Netsanet: Oktober 2015

Samstag, 31. Oktober 2015

አይኔ አያየ እዚህ ዉስጥ አልገባም – መሠረት ሙሌ (ኤፍሬም ማዴቦ ከአርበኞች መንደር)

አይኔ አያየ እዚህ ዉስጥ አልገባም – መሠረት ሙሌ (ኤፍሬም ማዴቦ ከአርበኞች መንደር)
Ephrem Madebo
መብራቱን አጥፍቼዉ አልጋዬ ላይ የወጣሁት በግዜ ነዉ። አለወትሮዬ እንቅልፍ የሚባል ነገር በአይኔ አልዞር ብሎኝ ከጨለማዉ ጋር ፊት ለፊት ተፋጥጠናል። የነፋስ ሸዉታ እንኳን የማይሰማበት ደረቅ ሌሊት ነዉ። ጨላማዉ አይን ይበሳል። እቤቱ ዉስጥ ያለዉ ሰዉ ሁሉ ተኝቷል። ቀኑን በሠላም ላዋለኝ አምላክ ምስጋና ሰጥቼ ሌሊቱንም አደራ ብዬዉ ፀሎቴን ጨረስኩ። ያ ምቀኛ እንቅልፍ ግን አሁንም እንደከዳኝ ነዉ። ትንሿ አልጋዬ ላይ ግራ ቀኝ እያልኩ ተገለባበጥኩ። እንቅልፍ ተጎትቶ የሚመጣ ይመስል አሁንም አሁንም ላይ ታች እያልኩ አልጋዉ ላይ እራሴን ጎተትኩት . . . እንኳን እንቅልፍ ሊወስደኝ ጭራሽ አይኖቼ መርገብገባቸዉን ያቆሙ ይመስል ቀጥ ብለዉ ቀሩ። ከተጋደምኩበት ብድግ ብዬ መብራቱን አበራሁና ለመንገድ ከያዝኳቸዉ ሁለት መጻህፍት አንዱን አዉጥቼ ማንበብ ጀመርኩ። እኔ ላንብበዉ ወይ መጽሀፉ ያንብበኝ አላዉቅም። ጧት ስነሳ ግን “The Architecture of Democracy” የሚል መጽሐፍ ደረቴ ላይ ተለጥፎ ነበር። ሰዐቴን ሳየዉ ከሌሊቱ ስምንት ሰዐት ተኩል ይላል። ከአልጋዬ ላይ ዘልዬ ወረድኩና ሰዉነቴን ታጥቤ ልብሴን ከለበስኩ በኋላ መኪናዉ ዉስጥ ገብቼ “I’m ready” አልኩ። የመኪናችን መብራት ጨለማዉን እየገላለጠዉ የአስመራ ከረንን መንገድ ተያያዝነዉ። መኪናዉ ዉስጥ ከገባሁ በኋላ እንደገና አፌን የከፈትኩት ባሬንቱ ደርሰን ቁርስ ሳዝ ነዉ። ባሬንቱ በግዜ መድረሳችን ደስ ቢለኝም የቀረን መንገድ ርዝመት ታየኝና ቁርስ መብላቴን ትቼ . . . በሰዐት ይህን ያክል ብንጓዝ እያልኩ ዋናዉ ጉዳያችን ቦታ የምንደርስበትን ሰዐት ማስላት ጀመርኩ። የስሌቱ ዉጤት ከሦስት ሰዐት ሲበልጥብኝ ተናደድኩ። ቀሪዉ መንገድ ገና ሳልጀምረዉ ሰለቸኝ። በተፈጥሮዬ መንገድና መኃላ ሲረዝም አልወድም። ተሰነይ ስንደርስ መኪናዉ ዉስጥ የነበረዉ ሰዉ ሁሉ ቡና ካልጠጣሁ አለ። መኪናችንን አቁመን በቁማችን ቡናችንን ፉት አድርገን መንገዳችንን ተያያዝነዉ። እሁድ ጥቅምት 7 ቀን 2008 ዓም አርበኞች ግንቦት ሰባትን የፈጠሩት ሁለት ድርጅቶች ከተዋሃዱ በኋላ ለሁለተኛ ግዜ የሰለጠኑ ታጋይ አርበኞች የሚመረቁበት ቀን ነበር። ከዚህ ቀደም እንደዚህ አይነቱን የምርቃት ዜና የምሰማዉ በኢሳት ሬዲዮና ቴሌቭዥን ብቻ ስለነበር እቦታዉ ደርሼ የምረቃዉን ስነስርዐት ለማየት የነበረኝ ጉጉት እጅግ በጣም ከፍተኛ ነበር። የምሳ ሰዐት ከመድረሱ በፊት በቀኝ በኩል ዋናዉን መንገድ ለቅቀን ዉስጥ ዉስጡን ወደ ምርቃቱ ቦታ የሚወስደዉን ኮረኮንች መንገድ ተያያዝነዉ። ግቢዉ ዉስጥ ያለዉ ጥድፊያና ግርግር አንድ ትልቅ ዝግጅት መኖሩን በግልጽ ይናገራል። የተለያየ ወታደራዊ ዩኒፎርም የለበሱና መሳሪያ የተሸከሙ አርበኞች ግቢዉን ሞልተዉታል። ያነገቱትን ጠመንጃ ስመለከት ቆራጥነታቸዉ ታየኝ። በቀጭኑ ተጎንጉኖ ማጅራታቸዉ ላይ የወደቀዉን ፀጉራቸዉን ሳይ ቴዎድሮስና ዮሐንስ ትዝ አሉኝ። ፈገግታ በፈገግታ የሆነዉን ፊታቸዉን ስመለከት ደግሞ የእናት አገሬ ኢትዮጵያ ትንሳኤ ደጃፍ ላይ መሆኑ ታየኝና የኔም ፊት እንደነሱ በፈገግታ ተሞላ። ተራ በተራ እየመጡ “ጋሼ አፍሬም” እንደኳን ደህና መጣህ ብለዉ ሲጠመጠሙብኝ በአንዱ ትከሻዬ ፍቅራቸዉ በሌላዉ ጀግንነታቸዉ ዘልቆ ሰዉነቴ ዉስጥ ገባ። ጥንካሬያቸዉ በጅማቴ ፍቅራቸዉ በደም ስሬ ዘለቀ። እኔነቴ ሲታደስና በአገሬ ላይ ያለኝ ተስፋ ሲለመልም ተሰማኝና ደስ አለኝ። አዎ ደስ አለኝ . . . እየመጣ የሚሄድ ግዜያዊ ደስታ ሳይሆን የዉስጥ አካላቴን የዳሰሰ ዘላቂ የመንፈስ ደስታ ተሰማኝ። በጣም ደስ የሚልና በአሁኖቹ ቋንቋ “የሚመች” ቀን ነበር። የዕለቱን ዝግጅት ለማየት መቸኮሌን ያወቁት እግሮቼ የምረቃዉ በዐል ወደሚከበርበት ዳስ- ፍትህ፤ ነጻነትና እኩልነት የናፈቀዉ ልቤ ደግሞ ወደ ወደፊቷ ኢትዮጵያ ይዘዉኝ ጭልጥ አሉ፡ . . . ለካስ የወደፊቷ ኢትዮጵያ ሩቅ አይደለችም። “ማነዉ ሚለየዉ . . .ሚለየዉ፤ ይህም ትዉልድ ፍም እሳት ነዉ” የሚለዉን የጃሉድ ዘፈን በርቀት ሲሰማ በቀኑና በዘፈኑ መግጠም ተገረምኩ። “እዉነትም ይህ ትዉልድ ፍም እሳት ነዉ” እያልኩ በለሆሳስ ለራሴ እየነገርኩት ዳሱ ዉስጥ ገብቼ ቁጭ አልኩ። እርግጠኛ ነኝ ይህንን ጽሁፍ የሚያነብ ሰዉ ዳሱ ዉስጥ የነበረዉን ፍጹም ኢትዮጵያዊ የሆነ የጀግንነት፤ የቆራጥነት፤ የእልህና የመተማመን ልዩ ስሜት መረዳት የሚችለዉ እኔ በዚህ ባልተባ ብዕሬ ስገልጸዉ ሳይሆን እንዳዉ በደፈናዉ ዳሱ እራሱ ኢትዮጵያዊ ነበር ብዬ ባልፈዉ ነዉ። አገራችን ኢትዮጵያ ከራሱ ምቾትና የተደላደለ ኑሮ ይልቅ የወገኖቹ መብትና ነጻነት የሚያንገበግበዉና እራሱን ለፍትህ፤ ለአንድነትና ለነጻነት ለመሰዋት ዝግጁ የሆነ የየዘመኑ ምርጥ ትዉልድ አላት። ይህንን የኛን ዘመን ምርጥ ትዉልድ ነዉ አርቲስት ጃሉድ “ይህም ትዉልድ ፍም እሳት ነዉ” ብሎ በጣፋጭ ዜማዉ ያወደሰዉ። እኔ ጥርጥርም የለኝ ይህ ትዉልድ አንድና ሁለት ብቻ ሳይሆን ለቁጥር የሚታክቱ ብዙ ፍም እሳቶች አሉት። ችግሩ የእሳት ነገር አዚህ ቤት ነደዳ እዚያም ቤት ነደደ ስራዉ ማቃጠል ነዉና አንዱን እሳት ከሌላዉ እሳት መለየት አስቸጋሪ ነዉ። እኔም ችግሬ እዚህ ላይ ነዉ። ፊት ለፊቴ ላይ ቁጭ ብለዉ ስለማያቸዉ ፍም እሳቶች (ጀግኖች) ላወራችሁ እየፈለኩ ምርጫዉ አዋጅ ሆነብኝ. . . የራሱ ጉዳይ ብዬ አንዱን ጀግና መረጥኩ። ይህንን ዛሬ የምተርክላችሁን ጀግና ስመርጥ ግን እንዳዉ በደፈና አልነበረም። ጉዳይ አለኝ . . . . ጉዳዩ አንዲህ ነዉ። በዕለቱ በተመራቂ አርበኞች ተዘጋጅተዉ ከቀሩቡት የተለያዩ የኪነት ስራዎች ዉስጥ አንዱ የድራማ ዝግጅት ነበር። ሦስት የተለያዩ ድራማዎች መታየታቸዉ ትዝ ይለኛል። ዳሱ ዉስጥ የተሰበሰበዉን በብዙ መቶዎች የሚቆጠር ሰዉ ስሜት የኮረኮረዉና የእያንዳንዱን ሰዉ የልብ ትርታ ሰቅዞ የያዘዉ ግን በእዉነተኛ ታሪክ ላይ ተመስርቶ የተከወነዉ የመጨረሻዉ ድራማ ነበር። ድራማዉ ኢትዮጵያ ዉስጥ በተለይ ሰሜን ኢትዮጵያ ዉስጥ የአርበኞች ግንቦት 7 አባላት ናችሁ እየተባለ በየቀኑ በህወሃት የደህንነት ሠራተኞች እጃቸዉ እየታሰረ በየወንዙና በየፈፋዉ በግፍ እየተገደሉ ስለሚጣሉ ኢትዮጵያዉያን የሚተርክ ድራማ ነበር። ድራማዉ “ኮሜዲ” የሚባል ክፍል የለዉም። ተጀምሮ እስኪያልቅ “ትራጄዲ” ብቻ ነዉ። ያሳዝናል፤ ያስቆጣል፤ ያስቆጫል፤ያንገበግባል፤ አንጀት ያቆስላል፤ ልብ ያነድዳል . . . ወይ ነዶ ያሰኛል ። እኔማ እንኳን ትራጄዲ አይቼ በተፈጥሮዬ ሆደ ቡቡ ነኝና በደል ስመለከት ማዘን ልማዴ ሆኖ አምባዬ መፍሰስ የጀመረዉ ገና ድራማዉ ሲጀምር ነበር። በተለይ አናታቸዉ እየተደበደበ የሚቀበሩበትን ጉድጓድ በግድ እንዲቆፍሩ የተደረጉትን ሁለት ወጣት ወገኖቼን ሳይ ሆዴ ባባ፤ አንጀቴም ቆሰለ። ልቤ ዉሰጥ የነደደዉ እሳት ትንታጉ እየተንቦገቦገ ወጥቶ የዉጭ ሰዉነቴን ጭምር ለበለበዉ። ለወትሮዉ ነገር ማመዛዘን የሚቀድመዉ አዕምሮዬ በቀል በቀል አሰኘዉ። የነደደዉ ልቤም ለበቀል አደባ። ጉድጓዱ ተቆፍሮ ካለቀ በኋላ የደህንነት ሠራተኛዉ AK ጠመንጃዉን አንደኛዉ ወጣት አገጭ ላይ ቀስሮ በአፈሙዙ አንገቱን ቀና እንዲያደርግ እያስገደደዉ . . . “አየኸዉ የምትገባበትን ጉድጓድ” እያለ ወጣቱ ወገኔ ላይ ሲሳልቅበት ሰማሁና በሀይወቴ ለመጀመሪያ ግዜ ኢትዮጵያዊነቴን ጠላሁት። አጠገቡ የቆመዉና በቁሙ ሞቱን የሚጠባበቀዉ ሌላዉ ወጣት ወገኔ ደግሞ . . . ግደለኝ . . . ግደለኝ. . . ግደለኝ እንጂ! . . . ምን ትጠብቃለህ እያለ የጓደኛዉን ሞት በአይኑ ከሚያይ የራሱን ሞት የሚለምነዉን ቆራጥ ኢትዮጵያዊ ድምጽ ስሰማ ደግሞ 360 ዲግሪ ተገለበጥኩና ከደቂቃዎች በፊት የጠላሁትን ኢትዮጵያዊነት መልሼ ወድድ አደረኩት። የወያኔዉ ጨካኝ ነብሰ ገዳይ ፉከራና ቆራጡ ኢትዮጵያዊ ያደረጉት የቃላት ምልልስ እምባዬን ጎትቶ አመጣዉና ፊቴ እምባ በእምባ ሆነ። ያ ከግማሽ ሰዐት በፊት ሲጨፈርበትና ሲደነስበት የነበረዉ ዳስ ሰዉ የሌለበት ባዶ ቤት ይመስል ጭጭ አለ። እኔ ኤፍሬም ሰዉ አልገድልም፤ በእኔ እጅ የሰዉ ህይወት ይጠፋል ብዬ አስቤም አልሜም አላዉቅም። ያንን የህወሃት ቅጥረኛ በዚያች ሰዐት ባገኘዉ ኖሮ ግን ለመበቀል ሳይሆን ለሰዉ ልጅ ህይወት ክብር ስል እገድለዉ ነበር። ድራማዉ እንዳለቀ ወደ ዉጭ ወጣሁና ድቅድቅ ጨለማ ዉስጥ ብቻዬን ቁጭ አልኩ። ሀሳብ. . . የትናንት ሀሳብ፤ የዛሬ ሃሳብ፤ የነገ ሀሳብ፤ የከረመ ሀሳብና ሁሉም ሀሳብ አንድ ላይ ተሰባስበዉ ወረሩኝ። ግራ ሲገባኝና መላቅጡ ሲጠፋኝ ግዜ ትንፋሼን ዋጥ አደረኩና አንቺ እማማ ብዬ አገሬን ተጣራሁ . . . አሁንም አሁንም ደግሜ ተጣራሁ። ህመሟ ብርቱ ነበርና አልሰማችኝም። አይዞሽ ይህ ቀን ያልፍና አንቺም ከህመምሽ እኔም ከማያባራዉ የሀሳብ በሽታ ድነን አዲስ ታሪክ እንጽፋለን ብዬ ከአገሬ ጋር ቃል ኪዳን ገባሁና ከተቀመጥኩበት ተነስቼ ዳሱ ዉስጥ ከነበሩት አርበኞች ጋር ተቀላቀልኩ። እለቱን ሲያስጨፍረን የዋለዉ አደራ ባንድ “ነይ ደኑን ጥሰሺ” የሚለዉን ቆየት ያለ የመሀሙድ አህመድ ዘፈን ሲጫወት ልጅነቴ ትዝ አለኝና ከፍም እሳቶች ጋር መደነስ ጀመርኩ። ጭልጋን ይዞ፤ጋይንትን ይዞ፤ የጎበዞቹን ጎራ ጃናሞራን ይዞ፤ ደምቢያን ይዞ፤ ወልቃይት ጠገዴን ይዞ፤ ላይ አርማጭሆንና ታች አርማጭሆን ይዞ ወዘተ . . .ድፍን ጎንደር የጀግኖች አገር ነዉ። አዎ! ወልቃይት ጠገዴ ከጀግናም የጀግና አገር ነዉ።ወልቃይት ጠገዴ ጎንደሬ አይደለህም ተብሎ ከተነገረዉ ከሃያ አራት አመታት በኋላ ዛሬም ህልዉናዉን ለወያኔ ፋሺስቶች አላስረክብም ብሎ ጎንደሬነቱን ለማረጋገጥ ሽንጡን ገትሮ የሚዋጋ የጀግኖች አገር ነዉ። ጎንደር የአፄ ቴዎድሮስ፤ የእቴጌ ምንትዋብ፤ የፊትአዉራሪ ገብርዬ፤ የአየለ አባ ጓዴና የጄኔራል ነጋ ተገኝ አገር ናት። ጎንደር ኢትዮጵያ ከሌለች እኛ የለንም ብለዉ ሙሉ ህይወታቸዉን ለትግል የሰጡ እነ ታማኝ በየነንና እነ አርቲስት ሻምበል በላይነህን ያበቀለች አገር ናት። ወላድ በድባብ ትሂድ. . . የጎንደር ማህፀን ዛሬም አልነጠፈም። ዛሬ ይዤላችሁ የመጣሁት ጀግና ተወልዶ ያደገዉ አማራ ክልል ጭልጋ ወረዳ ልዩ ስሟ ጫኮ በምትባል ቦታ ነዉ። የገበሬ ልጅ ነዉ፤ እሱም ምኞቱ ገበሬ መሆን ነዉ። የሚኖረዉ መተማ ከተማ ዉስጥ ነዉ። ስሙ መሠረት ሙሌ ይባላል። ፈገግታ የማይለየዉ ፊቱ የዋህነቱንና ገራገርነቱን አፍ አዉጥቶ ይናገራል። ሲናገር ረጋ ብሎ ነዉ። አተኩሮ ላየዉ ሰዉ አይነ አፋር ይመስላል፤ የቁርጥ ቀን ሲመጣ ግን እንደ መሠረት ሙሌ ደፋር ሰዉ የለም። አይኑ እፊቱ ላይ ቆሞ ከሚያናግረዉ ሰዉ አይን ጋር ሲጋጭ አንገቱን ይሰብራል። እቺ የሰዉ አይን የመሸሽ በሽታ ደግሞ አበሾች ስንባል የሁላችንም በሽታ ናት። ጠይም ፊቱ ላይ እንደ ችቦ የተተከሉት የመሠረት ሙሌ አይኖች የሰዉን ዉስጥ ዘልቀዉ የሚያዩ ይመስላሉ። ሰዉነቱ ደንዳና ቁመቱ መካከለኛ ነዉ። ልቡ ግን ትልቅ ነዉ። አዎ መሠረት ሙሌ ልቡ ትልቅ ነዉ። ዕለቱ ሰኞ ነዉ – ሰኞ ሚያዝያ 26 ቀን 2007 ዓም። የህወሃት የደህንነት ሰዎች አንድ ኮሎኔልና ሌሎች አራት ሰዎች ተገድለዋል በሚል ድፍን መተማን እያመሷት ነዉ። እያንዳንዱ የመተማ ነዋሪ በግድያዉ የተሳተፈ ይመስል በአጠገባቸዉ ያለፈዉን ሁሉ ወንድ፤ ሴት፤ ወጣትና ሽማግሌ ሳይለዩ ሁሉንም እያስቆሙ አጥንት ዉስጥ ዘልቆ የሚገባ ስድብ ይሰድባሉ፤ ይደበድባሉ ያስራሉ። በሠላም አዉለኝ ብሎ በጧት የተነሳዉ መሠረት ሙሌ የእህል ወፍጮዉን አስነስቶ የዕለት ስራዉን ለመጀመር ጉድ ጉድ ማለት ጀምሯል። ሴቶች እህላቸዉን ያስመዝናሉ። ሸክም የተራገፈለት አህያ ያናፋል። ነጋዴዉ፤ ደላላዉ፤ ገበሬዉና ሸማቹ ዋጋ ቀንስ ዋጋ ጨምር እያሉ ይንጫጫሉ። መተማ መደበኛ ስራዋ ላይ ናት። “ቁም . . . እጅ ወደ ላይ . . . እንዳትነቃነቅ” የሚል ድምጽ የደራዉን የመተማ ገበያ በአንድ ግዜ ጭጭ አሰኘዉ። መሳሪያ ያነገቡ ፖሊሶችና ሲቪል የለበሱ የደህንነት ሰራተኞች ከመኪና እየዘለሉ ወርደዉ መሠረትን የፊጥኝ አስረዉ መኪናዉ ላይ ወረወሩት። ምነዉ? ምን አጠፋሁ . . . ዬት ነዉ የምትወስዱኝ? አለ መሠረት በሁኔታዉ እጅግ በጣም ተደናግጦ። አንድ አጠገቡ የነበረዉ የህወሃት ነብሰ ገዳይ . . . ዝም በል ብሎ በጥፊ አጮለዉና ለአርበኞች ግንቦት 7 የመለመልካቸዉን ሰዎች አድራሻና ስም ዝርዝር ካላመጣህ ዕድሜህ ከአንድ ጀምበር አያልፍም አለዉ። መኪናዉ ዉስጥ ከተቀመጡት ሁለት ሰዎች አንደኛዉ አንሂድ ብሎ በእጁ ምልክት ሲያሳይ መሬት ላይ የነበሩት ፖሊሶች እየዘለሉ መኪናዉ ላይ ወጡና መሠረትንና ሌሎች ሦስት እስረኞችን የያዘችዉ ቶዮታ ሂሉክስ መኪና ፍጥነት እየጨመረች የመተማ ሁመራን መንገድ ተያያዘቸዉ። በሚቀጥለዉ ቀን ጧት ሲነጋጋ ሁመራ ደረሱና አራቱ እስረኞች እጃቸዉ እንደታሰረ ፖሊስ ጣቢያ እንዲቆዩ ተደረገ። ከምሽቱ ሦስት ሰዐት ሲሆን መሠረትና ጓደኞቹ እጅ ለእጅ እንደተሳሰሩ ጉዞ ወደ ተከዜ ወንዝ ሆነ። የዚህች ከንቱ አለም የመጨረሻ ጉዟቸዉ ነበር። ዶማና አካፋ ያዙ እንጂ . . . ደግሞም ፈጠን በሉ ግዜ የለንም. . . አለ የነብሰ ገዳዮቹ አለቃ። ከሁመራ ፖሊስ ጣቢያ ወደ ተከዜ ወንዝ የሚያደርገዉ ጉዞ በህይወቱ የመጨረሻዉ ጉዞ እንደሆነ የተረዳዉ መሠረት . . . አንተዬ ልትገድሉን ነዉ እንዴ ብሎ ጠየቀ። ፊት ለፊቱ የነበረዉ ፖሊስ ከተቀመጠበት ዘልሎ ተነሳና . . .ዝም በል . . . አንተ የሴት ልጅ . . . ምን አስቸኮለህ ይልቅ የተጠየከዉን ጥያቄ መልስ አለዉና የያዘዉን የእጅ መከርቸሚያ ካቴና ፊቱ ላይ ወረወረበት። ካቴናዉ ሳይሆን ከዚያ ባለጌ አፍ የወጡት ቃላት ጅማቶቹ ድረስ ዘልቀዉ ገብተዉ መንፈሱን ጎዱትና መሠረት ለመጀመሪያ ግዜ ተስፋ ቆረጦ . . . ምንም የምሰጥህ መልስ የለኝም አለና አንገቱን ደፋ። . . . አንቺ ወላዲት አምላክ ምነዉ . . . ምን አደረኩሽ ብሎ ቀና ሲል እሱንና ሦስት ጓደኞቹን ለመዋጥ አፋቸዉን ከፍተዉ የሚጠባበቁትን አራት ጉድጓዶች ተመለከተ። አይኔ እያየ እዚህ ወስጥ አልገባም ብሎ ንግግሩን ሳይጨርስ ተከታታይ የጥይት ድምጽ ሰማ። ዞር ሲል ፖሊሶች አብረዉት ከታሰሩት ሦስት እስረኞች ዉስጥ አንዱን በእግራቸዉ እየገፉ የተቆፈረዉ ጉድጓድ ዉስጥ ሲጨምሩት አየ። ደቂቃዎች የቀሩት የሱ የራሱ ህይወት ሳይሆን በህወሃት ነብሰ ገዳዮች በግፍ የተገደለዉ የጓደኛዉ ህይወት አንገበገበዉ። አዘነ – በአይኑም በሆደም አነባ። “አይኔ እያየ እዚህ ወስጥ አልገባም” ብሎ የተናገረዉ የራሱ ድምጽ ጆሮዉ ላይ አቃጨለበት። መሠረት ሞት ፈርቶ አያዉቅም፤ ግን ህይወቱ የህይወትን ክቡርነት በማይረዱ ባለጌዎች እጅ እንድታልፍ አልፈለገም። ያ የንጹሃን ኢትዮጵያዉያንን ሰዉነት ማፍረስ የለመደዉ የህወሃት ጠመንጃ ወደሱ ከመዞሩ በፊት አንድ ነገር ማድረግ አለብኝ ብሎ ወሰነ። እጁ ከጓደኛዉ ጋር የታሰረበትን ገመድ በጥርሱ በጣጠሰዉና ከቀለሁ እንደተላቀቀ ጥይት ተወርዉሮ እግሬ አዉጭኝ ብሎ ጫካ ዉስጥ ዘልሎ ገባ። የህወሃት ነብሰ ገዳዮች የጥይት ናዳ ለቀቁበት፤ እሱ ግን ጫካ ጫካዉን ይዞ ወደማያዉቀዉ ቦታ ሩጫዉን ተያያዘዉ። መሠረት- ቆራጥነቱና የልቡ ትልቅነት ጉልበት እየሆኑት ነዉ እንጂ ያ የሚጠላዉ የህወሃት ጥይት አካሉን በሳስቶ ወንፊት አድርጎታል። ሰዉነቱ ቁስል በቁስል ሆኗል። ከራሱ ሰዉነት እንደ ጎርፍ የሚፈስሰዉ ደም ጠልፎ የሚጥለዉ እስኪመስለዉ ድረስ አካሉ ደምቷል። ሩጫዉን ግን አላቆመም። ደም እንዳይፈሰዉ ጥይት የበሳዉን ቦታ ሁሉ በሁለት እጆቹ ሸፈነ። እንደኛዉ ቁስል ጋብ ሲልለት እጁን ከሱ ላይ እያነሳ ሌላዉን ቁስል ሸፈነ። ደሙ መፍሰሱን ግን አላቆመም። መሠረትም ሩጫዉን አላቆመም። መሠረት ሙሌ ህይወቱን ለማዳን ወደ ፊት የህወሃት ነብሰ ገዳዮች ደግሞ ወንጀላቸዉን ለመደበቅ ወደኋላ በተለያየ አቅጣጫ ሩጫቸዉን ተያያዙት። ሁለቱም አግሬ አዉጭኝ አሉ። መሠረት ሞትን እየሸሸ መሆኑን ነዉ እንጂ ከሞት ለመራቁ ምንም ዋስትና አልነበረዉም። ደግሞም መሮጡን ብቻ ነዉ እንጂ ወዴት እንደሚሮጥ አያዉቅም ነበር። ከኋላዉ የሚከተለዉ ማንም ሰዉ እንደሌለ ቢረዳም ከፊት ለፊቱ ህይወቱን የሚታደግለት ሰዉ እስኪያገኝ ድረስ ሩጫዉን ቀጠለ። ጧት ጎህ ከመቅደዱ በፊት “ጠጠዉ በል” የሚል ድምጽ ሲሰማ ያ ሁሉ ሩጫዉ መልሶ ሞት ዉስጥ የከተተዉ መሰለዉና ደነገጠ። ሩጫዉን እንዳይቀጥል ቁም ያሉት ሰዎች ከበዉታል። እሺ ብሎ እንዳይቆም ሞትን አልቀበልም ያለዉ ልቡ አሁንም እንደደነደነ ነዉ። ትንፋሹን ሰበሰበና. . . ማናችሁ እናንተ ብሎ ያቆሙትን ሰዎች ጥያቄ ጠይቆ መልሱን ሳይሰማ ተዝልፍለፎ መሬቱ ላይ በግንባሩ ተደፋ። የኤርትራ ድንበር ጠባቂ ወታደሮች መሠረትን አንድ ወር ሙሉ በህክምና ሲንከባከቡት ቆዩና እሱ እራሱ በጠየቃቸዉ መሠረት ሃሬና ወስደዉ ለአርበኞች ግንቦት 7 አስረከቡት። መሠረት ሙሌ ጥቅምት 7 ቀን ከተመረቁት አርበኞች ዉስጥ አንዱ ነዉ። ለዚህ ጀግና ያቀረብኩለት የመጨረሻ ጥያቄ . . . ሊገድሉህ የነበሩትን የህወሃት ሰዎች አሁን ብታገኛቸዉ ምን ታደርጋቸዋለህ የሚል ጥያቄ ነበር። ነጻ አወጣቸዋለኋ! አለኝና ጭፈራዉ ዉስጥ ዘልሎ ገባ። አርግጠኛ ነኝ መሠረት ሙሌ አንድ ቀን ሁላችንንም ሸገር ላይ ያስጨፍረናል። ቸር ይግጠመን። ኤፍሬም ነኝ ከአርበኞች መንደር 

