መንፈሳዊ ወኔና ሥልጣን
መስፍን ወልደ ማርያም
ጥቅምት 2009
ባለሥልጣኖቻችን ሚስቶቻቸውንና ልጆቻቸውን በጣም የናቋቸው ይመስላል፤ ሚስቶቻቸውና ልጆቻቸው የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚያውቀውን ሁሉ ያውቃሉ፤ የኢትዮጵያን ቴሌቪዥን ያያሉ፤ የኢትዮጵያን ራድዮ ይሰማሉ፤ ባሎቻቸውና አባቶቻቸው የዛሬ ሳምንት የተናገሩትን ረስተው፣ ወይም ክደው፣ ወይም ዋሽተው ተቃራኒውን ሲናገሩ መሸማቀቃቸው አይቀርም፤ እንዲህ ያለው የንግግር መገለባበጥ የእምነት መገለባበጥን፣ የማሰብ ችግርን፣ የመንፈስ ልልነትን ያሳያል፤ ታዲያ ሚስቶችና ልጆች እየተሸማቀቁ አካላቸውም ነፍሳቸውም ሲያልቅ ለባለሥልጣኖቹ አይታወቃቸውም? ወይስ የቤተሰብ አባሎች ጠባይ እየሆነ ሽታዬ ሽታዬ እየተባባሉ ነው?
አንዳንዶች ባለሥልጣኖች ወንበሩ ላይ የወጡት እግዚአብሔርን ሳይይዙ ነው፤ አንዳንዶቹ ደግሞ እግዚአብሔርን ይዘው ወንበሩ ላይ ይወጡና እግዚአብሔርን ከተቆናጠጡ በኋላ እግዚአብሔርን ከውስጣቸው የሚያስወጡት ይመስላል፤ የእግዚአብሔርን መንገድ ብዙ አናውቅምና ለሱ እንተውለት፡
ግን እኛም ሰዎቹ ባለሥልጣኖቻችን እውነተኞች ቢሆኑ፣ በትክክል ቢያስቡና የመንፈስ ልዕልና ቢኖራቸው እንኮራባቸው ነበር፤ አርአያም ይሆኑን ነበር፤ ልጆቻቸውም ከልጆቻችን ጋር ተግባብተው ያድጉ ነበር፤ ባለሥልጣኖቻችን ለቤተሰቦቻቸው ብቻ ሳይሆን ለኢትዮጵያ ሕዝብ በሙሉ የመንፈስ ልዕልና አርአያ እንዲሆኑልን ኃላፊነት አለባቸው፤ ተደጋግሞ እንዳየነው በየዘመኑ የተሰየሙልን ባለሥልጣኖቻችን የኃላፊነት ግዴታ የሚጎድላቸው ናቸው፤ ለአምላካቸው የኃላፊነት ግዴታ አይታይባቸውም፤ ለቤተሰቦቻቸው የመንፈሳዊ ኃላፊነት ግዴታ አላደረባቸውም፤ ለአገራቸውና ለወገናቸው ደኅንነትና ብልጽግና ኃላፊነት አይሰማቸውም፤ የሥልጣን ወንበሩ የሚፈለገው ለሁለት ዓላማዎች ብቻ ነው፤ ለጉልበትና ለሀብት ብቻ!
በእኔ ዕድሜ ሥልጣንና የኃላፊነት ስሜት ሲጋጩና ነፍስን ሲገነጥሉ ‹‹በቃኝ!›› ብለው የመንፈስ ልዕልናቸውን መርጠው ሥልጣናቸውን ያስረከቡት ጸሐፌ ትእዛዝ አክሊሉ ኃብተ ወልድ ናቸው፤ አጼ ኃይለ ሥላሴ ፊት ቀርበው፣ የማይደፈረውን ደፍረው፣ አሻፈረኝ! የማይባለውን አሻፈረኝ! ብለው ሥልጣን የሌለበትን የአገር ኃላፊነት በአጼ ኃይለ ሥላሴ እግር ስር አስቀምጠው ራሳቸውን ነጻ አወጡ! ትልቅ ድፍረት ነው፤ እንኳን በአገር ደረጃ ጠቅላይ ሚኒስትርን የሚያህል ሹመትና በትንሹ በአውራጃ አስተዳደሪ ደረጃም ቢሆን የጃንሆይን ትእዛዝ አልቀበልም ማለት ዋጋ ያስከፍላል፤ (እኔ በትንሹ ከፍያለሁ!)
ጸሐፌ ትእዛዝ አክሊሉ ለአገራቸው ብዙ የደከሙ ሰው ናቸው፤ በታወቀው በፈረንሳዩ ሶርቦን ዩኒቨርሲቲ ተኮትኩተው ያደጉና በኢጣልያ ወረራ ጊዜ በአውሮፓ እየተዘዋወሩ ለኢትዮጵያ ነጻነት የታገሉ ሰው ናቸው፤ ከጦርነቱም በኋላ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆነው የተባበሩት መንግሥታት የአውሮፓውያን (የነጮች)ኃይል አክሊሉ በልበ-ሙሉነት ከምዕራባውያን ኃይሎች የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ጋር በክርክር ሲተናነቁ ነበር፤ የምዕራባውያን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ጸሐፌ ትእዛዝን በጥቁርነታቸው ሊንቁ ሲቃጡ በአእምሮና በመንፈስ ልዕልናቸው እያሳፈሩ ልካቸውን አሳይተዋቸዋል፤ ነጮቹ በግዳቸው እንዲያከብሯቸው አደረጉ፤ እኝህ ሰው ናቸው በባህል ተጽእኖና በይሉኝታ ሥልጣን የሌለበትን ኃላፊነት ተቀብለውና ተሸክመው ለብዙ ዓመታት በጨዋ ደንብ የታገሉት፤ በመጨረሻም በቃኝ! አብዮታዊ እርምጃ ወሰዱና ለአጼ ኃይለ ሥላሴ ገበጣ መጫወቻ አልሆንም ሲሉ የኢትዮጵያ ታሪክ አዲስ አቅጣጫን ያዘ፡፡
የዛሬው ጠቅላይ ሚኒስትር ከመጽሐፍ ቅዱስ ካልተማረ ከጸሐፌ ትእዛዝ አክሊሉ ሀብተ ወልድ ሊማር ይችላል፤ በመማርም ኢትዮጵያንና የኢትዮጵያን ሕዝብ ከአደጋ ሊያድን ይችል ይሆናል፤ አንድ ሰው ታሪክን ለመሥራት ይችላል፤ እግዚአብሔር መንፈሳዊ ወኔውን ይስጠው!
http://wp.me/p5L3EG-dL
Keine Kommentare:
Kommentar veröffentlichen