“የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እርምጃ አፈፃፀም መመሪያ” VS ሕዝባዊ አሻጥርና ሕዝባዊ እምቢተኝነት
“በይፋ አለመታወጁ ነው እንጂ ድሮም አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ውስጥ ነው የነበረነው” በሚል እሳቤ ስለዚህ ጉዳይ ምንም የመፃፍ ፍላጎት አልነበረኝም። ማታ “የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እርምጃ አፈፃፀም መመሪያ” ስሰማ ግን መሳሳቴን አወቅሁ። በዚህ ላይ ካልተፃፈ በምን ይፃፋል???
ስለዚህ መመሪያ ያለህን አስተያየት በአንድ ዓረፍተ ነገር ግለጽ ብባል እንዲህ እላለሁ።
“የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እርምጃ አፈፃፀም መመሪያ” ስለሕዝባዊ አሻጥር እና ሕዝባዊ እምቢተኝነት ውጤታማነት የተሰጠ የምስክርነት ቃል ነው።
ወደፊት የምመለስበት ሆኖ አሁን ትንሽ ዘና እንበልበት።
1. የኢትዮጵያ ከተሞች ከገጠር የሚለያቸው ዋና ባህሪ የቤቶቻቸው ጣራዎች ቆርቆሮ መሆኑ ነው። “ከዋና ዋና መንገዶች በግራና በቀኝ 25 ኪሜ ርቀት” እያሉ ለመለካት የሚያስቸግር ነገር ከሚያስቀምጡ “የቆርቆሮ ቤቶች ባሉባቸው ቦታዎች ሁሉ“ ቢባል ይሻል ነበር።
2. መመሪያውን እንደወረደ ለሚተረጉመው ሰው የሚገባው ነገር የሚከተለው ነው - “የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በሚፀናበት ቦታ መኖር ክልክል ነው”። በህገመንግሥታቸው “ኢትዮጵያዊያን የመኖር መብት አላቸው” የሚል አንቀጽ እንዳለ አስታውሳለሁ። ይህ መመሪያ የከለከተለው እሱን ነው፤ ኢትዮጵያዊያን በኢትዮጵያ የመኖር መብት የላቸውም እያለን ነው።
3. መመሪያውን እንደወረደ ሳይሆን በጥንቃቄ ለሚያጠና ሰው ግን በርካታ ጠቃሚ ነገሮችን ያገኛል፤ ትኩረቴ ሁለት ነጥቦች ላይ ነው።
3.1. መመሪያው ሕዝባዊ እምቢተኝነት ምን ላይ ማትኮር እንዳለበት ፍንጭ ሰጥቷል። ለምላሴ፣ ሁከት ማስነሳት፤ ዘረፋ መፈፀም፤ ንብረት ማውደም ከልክሏል (እነዚህ የተፈቀዱበት አገር ስለመኖሩ እኔ አላውቅም)። የሕዝባዊ እምቢተኝነት ትርጉም አድርጉ የተባሉትን አለማድረግ፤ አታድርጉ የተባሉትን ማድረግ በመሆኑ ምን ምን ላይ ማትኮር እንዳለብን ጥቆማ ሰጥቶናል። መንገዶች፣ የአገዛዙ ተቋማት ንብረቶች፣ ተሽከርካሪዎች የሕዝባዊ እምቢተኝነት ዒላማዎች የነበሩ መሆናቸው ትክክል መሆኑ መመሪያው አረጋግጦልናል፤ ይህንኑ አጠናክሮ መቀጠል ነው።
3.2. መመሪያው ስለሕዝባዊ አሻጥር ውጤታማነት የተሰጠ መረጃ አድርገን ልንወስደው እንችላለን። “ሥራ መበደል ክልክል ነው” (በነገራችን ላይ ሥራ መበደል አለመበደሉን ማረጋገጥ ራሱ ትልቅ ሥራ ነው)፤ ሥራን ማስተጓጎል፤ አገልግሎት አለመስጠት፤ የስፓርት ሜዳዎችን ለተቃውሞ አለመጠቀም .... እያለ እኛ አገር ውጤታማ የሚሆኑ የሕዝባዊ አሻጥር ዓይነቶችን ይዘረዝራል። መመሪያው የሕዝባዊ አሻጥር ዋና ዋና ማዕከላትንም ይዘረዝራል፤ ለምሳሌ የትምህርት ተቋማት፣ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶችም፣ የአገልግሎት መስጫ ተቋማት። ባጭሩ ይህ መመሪያ ስለሕዝባዊ አሻጥር የተፃፉ ጽሁፎችን እንድናነብ፤ እኛም ለሀገራችን በሚስማማ መንገድ እንድንጽፍ እና ተግባራዊ እንድናደርጋቸው ይማፀናል።
http://wp.me/p5L3EG-dU
Keine Kommentare:
Kommentar veröffentlichen