Dienstag, 13. Oktober 2015

የኢትዮጵያ መንግሥት ገመና – ጋዜጠኛ ተመስገን ደሣለኝ (ከዝዋይ እስር ቤት)




በዚህ አውድ ለማቅረብ የተገደድኩበትን ዘግናኝ ታሪክ፣ ወደር በሌለው አስከፊነቱ የተነሳ ለንባብ ባላበቃው በወደድኩ ነበር፡፡ ግና! ይህ መንግስታዊ የጭካኔ ተግባር፣ ዛሬም በምስኪን ዜጎች ላይ እየተፈፀመና ብዙዎችን ሰለባ እያደረገ በመሆኑ ህዝቡ ይህን ሊሸሸግ እየተሞከረ ያለውን መከራ ተረድቶ ሥርዓቱን በአደባባይ ዓመፅ “ሃይ!” ይል ዘንድ ትርክቴን ለማጠናቀር ተገድጄያለሁ፡፡ ለእስር ያበቃኝ የጋዜጠኝነት ሙያዬም ተጨማሪ ዕዳ ጭኖብኛል፡፡
“ጄል-ኦጋዴን”
ጄል ኦጋዴን በሱማሌ ክልል ርዕሰ-መዲና የሚገኝ፤ ለ800 እስረኞች ታቅዶ በ1992 ዓ.ም የተገነባ እስር ቤት ነው፡፡ የግቢውን ዙሪያ ከከበበው አጥር በግምት 15 ሜትር ፈንጠር ብሎ ሌላ ተደራቢ የድንጋይ አጥር ተበጅቶለታል፡፡ እስከ ሚያዝያ 24 1999 ዓ.ም ድረስ እስር ቤቱ በሌሎች የሀገሪቱ አካባቢዎች ካሉ መሰል ማጎሪያዎች ብዙም የተለየ አልነበረም፡፡ በዚህ በተጠቀሰው ቀን የኦጋዴን ነፃ አውጭ ግንባር (ኦብነግ) ታጣቂዎች፣ አቦሌ እና ሰንደሬ ወታደራዊ ካምፖችን ጨምሮ፣ በነዳጅ ዘይት ፍለጋ ላይ የተሰማሩ ቻይናውያን ባለሙያዎች መኖሪያ ሰፈር ላይ የሰነዘሩትን ከባድ ጥቃት ተከትሎ የፖለቲካ እስረኞች ብቻ የሚታጎሩበት እስር ቤት ከሆነ ወዲህ ግን በዋይታ የሚናወፅና በደም ጅረት የሚጥለቀለቅ ምድራዊ ሲኦል ለመሆን በቅቷል፡፡
መንግስት በጥቃቱ ከዘጠኙ ቻይናውያን ጋር 74 ሲቪል ዜጎችና ወታደሮች መገደላቸውን ቢያምንም፤ የአካባቢው የአይን እማኞች ከሰራዊቱ ብቻ እስከ 300 እንደተሰዉ ይናገራሉ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ኦብነግ እንደ አል-ቃይዳ እና አል-ሸባብየአባላቱን አስከሬን ትቶ የመሸሽ ልምድ ስለሌለው በቡድኑ ላይ የደረሰውን ጉዳት በትክክል ለማወቅ አዳጋች እንደሆነቀጥሏል፡፡
የሆነው ሆኖ ከዚህ ጥቃት በኋላ በቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስቴር መለስ ዜናዊ የሚመራ አምስት ከፍተኛ ባለስልጣናትን ያካተተ የደህንነትና (ጄነራል ሳሞራ የኑስ እና ጌታቸው አሰፋ ያሉበት) የፀጥታ ኮሚቴ ተቋቁሞ የሚከተሉትን(ዛሬም ድረስ እየተተገበሩ ያሉ) አስቸኳይ ውሳኔዎችን አስተላልፏል፡፡ ‹‹ከጅጅጋ ውጭ ባሉ በክልሉ ማንኛውም የመንግስትም ሆነ የግል ተሽከርካሪ እንዳይንቀሳቀስ፣ ትዕዛዙን ጥሶ የተገኘ ከነጭነቱም ሆነ ተሳፋሪዎቹ በከባድ መሳሪያ እንዲመታ፤ አብዛኛውን ህዝብ በፍጥነት ከመኖሪያ ቀዬው በማፈናቀል ለቁጥጥር ወደሚያመቹ ከተሞች ማስፈር (በ2006 ዓ.ም መጀመሪያ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ካሳ ተክለብርሃን 2300 መንደሮችን ወደ ተመረጠ ቦታ ማስፈሩ እንደተሳካ መናገሩን ልብ ይሏል)፤ ወታደራዊ መኪና ላይ ምንም አይነት የደፈጣ ጥቃት ከደረሰ በአቅራቢያው የሚገኝ መንደርን ያለርህራሄ ማውደም (ለማሳያ ያህልም ፍልቼ፣ ቃሙዳ፣ ሳስባኒ፣ ሁለሌ፣ ለንካይርተ፣ ቻለሌን… የመሳሰሉ ከተሞች ወደ ፍርስራሽነት መቀየራቸውን መጥቀስ ይቻላል) እና ከአንድ ሻምበል ያነሰ ኃይል ለአስቸኳይ ጉዳይም ቢሆን ከቦታ ቦታ እንዳይንቀሳቀስ›› የሚል እንደነበር ይታወሳል፡፡ ከዚህ በኋላም ኤታማዦር ሹሙ ጄነራል ሳሞራ የኑስ በክልሉ የሚገኘውን የደቡብ ምስራቅ ዕዝ ወታደራዊ አዛዦችን በቪዲዮ ኮንፈረንስ ሰብስቦ ማብራሪያ ሰጥቶ ሲያበቃ ውሳኔውን ያለምንም ማቅማማት ተግባራዊ እንዲያደርጉት በጥብቅ አሳስቧል፡፡
ደቡብ ምስራቅ ዕዝ ከኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት (ከ1993 ዓ.ም) በኋላ በምስራቅ ኢትዮጵያ የሰፈረ ሲሆን እስከ ታህሳስ 1999 ዓ.ም ድረስ በሜ/ጀነራል ባጫ ደበሌ ሲመራ ቆይቷል፡፡ ከታህሳስ 1999 እስከ 2000 ዓ.ም ደግሞ ብርጋዴር ጄነራል ስዩም አስተዳድሮታል፤ በዚሁ ዓመት ከጥቅምት እስከ ሚያዚያ ድረስ ባሉት ጊዜያትም በብ/ጄነራል ሙሉጌታ በርሄ ስር የቆየ ሲሆን፤ ከሚያዚያ 2000 ዓ.ም አንስቶ አሁን ድረስ እየተመራ የሚገኘው በሌ/ጄነራል አብርሃም ወ/ማርያም (ቅፅል ስሙ ‹‹ኳርተር››) እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ከዚህ ዕዝ ውስጥ በዋናነት ሶስት ክፍለ ጦሮች (12ኛ፣ 13ኛ እና 32ኛ) ክልሉን ሶማሊያ ድንበር ድረስ እንዲቆጣጠሩት ተመድበዋል፡፡ ሰፈራቸውን ነገሌ ቦረና ያደረጉት 43ኛ እና 44ኛ ክፍለ ጦሮችም፣ ኦጋዴን ድረስ እንዲንቀሳቀሱ ትዕዛዝ ተሰጥቷቸዋል፡፡ በአናቱም የአግአዚ ኃይል በቀድሞ ምክትል አዛዡ ብ/ጄኔራል ገ/መድህን ፈቀደ (‹‹ወዲ ነጮ››) ስር ሆኖ አልፎ አልፎ በተደራቢነት እየተላከ በነዋሪዎቹ ላይ በደረሰው ጅምላ ጭፍጨፋ እና ዘግናኝ የሰብዓዊ መብት ጥሰት የተሳተፈ ስለመሆኑ ከወታደራዊ መረጃ ምንጮቼ ሰምቻለሁ፡፡ 
ይህም ሆኖ ለደረሱ እልቂቶችና ጭፍለቃዎች በግንባር ቀደምትነት ተጠያቂ ተደርገው የሚጠቀሱት ከጄነራል ሳሞራ፣ ከጀኔራል ‹‹ኳርተር›› እና ከክልሉ ፕሬዝዳንት በተጨማሪ በብ/ጄነራል በየነ ገ/እግዚአብሔር (‹‹ወዲ አንጥር››) የተመራው 12ኛ ክ/ጦር እና በብ/ጄነራል ፀጋዬ ገ/ጨርቆስ (‹‹ጀብጀብ››) ዕዝ ስር የነበረው 13ኛ ክ/ጦር እንደሆነ ይነገራል፡፡ ኦብነግ በስፋት
ይንቀሳቀስባቸዋል ተብለው የሚታሰቡት፡- ደገሃቡር፣ ቀብሪደሃር፣ ዋርደር፣ ጎዴ እና ቪቅ ከተሞች መደበኛ የጦር ቀጠናዎች ከሆኑ 15 አመት ያለፋቸው በመሆኑ፣ ከሌሎች የክልሉ አውራጃዎች በተለየ ሁኔታ የችግሩ ቀጥተኛ ተጠቂ ሆነዋል፡፡ የኢትዮጵያ መንግስትም የሚፈፅማቸውን ኢ-ህገ መንግስታዊ ድርጊቶች ለመሸፈን እንደ ቀይ መስቀል፣ ዓለም- አቀፍ ሚዲያዎች፣ ግብረሰናይ ድርጅቶችና መሰል ተቋማት ከጅጅጋ ውጪ እንዳይንቀሳቀሱ በኃይል አግዷል፡፡

