ደረጄ ሀብተወልድ
-በ97ቱ ምርጫ ቅንጅት ማሸነፉን ተከትሎ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት በተጠራው የኢህአዴግ ማእከላዊ ኮሚቴ አስቸኳይ ስብሰባ ላይ መለስ (በአዲስ አበባ ተወዳድረው በህዝብ ድምጽ ክፉኛ የተቀጡትን) ቱባ ቱባ ሹመኞቻቸውን ፦”የአዲስ አበባን ሕዝብ ምን አድርጋችሁት ነው እንዲህ የቀጣችሁ?” በማለት ነበር ያሸማቀቋቸው። ልብ በሉ፤ “ምን አድርገነው ነው?” ሳይሆን- “ምን አድርጋችሁት ነው?” ነው ያሉት።
-ኋላ ላይም ከተቃዋሚ መሪዎች ጋር በተደረጉት የምርጫ ክርክሮች እንደ ሌሎቹ የኢህአዴግ ሹመኞች መድረክ ላይ ወጥተው ለምን እንዳልተከራከሩ ሲጠየቁ ፦”ድርጅቴ አንተ ክርክር መድረኩ ላይ ከወጣህ ሂሳብ ስለምታወራርድ የአንተ መከራከር ይቅር” ብሎኝ ነው ማለታቸው ተሰምቷል። ( በዚህ አገባብ “ሂሳብ ታወራርዳለህ” የሚለው ቃል “ተገቢ ያልሆነ ቃል ትናገራለህ” የሚል ትርጉም የያዘ ይመስላል።
-በወቅቱ መለስ በአዲስ አበባ ቢወዳደሩ ያሸንፉ ነበር?- በፍጹም!
-ከተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር በግልጽ ቢከራከሩ የሚፈጥሩት ለውጥ ይኖር ነበር?-በፍጹም!
ሆኖም ሁሌም አደጋ ሲመጣ የድርጅቱን ውድቀትና ሽንፈት በተወሰኑ “አቅመ-ቢስ ሹመኞች” ጫንቃ ላይ መጣል የኢህአዴግ የተለመደ “ታክቲክ” በመኾኑ፤ በመቀሌ በመወዳደራቸው ብቻ እንደ ግለሰብ ከሽንፈት የተረፉት መለስ በ አዲስ አበባ የተወዳደሩትን ጓዶቻቸውን አሸማቀቋቸው።
ቀደም ባሉት ዓመታትም ለአዲስ አበባ መስተዳድር ውድቀት - አሊ አብዶን እንደሰቀሉት ያስታውሷል።
አሁንም ከዚያው ያፈጀ ዘዴ በመነሳት ለኦሮሚያ ክልሉ ተቃውሞ ጥቂት የኦህዴድ ሹመኞችን ተጠያቂ እያደረጉና ከኃላፊነታቸው እያነሱ ይገኛሉ። የድርጅትን ውድቀትና ሸክም ግለሰቦች ጫንቃ ላይ ማራገፉ ቀጥሏል። አጋዚ ክፍለ-ጦርና ፌዴራል ፖሊስ ተቀናጅተው ሊያቆሙት ላልቻሉት ተቃውሞ፤ ዳባ ደበሌንና ጀማነህ ዘላለምን ተጠያቂ በማድረግ መፍትሔ ይገኛል ብሎ ማሰብ ኅሊናን መሸንገል ነው።ጥያቄው የሥርዓት እንጅ የግለሰቦች ለውጥ አይደለም!
http://wp.me/p5L3EG-aF
Keine Kommentare:
Kommentar veröffentlichen