“አለባብሰው ቢያርሱ በአረም ይመለሱ”
ሜጀር ጄኔራል አበበ ተ/ሃይማኖት፣ በኔ ግምት አገራችን የገባችበትን ማጥ በጥሩ ሁኔታ የተነተነ ጽሁፍ አቅርበዋል። የጽሁፉ አጠቃላይ ይዘት መደምደሚያ ላይ በቀረቡት የሚከተሉት ዓረፍተ ነገሮች ማጠቃለል ይቻላል።
“አገራችን የገጠማት ችግር ተራ ፖለቲካዊ ቀውስ ሳይሆን፣ እንደ አገር ቆሞ የመቀጠልን ሥጋት የጋረጠ ከፍተኛ የደኅንነት አደጋ [ነው] .... መወያያትና መነጋገር ያለብን ከሕገ መንግሥቱ በታች የፖሊሲዎች ቁንጮ በሆነው የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይና የብሔራዊ ደኅንነት ፖሊሲ ዙርያ ነው። ... የደኅንነታችን ዋና የሥጋትም የኩራትም ምንጭ ውስጣዊ የዴሞክራሲና የልማት ሁኔታ መሆኑ በመገንዘብ፣ የችግሩን ሥረ መሠረት ትቶ አጫፋሪ በሆኑ ትምክህት፣ ጥበት፣ አክራሪነት በሚባሉ ቅርንጫፎች ላይ ተንጠላጥሎ የሚመጣ ለውጥ ሊኖር እንደማይችል መረዳት [አለብን]።”
ሜጀር ጄኔራል አበበ ተ/ሃይማኖት አገዛዙ አገራችንን ወዴት እየመራት እንደሆነ በትክክል ያብራሩ በመሆኑ ሊመሰገኑ ይገባል። ይሁን እንጂ ችግሩን በተገነዘቡበት ጥልቀት ልክ ለመፍትሄ ሲተጉ አልታየኝም። ለመዋቅራዊ ችግር መዋቅራዊ መፍትሄ የሚያስፈልገው መሆኑ ተቀብለው እያለ “ይህን መዋቅራዊ መፍትሄ የሚያመጣው ማነው? እንዴት ነው?” የሚሉትን ቁልፍ ጥያቄዎች አድበስብሰው አልፈዋቸዋል። እሳቸው መፍትሄ ብለው ያቀረቡት ሃሳብ ሲጨመቅ የሚከተለው ነው “እያጠናሁት ነው የሚለው የፖሊሲ ክለሳም ሆነ ጥልቅ ተሃድሶ ... የፖለቲካዊ ፓርቲዎች፣ የሲቪልና የሙያ ማኅበራት፣ የክልል ምክር ቤቶች፣ ወዘተ. ተሳትፎና የተለያዩ አስተያየቶች ተጨምሮበት መሆን ይገባዋል።”
ሜ/ጄኔራል አበበ ተ/ሃይማኖት የሚከተሉት ጥያቄዎችን እንዲያጤኑልኝ እጠይቃለሁ።
1. እምነትዎ ”እያጠናሁት ነው” በሚለው አካል ነው። የችግሩ ፈጣሪ የመትሄው አምጭ ይሆናል ብለው እንዴት ሊያምኑ ቻሉ?
2. “የፓለቲካ ፓርቲዎች” ሲሉ እነማንን ነው? በነፃነት የሚንቀሳቀሱ የፓለቲካ ፓርቲዎች አሉ ወይ?
3. “የሲቢክና የሙያ ማኅበራት” ሲሉስ እነማንን ነው? በኢትዮጵያ ውስጥ የሲቢክ ማኅበራት አሉ ወይ? በኢትዮጵያ ነፃ የሙያ ማኅበራት አሉ?
4. የክልል ምክር ቤቶችስ ያው “እያጠናሁት ነው” የሚሉ ሸንጎዎች አይደሉምን?
5. የችግሩ ጥልቀት ስር ነቀል የፓለቲካ ሥርዓት ለውጥ የሚሻ መሆኑ ትንተናዎ ፍንትው አድርጎ ያሳያል። እርሶ መፍትሄ ይሆናል ብለው ተስፋ ያደረጉት ”የብሔራዊ ደህንነት ፓሊሲና የአመራሩ መግባባት” ውጤት የሆነ “የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይና የብሔራዊ ደኅንነት ፖሊሲ“ ነው። ለእርስዎ ቁልፍ መፍትሄ የሆነው ይህ ፓሊሲ እንዴት በክለሳና በተሃድሶ ይመጣል? ይህንን ትልቅ ተቃርኖ እንዴት ዘለሉት?
6. እርስዎ በመፍትሄነት ያቀረቡት ፓሊሲ የፓለቲካ ሥርዓት ለውጥ ይሻል። የራስዎ ትንተና ወደሚመራን መፍትሄ ከመሄድ ማፍግፈግን ለምን መረጡ? “አለባብሰው ቢያርሱ በአረም ይመለሱ” አይሆንም ወይ?
http://www.zehabesha.com/amharic/?p=75797
Keine Kommentare:
Kommentar veröffentlichen