ይህ ኩነትም በ ዙ-23 እና በሌሎች ከባድ መሳሪያዎች ተደብድበው ከምድረ-ገፅ የጠፉ መንደር ነዋሪዎች፣ የቤት እንስሳት እና ቁሳዊ ንብረቶች በአንድነት ተቃጥለው መውደማቸውን ዛሬም ድረስ በምስጢርነት ሸሽጎ ለማቆየት አስችሎታል፡፡ የሆነው ሆኖ የመከላከያ ሰራዊቱ እና በክልሉ ከ70-80 በመቶ በሚሆኑ አካባቢዎች ላይ መንቀሳቀስ የቻለው ኦብነግ፣ ቢያንስ በሳምንት አንድ ጊዜ ከባድ ውጊያ እንደሚያደርጉ ይታወቃል፡፡ በእርግጥ ግጭቱ አሁንም ሳያበራ የመቀጠሉ ምክንያት አማፂው ቡድን ያን ያህል ከመንግሥት አቅም በላይ ሆኖ አይደለም፤ ይልቁንም የጄነራሎቹ እጅ በዘወርዋራ ስላለበት መሆኑን ወታደራዊ ምንጮቼ ያስረግጣሉ፡፡ ‹‹የኦብነግ ህልውና በተለይም ለከፍተኛ መኮንኖች ዋነኛ ንግድ (ቢዝነስ) ነው›› ይላሉ፡፡
 የክልሉ መንግስት ‹‹የመረጃ እና ፀጥታ ባጀት›› በሚል ሽፋን በዓመት የሚመድበውን ከ30 ሚሊዮን ብር በላይ የህዝብ ሀብት እንዲያወራርዱ አዛዦቹ አይገደዱም፡፡ መከላከያ ራሱም ‹‹የመረጃ እና የበረሃ ፍሳሽ›› በሚል የሚበጅተው አመታዊ ወጪ በብዙ ሚሊዮን ብሮች የሚቆጠር እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ይህ በጀት እስከ ኃይል አመራሮች ድረስ ወርዶ እንደየድርሻቸው መጠን የሚመዘበርበት አሰራርም ተዘርግቶለታል፡፡ እናም ጀነራሎቹ ኦብነግ ሙሉ በሙሉ ተወግዶ የገቢ ምንጫቸው እንዳይደርቅም ሆነ፤ ከአቅም በላይ ተጠናክሮ በብቃት ማነስ እንዳያሳጣቸው (እንዳያስወቅሳቸው) ተቆጣጥረው ለመዝለቅ የቻሉበትን ቀመር እንዲከተሉ ይህ የገቢ ምንጭነት ገፊ ምክንያት መሆኑ ይነገራል፡፡ ሌላው ቀርቶ ከመከላከያ ሠራዊቱ እና ከፌዴራል ፖሊስ በተጨማሪ በቀጥታ የክልሉ አስተዳደር የሚያዝዘውና ‹‹ልዩ ኃይል›› ተብሎ የተቋቋመው ታጣቂ ቡድን ዛሬም ድረስ የሎጅስቲክ አቅርቦቱን ያለጨረታ ጠቅላላ የያዘችው የሜ/ ጀነራል ዮሐንስ ወ/ጊዮርጊስ (በአሁኑ ወቅት ጀነራል አበባውን ተክቶ የማዕከላዊ ዕዝ አዛዥ ነው) ባለቤት ሃዋ መሆኗ በራሱ የሚነግረን ነገር አለ፡፡ (በነገራችን ላይ ክልሉን የሚያስተዳድሩት በህዝብ የተመረጡት ሳይሆኑ ‹‹የፀጥታ አማካሪ›› በሚል በየወረዳው የተመደቡ የሻለቃ ወይም የሻምበል አዛዦች ከጀርባ ሆነው ነው፡፡ ለነርሱ ያልተመቸ ኃላፊን በሌላ እስከመቀየር ድረስ የሚንጠራራ ስልጣን አላቸው፡፡ የፕሬዚዳንት አብዲና እና የጄነራል ‹‹ኳርተር››ን የ‹‹ሥራ ግንኙነት›› መመልከቱ ጉዳዩን ፍንትው አድርጎ ለመረዳት ያስችላል፡፡ በርግጥም አስራ ሦስት ፕሬዚዳንቶች የተፈራረቁበት ክልል ዛሬ እንዲህ በጨካኙ አብዲ መርጋት መቻሉ እንቆቅልሽ ሊሆን አይችልም)፡፡ ‹‹ጄል-ኦጋዴን›› ከደረቅ ወንጀለኞች ማረሚያነት፣ በኦብነግ አባልነት የሚጠረጠሩ ንፁሃንን ወደማሰቃያ እስር ቤት እንዲቀየር የተደረገበት መግፍኤ ከላይ የጠቀስኩትን (የ1999 ዓ.ም የኃይል ጥቃትን) ተከትሎ ሟቹ አምባ-ገነን ጠ/ሚኒስቴር በደህንነት ኮሚቴው ስም የሰጠው ትዕዛዝ ነው፡፡ መቼም ዕድል ፊቷን አዙራበት ወደዚህ ግቢ የተላከ ምስኪን፣ በቀን አንድ መናኛ እንጀራ እየተወረወረለት፣ በ‹‹ምርመራ›› ስም የተወለደበትን ቀን ከመርገም አልፎ ዘላለማዊ ዕረፍት የሚያጎናፅፈው መልአከ-ሞት ቶሎ መጥቶ እንዲገላግለው እስከመናፈቅ ለሚያደርስ ስቀየት (ቶርቸር) ይዳረጋል፡፡ እስር ቤቱ የተገነባው 800 ታሳሪዎችን ታሳቢ ተደርጎ ቢሆንም፣ ወደምድራዊ ገሃነም ከተቀየረ ወዲህ ግን ከ5000 በላይ ሰዎች የሚታጎሩበት የሰቆቃ ግቢ ሆኗል፡፡ ሁሉም ታሳሪዎች ከጠዋት 2፡30 እስከ 7፡00 ሰዓት ድረስ አንድ ቦታ ተሰብስበው ክብርን፣ ሞራልን እና ሰብዕናን የሚያጎድፍ ግፍ ይፈፀምባቸዋል፡፡ በተለይም ሴት እስረኞች በየተራ እንዲቆሙ ይደረግና ወንዱ አንድ በአንድ እየተነሳ ሴተኛ አዳሪ መሆኗን፣ እሱ እና ጓደኞቹ ከእርስዋ ጋር ግብረ-ስጋ ግንኙነት መፈፀማቸውን፣ ወዘተ እንዲናገር ይገደዳል፡፡ ይህንን ለማድረግ ፈቃደኛ ሆኖ ካልተገኘም በጨካኝ ታጣቂዎቹ ፍዳውን ይበላል፡፡ ሁኔታውን መራር የሚያደርገው ደግሞ ‹‹ስብሰባው›› ሲጠናቀቅ፣ ሰብሳቢው እስረኞቹ ወደየክፍላቸው እንዲገቡ ትዕዛዝ የማይሰጥ መሆኑ ነው፤ ይልቁንም ወፋፍራም ዱላ ጨብጠው ዙሪያውን ለከበቡት ፖሊሶች በአይኑ ምልክት ያስተላልፋል፤ ይሄኔ በያዙት ቆመጥ ከአቅራቢያቸው ያገኙትን ሁሉ መቀጠቀጥ ይጀምራሉ፤ እስረኛውም ከዱላው ውርጅብኙ ለማምለጥ ባገኘው አቅጣጫ ይተራመሳል፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ድርጊት በየቀኑ የተለመደ በመሆኑ የዕለቱ ፕሮግራም ሊገባደድ በተቃረበ ቁጥር፣ ሁሉም ለመሸሽ ዝግጁ ሆኖ ይጠባበቃል፤ ከድብደባው ማምለጡ ግን ብዙም የሚሳካ አይሆንም፡፡
 በ‹‹ጄል-ኦጋዴን›› ሴት እስረኞችን አስገድዶ መድፈር፣ ሙዝ ልጦ እንደመብላት ቀላል ከሆነ ሰነባብቷል፡፡ በዚህም በርካቶች በየጊዜው ለውርጃ ወደ ሆስፒታል ሲላኩ ይስተዋላል፡፡ አልፎ አልፎ እዚያው ለመውለድ የሚገደዱ እህቶችም አሉ፡፡ አብዛኞቹ ሴት እስረኞች ፀጉራቸውን ከማሳደግ ይልቅ መላጨትን ይመርጣሉ፤ ምክንያቱ ደግሞ የሚፈፀምባቸው ስቅየት የበሰበሱ ቆሻሻዎችንና ፈሳሽ- ሰገራዎችን ፀጉራቸው ላይ መደፋትን ስለሚያካትት ነው፡፡
ከዚህ በተጨማሪ እዚህ ቦታ ሴቶች አንድ ላይ እንዲሰበሰቡ እና ልብሶቻቸውን እንዲያወልቁ ከተደረገ በኋላ እርቃናቸውን የሚገረፉበት ጊዜም እንዳለ ከአይን እማኞች ሰምቻለሁ፡፡ ከሁሉ የከፋው ደግሞ ንፅህናን ካለመጠበቅና በምግብ እጥረት የሚነዛው ወረርሽኝ ነው፡፡ በ2004ዓ.ም. መጀመሪያ አካባቢ በሽታው ተከስቶ አንድ ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ብቻ 700 ያህል ሰዎች በሞት መቀጠፋቸው ይነገራል፡፡ በወቅቱ አስከሬን ቶሎ ስለማይነሳ እስረኞቹ ከአስከሬኑ ጋር እስከ 3 ቀን ድረስ ጋር ለመቆየት ይገደዱ ነበር፡፡ በ‹‹ጄል-ኦጋዴን›› ግቢ ከሚገኙ ማጎሪያዎች መካከል 3ኛ፣ 4ኛ፣ 7ኛ እና 8ኛ ክፍሎች ‹‹የቅጣት ቤት›› ሲሆኑ፤ አሰራራቸውም ሶስት በሶስት ሜትር የሆነ እጅግ በጣም ጠባብ፤ ውስጣቸውም ሃምሳ ሳንቲ-ሜትር ጥልቀት ባለው ውሃ የተሞላ ነው፡፡ እያንዳንዱ ክፍልም የግድ ከ25 እና ከዚያ በላይ እስረኞች እንዲይዝ ስለሚደረግ ለቅጣት ወደግቢው የተላከ እስረኛ ለሳምንት ያህል እንቅልፍ በዓይኑ ሳይዞር ለመሰንበት ይገደዳል፡፡ በአናቱም የመከላከያ ሰራዊት አባላት ወደዚህ ግቢ እየተላኩ ስቅየትም ሆነ ግድያ እንደሚፈፀምባቸው ሰምቻለሁ፡፡ በግቢው ለአራት ወራት ገደማ ያሳለፈው ሀሰን፣ በውል በማያስታውሰው በአንድ የተረገመ ቀን 3 ወታደሮች ሲረሸኑ ማየቱንና ከመካከላቸው አንዱም ‹‹እባካችሁ አትግደሉኝ! የ3 ልጆች አባት ነኝ!›› እያለ ሲማፀን መስማቱን ያስታውሳል፡፡
እስረኞቹ ላይ የጭካኔ ተግባር የሚፈፅሙት ደግሞ ከዚህ ቀደም ‹‹አል-ኢትሀድ አል-ኢስላሚያ›› በሚል ስም ተደራጅቶ ሲንቀሳቀስ፤ በኦብነግ ተሸንፎ ከኦጋዴን የተባረረው አማፂ ቡድን አባላት የነበሩ ናቸው፡፡ እነዚህ ሰዎች መንግስት ምህረት አድርጎላቸው ወደ ሰላማዊ ህይወት ከተመለሱ በኋላ የክልሉ ፕሬዝዳንት አብዛኛውን አሰባስቦ ‹‹ልዩ ኃይል›› ብሎ አደራጅቷቸው ሲያበቃ፤ ከኦብነግ ጋር ተያይዞ የሚጠረጠሩ እስረኞች ላይ ያሻቸውን እንዲፈፅሙ ባልተፃፈ ሕግ ስልጣን ሰጥቷቸዋል፡፡ እነርሱም የቀድሞ ሽንፈታቸውን ለመበቀል እንደ መልካም አጋጣሚ እየተጠቀሙበት ይገኛሉ፡፡ ዛሬ በክልሉ ከተሞች በሚገኙ የተለያዩ የእስር ቤት ግቢዎች ውስጥ የጅምላ መቃብር መመልከት አስገራሚነቱም አስደንጋጭነቱም እየቀረ የመጣው ከዚህ አኳያ ይመስለኛል፡

Montag, 12. Oktober 2015

ከሁሉ በፊት የሰባዊ መብት ጥበቃ እና የብሔራዊ እርቅ ያስፈልጋል!! ከመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) የተሰጠ መግለጫ

ከሁሉ በፊት የሰባዊ መብት ጥበቃ እና የብሔራዊ እርቅ ያስፈልጋል!!12144958_896631350421800_1641189443633199080_n12115783_896631343755134_7789333707150151204_n

ከመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) የተሰጠ መግለጫ
የኢህአዴግ መንግሥት ለሚቀጥሉት አምስት ዓመታት እተገብረዋለሁ በሚለው የእድገት እና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ላይ የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ለማወያየት እንደፈለገ መስከረም 24 ቀን 2008 ዓ.ም በፃፈልን ደብዳቤ ገልጾልና፡፡ ይህ ሁኔታ መልካም ቢሆንም ቅሉ አንድ መንግሥት የሚነድፋችው እቅዶች ተግባራዊ ሊሆኑ የሚችሉት ሁሉም የሀገሪቱ ዜጎች አምነውበትና የኔ ብለው በሙሉ ልብ ሲቀበሉት እና ሙሉ ተሳትፎ ሲያደርጉበት መሆኑ ለማንም ግልጽ ነው፡፡
ይሁን እንጂ ዛሬ አገራችን ኢትዮጵያ በተበጣጠሰ ሁኔታ የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካ እና የማህበራዊ ትስስሯ ፈጽሞ በላላበት ሁኔታ፣ የዘርና የጎሳ ፖለቲካ የፈጠረው ችግር ተጋብቶና ተዋልዶ አብሮ የኖረውን ሕዝብ ለያይቶና አራርቆ በጠላትነት እንዲተያይ አድርጐታል፡፡ ይህ በመሆኑም የጉልበት (Labor) እና የካፒታል (capital) ዝውውር ተገትቶ ባለበት ሁኔታ እና ዜጎች በአገራቸው ውስጥ ከቦታ ቦታ ተዘዋውረው እንዳይሰሩና ሀብት ንብረት እንዳያፈሩ ተገትተው እና ተገድበው ባለበት በአሁኑ ወቅት፣ የዚህን አካሄድ አስከፊነት የሚያመላክተን በየዮኒቨርስቲው የሚገኙ ተማሪዎች በአንድ ስሜትና በወንድማማችነት ለምርምርና ለፈጠራ ከመነሳት ይልቅ የጎሳ ጎራ ለይተው እየተንቆራቆሱ መገኘታቸው ለሀገሪቱ በሚጠቅም ጉዳና ላይ አለመሆናቸውን ያመላክታል፡፡
ኢህአዴግ የፈጠረውና ያጠናከረው ወገን የሀገሪቱን ኢኮኖሚ በሞኖፖል ይዞ ሌላውና የገዥው ፓርቲ ደጋፊ ያልሆነው ክፍል ደግሞ ወደ ድህነት አዘቅት ውስጥ እንዲገባ ተደርጓል፡፡ ይህም የሚያሳየን እንደፖለቲካው ሁሉ ፍትሀዊ የሆነ የኢኮኖሚ ክፍፍል አለመኖሩን ነው፡፡ 
ዜጎች ከላይ እንደተጠቀሱት ያሉ ችግሮች እንዲስተካከሉ በሚናገሩበትና በሚጽፉበት ወቅት ሽብርተኛ እየተባሉ ህግን ባልተከተለ ሁኔታ ወደ እስር ቤት ይወረወራሉ፡፡ ፍትህም በወቅቱ አይሰጣቸውም፡፡ ለብዙ ጊዜ በዚያው ሲማቅቁ እንዲቆዮ ከተደረገ በኋላ ያለፍርድ ቤት ውሳኔና ትዕዛዝ ከእስር ቤት እንዲለቀቁ ይደረጋል፡፡ ይህ ሁኔታም ሠላምን ሳይሆን ጥላቻን፤ የሀገር መረጋጋትን ሳይሆን ብጥብጥን የሚፈጥር መሆኑን ገዢው ፓርቲም ቢሆን ቁልጭ አድርጎ የሚያውቀው ይመስለናል፡፡
የኢህአዴግ መንግሥት እንደነዚህ ያሉ ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ ከመፍታት ይልቅ ሕዝባችንን በሀብታም እና ደሀ፣ የኢህአዴግ ደጋፊና ጠላት በሚል ስለከፋፈለው፣ እርሱ የፈጠራቸው ሀብታሞች የሀገሪቱን ሀብት በሞኖፖል እንዲይዙ ሲደረግ ቀሪውና እውነትን በመፈለግ እርሱኑ ሲታገል የነበረው ሕዝብ ደግሞ ከሥራው ይፈናቀላል፣ ከንግድ ሥራው ከስሮ እንዲወጣ ይደረጋል፣ አርሶ አደር ከሆነም ከመሬቱ ይፈናቀላል፡፡ ይህ አካሄድም አንድነትን ሳይሆን መለያየትን፣ ወንድማማችነትን ሳይሆን ጠላትነትን፣ መደጋገፍን ሳይሆን በጠላለፍን የሚፈጥር መሆኑን በድጋሜ ለኢህአዴግ ለማሳሰብ እንወዳለን፡፡
ከላይ እንደተጠቀሰው የኢኮኖሚው እንቅስቃስ በጥቂቶች ቁጥጥር ስር ስለዋለና ፍትሀዊ የሆነ የኢኮኖሚ ክፍፍል ስለጠፋ ከሕዝባችን 80 በመቶ የሚሆነው በከፍተኛ ችግር ውስጥ ወድቆ ይገኛል፡፡ የኢህአዴግ መንግሥትም ይህን የተጎዳ ክፍለ ሕዝብ ዞር ብሎ ከማየትና ከመደገፍ ይልቅ የራሱን ፖለቲካ ማጠናከርና ሁኔታዎችን በቁጥጥሩ ሥር ለማድረግ ጥረት ሲያደርግ ይታያል፡፡
የኢህአዴግን መንግሥት ለመምከርና ለማሳሰብ የምንወደው በሀገሪቱ ውሰጥ፡-
1. የልማት፣ የእድገትና ብልጽግና መሠረቱ ዲሞክራሲና የዜጎች መብት መጠበቅና መከበር ሆኖ ሳለ ዜጎች በፖለቲካ አመለካከታቸው ብቻ በየእስር ቤቱ በመሰቃየት ላይ ባሉበት፣ ሌሎች አባላትም በዚህ አመለካከታቸው የተነሳ እየተሳደዱ፣ እየተዋከቡና ንብረታቸውን እየተነጠቁ በአጠቃላይ የሰብአዊ መብታቸው ተገፎ ከፍተኛ በደል እየተፈፀመባቸው ባለበት በአሁኑ ወቀት፣
2. ከላይ እንደተጠቀሰው ሁሉ በተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች ሕዝባችን ተጋብቶ፣ ተዋልዶና ሀብት አፍርቶ በሰላም ከሚኖርባቸው የተለያዩ አካባቢዎች “ክልልህ አይደለም ከክልላችን ውጣ” እየተባለ በገዢው ፓርቲ ካድሬዎችና ደጋፊዎች ሀብታቸው እየተነጠቀ፣ እየተቃጠለ፣ እየተቀማ፣ እነርሱም እየተደበደቡና እየታሰሩ በአሳዛኝ ሁኔታ ከነቤተሰባቸው እየተባረሩ ባሉበት በአሁኑ ወቅት ዜጎች በወጣው እቅድ ላይ በሙሉ ልብ ሊሳተፉ ይችላሉ ለማለት ያስቸግራል፡፡ 
3. እንደዚህ ያለውን ግዙፍ ብሔራዊ እቅድ ተግባራዊ ለማድረግ ሁሉም ኢትዮጵያዊያን በባለቤትነትና በእኔ ባይነት መሳተፍና ለተግባራዊነቱም በትጋት ይነሱ ዘንድ ከላይ የተጠቀሱት ከፍተኛ የሆኑ ችግሮች መፈታት አለባቸው ብለን እናምናለን፡፡
እንደነዚህ ባሉ ማነቆዎች እና ችግሮች ላይ እርምት ሳይደረግ የወጣውን እቅድ ሕዝባችን በአንድ ልብ ደግፎ በመረባረብ ከዳር ያደርሰዋል ብሎ ማሰቡ ብዙ እርምጃ ያስኬዳል የሚል እምነት የለንም፡፡ ስለዚህ የአህአዴግ መንግሥት ሁሉም ዜጎች በሀገሪቱ እንቅስቃሴዎች ላይ ሙሉ ተሳትፎ እንዲኖራቸው ከፈለገ ከላይ የተጠቀሱ ችግሮች ሙሉ ለሙሉ በአስቸኳይ መፈታት አለባቸው የሚል ምክራችንን ልንለግስ እንወዳለን፡፡
በአጠቃላይ የኢህአዴግ መንግሥት በዚህ እቅድ ላይ ሕዝባችንን ለውይይት ከመጥራቱ በፊት መቅደም ያለባቸው አንገብጋቢ ጉዳዩች እንዳሉና በቅድሚያ መፈፀም እንዳለባቸው እያሳሰብን ሁሉም የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላትን ያካተተ ስብሰባ ተደርጎ ብሔራዊ ውይይት፣ እርቅና መግባባት የሚደረስበት ስብሰባ ኢህአዴግ መጥራት እንዳለበት እናሳስባለን፡፡
አንዲት ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!!!
ጥቅምት 01 ቀን 2008 ዓ.ም

Sonntag, 11. Oktober 2015

በሶማሊያ የተጎዱ ኢትዮጵያዊያን የሰላም አስከባሪዎች በኬንያ ሆስፒታል ተረስተዋል (Dawit Solomon)

በሶማሊያ የተጎዱ ኢትዮጵያዊያን የሰላም አስከባሪዎች በኬንያ ሆስፒታል ተረስተዋል (Dawit Solomon)12108995_896253477126254_1678758653615688345_n
--አስታማሚ ባለማግኘታቸው ጭንቀት ውስጥ ገብተዋል
--115 ዶላር ብቻ ሲከፈላቸው መቆየታቸውንም ይናገራሉ
(በዛብህና በየነ እውነተኛ ስማቸው ለዚህ ጽሁፍ ሲባል ተለውጧል) ሁለቱም በሐያዎቹ አጋማሽ የዕድሜ ክልል ውስጥ ይገኛሉ፤አገራቸውን በወታደርነት ለማገልገል ቅጥር የፈጸሙት ከዛሬ ስድስትና አራት አመታት በፊት ነው፡፡የትውልድ አካባቢያቸው የነበሩትን ዲላና ሆሳህናን ለቅቀው በተለያዩ ግዳጆች አገራቸውን እንደተመኙት ሲያገለግሉ ቆይተው የዛሬ አንድ አመት አካባቢ የተባበሩት መንግስታትን የሰላም አስከባሪ ሐይል በመቀላቀል በሽብርተኛው አልሻባብ ወደ ምትታመሰው ሶማሊያ አቅንተዋል፡፡
በሶማሊያ የሰላም ማስከበር ተግባራቸውን እየፈጸሙ በነበረበት አንድ መጥፎ ቀን በዛብህ በተተኮሰበት ሁለት ጥይት ሆዱ አካባቢ ተመትቷል፡፡ራሱን በህይወት ያገኘው ግን በሌላኛዋ ጎረቤት አገር ኬንያ በሚገኝ ሆስፒታል ውስጥ ነበር፡፡በየነ የተቀበሩ ፈንጂዎችን የመፈተሸ ግዳጅ ተሰጥቶት የያዘው የፈንጂ መጠቆሚያ መሳሪያና የተቀበረው ፈንጂ በመሳሳባቸው በተፈጠረ ፍንዳታ ሁለት እግሩንና የአንድ እጁን አንድ ጣት ለማጣት ተገድዷል የአንድ አይኑ የማየት አቅምም ክፉኛ መጎዳቱን ይናገራል፡፡
በዛብህና በየነ አደጋውን ካስተናገዱ በኋላ ናይሮቢ ውስጥ በሚገኝ ሆስፒታል በአንድ ክፍል ውስጥ እንዲተኙ በመደረጋቸው ለመተዋወቅ በቅተዋል፡፡በየነ የተሰጠው ዊልቼይር ላይ ተቀምጦ በዛብህ መጽሐፍ ቅዱስ እያነበበለት ልጎበኛቸው በሄድኩበት ሰዓት አግኝቻቸዋለሁ፡፡ሰው የተራቡት ሁለቱ የአገሬ ልጆች የቅርብ የቤተሰቡን አካል እንዳገኘ ሰው እቅፍ አድርገውኝ ስመውኛል፡፡
‹‹የቋንቋ ችግር አለብን፣ካለንበት ሆስፒታል ሰዎች ጋር መግባባት አልቻልንም››፡፡በየነ እንባ አቅርሮ ይናገራል ‹‹እርሱን አጠገቤ ማግኘት ባልችል ኖሮ እንዴት አድርጌ ሁኔታውን እንደምለምደው አላውቅም፡፡ፈንጂው በፈነዳበት ወቅት አንድ እግሬ ተቆርጦ ሲቃጠል ተመልክቼው ነበር፡፡ አንደኛው እግሬ ቢቆስልም ሊድን ይችል እንደነበር አምናለሁ፡፡ነገር ግን እዚህ ከመጣሁ በኋላ ቆረጡት፡፡ለምን እንደቆረጡት እንኳን እስካሁን ለእኔ ግልጽ አይደለም››ብሏል ፡፡
ወደ ሆስፒታሉ ከመጡ በኋላ ዲላና ሆሳህና ያሉ ቤተሰቦቻቸውን ለመገናኘት ቢያስቡም በየነ በፈንጂው አደጋ ወቅት ተንቀሳቃሽ ስልኩ በመጥፋቷና የበዛብህ ደግሞ ለብልሽት በመጋለጧ ምንም ማድረግ ሳይችሉ መቅረታቸውን በሐዘን ተውጠው ይናገራሉ፡፡
‹‹የተባበሩት መንግስታትን ተልእኮ ተቀብላችሁ የዘመታችሁ በመሆናችሁ እንዴት እንዲህ ያሉ ጥቃቅን ነገሮችን እንኳን ሊያሟሉላችሁ አይችሉም ?›› በአግራሞት ተሞልቼ የወረወርኩት ጥያቄ ነበር፡፡
‹‹ወደ ሆስፒታሉ እንደመጣን አንድ ኮሎኔል የእኛን ሁኔታ እንደሚከታተል ተነግሮን የነበረ ቢሆንም ሰውዬው የሚመጣው በጣም እየዘገየ ነው፡፡የሚያደርግልን ምንም የተለየ ነገር የለም፣ እነርሱ ከህክምናችን ውጪ የሚያደርጉልን ምንም የለም››፡፡ለጥያቄዬ የሰጡኝ ምላሽ ነበር፡፡
ከሁለቱ ኢትዮጵያዊያን ወታደሮች አጠገብ አንድ እግሩን በአደጋ ያጣ ጎልማሳ ኬንያዊ ተኝቷል፡፡በዛብህ ጣቱን ወደ ኬንያዊው እየቀሰረ ‹‹እባክህ ስለእኛ ሆነህ ይህንን ኬንያዊ አመስግንልን ፤ የእርሱ ቤተሰቦች ሊጠይቁት ሲመጡ አትክልት፣ምግብና ወተት ሁልግዜም ያመጡልናል››አለኝ፡፡
ወታደሮቹ በሆስፒታሉ ከሚያገኙት የህክምና፣የምግብና የአልጋ አገልግሎት ውጪ ምንም አይነት እርዳታ አያገኙም፡፡በየነ ሁለት እግሮቹን በማጣቱ መጸዳጃ ቤት የሚወስደው፣አልጋው ላይ የሚያወጣውና የሚያወርደው ረዳት ያስፈልገዋል፡፡በአሁኑ ወቅት ይህንን አገልግሎት እየሰጠው የሚገኘው በሁለት የሆዱ ክፍሎች ላይ ቀዶ ጥገና ያደረገውና ቁስሉ ያልደረቀለት በዛብህ ነው፡፡
‹‹በየነ በጣም ሰው ያስፈልገዋል፡፡እኔ ደግሞ እንደምታየኝ ቀዶ ጥገና ያደረግኩት በቅርቡ ነው፡፡ግን እርሱ ከእኔ በሚብስ ሁኔታ ውስጥ ስለሚገኝና ከእኔ ውጪ ሊረዳው የሚችል ሰው ባለመኖሩ እያመመኝም ቢሆን እረዳዋለሁ››ብሎኛል፡፡
በየነ አሁን ከሁሉም በላይ አገሩ መግባትን ናፍቋል፡፡‹‹በዚህ ሁኔታ መቀጠል ስለማልችል ወደ አገሬ እንዲወስዱኝ እፈልጋለሁ ቢያንስ ቤተሰቦቼ አጠገቤ ሆነው ሊያስታምሙኝ ይችላሉ››ይላል፡፡
ሁለቱ ወታደሮች በሶማሊያ ቆይታቸው በወር 115 የአሜሪካ ዶላር አበል እየተባለ ሲከፈላቸው መቆየታቸውን ይናገራሉ፡፡በየነ በፈንጂው ወዲያውኑ በተቆረጠው እግሩ ባጠለቀው ሱሪ ኪስ ውስጥ የተቀበለውን ዶላር አስቀምጦ እንደነበር በማስታወስ ፈገግ ይላል፡፡
ወታደሮቹ ምንም እንኳን ስለሚገኙበት ሆስፒታል የህክምና አሰጣጥ ባያማርሩም መረሳታቸው ግን ያበሳጫቸዋል፡፡ከአገራችን አልፈን ለአህጉሪቱ ችግር መፍትሄ ለመስጠት በተሰማራንበት ግዳጅ ጉዳት አስተናግደን የምንፈልጋቸውን ጥቃቅን ነገሮች ሊያሟልልን የሚችል ረዳት ከአጠገባችን ማጣታችን ቅስማችንን ሰብሮታል ይላሉ፡፡
በሶማሊያ የሰላም ማስከበር ግዳጅን በመወጣት ላይ የሚገኙ 5000 ያህል ኢትዮጵያዊያን ወታደሮች እንደሚገኙ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡በኬንያ በተለይም በዋና ከተማይቱ ናይሮቢ የምትገኙ አገር ወዳድ ኢትዮጵያዊያን ጉዳተኞቹ ወደሚገኙበት ሆስፒታል በማምራት እንድትጎበኟቸው ትጠየቃላችሁ፡፡
-----------

Freitag, 9. Oktober 2015

በሙሉጌታ ሉሌ አሟሟት ተደስቻለሁ!! በDassenech Tsemai

በሙሉጌታ ሉሌ አሟሟት ተደስቻለሁ!! በ 
Dassenech Tsemai
1891166_935478479853353_5623313573126541231_nስለሙሉጌታ ሉሌ ስብዕና፤ ተግባር፤ ስነምግባር፤ ስላበረከተው አስተዋጽኦ፤ ስለፈጸመው ገድል ከኔ በላይ ብዙዎች ስለሚናገሩለት፤ ከነሱም በላይ ተግባሩ፤ ህያው ስራዎቹ ስለሚመሰክሩለት እኔ ምንም መናገር አልፈልግምና አልፈዋለሁ።
እንደሙሉጌታ ያሉ መስጠት እንጂ መቀበል የማይወዱ; ለሌላው ማድረግ እንጂ ሲደረግላቸው የማይደሰቱ፤ የወደቀን ለማንሳት እንጂ እነሱ ሲወድቁ ሰው እንዲያነሳቸው እጃቸውን የማይዘረጉ፤ በራሳቸው ሙሉ እምነት፤ ለሰው ልጅ ታላቅ አክብሮት ያላቸው ትሁት ሰዎች ትልቁ ሞታቸው የስጋና ነፍስ መለያየት ሳይሆን ታሞ ወይም አቅም አጥቶ ሰው እጅ ላይ መውደቅ፤ የሰው ተረጂ መሆን ነው። ይህ ሳይሆን በማሸለቡ በጣም ደስተኛ ነኝ።
ሙሉጌታ ሉሌ በራሱ አንደበት እንደተናገረው "ይህን ትውልድ ስረግም ኖሬያለሁ፡ አሁን ግን እነ ብርሃኑ፤ እነ ኤፍሬም ክብራቸውን; የሞቀ ትዳራቸውን፤ የሚሳሱለትን ቤተሰባቸውን ጥለው በረሃ ሲገቡ ሳይ ይህን ትውልድ ይቅርታ መጠየቅ እንዳለብኝ ተሰማኝ" (አነጋገሩን በትክክል ላልጠቅሰው እችላለሁ ግን ሃሳቡ ይህ ነው)።
ሙሉጌታ ይህን በተናገረ ቅጽበትና ከዚያም ቀደም ሆነ ከዚያ በሗላ ባሉት ጊዜያት ይሰማው የነበረው ስሜት፡ የድል አድራጊነት፤ በትውልድ የመኩራት ነበር ማለት እችላለሁ፡ በመጨረሻዋ ምሽትም ባንቀላፋባት ጊዜ ሙሉ የመንፈስ እርካታን አግኝቶ፤ ሲመኘው የነበረው ነጻነት እንደሚመጣ እርግጠኛ ሆኖ በሩህ ተስፋ እየታየውና በዚህ ትውልድ እየኮራ እንደነበር ለደቂቃ አልጠራጠርም። በመሆኑም መንፈሱ ሆሌም እንደተደሰተች፤ ድል አድራጊነቷን እንዳረጋገጠች፤ የሰላም እረፍት አግኝታ ትኖራለችና አሟሟቱ አስደስቶኛል።
ይህ ሳይሆን ቀርቶ አልጋ ላይ ውሎ፤ እሰው እጅ ላይ ወድቆ፤ ምናልባትም በቂ እንክብካቤ ሳያገኝ ቢያልፍ ኖሮ (ከዚህ ቀደም እንዳለፉት ብርቅዬ ወገኖቻችን) ዳግም ሞት ይሆን ነበር፡ መንፈሱ ተሰብራ፤ በሃዝን ልቡ ጨልማ፤ ድል ሳይሆን ውድቀትን እንደሰነቀ ያንቀላፋ ነበር።
እግዚአብሄር ደግ ነውና አሟሟቱን የጌጥ አደረገለት፡ ስለዚህ አሟሟቱ አስደስቶኛል።
በመጨረሻ ግን ለዚህ ትውልድ ጥሎ ያለፈውን አደራ ክብደት ሳላነሳ መሞነጫጨሬን ላቆም አልፈለኩም። ባንደበቱ እንደተናገረው፡ "አሁን እኔ ምን ማድረግ እችላለሁ እያልኩ ነው" ይህ መልእክት ለራሱ ብቻ የተናገረው አለመሆኑን መረዳት አስቸጋሪ አይመስለኝም፡ አሱዩማ ህይወቱን ሙሉ ማድረግ ያለበትን ሲያደርግ፤ መከፈል ያለበትን መስዋዕትነት ሲከፍል፡ ማስተላለፍ የሚገባውን ታሪክ ሲያስተላልፍ፤ ማስተማር የሚገባውን ሲያስተምርና ሲማር ኖሯል፡ አሁንም በሰባ አምስት አመት አረጋዊ እድሜው እንደ አፍላ ጎረምሳ ሩጫ ላይ ነበር፡ እንኳን ሊቀድመው ቀርቶ እኩል ሊራመድ ወይም በቅርብ ርቀት ሊከተለው የቻለ እንደሌለ ግልጽ ነው፡ መልእክቱ ለሁላችንም ነው፡ ለኔም፤ ላንቺም፤ ላንተም።
ራዕዩ እንዲፈጸም፡ ነጻነት ይመጣል ብሎ የሰነቀው ብሩህ ተስፋ እውን እንዲሆን፡ ይቅርታ የጠየቀው ትውልድ አውነትም ይቅርታ ለመጠየቅ የሚበቃ ትውልድ መሆኑን ለማስረገጥ ምን ማድረግ አለብኝ የሚለው ለሁላችንም ጥሎት ያለፈ ኑዛዜ ነው።
ቃሉን ለማክበር፤ ኑዛዜውን ተግባራዊ ለማድረግ ያብቃን።

