Netsanet: ለዲያቆን ዳንኤል ክብረት ( የመጨረሻ አስተያየት)Ermias Legess / የ መለስ ትሩፋቶች

Freitag, 6. März 2015

ለዲያቆን ዳንኤል ክብረት ( የመጨረሻ አስተያየት)Ermias Legess / የ መለስ ትሩፋቶች


በመጀመሪያ ጊዜህን ሰጥተህ የጠየኩትን መረጃ ስለሰጠኸኝ ምሥጋናዬ ይድረስህ። በተደጋጋሚ እንደገጵኩት የአንተን የድምጵ መልእክት የሰማሁት ማስታወሻውን ከመጳፌ በፊት በማህበራዊ ድረገጶች በሰፊው እየተራገበ በመመልከቴ ነው። አንተ እኔን ለመወረፍ እንደሞከርከው ” ጊዜና ሁኔታ ያላገናዘበ” ሳይሆን አጀንዳውን ጐትተው ወደ መድረክ ያመጡት ወቅታዊ በመሆኑ ነው። ( በፌስ ቡክ ላይ የተለቀቀበትን ቀን መመልከት ትችላለህ)
ከአንዳንድ ወዳጆቼ ጋር በነበረን ምልልስ እንደገለፅኩት ይህን ሰነድ ወደ ፊት ይዞ መምጣት አሁን የሚደረገውን የኢትየጵያ ሙስሊሞች የነፃነት ትግል ጥላሸት ለመቀባትና ለመቀልበስ በማሰብ ነው። ባጭሩ ያቀረብከው ሰነድ መቼም ይሁን መቼ ” ጊዜውን እየጠበቀ የሚፈነዳ ፈንጂ” መሆኑን አስምሬበታለሁ። አሁንም እምነቴ ይህ ነው።
በዝርዝር ካነሳሀቸው ጉዳዬች አንዳንዶቹን ነቅሼ በማውጣት ነጥብ በነጥብ አስተያየት ልስጥበት፣
1• ” ኦርቶዶክስና የአማራ ፓለቲካ”
እጅግ በጣም የገረመኝ ከኪዳነ ምህረት ቤተክርስቲያን ጋር ተያይዞ ” ቢሮህ ጠርተኸን የፈረደበትን አማራ” ሰደብክ ብለሃል። በጣም አዝናለሁ። ሰዎች ፊት ቆመህ የምትሰብከው እንደዚህ አይነት የከረፋ አመለካከትና ውሸት ተሸክመህ መሆኑን መመልከቴ ርግጥም አሳዝኖኛል ።
ሲጀመር ከኪዳነምህረት ቤተክርስቲያን ጋር በተያያዘ አንተንም ሆነ ሌሎች የኦርቶዶክስ ሐይማኖት አባቶችን ቢሮ ጠርቼ አላናገርኩም። በመጵሀፌ ላይ እንደገለፅኩት መስኪዱ እንደሚገነባ የሰማሁት በምሳ ሰአት፣ የተገነባው የዛኑ ቀን ለሊት ነበር። ወደ ቢሮዬ የተመለስኩት ደግሞ መስኪዱ ተገንብቶ ባለቀ በሶስተኛው ቀን ። ርግጥ በወረዳ 23፣24 ፓሊስ ጣቢያ የዞኑ ፓሊስ አዛዥ ( ኮማንደር ተሰማ) እና የወረዳው ፓሊስ አዛዥ ( ኮማንደር ተስፋ ፈርሻ) ጋር በመሆን በቁጥጥር ስር ውለው ከነበሩ አባቶች ጋር ተወያይተናል ። ታዲያ ከአንተ ጋር ቁጭ ብዬ ባልተነጋገርኩበት እንዲህ አይነት ቅጥፈት ከየት አመጣኸው?
