Netsanet

Mittwoch, 29. August 2018

አብዲ ዒሌ እስር ቤት ገብቷል። በረከት ስምዖን የውርደትን እፍታ ቀምሷል። ጌታቸው አሰፋ የሚደበቅበት ጉድጓድ ፍለጋ ላይ ተጠምዷል። (መሳይ መኮንን)

አብዲ ዒሌ እስር ቤት ገብቷል። በረከት ስምዖን የውርደትን እፍታ ቀምሷል።  ጌታቸው አሰፋ የሚደበቅበት ጉድጓድ ፍለጋ ላይ ተጠምዷል።
አባይ ጸሀዬ ድምጹን አጥፍቷል። ስብሃት ነጋ በመቀሌ አክሱም ሆቴል ውስኪውን እየላፈ ቆዝሟል። በእብሪትና ትዕቢት ያበጠው የጌታቸው ረዳ ልብም ተንፍሷል። ሳሞራ የኑስ የጡረታ ዘመኑን በስጋት ይገፋል። አስመላሽ ወ/ስላሴ ግን አሁንም ይፎክራል። ሞንጆሪኖም ''የትላንቱ ይበጀናል'' ዜማ እያቀነቀነች በትካዜ ተውጣለች። ደብረጺዮን መሀል ላይ ይዋልላል። አዲስ አበባ ሲደርስ ይደመርና ወደ መቀሌ ሲመለስ ይቀነሳል።

ወደ ለውጡ ቅጥር ግቢ ለመግባት አጥር ላይ የተንጠለጠሉ አንዳንድ የህወሀት አመራሮች እንዳሉ ይሰማል። የህዝብ ማዕበል ወደ ለውጡ ይጎትታቸውና የነባሮቹ ህወሀቶች ቁንጥጫ ይመልሳቸዋል። አጥሩ ላይ እንደተንጠለጠሉ አራት ወራት አለፋቸው። ህወሀቶች ዘይቱን ሳያዘጋጁ ሙሽራው መጥቶባቸዋል። ዘይቱ ንሰሀ ነበር። ሙሽራው ደግሞ ለውጥ። እናም ዘይቱን ያላዘጋጀ ሙሽራውን እንዴት ይቀበለው?

ባለፈው ሳምንት አንድ የናዚ የጦር ወንጀለኛ ለ70 ዓመታት ከተደበቀባት አሜሪካ ለጀርመን ተላልፎ ተሰጥቷል። በ95 ዓመቱ በእጆቹ ላይ ሰንሰለት ጠልቆ ከርቸሌ ገብቷል። በእኛም ታሪክ ተመሳሳይ ክስተት ተመዝግቧል። በቀይ ሽብር ዘመን መሪ ተዋናይ የሆኑ ነፍሰ ገዳዮች ለዘመናት ከተደበቁባቸው ሀገራት ማንቁርታቸው እየታነቀ ለፍርድ ቀርበው አይተናል። የቀልቤሳ ነገዎን እዚህ ላይ መጥቀስ ይቻላል። ከፍትህ ለጊዜው ማምለጥ ይቻል ይሆናል። ቢዘገይም ግን አይቀርም። ሞት ቢቀድም እንኳን ነፍስ ዘላለሟን እረፍት ታጣለች። መለስ ዜናዊ ለፍርድ ሳይቀርብ ቢሄድም ስሙ በምድር እየተረገመ፡ ነፍሱ በሰማይ እየተሰቃየ ነው። ከመቃብር በላይ ትቷት ያለፈው በዘር ልትበጣጠቅ ጫፍ የደረሰች ሀገር ነበረችና መለስ ከምድራዊ ፍርድ ቢያመልጥም ዘላለማዊ ስሙ የተወገዘ፡ የረከሰ ሆኗል።

ጌታቸው አሰፋ ለጊዜው ከፍትህ ተደብቋል። እንደሰማሁት በኢንተርፖል ራዳር ስር እንዲሆን እንቅስቃሴው ተጀምሯል። ወደ አሜሪካ ያሸሻቸው ቤተሰቦቹ ዘንድ ሊመጣ እንደሚችል ይገመታል። ከፎቶና ከቪዲዮ ተደብቆ ስለኖረ በቀላሉ ላይታወቅ ይችላል። ግን አያመልጥም። እየተሽሎከለከ እድሜውን ሊያቆይ እየሞከረ ነው። ከመደበኛው ፍርድ ለጊዜው ሊሸሸግ ይችላል። ከምንም በላይ ከህሊና ፍርድ አያመልጥም። በሄደበት የሚከተለው ትንሹ እግዚያብሄር የሆነው ህሊናው እረፍት ሲነሳው ይኖራል። የኢትዮጵያ እናቶች እምባስ መች በከንቱ ፈሶ ያውቅና?

ህወሀቶች ጸሀይ እየጠለቀችባቸውም የተሰጣቸውን እድል መጠቀም አልቻሉም። ወይም አልፈለጉም:: ሰሞኑን ከመቀሌ ተሰብስበው ያወጡት መግለጫ ጥርሱ አልቆበት በድዱ ለመናከስ የሚንገታገት ያረጀ አውሬ አስመስሏቸዋል። በምስራቁ በር አንዱ የጥፋት እጃቸው ተቆርጦባቸውም ለተስፋ መቁረጥ እጅ መስጠት አልፈለጉም። አብዲ ዒሌ የተሰኘ የጥፋት ፈረሳቸው አይናቸው እያየ  ከፍትህ እጅ ላይ ወድቋል። አያስመልጡት ነገር አቅም የለም። የእነሱንም እድል እጣ ፈንታ እርግጠኛ አይደሉም። ለጊዜው እድል ሰጥቶ የተዋቸውን ህዝብ ትዕግስት ግን እያስጨረሱት ነው።

ብአዴን

ብአዴን መጨረሻውን እያሳመረ ይመስላል። ከአፈጣጠሩ ጀምሮ በህወሀት ልክ የተሰፋለትን ጥብቆ አድርጎ የኖረው ብአዴን ሰሞኑን ያወጣው መግለጫ ከህወሀት ጋር የሚደረገው ፍቺ ቅርብ መሆኑን አመላካች ነው። ብአዴን ቆርጧል። የህወሀትን ቀሚስ አውልቋል። አርማና ስያሜ መቀየሩ ትርጉሙ ቀላል አይደለም። ህወሀት ብአዴንን ጠፍጥፎ ሲሰሰራ የልደት ቀኑን ከህወሀት የአፈጣጠር ታሪክ ጋር እንዲመሳሰል ስለመደረጉ መገመት ይቻላል። 11 ቁጥር ላይ የቆረበው ህወሀት የብአዴንን የልደት ቀን ህዳር 11 ላይ ያደረገው ያለምክንያት አልነበረም። አርማውን ከህወህት አርማ የተቀዳ አድርጎታል። ብአዴን አርማውን ብቻ ሳይሆን በህወሀት የተተከለትን የልደት ቀኑንም መቀየር ይኖርበታል። 

የብአዴን መግለጫ የህወህት የበላይነት ፍጻሜ ላይ ትልቅ ሚስማር የቸነከረ ነው። ኦህዴድ ታህሳስ ላይ የብሄር ጭቆና የለም የሚል አዲስ ትርክት ይዞ ሲመጣ ህወሀት የሚይዝ የሚጨብጠው አጥቶ ነበር። የመጽአት ቀኑን ያየበት አስደንጋጩ ምልክት የታህሳሱ የኦህዴድ መግለጫ ነው ማለት ይቻላል። በብሄር ጭቆና ላይ ታሪክ ፈጥሮ ስጋ ደምና አጥንት አልብሶ፡ እስትንፋስ ዘርቶበት ኢህአዴግ በሚባል ፈረስ ኢትዮጵያን ለብዙ ዘመናት ሊጋልብ የተፈናጠጠው ህወሀት በኦህዴድ መግለጫ ህልሙ በአጭሩ ተቀጭቷል።  ሲጠበቅ የነበረው የብአዴን አቋም ነበር። ሰሞኑን ብአዴንም አፈረጠው። የብአዴን መግለጫ በህወሀት አንገት ላይ የጠለቀ ገመድ ማለት ነው። የሚቀረው ገመዱን ሸምቀቅ ማድረግና ህወሀት የረገጠውን መንጠልጠያ ማንሳት ነው። አዲዮስ ህወሀት!

