቅሉ የእነዚህ ‹‹ጥናት›› ተብዬዎች መደምደሚያ ‹‹ማሕበሩ የትምክተኞች ምሽግ ነው፣ አክራሪነት አለበት፣ አመራሩና የሕትመት ውጤቶቹ የፖለቲካ አዝማሚያ ይታይባቸዋል፣ በቤተ-ክርስቲያን አስተዳደር ጣልቃ ይገባል፣ ሕዝቡ በመንግስት ላይ አመኔታ እንዳይኖረው ይሰራል፣ በውጭ ፅንፈኛ የፖለቲካ ኃይሎች ይዘወራል›› የሚሉ ናቸው፡፡ የማሕበሩ የአመራር አባላት እንዲህ አይነቱን ውንጀላ በተመለከተ በተለያየ ጊዜ ከአቶ በረከት ስምኦን እስከ ዶ/ር ሽፈራው ተክለማሪያም፤ ከአዲስ አበባ የፀጥታ ኃላፊዎች እስከ ጠቅላይ ሚንስትሩ የደህንነት አማካሪ ፀጋዬ በርሄ ድረስ ያሉ ባለሥልጣናትን በቢሮአቸው ተገኝተው ውንጀላው ማስረጃ የማይቀርበበት የሀሰት እንደሆነ ቢያስረዱም መፍትሄ እንዳላገኙ ምንጮች ተናግረዋል፡፡ በግልባጩ በመንግስት ተቋማት ያሉ የፋክት መረጃ አቀባዮች፣ በግንቦት ወር ከሚካሄደው የሲኖዶሱ መደበኛ ጉባኤ በፊት፣ ከሃያ የሚበልጡ የማህበሩ አመራርን ከሽብርተኝነት ጋር በማያያዝ ለመክሰስ እና ማሕበሩንም እንደተለመደው በዶክመንተሪ ፊልም ለመወንጀል ዝግጅት መደረጉን ተናግረዋል፡፡ ከሶስት ሳምንት በፊት በአቡነ ገብርኤል ሰብሳቢነት የሚመራው የሐይማኖቶች ምክር ቤት ስብሰባውን ካጠናቀቀ በኋላ ዶ/ር ሽፈራው አቡኑን ቃል-በቃል የጠየቃቸው ጥያቄም ይህንን መረጃ የሚያጠናክር ነው፡-

‹‹በማሕበረ ቅዱሳን አመራር ውስጥ ከሃያ በላይ የተቃዋሚ ፓርቲ አባላት አሉ››
‹‹ለዚህ ምንድን ነው ማስረጃህ? አቅርበውና እስቲ እንየው?››
‹‹ሀገር ውስጥ ካሉ ፅንፈኛ ጋዜጠኞች በተጨማሪ በስደት የሚገኙና በሽብር ተግባር የተሰማሩ ጋዜጠኞች በአመራርነት አሉበት (የሁለት ሰዎችን ስም ጠቅሷል)››
‹‹እኛ እስከምናውቀው ማሕበሩ ከእንዲህ አይነት ተግባር የራቀ ነው፤ እናንተ ማስረጃ አለን ካላችሁ ደግሞ አቅርቡልንና እንየው፤ ከዚህ ውጪ ይህንን አይነት ክስ አንቀበልም፡፡››

በአናቱም ከወራት በፊት የስርዓቱ የንድፈ ሃሳብ መጽሔት የማሕበሩን ስም ሳይጠቅስ በደፈናው የወነጀለበትን እና ‹‹ለምን?›› ብለው የሚጠይቁ ጳጳሳትን በሚከተለው አገላለፅ ማሸማቀቁን ስናስታውስ የማሕበሩ ዕጣ-ፈንታ በመጨረሻዎቹ ቀናት ላይ መቆሙን ያስረግጥልናል፡፡

‹‹በኦርቶዶክስ ቤተ-ክርስቲያን ውስጥ ትርምስና ብጥብጥ ለመፍጠር፤ በኦርቶዶክሶችና ሌሎች ሐይማኖቶች መካከል ግጭት ለመቀስቀስ የሚሞክሩት የደርግና የተለያዩ ትምክህተኛ ኃይሎች ቅሪቶች ናቸው፡፡ እነዚህ የትምክህት ኃይሎችና አንዳንድ የእምነቱ አባቶች በጋራ ሐይማኖትን በፖለቲካ ዓላማ ዙሪያ መጠቀሚያ አድርገው እየሰሩ ለመሆናቸው ከ97 ምርጫ በኋላ እንዳንድ በአሜሪካ የሚገኙ ጳጳሳት ቅንጅት በጠራው ሰልፍ ላይ የሐይማኖት አባትነት ካባቸውን እንደለበሱ ከመሰለፍ አልፈው አስተባባሪ ሆነው መታየታቸው በቂ ማረጋገጫ ነው፡፡›› (አዲስ ራዕይ ሐምሌ-ነሐሴ 2005)