( በዞን ሁለት በነበረኝ ቆይታ ከአዲሳአባ ሀገረ ስብከትም ሆነ ሲኖዶሱ ጋር የተወያየሁት በቅድስት ልደታ ቤተክርስቲያን እና በጐፋ ገብርኤል በተነሳው ችግር ምክንያት ብቻ ነው። እሱም ቢሆን እኔ፣ ደረጄ ( የወረዳ 22 አስተዳዳሪ) ፣ መኮንን ( ፓሊስ አዛዥ) እና ፊዬሪ ( የሚሊሻ ጵ/ ቤት ሐላፊ) ወደ ተጠቀሱት ቦታዎች ሄደን እንጂ እነሱ መጥተው አይደለም ። በወቅቱ ከጳጳሱ ( ነብሳቸውን ይማረውና) የደረሰብን ማስፈራሪያ እና በእሳቸው ዛቻ ምክንያት የተፈጠረው ቀውስ የቤተክርስቲያኗን ክብር ስለሚነካ ከመግለፅ ተቆጥቢያለሁ። አንዳንድ ወዳጆቼ ለምን አስቀረኸው የሚል ወቀሳ ቢቀርብብኝ ህውሀትን ለማጋለጥ ሃይማኖቱን አላዋርድም በሚለው ጵናቴ ትቼዋለሁ።)
” የፈረደበት አማራ” የሚለው ቅፅል የጵሁፍህ አንዱ ማጠንጠኛ እንደሆነ ለመገንዘብ በህውሀት ፓለቲካ ውስጥ አንድ ወር መቆየት በቂ ነው። ኦርቶዶክስና አማራን ህውሀት ጠላት አድርጐ እንደዘመተባቸው ስለምታውቅ እኔን በ” ፀረ አማራ” ፈርጀህ ብትጵፍ ሚዛን እንደሚደፋልህ የተቀመረች ” አቦይ ስብሀታዊ” ሂሳብ ሰርተህ መጣህ። ሐይል ለማሰባሰብ ተጠቀምክበት። አዲሳአባ ከኦሮሞና አማራ ተወልዶ፣ አድጐ፣ አማራ አግብቶ ለሚኖር ሰው ” ፀረ – አማራ” ታፔላ ለመለጠፍ ህሊናህ እና እምነትህ እንዴት እንዳልገቱህ ሳስበው እጅጉን ገርሞኛል ። ርግጥ ዘርን ጐትቶ ወደ እምነት ተቋማት ማምጣት( በተለይ ኦርቶዶክስና አማራ) የማን የፓለቲካ ቁማር እንደሆነ አንተም፣ እኔም፣ አንባቢያንም፣ ” ኢትዬጲያም” …ወዘተ እናውቀዋለን ። በዚህ ምክንያት ” አቦይ የላከው…” እንድልህም አስገደደኝ። በአንድ ወቅት ስብሐት ነጋ በሚመራው ” የሰላምና አለም አቀፍ ምናምንቴ ኢንስቲትዩት ” ኔትወርክ እንድትታቀፍ ካድሬዎች ሊመለምሉህ እንደሆነ ስለማውቅ ። መጨረሻውን ባላውቀውም።
2• ” መወደሰ መከላከያ ሰራዊት ”
ህውሀት የተፈጠረውንና የጭቆና መሣሪያ ሆኖ የሚያገለግለው መከላከያ እውቅና የሰጠህበት ምክንያት አሁን ላይ ስመለከተው በጣም ግልፅ ሆኖልኛል ። ህውሀት የእምነት ተቋማትን በተጠና እና በታቀደ መልኩ ይበጠብጣል። ከዛም እርስ በራስ ያጨፋጭፋል። በመጨረሻም መከላከያ ( የፀጥታ ሀይል) ገብቶ አበረደው የሚል ፕሮፐጋንዳ ይረጫል ። በተለይ ከምርጫ 97 በኃላ የተፈፀሙ ድርጊቶች ቅኝት ይሄ ነበር። ስለዚህ ግልፅ የሆነልኝ ነገር ከጀርባ ምን እንደሚሸረብ አታውቅም አሊያም ለመካድ ፈልገሀል። አሊያም እንደገለጵከው ፓለቲከኛ አይደለህም ።
3• ጥናቱ ለመንግሥት ስለመቅረቡ
በምላሽህ ላይ ” ያ ጥናት ለመንግስት አካላት ሳይለዋወጥ መቅረቡን በወፍ በረር እናውቅ ነበር።” አየህ! ዲያቆን ዳንኤል ትልቁ ነጥብ ይህ ነው። በጥናቱ ውስጥ ያሉትን መረጃዎች እንደወረደ ለመጀመሪያ ጊዜ የሰማሁት በ2001 አ•ም• ከሽመልስ ከማል ነበር። ይህንን ጥናት መሰረት በማድረክ የመወያያ ሰነድና የድርጊት መርሐ ግብር ተዘጋጀ። ( ዶክመንቱን በአዲስ ራዕይ መፅሔት ላይ ይገኛል)
