Netsanet: ማስጠንቀቂያውን እንስማ፤ ኢትዮጵያ በአደጋ ላይ ናት!

Samstag, 12. Dezember 2015

ማስጠንቀቂያውን እንስማ፤ ኢትዮጵያ በአደጋ ላይ ናት!

ማስጠንቀቂያውን እንስማ፤ ኢትዮጵያ በአደጋ ላይ ናት!

ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ መግለጫ
ታኅሣሥ 1፤2008ዓም
አንዲት ኢትዮጵያዊት እናት ስለ ልጇ እንዲህ አለች፡ “ልጄን በጥቅምት ወር ለትምህርት ላኩት በኅዳር ሬሣውን ለቀብር ተቀበልኩ!” ይህችእናት የሁላችንንም ወላጅ እናት የምትወክል ናት፤ ኢትዮጵያን እና በአሁኑ
ጊዜ በአገራችን ላይ ያለውን ሁኔታም በግልጽ የምታሳይም ናት፡፡ ሟች ልጇ የሷ ልጅ ብቻ ሳይሆን የሁላችንም ወላጆች ልጅ፤ ወንድም
የሚወክል ነው፡፡ ይህ ልጅ የእናንተን በህወሃት ውስጥ ያላችሁትንየሥርዓቱ መሪዎች፣ ተላላኪዎችና አጎብዳጆችን ልጅ የሚወክልም ነው፡፡
ይህ ዓይነቱ ግፍ እና ሰቆቃ በአንዲት ኢትዮጵያዊት እናት ላይ ብቻ ሳይሆን በእያንዳንዱ እናት ላይ እየደረሰ ነው፡፡ እናንተም እንደ ሰው ከእናት በመፈጠራችሁ ይህ ስቃይና መከራ
አይደርስብንም፤ አይነካንም ማለት አትችሉም፡፡ ከሕዝብ ለመሰወር ብትሞክሩ እንኳን ሁሉን ከሚችል ፈጣሪ በጭራሽ መሰወር አትችሉም፡፡
ስለዚህ ይህ ሰቆቃ እና ስቃይ በአስቸኳይ መቆም አለበት!!ሰሞኑን በአገራችን እየተካሄደ ያለው ሕዝባዊ እንቅስቃሴ በገሃድ እየተመለከትን ነው፡፡ በተለይ ከሁለት ቀናት በፊት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የተወሰደው አቋም እጅግ የሚያስደንቅና
የሁላችንንም ዕይታ የሳበ ነው፡፡ ተማሪዎቹ እንደተለመደው ወደ መመገቢያ ቦታቸው ሲደርሱ ምግባቸውን ወስደው በሥፍራቸው
ተቀመጡ፡፡ ወደ ፈጣሪያቸው እየሞቱ፣ እየተሰቃዩና እየተራቡ ለሚገኙት ወገኖቻቸው ጸሎት አደረሱ፡፡
ከምግቡ አንዲት ቁራሽ ሳይቀምሱ ከተቀመጡበት በመነሳት ምግቡ ጠረጴዛው ላይ በመተው የመመገቢያ አዳራሹን ለቅቀው ወጡ፡፡ 15
ሚሊዮን ወገናቸው እየተራበ፣ ሌላው ደግሞ እየተፈናቀለ፣ እየተገደለ፣ የመኖር ኅልውናውን እያጣ በሰላም እየበሉ ለመኖር እንደማይፈቅዱ
ሰላማዊ በሆነ መንገድ አሳዩ፡፡ ተማሪዎቹ ስለወሰዱት እርምጃ ብዙ መባል ቢችልም ይህ ዓይነቱ
የሰላማዊ ተቃውሞ ደም በማፍሰስ ከፍተኛ ብቃት ላካበተው የህወሃት
