በኮሎኔል መንግስቱ ኃይለማርያም የሚመራው መንግስት ከናቅፋ እስከ ጉና ተራራ ያሉ ምሽጎቻቸውን ከሰማይ በጦር አይሮፕላን፣ ከምድር እሳት በሚያዘንቡ ቢ.ኤሞችና መድፎች ሳያቋርጥ ደበድብም፤ በሀገሪቱ ሰሜናዊ አካባቢ ከቀን ወደ ቀን ግዛታቸውን እያሰፉ የተጠናከሩት ‹‹ወንበዴዎች›› ራስ ምታት ሆነውበታል፡፡ የኤርትራ ‹‹ነጻ አውጪ›› ቤዝ-አምባው በተወሰነ መልኩም ቢሆን ለጥቃት የመጋለጥ እድሉ አናሳ በሆነው የሳህል በረሃ በመሆኑ አብዛኛው የአመራር አባል መሸሸጊያው አድርጎታል፡፡
በተመሳሳይ መልኩ በትግራይ አካባቢ የሚንቀሳቀሱት የወያኔ መሪዎች ምሽጋቸው እንደ ሳህል ምቹ ባለመሆኑ፤ በርካታ ክፉ ቀናትን ያሳለፉት በተራራማ አካባቢዎች በሚገኙ የኦርቶዶክስ ክርስትና እምነት ገዳማት ውስጥ ተደብቀው እንደሆነና ከቦታ ቦታ መዘዋወር ሲፈልጉም የመነኮሳቱን አልባሳት ይጠቀሙ እንደነበረ በትግሉ ዙሪያ የተዘጋጁ ድርሳናት ያወሳሉ፡፡ በተለይም ታጋይ መለስ ዜናዊ፣ አባይ ፀሀዬ፣ ግደይ ዘርአፅዮን፣ ስዩም መስፍን፣ ስብሐት ነጋን…. የመሳሰሉ የአመራር አባላት የገዳማቱ ቤተኛ ነበሩ፡፡ ከዚሁ ጋ ተያይዞ የሚነገርም አንድ ታሪክ አለ፤ የመንግስት ፀጥታ ሰራተኞች ሁለት የ‹‹ወንበዴ›› መሪዎች በትግራይ በሚገኝ አንድ ገዳም ውስጥ ከመነኮሳቱ ጋር ተመሳስለው መሸሸጋቸው መረጃ ይደርሳቸውና በጥቂት ሰዓታት ውስጥ እስከ አፍንጫቸው የታጠቁ ወታደሮችን በመላክ ዙሪያ ከበባ ያደርጋሉ፡፡ ይሁንና መደበቂያ በመስጠት የረዷቸው መነኮሳት ሁለቱን ታጋዮች ‹‹ወይባ›› በመባል የሚታወቀውን ረጅሙን ቀሚሳቸውን አልብሰው እና ቆብ አስደፍተው ከአካባቢው በማሸሽ ይታደጉዋቸዋል፡፡ የታሪኩ ባለቤት መለስ ዜናዊ እና አባይ ፀሀዬ ነበሩ፡፡ በርግጥ እነዚህ የ‹‹ወንበዴ›› መሪዎች ‹በእንዲህ አይነቱ ከመርፌ አይን እጅግ በጠበበ ዕድል ህይወታችን ከሞት መንጋጋ ተርፎ ኮለኔል መንግሥቱን በጓሮ በር ወደ ዜምባብዌ ሸኝተን በትረ-መንግሥቱን ለመጨበጥና ለሃያ ምናምን ዓመታት ኢትዮጵያን ታህል ታላቅ ሀገር አንቀጥቅጠን ለመግዛት እንበቃለን› የሚል ጠንካራ እምነትና የእርግጠኝነት ስሜት በወቅቱ ነበራቸው ብሎ ማሰብ ለእነርሱም ቢሆን እጅግ አዳጋች ይመስለኛል፤ የሆነው ግን ይህ ነበር፡፡
‹‹ማሕበረ-ቅዱሳን››
መለስ ዜናዊና ጓዶቹ በለስ ቀንቷቸው ባልጠበቁት ፍጥነት የመንግሥት ‹‹ጠንካራ ይዞታ›› የሚባሉ ከተሞችን ሳይቀር እየተቆጣጠሩ ወደ አዲስ አበባ የሚያደርጉትን ግስጋሴ ሲያፋጥኑ፤ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ደግሞ በመንግሥቱ ኃይለማርያም ሰብሳቢበት፣ በደህንነት ሠራተኞች እና የኢሠፓ ካድሬዎች ገፋፊነት ትምህርታቸውን አቋርጠው ለወታደራዊ ስልጠና ደቡብ ኢትዮጵያ ወደሚገኘው ብላቴና የጦር ማሰልጠኛ ከተቱ፤ ዩኒቨርሲቲውም ተዘጋ፡፡
…ከመላው ዘማቾቹ አስራ ሁለት የሚሆኑ ተማሪዎች ተሰባስበው ሲያበቁ፣ በየቀኑ ካምፓቸው አቅራቢያ ወደሚገኘው ‹ሚካኤል ቤተ-ክርስቲያን› በመሄድ፣ ከመዓቱ ይታደጋቸው ዘንድ ፈጣሪያቸውን በፀሎት መማፀን የህይወታቸው አካል አደረጉት፤ ከቀናት በኋላም በአንዱ ዕለት አንድም ለመታሰቢያና ለበረከት፣ ሁለትም ስብስቡ ሳይበተን ወደፊት እንዲቀጥል በሚል ዕሳቤ ‹ማህበረ ሚካኤል› ብለው የሰየሙትን የፅዋ ማህበር መሠረቱ፡፡ …ይሁንና ከመካከላቸው አንዳቸውም እንኳ በ1977 ዓ.ም በ‹ፓዊ መተከል› ዞን የተደረገውን ‹የመልሶ ማቋቋም› ፕሮግራም እንዲያመቻቹ በዘመቱ ተማሪዎች ከተመሠረተውና ከተለያዩ የፅዋ ማህበራት ጋር በመዋሀድ የዛሬውን ‹ማህበረ-ቅዱሳን› እንደሚፈጥሩ መገመት የሚችሉበት የነብይነት ፀጋ አልነበራቸውም፤ የሆነው ግን እንዲያ ነበር፡፡
ኃይማኖትን ጠቅልሎ የመያዝ ዕቅድ