Sonntag, 4. Oktober 2015

የሃሳብ መንገድ፡ ጉድ ሳይሰማ _ገብረጻዲቅ አበራ

ጉድ ሳይሰማ
ጉድ ሳይሰማ  መስከረም አይጠባም እንዲሉ  አጀብ አሰኝቶን የተጀመረው 2007 ጉድ አሰኝቶን ተጠናቋል። በሌላ  ሃያሏ ዩኤስ አሜሪካ መዲና  ዋሽንግተን ዲሲ  የሚገኘውን የኢትዮጵያን ኢንባሲ  ኢትዮጵያዊያን የለውጥ አቀንቃኞች  መስከረም 26 /2007 ዓም ለደቂቃዎች ሲቆጣጠሩ የኢምባሲው የጥበቃ  ሃላፊ ተኩስ በመክፈት ለትእይንቱ ድምቀጥ ከመስጠት ባሻገር የህወሃት ሰዎች ድንቁርና ድንበር የማያግደው እርቀት የማይገድበው መሆኑን አሳይቶናል። የህወሃት ህዝባዊ ወያኔ  ሃርነት ታጋይ የአለም የፖለቲካ  መአከል በሚባለው  ዋሽንግተን ዲሲ ውስጥ ቁጭ ብሎ የ ጌትነት ካባ  ደርበው ልምጭ ባልያዙ ያገሩ ልጆች ላይ አነጣጥሮ ሲተኩስና  ጥይቱ ሲደነብሽበት አይተናል። በ48 ሰአታት ውስጥ አመሬካን ለቆ  እንዲወጣ  ተወስኖበት ጓዙን ጠቅልሎ  መውጣቱንም ተከታትለናል። በዚህም ሳቢያ  የህወሃት ካምፕ የነበረው ሃዘን ቁጭትና  እልህ እንዲሁም ቀለብ በሚሰፈርላቸው አገልጋይ ወገኖች የነበሩ ማላዘን አንዳመት ብቻ  ነውና  አንረሳውም። የህወሃት ታጋዮች የነጻነት  አርበኛውን አንዳርጋቸው ጽጌን ከየመን የጸጥታ  ሃይሎች በረብጣ ዶላሮች በመግዛት የዘረኝነትና  የዘረፋ ስርአታቸውን ለማደላደል ቢቋምጡም ነጻነትን የተራቡ ኢትዮጵያዊያን ሁለት ወር ባልበለጠ  ጊዜ ውስጥ ዋሽንግተን ዲሲ ላይ ምላሽ ሰተዋል። እኛም አንዳርጋቸው ነን  ያሉት ደግሞ  አመቱን ሙሉ መረብን እየተሻገሩ ብረት ማንሳታቸውን ሰምተናል። የጠመንጃው ግብግብ እንዲያበቃና የሰለጠነ  ፖለቲካ በሃገራችን እውን እንዲሆኑ  የጣሩ ስልጡን ፖለቲካ   ስልጡን  ካልገባው ሃይል ጋር እንደማይሆን ተገንዝበው ነጻነት ፍለጋ  ድንበር እያቋረጡ መሳሪያ  አንስተዋል። ብረሃኑ ተክለያሬት  እየሩሳሌም ተስፋሁንና  ፍቅረማሪያም አስማማውን የመሳሰሉ ወጣቶች ነጻነት በሰላማዊ መንገድ እንደማይቻል በድርጊት ሲነገራቸው ነጻነት ፍለጋ  ድንበር  ሲያቋርጡ መያዛቸውን ለፍርድቤት በኩራት  በመናገር ለወኔያቸው የብዙዎችን አትኩሮት አትርፈዋል።  ሙሉውን ለማንበብ እዚህ ይጫኑ ጉድ ሳይሰማ  https://www.facebook.com/%E1%88%B3%E1%88%9D-%E1%89%AE%E1%8B%B5-%E1%88%B6%E1%8A%95-%E1%8A%A0%E1%8A%95%E1%8B%B3%E1%88%AD%E1%8C%8B%E1%89%B8%E1%8B%8D-EH-407502636113775/timeline/#

Samstag, 3. Oktober 2015

ረሃብ በኢትዮጵያ በባቡር ይጋልባል (ፕሮፌሰር አለማየሁ ገብረማርያም)