መግለጫው በህወሀት ህልውና ላይ ሪፈረንደም ያደረገ ነው። የአማራ ክልል ወሰን ከእንደገና ይሰመር ዓይነት አቋም ከብአዴን ሲሰማ መቼም ተአምር ነው። ይህ ማለት የወልቃይት፡ ራያና ሌሎች አከባቢዎችን በተመለከተ ብአዴን ጥያቄ ለማንሳት ወስኗል ማለት ነው። በቅርቡ በአንድ መድረክ ላይ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው የወልቃይትን ጉዳይ ከእንግዲህ ችላ የምንለው አይደለም ሲሉ ጠርጥሬአቸው ነበር። ይሀው የድርጅታቸው አቋም ሆኖ ይፋ ተደርጓል። የሱዳን ወታደሮች ከያዙት የኢትዮጵያ መሬት እንዲለቁ በብአዴን መጠየቁ ለህወሀት ትልቅ መርዶ ነው። ህወሀት ለሱዳን የኢትዮጵያን መሬት የሰጠበት ድብቅ ስምምነት የራሱ የሆነ ምክንያት አለው። ሱዳን ለህወሀት ምሽግ ናት። የክፉ ጊዜ መደበቂያ ናት። የትግራይ ህዝብ ቢከዳቸው የሚያመልጡባት ጎሬ ናት ሱዳን:: ለውለታዋ የጎንደር መሬት በስጦታ ተብርክቶላታል። ሱዳን ያን መሬት ከተነጠቀች ከህወሀት ጋር ያላትን ድብቅ ፍቅር መቀነሷ አይቀርም። ያ ደግሞ ለህወሀት የመጨረሻው ጥይት ነው። የትግራይ ህዝብ የተፋው ዕለት የሚደበቅበትን ዋሻ ያጣል ማለት ነው።

ብአዴን በግል መብት ላይ የወሰደው አቋም በራሱ ለህወሀት አስደንጋጭ ነው። በቡድን መብት ስም ዘረኝነትን በማስፋፋት የበላይነቱን አስጠብቆ ለመኖር ፕሮግራም(ህገመንግስት) የቀረጸው ህወሀት ከብአዴን በቃህ ተብሏል። የቡድን መብት እንዳለ ሆኖ የግለሰብ መብት ላይ ማተኮር ለዴሞክራሲ ወሳኝ ነው የሚል አቋም ላይ የደረሰው ብአዴን በብሄራቸው እየተደበቁ ቁማር የሚጫወቱ የዘር ፖለቲካ አቀንቃኞችንም ቅስማቸውን የሰበረ አቋም ላይ መድረሱ አስደናቂ ነው። ህወሀት በቁሙ ተዝካሩን በላና አረፈው። በዚህ አልቆመም። የህወሀትን ጥቅም በአማራው ህዝብ ኪሳራ ለማስጠበቅ በብ አዴን ውስጥ የተሰገሰጉ አፍቃሪ ህወሀት የሆኑ ቀንደኛ አመራሮችን ጠራርጎ ማባረር የጀመረው ብአዴን ለህወሀት አንድ መልዕክት እንዲደርሰው የፈለገ ይመስላል። ''በቃ''

በረከተ መርገምት

አቶ በረከት ስምዖን አየሩን ተቆጣጥሮታል። የመንደር የኮሚኒቴ ሬዲዮ ሳይቀር ደጅ እየጠና እንዳለም ሰምቼአለሁ። ብዙ ሰዎች በረከት ሰሞኑን የሰጠው ቃለመጥይቅና አብሮት ከተባረረው ታደሰ ጥንቅሹ ጋር የጻፉት ደብዳቤ ላይ በማተኮር የበረከት ቅጥፈቶች ላይ ጊዜ ሰጥቶ ሲወያዩ ታዝቤአለሁ። ለእኔ በረከት እንዲህ ተዝረክርኮ፡ በስጋት ተንጦ፡ ቅስሙ ተሰብሮ፡ የሚደገፍበት አጥቶ፡ ሲንከራርተት እንደማየት የሚያስደስት ነገር አላየሁም። ከሰሜን ጫፍ እስከ ደቡብ፡ በምዕራብና ምስራቁ እየተወነጨፈ ያሻውን ሲያደርግ፡ ሲያስገድልና ሲያሳስር የከረመ፡ ምድር አልበቃ ብላው በሰማይ መንሳፈፍ እስኪቀረው የደረሰ፡ ኢትዮጵያዊነትን ለማጥፋት ረጅሙን ርቀት የተጓዘ ሰው ዘመን ተገልብጦ፡ በሰፈረው ቁና የሚሰፈርበት ጊዜ መጥቶ ''እንዳልንቀሳቀስ ገደብ ተጥሎብኛል'' ዓይነት እዬዬውን ሲያስነካው እንደመስማት ያለ ምን ድል ይገኝ ይሆን? እንደዚያ በትዕቢት ተወጥሮ የሚታወቀው በረከት ኩምሽሽ ብሎ፡ በፍርሃት ርዶ የምቆም የምቀመጥበት አጣሁ ሲል መስማት ለእኔም ሆነ የፍትህን መረጋገጥ ሲናፍቁ ለነበሩ ኢትዮጵያውያን ትልቅ ድል ነው።

በረከትን ሳስበው ሁል ጌዜ ከአእምሮዬ ጓዳ ብቅ የሚለው አንድ ወቅት ፕ/ር መስፍን ወልደማርያም ስለበረከት የተናገሩት ነው። ''መለስ ክፉ ነው። መለስን የበለጠ ክፉ ያደረገው ደግሞ በረከት ስምዖን ነው'' እንግዲህ የክፋት አለቃ፡ የጭካኔ ደቀመዝሙር፡ የተንኮል ሀዋሪያ፡ የቅጥፈት አምባሳደር የሆነው በረከት ስምዖን ጊዜ ጥሎት፡ ዘመኑ አብቅቶ ዋጋውን ሊያገኝ ነው። በየሚዲያው ቀርቦ ''ቅዱስ ነበርኩ፡ ክንፍ የሌለው መላዕክ ከእኔ በላይ የት ይገኛል?'' ዓይነት የሌባ አይነደረቅ ዲስኩሩን እየለቀቀው ነው።  በረከት ብአዴኖች ላይ የጀመረው ውግዘት አፈጣጠሩንና ስነልቦናውን እንድንመራመርበት የቤት ስራ የሚሰጠን ሆኗል። ምድር የተጠየፈችው፡ በእኩይ ምግባሩ ሀገርና ህዝብ በአንድ ሰልፍ ፊት የነሳው ሰው፡ ከደሙ ንጹህ ነኝ የሚል መፈክር ይዞ መልሶ ለእኛው ልንገራችሁ ማለት የጤና አይመስለኝም። የሚቀርቡት ወዳጆች ካሉት በጊዜ ዶክተሩን እንዲጎበኝ ቢመክሩት ጥሩ ነው። ጤናም እንዳልሆነ በብዙ ይነገርለታል።

በዘመኑ በሀሳብ የተለዩትን በጭካኔ አስሯል። የፖለቲካ ተቀናቃኝ ያላቸውን የሀሰት ዶሴ እየከፈተ ከእድሜአቸው ላይ ተቀንሶ በማጎሪያ እስር ቤት እንዲሰነብቱ አድርጓል። መለስ ሲሞት ለቅሶን በሀገር ደረጃ አደራጅቶ፡ ማቅ አስለብሶ፡ ህዝቡን በማህበር እንዲያዝን በማድረግ ታላቅ ግፍ የፈጸመ ወንጀለኛ ነው። በረከት በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ጥቁር ስም ያለው ነው። ዛሬ ''በነጻነት፡ በፖሊሲ'' እንከራከር ሲል አለማፈሩ ይገርማል። ዛሬ እሱ የሚጠይቀውን መብት ትላንት የጠየቁትን ሲያዋርድ፡ የቴሌቪዥን ድራማ እያሰራ ስም ሲያጨቀይና ገፍቶም ሲያሳስርና ሲያስገድል ዓለም የሚያውቀው ሰው ዛሬ ተነስቶ ''በፖሊሲ እንከራከር'' ብሎ አይኑን በጨው አጥቦ መጥቷል። እንግዲህ 'ፍትህ' ለዚህ ሰውዬም ያስፈልጋል።

በረከትን 'ኢትዮጵያዊው' ጎብልስ በሚል የሚጠቅሱትም አሉ። የናዚው የፕሮፖጋንዳ ማሽን ጆሴፍ ጎብልስ ''ውሸት ሲደጋገም እውነት ይሆናል'' የሚለውን አስቀያሚ ትርክት ለዓለም ያስተዋወቀ፡ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት በዚሁ ትርክቱ የናዚን ወታደሮችና የጀርመንን ህዝብ ለጦርነት የማገደ እንደነበረ ይነገርለታል። በረከት ስምዖን የዘመኑ ጎብልስ ሆኖ ኢትዮጵያውያን ላይ ተሰይሟል። ሀገሪቱን የውሸት ፋብሪካ አድርጓት አንድ ትውልድ በውሸት ተወልዶ እንዲያድግ ፈርዶበታል። በእርግጥ በናዚው ጎብልስና በህወሀቱ ጎብልስ መሀል ልዩነት አለ። ጎብልስ የቆመለት የናዚ ስርዓት ሲገነደስና እንደአምላክ የሚያየው አዶልፍ ሂትለር ራሱን ሲያጠፋ ጎብልስም ስድስት ልጆቹን መርዝ አብልቶ እሱንና ሚስቱንም በሽጉጥ ገድሎ ይህቺን ምድር ተሰናብቷል። በረከት ስምዖን ግን ፈሪ ነው። አምላኩ መለስ ዜናዊ ሞቶም እሱ እስከአሁን አለ። ወንድሙን ገድሎበት እንኳን በታማኝነት የገበረለትና የተገዛለት የህወሀት ስርዓት በቁሙ ሲገነደስ እያየ በረከት ግን መኖር ይፈልጋል። ፈሪ። መርገምት።

