በልጅግ ዓሊ
ከጥቂት ዓመታት በፊት ጀርመን ፍራንክፈርት ማርዮት ሆቴል ውስጥ “ኢንቬስተሮችን“ ለመሳብ በሚል ፈሊጥ አባዱላ ገመዳ በተገኘበት የወያኔ አባላትና ደጋፊዎች ስብሰባም ተጠርቶ ነበር። በዕለቱ ተቃዋሚዎች ከደጅ ተኮልኩለው ወያኔን በመቃወም ላይ ነበሩ። በሁለት ስለት ቢላዋ መብላት የዘመኑ ብልጠት በመሆኑ፤ የቤት መስሪያ ቦታ መደለያ ለማግኘት የሚቋምጡ ሁሉ በዚህ ስብሰባ ላይ ተገኝተው ነበር። በተለይ የወያኔ ደጋፊ የሆኑ “የአብዮታዊ ዴሞክራሲ ኢንቬስተሮች“ አለያም በዘመኑ አጠራር የልማት ባለሃብት ተብዬዎች ማንነታቸው በሰልፈኞቹ እንዳይለይ በመፍራት ማንነታቸውን በመነጽርና ኮፍያ ውስጥ በመደበቅ ወደ አዳራሹ ይገቡ ነበር። በሌላ ስልት ደግሞ ከተቃዋሚዎች መሃል አንዳንዶች ገብተው ስብሰባውን እንዲካፈሉና የስብሰባውን ይዘትና ጭብጥ ተረድተው እንዲወጡ ተደርጎ ነበር። ቀደም ሲል በስንት ጣር በመነጽርና በኮፍያ ታግዞና እራሱን ደብቆ የገባው “ኢንቬስተር“ ተሽቀዳድሞ ወደ ሽንት ቤት በመግባት ጣጣ እንደሌለበት ሰው ኮፍያውንና መነጽሩን አውልቆ፣ አለባበሱን አስተካክሎ ወደ ስብሰባው አዳራሽ ብቅ ሲል ከውስጥ ቀደም ሲል ሆን ተብሎ ለማጥናት የገባው ተቃዋሚ ይጠብቀዋል። እንደገና ሌላ መደናገጥ ይፈጠራል። ግማሹ መግቢያ ያጣል ፣ ግማሹ እንዳላየ አይቶ ለማለፍ ይሞክራል፣ አንዳንዱ ደግሞ እንደምንም እራሱን አረጋግቶ የማስመሰል ጨዋታውን ይገፋበታል።
እንደ አጋጣሚ በእለቱ ስብሰባ ላይ በቅርብ የማውቀው ተቃዋሚ የነበረ ወዳጄ ተገኝቶ ነበር። አዳራሹ ውስጥ ከሰልፈኛው ተሽሽጎ የገባ “ግማሽ ኢንቬስተር“ “ግማሽ ተቃዋሚ“ ከሆነ ሰው ጋር ይገናኛሉ። ይህ ከሆነ በኋላ “ኢንቬስተሩ“ ሁኔታው መሰማቱ አይቀርም በሚል ብዙዎቻችን ጋር እየደወለ ሃጢአቱን ያስተባብል ጀመር። “እኔ የሠራሁት ቤት እንዳይወረስብኝ ብዬ እንጂ ሌላ ነገር ፍለጋ አይደለም። እኔ ወያኔ አይደለሁም… ወዘተረፈ ብቻ ያልለፈለፈው የለም። እኔም በውል አዳምጬው ሳበቃ ስብሰባውን ወደ ተካፈለው ሌላ ተቃዋሚ ደውዬ የስብሰባው ውሎ እንዴት እንደነበር? ብዬ ጠየቅሁት። ሃቁ ግን “ግማሽ ኢንቬስተሩ“(ልማታዊ ባለሃብቱ) እንደነገረኝ ሳይሆን እንደውም በተቃራኒው ስብሰባው ላይ ያዙኝ ልቀቁኝ ሲል እንደነበረና ቀንደኛ ተዋናይ ሆኖ እንደዋለ አስረግጦ ነገረኝ። የአባ ዱላ ስብሰባ “የግማሽ ኢንቬስተሩ“ “የግማሽ ተቃዋሚነት“ ሚናው የመጨረሻው ሆነ። ይህ ግማሽ “ኢንቬስተር“ ከአባ ዱላ ስብሰባ በፊት በተቃዋሚዎች ስብሰባም ላይም እንዲሁ ያዙኝ ልቀቁኝ ባይ ነው።