የሆነው ሆኖ ከፍረጃውና ከእስራቱ በተጨማሪ ማሕበሩን ለማዳከም በዋናነት በአገዛዙ የተነደፉት እቅዶች ማሕበሩ መሰረቱን የጣለበት የግቢ ጉባኤን ከመከልከልና ንብረቶቹን ከመውረስ ጋር የሚያያዙ ናቸው (ከላይ የተጠቀሰው የአቋም መግለጫም ለማሕበሩ የደም-ስር የሆኑትን እነዚህን ሁለት ጉዳዮች ትኩረት እንደሰጣቸው ልብ ይሏል)

ስቅለትን-ለተቃውሞ


ኢህአዴግ ወደ ስልጣነ-መንበሩ ከመጣ ሦስተኛ ዓመት ላይ ‹‹የአብዮታዊ ዴሞክራሲ ግቦችና ቀጣይ እርምጃዎች›› በሚል ርዕስ ለካድሬዎቹ በበተነው ድርሳን (በሟቹ አቶ መለስ ዜናዊ የተዘጋጀ ነው ተብሎ ይገመታል)፤ ይህን አሁን የተነጋገርንበትን ሐይማኖታዊ ተቋማትን በሚያቅዳቸው የስልጣን ማራዘሚያ አማራጮች ስለመጠቀም ካወሳ በኋላ ተቋማቱን ለስርዓቱ ፖሊሲዎች እንዲታመኑ ማድረጉ ዋነኛ እንደሆነ ያሰምርበታል፡፡ ይህ የማይቻል ከሆነ ደግሞ፣ እስከ ከፍተኞቹ መንፈሳዊያን መምህራን ድረስ ዘልቆ በመግባት ሐይማኖቶቹን መምራት የአብዮታዊ ዴሞክራሲ ግብ መሆን እንዳለበት ያው ሰነድ በግልፅ ቋንቋ ይናገራል፡፡ እንግዲህ ከመጅሊሱ እስከ ማሕበረ ቅዱሳን ያየነው መንግስታዊ አፈና የዚህን ሃያ ዓመት የሞላው የተፃፈ ሀሳብ መተግበርን ነው፡፡

ግና፣ ከዚህ ቀደም በተፃፈ ነውረኛ ሀሳብ ትግበራ ፊት ከሁለት አስርት በላይ ህልውናውን ለማቆየት የተጋው ማሕበረ ቅዱሳን፣ ከላይ በሚገባ በጠቀስኳቸው አሳማኝ መረጃዎች እና ተጨባጭ ሁነቶች በተከታታይ መከሰት መጨረሻው ምዕራፍ ላይ እንደደረሰ ተመልክተናል፡፡ በዚህ አስቸጋሪ ወቅት ደግሞ፤ መነሳት የሚኖርበት መሰረታዊ ጥያቄ፣ እንዴት ይህን ማሕበር ወደ ቀጣዩ ትውልድ ማሻገር ይቻላል? የሚለው ሲሆን፤ ምላሾቹም ሁለት ናቸው፡፡ የመጀመሪያው የማሕበሩ አመራሮችና አባላት እስከዚህች ቀን እያደረጉ ያለው የውስጥ ለውስጥ የእርምት እንቅስቃሴን ይመለከታል፡፡ በሐይማኖቱ ተቋማት በኩል ለዓመታት ሲሞከር የቆየው ይኸኛው አማራጭ፣ እንደ አስተዋልነው ማሕበሩን ሞት አፋፍ ላይ ከመድረስ ሊታደገው አልቻለም፡፡ ስለዚህም፣ ወደ ሁለተኛውና ዋነኛ የመፍትሔ አማራጭ መሻገር ግድ የሚል ይመስለኛል፡፡ ከዚህ ቀደም በተመሳሳይ ርዕሰ-ጉዳይ ላይ ስፅፍ ለማስረዳት እንደሞከርኩት፤ የማሕበሩ አመራሮች፣ አባላት እና ደጋፊዎች ወደ አደባባይ በመውጣት፤ ማሕበራቸውን ብቻ ሳይሆን ህልውናቸውንና ህያውነታቸውን የመሰረቱበትን ሐይማኖት ለማውደም የሚተጋውን ስርዓት በሰላማዊ አመፅ መናድ ብቸኛው የዚህ አስቸጋሪ ጊዜ መሻገሪያ መንገድ ነው፡፡ በዋናነት የተማሩ ከተሜ ወጣቶችን፣ በአለማዊም ሆነ በትምህርተ-ሐይማኖቱ የማይታሙ ዜጎችን የያዘው ይህ ማሕበር፤ ከህዝበ ሙስሊሙ ‹‹ድምፃችን ይሰማ›› የአደባባይ ተቃውሞ ስኬቶችና ሂደቶች በመማር፤ ፊቱ በተገተረው ኢህአዴግ ላይ በሕጋዊና ሰላማዊ እምቢተኝነት ከማመጽ የተሻለ አማራጭ እንደማይኖረው የሚረዳ ይመስለኛል፡፡

