Netsanet: März 2016

Dienstag, 29. März 2016

በእኔ እምነት የታለመለትን ዓላማ የማያሳካ ማነኛውም ዓይነት ስብስብ፣ የፖለቲካ ፓርቲን ጨምሮ ቢፈርስ ግድ አይሰጠኝም፡፡

በአንድ ወቅት በመድረክና በአንድነት መካከል የነበረው ጫጫታ አንዱ መንስዔ “መድረክ የታለመለትን ዓላማ ካላሳካ መፍረስ አለበት” የሚለው የሀብታሙ አያሌው አስተያየት ነበር፡፡ እንዴት እንዲህ ይባላል በሚሉ እና ልክ ቢሆንም “Politically incorrect” ነው በሚል እስጥ አገባው በዝቶ ነበር፡፡ የእኔ አቋም ግልፅ ነበር፡፡ መድረክ አይደለም አንድነትም ቢሆን የታለመለትን ዓላማ ካላሳካ ይፈርሳል፡፡ ምንም እሹሩሩ አያስፈልግም የሚል ነበር፡፡ ይህን አቋም መሰረት ባደረገ አንድነትን የተሳካለትን ዓላማ ለማሳካት የሚችል ባደረግነው እንቅስቃሴ የተደናገጠው ገዢ ፓርቲ ያለምንም ይሉኝታ አንድነትን አፍርሶታል፡፡ እኛም ድንክ የሆነ አንድነት ከሚኖረን የፈረሰው አንድነት ለጥቂት ጊዜም ቢሆን ያሳየው መነቃቃል ያስደስተናል፡፡ አሁንም ብዙ ሰዎች ለስም መጠሪያ ፓርቲዎች እንዲኖሩ የሚፈልጉ አሉ፡፡ በእኔ እምነት የታለመለትን ዓላማ የማያሳካ ማነኛውም ዓይነት ስብስብ፣ የፖለቲካ ፓርቲን ጨምሮ ቢፈርስ ግድ አይሰጠኝም፡፡ በተለይ በአሁኑ ጊዜ በሀገራችን ኢትዮጵያ ለመድበለ ፓርቲ የተዘጋጀ መንግሰት ይህን ለማምጣት ቁርጠኛ ህዝብ በሌለበት ፓርቲ ማለት ምንም ማለት ነው፡፡ እያንዳንዱ ሰው ከየትኛውም ክፍል ምንም ዓይነት መመሪያ ሳይጠብቅ መብቱን ለማሰከበር በጉብዝና መነሳት ይኖርበታል፡፡ የዛን ጊዜ ከጎበዞቹ መካከል የጎበዝ አለቃ ይገኛል፡፡ የጎበዞቹ ስብስብም ፓርቲ ይባላል፡፡

አቶ ግርማ ሰይፉ
https://netsanetlegna.wordpress.com/2016/03/29/%e1%89%a0%e1%8a%a5%e1%8a%94-%e1%8a%a5%e1%88%9d%e1%8a%90%e1%89%b5-%e1%8b%a8%e1%89%b3%e1%88%88%e1%88%98%e1%88%88%e1%89%b5%e1%8a%95-%e1%8b%93%e1%88%8b%e1%88%9b-%e1%8b%a8%e1%88%9b%e1%8b%ab%e1%88%b3/

የነጻነት ዋጋ (አቤል ዋበላ)

