OPPOSITION PARTIES
Sonntag, 21. Oktober 2018
21/10/2018 አላማጣ በአላማጣ እየተካሄደ ባለው የራያ ህዝብ ተቃውሞ በትግራይ ልዩ ኀይል 4 ሰዎች ተገደሉ
በአላማጣ እየተካሄደ ባለው የራያ ህዝብ ተቃውሞ እስካሁን 4 ሰዎች በትግራይ ልዩ ሃይል አባላት መገደላቸውን እንዲሁም ከ15 በላይ ሰዎች ደግሞ ቆስለው ሆስፒታል መግባታቸውን ከስፍራው ያነጋገርናቸው ሰዎች ተናግረዋል። ተቃውሞው እንደቀጠለ ነው። ፊልሙ ከስፍራው የሚገኙ ተወላጆች የላኩልን ነው።
Samstag, 20. Oktober 2018
የለውጥ ሀይሉ እውነተኛ ከሆኑ ስራቸውን ይስሩ እኛም ስራችን እንስራ:: ማገዝ የሚለውን ቃል አልወደውም ::(በ ርዕዮት አለሙ)
የለውጥ ሀይሉ እውነተኛ ከሆኑ ስራቸውን ይስሩ እኛም ስራችን እንስራ:: ማገዝ የሚለውን ቃል አልወደውም :: ምንድን ነው ማገዝ ማለት ለመሆኑ ? እኔ እኮ ኢትዮጵያ ሀግሬን ዲሞክራሲያዊ ለማድረግ ድሮ ያኔ ለትግል ስነሳ ዶር አብይ የሚባል ሰው ከነመፈጠሩም አላውቅም ::
የ ትግሌ አላማ እና ግብ ዶር አብይን ለማገዝ አይደለም አይሆንምም... አላማየ ኢትዮጵያ ሀግሬን ዲሞክራሲት የማድረግ ትልቅ ራዕይ ነው:: እኔ ይህ አላማየ እስኪሳካ ትግሌን እቀጥላለሁ:: በዚህ የ ትግል ጎዳና ላይ እያለሁ ዶር አብይ የሚባል ሰው ከ ኢህአዴግ ወጥቶ አይ እየሄድንበት ያለው መንገድ ልክ አይደለም ብሎ ኢትዮጵያን ለመቀየር ከተነሳ እሽ ጥሩ ...ይህ ከሆነ ትክክለኛ ስሜቱ ደግ ነው:: እኔም ትግሌን እቀጥላለሁ መንገድ ላይ እንገናኛለን:: ነገር ግን እየሆነ ያለው ነገር ይህን አያሳይም::
በ ግልፅ በ አደባባይ ሀገራችን ውስጥ እየተካሄደ ያለው ሀቅ ግን ተስፋ ሰጭ አይደለም ...እንደተባለለትም ወደ ዲሞክራሲ እየሄድን አይደለም...አንድ አንዶች ይህን ጥሬ ሀቅ እያዩ ዶር አብይን ከማገዝ ውጭ ምን ምርጫ አለ ለምትሉ መልሴ ምርጫ ካሳጡ በሗላ ምን ምርጫ አለ ይባላል እንዴ ? እየሆነው ያለው እኮ ምርጫ የማሳጣት ነገር ነው::
ለምሳሌ አሁን የተፈጠረውን ችግር ከስሩ እንመልከተው:: የ አዲስ አበባ ወጥቶች ለምን ለመደራጀት ተነሱ ብሎ መጠየቅ ደግ ነው? ሆሮሞሳ ፊንፊኔ በሚል ስም የተደራጁ ወይም እንዲደራጅ ያደረጉ ሰወች እኮ በ አደባባይ የ ጥላቻ ንግግር ሲያደርጉ የነበሩ ናቸው ይህም ይታወቃል:: እነዚህ ሰወች ተሰብስበው ምን ነበር ሲያወሩት የነበረ ? የ ሚያቃቅር የሚያጣላ የምያጋጭ አይደለም ን? እነዚህ ሰወች ተደራጅተው የፍለጉትን እንዲናገሩ እየተደረገ ነው :: እንዲህም እንዲያደርጉ ተፈቅዶላቸዋል::
በሌላ በኩል ይህን አደጋ የተገነዘቡ የ አዲስ አበባ ወጣቶች የ አዲስ አበባን ወጣት ለማደራጀት ሲሞክሩ አንጠልጥለው እስር ቤት ወረወሯቸው:: እነዚህ ወጥቶች ሄኖክ እና ማይክ ወንጀላቸው ምንድን ነው ? ወንጀላቸው መደራጀት ነው ተባለ ...
ይህ ግልፅ መድሎ ነው ! ለ አንዱ መፍቀድ ሌላውን መከልከል ብቻ እንኳ አይደለም ልትደራጅ ነው ብሎ ማሰር ! እዚህ ውስጥ የ ዶር አብይ እጅ የለበትም ብሎ ነገር አይጥመኝም... ጥሩ ጥሩውን ለ ዶር አብይ እንዲህ አይነት ግፍ እና በደሉን ለ ለውጥ ቀልባሾች መስጠት ትክክል አይደለም::
ሲጀመር የለውጥ ሀይሉ የ ለማ ቲም የሚባለው ቁጥራቸው ስንት ነው እነማን ናቸው የሚባለው ነገር ግልፅ አይደለም::
ሌላው የሚገርመው ነገር የ ቤተመንግስቱ የ ወታደሮች ሁኔታ ነው:: በ እለቱ ዶር አብይ ወጥተው ከ ደሞዝ ጋ የተያያዘ ነው አሉን ከዛም ከዚህ በተቃራኒ መረጃ አለን ያሉትን ሰወች ውሸታማሞች አስባሉ::
አሁን ወጥተው አይ ያን ጊዜ የነገርኳችሁ እውነት አይደለም ሌሎች ያሉት የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ ትክክል ነበረ አሉን :: እንግዲህ ከሁለቱ የቱን እንመን ሲባል ያንም ይህንም እመኑኝ የሚሉት ነገር ነው:: እኔ ያ ነው ይህ ነው የሚል ክርክር ውስጥ አልገባም ነገር ግን ሁለቱንም እመኑኝ የሚሉት ነገር ትክክል አይደለም:: ስለ ሰበታ ለጋጠፎ እና ቡራዮ የተናገሩት ነገር የሚገርም ነው ! እውነት እየመጡ ነበር የሚለው ነገር እንዳለ ሁኖ ለማስተላለፍ የፈለጉት ነገር ምንድን ነው ብሎ መጠየቅ ግድ ይላል :: እኔ የሚታየኝ ድራማ ነው ለምን እንዲህ አይነት ድራማ ለመስራት ተፈለገ::
ማሳስቢያ::
ይህን ፅሁፍ የ ፃፍኩት ርዕዮት አለሙ በ ኢሳት እለታዊ ያደርገችውን ውይይት ተመርክዤ ቢሆንም ንግግሩን ወደ ፅሁፍ ሲገለብጥ ትንሽ ማጣፈጫ ተጠቅሚያለሁ::
CC Eskedar Alemu Gobebo
Donnerstag, 18. Oktober 2018
ጊዜው የእኛ ነው በሚሉ የብሄር አቀንቃኞች ዜማ መደነስን መርጠዋል። ( ጋዜጠኛ መሳይ መኮንን)
አቶ ታዬ በዚሁ መቀጠል የሚገባቸው አይመስለኝም። ስሜታቸውን መቆጣጠር ካቃታቸው፡ ነጻ ግለሰብ ሆነው እንደፈለጋቸው ሀሳባቸውን የሚያስተላልፉበትን፡ አቋማቸውን የሚያንጸባርቁበትን፡ ወገኔ ለሚሉት አካል የሚቆሙለትን ሌላ መንገድና ቦታ ቢፈልጉ ለእሳቸውም፡ ለጤናቸውም፡ ለድርጅታቸውም፡ ለመንግስታቸውም የሚበጅ ይሆናል። ከተቀመጡበት ወንበር እኩልነትን እንጠብቃለን። ከጨበጡት ሃላፊነት ሚዛናዊ ፍርድ እንሻለን። ተራ ብሽሽቅ ውስጥ ተነክረው፡ የቃላት ጦርነት ላይ መጠመዳቸውን ያቁሙት። ቢያንስ ለወንበራቸው ክብር ዘብ ይሁኑ።
አንድ ተጨማሪ ወንድማዊ ምክር። እንዲህ እልህ ሲተናንቅዎት ከፌስ ቡክ አከባቢ ይራቁ። ሰውነትዎን ላላ አድርገው፡ ቀዝቃዛ ውሃ ፈልገው ትንሽ ጎንጨት ይበሉ። እርስዎ ዘንድ ያለው አይበገሬነት ሌላውም ጋር መኖሩን እንደማይዘነጉ ተስፋ አደርጋለሁ። የጊዜ እንጂ የሰው ጀግና የለም። ጊዜው የእኛ ነው የሚለው ጋርዮሻዊ አስተሳሰብ ብዙ ርቀት አይወስድም። የህወሀት ባለሟሎች የትዕቢት ተራራ እንዴት እንደተናደ ከእርስዎ የተሰወረ አይመስለኝም። ትዕቢት የሰነፎች ጊዜያዊ ጉልበት ነው።
ቤተመንግስት የሚገኘው የለውጥ ሃይል በከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት ደረጃ የሚተላለፉ መልዕክቶች ላይ ጥብቅ ቁጥጥር ያደርግ ዘንድ ይጠበቃል። ዜጎችን በእኩል አይን መመልከት የሚገባቸው የመንግስት ሃላፊዎች ደምና አጥንት እየቆጠሩ ፍርድ የሚሰጡ ከሆነ ውጤቱ ለሁላችንም አይበጅም። የህወሀት መሪዎችም እኮ ኢትዮጵያውያን ናቸው። ያወገዝናቸው፡ የታገልናቸው፡ እኩል ስለማያዩን ነበር። ውድቀታቸውን በጸሎትና በእልህ አስጨራሽ ትግል እንዲመጣ የናፈቅነው እኮ የበላይና የበታች መሆንን ተጠይፈን፡ አንገሽግሾን ነው።
ስሜታቸውን በማይቆጣጠሩ፡ ከሀሳብ ይልቅ ዘርና ብሄር እየጠሩ የሚሰብኩ፡ የሚፈርዱ መሪዎችን አደብ ማስገዛት የመንግስት ሃላፊነት ነው።
Dienstag, 25. September 2018
“የአዲስ አበባ ፓሊስ” ለሉአላዊ ባለቤቱ ይመለስ! ከኤርሚያስ ለገሰ
“የአዲስ አበባ ፓሊስ” ለሉአላዊ ባለቤቱ ይመለስ!