እኔ በእሱ ቦታ ብሆን የክብር ሞቴን በገዛ ፍቃዴ እውን አደርጋለሁ። ሰው እንዴት ሳር ቅጠሉ ሳይቀር ጠልቶት፡ እዚህም እዚያም ቤተክርስቲያን እንደገባች ድመት እየተባረረ መኖርን ይመርጣል? በረከት ስምዖን ለፍርድ ቀርቦ ማየት እፈልጋለሁ። በየሚዲያው የሚለውን ለመስማት ጊዜም አፕታይቱም የለኝም። በረከት የሚነግረኝ የማላውቀው የለም። እሱ ዘንድ ለእኔ የሚጠቅም መረጃም ሆነ እውቀት ይኖራል ብዬ አላምንም። በረከት የውሸት አቁማዳውን ይዞ በየሚዲያው ደጅ እየጠና ነው። የክፋት መርዙን አሁንም ለመርጨት ታጥቆ ተነስቷል። በረከት የክፋት አቅሙ አልደከመም። ለብአዴን ከታደሰ ጥንቅሹ ጋር በጻፈው ሀሜት መሰል ደብዳቤ ላይ ለማ መገርሳንና ገዱ አንዳርጋቸውን ለማጋጨት ይሞክራል። እናም ሚዲያዎች ይህን ሰው ሲያገኙት መርዙን ረጭቶ ብቻ እንዲሄድ ባይፈቅዱለት ጥሩ ነው። ነፍሱ እስኪላቀቅ የሚጠይቅ በመረጃና ማስረጃ በረከትን ራቁቱን የሚያስቀር እንጂ የበረከትን ዲስኩር እንደወረደ የሚያስተናግድ ሚዲያ ለጊዜው አያስፈልገንም። በረከት በቃው!
(Mesay Mekonnen)

Dienstag, 7. August 2018

ታሪክ (ጋዜጠኛ ፋሲል የኔዓለም)

ታሪክ (ጋዜጠኛ ፋሲል የኔዓለም)

ነሃሴ 7, 2018 ነጻነት freedom

የአንድ ጀግና ወታደር ታሪክ
የዛሬ 5 አመት ገደማ ነው፤ አንድ መረጃ ያቀብለን የነበረ መኮንን ደጋግሞ ስልክ ይደውልልኛል፤ ስራ እንደጨረስኩ ደወልኩለት። ሰላም ነው አንበሳው። “ምን ሰላም አለ፤ ስልኩን አላነሳ ስትል ሳልሰናበተው ልቀር ነው እያልኩ ቆጭቶኝ ነበር፣ ስልክህ ሲጠራ እንዴት እንደተደስትኩ አትጠይቀኝ” አለኝ። ይቅርታ ስራ በዝቶብኝ ነው፣ ልትዛወር ነው እንዴ አልኩት። “ እረዳሃለሁ ፋሲሎ፣ ለማንኛውም ጠፍቼ እየሄድኩ ነው፣ የት እንደምሄድ ግን አላውቅም፤ ዛሬ ያየሁትን ነገር ህሊናዬ ሊሸከመው አልቻለም” ። ቆይ ምን ተፈጠረ? “ምን ያልተፈጠረ ነገር አለ፣ እናቶችንና ህጻናትን በጠራራ ጸሃይ ጨረሷቸው፣ እናቶችን ሳይ እናቴ ትዝ አለችኝ”፣ ድምጹ ተቆራረጠ። ወታደር የሚያለቅስ አይመስለኝም ነበር፤ አይዞህ አይዞህ እያልኩ አጽናናሁት። ምንድነው የሆነው እስኪ ተረጋግተህ ንገረኝ አልኩት። “ዛሬ ጠዋት ኦብነግ አንድ መንደር ውስጥ ገብቷል ተብለን ግዳጅ ወጥተን ነበር፤ የክልሉ ልዩ ሃይል አባላት እኛን እየመሩ ወሰዱንና ቦታው ስንደርስ ኦብነጎች ማምለጣቸውን ሰማን፤ ከዚያ በሁዋላ ህዝቡን ማሸበር ተጀመረ፣ እናቶች አትግደሉን እያሉ ተገደሉ፣ ህጻናት መሸሸጊያ ፍለጋ ሲራወጡ ፊት የተገኙት ሁሉ ተገደሉ፣ ወጣት የሚባል የለም፣ አሮጊቶችና ሴቶች ናቸው ታጨዱ፣ ምን ልበልህ፣ መፈጠርክን ትጠላለህ፤ ያየሁትን ለመግለጽ አልችልም፤ ከእንግዲህ ወዲያ ከዚህ ሰራዊት ጋር መቀጠል አልፈልግም ፣ እነሱ ወደ ፊት ሲሄዱ እኔ ጠፍቼ መንገድ ጀምሬያለሁ።” መኮንኑ በስሜት ውስጥ ሆኖ ሲገልጸው የነበረው እና እኔ ከአመታት በሁዋላ ስጽፈው ያለውን ልዩነት እያስተዋልኩ ተናደድኩ። እንደ ዛሬ የደራሲነት ተሰጥዖ እንዲኖረኝ ተመኝቼ አላውቅም።

ስሜትን ዋጥ አደርኩና፣ ለመሆኑ የት ነው የምትሄደው አልኩት። “አላውቅም ኦጋዴንን ታውቀዋለህ፣ ምደረበዳ ነው፤ ከተሳካላኝ ጅቡቲ ወይም ሶማሊያ ልገባ እችላለሁ፤ ምናልባትም በኦብነግ ወይም አልሸባብ እጅ ልወድቅ እችላለሁ፣ የእኛ መከላከያዎች ካሉበት በተቀራኒ አቅጣጫ ነው የምጓዘው። እነሱ እንዲይዙኝ አልፈግልም፤ ከተያዝኩም ምን እንደሚያደርጉኝ አውቃለሁ፣ በእነዚህ ዘረኞች እጅ ላይ ከምወድቅ ኦብነግ ወይም አልሸባብ ቢገድለኝ እመርጣለሁ፤ አሁንማ አያተርፉኝም፤ የሚይዙኝ ከሆነ ግን እራሴን አጠፋለሁ።” ወንድሜ ስማኝ፣ “ አሁን ወደ ቦታህ ተመለስ፣ አሞኝ ነው ወደ ሁዋላ የቀረሁት በላቸው፣ ሌላ ጊዜ አዘናግተህ ትጠፋለህ፣ እኔ ራሴ መንገድህን አመቻችልሃለሁ፣ በፍጹም ወደማታውቀው ቦታ አትሂድ…” እያልኩ ላሳምነው ሞከርኩ። “አላደርገውም፣ የእኔ ነፍስ ካለቁት እናቶችና ህጻናት ነፍስ አይበልጥም። አሁን ባትሪዬን አትጨርሰው፤ የሆነ ቦታ ላይ በሰላም ከደረስኩ ቁጥርህን በቃሌ ስለያዝኩት እደውልልሃለሁ፤ መንገድ ላይ ከቀረሁም ቻው፤ በርታ፣ በጣም አከብርሃለሁ፤ ኦጋዴን ውስጥ የተፈጸመውን ታሪክ በዝርዝር የምናገርበት እድሜ እንዲሰጠኝ ጸልይለኝ ” ብሎኝ፣ እኔም እንደምንም ስሜቴን ዋጥ አድርጌ መልካሙን ሁሉ ተመኝቼ ስልኩን ዘጋሁት። ዛሬም ድረስ ያ ጀግና ወታደር ይደውል ይሆን እያልኩ ስልኩን በጉጉት እጠብቃለሁ። ከተለያየን ከ3 ዓመታት በሁዋላ ቁጥሬን የቀየርኩ በመሆኔ አዲሱ ቁጥሬ ላይኖረው ቢችልም፤ በ3 ዓመታት ውስጥ ለእሱ በሰጠሁት ቁጥር ደውሎልኝ አያውቅም።
ወዳጄ፣ በአንድ ወቅት በብሄራቸው የሚያስቡ አዛዦች የሞሉበት ሰራዊት ተቀይሮ ህዝባዊነትን ሲላበስ ቢያይ ኖሮ፣ ምንኛ ደስ ባለኝ፤ እሱና መሰሎቹ ይህ ቀን እንዲመጣ ስንትና ስንት መስዋትነት መክፈላቸውን አፍ ቢኖረው ኖሮ የውቅሮ እስር ቤት በዝርዝር ያጫውተን ነበር።

https://netsanetlegna.wordpress.com/2018/08/07/%e1%8b%a8%e1%8a%a0%e1%8a%95%e1%8b%b5-%e1%8c%80%e1%8c%8d%e1%8a%93-%e1%8b%88%e1%89%b3%e1%8b%b0%e1%88%ad-%e1%89%b3%e1%88%aa%e1%8a%ad-%e1%8c%8b%e1%8b%9c%e1%8c%a0%e1%8a%9b-%e1%8d%8b%e1%88%b2%e1%88%8d/

Mittwoch, 4. April 2018

ቀጣዬ 100 ቀናት! (በኤርሚያስ ለገሰ)

ቀጣዬ 100 ቀናት!