በትጥቅ ትግሉ ወቅት የህወሓት አመራር ገዳማትን ለመሸሸጊያነት ብቻ ሳይሆን ለእርካብ መወጣጫነትም ጭምር ተጠቅሞባቸዋል፡፡ ከድርጅቱ መስራቾች አንዱ የነበረው አረጋዊ በርሄ ለዶክትሬት ዲግሪ ማሟያ ‹‹A Political History of the Tigray People’s Liberation Front (1975-1991): Revolt, Ideology and Mobilisation in Ethiopi›› በሚል ርዕስ ጽፎት፤ ኋላም ወደ መጽሐፍ በቀየረው የጥናት ጽሁፉ ላይ፣ ‹‹የቤተ-ክርስቲያኗን ሥልጣን (በትግራይ የነበረውን) ለማድቀቅ ሲባል በስብሀት ነጋ የሚመራ የስለላ ቡድን ተቋቋመ፡፡ ይህ ቡድንም ደብረ-ዳሞን ጨምሮ በትግራይ ውስጥ ባሉ ገዳማት አባላቱን መነኮሳት በማስመሰል፣ የገዳማቱን እንቅስቃሴ በህወሓት ፍላጎት ስር የማስገዛት ስራ ሰርቷል›› ሲል በገፅ 317 ላይ ገልጿል፡፡ ድርጅቱ ሙሉ በሙሉ ሐይማኖትን ጠቅልሎ ለመያዝ የተነሳበትን ገፊ-ምክንያትም እንዲህ በማለት አብራርቶታል፡-
‹‹ቤተ-ክርስቲያኗ ተከታዮቿን፣ ለነበረው የኢትዮጵያ መንግስት እንዲገዙ ከማስተማር በዘለለ የብሔራዊ ንቃት (ማንነት) ማስተማሪያም ነበረች፡፡ …ለህወሓት እንቅስቃሴ እንቅፋት እንደነበረች ግልፅ ነው፡፡ ስለዚህም ቤተ-ክርስቲያኒቱን በህወሓት ዓላማ ስር ለማሳደር ፍላጎት ነበር፤ በዚህ የተነሳም የእርሷን ተፅእኖ ለማግለል ጥልቅ እርምጃዎች ተወስደዋል፡፡›› (ገፅ 315-316) ዶ/ር አረጋዊ ‹‹ጥልቅ እርምጃዎች›› ብሎ ከጠቀሳቸው መካከል አንደኛው ‹‹ለአጥቢያ ቀሳውስቱ ኮንፍረንስ በማዘጋጀት፣ በትግራይ ውስጥ ያሉትን ቤተ-ክርስቲያናት ለብቻ ነጥሎ ህወሓት በሚያራምደው የትግራይ ብሔርተኝነት ስር ማካተት›› እንደነበረ በዚሁ መጽሐፍ ጠቅሷል፡፡ ይሁንና አስገምጋሚ መብረቅ የወረደብን ያህል የምንደነግጠው፣ ዶ/ሩ ከዚሁ ጋ አያይዞ ‹‹የተጨቆነው የትግራይ ብሔርተኝነት የተነሳሳውም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ-ክርስቲያንን ተፅእኖ ለመገዳደር ነው›› በማለት መመስከሩን ስናነብ ነው፡፡ የአረጋዊ መረጃ የሰሚ-ሰሚ ወይም በቢሆን ሃሳብ የተቀኘ አይደለም፤ ይልቁንም ራሱም በመሪነትና ሃሳብ በማዋጣት ከተሳተፈበት ከድርጅቱ የፖለቲካ ፕሮግራም የተቀዳ እንጂ፡፡
የሆነው ሆኖ ህወሓት ከ1970-72 ዓ.ም ድረስ ባሰለጠናቸው ካድሬ ‹‹ካህናት›› አማካኝነት ‹‹ነፃ በወጡ›› መሬቶች ላይ ራሱን የቻለ የቤተ-ክህነት አስተዳደር (ከሲኖዶሱ የተገነጠለ) መመስረቱ ይታወሳል፡፡ ድርጅቱ ለእነዚህ ቤተ-ክርስቲያናት መተዳደሪያ ደንብ ከመቅረፅ አልፎ ዓላማውንም እንደ አስርቱ ትዕዛዛት በፍፁም ልባቸው የተቀበሉ ‹‹መንፈሳዊ ክንፍ›› አድርጓቸው እንደነበረ፣ አረጋዊ በርሄ ተንትኖ አስረድቷል፡፡ እንዲህ አይነቱ ሰርጎ ገብነት በእስልምናም ላይ መተግበሩ አይዘነጋም፡፡ በተለይም የእምነቱ ተከታዮች በሚበዙበት አካባቢዎች ወላጆቻቸው ሙስሊም የሆኑ ታጋዮችን እየመረጠ እና ከክርስቲያን ቤተሰብ የወጡ ካድሬዎችንም ሀሰተኛ የሙስሊም ስም እየሰጠ ‹የትግሉ ዓላማ እስልምናን ማስፋፋት› እንደሆነ በመግለፅ የፕሮፓጋንዳ ስራ ይሰራ ነበር፡፡ በዚህ ስልቱ በተወሰነ ደረጃም ቢሆን የአንዳንድ ዓረብ ሀገራትን ቀልብ ማግኘት ችሏል፡፡ ይህ ደግሞ ከዓረቦች በገፍ ዕርዳታ ያጎረፈለት ሲሆን፣ ወደ መሀል ሀገር የሚያደርገውን ጉዞም አፋጥኖለታል፡፡
