Netsanet: ትራንስፎርሜሽን ወይንስ.......? ገብረጻዲቅ አበራ

Sonntag, 12. April 2015

ትራንስፎርሜሽን ወይንስ.......? ገብረጻዲቅ አበራ

የሃሳብ መንገድ
ትራንስፎርሜሽን ወይንስ.......?
https://www.facebook.com/video.php?v=1591837571056663&video_source=pages_finch_main_video
ዛሬ በኢትዮጵያችን ዘወትር የሚታየውን ትተን ከወዳጅ ዘመዶቻችን የምንሰማውንም ችላ ብለን የመንግስት ባለስልጣናት የሚነግሩንን መስማትና በመንግስት ሚድያዎች ስር መጣድ ላስቻለው ገነትን ከመጨበጥ በመመለስ ኢትዮጵያ ሁሉ ነገር ሞ ልቶ የተረፈባት የጎደላትም ባጭር ግዜ ውስጥ መስመር የሚይዝላት የሚሳሳላትና ብዙዎች የሚጎመዧት ሃገር እየሆነች ነው። ኢትዮጵያ ኑሮ ን ለማሸነፍ ባህር እያቋረጡ የሚሰጥሙበት በበረሃ ንዳድ የሚያልቁበት የጨለማ ዘመን እየተሻረ የጎረቤት ሃገር ሰዎች የሚፈልሱባት ጥቂት አመት ከጨመርን ደግሞ አሜሪካዊያን እና አውሮፓውያን የ ኢትዮጵያን ቪዛ ለማግኘት ደጅ የሚጠኑበት ግኔ በጣም እየቀረበ መምጣቱን እንረዳለን ። በመንግስትና በገዢው ፓርቲ ሚድያዎች ስር አስችሎን ከተጣድን። አሁንም ቢሆን ሃገር ጥለው የሚወጡት ስልጣን ቀረብን የሚሉ ጥቂቶች እንዲሁም ኢትዮጵያ ውስጥ ሰርቶ ከማግኘት ይልቅ ሳውዲ አ=ረብያ ውስጥ ሜዳላይ የሚረጨውን ሪያል ተኝተው ለማፈስና ደቡብ አፍሪካ ማሳላይ የተዘራውን ራንድ እያጨዱ ያለስራ ተንደላቀው ለመኖር የመረጡ ሰነፎች እንጂ ለሚሰራባት ኢትዮጵያ ባይነት ባይነቱ ስራ ሞ ልቶ የተረፈባት ብር የምታፈስባት ሃገር እየሆነች ነው። ብርታት ሰቶት መንግስት ሚድያ ስር ለተጣደ።
በረሃብና በችግር ብዛት ህሊናቸው ያልተነካባቸው ባይበሉም በቁንጣን የሚወጠሩ ጥቂቶችን እያዩ አቡጀዲ ቢቸግራቸውም በወርቅ የሚንቆጠቆጡትን እየገረመሙ ያቺ ኢትዮጵያ እነሱ የቆሙበትን የተወችውና ሃገራዊ .... አድርጋ የጥቂት ሺዎች ብቻ የሆነችው መቼ ነው ብለው እየጠየቁ ከረሃቡ በላይ የሚያመው ፕሮ ፖጋንዳ የውስጥ አካላቸው እየተጎዳ እንደሆነ መገመት አያስቸግርም ። በሌላም በኩል የድንቁርና ክፋቱ የዘረኝነት ብርታቱ ከሚታየው በላይ የሚሰማው እውነት ሆኖ ስለሚገለጥ እየተራቡ በቁንጣን የሚወጠሩ እየታረዙ በወርቅ የሚሽቆጠቆጡ ጥቂቶች አይደሉም። ጠኔ እያንጠራወዛቸው በአለማስተዋል የሚነገራቸውን አምነው አሜሪካኖች ኢትዮጵያ ለመግባት ጓጉተው ቪዛ የሚጠይቁበት ግዜ ሲመጣ የሚኖሩት የተደንላቀቀ ህይወት እየታያቸው በተስፋ ፍራሽ ላይ የሚንከባለሉ የሉም ብሎ የሚያምን ካለ አንብበው ያልተገለጠላቸው ብዙዎች ካጠገቡ ቃኝተው ሳያነቡ የተከደነባቸውን መገመት ይችላል። ድሃ በህልሙ ቅቤ ባይጠጣ ንጣት ይገድለው ነበር የሚለው ብሂል ለዚህ የሚስማማ ቢመስልም ይሄ ግን ከህልም ይልቅ የለየለት ቅዠት መሆኑ ደግሞ ሊሰመርበት ይገባል። በጨለማው ዘመን ለጨለማው መሃበርተኞች የዘረኝነትና የድንቁርና ጉዞ በብርሃን አሻግረው የሚያልሙ እነርሱ ድህነትን ብቻ ሳይሆን አለማስተዋልን የደረቡ ከሰው ተርታ ብዙ እርቀት ላይ የሚገኙ ናቸው ለማለት ያስደፍራል። እርግጥ ነው ጨለማው በብረሃን እንደሚረታ የጨለማው መሃበርተኞች በብረሃን መልእክተኞች እንደሚሻሩ ምልክቶችን አይተው በየ አቅማቸው የዘረኝነትና የድንቁርናን ቀንበር እንዲሰበር የሚሰሩና ሚመኙ ዋሻው ጫፍ ላይ እንደሚታየው ብረሃን እየተጓዙ ስለሆነ እነርሱም በተስፋዎች ውስጥ ስለመሆናቸው እውነት ነውና ተስፋ ሁሉ ግን መሬት የረገጠ ምኞት ደሞ ጤዛ እንዳልሆነም ሊሰመርበት ይገባል።
የዛሬ አምስት አመት አይተን በጠገብነው ቲያትር ሰምተን በጠገብነው ጫጫታ ወንበራቸውን ለ አምስት አመታት በነፍጥ ተመክተው ..... የአምስት አመታት ትራንስፎርሜችን እቅድ ብለው ግርግር ፈጠሩ። በዚህም ሃገሪቱ በሁሉም መስክ በአምስት አመት ግዜ ውስጥ በከፍተኛ ደረጃ መነሳት እንደምትጀምር መንገዱ ሃዲዱ ፋብሪካው ሁሉ ደጃፍ እንደሚደርስ ተለፈፈ። የአፍሪካ ሃገራትን ጥለን በሱፐር ሶል ጀቶች ፍጥነት አየሩን ቀዝፈን መካከለኛ ገቢ ወዳላቸው ሃገራት መወንጨፍ እንደምንጀምር ለወራት ተነገረን ለአመታትም ቀጠለ ። በኪነጥበብ ባለሙያዎች አማካኝነት በሙዚቃ ድራማም ተገለጸልን። አምስት አመቱ ሲቃረብ ቢቀዘቅዝም። በነፍስ ወከፍ ገቢ በጣም እንደምንነሳ ብዙ ቢነገርም የሞላላቸው ወደ መቶሺ ዶላር ሲቆጥሩ እኛ አንድ ሺ ዶላር አቀበት ሆኖብን አምስት መቶ እንኳን መጠጋት አቅቶናል። አሁንም ከአለም ጠርዝ ቁጭ ብለን በወሬ ግን ከሁሉም በላይ መንሳፈፉን ቀጥለናል። የተግባር አቻዎቻችን እንደኛው ለነፍስ ወከፍ ገቢ ሶስት መቶ ዶላሮች ውስጥ የሚዳክሩት ብሩንዲ ላይቤርያ ኒጀር እና ኮንጎ መሆናቸው ቀርቶ ከመቶ ሾሺ በላይ የነፍስ ወከፍ ገቢ ከሚያስመዘግቡት ከነሞናኮ ሉክሰንበርግ ወዘተ ወደ ሰማንያ ሺ ዶላር ከተጠጉ ኖርዌይ ስዊድን በላይ ህዝቡን በታጠፈ አንጀቱ ሊያንጠራሩት ይዳክራሉ።
ወደ አምስት አመቱ የትራንስፎርሜሽን እቅድ እንመለስ።