በተዘጋጀው ሰነድ ( ከግማሽ በላይ የአንተ ዶክመንት አባሪ የተደረገበት)ከአራት ሚሊዬን በላይ በሆኑ የኢህአዴግ አባላት ውይይት ተደረገበት። በጣም የሚገርመው አብዛኛው አባል በተለይ ኦሮሚያ እና አማራ ክልል ተቃውሞ ገጠመው። ሆን ተብሎ ክርስቲያንና ሙስሊሙን ለማጋጨት የታቀደ ነው የሚል ግዙፍ አስተያየቶች ተስተናገዱ። በተለይም “አክራሪነት በክርስትናም ፣ በእስልምናም አለ!” የሚለው ድምዳሜ ብዙዎችን አስቆጣ። የእኛ አባላት የሆኑ የዩንቨርስቲ ተማሪዎች በእኛ ተቃራኒ ተሰለፋ። እውነቱ ይሄ ነው። የሕውሐት ፓለቲለካ በማወቅም ሆነ ባለማወቅ አንተ አዘጋጀሁት ያልከው ሰነድ ይህን ሁኔታ ፈጥሯል። በዚህ ጉዳይ ለተፈጠረው ችግር ድርሻህን እንደመውሰድ ዛሬም በማር የተለወሰ አባባል ይዘህ ብቅ አልክ።
እስቲ ከጳፍከው ውስጥ የሚከተለው አርፍተነገር ምን ለማለት አስበህ እንደሆነ አስረዳኝ?
” ክርስቲያኖች ሁሉ ቅዱሳን ናቸው እንደማልለው ሁሉ ሙስሊሞች ሁሉ አክራሪዎች ናቸው ብዬ አላውቅም ”
ይህን አርፍተነገር እንገልብጠውና ፣ የተገለበጠውን የምታምንበት ከሆነ አክብሮቴን ከወዲሁ እገልጳለሁ። እስቲ ልገልብጠው ( እድሜ ለማቲማቲክስ!!)
” ሙስሊሞች ሁሉ ቅዱሳን ናቸው እንደማልለው ሁሉ ክርስቲያኖች ሁሉ አክራሪዎች ናቸው ብዬ አላውቅም”
ቀጣዩ ተግባር በድርጊት መርሐ ግብሩ መሰረት ወደ ተግባር መግባት ነበር። ለኢትየጵያ እስልምና ተከታዬች አዲስ ዶክትሪን በመንግስት መሪነት ተዘጋጀ፣ ከቀበሌ እስከ መጅሊስ የሚሆኑ አመራሮች በኢህአዴግ ተመረጡ ( በዚህ እንቅስቃሴ ውስጥ ተዋንያን ነበርኩ። ለዚህም ነው አንዳችም የሕውሐት ሸፍጥ መደበቅ የለበትም ብዬ በድፍረት የምናገረው።) እናም ጐበዝ ከሆንክ በኢትየጵያ ሙስሊሞች ላይ ህውሀት የሚያደርሰውን ጭቆና በአደባባይ አውግዝ!!
ኦርቶዶክስ ጋርም ጫናው ተመሳሳይ ነው። አባይ ፀሐዬ የተናገራት በሙሉ ተፈፅሟል ። በጣም የሚያሳዝነው የአባይ ፀሐዬን የድብብቆሽ ጨዋታ ልቦናህ እያወቀ ” የሲኖዶሱን የፓለቲካ ገጵታ አንተ ንገረኝ ” ትለኛለህ። ” ንገሩኝ ባይ! ” እንዳልልህ ላጠለከው ቆብ ክብር መንሳት ሆኖ ተሰማኝ። ሲኖዶሱ ህውሀት እንዴት እንደሚያሽከረክረው ለማወቅ እንዲሁ በመንገድ ላይ የሚሄድ ወጣት አቁምና ጠይቅ። አንተ የፈራኸውን የፓለቲካ ቁማር ይነግርሀል። ተመራምረህ ጥናታዊ ፅሁፍ ማዘጋጀት ከፈለክ ደግሞ ” ብታምኑም ባታምንኑም ሲኖዶሱ በቀኝ ግዛት ተይዟል ” ያሉትን አባት እንደመነሻ ለመጠቀም ፍቃድህ ይሁን።

Keine Kommentare:

Kommentar veröffentlichen