ከመንግስት ለውጥ በኋላም ሁለቱን ሐይማኖቶች የተቆጣጠረው በታጋይ ‹‹ካህናት›› እና ‹‹ሼሆች›› ለመሆኑ በርካታ ማሳያዎች አሉ፡፡ ዛሬም በኦርቶዶክስ ክርስትና እምነት የበላይ በሆነው ጠቅላይ ቤተ-ክህነት ውስጥ ከሚገኙት አስራ ስምንት መምሪያዎች፣ አስራ ስድስቱ በህወሓት ሰዎች የመያዛቸው ኩነት ስልቱ በተሳካ ሁኔታ መተግበሩን ያስረግጣል፡፡ በተለይ ዋነኛው ሰው አቡነ ማቲያስ ሲኖዶሱን ብቻ በሚመለከት ጉዳይ ላይ ጭምር ውሳኔ ከመተላለፉ በፊት ‹‹የመንግስት ባለሥልጣናትን ላማክር›› ሲሉ በተደጋጋሚ መደመጣቸው እና አንዳንድ ጳጳሳት ተቃውሞ በሰነዘሩባቸው ቁጥር በአፃፋው ‹‹መንግስት ያግዘኛል ብዬ ነው እዚህ መንበር ላይ የተቀመጥኩት፤ ባያግዘኝ ሥልጣኑን አልቀበልም ነበር›› በማለት በግላጭ ሲመልሱ መስተዋላቸው ለስርዓቱ ጣልቃ-ገብነት እንደማሳያ ሊቆጠር ይችላል፡፡ ከዚህ ቀደም ለሶስት ወር የቋሚ ሲኖዶሱ አባል ሆነው የሰሩ አንድ ጳጳስም ‹‹ሁልጊዜም ቋሚ ሲኖዶሱ ሲሰበሰብ እርሳቸው (ፓትርያርኩ) ‹መንግስት እንዲህ አለ›፣ ‹መንግስት ሳይፈቅድ›… የሚል ንግግር ይጠቀማሉ›› በማለት ለፋክት አስተያየት ሰጥተዋል (በነገራችን ላይ ፓትርያርኩ የመዘንጋት፣ ለውሳኔ የመቸገር፣ እንቅልፍ የማብዛትና መሰል ችግሮች ስራቸውን እያስተጓጎሉባቸው እንደሆነ ይነገራል፤ ራሳቸውም ‹‹ሲጨንቀኝ እተኛለሁ፤ ስተኛ ደግሞ እረሰዋለሁ›› በማለት ችግሩን አምነው ተቀብለዋል)
በእስልምና እምነት ውስጥም የመንግስት ጣልቃ-ገብነት ከቀድሞውም መጅሊስ የባሰ እንደሆነ በርካታ መዕምናን የሚያውቁት እውነታ ነው፡፡ ይህ መጅሊስ የሚዘወረው እንደተለመደው በምክትል ፕሬዚዳንቶች ሲሆን፤ ይች አይነቷ ጨዋታ ደግሞ ህወሓት ጥርሱን የነቀለበት ስለመሆኑ ነጋሪ አያሻም፡፡ ምክትል ፕሬዚዳንቱ ሼህ ከድር ለ17 ዓመታት የትግራይ ክልል መጅሊስና የሸሪአ ፍ/ቤቱን ደርበው በመያዝ መእምናኑን ቀጥቅጠው ሲገዙ ከመቆየታቸውም በላይ ታጋይ እንደነበሩ በኩራት ለመናገር የሚደፍሩ እንደሆነ የቅርብ ሰዎቻቸው ይመሰክራሉ፡፡ በአናቱም ከታማኝ የመረጃ ምንጭ ባይረጋገጥም የመጅሊሱ ፕሬዚዳንት ሼህ ኪያር መሀመድ ከእኚሁ ‹‹ታጋይ›› ምክትላቸው ጋር በአንዳንድ ጉዳዮች መስማማት ባለመቻላቸው እና ‹‹መንግስት የሚያዘውን ሁሉ ለመስራት ለምን እንገደዳለን?›› የሚል ተቃውሞ እስከማሰማት በመድረሳቸው በቅርቡ ከኃላፊነታቸው ሊነሱ እንደሚችሉ ተወርቷል፡፡
ኢህአዴግ እና ‹‹መንፈሳዊ›› ገበያው
ግንባሩ የእምነት ተቋማትን በአብዮታዊ ዲሞክራሲ አስተሳሰብ ጠርንፎ መያዝን እንደ ዋነኛ ዓላማ አድርጎ የመንቀሳቀሱ መግፍኤን ከሶስት ጉዳዮች አንፃር በአዲስ መስመር ለመተንተን እሞክራለሁ፡-
የመጀመሪያው ቤተ-ክህነት በነገስታቶቹ ዘመን የነበራትን ፖለቲካዊ ተሰሚነት (ምንም እንኳን ራሱ ኢህአዴግም በአፋዊነት ከማውገዝ ቸል ባይልም) ለቅቡልነት መጠቀሚያ የማድረግ ፍላጎቱ ነው፡፡ በገቢር እንደታየውም በኃይል በተቆጣጠራቸውም ሆነ ካድሬዎቹ ሊደርሱባቸው በማይችሉ የገጠር ቀበሌዎች ተቀባይነት ለማግኘት ማህበራዊ አክብሮት ባላቸው ሼሆች፣ ቀሳውስት፣ ዲያቆናት… ሲቀሰቅስ ተደጋጋሚ ጊዜ ተስተውሏል፡፡ እንዲሁም የእስልምና እምነት በታሪክ ያሳለፈውን አገዛዛዊ ጭቆናንም ሆነ የደርጉን ሁሉንም ሐይማኖት ማግለልን በማጎን ለፕሮፓጋንዳ ተጠቅሞበታል (በወቅቱ የድርጅቱ አመራር አባል የነበረው አቶ ገብሩ አስራት፣ እንደ ሼሆች በመልበስና በመጠምጠም ከፍተኛ አስተዋፆ ማበርከቱን ብዙሀኑ ታጋዮች አይዘነጉትም) በዚህ ዘመንም በቤተ-እምነቶች ካድሬ-ጳጳሳትንና ካድሬ-n ሼሆችን አሰርጎ የማስገባቱ ምስጢር ይኸው ነው፡፡
በሁለተኛነት እንደምክንያት ሊጠቀስ የሚችለው የታገለለትን ዘውግ ተኮር ፖለቲካ ያለአንዳች ተግዳሮት ማሳለጥን ታሳቢ ማድረጉ ይመስለኛል፡፡ ምክንያቱም የሁሉም ሐይማኖቶች ‹‹የሰው ልጅ በሙሉ የአንድ አምላክ ፍጡሮች ናቸው›› በሚል አስተምህሮ የሚመሩ ከመሆናቸው አኳያ፣ በዘውግ ከፋፍሎ ማስተዳደርን ቀላል አያደርገውምና ነው፡፡ ስለዚህም መፍትሔው አክራሪ ብሔርተኛ ‹‹መንፈሳውያን›› በየእምነት ተቋማቱ እንዲፈለፈሉ እና ከፍተኛውን የሥልጣን እርከን መቆጣጠር እንዲችሉ በማብቃት ላይ የተመሰረተ ብቻ መሆኑን የህወሓት መሪዎች ያውቃሉ፡፡ ይህ ‹‹እውቀታቸው››ም ይመስለኛል ሀገራዊ ስሜት የሌላቸው፣ በችሎታ ማነስ እና በስነ-ምግባር ጉድለት የሚታወቁ፤ እንዲሁም በእምነቱ ተከታዮች ዘንድ ቅቡል ያልሆኑ ሰዎች ቦታውን እንዲይዙ እስከማድረግ ያደረሳቸው፡፡
