Netsanet: እነ አቶ በላይ ሊያስመዘግቡ ከነበረው 5% ብቻ ነው የትግስቱ ቡድን ያስመዘገበው - አማኑኤል ዘሰላም

Freitag, 6. März 2015

እነ አቶ በላይ ሊያስመዘግቡ ከነበረው 5% ብቻ ነው የትግስቱ ቡድን ያስመዘገበው - አማኑኤል ዘሰላም

=======================
የአንድነት ፓርቲ በአገራችን ኢትዮጵያ ገዢውን ፓርቲ ማሸነፍ የሚችል ጠንካራ ፓርቲ እንደነበረ ይታወቃል። ፓርቲው ከሶማሌ ክልል በስተቀር በሁሉም የአገሪቷ ክፍሎች መዋቅር የነበረው ሲሆን ከ547 የፓርላማ መቀመጫ ወደ 480 በሚሆኑት ተወዳዳሪዎች አዘጋጅቶ የነበረ ፓርቲ ነው። ለፓርላማ ብቻ ሳይሆን ከ1200 በላይ ተወዳዳሪዎችን ደግሞ ለክልል ምክር ቤቶ ተዘጋጅተው ነበር። ኢሕአዴግ ለፓርላማ 501 ለክልል ደግሞ ወደ 1300 አካባቢ ነው ያስመዘግበው። አንድነት ምን ያህል ከኢሕአዴግ ጋር ተቀራራቢ እንደነበረ በግልጽ የሚያሳይ ነው።
የአንድነት ፓርቲ ልሳኖቹን በብርሃንና ሰላም እንዳያትም ቢደረግም፣ የራሱ ማሽን ገዛ። ሕወሃት መብራት አለቅም ሲል ደግሞ ጀኔሬተር ጨመረ። ሁለት ጋዜጦችን ማሳተም ጀመረ ( ፍኖት ነጻነት የምትባል ቅዳሜ ፣ቅዳሜ፣ የሚሊዮኖች ድምጽ የምትባል ማክሰኞ ፣ ማክሰኞ )። የምርጫ ማኒፌስቶ አዘግጅቶ፣ አማራጅ ፖሊሲዎችን ለህዝብ ይፋ ለማድረግ፣ ዳንዲ የምትባል የጽንሰ ሐሳብ መጋዚን አዘጋጅቶ ለማሳተም ጥቂት ቀናት ቀርተው ነበር።
በአንድነት ጥንካሬ የደነገጠው ሕወሃት፣ የፖለቲክ ዉሳኔ አሳልፎ፣ በአቶ በላይ ለሚመራው የአንድነት አመራር እዉቅና አልሰጥም አለ። በአንድነት ዉስጥ በተደረገ ምርጫ ለፕሬዘዳንትነት ተወዳድረዉ የነበሩና አንድ ድምጽ ብቻ እርሱም የራሳቸው ድምጽ ላገኙት፣ ለአቶ ትግስቱ ቡድን እውቅና ሰጠ።
የሕወሃት ምርጫ ቦርድ ያንን ያደረኩት ፓርቲዉን ለመጥቀም ነው፣ ፓርቲው መቀጠል ስላለበት ነው የሚል አስቂኝ መከራከሪያ ነው ያቀረበው። በርግጥ የምርጫ ቦርድ ዉሳኔ አንድነትን ለመጥቀም ነበርን ? በርግጥ ምርጫ ቦርድ እንዳለው አብዛኛው የአንድነት አባል ከትግስቱ ቡድን ጋር ነስለሆነ ነዉን?
