Netsanet: ያሁኑ የኢትዮጵያ ሁነታ፤ ይመስላል የተምታታ – ፕ/ር ጌታቸው ኃይሌ

Donnerstag, 31. Dezember 2015

ያሁኑ የኢትዮጵያ ሁነታ፤ ይመስላል የተምታታ – ፕ/ር ጌታቸው ኃይሌ

መግቢያ፤

 ፕ/ር ጌታቸው ኃይሌ
ፕ/ር ጌታቸው ኃይሌ
በአሁኑ ሰዓት የወያኔ አገዛዝ በአንድ በኩል በሕዝባዊ እምቢታ፥ በሌላ በኩል በትጥቅ ትግል ተቃውሞ በሰፊው እንደተነሣበት ይሰማል። ስሜትንና አስተያየትን ለሕዝብ ማቅረቢያውን መንገድ የዘመኑ ቴክኖሎጂ ለሁሉም ክፍት ስላደረው፥ ሕዝባዊ እምቢታውንም ሆነ የትጥቅ ትግሉን የሚደግፉና የሚቃወሙ እንዳሉ እያነበብንና እየሰማን ነው። ወያኔዎችና ደጋፊዎቻቸው ማናቸውንም ዓይነት ተቃውሞና እምቢታ ቢቃወሙ አይገርምም። ሊታሰብበት የሚገባው ዋናው ጥያቄ የወያኔን አገዛዝ የሚጠሉ አገር-ወዳድ ኢትዮጵያን የትጥቅ ትግሉንና የሕዝቡን ዓመፅ የሚፈሩት በሚገባ ነው ወይስ አይደለም የሚለው ነው። ዋስትና ያለው ታማኝ መልስ የለም። ግን ሁኔታው ግልጽ እንዲሆን ጥያቄው መተቸት አለበት። በእኔ በኩል የሚታየኝን ከመተቸቴ በፊት ሁለት ነገሮችን በሚገባ እንድንረዳ እፈልጋለሁ።
አንደኛ፥ ትግሉን ከሚፈሩት ውስጥ አገር-ወዳድና አገር-ወዳድ መስለው የሚጮሁ ተቃዋሚዎች አሉ። አገር-ወዳድ መሰሎቹን ወያኔዎች በአገር-ወዳዱ ውስጥ የሰገሰጓቸው መሆኑን ሰምቻለሁ። አማራ መስለው ለአማራው እንደሚቆረቆሩትና በክልል እንዲወሰን እንደሚፈልጉት ዓይነት ማለት ነው። ውይይቴ ከአገር-ወዳዶቹ ጋር ነው።
ሁለተኛ፥ አገር-ወዳዱ የወያኔን አገዛዝ በሚገባው ልክ እንዲረዳው ያስፈልጋል። ስለወያኔ አገዛዝ ብዙ ጊዜ የምሰማው (እኔም ሳልለው አልቀርም)፥ “ወያኔ ጨቋኝ ነው”፥” “ወያኔ ፋሺስት ነው”፥” “ወያኔ ሰብአዊ መብት የሚጥስ መንግሥት ነው” የሚሉ አገላለጾች ናቸው። እነዚህ አገላለጾች የሚገልጹት የወያኔን ዘዴ እንጂ የወያኔን ማንነት አይደለም። ወያኔዎች ይጨቁናሉ፤ እንደፋሺስቶች ዘር እየለዩ ሰው ይፈጃሉ። ይኼ ዘዴያቸው ነው። በዓላማ ግን አይመሳሰሉም። የወያኔዎች ዓላማ ዝርፊያ ነው–ድርጅታቸው የዘራፊ ድርጅት ነው።
ስጋቶች፤
ከወያኔ ቀጥሎ የሚመጣውን የሚፈሩ ለሀገርና ለሕዝብ አሳቢዎች “ከዘራፊ (ከማፊያ) የሚብስ ይመጣል ወይ?” ብለው ማሰብ አለባቸው። ወያኔዎች ኢትዮጵያ ለኛ ካልሆነች እናወድማታለን ብለው ምለው ተነሥተዋል። ዓላማቸውን እንዲቀይሩና ዲሞክራሲን አብረን እናስፍን ቢባሉ፥ ብዙ ዓመታት ቢወተወቱ፥ አሻፈረን ብለዋል። እንዲህ ከሆነ፥ የሀገር-ወዳዱ አማራጭ ምንድን ነው? “ከሚያወድሟት ይውሰዷት” ይበል ወይስ የሚመጣውን ደግፎ ውጤቱን ለሁሉ የሚጠቅም ለማድረግ ዘዴ ይፈልግለት?