የራሳቸው የስለላ መዋቅርም በጥቅምት 2 ቀን 1995 ዓ.ም ‹‹ለዋናው መ/ቤት፣ አዲስ አበባ፤ ከ-ል.ዮ፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ አቡነ ጳውሎስን ጉዳይ ይመለከታል›› በሚል ርዕስ ለደህንነቱ ዋና መስሪያ ቤት በላከው ጥናታዊ ዘገባ ላይ እውነታውን እንዲህ ሲል ገልፆታል፡- ‹‹…ለፓትርያርኩ ወዳጅነት አላቸው የሚባሉ ሊቃነ ጳጳሳት ከሦስትና አራት ብዙም ያልበለጡ ናቸው፡፡ ፓትርያርኩ ምንም ዓይነት ተቀባይነትና ከበሬታ ያጡ በመሆናቸው ህልውናቸውን የአንዳንድ መሪዎችን ስም በመጥራትና እንደማስፈራሪያ በመጠቀም ላይ የተንጠላጠለ ሆኗል››፡፡ ከዚህ ሪፖርት በኋላም እንኳ ለማስተካከል አለመሞከሩ መከራከሪያውን አምነን እንድንቀበል ያስገድደናል፡፡
አገዛዙ መንፈሳዊ ተቋማትን ጠቅልሎ ለመያዝ ለሚያደርገው እንቅስቃሴ በሶስተኛነት ሊጠቀስ የሚችለው ምክንያት፣ ምንም እንኳ ‹‹ተሳክቷል›› ሊባል ባይቻልም፤ በስነ-ምግባር መታነፅ፣ በሀገር አንድነት ማመን፣ ለሕዝብ ጥቅም መቆም፣ የትኛውንም ህገ-ወጥነት ‹ለምን› ብሎ መጠየቅና መሰል መንፈሳዊ አስተምህሮዎችን መርሁ አድርጎ የሚነሳ ትውልድ እንዳይፈጠር መከላከልን ታሳቢ በማድረግ እየሰራ ያለውን ሴራ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ ምክንያቱም የስርዓቱ ሰዎች በዚህ መልኩ የሚቀረፅ ትውልድን ዛሬ ባነበሩት አይነት የጭቆና ቀንበር ለተራዘሙ ዓመታት መግዛት ከባድ እንደሆነ ለመረዳት አይሳናቸውምና ነው፡፡ ከዚሁ ጋር አንስተን ማለፍ ያለብን ጭብጥ፤ መቃብር ከሚቆፈርለት የኢትዮጵያዊ ብሔርተኝነት ጋር የሚያያዝ ነው፤ የሐይማኖቱና የማዕከላዊ መንግስቱ የቅድመ-አብዮቱ ጋብቻ (በምንም አይነት መከራከሪያ ትክክለኛነቱን ልንሟገትለት ባንችልም)፣ ቤተ-ክርስቲያኗ ለኢትዮጵያዊ ብሔርተኝነቱ የታሪክ ብያኔ ከፍተኛ አስተዋፆ ማድረጓን አያስክደንም፡፡ ይህም ‹የሐይማኖቱን ተቋም የብሔርተኝነቱ ወካይ ሆኖ እንዲታሰብ ይገፋዋል› ብሎ ለሚያምነው ህወሓት፣ ሐይማኖቱ ተቋማዊ ነፃነት እንዳይኖረው የሚቻለውን ሁሉ ሲያደርግ፤ ሐይማኖቱን በማዳከም የብሔርተኝነት መንፈሱንም ማላላት ይቻላል ከሚል መነሾ ነው ብሎ መደምደም ተምኔታዊ አያስብልም፡፡
ገደል አፋፍ የቆመው ማሕበረ ቅዱሳን…
ስርዓቱ የሐይማኖት ተቋማትንና መንፈሳዊ መሪዎቹን ለመቆጣጠር ገፊ-ምክንያቶች ሆነውታል ብዬ ከላይ ለማብራራት የሞከርኳቸውን ሶስት ምክንያቶች ሙሉ ለሙሉ መተግበርን አስቸጋሪ ያደረገበት፣ ቀጥታ በምዕምናኑ የተመሰረቱ ማሕበራት መሆናቸውን መገመት ይቻላል፡፡ ለማስረጃም ያህል ከኦርቶዶክስ ክርስትና-ማሕበረ ቅዱሳን፤ ከእስልምና ያለፉትን ሁለት ዓመታት የእምነቱ ተከታዮች ወካይ ሆኖ የተመረጠው ኮሚቴ አባላት መንግስትንም ሆነ መጅሊሱን በመገዳደር ያደረጉትን አበርክቶ መጥቀስ ይቻላል፡፡ ይሁንና የሙስሊሙን ተወካዮች በገፍ ሰብስቦ እስር ቤት ካጎረ በኋላ፣ ከሲኖዶሱም ሆነ መሰል ማሕበራት ጠንካራ እንደሆነ የሚነገርለትን ማሕበረ ቅዱሳንን ዋነኛ ኢላማው አድርጎ ለመደፍጠጥ የቆረጠ ይመስላል፡፡ የማሕበሩ አባላት በዓለማዊ እውቀት የተራቀቁ፣ በሀገር አንድነት በፍፁም የማይደራደሩ፣ በጥቅመኝነት የማይደለሉ… የመሆናቸው ጉዳይ አገዛዙ ከኃይል አማራጭ የቀለለ መፍትሔ የለም ብሎ እንዲያምን አድርጎታል ብዬ እገምታለሁ፡፡
