ይሄይስ አእምሮ (አዲስ አበባ)
ወቅቱ ለክርስቲያኖች የኢየሱስ ክርስቶስ የትንሣኤ በዓል ሰሞን እንደመሆኑ በዓሉ የሚመለከታቸውን አንባቢ ወገኖቼን “እንኳን ለብርሃነ ትንሣኤው [በሰላም] አደረሳችሁ” ማለትን እወዳለሁ፡፡ የደርግ ጊዜ አንድ ትዝታ አለኝ፡፡ በአብዛኛው በሀገር ወዳድ ደናቁርት የታጨቀው የደርግ መንግሥት ሠለጠንኩ ብሎ ሃይማኖተቢሱንና ሃይማኖተኝነትን ከልካዩን የሶሻሊዝም ሥርዓት ካወጀባት ጠማማ ዕለት ጀምሮ በዓል በመጣ ቁጥር በተለይም የአብዮቱ በዓል በሚከበርበት ወቅት “እንኳን ደረሳችሁ” ይል ነበር – ያ ለአገራችን ባዕድ የነበረ የአገዛዝ ሥርዓት አንዲት ፊደል ላይ እንዲያ ይጨነቅ የነበረው፣ ሰው ለበዓሉ የደረሰው በራሱ እንጂ በፈጣሪ እንዳልሆነ ለማጠየቅ ነበር፤ የሥርዓቱ አቀንቃኞች በአብዛኛውና በግልጽ ይዞታቸው ሶሻሊስትና ኮሚኒስት እንጂ የሃይማኖት ሰዎች አልነበሩም – አንዳንዶች አምልኮታቸውን በኅቡዕ ያከናውኑ እንደነበርና ልጆቻቸውን ሣይቀር በድብቅ ክርስትና ያስነሱ እንደነበር አስታውሳለሁ፡፡ በመሠረቱ አንድ ሰው ምንም ዓይነት እምነት ላይከተል ይችላል፡፡ መብቱም ይመስለኛል፡፡ ነገር ግን ሃይማኖት አልባነትን በግድ መንግሥታዊ ሥርዓት ውስጥ በማጫፈር በእምነትና በሃይማኖት ጸንቶ የኖረን ሕዝብ በአንዴ እግዜርን ወይም አላህን ወይም የምታመልከውን ሌላ መንፈሣዊ አካልን ክደህ ኮሚኒስት ሁን ማለት የደርግን ብልህነት ሣይሆን ጅልነት የሚያሣይ ነበር – ሠለጠነች ቢሏት ጊዜ የባሏን መጽሐፍ ያጠበችውን ሴት ዓይነት ጅልነት፡፡ መጨረሻው ባለማማሩ ይከተለው የነበረውንም የአካሄድ ሥርዓት አይረቤነት በእግረ መንገድ መረዳት አይከብድም፡፡ እንዲያው ትዝ ብሎኝ ነው፡፡
ርዕሴን በእንግሊዝኛ ብጽፈው ኖሮ “The Age of Terrorists, Extremists and Deviants” በሚል እንዲነበብ አደርገው ነበር፡፡ ያለንበትን ዘመን ከየአቅጣጫው ስንቃኘው ጥቂት የማይባሉ አክራሪዎች፣ ተስፈንጣሪዎችና አሸባሪዎች ዓለማችንን እያተረማመሱ እንደሚገኙ መገንዘብ አያስቸግርም፡፡ ሌላውን ዓለም ለአሁኑ እንተወውና ወዳገራችን ተስፈንጣሪዎችና ምናምንቴዎች እንመለስ፡፡ በነሱ ነውና መቅኖ አጥተን የቀረነው – “ትንቢትሰ ይቀድሞ ለነገር” የምትለዋን ሐረግ እንድታስታውሱልኝ ግን ልማጠን፡፡
ትናንት አንድ ወዳጄ ቤቴ መጥቶ በላፕቶፑ ከዩትዩብ ያወረዳቸውን አንዳንድ ድንቃድንቅ ቃለ መጠይቆችና ልዩ ልዩ ዝግጅቶች አስኮመኮመኝ፡፡ ሁለቱን ተስፈንጣሪዎችና ጠብ ጫሪዎች የተመለከትኩት በዚያን ጊዜ ነው፡፡ አንደኛው ተስፈንጣሪ
መምህር ገብረ ኪዳን ደስታ ይባላል፡፡ እኔን የታሪክ ተመራማሪ ያድርገኝና የታሪክ ተመራማሪ እንደሆነ ተነግሮለታል፡፡ አፄ ቴዎድሮስን እንዴት አድርጎ እንደሚስላቸው ብታዩ ትደመማላችሁ፡፡ አበሻቅጦ፣ አበሻቅጦ ነው የለቀቃቸው፡፡ ሲናገር ደግሞ ታሪክን እንደሚተርክ ሣይሆን በስሜት እየተወራጨና ክፉኛ እየተቆጣ እዚያው እቦታው ላይ ያለ ያህል ሆኖ ነው፡፡ የታሪክ ተመራማሪና ተንታኝ – በኔ ጥራዝ ነጠቅ ግንዛቤ – ትንታኔውንና ሀተታውን ማቅረብ ያለበት በጥላቻና በበቀል ስሜት እየተንዘረዘረ ሣይሆን የሆነውን ነገር እንዳለ በተረጋጋና አድልዖ በሌለበት ሁኔታ ነው – ታሪክ ነዋ! የዛሬ ሣይሆን የዱሮ ዘመን ድርጊት ነው፡፡ ዛር ከፈረስ የመሆን ወገንተኝነት ለታሪክ ተመራማሪ የሚፈቀድ አይመስለኝም፡፡ ይህ የታሪክ ተመራማሪ ግን አንድ ቦታ ሲናገር እንደሰማሁት አንሻፍፌም ቢሆን እጠቅሳለሁ፤ “ሀፄ ዮሐንስ ምኒልክን ቢያስሩት ኖሮ ጥሩ ነበር፡፡ መታሰር ነበረበት፡፡ ሀገር ከሃዲና ሻጭ ስለነበረ የሀፄ ዮሐንስ መኳንንትና መሣፍንት ‹ይህን ሰው ነገር ሳያመጣ እንሰረው› ሲሉ ሀፄው በምሕረት ማለፋቸውና ‹መኳንንቴ ሊያስሩህ ይፈልጋሉና አምልጣቸው› ብለው የሸዋን ንጉሥ እንዲያመልጥ ማድረጋቸው ትክክል አልነበረም፡፡…” እኔ የታሪክ ተማሪ አይደለሁም፡፡ ባልሆንም ግን እንዲህ ያለ ጭራሽ ወደ አንድ ወገን ያጋደለ የታሪክ ትንተናና ቅጥ ያጣ ዘረኝነት ስመለከት የምናደድና ምሁር ተብዬውን የምቃወም መሆኔን መግለጽ እፈልጋለሁ፡፡ ፕሮፌሰር ባሕሩ ዘውዴን የተቸበትንም መንገድ ስመለከት አዝኛለሁ፡፡ ባህሩ ዘውዴ ኢትዮጵያ በአጸደ ሕይወት ካሏት ብርቅ የታሪክ ተመራማሪዎች አንዱ መሆኑን አውቃለሁ፡፡ ሁሉም ነገር ለከት ሊኖረው ይገባል፡፡