‹‹ችግሮች ሁሉ የየራሳቸው በጎ ገፆች አሏቸው›› እንዲሉ፤ ማሕበሩ የደረሰበት ይህ ፈታኝ ጊዜን ተከትለው የሚመጡ ሁለት ወቅቶች አሉ፡፡ የመጀመሪያው፣ በቀጣዩ ወር የሚካሄደው የስቅለት በዓል ነው፡፡ የሐይማኖቱ ተከታዮች በሙሉ በየቤተ-ክርስቲያናቱ የሚውሉበት ይህ በዓል፣ አገዛዙ እጁን ከማህበሩ ላይ እንዲያነሳ ለመጠየቅ የተመቸ ቀን ስለመሆኑ ማስታወስ አባላቱን አሳንሶ መገመት እንደማይሆን ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ ሁለተኛውና በእጅጉ የተሻለ ነው ብዬ የማስበው ጊዜ ደግሞ ቀጣዩ የ2007 ምርጫን ነው፡፡ ለየትኞቹም የህገ-መንግስቱ ሀሳቦች አልያም የሞራል ዕሴቶች የማይገዛው ኢህአዴግ፣ በሐይማኖቱ ላይም ሆነ በማሕበሩ ላይ የዘረጋውን የረከሰ እጅ እንዲያነሳ ያለው ብቸኛ አማራጭ ሕዝባዊ አመፅ መሆኑ ላይ እስከተማመንን ድረስ፣ ከዓመታዊ የንግስ በዓላት ጀምሮ ያሉ መድረኮችን በዕቅድ ለመጠቀም የዝግጅቱ ጊዜ ዛሬ ነው፡፡ ይህ አይነቱ የተቃውሞ እንቅስቃሴም፣ ካነሳነው ርዕሰ-ጉዳይ አኳያ የማሕበሩን መኖር የሚሹ ሁሉ ቀጣዩን የምርጫ ወቅት ለማስገደጃነት የመጠቀም ተሞክሮዎቻቸውን ተፈላጊው ብቃት ላይ እንደሚያደርሰው አምናለሁ፡፡ ጥቂት ሊባሉ የማይችሉ አባላቱ፣ የምርጫውን ተጨባጭ ዕድል መንግስታዊ ተቋማት በማሽመድመድ ጭምር እንዴት ስርዓቱን ወደመቃብሩ ማሻገር እንደሚያውቁ ስንገነዘብ፤ ቀሪው ጉዳይ ‹‹ሐይማኖታችሁን ተከላከሉ›› ብለው ላስተማሩት ቅዱሳን መጻሕፍትና ለሰማያዊው መንግስት የመታመን ብቻ እንደሚሆን እንረዳለን፡፡