አገር-ወዳዱን የሚያሰጋው አንዱ የኦሮሞዎች ጥያቄ ነው። ለዚህም ዋናው ምክንያት የሆነው መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ በማፊያ ቀምበር ተጠምዶ ሳለ የኦሮሞ የፖለቲካ ድርጅቶች ኦሮሞች ብቻ የተጠቁ አስመስለው ሲናገሩ መሰማታቸው ነው። አገር-ወዳዱ የሚለው “ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ሲጠቃ ሁላችንም በአንድ ድምፅ እንቃወም፤ የሚጠቃው ኢትዮጵያዊ እንጂ፥ ኦሮሞ፥ ቅማንት፥ አማራ፥ ጉሙዝ፥ . . .፥ እስላም፥ ክርስቲያን አይደለም” ነው።  አማራውንና ኦርቶዶክሱን የበለጠ የሚያጠቁት ለሀገሪቱ አንድነት ማገር ሆነው ስለገኟቸው ነው።
ኢትዮጵያን በአስተዳደር ጊዜ በጎሳ፥ በሃይማኖት መከፋፈል የወያኔ ተንኮል ነው። በአስተዳደርና በፖለቲካ ጊዜ፥ ሀገር የጋራ ነው ሃይማኖትና ጎሳ ግን የግል ናቸው። ለጎሳና ለሃይማኖት ማሰብ  ክፋት የለበትም።ለጎሳቸውና ለሃይማኖታቸው የሚያስቡ ሰዎች ካሉ፥ መከልከል የለባቸውም፤ መብታቸው ነው። መብቱም ባህል ማዳበር ነው፤ ግን መንግሥት በሃይማኖት ጉዳይ ሊገባ እንደማይገባው ለጎሳቸውና ለሃይማኖታቸው የሚያስቡም የሃይማኖቻቸውንና የጎሳቸውን ጉዳይ የፖለቲካ ጉዳይ ሊያደርጉት አይገባም። አገር የጋራ ነው ሃይማኖትና ጎሳ ግን የግል ናቸው።
የከተማዎች መስፋፋት፤
ከተማዎች ሲስፋፉ ከከተማ ውጪ የነበሩ መሬቶችን ወደከተማ ክልል ማስገባት የማይቀር ነው። በዚህ አጋጣሚ መሬቱ ወደከተማ የተከለለለት ሰው ሎተሪ እንደወጣለት ነው የሚቈጠረው። ግማሹን ሸጦ የሚሊዮን ብር ጌታ ይሆናል። በግማሹ ላይ የሚኖርበትንና የሚያከራየውን ቤት ይሠራበታል። ከተራ ገበሬነት ወጥቶ ዘበኛና አሽከር ቀጣሪ ጌታ ይሆናል። ግን ማፊያዎቹ ወዲያው ከተፍ ይላሉ። ገበሬው የወጣለትን ሎተሪ (መሬቱን) ቀምተው ባለቤቱን አልባሌ ቦታ አሽቀንጥረው ይጥሉታል። ተቃውሞው ዛሬ ተጀመረ እንጂ ዘረፋው የተጀመረው ቀደም ብሎ ነው። ማፊያዎቹ ከተማ ውስጥ የሚያበለጽግ ቦታ ሲያዩ ባለቤቱን ወደሩቅ ቦታ ጥለው እነሱ ፎቅ ሠርተውበታል።