ዐፄ ምኒልክንና ዐፄ ቴዎድሮስን ለማቋሸሽና በሕዝብ እንዲጠሉ ለማድረግ ይህን ያህል ዘመቻ ማድረግ ትርፉ ለጊዜው ትዝብት ብቻ ቢሆንም እውነቱ ባለበት ይኖራልና የማስተባበሉን ዋና ኃላፊነት ለባለሙያዎቹ መተውን መርጫለሁ – አልተከታተልኩ ሆኖ እንጂ በጊዜው መልስ ተሰጥቶበትም ሊሆን ይችላል፡፡ ሰውዬው ግን በግብዝነቱ አሳዘነኝ፡፡ ደግሞም ሁለት ፀጉር ያበቀለ እንደኔው ትልቅ ሰው ይመስላል፡፡ ለምን ይህን ያህል ርቀት ተጉዞ ራሱን ትዝብት ውስጥ ማስገባት እንደፈለገ አልገባኝም – የእውነት አንጻራዊነት ደግሞ አስደነቀኝ፤ እውነት ሺህ ጊዜ አንጻራዊ ትሁን እንጂ ደግሞ ይህ ሰው ይህን ያህል ማፈንገጡ በሰዎች ተፈጥሮ እንድገረም አስገድዶኛል፡፡ ነገሥታቱን በዘራቸው ምክንያትም ይሁን በሌላ አይጥላቸው ወይም በግድ ይውደዳቸው ማለቴ አይደለም፤ ነገሥታቱ ምንም ጥፋት የሌለባቸው ምሉዕ በኩልሄ ናቸው ማለቴም አይደለም – ሰዎች እንደመሆናቸው እንደማንኛችንም ተራ ዜጎች ያጠፋሉ፤ ያለማሉም፡፡(በነገራችን ላይ ስለትግራይ ነገሥታትም ሆነ መሣፍንት እንዲሁም ስለ ዳግማይ ወያኔ የአስተዳደር በደል አንድም ነገር ትንፍሽ አላለም፤ ይህ ደግሞ ፍጹማዊ አድልዖና ወገናዊነትን ያሳያል፤ ምራቅ ከዋጠና ፈሪሃ እግዚአብሔር ካለው ጨዋ የትግራይ ሕዝብ የተገኘ የታሪክ ተመራማሪ እንዲህ ያለ ጭፍን አስተያየት ይሰነዝራል ተብሎ በጭራሽ አይጠበቅም – በኔ ግምት ንግግሩ ደመ-ሞቃታዊ ግልብ አስተያየት እንጂ በምርምር የተደገፈ እውነተኛ ታሪክ ነው ማለትም ያስቸግራል)፡፡
እኔ እምለው ታዲያ ጥላቻችንንም ይሁን ውዴታችንን የምንገልጽበት መንገድ አግባብ ይኑረው ነው ፡፡ ስንወድ፣ ስንወድ ሰዎች ባልዋሉበት ጦር ሜዳ ሺዎችን እንደገደሉና እንደማረኩ እያስመሰልን የምንኳሽ ፣ ስንጠላ ስንጠላ ደግሞ ጥቁሩን ነጭ፣ ነጩን ጥቁር እያደረግን ጥላሸት የምንቀባ ከሆነ አመክንዮታዊ ተፈጥሯችንን ገደል ከተትነው ማለት ነው፤ እንዲህ ስናደርግ ታሪክ ሣይሆን ኩሸትና ምናባዊ ገድል እየጻፍን ነው – እንደዚህ ያለ ነገር መጻፍ ወይ መናገር ካማረን ደግሞ በታሪክ ትምህርት አሳብበን ሣይሆን በልቦለድ ውስጥ ስሜታችንን መግለጽ እንችላለንና ወደዚያ መግባት ነው – የሰውዬው አካሄድ አህያን ተገን አድርጎ ጅብን እንደመውጋት ነው – ትልቅ የስብዕና ኪሣራ፡፡ ሰው የተባለ ፍጡር ደግሞ እንዲህ እንዲሆን አይጠበቅበትም፡፡ እንስሳ ብንሆንም ማሰብና ማመዛዘን የምንችል የሌሎች እንስሳት አለቃዎች በመሆናችን የማስተዋል ጥበብን እስከዚህን ድረስ በወረደ ሁኔታ ልንነጠቅ አይገባም፡፡ የዘረኝነትን ጭምብል አውልቀን፣ የሆድ አምላኪነትን ምኩራብ አፍርሰን፣ የጥላቻን ግምብ ንደን በሃቅ መፍረድ ካልቻልን ሰው መሆናችን ይቀርና በአንዲት አጥንት ሣቢያ የሰገሌን ጦርነት እንደሚያስታውሱን ውሾች እንሆናለን፡፡ ይህ ደግሞ ከንቱነትና እንደነቢዩ ሰሎሞን አነጋገር ንፋስንም እንደመከተል ያለ ሞኝነት ነው፡፡ ለምኑ ብለን? ነገ ጧት ሁሉም እርግፍ ብሎ ለሚቀረው? አቅል ጀባ መምህር ገብረ ኪዳን! ከጥቂት ጊዜ በኋላ ትግሬና አማራ ይቅርና የሰው ዘር በአጠቃላይ የሚበጠርበትና የሚበራይበት ዘመን ይመጣል፡፡ ያኔ እውነት የምትነግሥበት፣ ሀሰት የምትዋረድበት አዲስ ዘመን ይብታል፡፡ ያኔ ላለማፈር አሁን ትንሽ ስንቅ መያዝ ይገባናል፡፡ ጊዜ የሰጠው ቅል ድንጋይ መስበሩን ካላቆመ ድንጋዩም ቅል ለመሆን እንደሚመኝ ማሰብ ተገቢ ነው፡፡ ከኅሊና መታወር አምላክ ይሠውረን!