ከኤርሚያስ ለገሰ
የአዲስ አበባ ፓሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ሜጄር ጄኔራል ደግፌ በዲ በወቅታው የመዲናይቱ የፀጥታ ጉዳይ ላይ የሰጡትን መግለጫ ሰማሁት። ኮሚሽነሩን በተሰጣቸው ሃላፊነት እና ስልጣን የማክበር የዜግነት ግዴታ አለብኝ።እንደ አንድ ዜጋ እና ድምፅ አልባ ለሆነው አዲስአበቤ( በአዲስ አበባ በፍላጐቱ የሚኖር) እንደሚቆረቆር ሰው ደግሞ ቅሬታዮን የማቅረብ መብት አለኝ።
በመግለጫው ጄኔራሉ ላለፉት 27 አመታት የሰማነውን የመነቸከ አካሄድ እንደ ምርጥ ተሞክሮ በመውሰድ የህግ የበላይነት ሳይሆን የሕጉ የበላይ መስለው ታይተዋል። ሰውየውን ያለ ዛሬ አይቼአቸው ባላውቅም ከአንደበታቸው የሚወጣው አምባገነናዊ አቋምና እብሪት በተራዘመ ሂደት ስርአቱን ወደ አደገኛ ሁኔታ ሊወስደው ይችላል። በተለይም ጄኔራሉ እንደ ዛሬው በአክራሪዎቹ ተጠልፈው አይጥ በበላው ዳዋ እየፈለጉ የሚገድልና የሚያስሩ ከሆነ ለለውጥ ሀይሉ ከባድ ሸክምና እዳ መሆናቸው አይቀርም።
እዚህ ላይ የለውጡ መሪ ለሆነው ዶክተር አቢይ አንድ በጥሞና ማየት አለበት ብዮ የማስበውን ቁምነገር ላስገባ። የመጣጥፉም መዳረሻ ይሄ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ ጠንቅቆ እንደሚያውቀው ከምርጫ 97 በኃላ ከአዲስ አበባ ፓሊስ ጋር በተያያዘ አቶ መለስ ሶስት ትላልቅ አምባገነናዊ እርምጃዎች ወስደዋል። በቅርበት ለማየት እንደሚቻለው እነዚህ ሠይጣናዊ እርምጃዎች መዲናይቱን ከፍተኛ ዋጋ አስከፍለዋታል። በዚህ ምክንያት የተፈጠረው ችግር ፓለቲካዊ እና መዋቅራዊ በመሆኑ መፍትሔውም ፓለቲካዊ መሆኑ አይቀርም።
#የመጀመሪያው የአዲስ አበባና የአዲስ አበቤን ሉአላዊነት (በራሳቸው ህገ መንግስት አንቀፅ 49 የተጠቀሰውን) በመናድ የመዲናይቱን ፓሊስ ኮሚሽን ተጠሪነት ለፌዴራል መንግስት አድርገዋል። በሌላ አነጋገር አዲስ አበባም ሆነ የህዝቡ ሉአላዊነት መገለጫ ተደርጐ የሚወሰደው “የከተማው ምክርቤት” የአዲስ አበባን ፓሊስ የማዘዝ መብት የለውም። በዳቦ ስም “የአዲስ አበባ ፓሊስ” ይባል እንጂ በግብር፣ በተጠሪነት እና ተጠያቂነት አዲስአበቤ አይደለም። እዚህ ላይ ሌላም አስገራሚ ነገር ልጨምር። ለነገሩ አስገራሚ ከምለው አስቂኝ ብለው እመርጣለሁ። ነብሷን ይማረው እና ወላጅ እናቴ ከአቅሟ በላይ የሆነ ነገር ሲያጋጥማት “ ወደው አይስቁ!” ትለን ነበር። ወደው አይስቁ! እናም አስቂኙ ነገር አዲስአበቤ ባለቤት ላልሆነበት፣ ተጠሪው ላልሆነ፣ ለማይጠይቀው “ የአዲስ አበባ ፓሊስ” በጀት ይመድባል። የሉአላዊነቱ አካል ያልሆነውን ፓሊስ ይቀልባል።
ውድ ጠቅላይ ሚኒስትር! መቼም የአለም ሶስተኛ የዲፕሎማሲ ከተማ፣ የአፍሪካ መዲና፣ የኢትዮጵያውያን ዋና መናገሻ የምታዘው ፣ ተጠያቂ የምታደርገው ፓሊስ የላትም ብሎ እንደ መናገር የሚያሳፍር የለም። እርግጠኛ ሆኖ መናገር ባይቻልም እርሶም በሟቹ ጠቅላይ ሚኒስትር የፓለቲካ ቧልትና ጠላታዊ እርምጃ የሚሸማቀቁ ይመስለኛል።
በእርሶ የስልጣን ዘመን ይህን ውንብድና በማስተካከል በቀድሞው ስርአት ፓለቲካ ቁስለኛና ሰለባ የሆነውን አዲስአበቤ ከይቅርታ ጋር እንደሚክሱት ሙሉ እምነት አለኝ። በአዲስ አበባ ፓሊስና አዲስአበቤ መካከል የተጋረደውን መጋረጃ ቀዳደው ለመጪው በነፃና ዲሞክራሲያዊ ምርጫ ለሚመጣው የአዲስ አበባ መንግስት እንደሚያስረክቡ ጥርጥር የለኝም።
#ሁለተኛው የአቶ መለስ የውስጥ መመሪያ የፓሊስ ምልመላና ስልጠናን የተመለከተ ነው። ከምርጫ 97 ጀምሮ ለነበሩት ሶስት አመታት የአዲስ አበባ ፓሊስ ለመሆን በሚደረገው ምልመላ ለአዲስአበቤ የሚሰጠው ኮታ 10 በመቶ በታች ነበር። በሂደትም ከሃምሳ በመቶ የሚበልጥ አይደለም። የተቀረው ግማሹ በኮታ ከሌሎች አካባቢዎች ተመልምሎ የሚመጣ ነው።ከኦሮሚያ፣ አማራና ትግራይ…ወዘተ። ከሌላ አካባቢ የሚመጡት ፓሊሶች ደግሞ ከከተሜው ባህሪ ጋር መላመድ ስለሚያቅታቸው ነዋሪው እንደሚንቃቸው ስለሚያስቡ በበታችነት ስሜት ይሰቃያሉ። በተበቃይነት ስሜት መንፈሳቸው ይረበሻል። ፈሪና ድንጉጥ ፍጡር ይሆናሉ። ፈሪ ሰው ደግሞ ሁሉንም ሰው ጠላት ያደርጋል።
በፓሊሱና በከተማው ነዋሪ መካከል ያለው ግንኙነትም የፋራና አራዳ ፣ የተታላይና አታላይ፣ የከተማ ቀመስና ከተሜ፣ የሰገጤና ጩሉሌ መሆኑ አይቀርም። በዚህም ምክንያት በአዲስ አበባ ፓሊስ አባላትና አዲስአበቤ መካከል ያለው ግንኙነት ከፍተኛ የመተማመን እጦት ያለበት ሆኗል። ነዋሪው እንኳን በሲነርጂ አብሮ ሊሰራ ቀርቶ በመንደሩ ያስቸገረ ሌባን ለፓሊስ አሳልፎ መስጠት አይፈልግም። ፓሊስ በፓትሮል ለአሰሳ ሲመጣ “ ዛፓው! ሰገጤው! እየመጣላችሁ ነው ወደ ቤት ግቡ!” የምትለው የአራዶች ቃል በእናቶቻችንም ዘንድ የተለመደ ሆኗል።
የምልመላ መስፈርቱም የኢህአዴግ ሊግ አባል (60 ነጥብ)፣ የወጣት ፎረም አባል (20 ነጥብ)፣ የትምህርት ዝግጅት እና ሌሎች የጤና መመዘኛዎች (20 ነጥብ) ነበሩ። በሌላ አነጋገር አዲስአበቤ የኢህአዴግ የወጣት ሊግ ውስጥ መታቀፍ ካልፈለገ ፓሊስ የመሆን የልጅነት ህልም ቢኖረው እንኳን ፓሊስ መሆን አይችልም። በዚህ እኩይ ተግባር ሁላችንም የታሪክ ተወቃሾች ነን። የታሪክ ተወቃሽነት የሚያመጣው ድርጊቱን መፈፀም አሊያም አጋዥ መሆን ብቻ አይደለም። መጥፎው ውሳኔ እንዳይተገበር ለመከላከል ቁርጠኝነት አልፎ ሔዶም ማጋለጥ አለመቻል በዚህ ፈርጅ ይመደባል።
እናም ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ከላይ የጠቀስኩት አካሄድ እንዲሁ ቢቀጥል አዲስአበቤ ለእርሶ ያለው ድጋፍ ከተወሰነ በኃላ ምን ሊመስል እንደሚችል መገመት ይችላሉ። የመዲናይቷን ሰላም የሚያስጠብቀው ክፍል ውስጥ ባለቤቱ ከሌለበት እና ባይተዋር ሆኖ የሚቀጥል ከሆነ በሂደት እርሶንም በባላንጣነት የሚመለከትበት ሁኔታ ይፈጠራል።