መንደርደሪያ

የትግራይ ነፃ አውጪ በገጠመው ሕዝባዊ ማእበል፣ እንዲሁም የሕዝቡን ተቃዉሞ በተከተለበት ጫና ዶክተር አቢይን ወደ ጠቅላይ ሚኒስትርነት አምጥቷል። የዶክተር አቢይ ወደ ፊት መምጣት በብዙ መልኩ የተደበላለቀ ስሜቶችን ፈጥሯል። በህውሓት ደጃፍ ከፍተኛ ቁዘማና ንዴት የፈጠረ ሲሆን በለውጥ ፈላጊው ዘንድ የተከፋፈለ አስተያየቶች በመስተናገድ ላይ ናቸው። በተለይም ዶክተሩ በበአለ ሲመቱ እለት ያቀረበው ንግግር የብዙ ኢትዬጲያውያንን አንጀት ቅቤ ያጠጣ ነበር። በታሪካዊነቱም ተመዝግቧል።

በአጭር ጊዜ ውስጥ በስልጣን ኮርቻው ላይ የወጣው ዶክተር አቢይ እጅግ ውስብስብ የሆኑ ችግሮችን ለመፍታት፣ መንፈሱ የተበታተነውን የኢትዬጲያ ህዝብ ለማረጋጋት፣ ኢትዬጲያን ወደ ፊት ሊያራምዱ የሚችሉ ሁሉንም ኃይሎች ለማስተባበር፣ የኢኮኖሚ እና ፓለቲካ እቅዶችን ለማስተዋወቅ ጥረት አድርጓል።

ይህንም ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቀጣይ ቀናት ወደ ተግባር ሊመነዝራቸው ይገባል የተባሉ ስፍር ቁጥር የሌላቸዉ ድርጊቶች መዘርገፍ ጀምረዋል። ሰውየው ለወደፊቱ ያለበትን ተልእኮ የሚያሳስበውም ብዙ ነው። እኔም እንደ አንድ ኢትዬጲያዊ ዶክተር አቢይ በኦሮሚያ የጀመረውን ስራ ሳይጨርስ ወደ ፌዴራል መምጣቱ ልቤ አልተቀበለውም። ተቃውሞዬን በአደባባይ ገልጫለሁ። በጠላቶቹ ሜዳ ላይ ከመጫወቱ በፊት የራሱን ሜዳ በብረት እንዲያጥረው ፍላጐቴ ነበር።

አሁንም ቢሆን ከትላንት አቋሜ የተለወጠ ነገር የለኝም። በስልጣን ላይ ያለው ሽፍታ አገዛዝ አሁንም የስለላና ወታደራዊ መዋቅሩን የተቆጣጠረው ነው። ወደድነውም ጠላነውም የኢኮኖሚ መዋቅሩን የተቆጣጠረው ይህ ከፋፋይ ቡድን ነው። ሌላው ቀርቶ የአሁኖቹ የዶክተር አቢይ የግልና የቤተመንግስት ጠባቂዎች የሟቹ መለስ ዜናዊ ጠባቂዎች ናቸው።

በመሆኑም ሰውየው በአምባገነኖች፣ በዘረኞች፣ በማይማን፣ ኢትዬጲያን በሚጠሉና በሚያሳፍሩ ሰዎች መዳፍ ውስጥ መግባቱን ስመለከት መንፈሴ ይረበሻል። የትግራይ ነፃ አውጪ ካድሬዎች እና ባለሟሎች እንዳይሰራ መውጪያ መግቢያውን እንደሚዘጉበት ሳውቅ ልቤ ይደማል። በፈላ ውሃ እንደምትቀቀለው እንቁራሪት እየሆኑ ያሉት ህውሓቶች የተካኑበትን አጥፍቶ መጥፋት ፓሊሲ እንዳይፈፅሙበት እሰጋለሁ።

በሌላ በኩል አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ለኢትዬጲያ ህዝብ ያቀረበው ራዕይ አስደስቶኛል። የኢትዬጲያ ተስፋና የኢትዬጲያችን መቀጠል ሲያስጨንቀው አብሬ ተጨንቄያለሁ። ዶክተር አቢይ የሕዝብ አሽከር ሆኖ ሕዝብን ለማገልገል ቆርጦ መነሳቱን ሳይ በምን ልደግፈው እችል ይሆን የሚል ጥያቄ አንስቻለሁ። የጠላት ሜዳ ላይ አሸንፎ ለመውጣት እንዴት ቢጫወት ያዋጣዋል የሚለውን አስቤያለሁ።

እናም ዶክተር አቢይ የኢትዬጲያ ህዝብ ትግልና እምቢተኝነትን እንደ ነዳጅ እየወሰደ የተቆጠረ ግቦችን በተቆጠረ ጊዜ ቢፈፅም አሸናፊ ሆኖ ሊወጣ ይችላል። ባለፈው መጣጥፌ በተራዘመ ጊዜ ሊፈፅማቸው የሚችሉትን አላማዎች ጠቆም አድርጌ ነበር። ለዛሬው በመቶ ቀናት ሊፈፅማቸው ይገባል ያልኳቸውን የአደረጃጀትና የፓለቲካ ግቦች ጠቁሜያለሁ። እነዚህ አራት ግቦችና በስራቸው ያሉ የተቆጠሩ ተግባራት ከአረጃጀት፣ በመንግስትና በፓርቲ መካከል መኖር ስለሚገባው ግንኙነት፣ ስልጣንን እና ሌብነትን እንዲሁም የዲሞክራሲ እሴቶችን ለመገንባት የተዘረዘሩ ናቸው። ግቦቹና ዝርዝር ተግባራቱ ያለቀላቸው ሳይሆኑ ለውይይት መነሻ ሆነው የሚያገለግሉ ናቸው።
                    ***

        ##ግብ አንድ:-

  በሕገ መንግስቱ መሰረት በኢትዬጲያ ህዝብ አመኔታ እና ተቀባይነት የላቸውን በመለየት የሚኒስትሮች ምክር ቤትና ሌሎች ከፍተኛ የስልጣን እርከኖች ማዋቀር።
             *

    #የግብ አንድ ተግባር አንድ:-

ሕገ መንግስቱ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከህዝብ ተወካዬች ምክር ቤት አባላት እና ከምክር ቤት አባላት ውጪ ሚኒስትሮችን በመመልመል በፓርላማው ያፀድቃል በሚለው መሰረት እጩዎችን ከሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች መመልመል።
             *

     #የግብ አንድ ተግባር ሁለት፣

ከተመለመሉት ውስጥ በብቃታቸው፣ በስነምግባራቸውና ተቀባይነታቸው የላቁትን ለሽግግር ጊዜው በሚኒስትርነት መመደብ። በዚህ መሰረት የሚከተሉት ግለሰቦች ለሽግግር ጊዜው ለእጩነት ቢቀርቡ በምክረ ሃሳብ የቀረቡ ናቸው፣

° ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርነት: አቶ ደመቀ መኮንን
° ውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነት:  ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና
° ኢኮኖሚና ፋይናንስ ሚኒስትር: አቶ ስዩም ተሾመ
  ° ፍትሕ ሚኒስትር: አቶ ተማም አባቡልጋ
  ° ደህንነት ሚኒስትር: አቶ ገዱ አንዳርጋቸው
° ኮሙዩኒኬሽን ሚኒስትር:  አቶ ንጉሱ ጥላሁን
  °የአገር ደህንነት ሚኒስትር:  አቶ አንዷለም አራጌ
  ° ገቢዎች ሚኒስትር: - አቶ አስራት አብርሃም
° አርብቶ አደር ሚኒስትር:  ዶክተር አብርሃ ተከስተ
° መገናኛ ሚኒስትር: አቶ የሺዋስ አሰፋ
  ° መከላከያ ሚኒስትር : አቶ በቀለ ገርባ
° ትምህርት ሚኒስትር:- አቶ ሬድዋን ሁሴን
° አሳ ሐብት ሚኒስትር: ወ/ት ፈትለወርቅ ገብረእግዚአብሔር
° የጡረታ ሚኒስትር: አቶ አስመላሽ ወልደስላሴ ( አባይ ነብሶ)
° ቱሪዝም ሚኒስትር:- ዶክተር አዲሳለም ባሌማ
  ° የኢንቨስትመንት ሚኒስትር:- አቶ ግርማ ሰይፉ
  ° ወጣቶች ሚኒስትር: - አብርሃ ደስታ
   ° ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር: - አርቲስት አስቴር በዳኔ
   ° ኤታማዦር ሹም: - ጄነራል ተፈራ ማሞ
   ° ፌዴራል ፓሊስ ሹም:- ኮረኔል ደመቀ ዘውዴ
   ° ሴቶችና ህፃናት ሚኒስትር:- ወይዘሮ የትነበርሽ
  ° የጽህፈት ቤቱ ሚኒስትር:- አቶ ደግፌ ቡላ
   ° የንግድ ሚኒስትር:- ተስፋዬ በጅጋ
  ° የግብርና ሚኒስትር: - አቶ ሲራጅ ፈርጌሳ
                   * 