በአሁኑ ወቅት አያሌ ለሆዳቸው ያደሩ ባንዳ “ኢንቬስተሮች“ ከተቃዋሚው ጋር “ተቃዋሚ“ ከወያኔው ጋር ቀንደኛ ወያኔ ሆኖ የመታየት አባዜ እየተጠናወታቸው መጥቷል። ወያኔ በየጠራው ስብሰባ እየሄዱ የግል ጥቅማቸውን እንደሚያሳድዱ ሁሉ በተቃዋሚው አካባቢ ደግሞ ተቃዋሚ ሆኖ ለመታየት የማያደርጉት ጥረት የለም። በአዘቦቱ ቀን ከወያኔ ደጀሰላም (ቆንስላ) እንደማይጠፉ ሁሉ በተቀቃሚ እንቅስቃሴዎች ደግሞ እንዲሁ በለመደባቸው ቀንደኛ ተዋናይ ሆነው መታየትን ይሻሉ። ለእነዚህ አድርባዮች ዋናው ጠላታቸው ደግሞ ፎቶ ነው። መረጃ በሁለቱም(በተቃዋሚም ሆነ በወያኔ) በኩል ማስያዝ ስለማይፈልጉ ፎቶ መነሳት እርማቸው ነው።
የእነዚህ “የልማት ባለሀብቶች“ የጥፋት ተልእኮ በአሁኑ ወቅት ፍራንክፈርት ውስጥ በጣም ጎልቶ እየታዬ ነው። “የትግራይ ልማት“ አስረሽ ምችው፣ የባለ ራእዩ መሪ ተስካር፣ የወያኔ ምሥረታ በዓልና የትራንስፎርሜሽኑ ድግስና አሸሼ ገዳሜ እየተገኙ ፊታውራሪነታቸውን ለማረጋገጥ የማይፈነቅሉት ድንጋይ የለም። ለዓብነት በቅርብ የተካሄደው የኦህዴድ (የወያኔ የኦሮሞ ክንፍ) 25ኛ ዓመት የምሥረታ በዓል በፍራንክፈርት በተከበረበት ወቅት የታየው ሁኔታ ጉልህ ማስረጃ ነው። በአካልም በቃልም ከታዘብነው ባሻገር የበዓሉን አከባበር አስመልክቶ በዓይጋ ፎረም ድረ-ገጽ የተለጠፈውን አንብበናል። ግን ዜናውን ለሚያነቡ ትልቅ በዓል የተደረገ ይመስላል። እውነቱ ግን ከተራ ፕሮፖጋንዳነት ውጭ ሚዛን የሚደፋ፣ ወንዝ የሚሻገር አንዳች ጭብጥ የለውም። ሃቁ ደግሞ ወያኔ በፍራንክፈርት አትዮጵያውያንን በዘር ከቶ መከፋፈል የቻለበት አጋጣሚ እሰከዛሬ ድረስ አልተፈጠረም።
በድረ ገጹ ላይ የተጻፈው የተውኔት(ተውኔት ያልኩበት ተዋንያኖቹ ስለገረሙኝ ነው) ትዕይንተ-ዜና ግን እንዲህ ይላል። “25ኛው የኦህዴድ የምስረታ በዓል በጀርመን ፍራንክፈርት ተከብሯል“ በሚል እርዕስ በፎቶ የታጀበ ዘገባ ቀርቧል። የፍራንክፈርት ነዋሪ እንደመሆኔ ዜናው ሳበኝና ለማንበብ ገጹን ከፍቼ ተመለከትኩት። ከዜናው ይበልጥ ከዜናው ጋር ተያይዞ የተለጠፈው ፎቶግራፉ ይበልጥ ስላስገረመኝ ቀልቤን ሳበው። መቼም ፍራንክፈርት ለኖርነው ፍቶው ላይ የምናያቸው “ኦሮሞዎች“ በአብዮታዊ ዴሞክራሲዊ የተሰጣቸው “የብሄር ብሄረሰብ“ ስያሜ ካልሆነ በስተቀር ለሃያ ዓመታት ሳውቃቸው የትግራይ ነጻ አውጪ ድርጅት(ተሓህት) አባላት ናቸው። ለዚህ ነው ማሞ ሌላ ፎቶው ሌላ የሆነብኝ። ፕሮፖጋንዳውን ያነበብን ብዙዎቻችን ኦሮሞዎቹ የት አሉ? ብለን ጠይቀናል። እንደኔ እንደኔ ዜናው መሆን ያለበት “በፍራንክፈርት የሚገኙ ወያኔን የሚደግፉ የትግራይ ተወላጆች የኦህዴድን 25ኛ ዓመት ምሥረታን አከበሩ“ ቢባል እውነተኛ ሊሆን ይችላል። ምክንያቱም በስብሰባው ላይ የተገኙት በአብዛኛው የተሓህት አባላት መሆናቸውን በግልጽ ከፎቶው ብቻ መረዳት ስለሚቻል ነው። ያም ቢሆን በቁጥር አነስተኛ እንጅ ብዙዎቹ ሃቀኛ የትግራይ ተወላጆች በዚህ አጸያፊ ተግባር ላይ እንዳልተገኙ ፎቶግራፉ በውል ያስረዳል።
ምንም እንኳን በፎቶው ላይ ባይታዩም በዚህ ስብስብ ውስጥ ጥቂት ኦሮሞዎች ሊኖሩ እንደሚችሉ አውቃለሁ። እነሱም ቢሆኑ ደፍረው ግን ፎቶግራፍ መነሳት አይሹም። ሕዝብም ወያኔ መሆናቸውን እንዲያውቅባቸው አይፈልጉም። የዘመኑ የልማት ባለሃብትና የነጻ ገብያ “ኢንቬስተሮች“ ናቸውና በእንደዚህ ዓይነት ስብሰባ እንዲገኙ ደግሞ በወያኔ የፍራንክፈርት ቆንስላ ስለሚገደዱ ስብሰባ ከመምጣት ውጭ ሌላ አማራጭ የላቸውም። ድብብቆሽ ተጫውተው ይመለሳሉ። እንግዲህ እንዲህና እንዲያ እያለ ነው በፍራንክፈርት የብአዴንና የኦህደድ ኢንቬስተሮች ተግባር ። ከዚህ ውጭ በይፋ በዓል ለማክበር የሚያስችል የሞራል ጥንካሬ ከቶ የላቸውም ።
እነዚህ ለጥቅም ራሳቸውን የሸጡ ኢንቬስተሮች ከየትናውም ጎራ ይምጡ ቁጥራቸው ግን ጥቂት ነው። የሚበዛው ትግራይ ነጻ አውጪ አባላት ቁጥር ነው። ሰለሆነም ከላይ ከፎቶው እንደምንመለከተው የትሓህት(የትግራይ ነጻ አውጪ) አባላት የተሰብሳቢውን ቁጥር እንዲበዛ ወያኔ ስብሰባ በተጠራበት ሥፍራ ሁሉ በነቂስ ወጥተው ይገኛሉ። ሕውሀትን እስከጠቀመ ድረስ የወያኔ ደጋፊ የሆኑ የትግራይ ተወላጆችን አንዴ አማራ ሆነው፣ ሌላ ጊዜ ኦሮሞ፣ ሲያሻቸው የደቡብ ህዝብ እየሆኑ በመገለባበጥ ለፕሮፖጋንዳ ሥራ በስፋት ያገለግላሉ። የማያውቃቸው እውነት ይመስለዋል። የሚያውቃቸው ደግሞ ስቆም ታዝቦም ያልፋል።
እነዚህ ተሰብሳቢዎች “በአብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ” ስም ያገኙትን የግል ጥቅም እንደ ሃገር ልማት የሚቆጠሩ ናቸው። ለግል ጥቅማቸው ሲሉ በሌላው ህይወት ላይ ተረማምደው የሚሄዱ፣ ሃገር እያፈረሱ የሚነግዱ፣ በዘር ክፍፍል የሚሞዳሞዱ፣ በመጭው ትውልድ ዕጣ ፈንታ ላይ የሚቀልዱ ናቸው። በልካቸው በተሰራ የድሎት መነጽር ሀገር ስለሚቃኙ፣ ህሊናቸው በንዋይ የታወረ፣ አእምሮአቸው በጥቅም የሰከረ፣ ከህዝብ ይልቅ ለአጉራሽ፣ ከማንነት ይልቅ ላፍራሽ ያደሩ ህሊና ቢሶች ናቸው ማለት ይቻላል።
