Netsanet: ወቅቱ የተግባራዊ ትግል ነው። አርበኖች ግንቦት 7፡ የአንድነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ

Donnerstag, 2. April 2015

ወቅቱ የተግባራዊ ትግል ነው። አርበኖች ግንቦት 7፡ የአንድነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ

pg7-logoለገዛ ራሱ፣ ለኢትዮጵያ ሕዝብ እና ለኢትዮጵያ ቅን የሚመኝ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ዜጋ ህወሓትን ለማስወገድ ተግባራዊ ትግል ውስጥ መሳተፍ የሚኖርበት ወቅት ላይ እንገኛለን። በዚህ ወሳኝ ወቅት ከዳር ሆኖ መታዘብ ዘረኛውን፣ አምባገነኑን፣ ፋሽስቱን ህወሓት እንደመደገፍ ይቆጠራል።
ዛሬ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ህሊናውና አቅሙ በሚፈቅድለት የትግል ዘርፍ የመሰማራት ሰፊ እድል ተፈጥሮለታል። በዚህም መሠረት የህወሓትን አፈና በጠነከረ ክንድ ለመመከት የቆረጡ ኢትዮጵያዊያን ወደ በረሃዎችና ተራራዎች አቅንተዋል። ብዙዎች በመንገዱ ላይ ያሉ ጋሬጣዎችን ተቋቁመው እየተቀላቀሏቸው ነው። በደል የመረራቸው ሌሎች በርካታ ኢትዮጵያዊያን በተለያዩ የኢትዮጵያ ክልሎች በቡድን ለነፃነታቸው ዘብ ቆመው በህወሓትና አገልጋዮቹ ላይ እርምጃ መውሰድ ጀምረዋል። ይህ የሚበረታታ እና ተቀናጅቶ ሊጠናከር የሚገባው ጉዳይ ነው።
አሁን ያለንበት ጊዜ ልዩ የትግል ወቅት ነው። ትናንት በከተሞች ይካሄድ የነበረው ፀረ ወያኔ ትግል ዓይነተኛ መታወቂያው ሕዝባዊ ተቃውሞ ነበር። ዛሬ ግን ይህ ሁኔታ ተቀይሯል። በተለይ በአገዛዙ ፈቃድ የሚደረጉ ተቃውሞዎች ፋይዳ ቢስ ሆነዋል። በአገዛዙ ፈቃድ በሚደረጉ ተቃውሞዎች ለውጥ እንደማይመጣ የኢትዮጵያ ሕዝብ በማያሻማ ሁኔታ ተረድቷል። ስለሆነም ትግሉ ወደ ሕዝባዊ እምቢተኝነት አድጓል።
ዛሬ ከዚህ በፊት ያልተሞከሩ የትግል ስልቶች ተግባራዊ እየሆኑ ነው። በዚህ ረገድ የሙስሊም ኢትዮጵያዊያን የተቀናጁ ርምጃዎች በአርዓያነት የሚጠቀሱና የሁሉም ኢትዮጵያዊያን ድጋፍ የሚሹ ናቸው። እነዚህ የሕዝባዊ እምቢተኝነት ተግባራት የእምነት አጥር ሳይለያየን ፍትህ የተጠማን ዜጎች ሁሉ ልንተገብራቸው የሚገቡ ናቸው።
ለምሳሌ፣ ተንቀሳቃሽ ስልኮችን በተወሰኑ ቀናት መዝጋት በተቀናጀ ሁኔታ ከተደረገ ከፍተኛ ውጤት ሊያመጣ የሚችል፤ በሙስሊም ወገኖቻችን ግንባር ቀደም መሪነትና አስተባባሪነት ተሞክሮ በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ተግባራዊ ሊደረግ የሚችል መሆኑ የታየ አንድ የትግል ስልት ነው።