በመሆኑም በእርሶ የስልጣን ዘመን ይሄን ያልተፃፈ የውስጥ መመሪያ ሙሉ በሙሉ ያስቁሙ። የኦሮሚያ ክልል ፓሊስ አባላት በኦሮሚያ የሚኖሩ ዜጐች እንተደረገ ሁሉ፣ የአማራ ክልል የፓሊስ አባላት በአማራ ክልል እንደሚመለመሉ ሁሉ…ወዘተ በአዲስ አበባ ክልልም የሚመለመሉ ፓሊሶች አዲስአበቤ( በፍላጐቱ የአዲስ አበባ ነዋሪ የሆነ) ብቻ እንዲሆኑ አድርጉ። መመዘኛውም እንደ እርሶ ሙሉ ቁመና ያለው፣ ፓሊስ ሆኖ ማገልገል ፍላጐት ያለው፣ በህብረተሰቡ ዘንድ በፀባዩ ተቀባይነት ያለው/ ያላት ያድርጉ። የፓርቲ አባልነት እንደ መመዘኛ መወሰዱ ፀያፍ እንደነበር በአደባባይ ይግለጡ።
#ሶስተኛው ከአዲስ አበባ ፓሊስ አመራር ጋር የተያያዘ ነው። አስቀድሜ እንደገለጥኩት ከምርጫ 97 በኃላ የአዲስ አበባ ፓሊስ አመራር የሚመደበው ከፌዴራል ፓሊስና መከላከያ ሰራዊት ነው። በተለይም ቁልፍ ስራ የሆነውን አዛዥነት፣ ወንጀል መከላከል እና ምርመራ መምሪያ የሚያዘው ለፓርቲው ታዛዥ የሆኑ የፌዴራል ፓሊስና የመከላከያ መኮንኖች ናቸው። ይሄ በራሱ የፈጠረው ችግር አለ።
ለቀባሪው ማርዳት እንዳይሆንብኝ እንጂ የፓሊስ አመራር ሳይንስም ጥበብም ነው። ሳይንስ በመሆኑ ፕሮፌሽናሊዝም እና ምሁራዊ ግንዛቤ ይጠይቃል። ጥበብ በመሆኑ የሰዎችን አእምሮ የሚማርኩ ስልቶችን ማወቅ ይጠይቃል። የፓሊስ አመራር ከሌሎቹ ሙያዎች በተለየ ረቀቅ ያለ ጥበብ ይጠይቃል። በእውቀት፣ በችሎታ፣ በእምነትና ሕዝብ ለሚቀበለው መርሕ መቆምን ይጠይቃል። የሕግ የበላይነትን አምኖ መቀበል ይጠይቃል።
ስለዚህ የፓሊስ አመራር መሆን ያለበት እንደ ድሮው በፓሊስ ኮሌጅ ገብቶ በከፍተኛ መኮንንነት የሰለጠነ ፕሮፌሽናል ሰው ሊሆን ይገባል። የመከላከያ ሰራዊት ጄኔራል ተመልሶ ፓሊስ ኮሌጅ ገብቶ የአራት አመት ስልጠናውን ካልወሰደ በስተቀር ወደ ፓሊስ አመራርነት መምጣት የለበትም። አሁንም ድፍረት አይሁንብኝ እና አንድ የመከላከያ ሰራዊት መኮንን ስልጠናም ሆነ የአእምሮ ኦረንቴሽኑ ወታደርተኝነት ነው። ጠላትን የማንበርከክ ጀብደኝነት እና የጦረኝነት ዝንባሌ ነው።
ነብሱን ይማረው እና አቶ መለስ ዜናዊ የአዲስ አበባ ፓሊስ አመራሮችን ከመከላከያ ሲያመጣ አዲስአበቤን እንደ ጠላት፣ አዲስ አበባን እንደ ጦርነት አውድማ ስለሚቆጥራት ነበር። የአቶ መለስ የጦረኝነት ጽንሰ ሐሳብ የሚመነጨው መዲናይቱን መቆጣጠር የሚቻለው በአብዮታዊ ዲሞክራሲ በታነፀ ወታደራዊ ኃይል ነው ከሚል እምነት ነው። በጠላትነትና በአደገኛ ቦዘኔነት የፈረጀውም አዲስአበቤ ወጣት ፀጥ ረጭ ማድረግ የሚቻለው በዚህ አይነት የጦር አመራር መሆኑን ያምናል።
ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር እርሶም በማወቅም ይሁን የቀድሞ አሰራር ትክክል መስሎት የፓሊስ አመራርን የቀየሩበት አሰራር ተመሳሳይ ነው። እርሶም ለአዲስ አበባ ፓሊስ ኮሚሽርነት የሾሙት የመከላከያ ሜጄር ጄኔራል ሆኗል። ሰውየው የፓሊስ አካዳሚ ገብተው ስልጠና መውሰዳቸውን ባላውቅም ከአነጋገር ለዛቸው ከወታደርተኝነት የተላቀቁ አይመስለኝም። ዶሮ ሶስት ጊዜ ሳትጮህ ጠርብ ጠርብ የሚያካክሉ ኩሸቶችን ሲያወሩ አንደበታቸው አልተደናቀፈም። መስከረም 4፣ መስከረም 5 የሰጡት መግለጫ መስከረም 14 ከሰጡት ጋር እርስ በራሱ ሲደባደብ ከመጤፍ አልቆጠሩትም( የእነዚህ ቀናት አስቂኝ ድራማ በሌላ ጽሁፍ እመጣበታለሁ።) ጆሮአቸውን በጥይት የደፈኑት እኝህ ጄኔራል ሰዎች ያለ ፍርድ ቤት ትእዛዝ መያዝ አይችሉም የሚለውን የህገመንግስት ቃል አንብበውት የሚያውቁም አይመስልም። በአመራር ሳይንስ ውስጥ ቅድሚ ለሚሰጥ ቅድሚያ እንስጥ በሚለው ጥበብ አጠገቡ ያለፉ አይመስልም። የጄኔራሉ አድርባይነት እና የስልጣን ብልግና ከወዲሁ ቁልጭ ብሎ ወጥቷል።
በመሆኑም እንዲህ አይነት ወታደርተኝነት ግርዶሽ የጣለባቸውን የጦር መኮንኖች ያለምንም ስልጠና ሕዝብ ውስጥ መቀላቀል ጦሱ ብዙ ነው።አዲስአበቤ በለውጡ ላይ ያሳደረው አመኔታ ይሸረሽራል። በነዋሪው አንድ “ወዴት እየሔድን ነው?” የሚል ጥያቄ ያስነሳል። በጠቅላላው አነጋገር በዚህ ዙሪያ የሚታየው ስህተት በቀላሉ የሚታረም አይደለም። የመጀመሪያው ድንጋይ ከመወርወሩ በፊት መሰረታዊ የሆነ የአመራር ስርአት ለውጥን ይጠይቃል። መሪ መለወጥም ግድ ይላል። ከእንግዲህ በኃላ አዲስአበቤዎች በቀቢጸ ተስፋ የሚኖሩ አይደሉም። እንደ ጥቁሩ አሜሪካዊ የመብት ታጋይ ማርቲን ሉተር ኪንግ ጁኒየር ህልም አላቸው። አንድ ቀን አዲስአበቤዎች በነፃና ዲሞክራሲያዊ ምርጫ ራሳቸውን ያስተዳድራሉ።
Mittwoch, 29. August 2018
አብዲ ዒሌ እስር ቤት ገብቷል። በረከት ስምዖን የውርደትን እፍታ ቀምሷል። ጌታቸው አሰፋ የሚደበቅበት ጉድጓድ ፍለጋ ላይ ተጠምዷል። (መሳይ መኮንን)
አብዲ ዒሌ እስር ቤት ገብቷል። በረከት ስምዖን የውርደትን እፍታ ቀምሷል። ጌታቸው አሰፋ የሚደበቅበት ጉድጓድ ፍለጋ ላይ ተጠምዷል።
አባይ ጸሀዬ ድምጹን አጥፍቷል። ስብሃት ነጋ በመቀሌ አክሱም ሆቴል ውስኪውን እየላፈ ቆዝሟል። በእብሪትና ትዕቢት ያበጠው የጌታቸው ረዳ ልብም ተንፍሷል። ሳሞራ የኑስ የጡረታ ዘመኑን በስጋት ይገፋል። አስመላሽ ወ/ስላሴ ግን አሁንም ይፎክራል። ሞንጆሪኖም ''የትላንቱ ይበጀናል'' ዜማ እያቀነቀነች በትካዜ ተውጣለች። ደብረጺዮን መሀል ላይ ይዋልላል። አዲስ አበባ ሲደርስ ይደመርና ወደ መቀሌ ሲመለስ ይቀነሳል።
ወደ ለውጡ ቅጥር ግቢ ለመግባት አጥር ላይ የተንጠለጠሉ አንዳንድ የህወሀት አመራሮች እንዳሉ ይሰማል። የህዝብ ማዕበል ወደ ለውጡ ይጎትታቸውና የነባሮቹ ህወሀቶች ቁንጥጫ ይመልሳቸዋል። አጥሩ ላይ እንደተንጠለጠሉ አራት ወራት አለፋቸው። ህወሀቶች ዘይቱን ሳያዘጋጁ ሙሽራው መጥቶባቸዋል። ዘይቱ ንሰሀ ነበር። ሙሽራው ደግሞ ለውጥ። እናም ዘይቱን ያላዘጋጀ ሙሽራውን እንዴት ይቀበለው?