የነጻነት ዋጋ
ይህ የአእምሮ ጨዋታ አርነት የወጣች ነፍስ ላላቸው ወይም ነፍሳቸው አርነት እንድትወጣ በመፈለግ በታላቅ ፍርሃት እና መራድ ውስጥ ለሚገኙ እና በህይወታቸው ምክንያታዊ ውሳኔን ማሳለፍ ጥረት ለሚያደርጉ ነው፡፡ ብዙ ጊዜ ይህንን ትግል የሚያደርጉ ሰዎች በራሳቸው ተነሳሽነት አሊያም በማኀበረሰባዊ ተጽዕኖ ምክንያት ሂሳባዊ ስሌት ይሰራሉ፡፡ ይህ የማደርገው ነገር የሚያመጣብኝ ችግር መከራውን ተቀብዬ ከማገኘው ጥቅም አንጻር ሲመዘን ያዋጣኛል? ብዙዎች እንደሚያደርጉት ራሴን በተፈቀደለኝ መጠን ማኖር፣ ማዝናናት አይሻለኝምን? ይህን የነጻነት ድርጊት/ዐሳብ፣  ብፈጽም/ ባስብ በዚህ ምክንያት የምቀበለው እንክርት እና እንግልት ተገቢ ነውን? ትንሽ ራስን ከማሰቃየት የሚገኝ ደስታን ፈላጊ(ሳዲስት) አልሆንኩም? የመሳሰሉት ጥያቄዎች በሰልፍ ወደ አእምሮ ይመጣሉ፡፡ Selfless እንዳልሆንን ስለምናውቀው የእነዚህ ጥያቄዎች አግባብነት ጮክ ብሎ ይሰማናል፡፡ ወላጆቻችን ያወረሱን “የሚያልፍ ዝናብ አይመታህ” የሚለው ምርቃት ያቃጭልብናል፡፡ ይሄ ነጻነት የሚሉት ነገር አዋጭ ነው ወይ?

ይህ መልሱ ቀላል እና አጭር ነው፡፡ ብዙዎችን በሩቅም በቅርብም ሆነው ይህንን ስሌት በማደረግ እንደነጋዴ ሲመትሩ የሚደረስባቸውን ችግር ለማሳነስ ነጻነትን በማድረግ እና ባለማደረግ መሀል ሲዋልሉ ተመልክቻለው፡፡ ይህ ፍርሃታቸውን አሸንፈው የከፈሉትን መስዋዕትነት እንኳን በዜሮ የሚያባዛ ነው፡፡  ‘ሞኝ አትሁን’ የሚል የወዳጅ የዘመድ ምክር የሚጠይቅም አይደለም፡፡ነጻነትን ማከናወን ብዙ ጊዜ የሚጠናቀቀው በኪሳራ ነው ፡፡ ነገር ግን ነጻነትን መከወን ምርጫ ነው፡፡ ነጻነትን ማድረግ ገቢ የሌለው ክፍያ ነው፡፡ ለቀጣይ ትውልዶች እየተባሉ ነገሮች በኃላፊነት መደረጋቸውን ብድግፍም የእኔ ትውልድ ፍትሓዊ ጥቅም የማያገኝበት ነገ ስሜት ስለማይሰጠኝ  ስምን ከመቃብር በላይ የማኖር አስፈላጊነትን መረዳት ይከብደኛል፡፡  ስለዚህ ነጻነትን የምናደርገው እና የምንኖረው ስለሚያዋጣን ሳይሆን ልክ ስለሆነ ነው፡፡ ነጻነት ትክክለኛ ነው ስለዚህ እንኖረዋለን፤ እናደርገዋለን፡፡ የሰው ልጆች ታሪክም የሚነገረን ይህነን ነው፡፡ ልክ የሆነውን ነጻነት በማድረጋቸው ብቻ ተነግሮ የማያልቅ ግፍን የተቀበሉ ሰዎች ብዙ ናቸው፡፡ የነጻነት ዋጋው ለሚያምኑበት ነገር መከራን መቀበል ነው፡፡ ይህ የምድሪቱ በረከት ነው፡፡ የሀገሬ ሰው ‘ሰው የዘራውን ያንኑ ያጭዳል’ እንደሚለው ሳይሆን ሰው ለሚያምንበት ልክ ነገር ዋጋ ይከፍላል፡፡
https://netsanetlegna.wordpress.com/2016/03/29/%e1%8b%a8%e1%8a%90%e1%8c%bb%e1%8a%90%e1%89%b5-%e1%8b%8b%e1%8c%8b-%e1%8a%a0%e1%89%a4%e1%88%8d-%e1%8b%8b%e1%89%a0%e1%88%8b/

Montag, 28. März 2016

መነጋገር፤ መተማመን፤ መተራረቅ! የኢትዮጵያ የዕርቅና ርትዓዊ ፍትሕ ምክርቤት እኛ ለኛ ሕዝባዊ መድረክ!