ታሪክ ሲጻፍ በስማ በለው ሊሆን አይገባም፡፡ የስማ በለው ታሪክ አፈ-ታሪክ(ሌጄንድ) እንጂ እውናዊ ታሪክ ሊሆን አይችልም፡፡ ታሪኩን ወደድነውም ጠላነውም እኛ ግን እንዳለ ማስተላለፍ ይኖርብናል፡፡ አንድ ሃኪም ጠላቱ ታሞ ቢመጣ በመርፌ ወይ በከኒና ሊገድለው እንደማይገባ ሁሉ(በሙያዊ ሥነ ምግባር ኮዱ መሠረት አስቀድሞ መሃላም ገብቷልና) አንድ የታሪክ ቅንጫቢም እኛ ጋ ሲደርስ ስለማንፈልገው ብቻ አንሻፈን መናገሩ ወይም መጻፉ እኛን ለትዝብት ከሚዳርገን ውጪ ታሪኩን አንሰርዘውም፤ እውነት አትሰረዝምና፡፡ ስለሆነም ያ አፈንጋጭ የታሪክ ሰው ራሱን እንዲመረምር በዚህ አጋጣሚ ልጠቁመው እወዳለሁ፤ የጎመን ጥጋብ ያልፋል፤ የጉሽ ጠላ ስካርም ይበርዳል፡፡ ለነገሩ እንኳንስ ብዙም የሚያስደስት ነገር የሌለው የኢትዮጵያ ታሪክ ይቅርና ሰማይና ምድርም ያልፋሉ – ሊያውም ይህም ሊሆን የቀረው ጊዜ ከአንድና ሁለት ሐሙሶች የሚዘል አይመስለኝም፡፡ ጤናማ አተያይ ለሁላችን እንዲያድለን ፈጣሪን እለምናለሁ፡፡ ደግሞስ አንዳችን አንዳችንን አበሻቅጠን የት እንደርሳለን፡፡ የሁላችንም ታሪክ በየራሱ የቆመ ሣይን እርስ በርሱ የተጋመደ ነው፡፡ ትግሬ ውስጥ አማራ አለ፤ አማራ ውስጥ ትግሬና ኦሮሞ ሌላውም አለ፡፡ ተማርን የምንል ወገኖች ግን አይፈጥሩ ጠብና ቅራኔ እየፈጠርን ደጉን ባላገር ባናምሰው ይሻላል፡፡ ማወቃችንን በቅጡ እናድርገው፡፡ ልሂቅነት ለዕልቂት ከበሮ ጉሰማ ሣሆን ለዕርቅና ለዕድገት አቅጣጫ ትለማ እናውለው፡፡ ኃላችንን ወደ ማፈርስ ሣይሆን ወደመግናበት አናዙረው፡፡ ጥላቻን መዝራት ይብቃን፡፡ ወደፍቅርና መተሳሰብ አምባ እንውጣና ሌሎች ያበላሹትን እኛ እናቃና፡፡ በተበላሸና በተሰባበረ መንገድ እየተጓዝን ቁስላችን ይበልጥ እያመረቀዘ የሚሄድበትን ሥልት ከመንደፍ ይልቅ በምንፈወስበት ዘዴ ላይ ጊዜና መላ አቅማችንን እናፍስስ፡፡…
ሌላው አፈንጋጭ ወይም ተስፈንጣሪ ደግሞ ያ የሰንበት ጽንስ ተስፋየ ገብረ“ባብ” የሚባለው ነው፡፡ ይህን ሰው አደብ የሚያስገዛ ጠፍቶ ይሄውና ሽብልቁን እየቀበቀበብን ከኛም አንዳንዶቻችን የሚቀበቀብብንን ሽብልቅ ባለማጤን እያጨበጨብንለት መቃቃርንና ግጭትን ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ እየነዛ ይገኛል፡፡ ሼክስፒር እንደሚለው – እጠቅሳለሁ – “To do a great right do a little wrong” እንደሚለው ይህን የእባብ ልጅና አለምነው መኮንን የተባለውን የዲያብሎስ ውላጅ በአንዳች ጥበብ የሚያስወግድ ኃይል ቢኖር በኔ በኩል ድጋፌን እንደማልነፍግ እገልጻለሁ – የንስሃ ዕድሜ እንዳገኝ ከመጸለይ ጭምር፡፡ ሰይጣንን ማስወገድ ወይም ቢያንስ አደብ ማስገዛት ከኃጢኣት አይቆጠርም ባይ ነኝ፡፡ ጠላትን መውደድ ጥሩ ነው፡፡ ነገር ግን ስትወደው የሚጠላህን መሠሪ ጠላት ከይሁዳ እንጂ ከተራ ጠላት አትመድበውም፡፡ እነዚህን መሰል ፀረ-ሰውና ፀረ-እግዚአብሔር ግለሰቦች ሰባት ጊዜ ሰባ ብቻም ሣይሆን ሰባ ጊዜ ሰባት መቶ ያህልም ይቅር ቢባሉ ተፈጥሯዊ የፀላኤ-ሠናያት ባሕርያቸውን ሊያቆሙ አይችሉም – ተፈጥሮን ደግሞ ተመክሮ አይመልሰውም፡፡ ይሁዳ ምሕረትን እንደማያገኝ ክርስቶስ በአንደበቱ ተናግሯል – “የሰውን ልጅ በመሳም አሳልፎ የሚሰጥ የወፍጮ መጅ ባንገቱ ታስሮ ወደ ጥልቁ ባህር ቢወረወር ይሻለዋል” በሚል ልዩ አንደበታዊ ማኅተም፡፡ ስለሆነም ተስፋዬ ገብረባብና ይሁዳ አንድ ናቸውና ሞት ቢያንሳቸው እንጂ አያንሳቸውም የሚል እምነት አለኝ፡፡ ጨካኝ ሆኜ ግን እንዳይመስላችሁ፡፡ በፍጹም፡፡ ያጨከነኝ ሥራቸው ነው፡፡