በርግጥ በአቶ መለስ ዜናዊ ይዘጋጅ እንደነበረ ከህልፈቱ በኋላ በተነገረለት የኢህአዴግ የንድፈ ሃሳብ መጽሔት ‹‹አዲስ ራዕይ›› ከተወሰኑ ዓመታት በፊት አብዛኛውን ጊዜ ‹‹የከሰሩ ፖለቲከኞች ‹ኢትዮጵያ የክርስቲያን ደሴት ናት፣ አንድ ሐይማኖት አንድ ሀገር› እና ‹ሙስሊሙ ማሕበረሰብ ቀደም ሲል ሲደርስበት የነበረውን በደል በማራገብና በመቀስቀስ፤ ከዚህም አልፎ ተገቢነት የሌላቸው አዳዲስ ጥያቄዎችን በማቅረብ ለማነሳሳትና ለማተረማመስ ሲሰሩ ማየት የተለመደ ሆኗል›› በማለት ከሚያቀርበው የሾላ-በድፍን ፍረጃ ዘልሎ ብዙም መንፈሳዊ ማሕበራትን በስም ጠቅሶ ሲያወግዝ አይሰማም ነበር፡፡ ዛሬ ዛሬ ግን ማንኛውንም ሐይማኖታዊ የመብት ጥያቄን ‹‹ወሃቢያም ይሁን ማሕበረ ቅዱሳን…›› በማለት ማውገዙ የተለመደ ሆኗል፡፡ ከውግዘትም ተሻግሮ ጥያቄያቸውን በሕጋዊ መንገድ ወደ አደባባይ ያወጡትን የሙስሊሙን ተወካዮች ሰብስቦ አስሯል፤ በተለያየ ጊዜ የተደረጉ ሰላማዊ ተቃውሞዎችንም በማስታከክ በበርካታ የእምነቱ ተከታዮች ላይ ግድያና ስቀየትን ጨምሮ ብዙ ግፍ በመፈፀም ጉዳዩን በጠብ-መንጃ ብቻ የሚፈታ አድርጎ ካወሳሰበው ሰነባብቷል፡፡
‹‹ቀጣዩ የኢህአዴግ ኢላማ ማሕበረ ቅዱሳን ይሆን?›› በሚል ርዕስ ከስድስት ወር በፊት በዚሁ መጽሔት ላይ ለማተት እንደሞከርኩት ሁሉ፤ ከላይ በተዘረዘሩ የፖለቲካ አጀንዳዎች እና በሚቀጥለው ዓመት የሚካሄደውን አገር አቀፍ ምርጫ በለመደው የማጭበርበር መንገድ አሸንፎ ያለኮሽታ የሥልጣን እድሜውን ለማራዘም ዓለማዊም ሆነ መንፈሳዊ ነፃ ተቋማት እንዳይኖሩ በይፋ ኢ-ሕገ መንግስታዊ ድርጊቶችን እየፈፀመ ያለው የእነ አባይ-በረከት መንግስት፣ በአሁኑ ወቅት ሙሉ ትኩረቱን ማሕበረ ቅዱሳን ላይ ማድረጉን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡
ይህንን አፈና ለማሳካትም ፓትርያርኩ አቡነ ማትያስ በፍፁም ልባቸው ከመተባበር ለአፍታም እንደማያመነቱ በርካታ ማሳያዎች አሉ፡፡
ለምሳሌ ያህልም አንዱን በአዲስ መስመር ላቅርብ፡-
ከወራት በፊት የአዲስ አበባ ሀገረ-ስብከት አስተዳደርን ወደ ዘመናዊነት ለማሻገር ሲኖዶሱ ጥናት ተደርጎ እንዲቀርብለት ውሳኔ አሳልፎ ነበር፡፡ እናም ጥናቱ ተጠናቆ ይፋ መደረጉን ተከትሎ ከአንዳንድ የደብር አስተዳዳሪዎች ብርቱ ተቃውሞ ስለገጠመው፣ በሀገረ-ስብከቱ ሥራ-አስኪያጅ አቡነ እስጢፋኖስ አማካኝነት በጠቅላይ ቤተ-ክህነት አዳራሽ ከሁሉም አድባራትና ገዳማት የተወጣጡ 2700 ሰዎች የሚሳተፉበትና አስራ አራት ቀን የሚፈጅ የውይይት ፕሮግራም ይዘጋጃል፡፡ ይሁንና ውይይቱ በተጀመረ በሁለተኛው ቀን ጠዋት ፓትርያርኩ፣ ከአቡነ እስጢፋኖስ ጋር በስልክ ከሞላ ጎደል እንደሚከተለው መወዛገባቸውን ሰምቻለሁ፡-
‹‹ጥናቱን የሚሰሩት ባለሙያዎች ናቸው ብለውኝ አልነበረም ወይ?››
‹‹አዎ! ታዲያስ ባለሙያዎች ናቸው የሰሩት፡፡››
‹‹አይደለም! የማሕበረ ቅዱሳን አባላት ናቸው፤ እርስዎ አታለውኛል!››
‹‹የጥናት ኮሚቴው አባላት በቤተ-ክርስቲያን ልጅነታቸውና በየአጥቢያው ባላቸው ተሳትፎ ተጠርተው የመጡ ሙያቸውን ‹አስራት› ያደረጉ ናቸው፡፡››
‹‹በፍፁም! ጥናቱ የማሕበረ ቅዱሳን ነው!››
‹‹ቅዱስ አባታችን ቢሆንስ? ከጠቀመን ችግሩ ምንድን ነው?››
‹‹በቃ! ውይይቱ ከመንግስት ይቋረጥ ተብሏል፡፡››
‹‹ለምን ይቋረጣል?››
‹‹የጥናቱ ተቃዋሚዎች ረብሻ ያስነሳሉና የፀጥታ ስጋት አለ፡፡››
‹‹ለምንድን ነው ረብሻ የሚያስነሱት? ከፈለጉ መጥተው መሳተፍ ይችላሉ፤ እኛ እየተወያየን አይደለም እንዴ! ተቃውሞ ያለው መጥቶ ሃሳቡን ይግለፅ እንጂ ማቋረጥ እንዴት መፍትሄ ይሆናል? ደግሞስ ሲኖዶሱ አይደለም ወይ ‹ሰነዱ ወደታች ወርዶ ይተችበት› ብሎ የወሰነው?››
‹‹የለም! ይቁም ተብሏል፤ ይቁም!››
‹‹እንግዲያውስ የከለከለው አካል ራሱ መጥቶ ይንገረን፡፡››