መነጋገር፤ መተማመን፤ መተራረቅ!
የኢትዮጵያ የዕርቅና ርትዓዊ ፍትሕ ምክርቤት
እኛ ለኛ ሕዝባዊ መድረክ!

በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን በሜነሶታ ጠቅላይ ግዛት እንደሚኖሩ ይታወቃል፡፡ በተለይ ከኦሮሚያ፣ ከጋምቤላ፣ ከሶማሊ፣ ከአማራና ከትግራይ ቦታዎች የመጡ እና ሌሎች ቁጥራቸው አነስተኛ የሆኑ ማኅበረሰቦች የሚገኙ ቢሆንም ከራሳቸው ወገን በስተቀር እርስበርስ አይገናኙም፤ አይቀራረቡም፡፡

በአገራችን ያለውን የዘርና የወገን መከፋፈልን ጨምሮ ሌሎች የሕዝባችንን ሕይወት አደጋ ላይ ለጣሉ ችግሮች መፍትሔ ለማምጣት ብዙዎቻችን እንፈልጋለን፡፡ በውጭ ያለነው ተቀራርበን ሳንነጋገር እንዴት ነው ይህንን ችግር መፍታት የምንችለው? “መቀራረብ አያስፈልገንም፤ ለብቻችን እንፈታዋለን” ብንል እንኳን በአንድም ይሁን በሌላ መልኩ በደም የተሳሰርንባቸውን ሌሎቹን ወገኖች ትተን እና ለእነርሱ ግድ ሳይለን የራሳችን ለምንለውን ብቻ እንዴት ተግባራዊ ማድረግ እንችላለን?

ከዚህ በተጻራሪው ደግሞ ለሌሎቹም ማኅበረሰቦች መሥራት እፈልጋለሁ፤ የራሴ ብቻ ሳይሆን የሌሎቹም ጉዳይ ግድ ይለኛል የምንል ከሆነ ተቀራርበን መነጋገርና መተማመን ሳንችል እንዴት ነው ይህንንስ ተግባራዊ ማድረግ የምንችለው? ሌሎች በውስጣቸው ያለባቸውን ሐዘንና ምሬት እርስበርስ ተቀራርበን ሳንነጋገር፤ ሳናዳምጣቸው፤ የውስጣቸውን ቁስል ሳንሰማ እንዴት ነው መተማመንና መተራረቅ የምንችለው? ይህ ሳይሆን የሁላችንም ልትሆን የሚገባትን ኢትዮጵያንስ እንዴት የራሳችን ማድረግ እንችላለን?

“ስለሌላው ከማውራት ይልቅ እርስበርሳችን እንነጋገር” በሚል መሪ ሃሳብ የአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ (አኢጋን) ያለፈው ዓመት በዚሁ በሜነሶታ አንድ መድረክ አዘጋጅቶ ነበር፡፡ የዚህ ዓይነቱ መድረክ እየሰፋ ሄዶ በተለያየ ቦታ የሚገኙ ወገኖች ይህንን የመነጋገርና የመተማመን መድረክ በስፋት ለማካሄድ እንዲረዳና ወደ ትልቁ ዓላማችን ለመድረስ እንድንችል በሚል የኢትዮጵያ የዕርቅና ርትዓዊ ፍትሕ ምክርቤትን በቅርቡ መሥርተዋል፡፡ በሜነሶታ የሚደረገው ይህ ውይይትም ከዚሁ ምክርቤት ምሥረታ ጋር በተያያዘ ውይይቱን ወደ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ለማድረስ የታቀደ ነው፡፡