ከፕሮፌሰር አለማየሁ ገብረማርያም
ትርጉም በነጻነት ለሀገሬ
የኢትዮጵያ ዓመታዊ የረሃብ አዝመራ፣Famine Rides a Light Train in Ethiopia
ባለጥቁሩ ፈረስ የረሃብ የምጽዓት ቀን አስፈሪውን ፊቱን በኢትዮጵያ እንደገና ማሳየት ጀመረ፡፡
በአሁኑ ጊዜ በባቡር ተቀምጦ በመጋለብ ላይ ይገኛል፡፡
እ.ኤ.አ የካቲት 2014 በዚሁ ወር ኤንቢሲ/NBC የተባለ ዓለም አቀፍ ድርጅት ያወጣውን የምርመራ ዘገባ መሰረት በማድረግ “እየተንፏቀቀ የመጣው ረሃብ በኢትዮጵያ “ በሚል ርዕስ ትችት አቅርቤ ነበር፡፡ በዚያን ጊዜ ኤንቢሲ/NBC እንዲህ የሚል ዘገባ አቅርቦ ነበር፡
ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ የዓለም የምግብ ቀውስ መግለጫ ሆናለች፡፡ በደቡብ ኢትዮጵያ በአንድ መንደር ውስጥ እናቶች በተመጣጣኝ የምግብ እጥረት ከተጎዱ ህጻናት ልጆቻቸው ጋር ለአስቸኳይ የምግብ ምፅዋት (ራሽን) ተደርድረው ታይተዋል፡፡ እነዚህ የረሃብ ሰለባ የሆኑ ወላጆች ህጻናት ልጆቻቸውን ለመመገብ የሚያስችል አቅም የላቸውም፡፡ እንዲሁም በአሁኑ ጊዜ የውጩ ዓለም የእርዳታ እጁን ለመዘርጋት የሚችል አይመስልም፡፡ የረኃብ ምልክት የሆነው የህጻናት ሆድ መነፋት ከሁለት ተከታታይ ደካማ የምርት ዓመታት በኋላ የተከሰተ ሲሆን በአሁኑ ጊዜ በየዕለቱ ተጨማሪ ሰዎች የረኃብ ሰለባዎች እየሆኑ ነው… [የገዥው አካል ተወካይ የሆኑት አቶ ዑመር አብዲ] ጉዳዩን አስመልክቶ እንዲህ በማለት ሀሳባቸውን ገልጸዋል፣ “ለእነርሱ ሁለት የማያሻሙ አማራጮች አሉኝ፣ መሞት ወይም መሬቱን መጫር፡፡” ሆኖም ግን በአሁኑ ጊዜ በዚህች አገር ላይ ከውጭ የሚደረገው እርዳታ ሚሊዮኖች በህይወት እንዲቆዩ በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡ ባልተመጣጠነ ምግብ ምክንያት ለአደጋ የተጋለጡ ዜጎች ብዛት እድገት በማሳየት ላይ ይገኛል፣ እናም ይህንን ክስተት ለመግታት የሚደረግ ምንም ዓይነት የጥረት ምልክት አይታይም፡፡ ይህ ዓለም አቀፍ የምግብ ቀውስ በምዕራቡ ዓለም ለምግብ መሸመቻ ገንዘብ ችግር ቢፈጥርም ግን እዚህ [ኢትዮጵያ ውስጥ] ያሉት ህዝቦች በጣም ከፍተኛ የሆነ ዋጋ እንዲከፍሉ ያደርጋል፡፡
እ.ኤ.አ ነሐሴ 2015 የተባበሩት መንግስታት እንዲህ የሚል ለምግብ እርዳታ የአስቸኳይ ጊዜ ማስጠንቀቂያ ዘገባ አውጥቷል፡
በኢትዮጵያ የምግብ ዋስትና እጦት መጠኑ እየሰፋ እና እየተስፋፋ መጥቷል፣ እንደዚሁም ከፍተኛ የሆነ የተመጣጠነ የምግብ ንጥረ ነገር እጥረት መጠን ከዓለም አቀፉ መስፈርት መለኪያ በላይ በእጅጉበመጨመሩ የአስቸኳይ ጊዜ የምግብ ቀውስ ክስተትን ፈጥሯል፡፡ ሁለት ተከታታይ የዝናብ ወቅቶች (የበልግ እና የመኸር) የሰብል አዝመራ ምርት የሳተ በመሆኑ ምክንያት በአሁኑ ጊዜ በእርዳታ ላይ ጥገኛ የሆነው የምግብ ፈላጊው ህዝብ ቁጥር (ከዚህ ዓመት መጀመሪያ ጀምሮ 2.9 ሚሊዮን የነበረ ሲሆን) ከፍተኛ በሆነ መልኩ ይጨምራል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ (ኢሲኤችኦ/ECHO፣ እ.ኤ.አ ነሐሴ 13/2015) (አጽንኦ ተጨምሯል፡፡)
በኢትዮጵያ የመንግስት ኮሙኒኬሽን ሚኒስትር የሆነው ሬድዋን ሁሴን የተባለው ቀልደኛ የሆነ ደንቆሮ በሀገሪቱ ውስጥ አስከፊ የሆነ የምግብ ቀውስ መኖሩን አምኖ ይፋ ያደረገ ሲሆን ይህም ሆኖ ከዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ምንም ዓይነት የምግብ እርዳታ እንደማያስፈልግ ዓይኑን በጨው ታጥቦ የተራ ቅጥፈት እና ክህደት ቃሉን ሰጥቷል፡፡
ሬድዋን እንዲህ ብሏል፣ “እራሳችንን መመገብ እንችላለን፣ እናም በዝናቡ እጥረት ምክንያት ለችግሩ ሰለባ የሆኑትን አካባቢ ህዝቦች ጨምሮ የረሃቡ ስፋት እና መጠን በአብዛኛው ህዝብ ላይ ምንም ዓይነት ተጽዕኖ አያመጣም፡፡“ ይህ ሰው ያለምንም ተጨባጭ መረጃ ይህንን የመሰለ  ነገር ሲናገር የረሃቡ ሰለባ የሆኑ ሰዎች መራባቸውን አያውቁትም ማለቱ ነውን? አሁን በህይወት የሌለው እና የሬድዋን ትንሹ አምላክ የነበረው አምባገነኑ መለስ ዜናዊ ስላለው ዓላማ ለቀረበለት ጥያቄ ካለፉት ሁለት አስርት ዓመታት በፊት አዲስ አበባ ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ “ኢትዮጵያውያን በቀን ሶስት ጊዜ መመገብ ከቻሉ የመንግስቴ ስኬት የሚለካው በዚህ ነው” ብሎ ነበር፡፡ (ከዚህ ጋ ጫን በማድረግ የቪዲዮ ምስሉን ይመልከቱ፡፡)
በአሁኑ ጊዜ 5 ሚሊዮን የሚሆኑ ኢትዮጵያውያን የዓለም አቀፉ የምግብ እጥረት መስፈርት እና መለኪያ ከሚያሳየው በላይ በመሄድ ለአስቸኳይ እና ለአስከፊ የምግብ እጥረት ቀውስ ተዳርገዋል፡፡
እ.ኤ.አ በጃንዋሪ 2010 የአምባገነኑ መለስ ዜናዊ መለስ የግብርና ሚኒስትር ተሿሚ የነበረው አቶ ምትኩ ካሳ እንዲህ በማለት አውጆ ነበር፣ “በኢትዮጵያ ሁኔታ ረሃብ የለም፣ ቸነፈር/ጠኔ የለም… [ረሃብ ወይም ቸነፈር አለ] የሚለው መሰረተቢስ ነው፣ ረሃብ አለ የሚለው አባባል በመሬት ላይ ካለው ተጨባጭ ሁኔታ በተቃራኒው ነው፡፡ በመረጃ የተደገፈ አይደለም፡፡ በአሁኑ ጊዜ ችግሮቹን ለማስወገድ መንግስት እርምጃ በመውሰድ ላይ ነው፡፡“ አሁን በህይወት የሌለው አምባገነኑ መለስ ዜናዊም በተመሳሳይ መልኩ ስለረሃብ መኖር እንዲህ በማለት ሙልጭ አድርጎ ያፈጠጠውን እና ያገጠጠውን እውነታ ዓይኑን በጨው ታጥቦ በመካድ አስተባብሏል፣ “ረሃብ በኢትዮጵያ ለረዥም ጊዚ እልቂትን ሲያስከትል ቆይቷል፣ እንደዚህ ዓይነት አደጋዎች ሊከሰቱ እንደሚችሉ አስቀድሞ መገንዘብ አለመቻል ደደብነት ነው፣ ሆኖም ግን በእኛ እይታ ረሃብ የለም… የአስቸኳይ ጊዜ፣ እንጂ ረሃብ የለም፡፡“ ረሃብ በፍጹም የለም! የፖለቲካ እስረኞች የሉም! የሰብአዊ መብት ጥሰቶች የሉም! አምባገነናዊነት የለም! በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ውስጥ ምንም ዓይነት ችግሮች የሉም! አዎ እውነት ነው እንደ እናንተ ዓይነት የክህደት እና የሸፍጥ አካሄድ ምንም ዓይነት ችግሮች የሉም፣ እኛ ግን ቅጥፈት ብቻ ነው ያለው እንላለን!
እ.ኤ.አ መስከረም በ2010 አሁን በህይወት የሌለው አምባገነኑ መለስ እራሱን ከፍ ከፍ በማድረግ እንዲህ በማለት የግነት አዋጅ አውጆ ነበር፣ “ትርፍ ምርት ለማምረት የሚያስችሉ ዕቅዶችን ቀይሰናል፣ እናም በ2015 ያለምንም የውጭ እርዳታ ፍላጎት ህዝባችንን መመገብ እንችላለን“ ብሎ ነበር፡፡
ይቅርታ ጉዳዩን በተሻለ መልኩ የሚገልጽ ቃል ስላላገኘሁለት ነው፣ ሁሉም ቢሆኑ እውነታውን ሙልጭ አድርገው በመካድ ትንሽ ትንሽ ብቻ መዋሸት ሳይሆን እንደ አቡጀዲ ይቀደዳሉ፣ እንደማዳበሪያ መያዣ ከረጢት ይተረተራሉ፡፡
እ.ኤ.አ በ2015 “በቀን ሶስት ጊዜ ምግብ መመገብ“ ለበርካታ ኢትዮጵያውያን ላም አለኝ በሰማይ ወተቷን የማላይ ሆኗል፡፡ እንደዚሁም “ካለውጭ የምግብ  እርዳታ አቅርቦት“ አምባገነኑ መለስ “እንደቀየሰው” ኢትዮጵያ በ2015 እራሷን ትመግባለች ማለት ዘበት ነው፡፡ እንዲያውም ከዚህም አልፎ እ.ኤ.አ በ2030 እንኳ የህዝቧ ቁጥር ከ130 ሚሊዮን በላይ ከፍ እንደሚል በሚገመትበት ጊዜም ቢሆን ይህ መንግስት እና የተሳሳተ ፖሊሲው እስካልተቀየሩ ድረስ ሀገሪቱ በፍጹም እራሷን ልትመግብ አትችልም፡፡
በአሁኑ ጊዜ የይስሙላ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆኖ በአሻንጉሊትነት እያገለገለ የሚገኘው ኃይለማርያም ደሳለኝ እ.ኤ.አ በ2011 የውጭ ጉዳይ እና ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር በነበረበት ጊዜ እርሱ የሚመራው መንግስት ረኃብን ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ መንግሎ ማስወገድ እንደሚችል እና በአጭር ጊዜ ውስጥ ድህነትን ተረት እንደሚያደርግ በጣም እርግጠኛ በመሆን ተናግሮ ነበር፡፡
ኃይለማርያም ከአፍሪካ ኮንፊደንሻል ጋር በተደረገ ቃለመጠይቅ እንዲህ በማለት ድንፋታ አሰምቶ ነበር፣ “ላለፉት ሰባት ዓመታት ኢትዮጵያ ባለሁለት አሀዝ የምጣኔ ሀብት እድገት አስመዝግባለች፣ ይህም የሚያመላክተን የምጣኔ ሀብት ፖሊሲያችን በጥሩ ሁኔታ እየሰራ ያለ መሆኑን ነው፡፡ ይህንን የምጣኔ ሀብት እድገት በዚሁ ፍጥነት የምናስቀጥል ከሆነ በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት የምጣኔ ሀብታችንን አሁን ካለበት በእጥፍ ማሳደግ እንችላለን፡፡ ይህም ማለት የማህበረሰባችንን ገቢ በእጥፍ እናሳድጋን፣ ይህንንም በማድረግ ድህነትን 50 በመቶ እንቀንሳለን፡፡” በማለት ጠብደል እና ዓይን ያወጣ ውሸት ዋሽቶ ነበር፡፡
በኢትዮጵያ ተንሰራፍቶ ለሚገኘው ረሃብ ዋና መንስዔዎች የመልካም አስተዳደር እጦት እንጂ ድርቅ አይደለም፡፡ የችግሩ መንስዔ አንኳር ችግር በየደረጃው የሚገኘው የመንግስት አካላት ብቃት የለሽነት እና ብልሹ አስተዳደር እንጅ አካባቢያዊ ነገሮች አይደሉም፡፡
በኢትዮጵያ በተደጋጋሚ እየተከሰተ ያለው ረሃብ ሰው ሰራሽ ነው፡፡ ይህም ማለት ለረሃቡ መንስዔ ሙስና፣ ብልሹ አስተዳደር፣ የሙያ እና የአስተዳደር ብቃትየለሽነት እና በአሁኑ ጊዜ በሀገሪቱ ላይ ተንሰራፍቶ የሚገኘውን ችግር ለማስወገድ የሚያስችል የፖለቲካ ፈቃደኝነት እና ፍላጎት የሌለው አምባገነን እና ጨካኝ የወሮበላ መንግስት በስልጣን እርካብ ላይ ተፈናጥጦ የመገኘቱ ሁኔታ ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ በስልጣን እርካብ ላይ ተንጠልጥለው የሚገኙት ቡድኖች ትክክለኛ ለሆነ ዕቅድ እና ለህዝቦች ደህንነት ጠቀሜታ ያላቸውን ፖሊሲዎች ለመንደፍ የማይችሉ ሀሳበ ግትር እና ለለውጥ በምንም ዓይነት መልኩ ዝግጁ ያልሆኑ የጫካ ወሮበላ የአስተሳሰብ አድማስን የተላበሱ ፍጡሮች ናቸው፡፡
የዓለም ባንክ ዋና የምጣኔ ሀብት ባለሙያ የሆኑት ወልፍጋንግ ፌንግለር እ.ኤ.አ ነሐሴ 17/2011 ቀጥተኛ በሆነ መልኩ እንዲህ ብለው ነበር፣ “ይህ በኢትዮጵያ ያለው የረሃብ/ቸነፈር ቀውስ ሰው ሰራሽ ነው፡፡ የድርቅ አደጋዎችደግመው ደጋግመው በየጊዜው ይከሰታሉ፣ ሆኖም ግን እነዚህ ድርቆች ወደ ረሃብ እንዲያመሩ የሚያደርጋቸውትልቁ ነገር መጥፎ ፖሊሲን የመንደፍ ሁኔታ ነው፡፡“
በእርግጥ ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ህዝቦቻቻውን በተሻለ ሁኔታ ከማይመግቡ በዓለም ላይ ከሚገኙ 125 አገሮች በ123 ደረጃ ላይ ትገኛለች፡፡ እንደ አዲሱ የኦክስፋም የምግብ መረጃ ቋት ከሆነ “በዓለም ላይ የተትረፈረፈ፣ የተመጣጠነ፣ ጤናማ እና ህዝቡ እንደልብ ሊገዛው የሚችል ምግብ በማግኘት ኔዘርላንድ በቁጥር አንድ ላይ የምትገኝ ስትሆን ቻድ በ125ኛ ደረጃ ላይ በመቀመጥ የመጨረሻ በመሆን ኢትዮጵያን እና አንጎላን ታስከትላለች፡፡”
አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ እየመነመነ ስለመጣው የዝናብ ስርጭት እና በኢትዮጵያ ስጋት ሆኖ በመቅረብ ላይ ስላለው ረኃብ ያሳሰበው መሆን አለመሆኑን በተጠየቀ ጊዜ ለሰጠው መልስ እንዲህ የሚል ቀልድ ወጥቶበታል፣ “ስለዝናብ ሁኔታ በኢትዮጵያ አንጨነቅም፣ እኛ የምንጨነቀው በአሜሪካ እና በካናዳ ስለሚኖረው ዝናብ ነው፡“ እኛ በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ በውጭ ሀገር ባሉ ባንኮች ስናጭቅ አሜሪካውያን እና ካናዳውያን የእኛን ረሃብተኛ ህዝብ ይመግባሉ፡፡
አሜሪካ የከባቢ አየር ለውጥ ክህደት ፈጻሚዎች አሏት፣ ኢትዮጵያ ደግሞ የረሃብ/ቸነፈር ክህደት ፈጻሚዎች አሏት፡፡ እራሱን ህዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ (ህወሀት) እያለ እንደሚጠራው የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ  ረሃብ በኢትዮጵያ ማታለያ ነው!
እውነታዎች እንዲህ ይናገራሉ፡፡
እ.ኤ.አ የካቲት 2014 እንዲህ የሚል ዘገባ ቀርቦ ነበር፣ “2.7 ሚሊዮን የሆኑ ለረሃብ የተጋለጡ ዜጎችን ለመመገብ ኢትዮጵያ የውጭ እርዳታ ሰጭዎችን እገዛ ትፈልጋለች፡፡“ ይህ እ.ኤ.አ በ2014 መጀመሪያ አካባ ነበር የተደረገው፡፡
እ.ኤ.አ በ2013 ኢትዮጵያ ከ4 ሚሊዮን በላይ የሆኑ የረሃብ ሰለባ የሆኑ ዜጎቿን ለመመገብ ወደ 700 ሚሊዮን ዶላር አካባቢ የሰብአዊ እርዳታ ተቀበለች፡፡
እ.ኤ.አ መስከረም 2012 “የኢትዮጵያ መንግስት ባለፈው ሳምንት 3.7 ሚሊዮን የሚሆኑ የኢትዮጵያ ዜጎች በዚህ ዓመት ከነሐሴ እስከ ታህሳስ ላሉት ወራት እስከ ጥር ደግሞ 3.2 ሚሊዮን ለሚሆኑ ለረሃብ ለተጋለጡ ዜጎች እንደሚያስፈልግ ይፋ አደረገ፡፡“
እ.ኤ.አ በ2011 በኢትዮጵያ የዓለም አቀፍ የሰብአዊ የምግብ እርዳታ አብዛኛው ከዩናይትድ ስቴትስ የሆነ 500 ሚሊዮን ዶላር እርዳታ ተገኘ፡፡
እ.ኤ.አ ነሐሴ 2010 የተባበሩት መንግስታት የምግብ እና የግብርና ድርጅት ኢትዮጵያን በማስመልከት እንዲህ የሚል አገባ አቀረበ፣ “ወደ 5.2 ሚሊዮን የሚገመቱ ኢትዮጵያውያን እስከ አሁን ድረስ ለአስቸኳይ የምግብ እርዳታ ጥገኛ ሆነው የዘለቁ ሲሆን በረዥም የጊዜ ዕይታ ደግሞ ሀገሪቱ ወደ ከፋ የምግብ ቀውስ ሁኔታ ውስጥ ልትገባ እንደምትችል ድርጅቶቹ ስምምነት ላይ ደረሱ፡፡“
እ.ኤ.አ ነሐሴ 2009 እንዲህ የሚል ዘገባ ቀርቦ ነበር፣ “በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ድሆች አስከፊ ለሆነ የምግብ ንጥረ ነገር ጉድለት በቀጣይነትም ወደ ረሃብ ቀውስነት ሊለወጥ ወደሚችል ችግር ተጋልጠዋል፣ እናም ለበርካታ አስርት ዓመታት በሀገሪቱ ታይቶ በማይታወቅ መልኩ ከዚህ የበጋ ወቅት ጀምሮ አስከፊ የምግብ ቀውስ ሊከሰት ይችላል፡፡ የምግብ እርዳታ ፈላጊው ቁጥር በዚህ ዓመት በጥር ወር ከ4.9 ሚሊዮን እስከ ግንቦት ድረስ 5.3 ሚሊዮን እንዲሁም እስከ ሰኔ ድረስ 6.2 ሚሊዮን የሚሆን ተረጅ ህዝብ ይኖራል ተብሎ ይገመታል፡፡“
ላለፉት ሁለት አስርት ዓመታት በእያንዳንዱ ዓመት ለረሃብ ሰለባነት የተጋለጡ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያንን ለመመገብ የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ አስቸኳይ የምግብ እርዳታ ጥያቄ ሲያቀርብ ቆይቷል፡፡
እርዳታ ሰጭ ድርጅቶች በረሃብ ለተጎዳው በ10 ሚሊዮኖች ህዝብ የእርዳታ እጃቸውን ሳይዘረጉ የዝሆን ጆሮ ይስጠኝ በማለት ጆሮ ዳባ ልበስ ባሉበት ወቅት የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ ምንም ዓይነት ኃላፊነትን ሳይቀበል በርካታ ህዝቦች በረሃብ እንዲያልቁ አድርጓል፡፡
የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ በኢትዮጵያ ለረሃቡ ያለው ኃላፊነት መለመን፣ አኩፋዳውን እየከፈተ ጨምሩልኝ እያለ መለመን እንጅ ሌላ ረሃብን ሊያስወግዱ የሚችሉ ፖሊሲዎችን በመንደፍ በስራ ላይ ማዋል አይደለም፡፡
በየዓመቱ የምግብ እርዳታ መለመን እና ምጽዋዕት መጠየቅ ለወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ የክብር መገለጫ ባህል ሆኖ በመዝለቅ ላይ ይገኛል፡፡
ለማኝ መንግስት መሆን ምን ያህል አሳፋሪ ነገር ነው!!!
በአሁኑ ጊዜ የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ በኢትዮጵያ ስም በመለመን ላይ ይገኛል፡፡ ምን ዓይነት የወረደ ነገር ነው፣ ምን ዓይነት የሚያሳፍር እና የሚያበግን ነገር ነው!
ረሃብ በቀላል ባቡር በመጋለብ ላይ ይገኛል፣
የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ ባለፈው ሳምንት በአዲስ አበባ ከተማ የባቡር አገልግሎት መጀመሩን ለህዝብ ይፋ አድርጓል፡፡
ይህ በህዝብ መገናኛ ብዙሀን ለህዝብ በሰፊው በመነገር ላይ ያለው ፕሮፓጋንዳ በአሁኑ ጊዜ እየተስፋፋ የመጣውን ረሃብ ለመሸፋፈን ሲባል የፕሮፓጋንዳ ዒላማ አድርጎ የተነሳ እንደሆነ አምናለሁ፡፡
