Netsanet: ሰማያዊ ፓርቲ የቅስቀሳ መልዕክት ለአራተኛ ጊዜ በሚዲያ እንዳይተላለፍ ተከለከለ • ኢቢሲ የሰማያዊ ፓርቲን የቅስቀሳ መልዕክት ‹‹አላስተላልፍም›› ብሎ መልሷል

Sonntag, 8. März 2015

ሰማያዊ ፓርቲ የቅስቀሳ መልዕክት ለአራተኛ ጊዜ በሚዲያ እንዳይተላለፍ ተከለከለ • ኢቢሲ የሰማያዊ ፓርቲን የቅስቀሳ መልዕክት ‹‹አላስተላልፍም›› ብሎ መልሷል


ሰማያዊ ፓርቲ የቅስቀሳ መልዕክት ለአራተኛ ጊዜ በሚዲያ እንዳይተላለፍ ተከለከለ
• ኢቢሲ የሰማያዊ ፓርቲን የቅስቀሳ መልዕክት ‹‹አላስተላልፍም›› ብሎ መልሷል
• ‹‹ኢቢሲ ከገዥው ፓርቲ ጋር ወግኗል›› አቶ ዮናታን ተስፋዬ
የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን (ኢብኮ) የሰማያዊ ፓርቲን የቅስቀሳ መልዕክት ‹‹አላስተላልፍም›› ብሎ መመለሱን ዛሬ የካቲት 29/2007 ዓ.ም ለፓርቲው በላከው ደብዳቤ ገልጾአል፡፡ ኢቢሲ በደብዳቤው ‹‹የምርጫ ቅስቀሳ መልዕክት ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ በምስሉ ግርጌ የተቀመጠው እንዲሁም በቅስቀሳ መልዕክታችሁ ውስጥ አልፎ አልፎ የሚታየው ሰንደቅ አላማ ምስል የሀገሪቱን ሰንደቅ አላማ የማይወክልና ህገ መንግስቱን…. የሚፃረር ሆኖ አግኝተነዋል›› በሚል እንደማያስተላልፍ ገልጾአል፡፡
በሌላ በኩል ‹‹ይህ የኢቢሲ ተግባር የሰማያዊን ፕሮግራም ላለማስተላለፍ ሆን ተብሎ የተሰጠ ሰበብ ነው›› ያለው የፓርቲው የህዝብ ግንኙነት አቶ ዮናታን ተስፋዬ በህገ መንግስት የተከለከለውን ቅድመ ምርመራ ኢቢሲ እየተገበረው ነው ሲል ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጾአል፡፡
‹‹ህግ ተጥሷል ከተባለ እንኳን ፕሮግራሙ ከተላለፈ በኋላ እንከሰስ ነበር እንጅ ባልረባ ምክንያት አላስተላልፍም ብለው መመለስ አልነበረባቸውም›› ያለው የህዝብ ግንኙነት ኃላፊው ሰንደቅ አላማ የሚውለበለበውን እንጅ ከዛ ውጭ ያለን ማናቸውንም ነገር የሚመለከት አይደለም ሲል ኢቢሲ የፓርቲውን መልዕክት ላለማስተላለፍ ያቀረበውን ሰበብ ተችቷል፡፡ አቶ ዮናታን አክሎም ‹‹በአዋጅ 654/201 ላይ የሰፈረው ህግ አንድም ቦታ ተሰቅሎ ስለሚውለበለብ፣ ከመኪና ከሚውለበለብ እና በአደባባይ ከሚያዝ ሰንደቅ አላማ ውጭ ስለ ሌላ አንዳችም የሚከለክለው ነገር የለም፡፡ ስለዚህ ኢቲቪ ለገዥው ፓርቲ በመወገን ፕሮግራማችን እንዳይተላለፍ እያደረገ ነው›› ሲል ወቅሷል፡፡
በተያያዘ ዜና ፓርቲው ነገ የካቲት 30 በሬድዮ ፋና ከአንድ ሰዓት ዜና በኋላ ለሚተላለፈው ፕሮግራም ትናንት ስድስት ሰዓት መልዕክቱን ለራዲዮ ጣቢያው ለማስገባት ቢሞክርም ‹‹ዘግተው ወጥተዋል፣ ሰኞ ነው የሚገቡት፡፡ ሰኞ አስገቡ›› በሚል የሰማያዊ ፓርቲን መልዕክት መልሰዋል፡፡የፓርቲዎች መልዕክት ከሚተላለፍበት 36 ሰዓት ቀድሞ እንዲገባ እንደተባለ የገለጸው አቶ ዮናታን ሰኞ ጠዋት የሚተላለፍን መልዕክት ‹‹ሰኞ ጠዋት አምጡ›› ብሎ መመለስ ላለማስተላለፍ እንደወሰኑ ያሳያል ብሏል፡፡
ከአሁን ቀደም ኤፍ ኤም 96.3 ሁለት ጊዜ እንዲሁም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ሬድዮ አገልግሎት አንድ ጊዜ የሰማያዊ ፓርቲን የቅስቀሳ መልዕክት የመለሰ ሲሆን ይህኛው ለአራተኛ ጊዜ መሆኑ ነው፡፡

Keine Kommentare:

Kommentar veröffentlichen