ስለዚህ ለችግሮቻችን መፍትሔውን የምናመጣው እኛው የችግሩ ባለቤቶች እንጂ ሌላ ማንም አይደለምና በዚህ የእኛ ለእኛ የውይይት፣ የንግግር፣ የመግባባት፣ የመተማመን ስብሰባ ላይ እንዲገኙ ተጋብዘዋል፡፡ ቀኑና አድራሻው ከላይ በተጠቀሰው መሠረት ሌሎችን ጋብዘው እንዲመጡ በአክብሮት ጠርተንዎታል፡፡ከተለያየ የኢትዮጵያ ክፍል የተወከሉ ወገኖች እውነተኛና ልባዊ የሆነ ንግግር ያዳምጣሉ፤ እርስዎም ሃሳብዎን በማካፈልና ጥያቄዎችን በማንሳት የመተማመን ውይይት ያደርጋሉ፡፡ እርስበርሳችን ተራርቀን የምንኖርባት አገር ልትኖረን የምትችለው እኛው ከእኛው ጋር ተገናኝተን ስንነጋገር፤ በመነጋገር ስንደማመጥ ይህም ወደ መተማመን ሲወስደን፤ መተማመናችን ደግሞ መተራረቅን ሲያመጣልን ነው፡፡

በስምምነት መኖር የሚችል ኅብረተሰብ መፍጠር የሚቻለው ስለሌላው ከማውራት ይልቅ እርስበርሳችን ስንነጋገር ነው!
ለተጨማሪ መረጃ፤
አቶ ነጌሦ ዋቀዮን nwakeyo@yahoo.com ወይም
አቶ ኦባንግ ሜቶን ያነጋግሩ፡
ኢሜይል፡ obang@solidaritymovement.org
www.solidaritymovement.org

ቀኑ፡ ቅዳሜ መጋቢት 24፤ 2008ዓም/Saturday, April 2, 2016
ሰዓቱ፡ 1:00 - 5:00 PM
ቦታ፡ University of Minnesota – Minneapolis
Willey Hall Room 125
(West Bank; behind Mondale Hall)
225 19th Avenue S
Minneapolis, MN 55455
Nearest Parking: C86 Lot, 19th Ave. Ramp, or 21st Ave. Ramp
https://netsanetlegna.wordpress.com/2016/03/28/%e1%88%98%e1%8a%90%e1%8c%8b%e1%8c%88%e1%88%ad%e1%8d%a4-%e1%88%98%e1%89%b0%e1%88%9b%e1%88%98%e1%8a%95%e1%8d%a4-%e1%88%98%e1%89%b0%e1%88%ab%e1%88%a8%e1%89%85%e1%8b%a8%e1%8a%a2%e1%89%b5%e1%8b%ae/

ዞን ዘጠኞች ዳግሞ ወደ ፍርድ ቤት (Zone 9 Update)

ዞን ዘጠኞች ዳግሞ ወደ ፍርድ ቤት

(Zone 9 Update)

ሚያዚያ 17/2006 በድንገት ከያሉበት ተይዘው የታሰሩት የዞን ዘጠኝ ጦማርያንና ጋዜጠኞች በሐምሌ 08/2006 የተፃፈ ክስ ሐምሌ 11/2006 ‹ስለ ፀረ-ሽብርተኝነት የወጣውን አዋጅ ቁጥር 652/2001 አንቀፅ 3/2/ እና 4 ተላልፋችኋል› በሚል ክስ ቀርቦባቸው የነበረ መሆኑ አይዘነጋም፡፡ ክስ ከቀረበባቸው አስር ግለሰቦች መካከል አምስቱ ሐምሌ 01/2007 በድንገት ከሳሽ ክሱን አንስቻለሁ በማለቱ ከእስር የወጡ ሲሆን፤ ቀሪዎቹ አምስት ግለሰቦች ላይ ግን ከሳሽ የመሰረተውን ክስ ቀጥሎበት ያቀረባቸው የሰውና የሰነድ ማስረጃዎች ጉዳዩን የያዘው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 19ኛ ወንጀል ችሎት መርምሮ በጥቅምት 05/2008 በዋለው ችሎት 1ኛ ተከሳሽ ሶልያና ሽመልስ፣ 3ኛ ተከሳሽ ናትናኤል ፈለቀ፣ 5ኛ ተከሳሽ አጥናፉ ብርሃኔ እንዲሁም 7ኛ ተከሳሽ አቤል ዋበላ ‹የቀረበባቸውን ክስ መከላከል ሳይገባቸው በነፃ ይሰናበቱ› በማለት ብይን የሰጠ ሲሆን፤ 2ኛ ተከሳሽ በፍቃዱ ኃይሉ በፀረ-ሽብርተኝነት አዋጁ መሰረት የቀረበበትን ክስ ወደ መደበኛው የወንጀል ሕግ አንቀፅ 256/ሀ/ በመቀየር ክሱን እንዲከላከል ብይን ሰጥቶ ነበር፡፡