ህዝብ ስለቀላል ባቡሩ “በአፍሪካ የመጀመሪያ የሆነው“ እና ሌላም እንቶ ፈንቶ እና የማይረቡ ነገሮችን የሚያወራ ከሆነ ከዚህ አልፎ እየተንፏቀቀ ስለሚመጣው ከባድ ረሃብ አያወራም፣ እንደዚሁም ደግሞ ስለ4.5 ሚሊዮን እና ከዚያ በላይ ስለሚሆነው ህዝብ የረሃብ ሰለባነት ጉዳይ ቀስ በቀስ ነው እየተገነዘበ የሚመጣው የሚል እምነት አለው የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ፡፡
የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ እኔ እነርሱ የሰሩትን ስራ ሁሉ እንደማንቋሽሽ አድርገው እንደሚያስቡ አውቃለሁ፡፡
እነርሱ የሚያስመዘግቧቸውን ስኬቶች ሁሉ እንደማንኳስስባቸው አድርገው ይናገራሉ፡፡
እነርሱን መጥፎ አድርጌ የማቀርብ እና ምንጊዜም እነርሱን የምቃወም አድርገው ይቆጥራሉ፡፡ ለእነርሱ ምንም ዓይነት እውቅና የማልሰጥ አድርገው ይገምታሉ፡፡
የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ ስለእኔ አንድም ጊዜ ቢሆን የማይናገሯት ነገር ብትኖር  በእነርሱ ጉዳይ ላይውሸት አቅርቧል የምትለዋን ነገር ነውአንድም ጊዜ ቢሆን በፍጹም አይሉም!!! 
በእርግጠኝነት ለመናገር የእኔ ሀሳብ ታዋቂ በሆነው ተንቀሳቃሽ ፊልም ይፋ እንደሚሆነው ሁሉ በተጨባጭ ሁኔታ የሚታይን እውነታ በመያዝ እንጅ “የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን የፈለገዉን ቢያስብ ቢናገር ጉዳዬ አይደለም።
የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ በሰብ ሰሀራ አፍሪካ የመጀመሪያ የሆነውን የባቡር ሀዲድ እንደገነቡ አድርገው ጉራቸውን ይቸረችራሉ፡፡
አሐ! አሐ! አሐ! ያስቃል በፍጹም አላደረጉም፣ ሀሰት ነው፡፡
ግማሽ ቢሊዮን ዶላር የቻይና የብድር ገንዘብ ነው የሰራው፡፡
ይኸ 28 (34?) ኪ/ሜ ርዝመት ይኖረዋል ተብሎ የሚገመተው የባቡር ሀዲድ ወደ 500 ሚሊዮን ዶላር በሚሆን ገንዘብ ተገነባ ሲባል በጣም አስገራሚ እና ታምራዊ ነገር ነው፡፡ በዚህ ስሌት መሰረት በአንድ ኪ/ሜ የባቡር ሀዲድ 18 ሚሊዮን ዶላር ውጭ ተደርጓል ማለት ነው፡፡
በአሜሪካ እንደዚህ ያሉት ግንባታዎች አጅግ በጣም ባነሰ ወጭ ይፈጸማሉ፡፡
በዚህ የባቡር ግንባታ ፕሮጀክት ተብዬ ስራ በወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ ውስጥ ያለ ወሮበላ እርባናቢስ ሀብትን ዘርፏል የሚል እምነት አለኝ!
በእርግጥ ቻይናዎች ለወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ የቀላል ባቡር ግንባታ በተቀበሏቸው የገንዘብ ቁርጥርጮች የብሩክላይንን ድልድይ ለወያኔዎቹ እሸጥላቸው ነበር፡፡ ለወደፊቱ ስምምነት እናደርጋለን፡፡
እንደ ዌልስ አገር በጎች የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ኢትዮጵያን አስላጭቷታል።
ሆኖም ግን የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ በኢትዮጵያ ልማትን እንዴት እንዳመጡ እንዲህ በማለት ሌት ቀን እንደ በቀቀን ይለፈልፋሉ፣ “የቀላል ባቡር ሀዲዱን ተመልከቱ… ከሰብ ሰሀራ አፍሪካ የመጀመሪያ የሆነውን…“
በደናቁርት ስብቦቹ እስቃለሁ፡፡
አንድ ደራሲ ነኝ ባይ ከፍሎ በሌላ ሰው ስላስፃፈው መፅሐፍ አስታወሰኝ። ከፍሎ መፅሐፍ ማስጻፍ ደራሲነት አያረግም።
(ያነጋገሬ  ዘይቤ ስለ ደራሲው ለምሳሌ ብቻ አይደለም። እንደምርመራ ጋዜጠኛ አበበ ገላው በግልጽ አንዳሳየው አብዛኞቹ የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ አመራሮች የአካዳሚክ ዲግሪዎቻቸውን እና የትምህርት ውጤቶቻቸውን ከየቦታው ከፍለው ነው ያገኙት፡፡ እ.ኤ.አ መስከረም 2010 “ማጥመቅ“ በሚል ርዕስ ባቀረብኩት ትችት መሰረት አሁን በህይወት የሌለው አምባገነኑ መለስ ዜናዊ ከኦፕን የኒቨርሲቲ ዲግሪው በቀጥታ ከቢሮው መጥቶለት እንዲቀበል ተደርጓል፡፡ በዚሁ ዓመት በየካቲት ወር አበበ ገላው እንዲህ በማለት አጋልጧል፣ “የኢትዮጵያ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈጉባኤ“ የሆነው አባ ዱላ ገመዳ የሕዝብ አስተዳደር የባችለር እና የማስተርስ ዲግሪዎችን ከኢንተርኔት የሸፍጥ የዲፕሎማ መፈልፈያ ወፍጮ ከሆነው ከአሜሪካ ሴንቹሪ ዩኒቨርሲቲ እ.ኤ.አ እንደ ቅደም ተከተላቸው በ2001 እና በ2004 ተቀብሏል፡፡)
እውነታው ፍርጥርጥ ብሎ ሲታይ ግን 28 ኪ/ሜ የሆነው የባቡር ሀዲድ በቻይናዎች ለወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ የመገንባቱ ሁኔታ ምንም ትልቅ ጉዳይ አይደለም፡፡
የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ ኢትዮጵያ ከቻይና ኢኤክስ-አይኤም/EX-IM ባንክ ከግማሽ ሚሊዮን ዶላር በላይ ብድር እንደወሰደች ሆኖ በእዳ መረብ ውስጥ የማስገባት ክስተት ነው፡፡
ስለባቡር ሀዲድ እየተነጋገርን እስከሆነ ድረስ እ.ኤ.አ በ1894 ዳግማዊ ምኒልክ 2ኛ በአደዋ ጦርነት የጣሊያን ወራሪ ኃይሎችን ድባቅ በመምታት ድል ከመቀዳጀታቸው ሁለት ዓመታት በፊት 617 ኪ/ሜ ርቀት ያለውን ከባድ የባቡር ሀዲድ እንዲገነቡት እና እንዲያስተዳድሩት ከፈረንሳዮች ጋር ስምምነት አድርገው ነበር፡፡
በአሁኑ ጊዜ የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ አሁን በህይወት የሌለው እና ትንሹ አምላካቸው የነበረው አምባገነኑ መለስ ዜናዊ ጀምሮት የነበረውን የባቡር ሀዲድ ፕሮጀክት እንደታላቅ ነገር በመቁጠር በሰብ ሰሀራ አፍሪካ የመጀመሪያ የሆነው እያሉ የዳግማዊ ምኒልክ 2ኛን ክብር እና ሞገስ በማሳነስ የአምባገነኑን የመለስን ስብዕና ከፍ ለማድረግ በማሰብ አደንቋሪ ልፍለፋቸዉን በማሰማት ላይ ይገኛሉ፡፡
ይኸ እውን የሚሆነው በህልማቸው ብቻ ነው!!!
የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ የንጉስ ዳግማዊ ምኒልክ 2ኛን የስልጣኔ መዝገብ ከአምባገነኑ መለስ ዜናዊ ጋር ለማነጻጸር የሚፈለግ ከሆነ ይህንን ንጽጽር ከህዝብ አስተዳደር ጀምሮ እስከረቀቀው ቴክኖሎጂ ድረስ ያሉትን ጉዳዮች በማካተት ልንወያይ እንችላለን፡፡
ንጉስ ዳግማዊ ምኒልክ 2ኛ በአፍሪካ አህጉር ውስጥ የስልክ እና የቴሌግራፍ መስመር ዝርጋታ ስርዓትን ተግባራዊ ያደረጉ ብቸኛው የአፍሪካ መሪ ነበሩ፡፡
አሌክሳንደር ግርሃም ቤል የድምጽ መነጋገሪያ መሳሪያውን የባለቤትነት መብት ማረጋገጫውን ፓተንት ከማግኘታቸው ከ13 ዓመታት በፊት እ.ኤ.አ በ1889 የመጀመሪያው የስልክ መስመር በምኒልክ ቤተመንግስት ውስጥ በተዘረጋበት ጊዜ የስልጣኔ አደናቃፊ አዛውንት መኳንንቶች እና መሳፍንቶቻቸው ንጉስ ምኒልክን ይህ ነገር የሰይጣን ስራ ነውና ከቤተመንግስትዎ ውስጥ ያስወግዱት ብለዋቸው ነበር፡፡
የብሩህ አዕምሮ ባለቤት የሆኑት ዳግማዊ አጼ ምኒልክ ግን በፍጹም አይሆንም በማለት ሳይቀበሏቸው በመቅረት ቴክኖሎጂውን እያስፋፉ በጥቅም ላይ እንዲውል ያደረጉ ብልህ እና ጀግና ንጉስ ነበሩ፡፡
በአሁኑ ጊዜ በወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ አምባገነናዊ ስርዓት ውስጥ አሳር ፍዳዋን በመቀበል ላይ ያለችው ኢትዮጵያ በኢንተርኔት ስርጭት ምጣኔ ከሰብ አፍሪካ ሀገሮች ውስጥ ከመጨረሻው በመሆን በ2ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች፡፡
የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ ሀሳብን በነጻ የመግለጽን እና የነጻ ፕሬስ መስፋፋትን ኢንተርኔት የተባለው የግንኙነት ሰይጣን ይቆጣጠረዋል በማለት ፍርሀት እና ስጋት ያለው እንደሆነ አድርጌ እገምታለሁ፡፡
በእርግጥ ቻይናዎች ለእነርሱ የግል ጥቅማቸው ሲሉ መንገዱን ዘርገተዋል፡፡ በማታለል የመሰረተ ልማትን መሸጣቸው ይሆን?
በእርግጠኝነት እ.ኤ.አ በ2012 በአፍሪካ ላይ የተደረገውን ታላቅ የቅሌት ክስተት በርካታ አንባቢዎቼ ታስታውሱታላችሁ ብዬ አስባለሁ፡፡
ስምን በመቀያየር እድገት እና ልማት ይመጣ ይመስል ከአውሮፓ ህብረት በመኮረጅ ቀደም ሲል የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ይባል የነበረውን ስም በመቀየር እና አሁን የአፍሪካ ህብረት ትብሎ እንዲጠራ ያደረጉትን ህንጻ ቻይናዎች በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ከ200 ሚሊዮን ዶላር በላይ በሚሆን ገንዘብ ገንብተው ለአፍሪካ መሪዎች በስጦታ መልክ ሰጡ፡፡
ሊታመን የማይችል ጉድ ነገር ነው!
የአፍሪካ መሪዎች እየተባሉ የሚጠሩት ስብስቦች ለሁሉም አፍሪካውያን ልዩ የክብር መገለጫ የሚሆነውን ህንጻ ትንሽ የሆነቸውን 200 ሚሊዮን ዶላር ከእራሳቸው ካዝና በማዋጣት ለማሰራት አልቻሉም፡፡
ከቻይናን ምጽዋት በመለመን ማሰራት ነበር የፈለጉት፡፡
የአፍሪካ መሪዎች የአፍሪካ አህጉርን የለማኞች እና የምጽዋት ፈላጊዎች አህጉር በማለት ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ማሳየታቸው ምን ያህል የወረደ እና አሳፋሪ ድርጊት ነው!
አፍሪካዊ በመሆኔ ብቻ በህይወቴ ውስጥ እስከ አሁን ድረስ በሀፍረት እንድሸማቀቅ ያደረገኝ ድርጊት ቢኖር ክስተት ብቻ ነው
“የአፍሪካ ለማኞች አዳራሽ” በሚል ርዕስ አቅርቤው በነበረው ትችቴ ላይ በአፍሪካ ለማኝ ፕሬዚዳንቶች እና ጠቅላይ ሚኒስትሮች በጣም ተበሳጭቸ እና በሀፍረት ተሸማቅቄ እንደነበር ግልጽ አድርጌ ነበር፡፡ በዚያ ትችቴ ላይ የአፍሪካውያን ክብር እና ሞገስ በትንሿ 200 ሚሊዮን ዶላር ለቻይናዎች ተሸጠ ብየ ነበር፡፡
ይቅርታ ሊደረግለት የማይችል ድርጊት!
ታዋቂ የሆኑት ጋናዊ የምጣኔ ሀብት ባለሙያ ጆርጅ አይቴይ የተባበሩት መንግስታትን መረጃ ዋቢ በማድረግ እንዲህ የሚል የክርክር ጭብጣቸውን አቅርበዋል፣ “እ.ኤ.አ በ1991 ብቻ 200 ቢሊዮን ዶላር ወይም ደግሞ የሰብ ሰሀራን ሀገሮች ዓመታዊ ጥቅል ምርት/Gross Domestic Product (GDP) 90 በመቶ የሚሆነው ገንዘብ ወደ ውጭ ሀገር ባንኮች ወጭ ተደርጎ ታጭቋል፡፡“
እ.ኤ.አ በ2011 ግሎባል ፋይናንሻል ኢንቴግሪቲ/Global Financial Integrity የተባለው ዓለም አቀፍ ድርጅት ኢትዮጵያን በማስመልከት እንዲህ የሚል ዘገባ አቅርቦ ነበር፣ “በአፍሪካ አህጉር ካለችው ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ በ2009 ካለፈው ዓመት በእጥፍ በሚበልጥ ሁኔታ በሕገ ወጥ መልክ 3.2 ቢሊዮን ዶላር የሚሆን ገንዘብ በሙስና፣ በስጦታ እና በጉቦ ከሀገር እንዲወጣ ተደርጓል፡፡“
ሁሉም 54ቱ የአፍሪካ ሀገሮች ለአህጉሩ ታላቅ ውበትን እና ልዩ የሆነውን ህንጻ ለመግንባት 200 ሚሊዮን ዶለር በማዋጣት ለመስራት አልቻሉም፡፡
እንግዲህ በዚህ ዓይነት ሁኔታ ነው አፍሪካውያን የአፍሪካን ህብረት የለማኞች የመሰብሰቢያ አዳራሽ ለማግኘት የቻሉት!
ሆኖም ግን ቻይናዎች የቀላል ባቡር ሀዲድ ፕሮጀክት እየተባለ የሚጠራው የባቡር ሀዲድ ቻይናዎች እንደሚሉት “በመስታወት ውስጥ እንደሚታይ አበባ” ወይም ደግሞ “በውኃ አካል ላይ እንደምትታየዋ ጨረቃ” ዓይነት ነው፡፡
ይህንን አባባል የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ ደናቁርት ምን ለማለት እንደፈለግሁ አይገነዘቡትም፣ ሆኖምግን ቻይናዎች በትክክል ምን ለማለት እንደፈለግሁ ይገነዘቡታል!
ይኸ ሁሉ የሚደረገው ነገር ለማስመሰያ እና ቀልብን ወደ ሌላ አቅጣጫ ለማስቀየስ ነው፡፡ የአፍሪካ ህብረት መናገሻ በሆነችው በአዲስ አበባ ከተማ የባቡር ሀዲድ ስራና ለቀሪው ዓለም በማሳዬት በቀሪዎቹ የአፍሪካ ሀገሮች አንቴና ቀንዶችን በደንብ አድርጎ በማስገባት ደማቸው እስኪደርቅ ድረስ ሙልጭ አድርጎ መምጠጥ ነው፡፡
ታላቅ ቅሌት!
ሆኖም ግን የእኔ ትልቁ ጥያቄዬ እንዲህ የሚል እና ፍጹም በሆነ መልኩ የተለዬ ነው፡ 28 ኪ/ሜ ርዝመት ያለው የጉራ እና የታዕይታ ፕሮጀክት በግማሽ ቢሊዮን ዶላር ከመገንባት ይልቅ በረሃብ የተጎዱ ኢትዮጵያውያንን ህይወት ለማዳን በሚያስችል ነገር ላይ ማዋል የበለጠ ትርጉም የሚሰጥ ሊሆን አይችልምን?
ድምጼን ከፍ በማድረግ እንዲህ በማለት ደግሜ እለዋለሁ፡ 28 / ርዝመት ያለው የጉራ እና የታዕይታፕሮጀክት በግማሽ ቢሊዮን ዶላር ከመገንባት ይልቅ በረሃብ የተጎዱ ኢትዮጵያውያንን ህይወት ለማዳን በሚያስችልነገር ላይ ማዋል የበለጠ ትርጉም የሚሰጥ ሊሆን አይችልምንአለቀ ይኸው ነው በቃ!!!
ለዘመናት የረኃብን የማስጠንቀቂያ ደወሎች መደወል!
የረሃብን የማስጠንቀቂያ ደወል ለጥቂት ዓመታት ያህል ደውያለሁ፡፡
እውነት ለመናገር የለጋሽ ሀገሮች እና የእርዳታ ሰጭ ድርጅቶች እንዲሁም የውጭ ጋዜጠኞች በኢትዮጵያ እየተንፏቀቀ የሚመጣውን ረሃብ በዓለም ላይ የአደባባይ ታላቅ ሚስጥር አድርገው ለመያዝ ይሞክራሉ፡፡ በረሃቡ አደጋ የሞቱትን የረሃብ ሰለባ ፍቶግራፎች በእርግጠኝነት እስከ አሁን ድረስ ያዬ ይኖራልን?
በረሃብ አደጋ ከተጠቁ አካባቢዎች ማንኛውም ዓይነት ዘገባ እንዳይወጣ ከፍተኛ የሆነ እገዳ እና ፍጹም የሆነ ቁጥጥር እንዳለ ግልጽ የሆነ ነገር ነው፡፡
እ.ኤ.አ. ጥቅምት 2012 “ኢትዮጵያ፡ በ2013 ስለሚከሰተው ረሃብ ቅድመ ማስጠንቀቂያ“ በሚል ርዕስ የረሃብ ማስጠንቀቂያ ደወሉን በመደወል ትችት አቅርቤ ነበር፡፡
የረሃብ ቅድመ ማስጠንቀቂያ ስርዓት መረብ/Famine Early Warning Systems Network (FEWS NET)ን ጨምሮ ሌሎች በርካታ ድርጅቶች ማለትም ኦክስፋም፣ የተባበሩት መንግስታት የምግብ ፕሮግራም፣ የተባበሩት መንግስታት የምግብ እና የግብርና ድርጅት እና የአዲሲቷ እንግሊዝ ውስብስብ ስርዓት ተቋም/New England Complex Systems Institute (NECSI) (የአካባቢ ስነምህዳር ለውጦች እንዴት አድርገው ወደ ፖለቲካ አለመረጋጋት እና ቀውስ ሊሸጋገሩ እንደሚችሉ የተለየ ልምድ ያካበቱት ከሐርቫርድ/Harvard እና ከኤምአይቲ/MIT ዩኒቨርሲቲዎች የትንበያ ሙያ ካላቸው የአካዳሚክ ቡድን የተውጣጣ ስብስብ) ያወጧቸውን ግኝቶች በጥንቃቄ በማጥናት እና በመተንተን እ.ኤ.አ 2013 በኢትዮጵያ ረሃብ የሚጀምረበት ወይም ደግሞ እነርሱ በተለያየ ስያሜ እንደሚጠሩት አሰቃቂ የምግብ ቀውስ እንደሚከሰት ግልጽ ሆኖልኝ ነበር፡፡
እ.ኤ.አ በ2012 ሁለተኛው አጋማሽ ከአምራች ሀገሮች ወደ ውጭ የሚወጡ ምርቶች መቀነስ እ.ኤ.አ በ2013 በዓለም አቀፍ የምግብ ሸቀጦች ላይ የዋጋ ጭማሪ ነውጥ ሊያስከትል እንደሚችል ጠቅላላ ስምምነት ተደርሶ ነበር፡፡
በአሁኑ ጊዜ የናሙና ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ መንግስት የውጭ ምንዛሬ ክምችቱ እየተሟጠጠ ባለበት ሁኔታ እና ከማይቀረው የዓለም የምግብ ቀውስ አንጻር በሀገሪቱ ውስጥ አስከፊ በሆነ መልኩ ወደፊት ሊከሰት የሚችለውን ረሃብ እንዴት አድርጎ ሊቋቋመው እንደሚችል ለማወቅ እፈልጋለሁ፡፡
የበለጠ ምጽዋዕት መጠየቅ እና የምግብ ልመናን የማካሄድ ዕቅድ ብቻውን በማድረግ በአስቸኳይ የምግብ እርዳታ መጠየቅ ችግሩን ሊቋቋመው አይችልም፡፡ በምግብ ለስራ ፕሮግራም/Productive Safety Net Program ላይ ጥገኛ በመሆን መስራት የሚያመጣው ለውጥ አይኖርም፡፡
ላለፉት 5 ዓመታት የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ አገዛዝ በተደጋጋሚ የሚከሰተውን ረሃብ ለማስቆም ምንም ዓይነት የሰራው ነገር የለም፡፡ ይቅርታ ማስተካከያ፡ የሰራውማ ስራ አለ እንጅ፣ ለምግብ እርዳታ የዓለምን ህዝብ ለምኗል!
