Netsanet: በሙሉጌታ ሉሌ አሟሟት ተደስቻለሁ!! በDassenech Tsemai

Freitag, 9. Oktober 2015

በሙሉጌታ ሉሌ አሟሟት ተደስቻለሁ!! በDassenech Tsemai

በሙሉጌታ ሉሌ አሟሟት ተደስቻለሁ!! በ 
Dassenech Tsemai
1891166_935478479853353_5623313573126541231_nስለሙሉጌታ ሉሌ ስብዕና፤ ተግባር፤ ስነምግባር፤ ስላበረከተው አስተዋጽኦ፤ ስለፈጸመው ገድል ከኔ በላይ ብዙዎች ስለሚናገሩለት፤ ከነሱም በላይ ተግባሩ፤ ህያው ስራዎቹ ስለሚመሰክሩለት እኔ ምንም መናገር አልፈልግምና አልፈዋለሁ።
እንደሙሉጌታ ያሉ መስጠት እንጂ መቀበል የማይወዱ; ለሌላው ማድረግ እንጂ ሲደረግላቸው የማይደሰቱ፤ የወደቀን ለማንሳት እንጂ እነሱ ሲወድቁ ሰው እንዲያነሳቸው እጃቸውን የማይዘረጉ፤ በራሳቸው ሙሉ እምነት፤ ለሰው ልጅ ታላቅ አክብሮት ያላቸው ትሁት ሰዎች ትልቁ ሞታቸው የስጋና ነፍስ መለያየት ሳይሆን ታሞ ወይም አቅም አጥቶ ሰው እጅ ላይ መውደቅ፤ የሰው ተረጂ መሆን ነው። ይህ ሳይሆን በማሸለቡ በጣም ደስተኛ ነኝ።
ሙሉጌታ ሉሌ በራሱ አንደበት እንደተናገረው "ይህን ትውልድ ስረግም ኖሬያለሁ፡ አሁን ግን እነ ብርሃኑ፤ እነ ኤፍሬም ክብራቸውን; የሞቀ ትዳራቸውን፤ የሚሳሱለትን ቤተሰባቸውን ጥለው በረሃ ሲገቡ ሳይ ይህን ትውልድ ይቅርታ መጠየቅ እንዳለብኝ ተሰማኝ" (አነጋገሩን በትክክል ላልጠቅሰው እችላለሁ ግን ሃሳቡ ይህ ነው)።
ሙሉጌታ ይህን በተናገረ ቅጽበትና ከዚያም ቀደም ሆነ ከዚያ በሗላ ባሉት ጊዜያት ይሰማው የነበረው ስሜት፡ የድል አድራጊነት፤ በትውልድ የመኩራት ነበር ማለት እችላለሁ፡ በመጨረሻዋ ምሽትም ባንቀላፋባት ጊዜ ሙሉ የመንፈስ እርካታን አግኝቶ፤ ሲመኘው የነበረው ነጻነት እንደሚመጣ እርግጠኛ ሆኖ በሩህ ተስፋ እየታየውና በዚህ ትውልድ እየኮራ እንደነበር ለደቂቃ አልጠራጠርም። በመሆኑም መንፈሱ ሆሌም እንደተደሰተች፤ ድል አድራጊነቷን እንዳረጋገጠች፤ የሰላም እረፍት አግኝታ ትኖራለችና አሟሟቱ አስደስቶኛል።
ይህ ሳይሆን ቀርቶ አልጋ ላይ ውሎ፤ እሰው እጅ ላይ ወድቆ፤ ምናልባትም በቂ እንክብካቤ ሳያገኝ ቢያልፍ ኖሮ (ከዚህ ቀደም እንዳለፉት ብርቅዬ ወገኖቻችን) ዳግም ሞት ይሆን ነበር፡ መንፈሱ ተሰብራ፤ በሃዝን ልቡ ጨልማ፤ ድል ሳይሆን ውድቀትን እንደሰነቀ ያንቀላፋ ነበር።
እግዚአብሄር ደግ ነውና አሟሟቱን የጌጥ አደረገለት፡ ስለዚህ አሟሟቱ አስደስቶኛል።
በመጨረሻ ግን ለዚህ ትውልድ ጥሎ ያለፈውን አደራ ክብደት ሳላነሳ መሞነጫጨሬን ላቆም አልፈለኩም። ባንደበቱ እንደተናገረው፡ "አሁን እኔ ምን ማድረግ እችላለሁ እያልኩ ነው" ይህ መልእክት ለራሱ ብቻ የተናገረው አለመሆኑን መረዳት አስቸጋሪ አይመስለኝም፡ አሱዩማ ህይወቱን ሙሉ ማድረግ ያለበትን ሲያደርግ፤ መከፈል ያለበትን መስዋዕትነት ሲከፍል፡ ማስተላለፍ የሚገባውን ታሪክ ሲያስተላልፍ፤ ማስተማር የሚገባውን ሲያስተምርና ሲማር ኖሯል፡ አሁንም በሰባ አምስት አመት አረጋዊ እድሜው እንደ አፍላ ጎረምሳ ሩጫ ላይ ነበር፡ እንኳን ሊቀድመው ቀርቶ እኩል ሊራመድ ወይም በቅርብ ርቀት ሊከተለው የቻለ እንደሌለ ግልጽ ነው፡ መልእክቱ ለሁላችንም ነው፡ ለኔም፤ ላንቺም፤ ላንተም።
ራዕዩ እንዲፈጸም፡ ነጻነት ይመጣል ብሎ የሰነቀው ብሩህ ተስፋ እውን እንዲሆን፡ ይቅርታ የጠየቀው ትውልድ አውነትም ይቅርታ ለመጠየቅ የሚበቃ ትውልድ መሆኑን ለማስረገጥ ምን ማድረግ አለብኝ የሚለው ለሁላችንም ጥሎት ያለፈ ኑዛዜ ነው።
ቃሉን ለማክበር፤ ኑዛዜውን ተግባራዊ ለማድረግ ያብቃን።

Keine Kommentare:

Kommentar veröffentlichen