ኦሮሞ የሚኮራ ታሪክ ያለው ታላቅ ህዝብ ነው። የሚዘበትበትም አይደል። ወላድ በድባብ ትግባ የኦሮሞ እናት በካር ነች። የኦሮሞ እንኳን የራሱን የሌላ ሰው ልጅ በጉዲፈቻ ማሳደግ ያውቅበታል። ኦሮሞ ልጅ እንደሌለው አስመስሎ ጽዋውን ሌላ እንዲዘክርለት ማድረግ ወይ ማስመሰል ወይም ንቀት ነው እሚሆነው። “ቅቤ አንጣሪዋ እያለች ጎመን ቀንጣሿን ምች መታት“ የማለት ያህል ካልሆነ በቀር፣ ኦሮሞ ስለ መብቱ መቆምና መከራከርም ያውቅበታል። ይህንን ወያኔ የሚዘነጋው ሆኖ አይደለም። ኦሮሞ ስለ ሀገሩ ኢትዮጵያም ዘብ የቆመ ህዝብ ነው። ቅድመ ታሪኩ ደግሞ ለዚህ ዋቢ ነው። ስለ መብቱም ሆነ ስለ ጥቅሙ፣ ስለ ሃዘኑም ሆነ ደስታው ዛሬ ሌላ አንጋችና ጋሻ ጃግሬ የሚያስፈልገው አይመስለኝም። በራሱ እራሱን ሁኖ በኢትዮጵያዊነት ልእልና እንደወትሮው ሲታይ በእጅጉ የላቀ ውበት አለውና ተለጣፊ አያሻውም።
ያም ሆነ ይህ በውጭ ያለው ኢትዮጵያዊ ከደሃው ተነጥቆ በተሰጣቸው መሬት ላይ ቤት እየሰሩ የሚንደላቀቁ ልማታዊ ባለሀብቶች በሚያደርጉት ብረት ለበስ የደባ ፕሮፖጋንዳ መወናበድ ያለበት አይመስለኝም። ሃገራችንን በክልል ከፋፍሎ ሕዝቡን ፍትህና የዴሞክራሲ መብት ያሳጣው ወያኔ ዛሬ እኛን በውጭ ያለውን ዜጎች በተለጣፊ ድርጅቱ የመከፋፈል ስልቱ ሊለያየን ከቶ አይገባም። በነጻው የአውሮፓ ምድር እየኖርን፣ ከፖርቱጋል እስከ ስዊዲን ያለቁጥጥር እየተጓዝን፣ ሌት ከቀን በነፃነት ወጥተንና ሰርተን እየገባንና እየኖርን በጠበበ የክልል ፖለቲካ ወያኔ ሊከፋፍል መሞከሩ ሞኝነት አለያም እብደት ይመስለኛል። ወያኔ ያደገው፣ የተቃኘው በዘር ፖለቲካ ነውና ከዚያ ከቶ ሊወጣ አይችልም ። ይልቁንስ እኛ ግን ዛሬም ነገም እራሳችንን ሆነን ልንገኝ ይገባል። ከትልቅ ሰውነት አስተሳሰብ ወደ ትልቅ ተቋምነት፣ በማንነት መለዩዎች ወደ ጋርዮሽ መለዮዎች፣ ከቁጥጥር ሥርዓት ወደ መብታዊ የብዙሃን ስርዓት የሚያሸጋግሩን ጠቃሚ ሥራዎች መስራቱ ለሃገርም ለራስም የሚበጅ የዜግነት ሃላፊነት ነው።
beljig.ali@gmail.com
ስለ ሃገራችን የሚያስቡ ሁሉ በሰላም ይሰንብቱ !
ፍራንክፈርት 28/03/15
ፍራንክፈርት 28/03/15
Keine Kommentare:
Kommentar veröffentlichen