ባለፈው ሳምንት አንድ የናዚ የጦር ወንጀለኛ ለ70 ዓመታት ከተደበቀባት አሜሪካ ለጀርመን ተላልፎ ተሰጥቷል። በ95 ዓመቱ በእጆቹ ላይ ሰንሰለት ጠልቆ ከርቸሌ ገብቷል። በእኛም ታሪክ ተመሳሳይ ክስተት ተመዝግቧል። በቀይ ሽብር ዘመን መሪ ተዋናይ የሆኑ ነፍሰ ገዳዮች ለዘመናት ከተደበቁባቸው ሀገራት ማንቁርታቸው እየታነቀ ለፍርድ ቀርበው አይተናል። የቀልቤሳ ነገዎን እዚህ ላይ መጥቀስ ይቻላል። ከፍትህ ለጊዜው ማምለጥ ይቻል ይሆናል። ቢዘገይም ግን አይቀርም። ሞት ቢቀድም እንኳን ነፍስ ዘላለሟን እረፍት ታጣለች። መለስ ዜናዊ ለፍርድ ሳይቀርብ ቢሄድም ስሙ በምድር እየተረገመ፡ ነፍሱ በሰማይ እየተሰቃየ ነው። ከመቃብር በላይ ትቷት ያለፈው በዘር ልትበጣጠቅ ጫፍ የደረሰች ሀገር ነበረችና መለስ ከምድራዊ ፍርድ ቢያመልጥም ዘላለማዊ ስሙ የተወገዘ፡ የረከሰ ሆኗል።
ጌታቸው አሰፋ ለጊዜው ከፍትህ ተደብቋል። እንደሰማሁት በኢንተርፖል ራዳር ስር እንዲሆን እንቅስቃሴው ተጀምሯል። ወደ አሜሪካ ያሸሻቸው ቤተሰቦቹ ዘንድ ሊመጣ እንደሚችል ይገመታል። ከፎቶና ከቪዲዮ ተደብቆ ስለኖረ በቀላሉ ላይታወቅ ይችላል። ግን አያመልጥም። እየተሽሎከለከ እድሜውን ሊያቆይ እየሞከረ ነው። ከመደበኛው ፍርድ ለጊዜው ሊሸሸግ ይችላል። ከምንም በላይ ከህሊና ፍርድ አያመልጥም። በሄደበት የሚከተለው ትንሹ እግዚያብሄር የሆነው ህሊናው እረፍት ሲነሳው ይኖራል። የኢትዮጵያ እናቶች እምባስ መች በከንቱ ፈሶ ያውቅና?
ህወሀቶች ጸሀይ እየጠለቀችባቸውም የተሰጣቸውን እድል መጠቀም አልቻሉም። ወይም አልፈለጉም:: ሰሞኑን ከመቀሌ ተሰብስበው ያወጡት መግለጫ ጥርሱ አልቆበት በድዱ ለመናከስ የሚንገታገት ያረጀ አውሬ አስመስሏቸዋል። በምስራቁ በር አንዱ የጥፋት እጃቸው ተቆርጦባቸውም ለተስፋ መቁረጥ እጅ መስጠት አልፈለጉም። አብዲ ዒሌ የተሰኘ የጥፋት ፈረሳቸው አይናቸው እያየ ከፍትህ እጅ ላይ ወድቋል። አያስመልጡት ነገር አቅም የለም። የእነሱንም እድል እጣ ፈንታ እርግጠኛ አይደሉም። ለጊዜው እድል ሰጥቶ የተዋቸውን ህዝብ ትዕግስት ግን እያስጨረሱት ነው።
ብአዴን
ብአዴን መጨረሻውን እያሳመረ ይመስላል። ከአፈጣጠሩ ጀምሮ በህወሀት ልክ የተሰፋለትን ጥብቆ አድርጎ የኖረው ብአዴን ሰሞኑን ያወጣው መግለጫ ከህወሀት ጋር የሚደረገው ፍቺ ቅርብ መሆኑን አመላካች ነው። ብአዴን ቆርጧል። የህወሀትን ቀሚስ አውልቋል። አርማና ስያሜ መቀየሩ ትርጉሙ ቀላል አይደለም። ህወሀት ብአዴንን ጠፍጥፎ ሲሰሰራ የልደት ቀኑን ከህወሀት የአፈጣጠር ታሪክ ጋር እንዲመሳሰል ስለመደረጉ መገመት ይቻላል። 11 ቁጥር ላይ የቆረበው ህወሀት የብአዴንን የልደት ቀን ህዳር 11 ላይ ያደረገው ያለምክንያት አልነበረም። አርማውን ከህወህት አርማ የተቀዳ አድርጎታል። ብአዴን አርማውን ብቻ ሳይሆን በህወሀት የተተከለትን የልደት ቀኑንም መቀየር ይኖርበታል።
የብአዴን መግለጫ የህወህት የበላይነት ፍጻሜ ላይ ትልቅ ሚስማር የቸነከረ ነው። ኦህዴድ ታህሳስ ላይ የብሄር ጭቆና የለም የሚል አዲስ ትርክት ይዞ ሲመጣ ህወሀት የሚይዝ የሚጨብጠው አጥቶ ነበር። የመጽአት ቀኑን ያየበት አስደንጋጩ ምልክት የታህሳሱ የኦህዴድ መግለጫ ነው ማለት ይቻላል። በብሄር ጭቆና ላይ ታሪክ ፈጥሮ ስጋ ደምና አጥንት አልብሶ፡ እስትንፋስ ዘርቶበት ኢህአዴግ በሚባል ፈረስ ኢትዮጵያን ለብዙ ዘመናት ሊጋልብ የተፈናጠጠው ህወሀት በኦህዴድ መግለጫ ህልሙ በአጭሩ ተቀጭቷል። ሲጠበቅ የነበረው የብአዴን አቋም ነበር። ሰሞኑን ብአዴንም አፈረጠው። የብአዴን መግለጫ በህወሀት አንገት ላይ የጠለቀ ገመድ ማለት ነው። የሚቀረው ገመዱን ሸምቀቅ ማድረግና ህወሀት የረገጠውን መንጠልጠያ ማንሳት ነው። አዲዮስ ህወሀት!
መግለጫው በህወሀት ህልውና ላይ ሪፈረንደም ያደረገ ነው። የአማራ ክልል ወሰን ከእንደገና ይሰመር ዓይነት አቋም ከብአዴን ሲሰማ መቼም ተአምር ነው። ይህ ማለት የወልቃይት፡ ራያና ሌሎች አከባቢዎችን በተመለከተ ብአዴን ጥያቄ ለማንሳት ወስኗል ማለት ነው። በቅርቡ በአንድ መድረክ ላይ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው የወልቃይትን ጉዳይ ከእንግዲህ ችላ የምንለው አይደለም ሲሉ ጠርጥሬአቸው ነበር። ይሀው የድርጅታቸው አቋም ሆኖ ይፋ ተደርጓል። የሱዳን ወታደሮች ከያዙት የኢትዮጵያ መሬት እንዲለቁ በብአዴን መጠየቁ ለህወሀት ትልቅ መርዶ ነው። ህወሀት ለሱዳን የኢትዮጵያን መሬት የሰጠበት ድብቅ ስምምነት የራሱ የሆነ ምክንያት አለው። ሱዳን ለህወሀት ምሽግ ናት። የክፉ ጊዜ መደበቂያ ናት። የትግራይ ህዝብ ቢከዳቸው የሚያመልጡባት ጎሬ ናት ሱዳን:: ለውለታዋ የጎንደር መሬት በስጦታ ተብርክቶላታል። ሱዳን ያን መሬት ከተነጠቀች ከህወሀት ጋር ያላትን ድብቅ ፍቅር መቀነሷ አይቀርም። ያ ደግሞ ለህወሀት የመጨረሻው ጥይት ነው። የትግራይ ህዝብ የተፋው ዕለት የሚደበቅበትን ዋሻ ያጣል ማለት ነው።
ብአዴን በግል መብት ላይ የወሰደው አቋም በራሱ ለህወሀት አስደንጋጭ ነው። በቡድን መብት ስም ዘረኝነትን በማስፋፋት የበላይነቱን አስጠብቆ ለመኖር ፕሮግራም(ህገመንግስት) የቀረጸው ህወሀት ከብአዴን በቃህ ተብሏል። የቡድን መብት እንዳለ ሆኖ የግለሰብ መብት ላይ ማተኮር ለዴሞክራሲ ወሳኝ ነው የሚል አቋም ላይ የደረሰው ብአዴን በብሄራቸው እየተደበቁ ቁማር የሚጫወቱ የዘር ፖለቲካ አቀንቃኞችንም ቅስማቸውን የሰበረ አቋም ላይ መድረሱ አስደናቂ ነው። ህወሀት በቁሙ ተዝካሩን በላና አረፈው። በዚህ አልቆመም። የህወሀትን ጥቅም በአማራው ህዝብ ኪሳራ ለማስጠበቅ በብ አዴን ውስጥ የተሰገሰጉ አፍቃሪ ህወሀት የሆኑ ቀንደኛ አመራሮችን ጠራርጎ ማባረር የጀመረው ብአዴን ለህወሀት አንድ መልዕክት እንዲደርሰው የፈለገ ይመስላል። ''በቃ''
በረከተ መርገምት
አቶ በረከት ስምዖን አየሩን ተቆጣጥሮታል። የመንደር የኮሚኒቴ ሬዲዮ ሳይቀር ደጅ እየጠና እንዳለም ሰምቼአለሁ። ብዙ ሰዎች በረከት ሰሞኑን የሰጠው ቃለመጥይቅና አብሮት ከተባረረው ታደሰ ጥንቅሹ ጋር የጻፉት ደብዳቤ ላይ በማተኮር የበረከት ቅጥፈቶች ላይ ጊዜ ሰጥቶ ሲወያዩ ታዝቤአለሁ። ለእኔ በረከት እንዲህ ተዝረክርኮ፡ በስጋት ተንጦ፡ ቅስሙ ተሰብሮ፡ የሚደገፍበት አጥቶ፡ ሲንከራርተት እንደማየት የሚያስደስት ነገር አላየሁም። ከሰሜን ጫፍ እስከ ደቡብ፡ በምዕራብና ምስራቁ እየተወነጨፈ ያሻውን ሲያደርግ፡ ሲያስገድልና ሲያሳስር የከረመ፡ ምድር አልበቃ ብላው በሰማይ መንሳፈፍ እስኪቀረው የደረሰ፡ ኢትዮጵያዊነትን ለማጥፋት ረጅሙን ርቀት የተጓዘ ሰው ዘመን ተገልብጦ፡ በሰፈረው ቁና የሚሰፈርበት ጊዜ መጥቶ ''እንዳልንቀሳቀስ ገደብ ተጥሎብኛል'' ዓይነት እዬዬውን ሲያስነካው እንደመስማት ያለ ምን ድል ይገኝ ይሆን? እንደዚያ በትዕቢት ተወጥሮ የሚታወቀው በረከት ኩምሽሽ ብሎ፡ በፍርሃት ርዶ የምቆም የምቀመጥበት አጣሁ ሲል መስማት ለእኔም ሆነ የፍትህን መረጋገጥ ሲናፍቁ ለነበሩ ኢትዮጵያውያን ትልቅ ድል ነው።