         #ግብ አንድ ተግባር ሁለት፣

የመንግስት የልማት ድርጅቶች፣ ኮርፓሬሽን፣ ባለስልጣናት እና ተቋማት ስራ አስኪያጅ፣ ዋና ስራ አስፈፃሚና ዴሬክተሮች ሹመት የየትኛውም የፓለቲካ ድርጅት አባላት ካልሆኑ ኢትዬጲያውያን ውስጥ ብቃት ያላቸውን መሾም። መመዘኛዎቹ በሚዲያ ተቋማት በግልፅ እንዲነገሩ ማድረግ። ሂደቱን ሕዝቡ በቀጥታ በሚከታተለው መልኩ እና ተወዳዳሪዎች ተቋማቱን እንዴት እንደሚመሩ እና የት ማድረስ እንደሚፈልጉ በሚገልፁበት ሁኔታ እንዲፈፀም ማድረግ። በውጭ የሚኖሩ ከፍተኛ ሙያተኛ የሆኑ ኢትዬጲያውያን እና ትውልደ ኢትዬጲያውያን የውድድሩ አካል እንዲሆኑ ማድረግ።

ከእነዚህ የስልጣን ቦታዎች መካከል ዋና ዋናዎቹ የሚከተሉት ይሆናሉ፣

• የብሔራዊ ባንክ ገዥ
• የልማት ባንክና ንግድ ባንክ ዋና ስራ አስፈፃሚ
• የኢትዬጲያ መድን ድርጅት
• የኢትዬጲያ አየር መንገድ
• የኢትዬጲያ ቴሌ ኮሙዩኒኬሽን
• የመንግስት ሆቴሎች
• የኢትዬጲያ ቴሌቪዥን እና ሬዲዬ
• የመንገዶች ባለስልጣን
• ምርት ገበያ ( ECX)
• ዋና ኦዲተር ጄኔራል
• ሁሉም የአምባሳደርነት ቦታዎች
• አደጋና ዝግጁነት ዴሬክተር ( አመዝኮ)

               *
   #የግብ አንድ ተግባር ሶስት:-
በመንግስት በጀት የሚተዳደሩ አላስፈላጊ የሚኒስቴር መስሪያቤቶች፣ ባለስልጣናት ፣ ተቋማት እና የሐላፊነት ቦታዎችን ማፍረስ። ከእነዚህ ውስጥ ቅድሚያ የሚሰጣቸው፣
• ፌዴራል ጉዳዬች ሚኒስትር
• የመንግስት ዋና ተጠሪ ፅህፈት ቤት
• የብሮድካስት ባለስልጣን
• የኢትዬጲያ ዜና አገልግሎት እና ፕሬስ ድርጅት
•  የእምባ ጠባቂ ኮሚሽን
• የሰብአዊ መብት ኮሚሽን
• ምርጫ ቦርድ
• የብረታ ብረት ኮርፓሬሽን ( ሜቴክ)
•  ብሔራዊ መረጃ መረብ ደህንነት ኤጀንሲ(ኢንሳ)
• የፓሊሲ ምርምር፣ ጥናትና አማካሪ ቢሮ

                *
    #የግብ አንድ ተግባር አራት፣

ጠቅላይ ሚኒስትሩን በቋሚነት የሚያሟክሩ በኢትዬጲያ ሕዝብ ተቀባይነት ያላቸው ከ25 እስከ 30 የሚጠጉ ምስጉን የአገር ሽማግሌዎች፣ የሐይማኖት አባቶችና አገራችንን በአለም ደረጃ ያስተዋወቁ አባላት የያዘ “ አማካሪ ምክር ቤት” ማቋቋም።
• አማካሪ ምክርቤቱ በሁለት ሳምንት አንዴ ( ቅዳሜ ከሰአት) ለግማሽ ቀን የሚሰበሰብ ይሆናል።
•  አማካሪ ምክር ቤቱ ዋነኛው ተልእኮ የሽግግር ሂደቱን ለማፋጠን ድልድይ ሆኖ የሚያገለግል ይሆናል። የፓለቲካ ፓርቲዎችን ድርድር በይፋና በሚስጥር ያደርጋል። ፓርቲዎቹ የሚያቀርቡትን የሽግግር ሰነድ እየመረመረ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ያቀርባል። የዲሞክራሲ ተቋማት ተአማኒነት ባለው መልኩ የሚዋቀሩበትን ሐሳቦች በማመንጨት ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ያቀርባል።

• የአማካሪ ምክር ቤት አባላት የገዥው ፓርቲ አባላትም ሆነ ደጋፊዎች መሆን የለባቸውም።

• ለአማካሪ ምክር ቤት አባልነት ለመነሻ እንዲሆን አቶ እየሱስ ወርቅ ዛፋ፣ አቶ ቡልቻ ደመቅሳ፣ ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ፣ አቶ ክቡር ገና፣ ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ፣ አቶ ገብረየስ ቤኛ፣ ዶክተር ዳኛቸው አሰፋ፣ ዶክተር በድሉ ዋቅጅራ፣  አቶ አርአያ ገ/ እግዚአብሔር፣ አቶ ገብሩ አስራት፣ ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም፣ ዶክተር ያዕቆብ ሐይለማርያም፣ ዶክተር በፍቃዱ ደግፌ፣ አርቲስት አሊ ቢራ፣ አርቲስት ቴዎድሮስ ካሳሁን፣አርቲስት አረጋኸኝ ወራሽ፣ አትሌት ሐይሌ ገብረስላሴ፣ አቶ አስገደ ገ/ ስላሴ፣ አቶ ገብሩ ገብረማሪያም፣ አቶ ቆስጠንጢኖስ በርሄ፣ ፕሮፌሰር ፍቅሬ ቶሎሳ የመሳሰሉት አባል የሚሆኑበት ይሆናል።
                  *

#የግብ አንድ ተግባር አምስት፣

የቀድሞ የሕውሓት/ ኢህአዴግ ባለስልጣናትን በሶስት ዙር በጡረታ ማሰናበት። ከጡረታ በኃላ በየትኛውም የሚዲያ ተቋም ፣ብሔራዊና ድርጅታዊ በአላት፣  ስብሰባዎች፣ ምርቃቶች እንዳይገኙ ማድረግ። አቶ ተፈራ ዋልዋ ልምዱን እንዲያካፍላቸው መድረክ ማዘጋጀት። በመጀመሪያው ዙር የሚሰናበቱት አቶ ስዩም መስፍን፣ አቶ በረኸት ስምኦን፣ አቶ አርከበ እቁባይ፣ አቶ ስብሃት ነጋ፣ አቶ አባይ ፀሀዬ፣ አቶ ግርማ ብሩ፣ ዶክተር ካሱ ኢላላ ፣ ኩማ ደመቅሳ ፣ አዲሱ ለገሰ፣ ሳሞራ የኑስ፣ ጌታቸው አሰፋ፣ አለማየሁ ተገኑ ይሆናሉ።
               ***

        #ግብ ሁለት፣
የመንግስት እና ፓርቲ ስራ እንዲለያዩ ማድረግ። ፓርቲ መንግስትን ተክቶ አመራር አይሰጥም። መንግስት በቀጥታ በፓርቲው እየተመራ አመራር አይቀበልም።
            *

#የግብ ሁለት ተግባር አንድ፣

የመንግስት አካላት የሚከተሉትን አጠቃላይ የፓለቲካ፣ የኢኮኖሚ፣ የማህበራዊና የባህል ፓሊሲዎች የሚቀየሱት በሚኒስትሮች ምክር ቤት ብቻ ይሆናል።
              *

  #የግብ ሁለት ተግባር ሁለት፣

በሕዝብ ምርጫ ከሚደራጁ ምክር ቤቶችና ካቢኔዎች ( እስከ ቀበሌ) ውጭ የሚሞሉ የመንግስት ሐላፊነት ቦታዎች የየትኛውም የፓለቲካ ፓርቲ አባል ያልሆኑ ኢትዬጲያውያን እንዲያዝ ማድረግ።
                *

#የግብ ሁለት ተግባር ሶስት፣

በሲቪል ሰርቪስ ውስጥ ተቀጥረው የሚሰሩ ሰራተኞችም ሆነ በቀጣይ የሚቀጠሩ ሰራተኞች የትኛውም የፓለቲካ ፓርቲ አባል እንዳይሆኑ ማድረግ። በሲቪል ሰርቪስ ውስጥ እየሰሩ አስቀድሞ አባል የሆኑ ሲቪል ሰርቫንቶች ለነበሩበት ፓርቲ በይፋ መልቀቂያ እንዲያስገቡ ማድረግ። የፓርቲ መልቀቂያ ለማስገባት ፍቃደኛ ያልሆኑ የመንግስት ሰራተኞች በፍቃደኝነት ስራቸውን እንዲለቁ ማድረግ።
          *

