Netsanet: የህዳሴው ገደል እምን ላይ ደረሰ? (በውቀቱ ስዩም)

Sonntag, 3. Januar 2016

የህዳሴው ገደል እምን ላይ ደረሰ? (በውቀቱ ስዩም)

የህዳሴው ገደል እምን ላይ ደረሰ? (በውቀቱ ስዩም)

በውቀቱ ስዩም
አውሮፕላን መጣ እየገሰገሰ
በዘፈን አንደኛ ሙሉቀን መለሰ
(እስከመቸ ድረስ ጥላሁን ገሰሰ)
የህዳሴው ገደል እምን ላይ ደረሰ? Lol
የህዳሴውን ግድብ ወደ “ህዳሴው ገደል” ያሸጋገረውን ስምምነት የፈረመው ሰውየ “እጁን ለቁርጥማት፤ ደረቱን ለውጋት” እንዲዳርገው በመመረቅ ወደ ሰላምታየ እገባለሁ፡፡ እንዴት ናችሁ፤ ያልታደላችሁ? እኔ በህይወቴ በተለያየ ጊዜ ተስፋ ቆርጫለሁ፡፡ እንደ ዘንድሮ ተስፋን፤ ከሻኛውና ከፍሪምባው አፈራርቄ የቆረጥሁበት ጊዜ አልገጠመኝም፡፡Ethiopian author and poet, Bewketu Seyoum
መንግሥትም ሃያ አመት ሙሉ አጥሮ፤ ሃያ ዓመት ሙሉ ቆፍሮ የተሳካለት ኣይመስልም ፡፡ “በየቦታው እንምሳለን፡፡ ለመጭው ትውልድ ነዳጅ ሳይሆን ጉዱጓድ እናወርሳለን” የሚል ነው የሚመስለው፡፡ የዛሬ አስራ አምስት አመት ገደማ ውሃ ማቆር የተባለ ፕሮጀክት ነድፎ ነበር፡፡ እናም ኅብረተሰቡ በየጓሮው ሮቶ ሮቶ የሚያክል ጉድጓድ እየቆፈረ የዝናብ ውሃ እንዲያቁር ትዛዝ ተላልፎለት ነበር፡፡ ከዚያ በኋላ ውጤቱ ምንድን ነበር? የየሰፈሩ ሰካራም በየጉድጓዱ እየገባ አለቀ ፡፡ ይሁን እንጂ መንግሥት፤ ስንት ሰካራም አጥንቱን የከሰከሰበትን ፤ ደሙን ያፈሰሰበትን ፕሮጄክት ድንገት ሰረዘ፡፡ በጊዜው የተወሰኑ ሰዎች ለዶማና ላካፋ መግዣ በሚል ወፍራም በጀት አስለቅቀው ከድህነት ተላቀቁ ፡፡ አገሪቱ ግን የግዜር ገበጣ መጫወቻ መስላ ቀጠለች፡፡ የውሃ ማቆር ፕሮጀክሩ ቢቀጥል ኖሮ ዛሬ የህዳሴውን ገደል ለመሙላት ግብጽን አንለማመጥም ነበር፡፡
መንግስት ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይል የማይፈጽመውን እያቀደ፤ አዲስአበቤም ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይል በችግሩ እየቀለደ፤ ሃያ አምስት አመት ተገባደደ፡ ፡በውቄም ስኮላርሺፕ በሚል ሰበብ፤ ማንነታቸው ያልታወቀ ፌዴራል ፖሊሶች የሚወረውሩት ቦምብ ወደማይደርስበት ቦታ ተሰደደ፡፡ በግንቦት ወር ወደ አገሩ ሲመለስ ችግር ይገጠመው ይሆን?ወይስ በእጃችን እንይጠፋብን ብለው ይተውት ይሆን? ቀጣዩን ክፍል በመጭው ግንቦት ይጠብቁ፡፡ግን መንግስትን መተቸት ህገመንግሥታዊ መብቴ መሆኑ ይሰመርበት ፡፡ በርግጥ ህገመንግስቱ እንደ ኣዲስ ኣበባ ምግብ ቤቶች Menu ነው፡፡ የተጻፈውን በተግባር ስትፈልገው አታገኘውም፡፡