…የስልክ ምልልሱ ከተጠናቀቀ ከሰዓታት በኋላ አንድ ባለሥልጣን አቡነ እስጢፋኖስ ቢሮ ድረስ መጥቶ ትእዛዙን ያስተላለፈው እርሱ እንደሆነ ገልፆ ውይይቱ እንዲቋረጥ አሳሰባቸው፤ እርሳቸውም ‹‹እናቋርጣለን፤ ነገር ግን እናንተ ‹የፀጥታ ስጋት አለ› ብላችሁ በደብዳቤ ኃላፊነቱን ውሰዱ፡፡ እኛም ለካህናቱም ሆነ ለመዕምናኑ ሁኔታውን ዘርዝረን እንገልፃለን›› የሚል ምላሽ ሰጥተው ይሸኙታል፡፡ ከዚህ በኋላ ነው እንግዲህ ለጊዜው ግልፅ ባልሆነ አንድ ምክንያት መንግስት ‹‹ይቋረጥ›› የሚለውን ማስፈራሪያ ሊያነሳ የቻለው፡፡ ኩነቱ ግን ፓትርያርኩ ማሕበሩን በጥርጣሬ ማየታቸውንና አገዛዙ ለሚወስድበት ማንኛውም አይነት እርምጃ ተባባሪ መሆናቸውን የሚያሳይ ይመስለኛል፡፡
ሌላው መንግስትና ፓትርያርኩ፣ ማሕበረ ቅዱሳንን ለማፍረስ በሰምና ወርቅነት እየሰሩ መሆናቸውን የሚያመላክተው የዛሬ ሳምንት በጠቅላይ ቤተ-ክህነት የማሕበሩ ተቃዋሚዎች ያደረጉትን ውይይትና የአቋም መግለጫ ስናስተውል ነው፡፡ ለመጽሔቱ ዝግጅት ክፍል የደረሰው በድምፅ የተቀረፀ የውይይቱ ሙሉ ክፍል እንደሚያስረዳው፣ ተሰብሳቢዎቹ ማሕበሩን በተመለከተ ባወጡት የአቋም መግለጫ የሚከተሉትን ነጥቦች ዘርዝረዋል፡- ‹‹የዋነኛ አመራሮቹ የባንክ አካውንት ይመርመር፣ የማሕበሩ ሒሳብ መንግስት በሚመድበው የውጪ ኦዲተር ይመርመር፣ ቋሚና ተንቀሳቃሽ ንብረቶቹ (ከቀረጥ ነፃ ያስገባቸው ቀላልና ከባድ መኪናዎቹ ሳይቀሩ) ወደ ቤተ-ክህነት ይግቡ፣ የንግድ ተቋማቱ (ትምህርት ቤት፣ ሬስቶራንቶቹን፣ ንዋየ ቅድሳት ማምረቻና ማከፋፈያውን) ያስረክብ፣ ከምዕምናን በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የሚቀበለው አስራት እየፈረጠመበት ስለሆነ እንዳይቀበል ይከልከል፣ የግቢ ጉባኤ (በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት) እርሱ በሚቀርፀው እንዳይወሰዱ መስራት፣ ተጠሪነቱ ከዋና ሥራ-አስኪያጁ ተነስቶ፣ በሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ ስር አንዱ ንዑስ ክፍል ይሁን…›› የሚሉና የመሳሰሉት ይገኙበታል፡፡
ከዚህ ሴራ ጀርባ ፓትርያርኩና መንግስት በትብብር መቆማቸውን የሚያሳየው በተቀረፀው ድምፅ ላይ፣ የውይይቱ መሪ አዳራሹን መጠቀም የቻሉት በአቡኑ መልካም ፍቃድ እንደሆነና እርሳቸው በዛሬው ውይይት ያልተገኙት የሕዳሴው ግድብ ምክር ቤት አባል በመሆናቸው ግዮን ሆቴል ስብሰባ ስላለባቸው መሆኑን ከመግለፅም በዘለለ፤ ‹‹ቅዱስ አባታችን በዚህ የተቃውሞ ምክንያት ከሥራ የሚባረር የለም አይዟችሁ አትፍሩ ብለውናል›› በማለት ሲናገሩ መደመጣቸው ነው፡፡ በተጨማሪም ‹‹ከዚህ ግቢ አቅም ኖሮት የሚያስወጣን የለም፤ ካስወጡን ግን መንግስታችን ስለሚተባበረን (ቸር ስለሆነ) ከእርሱ ሌላ መሬት ተቀብለን የራሳችንን ቤተ-ክርስቲያን እናቋቁማለን›› እና ‹‹የኦርቶዶክስ እምነት አገልጋዮች የሚል ማሕበር እንመሰርታለን›› እስከማለት መድረሳቸው ከአገዛዙ ጋር ያላቸውን የጠበቀ ቁርኝት ያመላክታል፡፡ በነገራችን ላይ በስብሰባው እንዲሳተፉ ከተጠሩት ከመቶ ስልሳ ዘጠኙ አድባራትና ገዳማት፣ እንዲሁም ከ10 ሺህ በላይ ሠራተኞቻቸው መካከል የተገኙት የስምንት አድባራት አስተዳዳሪዎችና 150 ሠራተኞች ብቻ እንደነበሩ ከመረጃ ምንጮቼ አረጋግጫለሁ፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ በተለይም በፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር ምኒስትር ዶ/ር ሽፈራው ተክለማሪያም አዝማችነት ማሕበሩ ላይ የደቦ ዘመቻ ከተከፈተ ሰነባብቷል፡፡ በተከታታይ በ‹‹ጥናት›› ስም የሚወጡ ወረቀቶች