ተስፋየን ይሁዳ ያልኩበት ምክንያት የበላበትን ወጪት በመስበሩና ያደገባቸውን ሁለት ማኅበረሰቦች ለማጋጨት ከራሱ ይሁን ከሌላ ተቀብሎ የተሸከመውን ታሪካዊ ኃላፊነት ሳይታክትና ሳይሰለች እየተወጣ የሚገኝ የእፉኝት ልጅ በመሆኑ ነው፡፡ ይህ ሰው ኢትዮጵያ ውስጥ ተወልዶ የእምዬ ኢትዮጵያን ጡቶች እየጠባ ቢያድግም አሁን እንደ ቀትር እባብ እየተቅነዘነዘ የሚያደርገውን ስንታዘብ ሰውዬው በማንነት ኪሣራ የተዘፈቀና ያን ለመርሳት በሚያደርገው ጥረትም የሚሠራውን እንደማያውቅ ሰው ትልቅ ጥፋት እያደረሰ መሆኑን ነው፡፡ በውነቱ ሰውዬው በራሱ አንደበት እንዳረጋገጠውና በድረገፆች በተጋለጠው መታወቂያውም እንደተመለከትነው ኢትዮጵያዊ አይደለም፡፡ ኢትዮጵያዊ ካልሆነ ታዲያ ስለኢትዮጵያ ይህን ያህል አብዝቶ መጨነቁ ለምን ይሆን ብሎ መጠየቅ አግባብ ነው፡፡ እኔ ለምሣሌ ስለ ኬንያና ታንዛንያ ከሀገሬ በላይ እንቅልፍ አጥቼ አልጨነቅም፡፡ “የራሷ አርሮባት የሰው ታማስል” እንዲሉ ካልሆነ በስተቀር ተስፋየ ሀገሬ ናት የሚላት የቀድሞዋ የኛም ሀገር ኤርትራ ብዙ የልማትና የብልጽግና ሥራ እንዲሠሩላት እጆቿን ዘርግታ ልጆቿን እየተማጸነች በምትገኝበት ወቅት ይህ ሰው ስለኢትዮጵያ እንዲህ መባዘኑ ይገርመኛል፡፡ ይህ ሁሉ መቸገሩ አለነገር እንዳልሆነ ደግሞ ለብዙዎቻችን የተሠወረ አይደለም፡፡ አንድ ሰው እንቅልፍ አጥቶ ማደር ያለበት ስለራሱ ጉዳይ መሆን አለበት፤ ከዚያ ውጪ ግን ያልበላውን እንደማከክ ነው፡፡ የሚያስደንቀው ደግሞ ህ ሰው እየባሰበት እንጂ እየቀነሰለት ሲሄድ አለመታየቱና ደህና የሚባሉ ኢትዮጵያውያን ሣይቀሩ የጥፋቱ ተባባሪዎች እየሆኑ መምጣታቸው ነው፡፡ “ዘይገርም ሻሸመኔ ትብስ ኮፈኔ” ማለት ይሄኔ ነው፡፡ ዘመነ ግርምቢጥ!
በትናንትናው የጓደኛየ የቪዲዮ ግብዣ ኦ.ኤም.ኤን(ኦሮሞ ሚዲያ ኔትወርክ) የተባለ የሚዲያ አውታር ያሠራጨውን አንድ ዝግጅት ተመለከትኩ፡፡ የቀድሞ ወዳጄ በፈቃዱ ሞረዳ ጠያቂ ጋዜጠኛ፣ ተስፋየ ገብረባብ ተጠያቂ እንግዳ ሆነው ነበር “እንግዳ” በሚል ፕሮግራማቸው ይህን ጉደኛ ውሉደ ዲያብሎስ ያሳዩን፡፡ በፈቃዱን ሳውቀው ኢትዮጵያዊ ሆኖ ነው፡፡ አሁን ግን ያነሰብኝ መሰለኝ – ግምቴ ትክክል ከሆነ ደግሞ በጣም ነው የማዝነውና የምጨነቀው – በተጣባን ሾተላይ እተክዛለሁ፡፡ በቃለ ምልልሱ እንደተረዳሁት ተስፋየና በፈቃዱ ቀደም ሲል ዐይጥና ድመት ነበሩ – ያ ጥሩ አልነበረም፡፡ ያስታረቃቸው ነገር ሲታይ በፈቃዱ በተወሰኑ ሰዎች ግፊት ምክንያት ዘረኛ እንዲሆን መገደዱን “የሚያበሥር” ግጥም በኢትዮጵያ ዛሬ ድረገፅ ተስፋየ አንብቦ የምኞቱን ሥኬትና የዓላማ መመሳሰል ካስተዋለ በኋላ ሁሉንም ቂሙን/ቁርሾውን እርግፍ አድርጎ በመተው በፈቃዱን ሊወደው እንደቻለ ነው፡፡ ይህ ፍሩዳዊ የምላስ ወለምታ – ኧረ ግልጽ ነው የምን ወለምታ – የሚያሳየን ተስፋየ የሚፈልገው ኢትዮጵያ ውስጥ ሁሉም ዜጋ እየተነሣ በየፈፋውና በየጢሻው በመውረድ ፍጹም ዘረኛና አንዱ ከአንዱ የማይስማማ ሌባና ፖሊስ እንዲሆን መሻቱን ለዚያ ዓላማ ሥኬትም የማይፈነቅለው ድንጋይ አለመኖሩን ነው፡፡ ይህ “የሰው ሀገር ሰው” የራሱን የማንነት ኪሣራ ችግር ሳያስወግድ በበጎች መሀል እንደገባ ተኩላ ኢትዮጵያን ለመበታተን የሚጥሩ ታሪካዊ ጠላቶችን እያገለገለ የሚገኝ ሁለት አፍ እንዳለው ሠይፍና ጎራዴ ሊታይ የሚገባው መሠሪ ጠላት ነው፡፡ ይህ ዓይነቱ አደገኛ ሰው በእንጭጩ ካልተቀጨ – አሁንና ዛሬ ‹እንጭጭ› የሚልን ቃል መጠቀም ከቻልኩ – የዞረ ድምሩ ከባድና በቀላሉም የማይፈታ ነው፡፡