በነገራችን ላይ ጠቅላይ ምኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ የሆነ መጽሄት ላይ “ያመቱ ሰው” ተብለው መሸለማቸውን ሰምቼ ተደስቻለሁ፤ ሲያንሳቸው ነው፡፡ ይሄን ያክል እየተተረበ፤ ይሄን ያክል እየተሰደበ፤ ይሄን ያክል ከታችም ከላይም ንቀት እየተከናነበ ቆሞ መሄድ የቻለ ሰው፤ ሽልማት አነሰው?
እኔም እንሆ፤ ሰሜን አሜሪካ ጫፍ አርፌ
በጀርባየ የካናዳን የጉም ግድግዳ ተደግፌ
ከጢሜ ላይ የኮካኮላ ጤዛ ፤ከኪቦርዴ ላይ በረዶየን አራግፌ
“የኢትዮጵያ ህዝብ ሆይ ተባብረህ ተነስተህ ላንዴና ለመጨረሻ ግዜ አምባገነኑን ሥርአት ገርስስ” እያልሁ ነጋሪት ስደልቅ ፤አዲስ አበቤም “ወይ ኦን ላይን ያለ ሰው!” እያለ በኔ ላይ ሲስቅ፤ ጀምበር ”ሎግ አውት” አድርጋ ጥልቅ፡፡
ባለፈው 53 የፖለቲካና የሃይማኖት ድርጅቶች መግለጫ አውጡ ሲባል ስቄ ልሞት፡፡ ያሁላ ፓርቲ ቢሮ አለው? ወይስ ህልሙን ባሮጌ ሳምሶናዊት ሸክፎ የሚዞረው ሁሉ ተቆጥሮ ነው?ግሩም ነው መቸም፡፡ ኢትዮጵያ በቀንድ ከብት አንደኛ ሆና ወተት ይርባታል ፤ አምሳ ሦስት የፖለቲካ ፓርቲ ኖሯት ፖለቲካው ቸግራታል፤ እንዲያው ምን ይሻላታል?
ድሮ የኔ ቢጤ ባይተዋር ሰው ሲጨንቀው ሰላም ፍለጋ ወደ ቸርች ነበር የሚሄደው፡፡ አሁን በየቤተክስያኑ ድብድብ ነው፡፡ እዚያ ዲሲ ቤተክስያን ልትስሚ ከሄድሽ በነጠላሽ ላይ የጥይት መከላከያ መደረብ አለብሽ ፡፡ እነ አባባ ቆባቸው በሮ እስኪሄድ ሲከታከቱ ታዝበሽ፤ ከተወረወረ መቋሚያ በመትረፍሽ ኣንድየን አመስግነሽ፤ ወደ ቤትሽ ትመለሻለሽ፡፡ ባገር ቤት፤ ቤተክርስትያን ውስጥ አንድ ቄስ በዲያቆናት ሲታጀብ፤ የዲሲ አበሻ ቄሶች ግን በፖሊስ ታጅበው ነው የሚቀድሱ፡፡ እንዲያውም የፈረንጅ ፖሊሶች ለግልግል እየተጠሩ ቤተክስያኑን ከማዘውተራቸው የተነሣ ቅዳሴውን ለምደው ተሰጥኦ ሁሉ መቀበል ጀምረዋል፡፡
በነገራችን ላይ ላገራችን የገጠር ቄስ ክብር አለኝ፡፡ “ዳዋ ጥሶ፤ ጤዛ ልሶ፤ ድንጋይ ተንተርሶ፤ ግርማ ሌሊትን፤ ጸብአ አጋንንትን ታግሶ ፤የሚኖር ነው፡፡ የዲሲ ቄስ በበኩሉ ሙዳየ ምጽዋት አፍሶ፤ አይስክሬሙን ልሶ ፤የንስሃ ልጁን ጡት ተንተርሶ ፤ በቴስታ ተከሳክሶ ይኖራል የሚል ሀሜት አለ፡፡
የዛሬውን የህትመት ዳሰሳየን የምቋጨው በመሬት “ ትንታኔ“ ነው፡፡ ያዲስ አበባ የመሬት ችግር የመነጨው ከዘጠና ሰባት በኋላ ይመስለኛል፡፡ ጌቶች በነዋሪው ተስፋ ስለቆረጡ፤ በስልጣናቸውም ዋስትና ስላጡ፤ “ኪስህ ነው የቅርብ ወዳጅህ” የሚለውን ዘፈን ማንጎራጎር መረጡ፡፡ ይህንን ዝንባሌ እኔና ቢጤዎቼ የቀኝ አዝማች ሰውነቴ “ ሲንድረም ”ብለን እንጠራዋለን፡፡
ቀኛማች ሰውነቴ ከደብረማርቆስ ባላባቶች አንዱ ነበሩ፡፡ እና በስድሳ ስድስቱ አብዮት ዋዜማ የጭሰኞቻቸውን መሬት ጆሮ ጆሮውን ብለው ካቲካላ ጠጡበት ፡፡ባላባት ጓደኞቻቸው ለምን እንዲያ እንደሚያረጉ ሲጠይቋቸው“ መሬት ሳትበላኝ ልብላት ብየ ነው” አሉ ይባላል፡፡
ትንታኔውም ይቀጥላል፡፡

Keine Kommentare:

Kommentar veröffentlichen