ማሕበሩን ከአክራሪነትም አሻግረው ‹‹የግንቦት ሰባት መንፈሳዊ ክንፍ›› ሲሉ ይወነጅሉታል፡፡ በጥቅሉ የእነዚህ ‹‹ጥናት›› ተብዬዎች መደምደሚያ ‹‹ማሕበሩ የትምክተኞች ምሽግ ነው፣ አክራሪነት አለበት፣ አመራሩና የሕትመት ውጤቶቹ የፖለቲካ አዝማሚያ ይታይባቸዋል፣ በቤተ-ክርስቲያን አስተዳደር ጣልቃ ይገባል፣ ሕዝቡ በመንግስት ላይ አመኔታ እንዳይኖረው ይሰራል፣ በውጭ ፅንፈኛ የፖለቲካ ኃይሎች ይዘወራል›› የሚሉ ናቸው፡፡ የማሕበሩ የአመራር አባላት እንዲህ አይነቱን ውንጀላ በተመለከተ በተለያየ ጊዜ ከአቶ በረከት ስምኦን እስከ ዶ/ር ሽፈራው ተክለማሪያም፤ ከአዲስ አበባ የፀጥታ ኃላፊዎች እስከ ጠቅላይ ሚንስትሩ የደህንነት አማካሪ ፀጋዬ በርሄ ድረስ ያሉ ባለሥልጣናትን በቢሮአቸው ተገኝተው ውንጀላው ማስረጃ የማይቀርበበት የሀሰት እንደሆነ ቢያስረዱም መፍትሄ እንዳላገኙ ምንጮች ተናግረዋል፡፡ በግልባጩ በመንግስት ተቋማት ያሉ የፋክት መረጃ አቀባዮች፣ በግንቦት ወር ከሚካሄደው የሲኖዶሱ መደበኛ ጉባኤ በፊት፣ ከሃያ የሚበልጡ የማህበሩ አመራርን ከሽብርተኝነት ጋር በማያያዝ ለመክሰስ እና ማሕበሩንም እንደተለመደው በዶክመንተሪ ፊልም ለመወንጀል ዝግጅት መደረጉን ተናግረዋል፡፡ ከሶስት ሳምንት በፊት በአቡነ ገብርኤል ሰብሳቢነት የሚመራው የሐይማኖቶች ምክር ቤት ስብሰባውን ካጠናቀቀ በኋላ ዶ/ር ሽፈራው አቡኑን ቃል-በቃል የጠየቃቸው ጥያቄም ይህንን መረጃ የሚያጠናክር ነው፡-
‹‹በማሕበረ ቅዱሳን አመራር ውስጥ ከሃያ በላይ የተቃዋሚ ፓርቲ አባላት አሉ››
‹‹ለዚህ ምንድን ነው ማስረጃህ? አቅርበውና እስቲ እንየው?››
‹‹ሀገር ውስጥ ካሉ ፅንፈኛ ጋዜጠኞች በተጨማሪ በስደት የሚገኙና በሽብር ተግባር የተሰማሩ ጋዜጠኞች በአመራርነት አሉበት (የሁለት ሰዎችን ስም ጠቅሷል)››
‹‹እኛ እስከምናውቀው ማሕበሩ ከእንዲህ አይነት ተግባር የራቀ ነው፤ እናንተ ማስረጃ አለን ካላችሁ ደግሞ አቅርቡልንና እንየው፤ ከዚህ ውጪ ይህንን አይነት ክስ አንቀበልም፡፡››
በአናቱም ከወራት በፊት የስርዓቱ የንድፈ ሃሳብ መጽሔት የማሕበሩን ስም ሳይጠቅስ በደፈናው የወነጀለበትን እና ‹‹ለምን?›› ብለው የሚጠይቁ ጳጳሳትን በሚከተለው አገላለፅ ማሸማቀቁን ስናስታውስ የማሕበሩ ዕጣ-ፈንታ በመጨረሻዎቹ ቀናት ላይ መቆሙን ያስረግጥልናል፡፡
‹‹በኦርቶዶክስ ቤተ-ክርስቲያን ውስጥ ትርምስና ብጥብጥ ለመፍጠር፤ በኦርቶዶክሶችና ሌሎች ሐይማኖቶች መካከል ግጭት ለመቀስቀስ የሚሞክሩት የደርግና የተለያዩ ትምክህተኛ ኃይሎች ቅሪቶች ናቸው፡፡ እነዚህ የትምክህት ኃይሎችና አንዳንድ የእምነቱ አባቶች በጋራ ሐይማኖትን በፖለቲካ ዓላማ ዙሪያ መጠቀሚያ አድርገው እየሰሩ ለመሆናቸው ከ97 ምርጫ በኋላ እንዳንድ በአሜሪካ የሚገኙ ጳጳሳት ቅንጅት በጠራው ሰልፍ ላይ የሐይማኖት አባትነት ካባቸውን እንደለበሱ ከመሰለፍ አልፈው አስተባባሪ ሆነው መታየታቸው በቂ ማረጋገጫ ነው፡፡›› (አዲስ ራዕይ ሐምሌ-ነሐሴ 2005)
የሆነው ሆኖ ከፍረጃውና ከእስራቱ በተጨማሪ ማሕበሩን ለማዳከም በዋናነት በአገዛዙ የተነደፉት እቅዶች ማሕበሩ መሰረቱን የጣለበት የግቢ ጉባኤን ከመከልከልና ንብረቶቹን ከመውረስ ጋር የሚያያዙ ናቸው (ከላይ የተጠቀሰው የአቋም መግለጫም ለማሕበሩ የደም-ስር የሆኑትን እነዚህን ሁለት ጉዳዮች ትኩረት እንደሰጣቸው ልብ ይሏል)
ስቅለትን-ለተቃውሞ