ኢህአዴግ የአፍሪካ ቀንድ ስጋት? አሜሪካ መለስ ከቆፈሩት ጉድጓድ ለመውጣት ወስናለች

አሜሪካ መለስ ከቆፈሩት ጉድጓድ ለመውጣት ወስናለች
March 31, 2014
ለአፍሪካ ቀንድ ሰላም ብቸኛ ተዋናይና ፊት አውራሪ አድርጎ ራሱን የሾመው ኢህአዴግ ለቀጠናው ስጋት እንደሚሆን ተጠቆመ። አልሸባብንና አልቃይዳን ከምንጩ እናጠፋለን በሚል ስትራቴጂ መለስ ከቆፈሩት ጉድጓድ ውስጥ ሰምጣ የነበረችው አሜሪካ ከጉድጓዱ ለመውጣት ወስናለች። ኢትዮጵያዊያን የሚያምኑትና የሚቀበሉትን መሪ በድፍረት አደባባይ የማውጣት ሃላፊነቱ “አገር ወዳድ” በሚሉ ዜጎችና የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች ጫንቃ ላይ ነው።
ህወሃት ያቋቋማቸው ጥቃቅን መንግስታት ከህዝብ ይልቅ ለህወሃት የወደፊት እቅድ ታማኝ በመሆን መጓዛቸው ከቀን ወደቅን የፈጠረው ስሜት ኢህአዴግን እየበላው እንደሆነ የጠቆሙ የዜናው ምንጮች፣ ኢህአዴግ የምስራቅ አፍሪቃ የሰላም አባት ሊሆን ቀርቶ የራሱንም ችግር መፍታት ወደማይችልበት የቁርሾ ማሳ ውስጥ እንደሚገኝ አመልክተዋል።
ህወሃት “በነጻ አውጪነት” ያሰላውና፣ ይህንኑ ዓላማውን በፈለገበት ቀን ተግባራዊ ለማድረግ ያመቸው ዘንድ በየክልሉ ለጣጥፎ ያቋቋማቸውን ፓርቲዎች ሲመሩ የነበሩት አቶ መለስ በድንገት ካለፉ በኋላ ኢህአዴግ ውስጣዊ ሰላሙ መናጋቱ በተደጋጋሚ እየተገለጸ ነው። ኢህአዴግ በበኩሉ “የጓድ መለስን ውርስና ራዕይ ያለማዛነፍ እናስቀጥላለን” እያለ አገሪቱን በደቦ እንድተመራ ማድረጉ የሚታወስ ነው።
አቶ መለስ በጓዶቻቸው ቋንቋ “ተሰው” ከተባለበት ጊዜ ጀምሮ ምክትል ጠ/ሚኒስትር የነበሩትን አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝን ለመተካት ተቸግሮ ነበር። ደህንነቱን፣ መከላከያውን፣ ፖሊስና ዋንኛ የአገሪቱን ተቋማት ጠቅልሎ የያዘው ህወሃት በቀጥታ አሜሪካ ባደረገችው ጫና ሳይወድ በግዱ አቶ ሃይለማርያምን በጠ/ሚኒስትርነት ለመሰየም ተገደደ። የስልጣን ክፍተቱን በተመለከተ አቻ ድርጅቶችና ህወሃት ውስጥ አለመግባባት ተፈጥሮ ስለነበር “ምደባ” በሚል ኢትዮጵያ በደቦ የሚመሯት አራት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሮች ተሰየሙላት።
ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ አንድ የአሜሪካ ዲፕሎማት እንዳሉት አሜሪካ ስጋት የገባት ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ነበር። መለስ እንዳለፉ ልዩ ልዑክ ወደ አዲስ አበባ በመላክ ሁኔታውን በመገምገም ስራ የጀመረችው አሜሪካ አሁን አሁን በህወሃት ስትራቴጂ የተሰራው ኢህአዴግ የምስራቅ አፍሪካ ቀንድ ዋንኛ የችግር ምንጭ ስለመሆኑ ድምዳሜ ላይ ደርሰዋል። በዚህም የተነሳ የአሜሪካ ፖሊሲ አውጪዎች ለጉዳዩ ልዩ ትኩረት በመስጠት እየመከሩበትና የመፍትሔ ስትራቴጂ እየነደፉ ነው።