ጠብመንጃ አንጋች የሚመቸው አካሄድ አይደለም፡፡ ሰላማዊ ትግል ማለትም ምን ማለት እንደሆነ ተማሪዎቹ በገሃድ አሳዩ፤ የአዲስ አበባ
ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ብቻ ሳይሆኑ በሌሎች ከፍተኛ ተቋማት የሚገኙ ተማሪዎችም ተመሳሳይ ዕርምጃዎች በመውሰድ ለወገናቸው ያላቸውን
ተቆርቋሪነት በግልጽ አሳይተዋል፡፡ የዝቅተኛ ትምህርት ተማሪዎች፣ የሆስፒታል ሠራተኞች፣ የተለያዩ መ/ቤት ሠራተኞችና ነዋሪዎችም
ሰላማዊ ሕዝባዊ ተቃውሞ በማድረግ በአንድ በኩል የኢትዮጵያ ሕዝብ ሰላማዊ መሆኑን በሌላ ደግሞ የሰላማዊ ትግል ብቃትና ፍሬያማነት
አሁንም በኢትዮጵያ መሥራት እንደሚችል እያስመሰከሩ ነው፡፡ኢትዮጵያን እንደ እህል በዘር መደብ ከፋፍሎ እየገዛ ያለው የትግራይ
ሕዝብ ነጻ አውጪ ግምባር (ህወሃት) የትግራይ ሕዝብን በፍጹምየማይወክል ቢሆንም አሁንም “በነጻ አውጪ” ስም አንድን ክልል ለማስገንጠል በቆመ ዓላማ ኢትዮጵያን በግፍ እየገዛ ነው፡፡ ከአነሳሱ
ጀምሮ በራሱ ውስጥ የነበሩና አሠራሩንና ዓላማውን የተቃወሙትን ሁሉ በመግደል፣ በማሰር፣ በማሰቃየት የጀመረው በሟቹ መለስ ዜናዊ
የተመራው ህወሃት ጨካኝነቱን ነጻ አወጣዋለሁ ባለው ሕዝብ ላይ አለገደብ ሲያሳይ ከቆየ በኋላ ወደ ሥልጣን መንበር ሲመጣ በሌሎች
ኢትዮጵያውያን ላይ ዘመቻውን አድርጓል፡፡ ሲጀምር አማራ ብሎ የሰየመውን ሕዝብ ማጥቃት ተያያዘ፤ ቀጥሎም ከአርባ በላይ የሚሆኑ ኢትዮጵያ በውድ ያስተማረቻቸውን የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን
የከፈሉትን ዋጋ እንኳን ከቁም ነገር ሳይቆጥር በሁለት መስመር ደብዳቤከማስተማር ሙያቸው አባረረ፡፡ ግፉ ቀጠሎ ሲዳማዎችን፣ አኙዋኮችን፣ ለቅንጅት ድጋፍ የወጡ ሰልፈኞችን፣ በዖጋዴን ሶማሊዎችን፣ አፋሮችን፣ ማጃንጂሮችን፣ ቤንሻንጉልና ጉምዞችን፣ የኦሞ ሸለቆ ነዋሪዎችን፣በደቡብ በርታዎችን፣ በሱዳን ጠረፍ የሚገኙ ገበሬዎችን፣ ሙስሊሞችን፣
ጋዜጠኞችን፣ የዴሞክራሲ አራማጆችን፣ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾችን፣የተቀናቃኝ ፓርቲ አመራሮችን፣ የከተማ ነዋሪዎችን፣ ሲገድል፣ ሲያስር፣ሲያሰቃይ ቆይቶ አሁን ደግሞ ከዚህ በፊት ያደረሰው መከራ ሳያንሰውበኦሮሞ ተወላጆች ላይ የበቀል በትሩን እየዘረጋ ነው፡፡