በተሰጠው ውሳኔ መሰረትም ነፃ የተባሉት የዞን ዘጠኝ አባላት ከእስር የተለቀቁ ሲሆን በመደበኛው ወንጀል ሕጉ መሰረት ክሱን እንዲከላከል የተወሰነበት በፍቃዱ ኃይሉ በሃያ ሽህ በር ዋስትና ከእስር ተለቋል፡፡ ነገር ግን ‹በከፍተኛው ፍርድ ቤት ውሳኔ ቅር ተሰኝቻለሁ› በማለት ከሳሽ ዓቃቤ ሕግ በታህሳስ 04/2008 የተፃፈ ይግባኝ ለፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የወንጀል ችሎት ይግባኝ አቅርቧል፡፡ ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤትም ከሳሽ በፅሁፍ አለኝ ያለውን ቅሬታ በቃል ሰምቶና የተከሳሾቹን ምላሽ በማዳመጥ ለነገ መጋቢት 20/2008 ብይን ለመስጠት ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

ምን ሊከሰት ይችላል?

በነገው የፍርድ ቤት ውሎ ችሎቱ መዝገቡን መርምሮ የጨረሰ ከሆነና ‹ተጨማሪ ማስረጃ አያስፈልገኝም› የሚል ከሆነ ሶስት የተለያዩ ነገሮች ሊከሰቱ ይችላሉ፡፡

የመጀመሪያው ነገር ‹የስር ፍርድ ቤቱ የሰጠው ውሳኔ ተገቢ ነው› በማለት የስር ፍርድ ቤቱን ውሳኔ በማፅናት የተከሳሾቹን ነፃነት ማስጠበቅ ነው፡፡

ሁለተኛው ሊከሰት የሚችለው ጉዳይ ደግሞ ከመጀመሪያው በተቃራኒ የከሳሽ ቅሬታን ተቀብሎ የስር ፍርድ ቤትን ውሳኔ በመሻር ‹ተከሳሾቹ ክሳቸውን እንዲከላከሉ› የሚል ውሳኔ በመስጠት ተከሳሾቹን ዳግም ወደ እስር ቤት መመለስ ነው፡፡

ሶስተኛው የሚጠበቀው ጉዳይ የስር ፍርድ ቤት 2ኛ ተከሳሽን በፍቃዱ ኃይሉን የሚመለከት ሲሆን፤ በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕጉ መሰረት አንድ ሰው በተመሳሳይ ጉዳይ በተመሳሳይ ጊዜ በሁለት የተለያዩ ፍርድ ቤቶች ክሱን ሊከታተል ስለማይገባ ከሕግ አግባብ ውጭ በፍቃዱ ላይ የቀረበውን ይግባይ ውድቅ ያደርገዋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