በደሉ የደረሰው በኢትዮጵያውያን ላይ ነው፤ የአሁኑን በደል የተቃወሙት ግን ኦሮሞዎች ናቸው። የተፈናቀሉት ኢትዮጵያውያን እንጂ ኦሮሞዎች ስለሆኑ አይደለም። ገብሬዎቹ ኦሮሞዎች መሆናቸው አጋጣሚ ነው። ጉራጌዎች፥ ዶርዜዎች፥ አማሮች ቢሆኑም ይዘረፉ ነበር። መቃወም ያለብን ማንም ቢዘረፍ ዝርፊያውን  እንጂ ማን ተዘረፈ ብለን መሆን የለበትም። የምናደርገው ግን በወያኔ አስተሳሰብ ለጎሳችን እያሰብን ሆኗል። አማሮች ሲፈናቀሉ የኦሮሞ ድርጅቶች ተቃውሞ ያላሰሙት ስለዚህ ነው። እንዲያውም የአፈናቃሊውና የአራጁ  አካል ሆነው ነበር። ተቃውሞ በተነሣ ቍጥር አገር-ወዳዱን የሚያሳስበው ይኸ ሁኔታ ነው። ማፊያዎች ማንንም ኢትዮጵያዊ ሲዘርፉ፥ ሲገድሉ፥ ሌላው ኢትዮጵያዊ ዝም ካለ የአንድ ሀገር ሕዝብ መሆናችን ይቀራል። ለጎሳ ማድላት ካማረን ጎሳችን ኢትዮጵያ ናት።
የትጥቅ ትግል፤  
በሰሜን በኩል የተነሣው የትጥቅ ትግል የሚያሰጋቸው አገር-ወዳድ ኢትዮጵያውያን አሉ። “እባብ ያየ ልጥ ቢያይ በራየ” (እባብ የነከሰው ልጥ ቢያይ ደነበረ) የሚለውን አባባል “እባብ ያየ እባብ ቢያይ በራየ” እንደ ማለት አይተውታል። አይፈረድባቸውም፤ በኛ ሀገር እንኳን፥ መጀመሪያ ደርግን፥ አሁን ደግሞ ወያኔንና ሻዕቢያን አይተዋል። እነዚህ በትጥቅ ትግል አሸንፈው ሥልጣን የያዙ ድርጅቶች የዲሞክራሲ ስም ሲጠራ ዛር እንደያዛቸው አፋቸው ዐረፋ ይደፍቃል፤ እንደ ተከበበ አውሬ ይወራጫሉ፤ ሰው ይፈጃሉ። “በትጥቅ ትግል የሚመጣ ሁሉ ከነዚህ እንደማይለይ ለምን ከታሪክ አንማርም?” ይላሉ።
ግን አማራጭ ሲጠፋ ከብዙ አንድ አይጠፋም ብሎ ዕድልን መሞከር የግድ ነው። የዛሬው ተቃውሞ ለዕድል ብቻ የሚጣል አይደለም። የታጣቂዎቹ ዓላማ እንደ ወያኔ ራሳቸውን ወይም አንድን ጎሳ ለማበልጸግ አይደለም (የቱን ጎሳ?)። ወያኔዎች ትግል ሲጀምሩ እነማን እንደሆኑ ልጆቹን አናውቃቸውም ነገር። ዓላማቸው ትግራይን ለይቶ ለመጥቀም መሆኑን ግን ሳይደብቁ ነግረውናል። ዛሬ የትጥቅ ትግል የሚያካሂዱትን ግን እናውቃቸዋለን። የወያኔ ብጤዎች አይደሉም።
ሁለተኛም አገር-ወዳዶች የትጥቅ ትግሉ አካሄድ ካሰጋቸው መድኃኒቱ ተደባልቀው በጦሩና በአመራሩ መሳተፍ ነው። ለመሳተፍ ፈልገው  እምቢ እንደተባሉ አልሰማንም። የምንሰማው ቁጭ ብለው ተቺዎችን ነው። “የምትሰጉትን ውጤት ለማስወገድ ለምን አብራችኋቸው አትታገሉም?” ሲሏቸው፥ “በዚያ በኩል የሚካሄ ትግል ወያኔን ሊጥል አይችልም” ይላሉ። የትጥቅ ትግሉ ውጤት ከሌለው ሊያሰጋቸው አይገባም ማለት ነዋ!! ወያኔዎችም ችላ ይሏቸው ነበር። የምንሰማው ግን ወያኔዎች በየቀኑ የሚያወርዱባቸውን የጥላቻና የፍርሃት ፕሮፓጋንዳ ነው።