ይህ በኦሮሞ ተወላጆች ላይ ብቻ የተቃጣ ሳይሆን ሁላችንም
በእያንዳንዳችን ላይ እንደተቃጣ ግፍ አድርገን ልንወስደው ይገባናል፡፡
የሚፈሰው የኦሮሞ ደም አይደለም፤ የሰብዓዊ ፍጡር እንጂ፡፡ ዘር፣
ጎሣ፣ ወገን፣ … የተለያየ ደም የለውም – ሁሉም ሰው በፈጣሪ
በእኩልነት የተፈጠረ የአምላክ ድንቅ ሥራ ውጤት ነው፡፡ ስለዚህ
ትግሉም፣ ተቃውሞውም የአንድ ቡድን ወይም የአንድ ወገን ብቻ
ሳይሆን የትግራይ ሰዎችንም ጨምሮ የመላው ኢትዮጵያዊ ነው፡፡
አለበለዚያ የወገንና የጎሣ አድርገን የምንወስደው ከሆነ ከዚህ በፊት
እንደተካሄዱት በአንድ ወቅት ተነስቶ የሚጠፋ ወደሌላው ቦታ
ለመቀጣጠል የማይችል፤ የሁሉም ኢትዮጵያዊ ውክልና የሌለው፤
ከጥቅሙ ጉዳቱ እጅግ የሚበልጥ፤ ጭፍን፣ ጠባብና ለህወሃት ዕድሜ
ማራዘሚያነት የሚያገለግል ቶሎ የሚዳፈን ግብታዊና ወቅታዊ ዓመጽ
ሆኖ ነው የሚቀረው፡፡ ስለዚህ ይህንን የሕዝብ እንቅስቃሴ በሰብዓዊነት
መነጽር ለማየት የማይፈልጉ ሁሉ ከፍተኛ ጥንቃቄ ሊወስዱ ይገባል፡፡
ጎሣቸውን ወይም ሕዝባቸውን ነጻ እናወጣለን ብለው ህወሃት ካደረሰው
ጉዳት እጅግ የከፋ ውድመት ሊያደርሱ እንደሚችሉ በጥብቅ ሊገነዘቡ
ይገባል፡፡ ሌሎችም ኢትዮጵያዊያን “እኔን አይመለከተኝም” በሚል
አስተሳሰብ ከዳር ለመሆን የሚፈልጉ ሁሉ ትግሉን ጎሣዊ ለማድረግ
ከሚመኙት ያልተናነሰ ጉዳት እንደሚያደርሱ እነርሱም በጥንቃቄ ሊያዩት
ይገባል፡፡ የአንድ ሰብዓዊ ፍጡር ደም መፍሰስ የራሳቸው እንደሆነ
አድርገው ካልወሰዱት ጉዳቱ የራሳቸውን በር ሲንኳኳ የሚደርስላቸው
ያጣሉ፡፡ ይህ ደግሞ ኢትዮጵያ የምትባለው አገር እንዳትኖር ወደማድረግ
የሚያደርስ የጥፋት ቁልቁለት ነው፡፡ ለዚህም ነው የአዲሲቷ ኢትዮጵያ
የጋራ ንቅናቄ (አኢጋን) “ከጎሣ ይልቅ ሰብዓዊነትን እናስቀድም” በሚል
መሪ መፈክር አንቅስቃሴውን የሚያካሂደው፡፡ከሰብዓዊነት በፊት ጎሣን፣
ወገንን፣ ዘርን፣…ማስቀደም ህወሃትን መልሶ በሥልጣን ማስቀመጥ
ነው፡፡
በሕይወት በነበሩ ጊዜ ኢትዮጵያን በጎሣ ከፋፍለው ሲያበቁ በሕዝብ
ለመወደድ ብለው “ሕዝብ ከሸፈተ ሠራዊት አያቆመውም” የሚል
ንግግር መለስ ዜናዊ ስለማድረጋቸው ይነገራል፡፡ በወቅቱ ሕዝብ ያሉት
ለተገንጣይ ቡድናቸው ድጋፍ ይሰጣል ያሉትን ሊሆን ቢችልም
አነጋገራቸው ግን አሁን በአገራችን ከሚታየው ተጨባጭ ሁኔታ አኳያ