እኛም ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት የስር ፍርድ ቤትን ውሳኔ በማፅናት ይህ በመናገር ነፃነት ላይ የተሰነዘረን ጥቃት ላንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እልባት ይሰጠዋል የሚል ተስፋ አለን፡፡
https://netsanetlegna.wordpress.com/2016/03/28/%e1%8b%9e%e1%8a%95-%e1%8b%98%e1%8c%a0%e1%8a%9e%e1%89%bd-%e1%8b%b3%e1%8c%8d%e1%88%9e-%e1%8b%88%e1%8b%b0-%e1%8d%8d%e1%88%ad%e1%8b%b5-%e1%89%a4%e1%89%b5zone-9-update/

Samstag, 26. März 2016

የሽብርተኛ ትርጉም መስፍን ወልደ ማርያም መጋቢት 2008

የሽብርተኛ ትርጉም
መስፍን ወልደ ማርያም
መጋቢት 2008

የሚማር የለም እንጂ የሚማር ቢኖር የሽብርተኛነትን ትርጉም ሰሞኑን በቤልጂክ እያየንና እየሰማን ነው፤ በኢትዮጵያ ያሉ የእውቀት ምልክቶችን በዶላር እየገዙ ስማቸው ላይ የለጠፉ ጉልበተኞች ተናገርክ(ሽ) ብለው ብቻ ሳይሆን አሰብህ(ሽ) ብለው ሰፋፊ እስር ቤቶች እያሰሩ ወጣቶችን ሲያጉሩበት ምክንያታቸው ሽብርተኛነት ነው፤ ሽብር ማለት ሰሞኑን በቤልጂክ አውሮጵላን ጣቢያና በባቡር ጣቢያ ላይ እንደታየው ከሆነ ኢትዮጵያ ውስጥ አልታየም፤ ከታየም በአገዛዙ ኃይሎች የተፈጸመ ነው፤ ለብዙ ዓመታት ሲፈጸም የቆየ ነው፤ የኢትዮጵያ ጉልበተኞች ከቻሉ ሊያስተውሉት የሚገባ አንድ ነገር አለ፡- ሽብርም ነጻነትን ይፈልጋል፤ በቤልጂክ ሽብሩን የፈጸሙት ሁሉ ነጻነትን ፈልገው ከአገራቸው የተሰደዱና በአገራቸው ያላገኙትን ነጻነት በሰው አገር እየተሞላቀቁበት እንደሆነ የሚያመለክት ነው፤ ትርጉሙ፡- ነጻነት በሌለበት ሽብር አይኖርም፤ እንዴት ብሎ? የት ተደብቆ? የት ሸምቆ?
ሽብርን የጸነሰውን እንዳያስብ አፍኖ፣ እንዳይናገር አንደበቱን መርጎ፣ እንዳይንቃሳቀስ በዳኛ ትእዛዝ ወህኒ ቤት ውስጥ ቆልፎ ሽብርን ማቆም አይቻልም፤ የሚቻለው፣ እየሆነ ያለውም ዝንባሌው ያላቸው ኢትዮጵያውያን ለሽብር ትምህርት ወደአውሮፓና ወደአሜሪካ እንዲሄዱ የሚገፋፋቸው ነው፤ የዚህን ግፊት ውጤት የኢትዮጵያ ጉልበተኞች የሚወዱት አይመስለኝም፤ መጠቃት እንደማጥቃት አያስደስትም!
የእኝ ጉልበተኞች ሽብር ምን እንደሆነ አያውቁም፡፡
የእኛ ጉልበተኞች በንግግርና በተግባር መሀከል ያለውን ልዩነት አያውቁም፤ በቤልጂክ ሽብር የተባለው ሠላሳ አንድ ያህል ሰዎች የሞቱበት፣ ወደሦስት መቶ ሠላሳ ያህል ሰዎች የተጎዱበት ነው፤ ኢትዮጵያ ውስጥ እንዲህ ያለ ነገር ደርሶ ያውቃል? እንዴታ! በዙ ጊዜ፤ ግን ሽብርተኞች በተባሉትና በታሰሩት አይደለም፤ በተመቻቸውና ሕግ በማይደርስባቸው ሌሎች ጉልበተኞች የተፈጸመ ነው፡፡
የእኛ ጉልበተኞች በፍርሃት የደነዘዘው አንጎላቸው ዓይናቸው እውነቱን እንዲያይ፣ ጆሮአቸው እውነትን እንዲሰማና ልባቸው ወደመወያየትና ወደእርቅ እንዲያቀና አያደርጋቸውም፤ ወላጆቻቸውን ንቀው ብቻቸውን የቆሙ ስለሆኑ መካሪ የላቸውም፤ መንፈስ ስለሌላቸው መንፈሳዊ አባት የላቸውም፤ ያሳዝናሉ፡–  
ሀሳቤን አንዱ ግጥሜ ይገልጽልኛል መሰለኝ፡– የሞተ ኅሊና