የባእዳንን ኪስ ተማምነው ሃገሪቱን በወለድ አግድ አሲይዘው በሚገኝ ብድር እና መዋእለ ንዋይ ለመስራት ቃል የገቡትን ወደ ተግባር ለመለወጥ የተቸገሩት በአንድ በኩል ብድሩ በተባለው ፍጥነት እና መጠን አለመገኘቱን በሌላም በኩል የአቅም ውስኑነት እንዲሁም አበዳሪዎቹንና የብርዱ ሁኔታ አለመገምገም ከምንም በላይ ከግዙፍ ፕሮጀክቶች ጀርባ የህወሃት መሪዎች ለኤፈርት እና ለግላቸው በሚያተርፈው ጉዳይ ላይ ይበልጥ ማተኮራቸው የውጪ ምንዛሬውን የማሸሽ ሂደት ላይ በመጠመዳቸው ኢትዮጵያ በጋራ በሚያመጡ ልጆቻቸው ስም ጭምር የተወሰደው ብድር እዳውን እንጂ ውጤቱን ማየት አልቻሉም። የህዳሴን ግድብ ጨምሮ በመቋቋም ላይ ባሉ ሰባት ግዙፍ የስኳር ፋብሪካዎች እና ለሌሎችም ሲሚንቶና ብረታብረት በማቅረብና መንገድ በመጥረግ የህወሃቱ ኤፈርት ኩባንያዎች መሶቦ መስፍን ኢንጅረሪንግ እና ሱር ኮ ንስትራክሽን በሃገሪቱና በህዝቧ ስም በብድር ከሚመጣው የውጭ ምንዛሬ ከፍተኛ ሃብት እያፈሱ ሲሆን የህወሃት በግለሰብም ሆነ በቡድን ተጠቃሚ በማድረግ ሃገሪቱን የ ኢኮኖሚ የበላይነት አስተማማኝ አድርገው ለመጥረግ በመወሰናቸው በስኳር ኮርፖሬሽኖቹም በድምር በድልደላ ወዘተ ከውጪ ብድር እና ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሚታፈሰውን ገንዘብ የሚቀራመቱት ያለጨረታና ውድድር መንገዱ የተለቀቀላቸው የህወሃት መሪዎች የመንደር ልጆች ናቸው። ባጭሩ የትግራይ ተወላጆች ብለን ልናልፋቸው እንችላለን።
በኢትዮጵያ ውስጥ በንጉሱ ግዜ ጀምሮ መገንባት የጀመሩትን አራቱን የስኳር ፋብሪካዎች ደረጃቸውን ከፍ በማድረግ እንዲሁም ተጨማሪ ሰባት ግዙፍ ፋብሪካዎችን በመገንባት ሁሉንም እስከ 2007 ዓ.ም አጠናቀን ስኳር ወደውጪ በመላክ በቢልየን የሚቆጠር የውጪ ምንዛሬ እናገኛለን የተባው አንዱ ባይፈጸምም የህወሃት ኩባንያዎችና የህወሃት ሰዎች ሃብት እያፈሱ መሆናቸው ግን ግልጽ ነው።ለነዚህ ፕሮጄክቶች ከውጪ ብድር ከተገኘው ገንዘብ ባሻገር የኢትዮጵያ ህዝብ ንብረት ከሆነው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሃያ ቢሊየን ብር በላይ መወሰዱንም የባንኩ ምንጮች ይጠቅሳሉ። በለሳ አንድና በለሳ ሁለት እንዲሁም ኩራዝ አንድ ኩራዝ ሁለት ኩራዝ ሶስት እና ኩራዝ አራት እንዲሁም ወልቃይት እና ከሰም ስኳር ፋብሪካዎች ከ2006 በፊት ተጠናቀው ስራ እንደሚጀምሩ እና ኩራዝ አምስት ደሞ በዚህ አመት ተጠናቆ ወደገበያው እንደሚገባ የተነገረ ቢሆንም