“We cannot afford to lose Ethiopia” አሜሪካ ኢትዮጵያን ልታጣት አይገባም በማለት ለጎልጉል የዋሽንግቶን ዘጋቢ የተናገሩት የዲፕሎማት ምንጭ “የአሜሪካን ባለስልጣናት ኢህአዴግን በተመለከተ የሚጠቀሙት ቃልና የድምጻቸው ቃና ተቀይሯል” ሲሉ የጉዳዩን ክብደት አመላክተዋል።
በዋሽንግቶን የአሜሪካ ፖሊሲ አውጪዎች፣ የምክር ቤት አባላት እንዲሁም ሌሎች የሚመለከታቸው ኢህአዴግን አስመልክቶ ተደጋጋሚ ስብሰባ መቀመጣቸው ታውቋል። አዲስ አበባም ተወካይ በመላክ ከሚመለከታቸው ባለስልጣናት ጋር በግል እየተነጋገሩ ነው። በያዝነው ሳምንትም ለተመሳሳይ ስራ አዲስ አበባ የተጓዙ አሉ። እንደ ዲፕሎማቱ ገለጻ የህወሃት ሰዎች ውስጣዊ ችግር እንዳለ አይቀበሉም። በግል ያነጋገሯቸው የሌሎች ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች ግን ኢህአዴግ ውስጡ አለመረጋጋትና ስጋት የተሞላው ስለመሆኑ ማረጋገጫ ሰጥተዋል።
በኢትዮጵያ አንድ ችግር ቢፈጠር ለማረጋጋት አስቸጋሪ እንደሚሆን፣ ህዝቡ በተለይ በህወሃቶች ላይ የሚያሳየው ጥላቻ እየተካረረ መምጣቱ፣ በአገሪቱ የሚፈጸመው ያልተመጣጠነ የሃብት ስርጭት፣ አፈናውና ሌሎች የህወሃት/ኢህአዴግ ተግባራት ተዳምረው ህዝቡን ክፉኛ ማስቀየሙ ያልታሰበ ችግር ሊቀሰቅስ እንደሚችል አሜሪካ መገንዘቧን ያወሱት ዲፕሎማት፣ “ህወሀቶች የቀጠናው የሰላም ምንጮች ስለመሆናቸው ለራሳቸው ምስክርነት ለመስጠት ቢሞክሩም በተግባር የሚታየው ግልባጩ ነው” ብለዋል።
ኢትዮጵያ ላይ የተተከለው የጎሳ አገዛዝ እንደሆነ ያመለከቱት እኚሁ ዲፕሎማት “በጎሳ አስተሳሰብ የተዋቀረው ኢህአዴግ ችግሩ ከገነፈለ ሊቆጣጠረው የሚችል ባለስልጣንና መሪ የለውም። አስተዳዳራዊ ማዕከላዊነት አይታይበትም። በግል የሚወስን ባለስልጣንና ርምጃ የሚወስድ አካል የለውም” ሲሉ የስጋቱን ግዝፈት ያሳያሉ። በዚህ ሂደት ውስጥ ችግሩ ቢከሰት ምን ሊፈጠር እንደሚችል ማሰቡ አዳጋች እንደማይሆን ይጠቁማሉ። አያይዘውም “አሜሪካ ቸል ብላ ስትመለከተው የነበረውን ጉዳይ አጽንኦት ብትሰጠው አይገርምም” ብለዋል። አሜሪካ ይህንን የምታደርገው ለራሷ ስትል እንደሆነ ያልሸሸጉት ዲፕሎማት አንድ ጥያቄም ጠይቀዋል። “እናንተስ ለራሳችሁ ስትሉ ምን እየሰራችሁ ነው?” ከረጅም ፈገግታ ጋር።
