ጎሠኛነት በባዶ ሜዳ
መስፍን ወልደ ማርያም
ኅዳር 2009
በተለያዩ የኢትዮጵያ አንገብጋቢ ጉዳዮች ላይ ሁሉ የሚደረገው ውይይትና ክርክር እንደተጠናቀቀ ተቆትሮ የአማራና የኦሮሞ ጎሠኛነት ትልቁ አንገብጋቢ ጉዳይ እየሆነ ነው፤ (ስለኢትዮጵያ ለማያውቅ ሰው በኢትዮጵያ ውስጥ ከጠሩና ከጸዱ አማራና ኦሮሞዎች በቀር በአገሪቱ ውስጥ ሌላ ሰው ያለ አይመስልም!) ጎሠኛነት ጉዳያችን ያልሆነው ኢትዮጵያውያን የዳር ተመልካች መሆኑ እየሰለቸን ነው፤ ምንም እንኳን አማራና ኦሮሞ የተባሎት ጎሣዎች በብዛት ከሁሉም ቢበልጡም ከሰማንያ በላይ የሚሆኑ ጎሣዎች እንደሌሉና በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ቃል እንደሌላቸው ተደርጎ የሚጎነጎነው የሚስዮናውያንና የስለላ ድርጅቶች ታሪክ ለኢትዮጵያውያን ባዕድ ነው፡፡
ሌላው የሚያስደንቀውና ዓይን ያወጣው ነገር እነዚህ ኢትዮጵያን በጠዋቱ ለመቃረጥ እየተነታረኩ ያሉ በአማራና በኦሮሞ ጎሣዎች ስም መድረኩን የያዙት ሰዎች በውጭ አገር የሚኖሩ፣ እነሱ ሌሎች መንግሥታትን የሙጢኝ ብለው ከወላጆቻቸው ባህልና ታሪክ ጋር ማንም ዓይነት ግንኙነት የሌላቸው፣ ልጆቻቸውም ከኢትዮጵያ ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት የሌላቸው የውጭ አገር ሰዎች ናቸው፤ የሚናገሩትና የሚሰብኩት ግን በኢትዮጵያ ውስጥ ላለነው፣ አገራችን ያፈራችውን ግፍና መከራ እየተቀበልን ለምንኖረው የነሱ ንትርክ፣ ውይይትና ክርክር ትርጉም የለውም፤ እዚያው በያገራቸው እየተነታረኩ ዕድሜያቸውን ጨርሰው መቀበሪያ ይፈልጉ፤ ሲመች ኢትዮጵያውያን ናቸው፤ ሳይመች የሌሎች አገሮች ዜጎች ናቸው፤ ሲመች የአንዱ ጎሣ አባል ናቸው፣ ሳይመች ሌላ ናቸው፤ እነሱ በምጽዋት እየኖሩ እዚህ በአገሩ ጦሙን እያደረ ስቃዩን የሚበላውን በጎሠኛነት መርዝ ናላውን ሊያዞሩት ይጥራሉ፡፡
የኢትዮጵያን ሕዝብ በጎሣ ለያይተው የሞተ ታሪክ እያስነሡ ከአሥራ አምስት ሺህና ከሃያ ሺህ ኪሎ ሜትር ርቀት አዛኝ ቅቤ አንጓች እየሆኑ ተነሥ-አለንልህ! እያሉ በአጉል ቀረርቶ ጉሮሮአቸው እስቲነቃ የሚጮሁ ሰዎች ቆም ብለው ቢያስቡ እኛና እነሱ ያለንበትን የአካል ርቀት ብቻ ሳይሆን በአስተሳሰበም በመንፈስም እጅግ መራራቃችንን በመገንዘብ አደብ መግዛት ይችሉ ነበሩ፤ የሥልጣን ጥም ያቅበዘበዛቸው ሰዎች የሚያስነሡት አቧራ በኢትዮጵያ የዘለቄታ መሠረታዊ ጉዳዮች ለመነጋገር እንዳይችሉ፣ እንዳይደማመጡና እንዳይተያዩ እያደረገ ነው፡፡