አንዱም አልተሳካም። ለኢትዮጵያዊያን የሚያስፈልገውን አመታዊ የስኳር ፍጆታ ስድስት ነጥም አምስት ሚሊዬን ኩንታል ገደማ ግማሽ እንኳን ማሟላት አሁንም ባለመቻሉ በውጪ ምንዛሬ ስኳር ማስገባቱ ም ቀጥሏል። በአለማችን በነፍስወከፍ የስኳር ፍጆታ ኢትዮጵያችን/ ግርግዎስ/ ስገልጽ በሽታ ቀረብን የሚል የድንቁርና መከራከሪያ እንደሚኖር ታሳቢ በማድረግ ጭምር ነው።
በመንግስት የአምስት አመቱ የትራንስፎርሜሽን እቅድ ውስጥ ከተያዙት ሰባት የስኳር ፋብሪካ ፕሮጀክቶች ብድሩ ከውጪም ከሃገር ቤትም ከውጪም እየፈሰሰ ለፍጻሜ ባይደርሱም የህወሃት መሪዎች ከአምስት አመቱ የትራንስፎርሜሽን እቅድ በፊት የተጀመረውን እና የመንግስት ያልነበረውን ፕሮጀክት ከሰሞኑ በማስመረቅ ለምርጫው እየተሟሟቁ ይገኛሉ። ከሰባት አመት በፊት ወለጋ ውስጥ በፓኪስታናዊ ባለሃብት የተመሰረተው አርጆ ደዴሳ የስኳር ፋብሪካ የኩባንያው ባለቤት ከሶስት አመታት በፊት በመኪና አደጋ ሲሞቱ ግንባታው ዘጠና በመቶ የተጠናቀቀ ሲሆን ከሰውዬው ሞት በኋላ ፋብሪካው ወደ መንግስት በመዞሩ ቀሪው አስር በመቶ ባለፉት ሰስት አመታትአልቆ ለምረቃ ተዘጋጅቷል። ያቀዱት ባይሳካም ያላቀዱትን ያስረከቧቸውን የሟቹን ፓኪስታናዊ ሞሻህንጀን ነፍስ በገነት ወይም በጀነት ያቆይልን እያሉ ጫጫታ መፍጠሩ አይከፋም።
ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊያንን በጠመንጃ አግቶ ለሃያአራት አመታት በስልጣን ላይ የቆየው ይሄ ቡድም የአምስት አመቱ የትራንስፎርሜሽኑ እቅድ ባይሳካም አበዳሪዎቹም የተሸከማችሁት ብድር ከአቅማቹ በላይ ነው ብለው ብድር መስጠት ባቆሙበት በጨበጣ ሌላ የአምስት አመት የትራንስፎርሜሽን ዶሴ ሲጠርዙ ተዘጋጅቷል። እስከዚያ ለሟሟቂያ ምንም በሌለበት ነዳጅ መገኘቱን የተፈጥሮ ጋዝ የሃገሪቱን ከርሰምድር ማጨናነቁን ነግረውናል። ወሬው በደንብ ሳይብላላ የጋዝ መተላለፊያ ትቦ ተዘረጋ ብለው ፎቶግራፍ ለጠፉ። ጉዳዩ ሲመረመርም ፎቶው የተወሰደው ከሩስያ ወደ ዩ ክሬን ከተዘረጋው የጋዝ ቱቦ መሆኑን ተደረሰበት። ይባስ ብለው ተናበው ስለማይዋሹ እንኳን ጋዝ ሊገኝ ጋዝ የሚፈልገው ኩባንያዎች ስራ አለመግባታቸው ወይም አለመጀመራቸው በሌላ የመንግስት ባለስልጣናት አንደበት የተጋለጠበትንም ሁኔታ ታዝበናል። የህዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ መሪዎች