Netsanet: መነጋገር፤ መተማመን፤ መተራረቅ! የኢትዮጵያ የዕርቅና ርትዓዊ ፍትሕ ምክርቤት እኛ ለኛ ሕዝባዊ መድረክ!

Montag, 28. März 2016

መነጋገር፤ መተማመን፤ መተራረቅ! የኢትዮጵያ የዕርቅና ርትዓዊ ፍትሕ ምክርቤት እኛ ለኛ ሕዝባዊ መድረክ!

መነጋገር፤ መተማመን፤ መተራረቅ!
የኢትዮጵያ የዕርቅና ርትዓዊ ፍትሕ ምክርቤት
እኛ ለኛ ሕዝባዊ መድረክ!

በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን በሜነሶታ ጠቅላይ ግዛት እንደሚኖሩ ይታወቃል፡፡ በተለይ ከኦሮሚያ፣ ከጋምቤላ፣ ከሶማሊ፣ ከአማራና ከትግራይ ቦታዎች የመጡ እና ሌሎች ቁጥራቸው አነስተኛ የሆኑ ማኅበረሰቦች የሚገኙ ቢሆንም ከራሳቸው ወገን በስተቀር እርስበርስ አይገናኙም፤ አይቀራረቡም፡፡

በአገራችን ያለውን የዘርና የወገን መከፋፈልን ጨምሮ ሌሎች የሕዝባችንን ሕይወት አደጋ ላይ ለጣሉ ችግሮች መፍትሔ ለማምጣት ብዙዎቻችን እንፈልጋለን፡፡ በውጭ ያለነው ተቀራርበን ሳንነጋገር እንዴት ነው ይህንን ችግር መፍታት የምንችለው? “መቀራረብ አያስፈልገንም፤ ለብቻችን እንፈታዋለን” ብንል እንኳን በአንድም ይሁን በሌላ መልኩ በደም የተሳሰርንባቸውን ሌሎቹን ወገኖች ትተን እና ለእነርሱ ግድ ሳይለን የራሳችን ለምንለውን ብቻ እንዴት ተግባራዊ ማድረግ እንችላለን?

ከዚህ በተጻራሪው ደግሞ ለሌሎቹም ማኅበረሰቦች መሥራት እፈልጋለሁ፤ የራሴ ብቻ ሳይሆን የሌሎቹም ጉዳይ ግድ ይለኛል የምንል ከሆነ ተቀራርበን መነጋገርና መተማመን ሳንችል እንዴት ነው ይህንንስ ተግባራዊ ማድረግ የምንችለው? ሌሎች በውስጣቸው ያለባቸውን ሐዘንና ምሬት እርስበርስ ተቀራርበን ሳንነጋገር፤ ሳናዳምጣቸው፤ የውስጣቸውን ቁስል ሳንሰማ እንዴት ነው መተማመንና መተራረቅ የምንችለው? ይህ ሳይሆን የሁላችንም ልትሆን የሚገባትን ኢትዮጵያንስ እንዴት የራሳችን ማድረግ እንችላለን?

“ስለሌላው ከማውራት ይልቅ እርስበርሳችን እንነጋገር” በሚል መሪ ሃሳብ የአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ (አኢጋን) ያለፈው ዓመት በዚሁ በሜነሶታ አንድ መድረክ አዘጋጅቶ ነበር፡፡ የዚህ ዓይነቱ መድረክ እየሰፋ ሄዶ በተለያየ ቦታ የሚገኙ ወገኖች ይህንን የመነጋገርና የመተማመን መድረክ በስፋት ለማካሄድ እንዲረዳና ወደ ትልቁ ዓላማችን ለመድረስ እንድንችል በሚል የኢትዮጵያ የዕርቅና ርትዓዊ ፍትሕ ምክርቤትን በቅርቡ መሥርተዋል፡፡ በሜነሶታ የሚደረገው ይህ ውይይትም ከዚሁ ምክርቤት ምሥረታ ጋር በተያያዘ ውይይቱን ወደ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ለማድረስ የታቀደ ነው፡፡

ስለዚህ ለችግሮቻችን መፍትሔውን የምናመጣው እኛው የችግሩ ባለቤቶች እንጂ ሌላ ማንም አይደለምና በዚህ የእኛ ለእኛ የውይይት፣ የንግግር፣ የመግባባት፣ የመተማመን ስብሰባ ላይ እንዲገኙ ተጋብዘዋል፡፡ ቀኑና አድራሻው ከላይ በተጠቀሰው መሠረት ሌሎችን ጋብዘው እንዲመጡ በአክብሮት ጠርተንዎታል፡፡ከተለያየ የኢትዮጵያ ክፍል የተወከሉ ወገኖች እውነተኛና ልባዊ የሆነ ንግግር ያዳምጣሉ፤ እርስዎም ሃሳብዎን በማካፈልና ጥያቄዎችን በማንሳት የመተማመን ውይይት ያደርጋሉ፡፡ እርስበርሳችን ተራርቀን የምንኖርባት አገር ልትኖረን የምትችለው እኛው ከእኛው ጋር ተገናኝተን ስንነጋገር፤ በመነጋገር ስንደማመጥ ይህም ወደ መተማመን ሲወስደን፤ መተማመናችን ደግሞ መተራረቅን ሲያመጣልን ነው፡፡

በስምምነት መኖር የሚችል ኅብረተሰብ መፍጠር የሚቻለው ስለሌላው ከማውራት ይልቅ እርስበርሳችን ስንነጋገር ነው!
ለተጨማሪ መረጃ፤
አቶ ነጌሦ ዋቀዮን nwakeyo@yahoo.com ወይም
አቶ ኦባንግ ሜቶን ያነጋግሩ፡
ኢሜይል፡ obang@solidaritymovement.org
www.solidaritymovement.org

ቀኑ፡ ቅዳሜ መጋቢት 24፤ 2008ዓም/Saturday, April 2, 2016
ሰዓቱ፡ 1:00 - 5:00 PM
ቦታ፡ University of Minnesota – Minneapolis
Willey Hall Room 125
(West Bank; behind Mondale Hall)
225 19th Avenue S
Minneapolis, MN 55455
Nearest Parking: C86 Lot, 19th Ave. Ramp, or 21st Ave. Ramp
https://netsanetlegna.wordpress.com/2016/03/28/%e1%88%98%e1%8a%90%e1%8c%8b%e1%8c%88%e1%88%ad%e1%8d%a4-%e1%88%98%e1%89%b0%e1%88%9b%e1%88%98%e1%8a%95%e1%8d%a4-%e1%88%98%e1%89%b0%e1%88%ab%e1%88%a8%e1%89%85%e1%8b%a8%e1%8a%a2%e1%89%b5%e1%8b%ae/

Keine Kommentare:

Kommentar veröffentlichen