አልቃይዳን ከምንጩ ማድረቅ በሚለው የመለስ ስትራቴጂ ለኢህአዴግ ግብር ስታስገባ የነበረችው አሜሪካ ግብሯን ስትገብር የኖረችው በፔንታጎን ወታደራዊ ውሳኔ መሰረት ነበር። ኢህአዴግም ግብሩ እንዳይቆምበት በአዲስ አበባ ታክሲ ላይና ህዝብ በሚያዘወትርባቸው ቦታዎች ፈንጂ በማፈንዳት ሲጫወተው የነበረውን ድራማ ዊኪሊክስ (ሹልክ ዓምድ) አምባሳደር ያማማቶን ጠቅሶ ማጋለጡ አይዘነጋም። በዚሁ መነሻ ይመስላል ኢህአዴግ የቀድሞውን ጨዋታ የመጫወት እድሉ እንዳከተመ እንደራሴ ክሪስ ስሚዝ ባደባባይ የመለስን ስብዕና በመዝለፍ ባልተለመደ መልኩ ተናግረው ነበር።
ለጎልጉል መረጃ የሰጡት ዲፕሎማት “እናንተስ” በሚል ለሰነዘሩት ጥያቄ ማብራሪያ ተጠይቀው “እኔ ኢትዮጵያዊ ብሆን አገሬን አስቀድማለሁ” የሚል አጭር ምላሽ ሰጥተዋል። አሜሪካ አማራጭ ማጣቷንም እንደ አንድ ችግር አንስተዋል።
በዲፕሎማቱ አስተያየት ላይ ገለልተኛ ወገኖችን አነጋግረናል። ያሰባሰባንቸው አስተያየቶች “አሜሪካ እዚህ ደረጃ ከደረሰች፣ ኢህአዴግም በዚህ ደረጃ ከተመደበ ተቃዋሚዎች የግል ጉዳያቸውንና ፕሮግራማቸውን ለህዝብ ውሳኔ በመተው ለመጪው ትውልድና ለአገር ሲሉ ከመቧደን በሽታ ሊፈወሱ ይገባል” የሚል ይገኝበታል።
የተቃዋሚ ፓርቲዎች ተቀናጅቶ መበተን፣ ተደራጅቶ መፍረክረክ፣ ተደላድለው መስለል በተለያዩ ወቅቶች ህዝብ ተስፋ እንዲቆርጥ አድርገዋል። የሚፎካከሩትን ፓርቲ ትተው እርስ በርሳቸው ለተራ ጉዳይ ሲሻኮቱ ዓመታት አሳልፈዋል። በዚህም የተነሳ “አማራጭ የለም” በሚል ኢህአዴግን ማንገስ ግድ እንደሆነ የጠቆሙት አስተያየት ሰጪዎች “የተቃዋሚ ፓርቲዎች ይህንን አስተሳሰብ ሰብረው አገር መምራት እንደሚችሉ የሚያረጋግጥ ህብረት መፍጠር ይገባቸዋል። ይህም ካልሆነ የርስ በርስ ውዝግባቸውን ማቆምና የራሳቸውን የቤት ስራ መስራት ላይ ማተኮር ግዳጃቸው ይሆናል” ብለዋል።
ምሁራን ከተደበቁበት ሊወጡ እንደሚገቡም ያሳሰቡ አሉ። አገር የመምራት፣ በህዝብ የመታመን፣ የህዝብን ይሁንታ ማግኘት እንችላለን የሚሉ ከፊት ለፊት፣ አሁን ከፊት ያለውን ችግር በመጥረግ የወደፊቷን ኢትዮጵያ በመገንባትና መጪውን ትውልድ በማዳኑ ስራ አጋዥ ሃይል ለመሆን መወሰን እንደሚገባቸው በመግለጽ ጥሪ አቅርበዋል። ከሁሉም በላይ ግን “አሁን ካለው ህዝብን ካገለለ ዘመናዊ የመሳፍንት ስርዓት ኢትዮጵያንና ህዝቧን ማሻገር የሚችል ሞገሰ ሙሉ፣ ቅን፣ ከጥላቻ የጸዳ፣ ከሥልጣን ይልቅ የወደፊቷን ኢትዮጵያ አሻግሮ መመልከት የሚችል መሪ ወደ ፊት ወጥቶ በግልጽ ለህዝብ የሚተዋወቅበትን መንገድ የማህበራዊ ሚዲያዎች፣ ድረገጾች፣ ሬዲዮኖች አገር ወዳድ የመገናኛ አውታሮች አጀንዳ አድርገው ሊወያዩበት ይገባል” የሚለው አስተያየት ሚዛኑን የደፋ ሆኗል።

በብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት… የህወሃት ሰዎች ጉድ!

በዝርፊያ ወንጀል ተጠርጥረው በተከሰሱ የደኅንነት ሠራተኞች ላይ ምስክሮች ተደመጡ
በውጭ ዜጋ ላይ ዝርፊያ በመፈጸም ወንጀል ተጠርጥረው በተከሰሱ የደኅንነት ሠራተኞች ላይ ምስክሮች መደመጥ ጀመሩ፡፡
የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት የአገር ውስጥ ደኅንነት ሠራተኛ በሆኑት አቶ ዮሐንስ ኪሮስ አብዩና በአቶ በኩረ ጽዮን አብረሃ ዜና፣ እንዲሁም ሾፌር መሆኑ በተገለጸውና ተባባሪ ነው በተባለው የኑስ አብዱልቃድር መሐመድ ላይ የፌዴራል የሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽን ዓቃቤ ሕግ ያቀረባቸውን ምስክሮች መስማት የጀመረው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ አንደኛ ወንጀል ችሎት መጋቢት 18 ቀን 2006 ዓ.ም. ነው፡፡
ክሱ እንደሚለው፣ ሁለቱ ተጠርጣሪዎች ከአሥር ወራት በፊት ግንቦት 14 ቀን 2005 ዓ.ም. ከምሽቱ 12፡30 ሰዓት ሲሆን በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ቀበሌ 19 ልዩ ቦታው ደንበል ሲቲ ሴንተር ሕንፃ አካባቢ፣ ሚስተር ካሊድ አዋድ የተባሉ የሳዑዲ ዓረቢያ ዜግነት ያላቸውን ግለሰብ ያገኟቸዋል፡፡
ግለሰቡን ሲፈትሿቸው 1,200 ዶላርና 1,600 የሳዑዲ ሪያል አግኝተው ከወሰዱ በኋላ፣ ወደ ካራማራ ፖሊስ ጣቢያ ወስደው እንዳሳደሯቸው ክሱ ያስረዳል፡፡ በማግሥቱ ግንቦት 15 ቀን 2005 ዓ.ም. የግል ተበዳይን ቤታቸው በመውሰድ ቤታቸውን በመበርበርና የተቆለፈ ሳምሶናይት በመስበር 8,000 የሳዑዲ ሪያልና 2,000 ዶላር፣ በድምሩ ወደ ኢትዮጵያ ብር ሲቀየር 106,880 ብር ለግል ጥቅማቸው ማዋላቸውንም በክሱ ተጠቁሟል፡፡
ሾፌር መሆኑ የተገለጸው የኑስ አብዱልቃድር የተባለው ተርጣሪ ደግሞ ከሁለቱ ተጠርጣሪዎች ጋር በመመሳጠር፣ የግል ተበዳይ የሆኑትን የሚስተር ካሊድ አዋድን ቦታና እንቅስቃሴ በመጠቆም፣ እንዲሁም የተሽከርካሪ አገልግሎት በመስጠትና በወንጀሉ ተሳትፎ በማድረግ 13,000 ብር ለግል ጥቅሙ ማዋሉን ክሱ ያብራራል፡፡
የደኅንነት ሠራተኞቹ የግል ተበዳይን በቁጥጥር ሥር ባዋሉበት ዕለት በግምት ከምሽቱ 3፡00 ሰዓት ሲሆን፣ የተበዳዩ ሠራተኛ መሆናቸው ለተገለጸ ግለሰብ ስልክ ደውለው 100 ሺሕ ብር ካልሰጧቸው ተበዳዩ እንደማይፈቱ መግለጻቸውን የኮሚሽኑ ዓቃቤ ሕግ ክስ ያስረዳል፡፡
በአጠቃላይ ተጠርጣሪዎቹ በዋና ወንጀል አድራጊነት ፈጸሙት በተባለው ገንዘብ ወስዶ መሰወርና ጉቦ መጠየቅ የሙስና ወንጀል ክስ ተመሥርቶባቸው፣ ዓቃቤ ሕግ እንደ ክሱ የሚያስረዱለትን ሦስት ምስክሮች ለፍርድ ቤቱ አቅርቧል፡፡
የዓቃቤ ሕግ የመጀመሪያ ምስክር ለፍርድ ቤቱ እንዳስረዱት፣ ሾፌሩ ስልክ ደውሎላቸው 100 ሺሕ ብር ካልሰጧቸው ተበዳዩን እንደማይለቋቸው እንደገለጹላቸውና በድጋሚ ከደኅንነት ሠራተኛው በኩረ ጽዮን ጋር በመሆን የተጠየቀውን 100 ሺሕ ብር ወደ 80 ሺሕ እና 50 ሺሕ ብር ዝቅ በማድረግ እንደተደራደሯቸው መስክረዋል፡፡
ሁለተኛው ምስክር የግል ተበዳዩ ሲሆኑ፣ በክሱ ላይ የሰፈረውን ቃል በቃል አስረድተዋል፡፡ ፍርድ ቤቱ ቀሪ ምስክር ለመስማት ለሚያዝያ 9 ቀን 2006 ዓ.ም. ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡
Source_ethioforum.org

መጋቢት 28 2006 ደረሰ !!! አዲስ አበባ‹‹ለእሪታ ቀን!››

March 31/2014

ኡኡ እንበል #UDJ #AddisAbba
መጋቢት ሃያ ስምንት በአዲስ አበባ ህዝብ እሪታ ኡኡ ሊል ነው ዳር እስከ ዳር የአዲስ አበባን ህዝብ አንድነት ፓርቲ ሰልፍ ጠርትዋል ውሃ የለም ቧንቧ ብቻ ስልክ የለም ገመድ ብቻ መብራት የለም ቆጣሪ ብቻ ትራንስፖርት የለም የትራንስፎርሜሽን እቅድ ብቻ እነሆ ነነዚህን ሁሉ ብሶት የሚገለፅበት የእሪታ ቀን መጋቢት ሃያ ስምንት አንድነተ ፓርቲ ቀን ቆርጦ ኑ ኡኡ እንበል ብልዋል

በሰሜን ጎንደር በላይ አርማጭሆ ትክል ድንጋይ አካባቢ የኢትዮጵያ ሕዝብ አርበኞች ግንባር በራሪ ወረቀት ተበተነ::