#የግብ ሁለት ተግባር አራት፣

በመንግስት የስራ ሰአት፣ በመንግስት ፅህፈት ቤት ውስጥ የየትኛውም የፓለቲካ ድርጅት የፓለቲካ ስራ( ማደራጀት፣ መሰብሰብ፣ ካድሬ መመልመል) እንዳይካሄድ ማድረግ። የመንግስት ንብረት ለመንግስት ስራ ብቻ ማዋል። ይሄን ተላልፎ የሚገኝ ማንኛውም ሰራተኛ ከስራ እንዲሰናበት እና የትኛውም የመንግስት መስሪያ ቤት በድጋሚ እንዳይቀጠር ማድረግ።

                      *
#የግብ ሁለት ተግባር አምስት፣

በዩንቨርስቲዎች፣ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት፣ቴክኒክና ሙያ እንዲሁም በአንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ማንኛውም የፓለቲካ ፓርቲ በይፋም ሆነ በግልፅ የድርጅት ስራ ( ምልመላ፣ ማደራጀት፣ ስብሰባ፣ መሰረታዊ ድርጅት) የመሳሰሉትን እንዳይሰራ ማድረግ። የትምህርት ተቋማቱ አመራሮች ምደባ የፓለቲካ ፓርቲ አባል አለመሆንን እንደ ቅድመ ሁኔታ በመውሰድ መመዘኛው ብቃት እና ብቃት ብቻ እንዲሆን ማድረግ። በየትኛውም ደረጃ ያሉ መምህራት እንደ ሲቪል ሰርቪስ ሰራተኝነታቸው ከየትኛውም የፓለቲካ ድርጅት አባል አይሆኑም። ህሊናቸው ካልፈቀደ በፍቃደኝነት ስራቸውን እንዲለቁ ይደረጋል።
             ***

         # ግብ ሶስት፣
ስልጣን የሐብት ምንጭ የማይሆንበት ሁኔታ መፍጠር።
                  *

#የግብ ሶስት ተግባር አንድ፣

ሚኒስትሮች፣ ምክትል ሚኒስትሮች፣ ዋናና ምክትል ስራ አስፈፃሚዎች፣ ስራ አስኪያጆች፣ ዴሬክተሮች፣ መምሪያ ሐላፊዎች፣አምባሳዳሮች፣ ዲፕሎማቶች፣ ከኮረኔል እስከ ጄኔራል ባለ ማእረግ የጦር አዛዦች ንብረታቸውን በመመዝገብ ለሕዝብ ይፋ ማድረግ። የወር የገቢና ወጪ መጠናቸውን፣ የልጆች ትምህርት ቤት ወጪ ወዘተ በምዝገባው እንዲካተት ማድረግ። ለምዝገባ ፍቃደኛ የሆኑትን እና ለመደበቅ ጥረት የሚያደርጉትን ለሕዝብ በማጋለጥ ለህግ ማቅረብ። በአርአያነት ጠቅላይ ሚኒስትሩ እና የካቢኔው አባላት በአንድ ወር ውስጥ ንብረታቸውን ይፋ እንዲያደርጉ ማድረግ።
                *

#የግብ ሶስት ተግባር ሁለት፣

በግብ ሶስት ተግባር ሁለት የተገለጡት ባለስልጣናት ከአንድ በላይ የቦርድ አመራርም ሆነ የቦርድ አባል እንዳይሆኑ ማድረግ። በቦርድ የሚተዳደሩ ተቋማት ውስጥ ቢያንስ ሁለት ከተፎካካሪ ፓርቲ፣ አንድ ከባለስልጣንም ሆነ ከሲቪል ሰራተኛ ውጭ ማድረግ። በቦርድ ውስጥ የማገልገል ስራ በፍላጐትና ያለምንም ክፍያ እንዲሆን ማድረግ።
            *

#የግብ ሶስት ተግባር ሶስት፣

በግብ ሶስት ተግባር ሁለት የተጠቀሱት ባለስልጣናት የቅርብ ዘመዶች ባለቤት የሆኑበት ቢዝነስ ከባለስልጣኑ ስራ ጋር በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የሚገናኝ ከሆነ ባለስልጣኑ ሐላፊነቱን በፍቃደኝነት እንዲለቅ አሊያም ሌላ ቦታ ተዘዋውሮ እንዲያገለግል ማድረግ። በተጨማሪም ባለስልጣናቱ ከመንግስት ተቋማት ውጪ ባሉ ድርጅቶች የቦርድ አባልነትም ሆነ የአማካሪነት ስራ መስራት አይችሉም።
              *

#የግብ ሶስት ተግባር አራት፣

የፓለቲካ ፓርቲዎች የሚያስተዳድሩት ንብረትም ሆነ ቢዝነስ እንደማይኖራቸው በሕጉ የተገለፀውም ተፈፃሚ ማድረግ። በዚህ ሕግ መሰረት የኤፈርት፣ የትልማ፣ ረስት፣ ጥረት፣ ዲንሾ፣ ወንዶ ንብረቶች ለግል ባለሀብት እንዲሸጡ ማድረግ። ከሽያጭ የሚገኘውን ገቢ ለአንደኛ ፣ሁለተኛና ዩንቨርስቲዎች ማከፋፈል።
                         *

#የግብ ሶስት ተግባር አምስት፣

የግሉ ዘርፍ በነፃ ገበያው መርህ እየተመራ በኢኮኖሚው ላይ የበላይነቱን እንዲያረጋግጥ ምቹ ሁኔታ መፍጠር። በመንግስት የተያዙ ተቋማት በነፃ ገበያ ህግጋት መሰረት በሂደት ወደ ግል የሚዞሩበት ጥናቶችን ሰርቶ ማጠናቀቅ።
        ***

             #ግብ አራት፣
በኢትዬጲያ ህዝብ ውስጥ ዲሞክራሲያዊ ባህልና እሴቶች እንዲጠናከሩ ማድረግ።
    *

#የግብ አራት ተግባር አንድ፣

የፀረ ሽብርተኝነት ፣ የመንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እና የፕሬስ ህጉን በገለልተኛ ወገን እንዲጠና ማድረግ። የሚኒስትሮች ምክርቤት እና የአማካሪ ምክር ቤት አባላት በጋራ በመሆን በገለልተኝነት አጥንተው የሚያመጡ ሙያተኞችን በስምምነት እንዲመድቡ ማድረግ። ጥናቱ ተጠናቆ እስኪመጣ ድረስ አዋጆቹ በጠቅላይ ሚኒስትሩ አቅራቢነት በፓርላማ እንዲታገዱ ማድረግ። በህውሓት ፓርላማ “ ሽብርተኛ!” ተብለው የተፈረጁ አገራዊ ድርጅቶች በአስቸኳይ እንዲሰረዙ ማድረግ።
                   *

#የግብ አራት ተግባር ሁለት፣

በሕግ መልኩ በፓርላማ ሊወጣ የተዘጋጀውን “ የማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም ሕግ” ሙሉ ለሙሉ ሂደቱ እንዲቋረጥ ማድረግ። እንደዚህ አይነት ከፀረ ሽብርተኝነት የባሰ ጨቋኝ ህግ እንዲወጣ በመታሰቡ ለወጣው የሕዝብ ገንዘብ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይቅርታ ጠይቀው እንደማይደገም ቃል መግባት።
        *

#የግብ አራት ተግባር ሶስት፣

ሬዲዬ ፋና፣ ዋልታ፣ ENN ፣ ድምፀ ወያኔ የመሳሰሉ የፓርቲ ሚዲያዎችን ማገድ። በግልፅ ጨረታ ወደ ግል ይዞታ የሚዞሩበትን ሁኔታ ማመቻቸት። ሂደቱ በሚኒስትሮች ምክርቤትና በአማካሪ ምክር ቤቱ መደበኛ ስብሰባ እየቀረበ አበረታች ምርመራ እንዲካሄድ ማድረግ።
          *

#የግብ አራት ተግባር ሶስት፣

የሽግግር ሰነድ ካዘጋጁ ተፎካካሪ የፓለቲካ ድርጅቶች ጋር ሚኒስትሮች ምክር ቤትና አማካሪ ምክር ቤቱ ይፋዊ ውይይቱን መጀመር። ውስጣዊ ድርድሮቹ ካለቁ በኃላ ለህዝብ ይፋ በሆነ መንገድ ውይይቱን መጀመር።
           -----//----
https://netsanetlegna.wordpress.com/2018/04/04/%e1%89%80%e1%8c%a3%e1%8b%ac-100-%e1%89%80%e1%8a%93%e1%89%b5-%e1%89%a0%e1%8a%a4%e1%88%ad%e1%88%9a%e1%8b%ab%e1%88%b5-%e1%88%88%e1%8c%88%e1%88%b0/