የማይጣላ ኅሊና ያለው
እንዴት የታደለ ነው!
እግዜር ብቻ ነው ኅሊና የሌለው፤
የማይሳሳት የማየወቆጨው፡፡
ሰው ሰውነቱ፣ ጭንቀቱና ልፋቱ፣
ኅሊናው ከስሜቱና ከፈላጎቱ መጣላቱ፣
የሚረሳ የሚሳሰት፣ የማይታየው የፊቱ፣
የሚወድ፣ የሚጠላ፣ የሚፈራ፣ ኧረ ስንቱ!
ከሳሽ፣ ተከሳሽ፣ ዳኛ መሆን
እንዴት ይችላል መበየን?
ሲያፍነው ግን ኅሊናውን
አይለይም ጨለማውን ከብርሃን!
ኅሊናውን ገደለ ሰው
ማን ሊቀረው? ምን ሊያቅተው?
የጉልበቱ መሣሪያ ነው፤
ጊዜ ጉልበቱን እስቲሰብረው! … …

እውነተኞቹ ሽብርተኞች በኢትዮጵያ ውስጥ ካሉ ከሥልጣን ውጭ አይደሉም፤ ከሥልጣን ውጭ ሆነው ቅራኔ የሚያሰሙ ጉልበታቸው እዚያው ላይ ያበቃል፤ በምድረ ኢትዮጵያ ሽብርን መቃወም ሽብርተኛ ያደርጋል፤ ወህኒ ያስገባል፤ ተመስገን ደሳለኝ፣ እስክንድር ነጋ፣ አብርሃ ደስታ፣ … በወህኒ ቤት የሚማቅቁት ቅንጣት የሚያህል የሽብር ተግባር ፈጽመው አይደለም፤ ሽብር እንዳይፈጸም ስለታገሉ ነው፤ ሽብር ከነገሠ ሰላም ወንጀል ይሆናል፤ በኢትዮጵያ ሰላም ዋጋ እያጣ መሄድ ላይ መሆኑን የሚጠራጠር የለም፤ ከባሕር ማዶ የተጀመረው ቀረርቶ ወደተግባር ሲለወጥ መፍራት ፋይዳ የለውም፤ ለጉልበተኞቹ የሚያዋጣው የፍርሃት ጊዜው አሁን ነው! እንደሳዳም ሁሴንና እንደጋዳፊ እንደአይጥ ከተሸጎጡበት ስርቻ እየተጎተቱ ሲወጡ አይደለም፡፡

https://netsanetlegna.wordpress.com/2016/03/25/%e1%8b%a8%e1%88%bd%e1%89%a5%e1%88%ad%e1%89%b0%e1%8a%9b-%e1%89%b5%e1%88%ad%e1%8c%89%e1%88%9d%e1%88%98%e1%88%b5%e1%8d%8d%e1%8a%95-%e1%8b%88%e1%88%8d%e1%8b%b0-%e1%88%9b%e1%88%ad%e1%8b%ab%e1%88%9d/

Montag, 7. März 2016

-በ97ቱ ምርጫ ቅንጅት ማሸነፉን ተከትሎ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት  በተጠራው የኢህአዴግ ማእከላዊ ኮሚቴ አስቸኳይ ስብሰባ ላይ መለስ  (በአዲስ አበባ  ተወዳድረው  በህዝብ ድምጽ ክፉኛ የተቀጡትን)  ቱባ ቱባ ሹመኞቻቸውን ፦”የአዲስ አበባን ሕዝብ ምን አድርጋችሁት ነው እንዲህ የቀጣችሁ?”