ሌላው ስጋት እርዳታው ከኢሳይያስ አፈ ወርቂና ከሻዕቢያ መምጠቱ ነው። “ኢሳይያስና ድርጅቱ ለኢትዮጵያ በጎ አያስቡም፤ ቢያስቡ ኖሮ የኤርትራን መገንጠል ለኢትዮጵያ ችግር መፍትሔ አያደርጉም ነበር” የሚል ነው። ይኸንን ልንክድ አንችልም፤ እውነት ነው። እርዳታቸውን ለማግኘት ስንልም ታሪክ አንከልስም። ኤርትራ ወስጥ አንድነቱን መቃወም የተጀመረው ከፌዴሬሽኑ መፈጠርም መፍረስም በፊት ነው። ሻዕቢያ ጦር ያነሣው ፌዴሬሽኑ በመፍረሱ ምክንያት አይደለም፤ እሱ ሰበብ (casus belli) ነበረ።
ፌዴሬሽኑ ማንንም ኤርትራዊ ያላስደሰተ፥ ትርጕሙ ለሁሉም እንቆቅልሽ የሆነ  ዱብ እዳ ነበር። አንድነቶች የተቀበሉት ውሕደቱን ሲያደናቅፍ ባለማየታቸው ነው። የኤርትራ ፓርላማ ፌዴሬሽኑ እንዲነሣ ሐሳብ ሲቀርብለት፥ የአንድነት አባላት ያሉት፥ “ለመሆኑ ምንድነው እሱ፥ አንድ ሆነን የለም እንዴ? ፌዴሬሽን የሚባለው ለአንድንታችን ገደብ ለመፍጠር የታቀደ ኖሯል ወይ? ኧረ ወዲያ ጣሉት” ነው።
ኢሳይያስ የሚሠራው ሥራና የሚያካሂደው ፖለቲካ ያቺን የነጠቃትን ግዛት ለመጥቀም ብሎ ነው። ከወያኔ በቀር ለያዘው አገር ጥቅም የማይሠራ ገዢ የለም። “ወያኔዎችን የሚቃወሙ ድርጅቶችን የሚደግፈው ለኢትዮጵያ ጥቅም ነው” የሚል ያለ አይመስለኝም። የአንድ ሀገር ገዢዎች ለሌላ ሀገር ጥቅም አይሠሩም። ግን ምክንያቱ ምን እንደሆነ ባናውቅም (ልንጠረጥር እንችላለን) ኢሳይያስ  የትጥቅ ትግል የሚያካሂዱ ተቃዋሚዎችን ይደግፋል። የሚፈልገውን ቢያገኝ/ሲያገኝ ድንገት ድጋፉን ሊነፍጋቸው ይችላል። በዚህ ጊዜ የወያኔ ማፊያ ተቃዋሚዎች ግዴታ ድጋፉን  እስካገኙ ድረስ  የሚያደናቅፉ ጥያቄዎችን ሳይሰሙ ቶሎ ቶሎ በድጋፉ መጠቀም ነው። “ጀምበር ሳለ ሩጥ . . .” ዋናው ነገር በሰላማዊ ትግል የዘመቱት የትጥቅ ትግሉን ብቻ ተስፋ በማድረግ የራሳቸውን ትግል እንዳያረግቡ ነው።
መደምደሚያ፤
ትግሉን የሚደግፉና የሚቃወሙ ድምፃቸው በየቀኑ ስለሚሰማ፥ ሁኔታው የተምታታ ይመስላል፤ ግን አይደለም። ምክንያቱ የተለያየ ይሁን እንጂ ዓላማው አንድ ነው። ከአገር-ወዳድ ነን ከሚሉ ሳይቀር መጠን የሌለው ስድብ ሲወርድባቸው ጆቷቸውን ዘግተው ለነፃነት መታገላቸው የሚያስደንቅ ነው።  አሸንፈው፣ ሥልጣን ሲይዙ ማየት እንፈልጋለን። ይዘው እነሱም እንደሌሎቹ የሚያስቸግሩን ከሆነም፥ ዕድላችን ነውና እንደፈረደብ አዲሱን (ሌላውን ዓይነት) ችግር ለማስወገድ እንታገላለን። ወያኔዎች አንገፍግፈውናል።

Keine Kommentare:

Kommentar veröffentlichen