በአሁኑ ወቅት ተግባራዊ በመደረግ ላይ ያለው ሣንቲሞችን የመሰብሰብ ዘመቻም ሌላ ከዚህ በፊት ያልተሞከረ፤ በተጨማሪ እርምጃዎች ከታገዘ ህወሓት መራሹ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የሀገሪቱን ገንዘብ መቆጣጠር የማይችልበት ደረጃ ላይ ሊያደርስ የሚችል ጉልበት ያለው ስልት ነው። ውሳኔው ሣንቲሞችን ብቻ ሳይሆን የወረቀት ኖቶችንም ሲያካትት በዝውውር ላይ የሚኖረውን ገንዘብ ብዛት የሚቆጣጠረው ህወሓት ሳይሆን በደል ያንገሸገሸው ሕዝብ ይሆናል። በባንኮች ያለ ተቀማጭ ገንዘብ በማውጣትም የህወሓት የፋይናንስ ተቋማትን ማሽመድመድ ሌላ ተግባራዊ ሊደረግ የሚችል ስልት ነው። በእነዚህ እርምጃዎች የተለማመደ ሕዝብም ወደ ግዢ እቀባ፤ ለተወሰኑ ቀናት ከቤት አለመውጣት ብሎም “ግብር አልከፍልም” ወደማለት ሊሸጋገር ይችላል።
እንዲህ ዓይነቱ ስልቶች ውጤታማ እንዲሆኑ ግን የመላው ሕዝብ ተሳትፎ እና የተቀናጀ አሠራርን ይፈልጋል። ለምሳሌ፣ ሰብስቡ ሲባል መሰብሰብን፤ በትኑ ሲባል መበተን ይጠይቃል። እንዲህ ዓይነት የተቀናጁ የጋራ እርምጃዎች በአምባገኑ የህወሓት አገዛዝ ላይ ከሚያደርሱት ጥቃት በተጨማሪ በኢትዮጵያዊያን መካከል ያለውን መግባባት ያጠናክራሉ። እንዲህ ዓይነት የተቀናጁ የጋራ እርምጃዎች በማኅበረሰብ ቡድኖች መካከል አዎንታዊ መስተጋብር ለመፍጠር የሚኖራቸው ሚና ከፍተኛ ነው።
አሁን አገራችን የምትገኝበት ሁኔታ በጥሞና ሲጤን የኢትዮጵያ ሕዝብ ሳይነጋገር መግባባት፣ እርስ በርሱ መናበብ የሚችልበት ደረጃ ላይ እየደረሰ መሆኑ መረዳት ይቻላል። ይህ ስነልቦናዊ ዝግጅት ደረጃ በደረጃ ጠንከር ያሉ እርምጃዎችን ለመውሰድ ያዘጋጀናል።
በማናቸውም የጋራ እርምጃዎች ለግል ጥቅሞቻቸው ቅድሚያ የሚሰጡ፤ ራሳቸው “ብልጥ” አድርገው በማየት በተፈጠረው ሁኔታ መጠቀም የሚፈልጉ፤ በሌላው ድካም ለማትረፍ የሚሯሯጡ ሰዎች መኖራቸው የማይቀር ነው። ህወሓት ለሃያ አራት ዓመታት ኮትኩቶ ያሳደገው የአድርባይነት ባህልም ሌላው እንቅፋት ሊሆን እንደሚችል መገመት ቀላል ነው። ድህነት ደግሞ በገዢዎች ላይ ጨክነን የመነሳት አቅማችንን እንደሚያዳክም የታወቀ ነው። ሆኖም ግን የኢትዮጵያ ሕዝብ ከፊቱ የቀረበለት ምርጫ “ባርነት ወይስ ነፃነት” መሆኑን የተገነዘበበት ጊዜ ላይ ደርሰናል።
በዚህም ምክንያት ለህወሓት ባርነት ከመገዛት ነፃነትን የሚመርጥ ዜጋ ሁሉ ዋጋ ለመክፈል መዘጋጀት ይኖርበታል። ለሁላችንም የሚሆን የትግል ዘርፍ መኖሩ የሕዝቡን ተሳትፎ ከፍ ያደርገዋል። የሁለገብ ትግል ስትራቴጂ ጥቅሙም እዚህ ላይ ነው። ማንም የማንም ነፃ አውጭ አይደለም። ሁላችንም ተባብረን ሁላችንንም ነፃ እናወጣለን።
አርበኖች ግንቦት 7፡ የአንድነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ “ትግላችን ዘርፈ ብዙ ነው፤ ተግባራዊ ትግል የሚደረገውን በሁሉም ቦታዎች ነው፤ እርጃዎቻችን እናቀናጅ፤ ወቅቱ የተግባራዊ ትግል ነው” ይላል።
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!

Keine Kommentare:

Kommentar veröffentlichen