በረከትን ሳስበው ሁል ጌዜ ከአእምሮዬ ጓዳ ብቅ የሚለው አንድ ወቅት ፕ/ር መስፍን ወልደማርያም ስለበረከት የተናገሩት ነው። ''መለስ ክፉ ነው። መለስን የበለጠ ክፉ ያደረገው ደግሞ በረከት ስምዖን ነው'' እንግዲህ የክፋት አለቃ፡ የጭካኔ ደቀመዝሙር፡ የተንኮል ሀዋሪያ፡ የቅጥፈት አምባሳደር የሆነው በረከት ስምዖን ጊዜ ጥሎት፡ ዘመኑ አብቅቶ ዋጋውን ሊያገኝ ነው። በየሚዲያው ቀርቦ ''ቅዱስ ነበርኩ፡ ክንፍ የሌለው መላዕክ ከእኔ በላይ የት ይገኛል?'' ዓይነት የሌባ አይነደረቅ ዲስኩሩን እየለቀቀው ነው። በረከት ብአዴኖች ላይ የጀመረው ውግዘት አፈጣጠሩንና ስነልቦናውን እንድንመራመርበት የቤት ስራ የሚሰጠን ሆኗል። ምድር የተጠየፈችው፡ በእኩይ ምግባሩ ሀገርና ህዝብ በአንድ ሰልፍ ፊት የነሳው ሰው፡ ከደሙ ንጹህ ነኝ የሚል መፈክር ይዞ መልሶ ለእኛው ልንገራችሁ ማለት የጤና አይመስለኝም። የሚቀርቡት ወዳጆች ካሉት በጊዜ ዶክተሩን እንዲጎበኝ ቢመክሩት ጥሩ ነው። ጤናም እንዳልሆነ በብዙ ይነገርለታል።
በዘመኑ በሀሳብ የተለዩትን በጭካኔ አስሯል። የፖለቲካ ተቀናቃኝ ያላቸውን የሀሰት ዶሴ እየከፈተ ከእድሜአቸው ላይ ተቀንሶ በማጎሪያ እስር ቤት እንዲሰነብቱ አድርጓል። መለስ ሲሞት ለቅሶን በሀገር ደረጃ አደራጅቶ፡ ማቅ አስለብሶ፡ ህዝቡን በማህበር እንዲያዝን በማድረግ ታላቅ ግፍ የፈጸመ ወንጀለኛ ነው። በረከት በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ጥቁር ስም ያለው ነው። ዛሬ ''በነጻነት፡ በፖሊሲ'' እንከራከር ሲል አለማፈሩ ይገርማል። ዛሬ እሱ የሚጠይቀውን መብት ትላንት የጠየቁትን ሲያዋርድ፡ የቴሌቪዥን ድራማ እያሰራ ስም ሲያጨቀይና ገፍቶም ሲያሳስርና ሲያስገድል ዓለም የሚያውቀው ሰው ዛሬ ተነስቶ ''በፖሊሲ እንከራከር'' ብሎ አይኑን በጨው አጥቦ መጥቷል። እንግዲህ 'ፍትህ' ለዚህ ሰውዬም ያስፈልጋል።
በረከትን 'ኢትዮጵያዊው' ጎብልስ በሚል የሚጠቅሱትም አሉ። የናዚው የፕሮፖጋንዳ ማሽን ጆሴፍ ጎብልስ ''ውሸት ሲደጋገም እውነት ይሆናል'' የሚለውን አስቀያሚ ትርክት ለዓለም ያስተዋወቀ፡ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት በዚሁ ትርክቱ የናዚን ወታደሮችና የጀርመንን ህዝብ ለጦርነት የማገደ እንደነበረ ይነገርለታል። በረከት ስምዖን የዘመኑ ጎብልስ ሆኖ ኢትዮጵያውያን ላይ ተሰይሟል። ሀገሪቱን የውሸት ፋብሪካ አድርጓት አንድ ትውልድ በውሸት ተወልዶ እንዲያድግ ፈርዶበታል። በእርግጥ በናዚው ጎብልስና በህወሀቱ ጎብልስ መሀል ልዩነት አለ። ጎብልስ የቆመለት የናዚ ስርዓት ሲገነደስና እንደአምላክ የሚያየው አዶልፍ ሂትለር ራሱን ሲያጠፋ ጎብልስም ስድስት ልጆቹን መርዝ አብልቶ እሱንና ሚስቱንም በሽጉጥ ገድሎ ይህቺን ምድር ተሰናብቷል። በረከት ስምዖን ግን ፈሪ ነው። አምላኩ መለስ ዜናዊ ሞቶም እሱ እስከአሁን አለ። ወንድሙን ገድሎበት እንኳን በታማኝነት የገበረለትና የተገዛለት የህወሀት ስርዓት በቁሙ ሲገነደስ እያየ በረከት ግን መኖር ይፈልጋል። ፈሪ። መርገምት።
እኔ በእሱ ቦታ ብሆን የክብር ሞቴን በገዛ ፍቃዴ እውን አደርጋለሁ። ሰው እንዴት ሳር ቅጠሉ ሳይቀር ጠልቶት፡ እዚህም እዚያም ቤተክርስቲያን እንደገባች ድመት እየተባረረ መኖርን ይመርጣል? በረከት ስምዖን ለፍርድ ቀርቦ ማየት እፈልጋለሁ። በየሚዲያው የሚለውን ለመስማት ጊዜም አፕታይቱም የለኝም። በረከት የሚነግረኝ የማላውቀው የለም። እሱ ዘንድ ለእኔ የሚጠቅም መረጃም ሆነ እውቀት ይኖራል ብዬ አላምንም። በረከት የውሸት አቁማዳውን ይዞ በየሚዲያው ደጅ እየጠና ነው። የክፋት መርዙን አሁንም ለመርጨት ታጥቆ ተነስቷል። በረከት የክፋት አቅሙ አልደከመም። ለብአዴን ከታደሰ ጥንቅሹ ጋር በጻፈው ሀሜት መሰል ደብዳቤ ላይ ለማ መገርሳንና ገዱ አንዳርጋቸውን ለማጋጨት ይሞክራል። እናም ሚዲያዎች ይህን ሰው ሲያገኙት መርዙን ረጭቶ ብቻ እንዲሄድ ባይፈቅዱለት ጥሩ ነው። ነፍሱ እስኪላቀቅ የሚጠይቅ በመረጃና ማስረጃ በረከትን ራቁቱን የሚያስቀር እንጂ የበረከትን ዲስኩር እንደወረደ የሚያስተናግድ ሚዲያ ለጊዜው አያስፈልገንም። በረከት በቃው!
(Mesay Mekonnen)
Dienstag, 7. August 2018
ታሪክ (ጋዜጠኛ ፋሲል የኔዓለም)
ታሪክ (ጋዜጠኛ ፋሲል የኔዓለም)
የአንድ ጀግና ወታደር ታሪክ
የዛሬ 5 አመት ገደማ ነው፤ አንድ መረጃ ያቀብለን የነበረ መኮንን ደጋግሞ ስልክ ይደውልልኛል፤ ስራ እንደጨረስኩ ደወልኩለት። ሰላም ነው አንበሳው። “ምን ሰላም አለ፤ ስልኩን አላነሳ ስትል ሳልሰናበተው ልቀር ነው እያልኩ ቆጭቶኝ ነበር፣ ስልክህ ሲጠራ እንዴት እንደተደስትኩ አትጠይቀኝ” አለኝ። ይቅርታ ስራ በዝቶብኝ ነው፣ ልትዛወር ነው እንዴ አልኩት። “ እረዳሃለሁ ፋሲሎ፣ ለማንኛውም ጠፍቼ እየሄድኩ ነው፣ የት እንደምሄድ ግን አላውቅም፤ ዛሬ ያየሁትን ነገር ህሊናዬ ሊሸከመው አልቻለም” ። ቆይ ምን ተፈጠረ? “ምን ያልተፈጠረ ነገር አለ፣ እናቶችንና ህጻናትን በጠራራ ጸሃይ ጨረሷቸው፣ እናቶችን ሳይ እናቴ ትዝ አለችኝ”፣ ድምጹ ተቆራረጠ። ወታደር የሚያለቅስ አይመስለኝም ነበር፤ አይዞህ አይዞህ እያልኩ አጽናናሁት። ምንድነው የሆነው እስኪ ተረጋግተህ ንገረኝ አልኩት። “ዛሬ ጠዋት ኦብነግ አንድ መንደር ውስጥ ገብቷል ተብለን ግዳጅ ወጥተን ነበር፤ የክልሉ ልዩ ሃይል አባላት እኛን እየመሩ ወሰዱንና ቦታው ስንደርስ ኦብነጎች ማምለጣቸውን ሰማን፤ ከዚያ በሁዋላ ህዝቡን ማሸበር ተጀመረ፣ እናቶች አትግደሉን እያሉ ተገደሉ፣ ህጻናት መሸሸጊያ ፍለጋ ሲራወጡ ፊት የተገኙት ሁሉ ተገደሉ፣ ወጣት የሚባል የለም፣ አሮጊቶችና ሴቶች ናቸው ታጨዱ፣ ምን ልበልህ፣ መፈጠርክን ትጠላለህ፤ ያየሁትን ለመግለጽ አልችልም፤ ከእንግዲህ ወዲያ ከዚህ ሰራዊት ጋር መቀጠል አልፈልግም ፣ እነሱ ወደ ፊት ሲሄዱ እኔ ጠፍቼ መንገድ ጀምሬያለሁ።” መኮንኑ በስሜት ውስጥ ሆኖ ሲገልጸው የነበረው እና እኔ ከአመታት በሁዋላ ስጽፈው ያለውን ልዩነት እያስተዋልኩ ተናደድኩ። እንደ ዛሬ የደራሲነት ተሰጥዖ እንዲኖረኝ ተመኝቼ አላውቅም።