አቶ ትግስቱ በዚህ ሳምንት ከሰንደቅ ጋዜጣ ጋር አጭር ቃለ ምልልስ አድርገዋል። በነ አቶ በላይ ከ 1700 በላይ ( 480 ለፌዴራል እና ከ1200 በላይ ለክልል) ተወዳዳሪዎች ለማዝመዝገብ ተዘጋጅቶ የነበረው አንድነት ፣ አሁን በነ ትግስቱ ሰማኒያ ብቻ ነው ያስመዘገበው። (ወደ 5% አካባቢ ብቻ) ከዚህ ቀደም 200 ተወዳዳሪዎ አሰልፈናል ነበር የትግስቱ ቡዱን ሲል የነበረው። አሁን ቁጥሩ ወደ ሰማኒያ ወርዷል። ምናልባት ከአንድ ሳምንት በኋላ ወደ 23ቱ የአዲስ አበባ ተወዳዳሪዎች ብቻ ሊወርድም ይችላል)
በአቶ በላይ ይመራ የነበረ አንድነት፣ ሁለት ጋዜጦችን በየሳምንቱ ያሳትም ነበር። ጋዜጣ ለማሳተም ማሽን ብቻ አይደለም። ጸሃፊዎች፣ ሐሳብ አምንጭዎች፣ አዘጋጆች ያስፈልጋሉ። ትልቅ የሰው ኃይል ያስፈልጋል። አንድነት ያ ነበረው። የታማሩ፣ የበሰሉ ፖለቲከኞች ነበሩት። እነዚህ የአንድነት ሰዎች አብዛኞቹ ወደ ሰማያዊ ጎርፈዋል። አንዳንዶቹም የትግስቱን ቡድን አንቀበልም ብለው ወደ ፍርድ ቤት ሄደዋል። የትግስቱ ቡድን ባዶነቱን ለማሳየት፣ በደንብ ሲሰራ የነበረን ማሽን «ተበላሽቷል» የሚል ሰበብ ለመስጠት እየሞከሩ ነው።
በአቶ በላይ የሚመራው አንድነት፣ ሁለት ድህረ ገጾች ( አድንነት.ኦርግ እና ፍኖተ ነጻነት. ኦርግ) እንዲሁም ሶስት የሶሻል ሜዲያ ፔጆች (የአንድነት ኦፌሴላዊ ፌስ ቡክ ፔጅ፣ የሚሊዮኖች ድምጽ ፔጅ፣ የፍኖተ ነጻነት ፔጅ ) ያንቀሳቀስ ነበር። የክልል ምክር ቤቶች ደግሞ የአዲስ አበባ ምክር ቤት ፔጅ፣ የጮሮ አንድነት ፔጅ፣ የኮምቦላቻ አድንነት ፔጅ፣ የአዳማ አንድነት ፔጅ፣ የአዲስ አበባ ወጣቶች ፔጅ ….እያሉ በጣም ስፋት ባለው መልኩ የሕዝብ ግንኙነት ሥራ ይሰራ ነበር። የአንድነቶች ድምጽ ከየቦታው እንሰማ ነበር።
የአቶ ትግስቱ ቡድን ምንም አይነት የድህረ ገጽ ሥራ እየሰራ አይደለም። ከሶሻል ሜዲያውም እንደዉም እንወጣለን እያለ ነው። ይሄ ለምን ሆነ ? አንድነት ከዚህ በፊት የነበሩ እንቅስቃሴዎችን ሲያደርግ የነበረው አባላትን ደጋፊዎች በብዛት ስላሉት ነው። የሶሻል ሜዲያው ዘመቻም ሆነ ድህረ ገጾች ባለሞያዎች፣ የተማሩ ሰዎች፣ ሐሳብን የሚያፈልቁ ያስፈልጋሉ። የአቶ ትግስቱ ቡድን ከሕወሃት የመጡ ቅጥረኞች እንጂ የተማሩ ሰዎች የሌሉበት ቡድን በመሆኑ ምንም ማድረግ አልቻለም።