ስለተስፋየ አንዲት ነገር በምሳሌ ልናገር፡፡ እንደዛሬው ሣይሆን በዱሮው ዘመን ጦጣን የሰው ልጅ ይይዛታል፡፡ ከሰው ጋር የከረመችዋን ጦጣ ዘመዶቿ ጋር እንድትቀላቀል ወደ ጫካ ቢሰዷት እርሷ ዕውቀቷ አነስተኛና ጦጥኛ በመሆኑ ልትቀላቀል ትሄዳለች፡፡ ነገር ግን በዚያን ደግ ዘመን ማኅበረጦጣ ያቺን ከሰው አምልጣ ወይም ነፃነቷን በሰዎች ይሁንታ አግኝታ የመጣች ጦጣ በቡጢና በክርን እየደለቀ ያባርራታል እንጂ አያስጠጋትም፡፡ ምክንያቱም ሰው ሰው ትሸታቸዋለችና የነሱ ቅርጽ ቢኖራትም በጠረኗ ምክንያት አያስጠጓትም፡፡ የሁለት አገር ሰው ፣ የሁለት አገር ፍጡር መሆን ዕዳ እንግዲህ እንደዚህ ነው – አጣምሞ እንዳይፈጥር ከመጸለይ ውጪ ምንም ማድረግ አይቻልም፡፡ሁሉም በጥርጣሬ ዐይን ስለሚመለከተው የማንነት ቀውስ ውስጥ ይዘፈቅና ከሚደርስበት ሥነ ልቦናዊ ችግር የተነሣ የወንጀለኝነትን ባሕርይ በቀላሉ ይላበሳል፡፡ ከዚያም የራሱ ጤናማ ኅሊናና ቀና አስተሳሰብ ስለማይኖረው እንደጠፍ አህያ ያገኘው ሁሉ የፈለገውን ይጭነዋል፤ ወደፈለገውም ይልከዋል፡፡
ሲላላክም መጠነኛ መቁሽሽ ስለሚሰጠው ስለሚያገኘው ድርጎ እንጂ ስለሚሠራው ዕኩይ ተግባር ቅንጣት አይጨነቅም – የሞራልና የሃይማኖት ዕሤቶችም ስለሌሉት ሕይወቱ በብዙ መልክ የተሰነካከለ ነው፤ በመጠጥ የሚናውዝ፣ በሴሰኝነት ካገኘው ጋር የሚከንፍ፣ በቃላባይነት ሁሉንም የሚያስቄም ከንቱ ዜጋ ሆኖ ይቀራል፡፡ ይህ ዓይነት ሰው እንደነዱሽ ነው – ልክ እንደሮቦት፡፡ ይህን መሰል ሰው ወደኅሊናው በቀላሉ አይመለስም፡፡ ቢመለስም ምናልባት እንደይሁዳ ራሱን ይገድል ይሆናል እንጂ በንስሃ ታጥቦና ተጸጽቶ ጥሩ ሰው የመሆን ዕድሉ በዜሮና በአንድ የመቶኛ ስሌት ውስጥ የሚገኝ ነው፡፡ ከዚህ ይሠውር ውድ ወገኖቼ፡፡ በሀገራችን ስንትና ስንት እንደነዱሽ ቀፎ ራስ ሞልቷል መሰላችሁ! ሆዱ ከሞላ እናቱንም፣ሚስቱንም፣ ልጆቹንም ባወጡ የሚሸጥ ገነት ዘውዴንና አለምነው -ገዱ – ልደቱ አያሌውን የመሰለ ብኩን ዜጋ ሞልቷል፡፡ እውነቴን ነው የምላችሁ እነዚህን “ሰዎች” ሳስብ ሰው ሆኜ መፈጠሬን እጸየፋለሁ፡፡ የጠራ ድህነት ወርቅ አይደለም እንዴ እባካችሁ!
ተስፋየ አቅሉን ስቶ የሚራወጠው ኢትዮጵያውያንን ለማደባደብ መሆኑ የታወቀ ነው፡፡ የነበፈቃዱ ዓላማ ግን ብዙም አልገባኝም፡፡ “ያልወለድኩት ልጅ ቢለኝ አባባ፣ አፌን አለው ዳባ ዳባ” ይባላል፡፡ ዛሬ ከመሬት ተነስቶ ተስፋየን “ኦሮሞ ነህ” ማለት መንስኤው ግልጽ ቢሆንም ውጤቱን ግን ማጤን ያስፈልግ ነበር፡፡ ተስፋዬ ለዓላማው ሥኬት ካዋጣው ልክ እንደወያኔ የማይሆነውና የማያደርገው ነገር የለም፡፡ የማርስና የቬኑስ ዜጋ ነህ ቢሉትም በደስታ ይቀበላል – እንዲህ ዓይነቱ ነገር በጣም ይስማማዋል(የቬኑስ ዜጋ እንኳን አሁንም ነው – ቬነስ ከወሲብ ጋር እንደምትገናኝ አስቡልኝ፤ ቬኔሪያል ዲዚዝ … ምናምን ከዚያ የመጣ ነው ይባላል፤ የሼክስፒርን ምናባዊ ፍጡር ሸፍጠኛውን ሻይሎክም (በቬኑሱ ነጋዴ ተውኔት) አስታውሱ)፡፡ ይህ ዓይነቱ “ማዕረግ” ለስንኩል ዓላማው ትልቅ እገዛ ያደርግለታል፡፡ ብዙም ባልተማረው ማኅበረሰባችን ውስጥ እንደዚህ ዓይነት የጭቡ ሥራ ምን ዓይነት ዳፋ ሊያስከትል እንደሚችል የቲያትሩ ደራሲያን ሊያስቡበት በተገባ ነበር፡፡ የሚያጣላ አላጣንም፡፡ የብሔር ማንነት ካባ ሳይደረብለት የሚያቆራቁሰን ሞልቶ ሳለ ይህን አሸባሪ ሰው – ይህን ተስፈንጣሪ ወጪት ሰባሪ – ይህን የአእምሮ በሽተኛ ሰው “ኦሮሞ ነህ” ማለት ትርጉምም ስሜትም የሚሰጥ አይደለም፡፡ ቀን ሲያልፍ የሚያስተዛዝብና እሳት የማያጫጭር፣ የማያቀባብርም አጉል ድርጊት መሥራት ሞኝነት ነው፡፡