ስሜትን ዋጥ አደርኩና፣ ለመሆኑ የት ነው የምትሄደው አልኩት። “አላውቅም ኦጋዴንን ታውቀዋለህ፣ ምደረበዳ ነው፤ ከተሳካላኝ ጅቡቲ ወይም ሶማሊያ ልገባ እችላለሁ፤ ምናልባትም በኦብነግ ወይም አልሸባብ እጅ ልወድቅ እችላለሁ፣ የእኛ መከላከያዎች ካሉበት በተቀራኒ አቅጣጫ ነው የምጓዘው። እነሱ እንዲይዙኝ አልፈግልም፤ ከተያዝኩም ምን እንደሚያደርጉኝ አውቃለሁ፣ በእነዚህ ዘረኞች እጅ ላይ ከምወድቅ ኦብነግ ወይም አልሸባብ ቢገድለኝ እመርጣለሁ፤ አሁንማ አያተርፉኝም፤ የሚይዙኝ ከሆነ ግን እራሴን አጠፋለሁ።” ወንድሜ ስማኝ፣ “ አሁን ወደ ቦታህ ተመለስ፣ አሞኝ ነው ወደ ሁዋላ የቀረሁት በላቸው፣ ሌላ ጊዜ አዘናግተህ ትጠፋለህ፣ እኔ ራሴ መንገድህን አመቻችልሃለሁ፣ በፍጹም ወደማታውቀው ቦታ አትሂድ…” እያልኩ ላሳምነው ሞከርኩ። “አላደርገውም፣ የእኔ ነፍስ ካለቁት እናቶችና ህጻናት ነፍስ አይበልጥም። አሁን ባትሪዬን አትጨርሰው፤ የሆነ ቦታ ላይ በሰላም ከደረስኩ ቁጥርህን በቃሌ ስለያዝኩት እደውልልሃለሁ፤ መንገድ ላይ ከቀረሁም ቻው፤ በርታ፣ በጣም አከብርሃለሁ፤ ኦጋዴን ውስጥ የተፈጸመውን ታሪክ በዝርዝር የምናገርበት እድሜ እንዲሰጠኝ ጸልይለኝ ” ብሎኝ፣ እኔም እንደምንም ስሜቴን ዋጥ አድርጌ መልካሙን ሁሉ ተመኝቼ ስልኩን ዘጋሁት። ዛሬም ድረስ ያ ጀግና ወታደር ይደውል ይሆን እያልኩ ስልኩን በጉጉት እጠብቃለሁ። ከተለያየን ከ3 ዓመታት በሁዋላ ቁጥሬን የቀየርኩ በመሆኔ አዲሱ ቁጥሬ ላይኖረው ቢችልም፤ በ3 ዓመታት ውስጥ ለእሱ በሰጠሁት ቁጥር ደውሎልኝ አያውቅም።
ወዳጄ፣ በአንድ ወቅት በብሄራቸው የሚያስቡ አዛዦች የሞሉበት ሰራዊት ተቀይሮ ህዝባዊነትን ሲላበስ ቢያይ ኖሮ፣ ምንኛ ደስ ባለኝ፤ እሱና መሰሎቹ ይህ ቀን እንዲመጣ ስንትና ስንት መስዋትነት መክፈላቸውን አፍ ቢኖረው ኖሮ የውቅሮ እስር ቤት በዝርዝር ያጫውተን ነበር።
https://netsanetlegna.wordpress.com/2018/08/07/%e1%8b%a8%e1%8a%a0%e1%8a%95%e1%8b%b5-%e1%8c%80%e1%8c%8d%e1%8a%93-%e1%8b%88%e1%89%b3%e1%8b%b0%e1%88%ad-%e1%89%b3%e1%88%aa%e1%8a%ad-%e1%8c%8b%e1%8b%9c%e1%8c%a0%e1%8a%9b-%e1%8d%8b%e1%88%b2%e1%88%8d/
Mittwoch, 4. April 2018
ቀጣዬ 100 ቀናት! (በኤርሚያስ ለገሰ)
ቀጣዬ 100 ቀናት!
መንደርደሪያ
የትግራይ ነፃ አውጪ በገጠመው ሕዝባዊ ማእበል፣ እንዲሁም የሕዝቡን ተቃዉሞ በተከተለበት ጫና ዶክተር አቢይን ወደ ጠቅላይ ሚኒስትርነት አምጥቷል። የዶክተር አቢይ ወደ ፊት መምጣት በብዙ መልኩ የተደበላለቀ ስሜቶችን ፈጥሯል። በህውሓት ደጃፍ ከፍተኛ ቁዘማና ንዴት የፈጠረ ሲሆን በለውጥ ፈላጊው ዘንድ የተከፋፈለ አስተያየቶች በመስተናገድ ላይ ናቸው። በተለይም ዶክተሩ በበአለ ሲመቱ እለት ያቀረበው ንግግር የብዙ ኢትዬጲያውያንን አንጀት ቅቤ ያጠጣ ነበር። በታሪካዊነቱም ተመዝግቧል።
በአጭር ጊዜ ውስጥ በስልጣን ኮርቻው ላይ የወጣው ዶክተር አቢይ እጅግ ውስብስብ የሆኑ ችግሮችን ለመፍታት፣ መንፈሱ የተበታተነውን የኢትዬጲያ ህዝብ ለማረጋጋት፣ ኢትዬጲያን ወደ ፊት ሊያራምዱ የሚችሉ ሁሉንም ኃይሎች ለማስተባበር፣ የኢኮኖሚ እና ፓለቲካ እቅዶችን ለማስተዋወቅ ጥረት አድርጓል።
ይህንም ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቀጣይ ቀናት ወደ ተግባር ሊመነዝራቸው ይገባል የተባሉ ስፍር ቁጥር የሌላቸዉ ድርጊቶች መዘርገፍ ጀምረዋል። ሰውየው ለወደፊቱ ያለበትን ተልእኮ የሚያሳስበውም ብዙ ነው። እኔም እንደ አንድ ኢትዬጲያዊ ዶክተር አቢይ በኦሮሚያ የጀመረውን ስራ ሳይጨርስ ወደ ፌዴራል መምጣቱ ልቤ አልተቀበለውም። ተቃውሞዬን በአደባባይ ገልጫለሁ። በጠላቶቹ ሜዳ ላይ ከመጫወቱ በፊት የራሱን ሜዳ በብረት እንዲያጥረው ፍላጐቴ ነበር።
አሁንም ቢሆን ከትላንት አቋሜ የተለወጠ ነገር የለኝም። በስልጣን ላይ ያለው ሽፍታ አገዛዝ አሁንም የስለላና ወታደራዊ መዋቅሩን የተቆጣጠረው ነው። ወደድነውም ጠላነውም የኢኮኖሚ መዋቅሩን የተቆጣጠረው ይህ ከፋፋይ ቡድን ነው። ሌላው ቀርቶ የአሁኖቹ የዶክተር አቢይ የግልና የቤተመንግስት ጠባቂዎች የሟቹ መለስ ዜናዊ ጠባቂዎች ናቸው።
በመሆኑም ሰውየው በአምባገነኖች፣ በዘረኞች፣ በማይማን፣ ኢትዬጲያን በሚጠሉና በሚያሳፍሩ ሰዎች መዳፍ ውስጥ መግባቱን ስመለከት መንፈሴ ይረበሻል። የትግራይ ነፃ አውጪ ካድሬዎች እና ባለሟሎች እንዳይሰራ መውጪያ መግቢያውን እንደሚዘጉበት ሳውቅ ልቤ ይደማል። በፈላ ውሃ እንደምትቀቀለው እንቁራሪት እየሆኑ ያሉት ህውሓቶች የተካኑበትን አጥፍቶ መጥፋት ፓሊሲ እንዳይፈፅሙበት እሰጋለሁ።
በሌላ በኩል አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ለኢትዬጲያ ህዝብ ያቀረበው ራዕይ አስደስቶኛል። የኢትዬጲያ ተስፋና የኢትዬጲያችን መቀጠል ሲያስጨንቀው አብሬ ተጨንቄያለሁ። ዶክተር አቢይ የሕዝብ አሽከር ሆኖ ሕዝብን ለማገልገል ቆርጦ መነሳቱን ሳይ በምን ልደግፈው እችል ይሆን የሚል ጥያቄ አንስቻለሁ። የጠላት ሜዳ ላይ አሸንፎ ለመውጣት እንዴት ቢጫወት ያዋጣዋል የሚለውን አስቤያለሁ።
እናም ዶክተር አቢይ የኢትዬጲያ ህዝብ ትግልና እምቢተኝነትን እንደ ነዳጅ እየወሰደ የተቆጠረ ግቦችን በተቆጠረ ጊዜ ቢፈፅም አሸናፊ ሆኖ ሊወጣ ይችላል። ባለፈው መጣጥፌ በተራዘመ ጊዜ ሊፈፅማቸው የሚችሉትን አላማዎች ጠቆም አድርጌ ነበር። ለዛሬው በመቶ ቀናት ሊፈፅማቸው ይገባል ያልኳቸውን የአደረጃጀትና የፓለቲካ ግቦች ጠቁሜያለሁ። እነዚህ አራት ግቦችና በስራቸው ያሉ የተቆጠሩ ተግባራት ከአረጃጀት፣ በመንግስትና በፓርቲ መካከል መኖር ስለሚገባው ግንኙነት፣ ስልጣንን እና ሌብነትን እንዲሁም የዲሞክራሲ እሴቶችን ለመገንባት የተዘረዘሩ ናቸው። ግቦቹና ዝርዝር ተግባራቱ ያለቀላቸው ሳይሆኑ ለውይይት መነሻ ሆነው የሚያገለግሉ ናቸው።
***
##ግብ አንድ:-
በሕገ መንግስቱ መሰረት በኢትዬጲያ ህዝብ አመኔታ እና ተቀባይነት የላቸውን በመለየት የሚኒስትሮች ምክር ቤትና ሌሎች ከፍተኛ የስልጣን እርከኖች ማዋቀር።
*
#የግብ አንድ ተግባር አንድ:-
ሕገ መንግስቱ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከህዝብ ተወካዬች ምክር ቤት አባላት እና ከምክር ቤት አባላት ውጪ ሚኒስትሮችን በመመልመል በፓርላማው ያፀድቃል በሚለው መሰረት እጩዎችን ከሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች መመልመል።
*
#የግብ አንድ ተግባር ሁለት፣