አገር-ቤት ያለነውን አላዋቂ ሞኞች ለማሳመን ስደተኞች በየቀኑ አዳዲስ ነገሮችን እያለሙ ያድራሉ፤ እኛ የምንኖረውን እንንገራችሁ ይሉናል፤ እኛ የምናስበውን እንምራችሁ ይሉናል፤ እኛ የሚሰማንን እንግለጽላችሁ ይሉናል፤ በአጭሩ እኛን የእነሱ አሻንጉሊቶች አድርገውናል፤ የእኛን መታፈን ከእነሱ ስድነት ጋር እያወዳደሩ፣ የእኛን የኑሮ ደሀነት ከእነሱ ምቾት ጋር እያስተያዩ፣ የእነሱን ቀረርቶ ከእኛ ዋይታ ጋር እያመዛዘኑ ያላግጡብናል፤ ይመጻደቁብናል፤ በስደት ቅዠት ያገኙትን ማንነት በእኛ ላይ ሊጭኑ ይዳዳቸዋል፡፡
ወላጆቹም እሱም የተወለደበትን አገር ትቶ በሰው አገር ስደተኛ የሆነ፣ የራሱን አገር መንግሥት መመሥረት አቀቶት የሌላ አገር መንግሥትን የሙጢኝ ያለ፣ ማንነቱን ለምቾትና ለሆዱ የለወጠ፣ የተወለደበትንና ያደገበትን ሃይማኖት በብስኩትና በሻይ የቀየረ፣ተጨንቆና ተጠቦ በማሰብ ከውስጡ ከራሱ ምንም ሳይወጣው ሌሎች ያሸከሙትን ጭነት ብቻ እያሳየ ተምሬለሁ የሚል፣ የመድረሻ-ቢስነቱ እውነት የፈጠረበትን የመንፈስ ክሳት በጭነቱ ለማድለብ በከንቱ የሚጥርና የሚሻክራን ስደት ለማለስለስ በሚያዳልጥ መንገድ ላይ መገላበጡ አያስደንቅም፤ እያዳለጠው ሲንከባለል የተነሣበትን ሲረሳና ታሪኩን ሲስት ሌሎች እሱ የካዳቸው ወንድሞቹና እኅቶቹ ከፊቱ በኩራት ቆመው የገባህበት ማጥ ውስጥ አንገባም ይሉታል፡፡
የአሊን፣ የጎበናን፣ የባልቻን፣ የሀብተ ጊዮርጊስን፣… ወገንነት ክዶና ንቆ ራቁቱን የቆመ፣ እንደእንስሳት ትውልድ ከዜሮ ለመጀመር በደመ-ነፍስ የሚንቀሳቀስ! ድንቁርናን እውቀት እያስመሰለ ሞኞችን የሚያታልል፣ ወዳጅ-ዘመድን ከጠላት ለመለየት የሚያስችለውን የተፈጥሮ ችሎታ የተነፈገ፣ አባቱን ሲወድ እናቱን የሚጠላ፣ እናቱን ሲወድ አባቱን የሚጠላ፣ ከወንድሙና ከእኅቱ ጋር የማይዛመድ ባሕር ላይ እንደወደቀ ቅጠል የነፋስ መጫወቻ ሆኖ የሚያሳዝን የማይታዘንለት ፍጡር፣ በጥገኛነት የገባበትን ማኅበረሰብ ማሰልቸቱ የማይገባው የኋሊት እየገሰገሰ ከፊት ቀድሞ ለመገኘት የሚመን የምኞት እስረኛ ነው፡፡
አሜሪካ፣ አውሮፓ፣ አውስትራልያ በጥገኛነት ታዝሎ፣ ከኢትዮጵያ ተገንጥሎ ከኢትዮጵያ ስለመገንጠል ይለፈልፋል! ተገንጥሎ የወጣ ከምን ይገነጠላል? ልዩ የነጻነት ታሪክ ባስተላለፉለት አባቶቹና እናቶቹ እየኮራ፣ በጎደለው እያፈረ፣ የአምባ-ገነኖችን ዱላ እየተቋቋመ በአገሩ ህልውና የወደፊት ተስፋውን እየወደቀና እየተነሣ የሚገነባው ኢትዮጵያዊ በፍርፋሪ የጠገቡ ጥገኞችን የሰለለ ጥሪ አዳምጦ የአባቶቹን ቤት አያፈርስም፤ አሳዳሪዎች ሲያኮርፉና ፍርፋሪው ሲቀንስ፣ ጊዜ ሲከፋና ጥቃት ሲደራረብ የወገን ድምጽ ይናፍቃል፤ ኩራት ራት የሚሆንበት ዘመን ይናፍቃል፡፡
Keine Kommentare:
Kommentar veröffentlichen