በፈቃዱ ሞረዳም ትልቅ ሰው ነው፡፡ በጣም የማከብረውና በጦማር ጋዜጣው ስለእናት ሀገሩ ኢትዮጵያ ብዙ የደከመ ሰው ነው፡፡ ጉድና ጅራት እንዲሉ ሆኖ አሁን በማንኛውም ምክንያት ይሁን ወደታች ወርዶ ፈፋ ውስጥ ተወሽቆ ከሆነ ከምር አዝናለሁ፡፡ “የት ይደርሳል የተባለ ጥጃ ሉካንዳ ደጅ ታዬ” እንዲሉ ካልሆነ በስተቀር ወደላይ መሄድ ቢያቅት እንኳን ባሉበት መቆየትም ትልቅ ጠጋ ነው፡፡ ሰዎች ሰዎችን ለማሳሳት ሆን ብለውም ሆነ ሳያውቁ አንዳንድ ነገር ሊያደርጉ ይችላሉ፡፡ እነሱን በጭፍን ከተከተልን ገደል እንገባለን፡፡ እርጥቡን ከደረቅ እየለየን በአስተውሎት ከተራመድን ግን ጊዜ ይፍጅ እንጂ የተሳሳተን ለማረምና ወደ ፍጹም ሰውነት ለመቅረብ ይቻለናል – ፍጹም መሆን በሒሣባዊ ትወራ ይጠጌ አይነኬ ቢሆንም፡፡ ታጥቦ ጭቃ መሆን በታሪክም ይሁን በትውልድ ራስን ዝቅ ያደርጋል፡፡ የበላሁትን ቁርስ ያህል የማውቀው ፍቄ እንዲህ ሆኖ ከሆነ ለማመን ብቸገርም እንደሚመለስ ግን ተስፋ አለኝ፡፡ እርግጥ ነው – ተስፋ መቁረጥ ብዙ ዕዳ ውስጥ እንደሚከት አላጣውም – ቢሆንም ፍቄን በዚህ ጠርጥሬው አላውቅም፡፡ በሥነ ግጥሙ እንደተረዳሁት “በነሱ ግፊት እኔም ዘሬን አሽትቼ ወደዘሬ ተቀላቀልኩ” የሚለው አስተሳሰብ ደግሞ አይሠራም፡፡ እንደተስፋየ አጠራር ኢትዮ-አማሮች የሚባሉት “አክራሪዎች” የፍቄን ጽኑ አቋም አናግተውት ከሆነ ስህተቱ አሁንም ከፍቄ ራስ አይወርድም፤ እንዲያ ከሆነ ዱሮም ፍቄ ባላመነበት ኢትዮጵያዊነት ይዳክር ነበር ማለት ነውና፡፡ ለመሆኑ እነሱ እነማን ናቸው? ስንትስ ናቸው? እነሱ ዘረኛ ቢሆኑ እኛስ ስህተትን በስህተት ልናስተካክል ይገባናል ወይ? የምወደው ፍቄ ያስብበት፡፡ ይህን የምለው በተመለከትኩት ቃለ ምልልስ በግልጽ ሣይሆን በ“ሦስተኛው ዐይኔ” አማካይነት የተገነዘብኩት አንዳች ነገር ስላለኝ ነው፡፡ ግጥሚቱ ቀላል መልእክት አይደለም የታቀፈችው፡፡ “ዘረኛ ሆነው ዘረኛ አደረጉኝ” ትላለችና፡፡
የሁለቱ ሰዎች መታረቅ ደስ ይለኛል፡፡ የታረቁት በፀረ-ኢትዮጵያዊነት የዓላማ ቁርኝት ከሆነ ግን ዕርቃቸው አሳሳቢ ነው፡፡ እንደ እውነቱ ከሆነ የሀገራችን ችግር የዘር አይደለም፡፡ ችግራችን የዴሞክራሲ ዕጦት ነው፤ የመልካም አስተዳደር ዕጦት ነው፤ የተማረና የተመራመረ ዜጋ ሥልጣኑን ያለመያዝና ሕዝባዊ ወደሆነ የዕድገትና ብልጽና አቅጣጫ ያለመግባት ችግር ነው ለዘመናት የተጠናወተን፤ የማይምነት መንሠራፋት ነው አበሳችን፤ የሆዳምነት መንገሥ ነው ችግራችን፤ የራስ ወዳድነት መንፈስ የሃይማኖት ያህል መስፋፋት ነው ራስ ምታታችን፤ በሙስናና በጉቦ መበስበስ ነው ናላ የሚያዞር ማኅበራዊ ነቀርሳችን፡፡ ዘረኝነቱ ጎልቶ የታየው ካለፉት 24 ዓመታት ወዲህ እንጂ ቀደም ሲል ይህን ያህል አሳሳቢ ችግር አልነበረም፡፡ ያገኛትን ትንሽ ቀዳዳ ተጠቅሞ ጎጃሜ ጎጃሜን ዌም ጎንደሬ ጎንደሬን ቢቀጥር፣ ሐረርም ሐረሬን ወለጋም ጊምቢንና ነቀምቴን ይስብ ነበር፡፡ ሁሉም በየፊናው የፈለገውንና የመሰለውን ያደርግ ነበር እንጂ አንድ ዘውግ ተለይቶ የሚወቀስበት ሁኔታ ሊኖር አይችልም፡፡ ይልቁንስ ፈታ እንድትሉ አንድ ቀልድ ቢጠየ ላስታውሳችሁ ከፈለጋችሁ፡- አንድ ኦሮምኛ ተናጋሪ ጄኔራል ወታደር ለመሆን ያመለከቱ ተመዝጋቢ ወጣቶችን በተርታ አሰልፈው የቅጥር ፎርም ለማስሞላት ወደግቢ ያስገባሉ አሉ፡፡ የሚያስገቡት ታዲያ ኦሮሞ ኦሮሞውን እየመረጡ ነው አሉ፡፡ ስማቸውን ሲጠይቁ ታዲያ ተሰላፊው ስሙን “ደቻሳ” ሲል ጄኔራሉ “ግባ”፣ “ጉርሜሣ” ሲል “ግባ”፣ “ፈይሣ” ሲል “ግባ”፣ “መልካሣ” ሲል “ግባ”፣ “ድንቄሳ” ሲል “ግባ” … “ዓለማየሁ” ሲል “ውጣ”፣ “ስንሻው” ሲል “ውጣ”፣ “ደምመላሽ” ሲል “ውጣ” … እያሉ ሲያስገቡና ሲያስወጡ የታዘበ አንድ “ተንኮለኛ” አማራ እውነተኛ ስሙን ትቶ “እኔሳ” ሲል “ግባ” አሉት እየተባለ በጨዋታ መልክ ሲወራ ሰምቻለሁ፡፡ ነገሩ እንዳልኳችሁ ጨዋታ ነው፡፡ ግን እሳት በሌለበት ጪስ የለምና ይህ ዓይነቱ የዘርና የቋንቋ ልዩነት አልነበረም ብሎ መካድ ከእውነት መራቅ ነው፡፡ ይህን ነገር ታዲያ ሙሉ በሙሉ በአማራ ላይ ብቻ ማላከክ ትልቅ ነውረኝነት ነው፡፡ ሁሉም ያደርገው ነበር፡፡ ሁሉም ተሰዳድቧል፤ ሁሉም ተፈቃቅሯል፤ ሁሉም ተጎሻምጧል፤ ሁሉም በጋብቻ ተሳስሯል፤ ሁሉም አማራ ሆኗል፤ ሁሉም ትግሬ ሆኗል፤ ሁሉም ኦሮሞ ሆኗል፤ በጥቅሉ ሁሉም ሁሉንም ሆኗል፡፡
የትኛው ከየትኛው ይበልጥ ተሰድቧል ወይም ተበድሏል ብሎ ለመፍረድ ደግሞ መሥፈሪያ ቁና ወይም መለኪያ ሚዛን ያስፈልጋል፡፡ ያን ለማድረግ ደግሞ አስፈላጊነቱ አይታየኝም፡፡ ወደፊት መሄድ እየተቻለ ጉድጓድ መቆፈርና ስላለፈ ታሪክ መነታረክ ለምን አስፈለገ? “በቅሎ አባትሽ ማነው” ስትባል “እናቴ ፈረስ ነች” ያለችውን መለሳዊ ያልተገናኝቶ መልስ እናስታውስና ይልቁናስ የሚያዋጣን ነገር ወደኋላ መሮጥ ሣይሆን ወደፊት መገስገስ ነው፡፡ በዱሮ ታሪክ ማላዘን ሥራ-ፈትነት ይመስለናል፡፡ ሥንፍናና ድንቁርናም ነው፡፡ ከዘመን ጋር ለመራመድ ያለመቻል የአስተሳሰብና የአመለካከት ደካማነትም ነው፡፡
ተስፋየ እንደትልቅ ችግር ያነሳውና እርሱ መፍትሔ እንደሰጠው የጠቀሰው በእስካሁን የኢትዮጵያ ልቦለዶች ውስጥ አንድም የኦሮሞ ገጸ ባሕርይ አለመኖሩ ነው፡፡ እዚህ ላይ ከማስገረምም አልፎ አስቆኛል፡፡ በቡርቃ ዝምታና በሌሎች የዐዞ ዕንባ አጉራፊ ድርሰቶቹ የፈጠረውን ክፍተት ይበልጥ ያሰፋ መስሎት ይህን ቢልም ለዚህ ድምዳሜ ያበቃውን የጥናት ውጤት ግን አልገለጸም፡፡ በብዙ ሺዎች የሚገመቱትን የኢትዮጵያ ልቦለዶች ሁሉንም አንብቦ እንዲህ ሊል እንደማይችል መቼም ግልጽ ነው፡፡ ደግሞም ደራሲያን የኦሮሞ ስም እንዳይጠቀሙ የከለከለ አንድም የቀድሞ መንግሥት አላውቅም፡፡ ይህ ወዘና የሌለው ጠብ-ጫሪ ሃሳቡ ብቻ ይህን ተስፋየ የሚባልን ጋኔን ለማውገዝና አክ እንትፍ ብሎ ለመጣል በቂ ነው፡፡
በዱሮ ጊዜ እኔም ነበርኩ፡፡ ስምን በሚመለከት ከመንግሥት ጋር ምንም ትስስር በሌለው ሁኔታ ኅብረተሰቡ ራሱ በልማድ የሚተገብረው የስም አወጣጥ ሂደት ነበር፡፡ የኔ የአክስቴ ልጅ ለምሣሌ ከአማራው አካባቢ ስትመጣ የነበራት እገሊት የሚባል ስም አዲስ አበባ ላይ ስለሚያስቅባት ለውጣለች – ትሠራ የነበረችውም ቡና ቤት ነው ፤ የብዙዎች አማሮች ሴቶች የመጨረሻ መዳረሻ ሴተኛ አዳሪነት ነበርና፡፡ ያኔ አማራ መሆን የተለዬ ጥቅም አያስገኝም ነበር፤ እኔ ራሴ የአማራ ዝርያ እንዳለብኝ የተረዳሁት ብዙ ዘግይቼ በ83ዓ.ም መጨረሻ አካባቢ ቢሆንም የስም ለውጥን በተመለከተ እኔ ራሴ ከመጀመሪያ ስሜ አንዷን ሆሄ ከግዕዙ ወደ ራብዕ ፊደል በገዛ ሥልጣኔ ለውጫታለሁ – ዘመናዊ ለመባል፡፡ እነሸንተሞ፣ እነየዝና፣ እነጓንጉል፣ እነ አዝብጤ፣ እነአንጓች፣ እነጠጂቱ፣ እነወርቅያንጥፉ፣ እነግምብወግሽ፣ እነጉማታ፣ እነባንችይርጉ፣ እነታንጉት፣ እነጉዝጉዝ፣ እነጣፈጡ፣ እነማንጠግቦሽ … ስንቱን ጠቅሼው… እነዚህ አማሮች ሁሉ አዲስ አበባ ሲገቡ ስማቸውን ለመለወጥ ይገደዱ ነበር – “ዝናር ባንገቴ”ና “ዱቤ ክልክል ነው” የሚያስብልባቸውን የአንገትና የፊት ንቅሳታቸውን ለማጥፋት ስንቶች አማራ ሴቶች ገላቸውን በማስፈቅፈቅ መከራቸውን ያዩ ነበር፡፡