የአንድነት አባላት በዚህ መልኩ ለትግስቱ ቡዱን ድጋፍ ነፍገው ይሄን የሕወሃት ቅጥረኛ ማጋለጣቸው በጣም የሚያስደንቅ ነው። የነበላይ አመራር መቼም ቢሆን ታማኝነቱ ለድርጅት ሳይሆን ለነጻነትና ለሕዝብ በመሆኑ፣ ዉስጥ ዉስጡን አባላት ተመሳሳይ ፕሮግራም ያለዉን የሰማይዊ ፓርቲን ተቀላቅለው ትግሉ እንዲቀጥሉ በአንድ በኩል ማድረጋቸው፣ በሌላ በኩል ሌላ ግብረ ኃይል አሰማርተው በፍርድ ቤት ጉዳዩን መከታተላቸው ፓርቲው አሁን የደረሰበት ከፍተኛ ዱላ ቢያሳምመዉም፣ አባላትና ደጋፊዎች አሁን ለአንድ አላማ አንድ ላይ መሆናቸው በግልጽ የሚያሳይ ነው።
አንርሳ ይሄ ሁሉ የሆነው የአንድነት ፓርቲ ሥራ ስለሰራ ነው። በከባድና ፈታኝ ሁኔታው ዉስጥም ሆኖ የሚታይ ነገር በማድረጉ ነው። ለዚህ የአንድነት አባላትና የአንድነት ደጋፊዎች ሊኮሩ ይገባል።
አቶ ትግስቱ ከሰንደቅ ጋር ያደረጉት አጭር ቃለ ምልልስ የተወሰኑት እንሆ !
ጥያቄ፡- በምርጫው ምን ያህል ዕጩዎችን አቅርባችኋል?
አቶ ትዕግስቱ፡- በአጠቃላይ በሀገሪቷ ውስጥ ከተዘጋጁት የምርጫ ጣቢያዎች ውስጥ ከሰማንያ በላይ በፓርላማና በምክር ቤት ደረጃ እንወዳደራለን። በአዲስ አበባ በሃያ ሶስቱም የፓርላማ መቀመጫ ወንበሮችን ለማግኘት እጩዎች አቅርበናል።
ጥያቄ፡- ፓርቲው በራሱ የሚያሳትመው የተለያዩ የህትመት ውጤቶች ነበሩት። እነዚህን የሕትመት ውጤቶች ለመቀጠል ምን እየተደረገ ነው? ወይንስ እንዲቋረጥ ወስናችሁ ነው የቆመው?
አቶ ትዕግስቱ፡- የሕትመቶቹ መቋረጥ ከእኛ በኩል ተነሳሽነት በማጣት የመጣ አይደለም። ለሕትመት ስራዎች የሚሆነን ማሽን አለን። ሆኖም ግን ሕገወጥ ቡድኑ ጽ/ቤቱን ሲለቅ ከማተሚያ ማሽኑ ላይ የተለያዩ ክፍሎቹን በመፈታታት አጉድሎ ነው የለቀቀው። እነዚህ መሳሪያዎች ለመተካት ስራዎችን አጠናቀናል። ሌላው ለጋዜጠኞች ተገዝተው የነበሩ መቅረጸ ድምፆችም ቢሮ ውስጥ የሉም። እነዚህን እና ሌሎች ቁሳቁሶችን በቅርቡ አሟልተን ወደ ሕትመት እንገባለን። ከዚህ በፊት የነበሩም ጋዜጠኞች የፓርቲያቸው ህልውና እንዲቀጥል ከሚፈሉጉት ጋር በጋራ ለመስራት ሁኔታዎችን እየተመለከትን ነው። ከዚህ በተጨማሪ አዳዲስ ጋዜጠኞችን የመቅጠር ስራዎች እንጀምራለን። በአጭር ጊዜው ወደሕትመት ስራዎች እንገባለን ብለን እናስባለን።
ጥያቄ፡- የሶሻል ሚዲያዎችና የድረ ገፅ ስራዎችን እየሰራችሁ አይደለም። ይህ በጽ/ቤት አቅም ሊፈጸም የሚችል ነው። ለዚህ የሚሰጡት ምላሽ ምንድን ነው?