ከተመለመሉት ውስጥ በብቃታቸው፣ በስነምግባራቸውና ተቀባይነታቸው የላቁትን ለሽግግር ጊዜው በሚኒስትርነት መመደብ። በዚህ መሰረት የሚከተሉት ግለሰቦች ለሽግግር ጊዜው ለእጩነት ቢቀርቡ በምክረ ሃሳብ የቀረቡ ናቸው፣
° ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርነት: አቶ ደመቀ መኮንን
° ውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነት: ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና
° ኢኮኖሚና ፋይናንስ ሚኒስትር: አቶ ስዩም ተሾመ
° ፍትሕ ሚኒስትር: አቶ ተማም አባቡልጋ
° ደህንነት ሚኒስትር: አቶ ገዱ አንዳርጋቸው
° ኮሙዩኒኬሽን ሚኒስትር: አቶ ንጉሱ ጥላሁን
°የአገር ደህንነት ሚኒስትር: አቶ አንዷለም አራጌ
° ገቢዎች ሚኒስትር: - አቶ አስራት አብርሃም
° አርብቶ አደር ሚኒስትር: ዶክተር አብርሃ ተከስተ
° መገናኛ ሚኒስትር: አቶ የሺዋስ አሰፋ
° መከላከያ ሚኒስትር : አቶ በቀለ ገርባ
° ትምህርት ሚኒስትር:- አቶ ሬድዋን ሁሴን
° አሳ ሐብት ሚኒስትር: ወ/ት ፈትለወርቅ ገብረእግዚአብሔር
° የጡረታ ሚኒስትር: አቶ አስመላሽ ወልደስላሴ ( አባይ ነብሶ)
° ቱሪዝም ሚኒስትር:- ዶክተር አዲሳለም ባሌማ
° የኢንቨስትመንት ሚኒስትር:- አቶ ግርማ ሰይፉ
° ወጣቶች ሚኒስትር: - አብርሃ ደስታ
° ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር: - አርቲስት አስቴር በዳኔ
° ኤታማዦር ሹም: - ጄነራል ተፈራ ማሞ
° ፌዴራል ፓሊስ ሹም:- ኮረኔል ደመቀ ዘውዴ
° ሴቶችና ህፃናት ሚኒስትር:- ወይዘሮ የትነበርሽ
° የጽህፈት ቤቱ ሚኒስትር:- አቶ ደግፌ ቡላ
° የንግድ ሚኒስትር:- ተስፋዬ በጅጋ
° የግብርና ሚኒስትር: - አቶ ሲራጅ ፈርጌሳ
*
#ግብ አንድ ተግባር ሁለት፣
የመንግስት የልማት ድርጅቶች፣ ኮርፓሬሽን፣ ባለስልጣናት እና ተቋማት ስራ አስኪያጅ፣ ዋና ስራ አስፈፃሚና ዴሬክተሮች ሹመት የየትኛውም የፓለቲካ ድርጅት አባላት ካልሆኑ ኢትዬጲያውያን ውስጥ ብቃት ያላቸውን መሾም። መመዘኛዎቹ በሚዲያ ተቋማት በግልፅ እንዲነገሩ ማድረግ። ሂደቱን ሕዝቡ በቀጥታ በሚከታተለው መልኩ እና ተወዳዳሪዎች ተቋማቱን እንዴት እንደሚመሩ እና የት ማድረስ እንደሚፈልጉ በሚገልፁበት ሁኔታ እንዲፈፀም ማድረግ። በውጭ የሚኖሩ ከፍተኛ ሙያተኛ የሆኑ ኢትዬጲያውያን እና ትውልደ ኢትዬጲያውያን የውድድሩ አካል እንዲሆኑ ማድረግ።
ከእነዚህ የስልጣን ቦታዎች መካከል ዋና ዋናዎቹ የሚከተሉት ይሆናሉ፣
• የብሔራዊ ባንክ ገዥ
• የልማት ባንክና ንግድ ባንክ ዋና ስራ አስፈፃሚ
• የኢትዬጲያ መድን ድርጅት
• የኢትዬጲያ አየር መንገድ
• የኢትዬጲያ ቴሌ ኮሙዩኒኬሽን
• የመንግስት ሆቴሎች
• የኢትዬጲያ ቴሌቪዥን እና ሬዲዬ
• የመንገዶች ባለስልጣን
• ምርት ገበያ ( ECX)
• ዋና ኦዲተር ጄኔራል
• ሁሉም የአምባሳደርነት ቦታዎች
• አደጋና ዝግጁነት ዴሬክተር ( አመዝኮ)
*
#የግብ አንድ ተግባር ሶስት:-
በመንግስት በጀት የሚተዳደሩ አላስፈላጊ የሚኒስቴር መስሪያቤቶች፣ ባለስልጣናት ፣ ተቋማት እና የሐላፊነት ቦታዎችን ማፍረስ። ከእነዚህ ውስጥ ቅድሚያ የሚሰጣቸው፣
• ፌዴራል ጉዳዬች ሚኒስትር
• የመንግስት ዋና ተጠሪ ፅህፈት ቤት
• የብሮድካስት ባለስልጣን
• የኢትዬጲያ ዜና አገልግሎት እና ፕሬስ ድርጅት
• የእምባ ጠባቂ ኮሚሽን
• የሰብአዊ መብት ኮሚሽን
• ምርጫ ቦርድ
• የብረታ ብረት ኮርፓሬሽን ( ሜቴክ)
• ብሔራዊ መረጃ መረብ ደህንነት ኤጀንሲ(ኢንሳ)
• የፓሊሲ ምርምር፣ ጥናትና አማካሪ ቢሮ
*
#የግብ አንድ ተግባር አራት፣
ጠቅላይ ሚኒስትሩን በቋሚነት የሚያሟክሩ በኢትዬጲያ ሕዝብ ተቀባይነት ያላቸው ከ25 እስከ 30 የሚጠጉ ምስጉን የአገር ሽማግሌዎች፣ የሐይማኖት አባቶችና አገራችንን በአለም ደረጃ ያስተዋወቁ አባላት የያዘ “ አማካሪ ምክር ቤት” ማቋቋም።
• አማካሪ ምክርቤቱ በሁለት ሳምንት አንዴ ( ቅዳሜ ከሰአት) ለግማሽ ቀን የሚሰበሰብ ይሆናል።
• አማካሪ ምክር ቤቱ ዋነኛው ተልእኮ የሽግግር ሂደቱን ለማፋጠን ድልድይ ሆኖ የሚያገለግል ይሆናል። የፓለቲካ ፓርቲዎችን ድርድር በይፋና በሚስጥር ያደርጋል። ፓርቲዎቹ የሚያቀርቡትን የሽግግር ሰነድ እየመረመረ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ያቀርባል። የዲሞክራሲ ተቋማት ተአማኒነት ባለው መልኩ የሚዋቀሩበትን ሐሳቦች በማመንጨት ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ያቀርባል።
• የአማካሪ ምክር ቤት አባላት የገዥው ፓርቲ አባላትም ሆነ ደጋፊዎች መሆን የለባቸውም።
• ለአማካሪ ምክር ቤት አባልነት ለመነሻ እንዲሆን አቶ እየሱስ ወርቅ ዛፋ፣ አቶ ቡልቻ ደመቅሳ፣ ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ፣ አቶ ክቡር ገና፣ ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ፣ አቶ ገብረየስ ቤኛ፣ ዶክተር ዳኛቸው አሰፋ፣ ዶክተር በድሉ ዋቅጅራ፣ አቶ አርአያ ገ/ እግዚአብሔር፣ አቶ ገብሩ አስራት፣ ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም፣ ዶክተር ያዕቆብ ሐይለማርያም፣ ዶክተር በፍቃዱ ደግፌ፣ አርቲስት አሊ ቢራ፣ አርቲስት ቴዎድሮስ ካሳሁን፣አርቲስት አረጋኸኝ ወራሽ፣ አትሌት ሐይሌ ገብረስላሴ፣ አቶ አስገደ ገ/ ስላሴ፣ አቶ ገብሩ ገብረማሪያም፣ አቶ ቆስጠንጢኖስ በርሄ፣ ፕሮፌሰር ፍቅሬ ቶሎሳ የመሳሰሉት አባል የሚሆኑበት ይሆናል።
*
#የግብ አንድ ተግባር አምስት፣
የቀድሞ የሕውሓት/ ኢህአዴግ ባለስልጣናትን በሶስት ዙር በጡረታ ማሰናበት። ከጡረታ በኃላ በየትኛውም የሚዲያ ተቋም ፣ብሔራዊና ድርጅታዊ በአላት፣ ስብሰባዎች፣ ምርቃቶች እንዳይገኙ ማድረግ። አቶ ተፈራ ዋልዋ ልምዱን እንዲያካፍላቸው መድረክ ማዘጋጀት። በመጀመሪያው ዙር የሚሰናበቱት አቶ ስዩም መስፍን፣ አቶ በረኸት ስምኦን፣ አቶ አርከበ እቁባይ፣ አቶ ስብሃት ነጋ፣ አቶ አባይ ፀሀዬ፣ አቶ ግርማ ብሩ፣ ዶክተር ካሱ ኢላላ ፣ ኩማ ደመቅሳ ፣ አዲሱ ለገሰ፣ ሳሞራ የኑስ፣ ጌታቸው አሰፋ፣ አለማየሁ ተገኑ ይሆናሉ።
***
#ግብ ሁለት፣
የመንግስት እና ፓርቲ ስራ እንዲለያዩ ማድረግ። ፓርቲ መንግስትን ተክቶ አመራር አይሰጥም። መንግስት በቀጥታ በፓርቲው እየተመራ አመራር አይቀበልም።
*
#የግብ ሁለት ተግባር አንድ፣
የመንግስት አካላት የሚከተሉትን አጠቃላይ የፓለቲካ፣ የኢኮኖሚ፣ የማህበራዊና የባህል ፓሊሲዎች የሚቀየሱት በሚኒስትሮች ምክር ቤት ብቻ ይሆናል።