ስማቸውንና የፊት ገጽታቸውን እንደዘመኑ ማድረግ ካልቻሉ ደግሞ ከብት ባልዋለበት ኩበት ለመልቀም እየታከቱ የሚገኙት አዛኝ ቅቤ አንጓቾቹ እነተስፋየ እንደሚሉት መንግሥታዊ ተፅዕኖ ኖሮ ሣይሆን ማኅበረሰቡ ራሱ ስለሚስቅባቸው ክፉኛ ይሳቀቁ ነበር፡፡ መንግሥትማ እንዴት ስምን ቀይሩ ሊል ይችላል? ኦሮሞና አማራው አጤ ምኒልክ፣ ጉራጌ፣ አማራ፣ የመኑና… ኦሮሞው አጤ ኃይለ ሥላሴ፣ አማራና ኦሮሞው መንግሥቱ ኃ/ማርያም፣ ተጋሩ አኅዋትና ፍስሐ ደስታና ጄኔራል አማን አንዶም፣ … በምን ድፍረታቸው ዜጎችን ከዚህ ወደዚያ ወይም ከዚያ ወደዚህ ስማችሁን ቀይሩ ሊሉ ይችላሉ? አያ ጅቦ ሳታመካኝ ብላኝ ነው ነገሩ፡፡ ኤዲያ! ምን ዓይነት ጊዜ ላይ ደረስን ጎበዝ፡፡
ከዚህ መሠረታዊ ጭብጥ አንጻር የወለጋው ሰርቤሳ አዲስ አበባ ሲገባ ወይም የአርሲዋ ጫልቱ ናዝሬት ስትደርስ ኤርምያስና ሉሊት ብለው ስማቸውን ቢቀይሩ ተወቃሹ ማን ነው? ዕቁብ ያልበላን ሰው፣ ዕቁብ ስለመኖሩም የማያውቅን ሰው “የበላኸውን ዕቁብ ውለዳት!” ብለው በማይገባው ነገር ቢከሱትና ቢያደነቁሩት ምን ዋጋ አለው? ፍርድ ከራስ ነውና አማራ ያልሆናችሁ ሰዎች በተለይ ፍረዱኝ፡፡ የዚህን የተስፋየ ገብረባብ ሥውር ተልእኮ ደግሞ አስተውሉልኝ፡፡ ጊዜው የፈቀደው ፋሽን ሆኖ እንጂ ይህ የፈረደበት አማራ ያመጣው ፈሊጥ ሆኖ አልነበረም – አማራ እንደአማራ ሣይሆን በስሙ የነገዱና አሁንም ድረስ ሊነግዱበት የሚቋምጡ ጥቂት ቆሻሻ ዜጎች የሉም ለማለት እንዳልፈለግሁ ግን ተረዱልኝ፤ ክፋትና ደግነት በብሔረሰብና በብሔር የሚገደብ አይደለም፡፡ ደግነቱ “ሥራ ለሠሪው እሾ ላጣሪው” እንዲሉ ሁሉም ክፉዎች ዜጎች በጊዜያቸው የሥራቸውን ያገኛሉ – እንደመለስ ዜናዊና መሰል የከይሲው ልጆች፡፡ እነተስፋየ ተሟጋችና ተከላካይ የለውም ብለው በወደቀ ግንድ ላይ ምሣር ለመቀብቀብ ሌት ከቀን የሚተጉት ዘመናቸው የሰጣቸው ሰይጣናዊ ኃላፊነት በመሆኑ ሕዝብን መከፋፈልና ማበጣበጥ ከዚያም የተላኩበትን መሠሪ ተልእኮ ሲፈጽሙ ከሀገራችን ግልጽና ድብቅ ጠላቶች የሚሠፈርላቸውን ድርጎ መቀበል ዓይነተኛ ሙያቸው ስለሆነ ነው፡፡ እነዚህ አፈንጋጮች ፀሐያቸው መጥለቋ አይቀርም – የጊዜ ጉዳይ ነው፡፡ ደህና የነበርን ሰዎች ግን ከተስፋ መቁረጥ ተቆጥበን ታሪክ የሚያሳየንን ተዓምር በትግስት እንጠብቅ፡፡ ቀኑ ደርሷል፡፡ የነፃነትን መባቻ ቀን የሚያውቅ አንድዬ ብቻ ቢሆንም ቀኒቱ መቅረቧን የምንገነዘብባቸው ብዙ ምልክቶችን እያየን ነው፡፡
ሰማይ ክፉኛ ሲጠቋቁር፣ ደመናው ሲከብድ፣ ጭቆናውና እንግልቱ፣ ስደቱና ሰቆቃው ሲበረታ የቀኑን መቅረብ መገመት እንችላለን፡፡ የኢትዮጵያ ሰማይ ጭጋግ መልበስ ጀምሯል፡፡ ተራሮች ደም ቋጥረዋል፡፡ ሸለቆዎች አንዳች ነገር ሊያፈነዱ አቆብቁበዋል፡፡ ወንዞችና ሐይቆች አኩርፈዋል፡፡ … እንደቅዱስ ጳውሎስ እንዲህ ልበልና ልጨርስ – “የቆምን የሚመስለን ይበልጥ እንጠንቀቅ፤ የተቀመጠውን የሚያሳስበው መውደቅ የለምና፡፡” ለማንኛውም ልብ ይስጠን፡፡ እያለንም ሞተንም መኖር እንድንችል ለሚያደርገን አኩሪ ተግባር እንጂ እያለንም ሞተንም የሞት ሞት እንድንሞት ለሚያደርገን አስነዋሪ ድርጊት እንዳንጋለጥ ተግተን እንጸልይ፡፡ እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ፡፡
yiheyiseaemro@gmail.com