Mittwoch, 15. November 2017

የብሄራዊ ደህንነት ዕቅድ ወይስ የህወሀት የስንብት ደብዳቤ? ( ጋዜጠኛ መሳይ መኮንን)

የብሄራዊ ደህንነት ዕቅድ ወይስ የህወሀት የስንብት ደብዳቤ?
መቀሌ
ይህን ጽሁፍ በማዘጋጅበት ሰዓት መቀሌና ሀራሬ ሁነኛ የፖለቲካ ክስተት ተፈጥሯል። የመቀሌው ይፋ የወጣ አይደለም። በህወሀት አፍቃሪያን ድረገጾች የተተነፈሰ ወሬ ነው። ወ/ሮ አዜብ መስፍን የመቀሌውን ህንፍሽፍሽ ረግጠው ወጡ የሚለው ከውስጥ አዋቂ ያፈተለከው ዜና በቀላሉ የሚታይ አይደለም። በትክክል ከሆነ የሀራሬው ዓይነት መፈንቅለ መንግስት ልናይ የምንችልበት እድል ሰፊ ነው። የጄነራል/ፕሮፌሰር ሳሞራ የኑስ ቡድን በመቀሌው ስብሰባ ከተሸነፈ እጁን አጣጥፎ የሚቀመጥ አይሆንም። በአቶ ስብሃት ነጋ የሚመራው የአዲስ አበባው ህወሀት በአንዳች ተአምር መከላከያውን ከሳሞራ የኑስ እጅ ፈልቅቆ ካልወሰደ በቀር የወ/ሮ አዜብ መስፍን ኩርፊያና ረግጦ መውጣት የሚያስከትለው መዘዝ ለህወሀት ፍጻሜው ሊሆን ይችላል።
ትያትሩን አድፍጦ መከታተሉ ጥሩ ነው። ያም መጣ፡ ይሄም ሄደ ልዩነት የለውም። ለኢትዮጵያ ህዝብ የትኛውም የህወሀት አንጃ አይበጀውም። ህወህት ቢከፈልም፡ ቢሰነጣጠቅም ያው ህወሀት ነው። ከነስሩ ተመንግሎ፡ ተጠራርጎ መወገድ ያለበት እንጂ ክፋዩ፡ ስንጣቂው ቢተርፍና በስልጣን ላይ ቢቆይ ለኢትዮጵያና ህዝቧ ተውሳክ፡ ነቀርሳ መሆኑ የማይቀር ነው።