ደረጄ ሀብተወልድ
-በ97ቱ ምርጫ ቅንጅት ማሸነፉን ተከትሎ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት  በተጠራው የኢህአዴግ ማእከላዊ ኮሚቴ አስቸኳይ ስብሰባ ላይ መለስ  (በአዲስ አበባ  ተወዳድረው  በህዝብ ድምጽ ክፉኛ የተቀጡትን)  ቱባ ቱባ ሹመኞቻቸውን ፦”የአዲስ አበባን ሕዝብ ምን አድርጋችሁት ነው እንዲህ የቀጣችሁ?” በማለት ነበር ያሸማቀቋቸው። ልብ በሉ፤ “ምን አድርገነው ነው?” ሳይሆን- “ምን አድርጋችሁት ነው?” ነው ያሉት። 
-ኋላ ላይም ከተቃዋሚ መሪዎች ጋር በተደረጉት  የምርጫ ክርክሮች  እንደ ሌሎቹ የኢህአዴግ  ሹመኞች መድረክ ላይ ወጥተው ለምን እንዳልተከራከሩ ሲጠየቁ ፦”ድርጅቴ አንተ ክርክር መድረኩ ላይ ከወጣህ ሂሳብ  ስለምታወራርድ የአንተ መከራከር ይቅር” ብሎኝ ነው ማለታቸው ተሰምቷል።    ( በዚህ አገባብ “ሂሳብ ታወራርዳለህ” የሚለው ቃል  “ተገቢ ያልሆነ ቃል ትናገራለህ” የሚል ትርጉም የያዘ ይመስላል።

-በወቅቱ መለስ በአዲስ አበባ ቢወዳደሩ ያሸንፉ ነበር?- በፍጹም!
-ከተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር በግልጽ ቢከራከሩ የሚፈጥሩት ለውጥ ይኖር ነበር?-በፍጹም!

ሆኖም ሁሌም አደጋ ሲመጣ  የድርጅቱን ውድቀትና ሽንፈት በተወሰኑ  “አቅመ-ቢስ ሹመኞች”  ጫንቃ ላይ መጣል የኢህአዴግ የተለመደ “ታክቲክ” በመኾኑ፤  በመቀሌ በመወዳደራቸው ብቻ እንደ ግለሰብ ከሽንፈት የተረፉት መለስ በ አዲስ አበባ የተወዳደሩትን ጓዶቻቸውን  አሸማቀቋቸው።

ቀደም ባሉት ዓመታትም ለአዲስ አበባ መስተዳድር ውድቀት - አሊ አብዶን እንደሰቀሉት ያስታውሷል።

አሁንም ከዚያው ያፈጀ ዘዴ በመነሳት  ለኦሮሚያ ክልሉ ተቃውሞ  ጥቂት የኦህዴድ ሹመኞችን ተጠያቂ እያደረጉና ከኃላፊነታቸው እያነሱ ይገኛሉ። የድርጅትን ውድቀትና ሸክም ግለሰቦች ጫንቃ ላይ ማራገፉ ቀጥሏል። አጋዚ ክፍለ-ጦርና  ፌዴራል ፖሊስ ተቀናጅተው ሊያቆሙት ላልቻሉት ተቃውሞ፤ ዳባ ደበሌንና  ጀማነህ ዘላለምን  ተጠያቂ በማድረግ መፍትሔ ይገኛል ብሎ ማሰብ ኅሊናን መሸንገል ነው።ጥያቄው የሥርዓት እንጅ የግለሰቦች ለውጥ አይደለም!
http://wp.me/p5L3EG-aF