አቶ ትዕግስቱ፡- እዚህ ጋር ግልፅ መሆን ያለበት የፓርቲው ድረ ገጽ አድሚኒስትራተር ቁልፍ ያለው በዲያስፖራው እጅ ነው። ከዚህ በፊት በኢንጅነር ግዛቸው ሊቀመንበር ወቅት እኔ የውጭ ግንኙነት ክፍል ውስጥ ስለነበርኩ በእኔ ደብዳቤ አዘጋጅነት ከፓርቲው ተፈርሞ በወጣው ደብዳቤ ዲያስፖራው የአዲሚኒስትራተር ቁልፉንና ሃላፊነቱን ለፓርቲው እንዲመልሱ ተደርጓል። አሁን ከፓርቲው ውጪ በሕገወጥ መንገድ የሰሜን አሜሪካ አሳተባባሪዎች መካከል የተወሰኑት እየተጠቀሙበት ነው የሚገኘው። በነገራችን ላይ እነዚህ ሰዎች የሚለጥፉት ማንኛውም አይነት ጽሁፍ ፓርቲውን የሚመለከት አይደለም። ለእኔ በሕገወጥ መንገድ የሚሰራ ወንጀል ነው። ከሀገር ኮብልለው ከወጡ አንድ ግለሰብ ጋር በጋራ ጥምረት ፈጥረው የሚወጡ ማናቸውም አይነት መረጃዎች ሕገወጥ መሆናቸውና ፓርቲው እውቅና የማይሰጣቸው መሆኑ ሁሉም ሊገነዘብ ይገባል።
ሰንደቅ፡- ሶሻል ሚዲያን በተመለከተስ?
አቶ ትዕግስቱ፡- ከሶሻል ሚዲያው ጠቅልለን መውጣት ነው የቀረን። እኛስ ፖለቲከኛ ስለሆንን እንችለዋለን። በእኛ ላይ የሚለቀቀው ኃላፊነት የጎደለው መረጃ እና ዛቻ ቤተሰቦቻችንን እየረበሸ ነው የሚገኘው። የማንም ቤተሰብ በጋጠወጦች መዘለፍ፣ መሰደብ፣ መዋረድ ያለበት አልመሰለኝም። በፌስቡክ ከእኛ ጋር በጓደኝነት የሚገናኙ ቤተሰቦቻችን ወዳጆቻችን ለእኛ የሚሰነዘረው ስድብና ዛቻ መመልከት ሰልችቷቸዋል። በተለይ ቤተሰቦቻችን የእነሱን አካውንት ወይም የእኛ አካውንትን መዝጋት ብቸኛው አማራጭ ነው። አንድ በተለይ ተምሬያለሁ የሚል ተመራጭ ‘ተምሮ’ የሚጽፈውን የታዘበ አንድ ወዳጄ “ይህ ሰው ባይማር ኖሮ ምን ሊጽፍ እንደሚችል” ግራ አጋቢ ነው ያለው ለሁሉም ማሳያ ተደርጎ የሚወሰድ ነው።
ሰንደቅ፡- እየደረሰብን ይገኛል የምትሉት ዛቻ መነሻው ምንድን ነው? ምን አይነት ዛቻስ ነው የሚደርስባችሁ?
አቶ ትዕግስቱ፡- የሚገርመው ለእኔ ለራሴ የግድያ ዛቻ ይደርሰኛል። አንዳንዱ ያለምንም ሃፍርት በሞባይል ደውሎ እደፋሃለሁ ይላል። በሶሻል ሚዲያም ተመሳሳይ ዛቻ ይደርሰኛል። ሌሎች አባሎቻችን መንገድ ላይ ሳይቀር ያስፈሯሯቸዋል። በአጠቃላይ አንድ አደገኛ ቦዘኔ ሊሰራው የማይችል ስራዎች ናቸው እየተፈጸሙ የሚገኙብን።

Keine Kommentare:

Kommentar veröffentlichen