*
#የግብ ሁለት ተግባር ሁለት፣
በሕዝብ ምርጫ ከሚደራጁ ምክር ቤቶችና ካቢኔዎች ( እስከ ቀበሌ) ውጭ የሚሞሉ የመንግስት ሐላፊነት ቦታዎች የየትኛውም የፓለቲካ ፓርቲ አባል ያልሆኑ ኢትዬጲያውያን እንዲያዝ ማድረግ።
*
#የግብ ሁለት ተግባር ሶስት፣
በሲቪል ሰርቪስ ውስጥ ተቀጥረው የሚሰሩ ሰራተኞችም ሆነ በቀጣይ የሚቀጠሩ ሰራተኞች የትኛውም የፓለቲካ ፓርቲ አባል እንዳይሆኑ ማድረግ። በሲቪል ሰርቪስ ውስጥ እየሰሩ አስቀድሞ አባል የሆኑ ሲቪል ሰርቫንቶች ለነበሩበት ፓርቲ በይፋ መልቀቂያ እንዲያስገቡ ማድረግ። የፓርቲ መልቀቂያ ለማስገባት ፍቃደኛ ያልሆኑ የመንግስት ሰራተኞች በፍቃደኝነት ስራቸውን እንዲለቁ ማድረግ።
*
#የግብ ሁለት ተግባር አራት፣
በመንግስት የስራ ሰአት፣ በመንግስት ፅህፈት ቤት ውስጥ የየትኛውም የፓለቲካ ድርጅት የፓለቲካ ስራ( ማደራጀት፣ መሰብሰብ፣ ካድሬ መመልመል) እንዳይካሄድ ማድረግ። የመንግስት ንብረት ለመንግስት ስራ ብቻ ማዋል። ይሄን ተላልፎ የሚገኝ ማንኛውም ሰራተኛ ከስራ እንዲሰናበት እና የትኛውም የመንግስት መስሪያ ቤት በድጋሚ እንዳይቀጠር ማድረግ።
*
#የግብ ሁለት ተግባር አምስት፣
በዩንቨርስቲዎች፣ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት፣ቴክኒክና ሙያ እንዲሁም በአንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ማንኛውም የፓለቲካ ፓርቲ በይፋም ሆነ በግልፅ የድርጅት ስራ ( ምልመላ፣ ማደራጀት፣ ስብሰባ፣ መሰረታዊ ድርጅት) የመሳሰሉትን እንዳይሰራ ማድረግ። የትምህርት ተቋማቱ አመራሮች ምደባ የፓለቲካ ፓርቲ አባል አለመሆንን እንደ ቅድመ ሁኔታ በመውሰድ መመዘኛው ብቃት እና ብቃት ብቻ እንዲሆን ማድረግ። በየትኛውም ደረጃ ያሉ መምህራት እንደ ሲቪል ሰርቪስ ሰራተኝነታቸው ከየትኛውም የፓለቲካ ድርጅት አባል አይሆኑም። ህሊናቸው ካልፈቀደ በፍቃደኝነት ስራቸውን እንዲለቁ ይደረጋል።
***
# ግብ ሶስት፣
ስልጣን የሐብት ምንጭ የማይሆንበት ሁኔታ መፍጠር።
*
#የግብ ሶስት ተግባር አንድ፣
ሚኒስትሮች፣ ምክትል ሚኒስትሮች፣ ዋናና ምክትል ስራ አስፈፃሚዎች፣ ስራ አስኪያጆች፣ ዴሬክተሮች፣ መምሪያ ሐላፊዎች፣አምባሳዳሮች፣ ዲፕሎማቶች፣ ከኮረኔል እስከ ጄኔራል ባለ ማእረግ የጦር አዛዦች ንብረታቸውን በመመዝገብ ለሕዝብ ይፋ ማድረግ። የወር የገቢና ወጪ መጠናቸውን፣ የልጆች ትምህርት ቤት ወጪ ወዘተ በምዝገባው እንዲካተት ማድረግ። ለምዝገባ ፍቃደኛ የሆኑትን እና ለመደበቅ ጥረት የሚያደርጉትን ለሕዝብ በማጋለጥ ለህግ ማቅረብ። በአርአያነት ጠቅላይ ሚኒስትሩ እና የካቢኔው አባላት በአንድ ወር ውስጥ ንብረታቸውን ይፋ እንዲያደርጉ ማድረግ።
*
#የግብ ሶስት ተግባር ሁለት፣
በግብ ሶስት ተግባር ሁለት የተገለጡት ባለስልጣናት ከአንድ በላይ የቦርድ አመራርም ሆነ የቦርድ አባል እንዳይሆኑ ማድረግ። በቦርድ የሚተዳደሩ ተቋማት ውስጥ ቢያንስ ሁለት ከተፎካካሪ ፓርቲ፣ አንድ ከባለስልጣንም ሆነ ከሲቪል ሰራተኛ ውጭ ማድረግ። በቦርድ ውስጥ የማገልገል ስራ በፍላጐትና ያለምንም ክፍያ እንዲሆን ማድረግ።
*
#የግብ ሶስት ተግባር ሶስት፣
በግብ ሶስት ተግባር ሁለት የተጠቀሱት ባለስልጣናት የቅርብ ዘመዶች ባለቤት የሆኑበት ቢዝነስ ከባለስልጣኑ ስራ ጋር በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የሚገናኝ ከሆነ ባለስልጣኑ ሐላፊነቱን በፍቃደኝነት እንዲለቅ አሊያም ሌላ ቦታ ተዘዋውሮ እንዲያገለግል ማድረግ። በተጨማሪም ባለስልጣናቱ ከመንግስት ተቋማት ውጪ ባሉ ድርጅቶች የቦርድ አባልነትም ሆነ የአማካሪነት ስራ መስራት አይችሉም።
*
#የግብ ሶስት ተግባር አራት፣
የፓለቲካ ፓርቲዎች የሚያስተዳድሩት ንብረትም ሆነ ቢዝነስ እንደማይኖራቸው በሕጉ የተገለፀውም ተፈፃሚ ማድረግ። በዚህ ሕግ መሰረት የኤፈርት፣ የትልማ፣ ረስት፣ ጥረት፣ ዲንሾ፣ ወንዶ ንብረቶች ለግል ባለሀብት እንዲሸጡ ማድረግ። ከሽያጭ የሚገኘውን ገቢ ለአንደኛ ፣ሁለተኛና ዩንቨርስቲዎች ማከፋፈል።
*
#የግብ ሶስት ተግባር አምስት፣
የግሉ ዘርፍ በነፃ ገበያው መርህ እየተመራ በኢኮኖሚው ላይ የበላይነቱን እንዲያረጋግጥ ምቹ ሁኔታ መፍጠር። በመንግስት የተያዙ ተቋማት በነፃ ገበያ ህግጋት መሰረት በሂደት ወደ ግል የሚዞሩበት ጥናቶችን ሰርቶ ማጠናቀቅ።
***
#ግብ አራት፣
በኢትዬጲያ ህዝብ ውስጥ ዲሞክራሲያዊ ባህልና እሴቶች እንዲጠናከሩ ማድረግ።
*
#የግብ አራት ተግባር አንድ፣
የፀረ ሽብርተኝነት ፣ የመንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እና የፕሬስ ህጉን በገለልተኛ ወገን እንዲጠና ማድረግ። የሚኒስትሮች ምክርቤት እና የአማካሪ ምክር ቤት አባላት በጋራ በመሆን በገለልተኝነት አጥንተው የሚያመጡ ሙያተኞችን በስምምነት እንዲመድቡ ማድረግ። ጥናቱ ተጠናቆ እስኪመጣ ድረስ አዋጆቹ በጠቅላይ ሚኒስትሩ አቅራቢነት በፓርላማ እንዲታገዱ ማድረግ። በህውሓት ፓርላማ “ ሽብርተኛ!” ተብለው የተፈረጁ አገራዊ ድርጅቶች በአስቸኳይ እንዲሰረዙ ማድረግ።
*
#የግብ አራት ተግባር ሁለት፣
በሕግ መልኩ በፓርላማ ሊወጣ የተዘጋጀውን “ የማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም ሕግ” ሙሉ ለሙሉ ሂደቱ እንዲቋረጥ ማድረግ። እንደዚህ አይነት ከፀረ ሽብርተኝነት የባሰ ጨቋኝ ህግ እንዲወጣ በመታሰቡ ለወጣው የሕዝብ ገንዘብ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይቅርታ ጠይቀው እንደማይደገም ቃል መግባት።
*
#የግብ አራት ተግባር ሶስት፣
ሬዲዬ ፋና፣ ዋልታ፣ ENN ፣ ድምፀ ወያኔ የመሳሰሉ የፓርቲ ሚዲያዎችን ማገድ። በግልፅ ጨረታ ወደ ግል ይዞታ የሚዞሩበትን ሁኔታ ማመቻቸት። ሂደቱ በሚኒስትሮች ምክርቤትና በአማካሪ ምክር ቤቱ መደበኛ ስብሰባ እየቀረበ አበረታች ምርመራ እንዲካሄድ ማድረግ።
*
#የግብ አራት ተግባር ሶስት፣
የሽግግር ሰነድ ካዘጋጁ ተፎካካሪ የፓለቲካ ድርጅቶች ጋር ሚኒስትሮች ምክር ቤትና አማካሪ ምክር ቤቱ ይፋዊ ውይይቱን መጀመር። ውስጣዊ ድርድሮቹ ካለቁ በኃላ ለህዝብ ይፋ በሆነ መንገድ ውይይቱን መጀመር።
-----//----
https://netsanetlegna.wordpress.com/2018/04/04/%e1%89%80%e1%8c%a3%e1%8b%ac-100-%e1%89%80%e1%8a%93%e1%89%b5-%e1%89%a0%e1%8a%a4%e1%88%ad%e1%88%9a%e1%8b%ab%e1%88%b5-%e1%88%88%e1%8c%88%e1%88%b0/