ውድ ጃዋር ፣ ሳልውቅ ፣ ጠነኝነቴ አሳስቶኝ ፣ አንተም ምንም የመረረ እና የተንዛዛ ዘረኛ ብትሆንም ቅሉ ፣ ጤነኛ ነህ ብዬ ፣ እንደ አንድ ሰው ልወቅስህ አስቤ ፣ ባንተ ላይ የጻፍኩዋቸው ጽሁፎች ፣ አሁን አንተን በደንብ ሳውቅ እና ስላንተ ስረዳ ፣ ይህንን የይቅርታ ደብዳቤ መጻፍ እናዳለብኝ ተረድቻለሁና ፣ ደብዳቤን አርቅቄ ይኸው ይደርስህ ዘንድ ይሁን።
ውድ ጃዋር ሆይ ፣ እንደምን ከርመሃል ? መቼም መጻፍ አስቸግሮኝ አያውቅም ፣ ይህንን ጽሑፍ ግን ለመጻፍ ስዘጋጅ ያየሁትን ፈተና እኔና መድሃኒያለም ነን የምናውቀው ። በመጀመሪያ ፣ ስለ አንተ በደንብ ከተረዳሁ እና ካወቅሁ በሁዋላ ፣ እንዴት አድርጌ ብጽፈው ፣ ይቅርታዬ ሊገባው ይችላል ብዬ ተጨነኩ ፣ ቀጥሎ ከዚህ ሁሉ የእርማት እና ፊደል የመልቀም ሥራ በሗላስ በእውነት የጻፍኩት ይገባው ይሆን ብዬ ድጋሚ ተጨነኩ ። መቼም እንደ አንተ አይነት ወንድሜን ፣ ያለብህን ችግር እና ይሄን ሁሉ ነገር የሚያናግርህን ነገር ሳላውቅ ፣ ያን ያህል ነገር መናገር አግባብ አለመሆኑን መረዳቴ እንዴት እንደቆጨኝ ማን በነገረህ?
ውድ ጃዋር ሆይ ። እንደምታውቀው ሰሞኑን አንድ ” ፍገራ ኒውስ ” በሚል ርእስ ስር ተቀናብሮ ፣ በኢትዮ-ትዩብ በኩል ለኛ ” ለተደራስያን ” ( አድማጭ አላልኩም ) የቀረበልንን ነገር ተመለከትኩ ። ደግሜ ደጋግሜ ተመለከትኩ ። ከዚያ በራሴ እና ለራሴ ምርር ብዬ አለቀስኩ ። ለምን መሰለህ ፣ ይቺ ኢትዮጵያ ሀገራችን ሰው እንደሌላት ፍንትው ብሎ ታየኝ ። አንተን የመሰለ ሸበላ ፣ አንተን የመሰለ ሰው ፣ እንዲሁ ከበው ሲወቅሱ ፣ ሲያሞግሱ ፣ እና ወዘተ ሳይ በጣም አዘንኩ።
ጃዋር ሆይ ። እንደምታቀው ሜንጫ ማለት ቦክስ እንደማለት ነው ። ይህም ማለት እንደው ባጋጣሚ አሩሲ ውስጥ ተሳስተህ አንድ ነገር ብትናገር ፣ በሜንጫ ቦክስ ፊትህ ሊያብጥ እንደሚችል ነው ። አንዳንድ ሰዎች ግን ፣ አይ ሜንጫ ቦክስ አይደለም ፣ ሜንጫ ካራ ወይም ስለት ነው እያሉ ሲከራከሩ ሰማሁ ። ይሄማ ሊሆን አይችልም ብዬ ወገቤን ይዤ ተከራከርኩ ። ምክንያቱም “ሚኒሊክ ጡት ቆረጠ!” ብለው የሚንጫጩ ሰዎች ፣ በፍጹም ሜንጫን እና ቦክስን አንድ ሊያደርጉ ስለማይችሉ እና እኔም በግሌ ስለማውቅ ። እና ታዲያ የይቅርታዬ መጀመሪያውም መጨረሻውም እዚህ ጋ ይጀምራል ። ትዝ ይልህ ከነበር ባለፈው ፣ ” አንገቱን በሜንጫ ነው የምንለው ” ብለህ አልነበር ? እና’ልህ ህዝቡ አንገቱን በስለት ነው የምንቆርጠው ማለቱ ነው ብሎ በጣም አዝኖ ነበር ። አሁን ግን ዕድሜ ለ “ኢትዮ- ትዩብ” ሜንጫ ምን ማለት እንደሆነ አንተ በሰጠኸው መልስ ስለተረዳው እና ስላወቅሁ፣ ሜንጫ ማለት ቦክስ ማለት ከሆነ ፣ እኔም ራሴ ስቧቀስ ስላደኩ ፣ አዎ ሜንጫ ማለት ቦቅስ ማለት ከሆነ ፣ ታዲያ ጃዋር ምን አረገ ብያለሁ።
በነገራችን ላይ ጃዋር ፣ እኔ የአዲስ አበባ ልጅ ነኝ እና አዲስ አበባ ሳለሁ ” የቦቅስ ፌድሬሽን ” የሚባል ነገር አውቅ ነበር ፣ እንደውም ባብዛኛው የአብነት ልጆች ናቸው የሚሳተፉት እኔ በነበርኩበት ( በማስታውስበት ) ሰዓት ማለት ነው ። እንዴት ነው አሩሲ የሜንጫ ፈድሬሽን የሚባል ነገር አለ ወይ ? ካለስ ባመት ስንት ግዜ ነው የሚደረገው ? ለውድድሩ ብቁ የሆኑ ተሳታፊዎች የመወዳደሪያ መስፈርታቸው ምን ይሆን ? አንደኛ ዲቪዚዮንን ከሁለተኛ ዲቪዚዮን የሚለየው የሜንጫው ክብደት ነውን ? ወይስ በመንጫው ኖክ አውት ታደረጉትን ሰው ብዛት ቆጥሮ ” አንተ ብቁ ነህ አንተ አይደለህም ” የሚል መስፈርት አለ ወይ ? እንዴት ነው መጀመሪያ በጩቤ እጃቸውን ካፍታቱ ወዲያ ነው ወይ ወደ ሜንጫ ዲቪዚዮን ከፍ የሚሉት ?። አንድ ወዳጄ ይህንን ጽሑፍ ስጽፍ አጠገቤ ቁጭ ብሎ ( እንዲሁ ጣልቃ እየገባ) ” በናትህ ሔኒ አሩሲ የገጀራ ፈድሬሽንስ አለ ወይ ?” በለው አለኝ ፣ እኔ እንኳ እንዲህ አይነት የልጅ ጥያቄ አንተን ለመሰለ ትልቅ ሰው ማቅረብ እንደማይገባኝ አውቃለሁ ፣ ግን ግን ሜንጫ ማለት ቦክስ ማለት እንደሆነ የታወቀ ነው ( እሱንም አንተ ወንድሜ ጃዋር ነግረኸኛል ) ፣ ገጀራስ ምን ማለት ይሆን ፣ እንዲሁ ስገምት ግን ጥፊ ይመስለኛል ። ቆንጨራስ ?ቴስታ ማለት ይሆን ? ትርጉም እኮ እንደ ተርጏምው ነው ። ሞኝ አይሙት እንዲያጫውት ያሉት አማሮች ናቸው ? እነሱንማ በሜንጫ ቦክስ ማለት ነበር ልል አልኩና ፣ ጃዋር ብሎት የለ እኔ ብደግመው ምን ዋጋ አለው ብዬ ተውኩት።
ለማንኛውም እነዛ በሜንጫ ቦክስ ታፍረውና እና ተከብረው የኖሩትን ሜንጫኞች ፣ የአኖሌ ሃውልትም በዚህ አካሄድ በጠረባ እንደተሰራ ያውቁ ይሆን አይሆን ትጠይቅልኝ ዘንድ ጠይቄ ጽሁፌን ላብቃ!
Keine Kommentare:
Kommentar veröffentlichen