ዓመት ከዓመት የይስሙላው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም እና የወያኔ ግብረ አበር ሸፍጠኞች አንድ ላይ ተቀምጠው የለመና አጃቸዉን ቀሰረው  የአሜሪካንን ግብር ከፋይ ህዝብ ዶላር የምግብ እርዳታው እስከሚመጣ ድረስ ቁጭ ብለው ዝንቦችን ከፊታቸው አያባረሩ ይጠብቃሉ።
በተጻራሪው አስገራሚው ነገር ደግሞ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ዜጎች በረሃብ እያለቁ በሚገኙበት ጊዜ የሀገሪቱ በጣም ለም የሆኑ መሬቶች በእነዚህ መሬቶች ላይ አምርተው ወደየሀገሮቻቸው በመውሰድ የእራሳቸውን ዜጎች መመገብ እንዲችሉ ለሳውዲ አረቢያ፣ ለህንድ እና በግብርና ስራ ላይ ለተሰማሩ የንግድ ኩባንያዎች እየታደሉ እና ቻይና በኢትዮጵያ በግብርናው ዘርፍ ጠልቃ በመግባት ዕቅዷን በቆሸሸ መልኩ በመተግበር ላይ ትገኛለች፡፡ ምን ዓይነት አዋራጅ እና አሳፋሪ ነገር ነው!
ባለሁለት አሀዝ የምጣኔ ሀብት ዕድገት፣ የምጣኔ ሀብቱን በእጥፍ ማሳደግ፣ ትርፍ እና የተትረፈረፈ ምርት፣ እና በቀን ሶስት ጊዜ መመገብ! ምን የማይባል ነገር አለ!
በእርግጥ ሰብአዊ እርዳታ ለወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ አመራሮች የገቢ ምንጭ ነው፡፡ (“የሌብነት ሕጋዊነት” በሚል ርዕስ ከዚህ ቀደም አቅርቤው የነበረውን ትችቴን ይመልከቱ፡፡)
በኢትዮጵያ የተደበቀውን ረሃብ ማጋለጥ፣
ባለፉት ጥቂት ዓመታት በኢትዮጵያ በተለያዩ ጊዚያት በተለይ ስለሚከሰቱት ረሃቦች ወይም ደግሞ በሌሎች ተመሳሳይ ጉዳዮች ላይ ትችት ሳቀርብ ቆይቻለሁ፡፡ (በግርጌ ማስታዋሻ ላይ የተቀመጡትን የግንኙነት መስመሮች ይመልከቱ፡፡)
ከምግብ እጦት ምክንያት ከሚሞቱት እና ከሚሰቃዩት በ10 ሺዎች የሚቆጠሩ የረሃብ ሰለባ ህዝቦችን ከዓለም አቀፍ እና ከሀገር ውስጥ ጋዜጠኞች ለመደበቅ እና ረሃብን ድብቅ አድርጎ ለማቆየት ገዥዎች የሚያደርጉትን ድብብቆሽ እና ክልከላ በተደጋጋሚ ግልጽ ለማድረግ ሞክሪያለሁ፡፡
የመለስ/ኃይለማርያም አገዛዞች ረሃብን ሚስጥራዊ አድርጎ ለመቆየት ከእነርሱ በፊት የነበሩትን ገዥዎች እግር ተከትለዋል፡፡ ግርማዊ ቀዳማዊ አጼ ኃይለ ስላሴ እ.ኤ.አ በ1974 ተከስቶ የነበረውን “ድብቁ ረሃብ” የሚለው ዘጋቢ ፊልም ለህዝብ ዕይታ በአየር ላይ እስከዋለ ድረስ ርሃብ መኖሩን አላውቅም ብለው ነበር፡፡
የቀድሞው ወታደራዊ አምባገነን መሪ የነበሩት ኮሎኔል መንግስቱ ኃይለ ማርያም እ.ኤ.አ በ1985-86 ተከስቶ በነበረው ረሃብ እብሪት በተቀላቀለበት መልኩ ሙልጭ አድርገው በመካድ ድንገተኛ በሆነ መልኩ “የምን ረሃብ?” የሚል ጥያቄ ያዘለ ምላሽ ሰጥተው ነበር፡፡
መለስ፣ ኃይለማርያም እና ግብረአበሮቹ እንዲሁም ከእርሱ በፊት የነበሩት ገዥዎች የረኃብን መከሰት ጉዳይ በማስመልከት ከህዝብ እይታ ለመደበቅ በሚያደርጉት ጥረት የበለጠ አታላዮች ነበሩ፡፡ ይህንን እኩይ ምግባራቸውን ለመደበቅ የሚጠቀሙባቸው ዘዴዎች ደግሞ፣ 1ኛ) የአገር ውስጥ ብዙሀን መገናኛዎች እንዳይዘግቡ ጥብቅ ቁጥጥር ማድረግ እና ሊያመጣ የሚችለውን እና ከፍተኛ የሆነ የሰብአዊ ቀውስ ሊያስከትል የሚችለውን ረኃብ ለመዘገብ ፍላጎት ላላቸው ለዓለም አቀፍ ጋዜጠኞች እና ለብዙሀን መገናኛ ወኪሎች ሁሉ አገሪቱ ዝግ እንድትሆን ማድረግ፣ 2ኛ) ከሚያብረቀርቁ የልመና አኩፋዳዎቻቸው ጋር በመሆን ከምዕራቡ ዓለም ኤምባሲዎች ቅጥር ግቢ ውጭ ለልመና መቆም ዋና ዋናዎቹ ናችው፡፡
እ.ኤ.አ በ2015 የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ፣ የእነርሱ ታዛዥ ሎሌዎች፣ ተባባሪዎች እና ካድሬዎች በአስር እና በሺዎች የሚቆጠሩ ዶላሮችን ልዩ ለሆኑ ልብሶች፣ ጫማዎች፣ የእጅ ቦርሳዎች እና ሽቶዎች፣ እንዲሁም በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ዶላሮችን በቅንጦት ተሽከርካሪ መኪኖች፣ በእስፖርት አገልግሎት መኪኖች ግዥዎች ወጭ ማድረግ እና በብዙ ሚሊዮን ዶላሮች ወጭ የተደረገባቸውን ህንጻዎች እና ለእነዚህ ውድ ህንጻዎች ማስዋቢያ የቤት ቁሳቁሶችን እና የምግብ ቤቶችን ዕቃዎች ከአውሮፓ ያስመጣሉ፡፡
ከግሎባል ፋይናንሻል ኢንቴግሪቲ ከተገኘው ዘገባ መገንዘብ እንደሚቻለው በቢሊዮን የሚቆጠሩ ዶላሮችን በውጭ ሀገር በሚገኙ ባንኮች እና ድብቅ በሆኑ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ላይ ያጭቃሉ፡፡
እ.ኤ.አ በ2015-16 በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ለአስከፊ ረሃብ ይጋለጣሉ፡፡
እንግዲህ ይህ ሁኔታ አሳዛኝ ክስተት ሆኖም ግን በኢትዮጵያ በእውን ያለ ተጨባጭነት ያለው ታሪክ ነው፡፡
ለህዝብ ዘገባ የሚያቀርበውን ፕሬሱን በማስፈራራት፣ በኢትዮጵያ በስልጣን ላይ ያለው ገዥ አካል በኢትዮጵያ ያለው ረሃብ ድብቅ ሆኖ እንዲቀር እና በሀገር ውስጥም ሆነ በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ዘንድ እንዳይታወቅ ሚስጥር ሆኖ እንዲቀመጥ ጥረት ያደርጋል፡፡
ሆኖም ግን ለማርቲን ጌይስለር፣ አይቲኤን/ITN እና ለኤንቢሲ/NBC ድፍረት ምስጋና ይግባውና ባለፈው ዓመት ስለነበረው ሰብአዊ ቀውስ የተወሰነ ግንዛቤ እንድንጨብጥ አስችሎናል፡፡
ለጋሽ ድርጅቶች፣ ዓለም አቀፍ እርዳታ ሰጭ ድርጅቶች፣ የውጭ ጋዜጠኞች በኢትዮጵያ ስላለው የረሃብ ሁኔታእውነታውን ይናገራሉ!
በኢትዮጵያ የተከሰተውን ረሃብ ከህዝብ ለመደበቅ ጸጥ የማለት ዓለም አቀፋዊ ሸፍጥ አለ፡፡
ለሁለት አስርት ዓመታት ያህል  በኢትዮጵያ ላይ ባለው ገዥ አካል እና በዓለም አቀፍ ለጋሽ ድርጅቶች፣ እርዳታ ሰጭ ባለሙያዎች፣ ዓለም አቀፍ ሰራተኞች እና መንግስታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች መካከል በሚገባ በተቀነባበረ የዝምታ ሸፍጥ ምክንያት አስፈሪውን በ “ረ” (ረሃብ ) በማለት የሚጀምረዉን ቃል በኢትዮጵያ ውስጥ አይጠቀሙም፡፡ ሆን ተብሎ ህዝብን ለማሳሳት በሚነገር በቢሮክራሲ የተተበተበ የሀሰት ቃላትና ንግግር ለህዝብ ግልጽ አንዳይሆኑ ዓለም አቀፍ የድህነት አቃጣሪዎች/International Poverty Pimps (IPPs) እያልኩ የምጠራቸው በብዙሀን መገናኛ ዘዴዎች እንዳይለቀቅ በሚል እሳቤ እውነታውን ሸፍኖ ረኃቡን ከህዝብ ደብቆለማቆየት ረዥም ርቀት ተጉዘዋል፡፡
የዚህን ሸፍጥ ውስጣዊ ባህሪ “እ.ኤ.አ በ2013 መጀመሪያ አካባቢ ስለሚከሰተው ረሃብ ማስጠንቀቂያ“ በሚል ርዕስ እ.ኤ.አ ጥቅምት 2012 አቅርቤው በነበረው ትችቴ ውስጥ ገለጻ አቅርቤበታለሁ፡፡
እነዚህ ዓለም አቀፍ የድህነት አቃጣሪዎች ስለምግብ ዋስትና እጦት የተለያዩ ደረጃዎች እንጅ ረሃብን በትክክለኛው ስሙ በፍጹም ረሃብ ብለው አይጠሩትም፡፡
የሰዎች የምግብ መራብ ፍላጎት እና የምግብ እጦት/Hungry and Starving “ኃይለኛ የምግብ ዋስትና እጦት”/”Acute Food Insecurity”፣ አሳሳቢ የምግብ ሁኔታዎች ማጋጠም/Face “stressed” food situations፣ ወደ ቀውስ አዝማሚያ የሚሄድ ምግብ እጦት/Go into “crisis” mode፤ ወደ አስቸኳይ የሆነ ምግብ እጦት ደረጃ/Graduate to “emergency” status፣ እና በመጨረሻም ወደ አስከፊ የምግብ እጦት/Catastrophic food shortages የሚሉ ደረጃዎች ስያሜን አያወጡ ይተርካሉ፡፡ በየትኛውም ቦታ ቢሆን “ረኃብ” ወይም “ጠኔ”/”Famine” or “Starvation” የምትል ቃል በአፋቸው አይጠሯትም፡፡
ረኃብ/Famine የሚለው ቃል በኢትዮጵያ ባለው ገዥ አካል እና በብዙ በዓለም አቀፍ ደረጃ በድህነት ስም ለርካሽጥቅማቸው በቆሙ አቃጣሪዎች ለምን እንደማይጠራ የተከለከለበት ምክንያት አለ፡፡
በኢትዮጵያ ውስጥ የሚኖሩ ዓለም አቀፍ ጋዜጠኞች በ”ረ” የምትጀምረውን ቃል ትንፍሽ አይሉም፡፡
ምናልባትም የሙዝ ጋሪው እንዳይገለበጥ ወይም ደግሞ አስከፊ የረሃብ ዘገባ በመቅረቡ ምክንያት ቀላሉ ባቡር እንዳይቆም ተፈልጎ ይሆናል፡፡ (ለመሆኑ ቀኑን ሙሉ ምንድን ሲያደርጉ ይውላሉ?)
በ”ረ” የምትጀምረውን ቃል ለምን ደፍረው እንደማይናገሩባት ምክንያቱ ግልጽ ነው፡፡ በኢትዮጵያ እ.ኤ.አ ከ1980ዎቹ ጀምሮ በረኃብ ብዙ ሆዳቸው የተነፋ በበረሃ በተቃጠለ የመሬት ገጽታ ላይ የሚንከላወሱ፣ እግር እና እጃቸው የተጠማዘዘ የረኃብ ሰለባ እሬሳዎችን በግራር ዛፎች ስር እና ሆዳቸው ተነፍቶ በዝንቦች የተወረሩ ህጻናት እናታቸውን አጥብቀው እንደያዙ በመመገቢያ ካምፖች ውስጥ ሆነው በአእምሮ ላይ ስሎ ያሳያልና ነው፡፡
በኢትዮጵያ ስለረኃብ በግልጽ ማውራት በለጋሽ ድርጅቶች/በመንግስታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች እና በገዥው አካል አደገኛ ሁኔታ ነው፣ ምክንያቱም የፖለቲካ አመጽን የሚጋብዝ ነውና፡፡
ፕሮፌሰር አንጌላ ራቬን ሮበርትስ እና ፕሮፌሰር ሱዊ ላውዜ በኢትዮጵያ ያለውን ተደጋጋሚ የረሃብ መከሰት በማስመልከት ባቀረቡት ትንታኒያቸው እንዲህ ይላሉ፣ “ረሀብን ይፋ ማድረግ ማለት ለኢትዮጵያ መንግስት የተወሳሰበ ጥያቄ ነበር፡፡ ረሃብ ለኢትዮጵያ ገዥዎች መውደቅ ምክንያት አስተዋጽኦ አድርጓል… አንዳንድ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ስኬቶቻቸውን በከፊል ረሃብን በማስወገድ ይለኳቸዋል፡፡“
የዝምታ ሸፍጥ ከረሃብ ጋር በተያያዘ መልኩ በኢትዮጵያ በመስራት ላይ ለሚገኙ ተዋንያን ሁሉ ፍላጎታቸውን ለማሟላት ያገለግላል፡፡ ገዥው አካል፣ ለጋሽ ድርጅቶች፣ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እና የእርዳታ ሰራተኞች የረሃብን መኖር አምነው ለመቀበል መሞከር የሌባ ጣትን ወደ እራስ እንደመቀሰር ተደርጎ ይቆጠራል፡፡
ለረሃብ መኖር በአዎንታዊነት ማረጋገጫ የሚሆኑት በሌላው መልኩ ሲታይ ረሃብ ከሌለ ለምግብ እርዳታ የሚሰጡት በሚሊዮን የሚቆጠር ዶላር፣ በስርጭት መስመሮች ላይ የሚገኙት መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እና ከፍተኛ ተከፋይ የሆኑት ዓለም አቀፍ የእርዳታ ሰራተኞች መከኑ ማለት ነው፡፡
በሚሊዮኖች የሚቆጠር ዶላር እርዳታ ቢኖርም ቅሉ ኢትዮጵያ በምግብ እህል እራሷን እንድትችል የሚያስችል ዕቅድ ለማውጣት ውድቀትን ያሳያሉ፡፡ የኢትዮጵያ ገዥ አካል ረሃቡን ለማስወገድ እንዲችል የሚያግዝ ጥረት የማድረግ ድፍረቱ የላቸውም፡፡
በኢትዮጵያ የምግብ እርዳታ ላይ የዩናይትድ ስቴትስ አሜሪካ የሞራል ዝቅተት፣
ዩናይትድ ስቴትስ አሜሪካ ለኢትዮጵያ የምትሰጠውን የምግብ እርዳታ አስመልከቶ ህሊናን የሚቆጠቁጥ አስገራሚ እና የማይገናኝ ሁኔታ አለ፡፡ በየዓመቱ ባለፉት አስርት ዓመታት የዩናይትድ ስቴትስ አሜሪካ ለአንድ ዓይነት የህብረተሰብ ክፍሎች በእርግጠኝነት እያወቀች በየዓመቱ የምግብ እርዳታ ትሰጣለች፡፡
እ.ኤ.አ በ2003 እና በ2012 ባሉት ዓመታት መካከል ኢትዮጵያ 29 ቢሊዮን ዶላር የውጭ የልማት እርዳታን/Overseas Development Assistance በመቀበል ከዓለም ታላቁን የ4ኛነት ደረጃን ይዛ ትገኛለች፡፡
አንዳንድ ለአጠቃላይ ደህንነት የሚውሉ እና እንደ ምርታማነት ደህንነት ፕሮግሞች/Productive Safety Net Programs (ገዥው አካል በገጠር ከሚኖሩ ገበሬዎች እና ኗሪዎች የፖለቲካ ድጋፍ ለማግኘት እየተጠቀመበት ይገኛል) የመሳሰሉ ፕሮጀክቶች በስተቀር ከረሃብ እርዳታው ጋር በተያያዘ መልኩ አሜሪካ በገዥው አካል ላይ የምትጥላቸው ጥቂት ቅድመ ሁኔታዎች እንኳ የሉም፡፡ እንዲህም ሆኖ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ከዓመት ዓመት ከፍተኛ በሆነ ችግር ውስጥ መውድቅ እና በሚሊዮን የሚቆጠር አሜሪካውያን ግብር ከፋይ ዶላሮች ለድርቁ ችግር መዋላቸው ቀርቶ ለማጭበርበር፣ ለሙስና እና ለብክነት ይዳረጋል፡፡
በአሜሪካ በምግብ እርዳታ ፖሊሲ ላይ ያለው ችግር የሚያሳየው እውነታ የመጣው የእርዳታ ገንዘብ በኢትዮጵያ በትልቅ የረሃብ አደጋ ጫፍ ላይ ተንጠልጥለው ያሉ ዜጎችን ከችግራቸው በማውጣት ተግባር ላይ መዋሉ በሚገባ ሊጤን ይገባዋል፡፡
ፓውል ሄበርት የተባሉት የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብቶች ጉዳይ አስተባባሪ ቢሮ ኃላፊ በኢትዮጵያ በቅርቡ የተመለከቱትን አንደሚከተለው አቅርበውታል፣ “[በኢትዮጵያ ውስጥ] እየገጠመን ያለው ችግር ብዙው እና በርካታው የህብረተሰብ ክፍል ውጥረት ላለው ሁኔታ እና ለአካላዊ አደጋ ይጋለጣሉ… ከዚያ አደጋ ለማውጣት የተደረገ ጥረት የለም፡፡ ከዚህም በላይ የሚያስፈራው ነገር በዚህች አገር ሌላ ትልቅ የድርቅ አደጋ ከተከሰተ እና ያለውን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ እና አሳሳቢ የሆነውን የምግብ እጦት ለመቅረፍ  አስተማማኝ ስራ ካልሰራን ነገሮችን በእጅጉ ቀድሞ ወደ ነበሩበት እንዲመለሱ ሊያደርግ ይችላል፡፡ የበርካታ ሰዎች የኑሮ ሁኔታ በጣም አደገኛ በሆነ ሁኔታ ላይ የሚገኝ በመሆኑ ምክንያት ኢትዮጵያ ውስጥ በቀላሉ አደገኛ ወደ ሆነ የድርቅ ረሃብ ውስጥ ልትገባ ትችላለህ፡፡“
ዩናይትድ ስቴትስ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ዜጎች  በችግር ጠርዝ ላይ ሆነው እያዩ ወደ ጎን ሆነው ለወንጀሉ ተባባሪነታቸውን በማሳየት በጸጥታ እየተመለከቱ ዝምታን ይመርጣሉን?
በተለይም ደግሞ ጋይሌ ስሚዝ የዩናይትድ ስቴትስን ዓለም አቀፍ የልማት ድርጅት/United States Agency for International Development (USAID)ን በበላይነት እንድትመራው የቀረበው ሹመት የሚጸድቅ ከሆነ ሁኔታው ምን ሊሆን እንደሚችል ለማሰብ ፍላጎት የለኝም!
ዓመታዊ የረሃብ አዝመራ፡ የግልጽነት እና ተጠያቂነት አስፈላጊነት አንገብጋቢነት፣
የምግብ እጥረት፣ የምግብ ዋስትና እጦት ወይም ደግሞ ማንም ሰው ሌላ የፈለገውን ዓይነት ስያሜ በመምረጥ በኢትዮጵያ ውስጥ በጥቅም ላይ ቢያውለውም ቅሉ በምግብ ተመጽዋችነት የረሃቡ ችግር ሊፈታ አይችልም፡፡
በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ ከሙስና ቀጥሎ እርዳታ ልመና በኢትዮጵያ ላለው ገዥ አካል ዋና አስፈላጊው ነገር ነው፡፡
ላለፉት ሁለት አስርት ዓመታት የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ ረሃብ እና ሀፍረትን ሲያጭድ ቆይቷል፡፡ የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ የምግብ ልመና ባህል ተዋህዶታል፣ በአሁኑ ጊዜ ተስፋን በቆረጠ ሁኔታለምግብ እርዳታ ሱሰኛ ሆኖ ይገኛል፡፡
ድሆቹ የኢትዮጵያ የረሃብ ሰለባዎች በወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ ችሎታ ወይም ደግሞ እርዳታ የማቅረብ አቅም ላይ እምነት የላቸውም፡፡
የረሃብ ሰለባዎቹ የአሜሪካንን እና የምዕራቡን ዓለም ለጋሽ ድርጅቶች እንዲረዷቸው ነው የሚመለከቱት፡፡
የአሜሪካ ግብር ከፋይ ህዝብ ለእራሱ ህዝቦች ደንታ ለሌለው አገዛዝ እየሰበሰቡ ዶላር ሲያስታቅፉት የሚኖሩት ለምን ያህል ጊዜ ነው?
የአሜሪካ ግብር ከፋይ ህዝብ በኢትዮጵያ በእራሱ ህዝቦች ስም የዶላር እርዳታ በመቀበል  ለሚያባክን፣ ከህግ አግባብ ውጭ ለሚጠቀም እና በሙስና ለሚያጠፋ ገዥ አካል ምን ዓይነት እና ለምን ያህል ጊዜ ታጋሽነት ሊኖረው ይችላል?
ባለጥቁሩ የምፃት ፈረስ በኢትዮጵያ እየጋለበ ነውን?
አይ አይደለም ረሃብ በኢትዮጵያ የቀላል ባቡር ላይ እየጋለበ ነው!
ድምጼን ከፍ በማድረግ እንዲህ በማለት ደግሜ እለዋለሁ፡ 28 / ርዝመት ያለው የጉራ እና የታዕይታፕሮጀክት በግማሽ ቢሊዮን ዶላር ከመገንባት ይልቅ በረሃብ የተጎዱ ኢትዮጵያውያንን ህይወት ለማዳን በሚያስችልነገር ላይ ማዋል የበለጠ ትርጉም የሚሰጥ ሊሆን አይችልምንአለቀ ይኸው ነው በቃ!!! ምንም ዓይነት ይቅርታ የለውም!!! 
ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር!
መስከረም 19 ቀን 2008 .