March 30/2014

በሰሜን ምዕራቡ የሀገሪቱ ክፍል ተሰማርቶ የሚገኘው የኢትዮጵያ ሕዝብ አርበኞች ግንባር ሠራዊት ተከታታይና ቀጣይ የሆኑ አውደ ውጊያዎችን በመፈጸም የወያኔን ጦር እያሽመደመደው ከመሆኑም በተጨማሪ ግንባሩ በአሁኑ ሰዓት የአካባቢውን ማሕበረሰብ የማንቃት፣ የማደራጀትና የመቀስቀስ ተግባር ላይ ተሰማርቶ እየሰራ ሲሆን የደርጅቱን ዓላማና ፕሮግራም ያነገቡ በራሪ ወረቀቶችንም በብዛት በማዘጋጀት ወደ ሕብረተሰቡ እንዲደርሱ ተግቶ በመስራት ላይ እንደሚገኝ ይታወቃል።
በዚህም መሰረት በመጋቢት 20 ቀን 2006 ዓ/ም በሰሜን ጎንደር በላይ አርማጭሆ ወረዳ ትክል ድንጋይ አካባቢ የኢትዮጵያ ሕዝብ አርበኞች ግንባርን ዓላማና ፕሮግራም ያነገቡ በራሪ ወረቀቶች በብዛት የተበተነ ሲሆን በአካባቢው ነዋሪ የማሕበረሰብ ክፍሎች እነዚህ በራሪ ወረቀቶች በብዛት የተሰራጩ ከመሆኑም ባሻገር ወረቀቶቹ ባልተዳረሱበት አካባቢ ለማሰራጨት ነዋሪዎች ተግተው በመንቀሳቀስ ላይ እንደሚገኙ ሪፖርተራችን ከስፍራው ያደረሰን መረጃ ያመለክታል።
ይህንኑ በራሪ ወረቀት ወደ ሕብረተሰቡ በፍጥነት እንዲሰራጩ ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል በሚልና ከዚሁ ጋር ተያያዥነት ባለው ጉዳይ በርካታ የአካባቢው ነዋሪዎች በገዢው ቡድን ታጣቂ ሃይሎች እየታደኑ ለእስር መዳረጋቸውን እንዲሁም በትክል ድንጋይና አካባቢዋ ከፍተኛ ውጥረት መንገሱን መረጃው ጨምሮ ገልጿል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በላይ አርማጭሆ ወረዳ ትክል ድንጋይ አካባቢ የተበተነው የኢትዮጵያ ሕዝብ አርበኞች ግንባር በራሪ ወረቀት በሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎች በሰፊው እንዲሰራጩ የአካባቢው ወጣቶች በራሪ ወረቀቶቹን እያባዙ በመበተን ላይ እንደሚገኙ የተገለፀ ሲሆን የኢትዮጵያ ሕዝብ አርበኞች ግንባር (ኢ.ሕ.አ.ግ) የወቅቱን የፖለቲካ ትኩሳትና ተጨባጭ የወያኔ እንቅስቃሴዎችን መሰረት በማድረግ የኢትዮጵያን ሕዝብ ለበለጠ የፀረ- ወያኔ ትግል የሚያነሳሱ በራሪ ወረቀቶች በማሰራጨትና የትጥቅ ትግሉ የደረሰበትን የዕድገት አቅጣጫና አናሳው የወያኔ ቡድን በሕዝብ እና በሀገር ላይ እየፈጸመ ያለውን ስውር ደባ በማጋለጥ በኩል ጉልህ የፕሮፖጋንዳ መሳሪያ በመሆን ሕዝብን ወደ ትጥቅ ትግሉ ጎራ እንዲቀላቀሉ ተነሳሽነትን የፈጠረ መሆኑ የአካባቢው ነዋሪ ማሕበረሰብ መናገራቸውን የሪፖርተራችን መረጃ ያስረዳል።
በመጨራሻም በራሪ ወረቀቶቹ በተሰራጩባቸው አካባቢዎች የሚኖሩ የሕብረተሰብ ክፍሎች በስፍራው ለሚገኘው ሪፖርተራችን እንደገለጹለት ከሆነ በራሪ ወረቀቶቹ ወቅታቸውን የጠበቁ የሁሉንም ሕብረተሰብ ብሶትና ምሬት ገላጭ መሆናቸውን ነዋሪዎቹ ገልጸው ለግንባሩ የሀገር አድን ጥሪ ምላሽ የምንሰጥበት ወቅት ላይ በመሆናችን የግንባሩን ሠራዊት በመቀላቀል የዜግነት ግዴታችንን ለመወጣት ቆርጠን ተነስተናል ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።