ግሩም ተ/ሀይማኖት (ከየመን)
ረቡዕ ሌሊት 8፡30 ላይ የተጀመረው የአየር ድብደባ አሁንም እንደቀጠለ ነው፡፡ የመን ነዋሪ የሆነ ሁሉ በፍርሃት ርዷል፡፡ በተለይ በትላንትናው ሌሊት የነበረው የአየር ድብደባ ከፍተኛ ስለሆነ ህዝቡ ላይ የጣለው ፍርሃት ከወትሮው የተለየ ነው፡፡ “በሁቲይን አማጽያን ሚሊሻ ላይ የተጀመረው የአየርጥቃት አሁንም በድርድሩ ካልተስማሙ ወይ ሰነዓ ከተማን ለቀው እስካወጡ አያቆምም!” ሲሉ የሳዑዲ አረቢያ ንጉስ ሰልማን ቢን አብድልአዚዝ ገልጸዋል፡፡ ይህን አባባላቸውን ተከትሎ እግረኛ ሰራዊትም ሊንቀሳቀስ መሆኑ እየተገለጸ ነው፡፡ 20.000 እግረኛ ወታደር ተዘጋጅቶ ድንበር ላይ መሆኑን የየመን መገናኛ ብዙሀን እየዘገቡ ነው፡፡ ከዚያ በፊት ተጀምሮ የነበረውን ድርድር እንዲቀበሉ ለሁቲይን አማጺዎች ከትላንት ወዲያ የ3 ቀን እድሜ ቢሰጣቸውም አልተቀበሉትም፡፡
በሳዑዲ ሰብሳቢነት የአረብ ሊግ ሀገራት መንግስታት በየመን ጉዳይ ለመመከር ግብጽ ሻርማ ሸኸ ተሰብስበው ነው ያሉት። በዚህ ስብሰባ ላይ የአየር ጥቃቱ የዘመቻ መሪ ሀገር የሳዑዲ አረቢ ንጉስ ሰልማን ሀቲይን የተባሉት አማጽያን ለቀው እስኪወጡና የመን እስክትረጋጋ ድረስ የተጀመረው ጥቃት ቀጣይ እንደሆነ ገልጸዋል በማለት የየመኑ ቶውራ ጋዜጣ ዘግቧል፡፡ በዚህ ስብሰባ ላይ የየመኑ መሪ አብድረቡ መንሱር ሀዴ ተገኝተዋል፡፡ ህዝቡ ግን ሀገራችንን እያስደበደበ ያለው ፕሬዘዳንታችን ነው በማለት ጥስ እየነከሰባቸው ነው፡፡ የቀድሞው ፕሬዘዳንት አሊ አብደላ ሳላ ድርድሩን እንደሚቀበሉ ቢገልጹም ተቀባይነት ያገኙ አይመስልም፡፡
ዛሬ ሌሊት በሳውዲ የተመራው የአስሩ ሀገራት ህብረት ጦር በሰንዓ ፈጂ አጣን የተባለው ቦታ ጋራ ላይ የሚገኘው ወታደራዊ ካምፕ ውስጥ ያለ የብላስቲክ ሚሳየል ክምችት ማውደሙ ታውቋል፡፡ ይህ የመሳሪያ ክምችት በተመታበት ወቅት መላ ከተማው የተርገደገደበት የመሬት መንቀጥቀጥ አይነት ሁኔታ ነበር፡፡ አንዳንድ ህንጻዎች መስታዎታቸው ሁሉ ርግፏል፡፡ ነዋሪው ሲነጋ እንቅልፍ አጥቶ መደሩ ዋነኛው ርዕስ ነበር፡፡ በተለይ ስደተኛ ኢትዮጵያዊን ከፍተኛ ፍርሃት ተውጠን እንዳለን በርካታ ያናገርኳቸው ወገኖቼ ገልጸውልኛል፡፡ በእርግጥ ሌላውስ ወገን የመን ያሉ ኢትዮጵያዊያንን እንዴት እያሰባቸው ይሆን?
የተመታው ካምፕ ላይ የሚቃጠለው መሳሪያ ፍንዳታም ከፍተኛ ነበር፡፡ ከሌሊቱ 8፡20 ጀምሮ ጠዋት ድረስ እሳቱን ለማጥፋት ርብርብ ነበር፡፡ የሁቲይን አማጺያን ድብደባውን በዝምታ እያዩት አይደለም፡፡ ከየአቅጣጫው በአየር መቃወሚያ ምላሽ ይሰጣሉ፡፡
እንደ አባባላቸው ከሆነ የአየር ጥቃቱን ከሚያደርሱት ጀቶች እስካሁን ሁለት መምታታቸውን ተናግረዋል፡፡ በዛሬው ሌሊት ሰነዓ ላይ ድብደባው ቀነስ ቢልም ሁዴዳና ሌሎች ደቡባዊ የመን ላይ ጠንከር ያለ እንደነበር መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ ሁቲይኖቹም ከየአቅጣጫው የሚደረገውን ጥቃት ለመከላከል ሙከራቸው በዛሬው ሌሊት ቀንሶ ታይቷል፡፡ ሰነዓ ያለ ኢትዮጵያዊ በጭንቅ ውስጥ ሲሆን አደን የተባለው ሁለተኛ ከተማ ውስጥ ያሉ ኢትዮጵያዊን በከፍተኛ ሁኔታ እያነቡ ነው፡፡
Keine Kommentare:
Kommentar veröffentlichen