ኢህአዴግ ወደ ስልጣነ-መንበሩ ከመጣ ሦስተኛ ዓመት ላይ ‹‹የአብዮታዊ ዴሞክራሲ ግቦችና ቀጣይ እርምጃዎች›› በሚል ርዕስ ለካድሬዎቹ በበተነው ድርሳን (በሟቹ አቶ መለስ ዜናዊ የተዘጋጀ ነው ተብሎ ይገመታል)፤ ይህን አሁን የተነጋገርንበትን ሐይማኖታዊ ተቋማትን በሚያቅዳቸው የስልጣን ማራዘሚያ አማራጮች ስለመጠቀም ካወሳ በኋላ ተቋማቱን ለስርዓቱ ፖሊሲዎች እንዲታመኑ ማድረጉ ዋነኛ እንደሆነ ያሰምርበታል፡፡ ይህ የማይቻል ከሆነ ደግሞ፣ እስከ ከፍተኞቹ መንፈሳዊያን መምህራን ድረስ ዘልቆ በመግባት ሐይማኖቶቹን መምራት የአብዮታዊ ዴሞክራሲ ግብ መሆን እንዳለበት ያው ሰነድ በግልፅ ቋንቋ ይናገራል፡፡ እንግዲህ ከመጅሊሱ እስከ ማሕበረ ቅዱሳን ያየነው መንግስታዊ አፈና የዚህን ሃያ ዓመት የሞላው የተፃፈ ሀሳብ መተግበርን ነው፡፡
ግና፣ ከዚህ ቀደም በተፃፈ ነውረኛ ሀሳብ ትግበራ ፊት ከሁለት አስርት በላይ ህልውናውን ለማቆየት የተጋው ማሕበረ ቅዱሳን፣ ከላይ በሚገባ በጠቀስኳቸው አሳማኝ መረጃዎች እና ተጨባጭ ሁነቶች በተከታታይ መከሰት መጨረሻው ምዕራፍ ላይ እንደደረሰ ተመልክተናል፡፡ በዚህ አስቸጋሪ ወቅት ደግሞ፤ መነሳት የሚኖርበት መሰረታዊ ጥያቄ፣ እንዴት ይህን ማሕበር ወደ ቀጣዩ ትውልድ ማሻገር ይቻላል? የሚለው ሲሆን፤ ምላሾቹም ሁለት ናቸው፡፡ የመጀመሪያው የማሕበሩ አመራሮችና አባላት እስከዚህች ቀን እያደረጉ ያለው የውስጥ ለውስጥ የእርምት እንቅስቃሴን ይመለከታል፡፡ በሐይማኖቱ ተቋማት በኩል ለዓመታት ሲሞከር የቆየው ይኸኛው አማራጭ፣ እንደ አስተዋልነው ማሕበሩን ሞት አፋፍ ላይ ከመድረስ ሊታደገው አልቻለም፡፡ ስለዚህም፣ ወደ ሁለተኛውና ዋነኛ የመፍትሔ አማራጭ መሻገር ግድ የሚል ይመስለኛል፡፡ ከዚህ ቀደም በተመሳሳይ ርዕሰ-ጉዳይ ላይ ስፅፍ ለማስረዳት እንደሞከርኩት፤ የማሕበሩ አመራሮች፣ አባላት እና ደጋፊዎች ወደ አደባባይ በመውጣት፤ ማሕበራቸውን ብቻ ሳይሆን ህልውናቸውንና ህያውነታቸውን የመሰረቱበትን ሐይማኖት ለማውደም የሚተጋውን ስርዓት በሰላማዊ አመፅ መናድ ብቸኛው የዚህ አስቸጋሪ ጊዜ መሻገሪያ መንገድ ነው፡፡ በዋናነት የተማሩ ከተሜ ወጣቶችን፣ በአለማዊም ሆነ በትምህርተ-ሐይማኖቱ የማይታሙ ዜጎችን የያዘው ይህ ማሕበር፤ ከህዝበ ሙስሊሙ ‹‹ድምፃችን ይሰማ›› የአደባባይ ተቃውሞ ስኬቶችና ሂደቶች በመማር፤ ፊቱ በተገተረው ኢህአዴግ ላይ በሕጋዊና ሰላማዊ እምቢተኝነት ከማመጽ የተሻለ አማራጭ እንደማይኖረው የሚረዳ ይመስለኛል፡፡
‹‹ችግሮች ሁሉ የየራሳቸው በጎ ገፆች አሏቸው›› እንዲሉ፤ ማሕበሩ የደረሰበት ይህ ፈታኝ ጊዜን ተከትለው የሚመጡ ሁለት ወቅቶች አሉ፡፡ የመጀመሪያው፣ በቀጣዩ ወር የሚካሄደው የስቅለት በዓል ነው፡፡ የሐይማኖቱ ተከታዮች በሙሉ በየቤተ-ክርስቲያናቱ የሚውሉበት ይህ በዓል፣ አገዛዙ እጁን ከማህበሩ ላይ እንዲያነሳ ለመጠየቅ የተመቸ ቀን ስለመሆኑ ማስታወስ አባላቱን አሳንሶ መገመት እንደማይሆን ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ ሁለተኛውና በእጅጉ የተሻለ ነው ብዬ የማስበው ጊዜ ደግሞ ቀጣዩ የ2007 ምርጫን ነው፡፡ ለየትኞቹም የህገ-መንግስቱ ሀሳቦች አልያም የሞራል ዕሴቶች የማይገዛው ኢህአዴግ፣ በሐይማኖቱ ላይም ሆነ በማሕበሩ ላይ የዘረጋውን የረከሰ እጅ እንዲያነሳ ያለው ብቸኛ አማራጭ ሕዝባዊ አመፅ መሆኑ ላይ እስከተማመንን ድረስ፣ ከዓመታዊ የንግስ በዓላት ጀምሮ ያሉ መድረኮችን በዕቅድ ለመጠቀም የዝግጅቱ ጊዜ ዛሬ ነው፡፡ ይህ አይነቱ የተቃውሞ እንቅስቃሴም፣ ካነሳነው ርዕሰ-ጉዳይ አኳያ የማሕበሩን መኖር የሚሹ ሁሉ ቀጣዩን የምርጫ ወቅት ለማስገደጃነት የመጠቀም ተሞክሮዎቻቸውን ተፈላጊው ብቃት ላይ እንደሚያደርሰው አምናለሁ፡፡ ጥቂት ሊባሉ የማይችሉ አባላቱ፣ የምርጫውን ተጨባጭ ዕድል መንግስታዊ ተቋማት በማሽመድመድ ጭምር እንዴት ስርዓቱን ወደመቃብሩ ማሻገር እንደሚያውቁ ስንገነዘብ፤ ቀሪው ጉዳይ ‹‹ሐይማኖታችሁን ተከላከሉ›› ብለው ላስተማሩት ቅዱሳን መጻሕፍትና ለሰማያዊው መንግስት የመታመን ብቻ እንደሚሆን እንረዳለን፡፡
Keine Kommentare:
Kommentar veröffentlichen