እውነትነት አለው፡፡ ህወሃት ሁሉንም ሲያደማ ስለኖረ አሁን ሕዝብ
ሸፍቶበታል፡፡ ይህንን ሐቅ ማመን ስላልፈለገ ግን ሠራዊት አሰማርቶ
የሕዝብን ቁጣ ለማፈን የሚቻለውን ሙከራ እያደረገ ነው፡፡
ሌጋሲያቸውን እንጠብቃለን እያለ በሙት መንፈስ የሚመራው ህወሃት
መሪው ያሉትን ቃል ቢሰማ ጥሩ ነው፡፡ እስካሁን ያሠማራውም ሆነ
ወደፊት ሊያሰማራ ያሰበውን ሠራዊት ሁሉ ቢጠቀም ሕዝብ
እስከሸፈተበት ድረስ በየትኛውም ዓይነት ሠራዊት ሊያስቆመው
አይችልም፡፡
ህወሃት “ትጥቅ ትግል” ባለው የበረሃ ጉዞው ላይ በጠብመንጃ አፈሙዝ
ለችግሮች ሁሉ መፍትሔ ሲያገኝ እንደነበረው ሳይሆን አሁን አገር እየገዛ
ነው፤ ህንጻም፣ መንገድም፣ … ሠርቷል፤ የጦር ሠራዊት ጡንቻውንም
አዳብሯል፤ ገንዘቡን ተቆጣጥሯል፤ ብዙ ዘመናትም ለመግዛት ቋምጧል፤
ሕዝብ ከሸፈተበት በኋላ ግን ዲስኩር የነፋባቸው ህንጻዎችና መንገዶች
ማንንም አይሸሽጉም፤ ሠራዊት ብሎ ለራሱ ያደለበውም ኃይል ማንንም
መከላከል አይችልም፤ የሸፈተን ሕዝብ ምንም አይገድበውም፤ ማዕበል
ነው፤ ጎርፍ ነው፤ ሱናሚ ነው፡፡ ስለዚህ እናንት የህወሃት ሹሞች በእጅጉ
ተጠንቀቁ! በንጹሃን ተማሪዎች ላይ የጠብመንጃ ቃታ እንዲሳብባቸው
የምታዙትን ሠራዊት አቁም በሉት፣ ካልተባለ ነገ ቃታውን ወደ እናንተ
ለማዞሩ ምንም ዋስትና የላችሁም፤ በችጋር የሚያልቀውን የኢትዮጵያ
ሕዝብና ህጻናት እንደ ራሳችሁ ሕዝብና ልጅ ተመልከቱት፤ የሙት ሌጋሲ
ለመጠበቅና ለልማት በሚል ከንቱ “ውዳሴና ህዳሴ” የምታፈናቅሉት
ምስኪን ገበሬ ስቃይ ይሰማችሁ፣ የፈጣሪ በትር የተመዘዘ ዕለት
የእናንተም ጽዋ ከዚህ እንደማያልፍ በቀረው ጥቂት የማሰብ ኅሊናችሁ
ለማስተዋል ሞክሩ፡፡
አገራችን በአደገኛ ሁኔታ ላይ ትገኛለች፡፡ ማስጠንቀቂያው ለሁሉም
ነው፡፡ በአንድ በኩል ደም ከማፍሰስና ከመግደል በቀል የአእምሮው
ክፍል ምንም ማሰብ የማይችል ጨካኝ ሠራዊት በመግደል ፈንጠዝያ
ላይ ነው፤ ከጌቶቹ በተሰጠው ትዕዛዝ ብዙ ለመግደልና ደም ለማፍሰስ
ጠብመንጃውን ወልውሏል፤ በሌላ በኩል ደግሞ አገራችንን በጎሣ፣
በዘር፣ በወገን፣ በሃይማኖት ለመከፋፈል ያሰፈሰፉ የውስጥና የውጭ
ኃይላት ሕዝባዊ ዓመጹን የራሣቸው ለማድረግ ቋምጠዋል፡፡ ሕወሃት
ለ24 ዓመታት ያመቻቸላቸው ዘረኝነትና ጥላቻ ለዚህ እኩይ ተግባራቸው
መንገዱን ወለል አድርጎ ከፍቶላቸዋል፡፡ ሁሉም ማቆም አለባቸው!!
ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ “ከጎሣ ይልቅ ለሰብዓዊነት ቅድሚያ
እንስጥ” በሚለው ቀዳሚ ዓላማው መሠረት “ሁላችንም ነጻ ካልወጣን
በስተቀር ማንም ብቻውን ነጻ መውጣት አይችልም” የሚለው መርህ
አሁንም በተግባር ላይ መዋል አለበት ብሎ ያምናል፡፡ ስለዚህ
ማንኛውንም የሕዝብ እንቅስቃሴ ለራሳችሁ የግል፣ የጎሣ፣ የወገንና
የሥልጣን ጥማት ማርኪያ ለማዋል ያሰባችሁ ከህወሃት ተማሩና
ትግሉን ለመቀልበስ የምታደርጉትን ሙከራ አቁሙ፤ ይህ የሕዝብ
ትዕይንት ነው፤ እናንተ በዘር በሽታ የተለከፋችሁ እና መፍትሔ
በጠብመንጃ አፈሙዝ እናገኛለን ብላችሁ የምታምኑ የህወሃት ሰዎች
ወደ ኅሊናችሁ ተመለሱ፤ ቀን ሳለ አሁን ልባችሁን ክፈቱና ዋይ በሉ፤
የሕዝብ ቁጣ ገንፍሎ የአምላክ በትር በእናንተ ላይ ሳይወርድ
በማጭበርበርና በማታለል ወይም በውሸት ሽምግልናና ዕርቅ ሳይሆን
ከልብ በመነጨ ቅንነት የሕዝብን ጥያቄ መልሱ፡፡
የገነባችሁት ሁሉ አልሰራ ብሎ በራሱ መፍረስ ከጀመረ ቆይቷል፤ ይህ
ደግሞ በጥገና እና ቀዳዳ በመድፈን አይስተካከልም፡፡ የድርብ አኻዝ
የኢኮኖሚ ዕድገት እያላችሁ ለዘመናት ስትዋሹ የኖራችሁበት ዲሰኩር
በችጋር ዓይኑን አፍጥጦ በገሃድ ታይቷል፡፡ ሁሉም ነገር አብቅቶለታል፡፡
አሁን ካለበት የከፋ ደረጃ ላይ ከመድረሱ በፊት አቁሙ! የኢትዮጵያውያን
ደም የፈጣሪ ደጅ ከደረሰ ቆይቷል፡፡ የእርሱን ዝምታ እንደ ስንፍና
ከቆጠራችሁት የበቀል በትሩን ሲዘረጋ የገተራችሁት ፎቅና ያደለባችሁት
ጦር በጭራሽ አይመክተውም፡፡
የአምላክ ፍርድ በሕዝብ ምሬትና ቁጣ ይገለጻል፡፡ ያንን ለማብረድ
ጊዜው አሁን ነው፤ የጋራ ንቅናቄው በዚህ ጉዳይ ላይ ከማንኛውም
ይመለከተኛል ከሚል ጋር ለመሥራት አሁንም ፍላጎቱን ያለው መሆኑን
ያስታውቃል፡፡ በአገር ውስጥና በውጭ ያላችሁ ባላችሁበት ኅብረተሰብ
ዘንድ ተደማጭነት ያላችሁ ሁሉ በሁሉም መስክ ባገራችን ላይ
የተነጣጠረውን መቅሰፍት ለማርገብ የሕዝብ ድምጽ መሆን
የምትችሉበት ወሳኝ ጊዜ አሁን ነውና ድምጻችሁን አሰሙ፤ለአዲሲቷ
ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ ከጎናችሁ ነው፡፡
አምላክ የፈሰሰውን ደማችንን ያብስልን፤ ቁስላችንን ይፈውስልን፤
ለለውጥ በግል ወይም በጥቂት ቡድን ወይም በጎሣ ወይም በዘር
ሳይሆን በአንድነት ለአንድ ዓላማ ለመነሳት እንድንችል ራዕይ ይስጠን፡፡
ዓይናችን እውነትን ለማየት ብርሃን ይስጠን፤ ጆሮዎቻችንም እውነትን
ለመስማት የተከፈቱ ይሁኑልን፤ ኅሊናችንም እውነትን ለመረዳትና
በተግባር ለማዋል የወሰነ ያድርግልን፡፡
ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ
የበለጠ መረጃ ለማግኘት የጋራ ንቅናቄውን ዋና ዳይሬክተር ኦባንግ
ሜቶን በዚህ አድራሻ ማግኘት ይቻላል፤
Obang@solidaritymovement.org

http://wp.me/p5L3EG-85

Keine Kommentare:

Kommentar veröffentlichen