ሁሌም የሚሰሙት ራሳቸውን ነው የሚያነቡትም ለነሱ ባለራእይ ለኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነትን ዘረኛና ማጣቀሻ የሆኑትን መለስ ዜናዊንና ፍልስፍናቸውን በመሆኑ ፍላጎትና ድርጊታቸው በራሳቸው ምህዋር ውስጥ ብቻ እንዲቀዝፉ አድርጓቸዋል። ሃገር ከተመለመሉ ደካሞችን ዲግሪ ገዝቶ በማደል?? አይገነባም። በመንደራቸው ፍቅር የተተበተቡና በኢትዮጵያዊነት ጭምብል ራሳቸውን ሸሽገው ዘረኝነትን በተከናነቡ የጎጥ ማህበርተኞች ሃገራይራይ ኢትዮጵያዊም አይከሰትም።ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊያንን የዘውድ ማስመለሻ መፎካከሪያ ሜዳ አድርገው ተፎካካሪው ልቆ በሄደበትና ሃያአንደኛው ክፍለዘመን ውስጥ በገባበት እነርሱ አስራዘጠነኛው ክፍለዘመን መጨረሻ ላይ ቆመው በቂም ፖለቲካ ተበክለው በጥላቻ በገነቡት ስረአት በደካሞች ተደግፈው ትራንስፎርሜሽ እያሉ ያላዝናሉ። በቂምና በጥላቻ በዛላይም ድንቁርና ተጨምሮ ስታግኔሽን እንጂ ትራንስፎርሜሽን አይኖርም።
ከቻይና የተገኘውን ጨምሮ ከሃያ ቢሊዮን ዶላር በላይ ብድር ከአርባ ቢሊየን ዶላር በላይ እርዳታ ያገኘ መንግስት ለማያዩ ብዙ እየሰራ ቢሆንም አይናቸው ለተገለጠ የሚከሰተው የዘረፋው ፍሰት ነው ። ስልሳ ቢሊየን ዶላር ማለት ግዙፉን የህዳሴ ግድብ አስር ገንብቶ ስኳር ፋብሪካዎቹ ለህንጻ እና ለመንገድ የሚተርፍ ከፍተኛ ገንዘብ ማለት ነው። ይህ ገንዘብ ለ እርሻና ለተለያዩ የንግድ እንቅስቃሴዎች ወደሃገር ቤት ገብተው ለመሬትና ለመሳሰሉት የሚከፍሉት የውጪ ምንዛሬ እንዲሁም አጠቃላይ ሃገራዊ ምርትን በውጪ ሃገር የሚኖሩ ኢትዮጵያዊ የሚልኩትን የውጪ ምንዛሬን አይጨምርም። አለመታደል ሆኖ አለማቀፉ ሁሌታ ፈቅዶ ለእድገትና ለብልጽግና መንገዱ የተከፈተበት ለግሎ ባላይዜሽን ዘመን መንደርተኞች እጅ ወድቀን በወሬ እየፋፋን በተግባር እየቀጨጭን ድህነትና ረሃብ በከተሞች ጭምር ተንሰራፍቷል። በወሬ ፊት ፊቱን እየተጣደፍን በተግባር ሃገራት ግርጌ ተቀምጠን በሁሉም መስክ ስርስሩን አጥብቀን ይዘናል።
አዎ ን እነዚህን መገላገል ከዘረኝነት የምንፈወስበት ከድንቁርና የምንፋታበት ብቻ ሳይሆን በርግጥ የምንለማበት ጭምር በመሆኑ በርግጥ ወስነው በረሃ የሚንከራተቱትን መንገድ ሲጀምሩ ስንቅ ማቀበል ይቻላል እና ተዘጋጅተን እንጠብቃቸው። ገብረጻዲቅ አበራ

Keine Kommentare:

Kommentar veröffentlichen