ሀራሬ
የዙምቧቡዌ ሰማይ ያልተለመደ አየር ነፍሶበታል። የ40 ዓመቱ የሙጋቤ ስዩመ እግዚያብሄር አገዛዝ ፍጻሜውን አግኝቷል። በስልጣን ላይ በመቆየት የዓለምን ክብረወሰን የጨበጡት ሽማግሌው ሙጋቤ ከነሚስታቸው በወታደሩ ክፍል ለጊዜው በማቆያ ይገኛሉ። ብሄራዊው ቴሌቪዥን ላይ የዚምቧቡዌ ጦር መሪዎች መግለጫ እየሰጡ ነው። በአጭሩ መፈንቅለ መንግስት ተካሂዷል። ለዚምቧቡዌ አዲስ ታሪክ ተመዝግቧል። ሰውዬው በአጥንታቸው ሳይቀር ጨምድደው እየገዟት ያለችው ሀገር በአዲስ የታሪክ ምዕራፍ ላይ ወጥታለች። ሁኔታዎች በፍጥነት በሚለዋወጡባት ዚምቧቡዌ የሚሆነው ነገር አይታወቅም። ታሪክ ግን ተቀይሯል።
ዚምቧቡዌ በአንድ ስልጣኑን እስከመቃብሩ ድረስ ላለመልቀቅ በወሰነ ሽማግሌ የስንግ ተይዛ ለ40 ዓመታት ቆይታለች። ኢትዮጵያ በዘርና ጎሳ በተቧደኑ፡ በዘረፋና ሌብነት ሀገሪቱን ለመጋጥ በተሰለፉ የአንድ መንደር ልጆች ከሩብ ክፍለዘመን በላይ ደሟ እየተመጠጠ ያለች ሀገር ናት። የዚምቧቡዌ ጦር የዚምቧቡዌ ነው። የኢትዮጵያ ጦር የኢትዮጵያ አይደለም። በዚምቧቡዌ መፈንቅለ መንግስት ቢካሄድ አዲስ ስርዓት በተስፋ ይጠበቃል። በኢትዮጵያ ግን መፈንቅለ መንግስት የህወሀትን አገዛዝ በመሳሪያ ሃይል የሚያስጠብቅ ሌላ የጨለማ ዘመን የሚያመጣ እንጂ ለውጥ አይኖረውም።
ዕቅድ ወይስ ስንብት?
ለአዲስ ስታንዳርድ በቅድሚያ ምስጋና ይገባዋል። ይህ ሰነድ ወይም ዕቅድ ወይም ኑዛዜ ወይም የስንብት ደብዳቤ ይደርሰን ዘንድ የአዲስ ስታንዳርድ ውለታው ላቅ ያለ ነው። ሰነዱ በጣም ጠቃሚ ነው። በጣምም ወሳኝ ነው። ለነጻነትና ዲሞክራሲያዊ ስርዓት መምጣት ለሚዋደቁ ሃይሎች በተለይም በለውጥ ምጥ ላይ ላለው የኢትዮጵያ ህዝብ ይህ ዕቅድ ተስፋን የሚያለመልም ነው። በእስከአሁኑ በዚህ ደረጃ የህወሀት መንግስት ውድቀቱን ያመነበት ሰነድ አላየሁም። የጠቃሚነቱን፡ የወሳኝነቱን ያህል ግን ትኩረት አልተሰጠውም። ኢትዮጵያ እንደዚምቧቡዌ ያረጀውንና፡ የጃጀውን ስርዓት ልትገላገለው በዋዜማው ላይ መሆኗን የሚያበስር ዕቅድ ሆኖ አግኝቼዋለሁ።
ዝርዝር ዕቅዱ የህወሀትን የወቅቱን ቁመና የሚያሳይ ነው። ውስጣዊ ሁኔታዎች በሚል በ10 ነጥቦች የተዘረዘሩትን ከወሰድን ከአንድ ድምዳሜ ላይ እንደርሳለን። የህወሀት መንግስት በእርግጥም አብቅቶለታል። በተቃራኒው ያለው የለውጥ ሃይል ጠንካራ ባለመሆኑ፡ ወይም፡ በአንድነት ባለመሰለፉ ወይም በሁለቱም ምክንያቶች የተነሳ እየፈራረሰ ያለውን የህወሀት ስርዓት ወደመቃብሩ መውሰድ ባለመቻሉ ህወሀት ለጥቂት ጊዜያትም ቢሆን እድሜው እንዲቀጥል እየሆነ ነው። የህወሀትን ኑዛዜ ዋና ዋና ክፍሎችን እንመልከተው።
ህዝብ ተስፋ ቆርጦብኛል
ህውሀት አልደበቀም። እንደሁልጊዜውም የህዝብ ተስፋ ነኝ የሚል ባዶ ኩሸት መደለቅ አልፈለገም። በዕቅዱ ላይ እንደተናዘዘው ህዝቡ ተስፋ ቆርጦበታል። ህዝብ በህይወት የመኖር ተስፋው እየቀነሰ፡ እየጨለመ መምጣቱን፡ በስርዓቱ ላይ ተስፋ የመቁረጥና ይህ ስርዓት ይቀጥል ይሆን የሚል ብዥታ ውስጥ መግባቱን ይገልጻል። ህዝቡ የሰላም ዋስትና ማጣቱንም ህወሀት አምኗል። ስጋት ውስጥ የተዘፈቀ፡ በስልጣን ላይ ባለው ስርዓት ላይ እምነት አጥቶ ውዥንብር ውስጥ የገባ ህዝብ ሲልም ያስቀምጣል። ህዝቡ ብቻ ሳይሆን ሰራዊቱም ተስፋ እንደቆረጠበት ተናዟል። ለህወሀት ትልቁ አደጋ ይሄ ነው። የጸጥታ ሃይሉ ሰላም የማስከበር አቅሙ መጎዳቱን፡ በመንግስት መቆየት ላይ ጥርጣሬ ውስጥ መግባቱን፡ በአጠቃላይ መሰላቸትና ተስፋ መቁረጥ በሰራዊቱ ውስጥ መከሰቱን አትቷል።
ጸረ-ሰላም ሃይሎች(የለውጥ ሃይሎች)
ይህን ዕቅድ ላነበበ አንድ ነገር ግልጽ ይሆንለታል። በኢትዮጵያ ውስጥ የህወሀትን ስርዓት ገንድሶ ለመጣል የተስለፉ ሃይሎች እግር አውጥተው ረጅም ርቀት እየተጓዙ ለመሆናቸው ትልቅ ማስረጃ የሚሆን ሰነድ ነው። ተቃዋሚዎች የታላችሁ? መሳሪያ የታጠቀ ቡድን ኢትዮጵያ ውስጥ አለ ወይ? ለሚሉ ሰዎች የህወሀት ዕቅድ አጥጋቢ መልስ ይሰጣል። በዕቅዱ ላይ እንደተገለጸው አርበኞች ግንቦት ሰባትና የኦሮሞ ነጻነት ግንባር በሀገሪቱ እንደፈለጉ በመፈንጨት ላይ ናቸው። እነዚህ ሃይሎች በፕሮፖጋንዳው ጭምር እንደበለጡትም አምኗል። ሃይላቸው ተጠናክሯል። ህዝብን ከጎናቸው እያሰለፉ ነው። ለጦርነት የሚሆን ከፍተኛ ገንዘብ እየሰበሰቡ ነው። መሳሪያ ግዢው ተጧጡፏል። እነዚህ ሃይሎች መንግስት ተዳክሟል፡ ሀገር ለመምራት አይችልም ከሚል ድምዳሜ ደርሰው ስርዓቱን ሊያፈራርሱ እየተረባረቡ ነው ሲል ህወሀት የመጣበትን አደጋ በግልጽ አስቀምጧል።
ጸረ ሰላም(የለውጥ) ሃይሎች ውስጡን እንደቦረቦሩት ህወሀት በገደምዳሜም ቢሆን ገልጿል። አመራሩ በተለይም መካከለኛውና የታችኛው አመራር በእነዚህ ሃይሎች ፕሮፖጋንዳ ታጥቦ ተወስዷል የሚለው ህወሀት በሀገሪቱ ለተከሰተው አጠቃላይ ቀውስም የራሱ መዋቅር ላይ ጣቱን ቀስሯል። አርበኞች ግንቦት ሰባትና ኦነግ የብአዴን፡ ኦህዴድንና ደኢህዴንን መዋቅር ሰብረው መግባታቸውን በመግለጽ በተለያዩ ጊዜያት ለሚወጡ ጥሬ መረጃዎች ማረጋገጫ የሚሰጥ ኑዛዜ ነው። ህወሀት በዚህ ዕቅዱ የተቃዋሚዎች(የጸረ ሰላም ሃይሎች) መጠናከርን የህዝብ ስጋት የፈጠረ ሲል ይገልጸዋል። በእርግጥ ተቃዋሚዎች በዚህ ደረጃ ማንሰራራትና መጠናከር መቻላቸው ለህዝብ ስጋት አይሆንም። መርዶም አይደለም። ተስፋ እንጂ። ተቃዋሚዎችን ፍለጋ በየሰፈርና መንደሩ የሚሰማውን የኢትዮጵያ ህዝብ ጥያቄ የሚመልስ የወቅቱ ታላቅ የምስራች እንጂ።
ኢኮኖሚው አደጋ ላይ ነው
የህወሀት ኑዛዜ በኢኮኖሚው ላይ ያስቀመጣቸው እውነቶች በተለያዩ የነጻነትና የዲሞክራሲ ደጋፊ ሚዲያዎች ሲባል የነበረውን የሚያረጋግጥ ነው። ህወሀት ግብር መሰብሰብ እንዳልቻለ ገልጿል። መንግስት የለም፡ ግብር አትክፈሉ የሚል ቅስቀሳ እየተካሄደ ነው ብሏል። በኢኮኖሚው ላይ ከፍተኛ ሳቦታጅ( ዶ/ር ታደሰ ብሩ አሻጥር ይለዋል) እየተፈጸመ መሆኑን አትቷል። ህዝቡን ለልማት ከማሰማራት ይልቅ የጦርነት ነጋሪት እየተጎሰመ ለግጭትና ለሰላም መደፍረስ ሚና እንዲጫወት እየተደረገ ነው ያለው ህወሀት በዚህም ምክንያት ኢኮኖሚው ክፉኛ መጎዳቱን አስታውቋል። የውጭ ኢንቨስትመንት ተዳክሟል። የቱሪስት ፍሰት ቀንሷል። የውጭ እርዳታ በከፍተኛ መጠን ወርዷል።
የህወሀት ዕቅድ ላይ እንደተገለጸው ባለሀብቶችና ኢንቨስተሮች ሀብትና ገንዘብ በከፍተኛ ደረጃ ከሀገር እያሸሹ ናቸው። እነማን እንደሆኑ በእርግጥ አልተገለጸም። መረጃዎች የሚያመለክቱት የህወሀት ባለስልጣናትና በዘር መስመር ሀብት ያፈሩ የትግራይ ተወላጆች በዋናነት ሀብት እያሸሹ መሆናቸውን ነው። በነገራችን ላይ ማክሰኞ አንድ ሪፖርት ወጥቷል። የአውሮፓ ህብረት ኢትዮጵያን ከ10ሩ ገንዘብና ሀብት ከሚሸሽባቸው የዓለም ሀገራት ውስጥ አስገብቷታል። በዚህም ምክንያት ከኢትዮጵያ በሚሸሸው ሀብትና ገንዘብ ላይ ጥብቅ ቁጥጥር ሊያደርግ ነው። ለ28ቱ የአውሮፓ ህብረት አባል ሀገራት ሰርኩላር ተበትኗል። የህወሀት ባለስልጣናት አንዱ የሀብት ማሸሺያ መስመር አሁን ሳዑዲ አረቢያ ውስጥ ታስሯል። የሼህ አላሙዲን መታሰር በህወሀት መንደር ሽብር የፈጠረው ያለምክንያት አይደለም። እናም ህወሀቶች ለጡረታቸው ያሸሹት ሀብትና ገንዘብ ወጥመድ ውስጥ ገብቷል።
ጄኖሳይድ
የዚህ ዕቅድ አስደንጋጩ ክፍል ይሄው ነው። በኢትዮጵያ ውስጥ የጅምላ ግድያ መፈጸሙን ህወሀት ገልጿል። በሶማሌና በኦሮሚያ ክልሎች መሃል በተፈጠረው ግጭት ጄኖሳይድ ተፈጽሟል ያለው የህወሀት የደህንነት ዕቅድ እነማን እንደፈጸሙ፡ ምን ያህል ሰዎ እንዳለቀ በዝርዝር አያስቀምጥም። የፖለቲካ ተንታኞች ህወሀት ሌሎችን ለማጥመድ የስነቀራት ምክንያት ልትሆን ትችላለች የሚል ሀሳብ ያቀርባሉ። በተለይም የሁለቱን ክልሎች በዋናነትም የኦሮሚያ ክልል መሪዎችን ለማስበርገግ ሊሆን እንደሚችልም ይገልጻሉ። ሆኖም ህወሀት ሳያስበው ራሱ ላይ ጥይቱን አቀባብሏል የሚሉ ወገኖችም አሉ። ህወሀት በሚቆጣጠራት ሀገር ጄኖሳይድ ተፈጽሞ ከሆነ ይህን የምድረግ አቅም ያለው የህወሀት ጦር በመሆኑ በቀጥታ ተጠያቂ የሚሆነው የህወሀት መንግስት ነው። ለዓለም ዓቀፍ ተቋማትና ለመንግስታቱ ድርጅት የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ጥሩ ዱላ ነው። ሌሎች በኢትዮጵያ የተፈጸሙና የተደበቁ የጅምላ ግድያዎች የሚነሱበትና ተጠያቂዎች ለፍርድ የሚቀርቡበትን ሁኔታ የሚቀሰቅስ ሊሆን ይገባዋል። በኦጋዴናን በአኝዋክ ኢትዮጵያውያን ላይ የተፈጽሙትን ጄኖሳይዶች ማን ይረሳቸዋል?
የጦስ ዶሮ
ህወሀት በኢትዮጵያ ውስጥ ለተፈጠሩ ቀውሶች ራሱን ተጠያቂ ከማድረግ ተቆጥቧል። ሶስት አካላት ላይ ጣቱተቀስሯል። ግብጽና ኤርትራ በረጅም እጃቸው ኢትዮጵያን እየበጠበጡ ነው የሚል ክስ በህወሀት ቀርቧል። አርበኞች ግንቦት ሰባትና ኦነግ ሀገሪቱን በማመስ ተወንጅለዋል። የስርዓቱ አመራሮች ለቀውስ የተመቸ ሜዳ በመፍጠር ጥርስ ተነክሶባቸዋል። በዕቅዱ ላይ አንድም ቦታ ህወሀት ሃላፊነት አልወሰደም። አሁንም ለኢትዮጵያ ህዝብ መላዕክ መሆኑን ይገልጻል። የጦስ ዶሮዎች እየተፈለጉ ነው። በተለይ በስርዓቱ ውስጥ ያኮረፉት ላይ እርምጃ ሊወሰድ ይችላል። መጠነ ሰፊ እስሮች ከፊት እንደሚኖሩ ይጠበቃል። የዕቅዱ አንድም ግብ እነዚህን አመራሮች ልክ ማስገባት ነው።
የዕቅዱ ግብ ሌሎች ተግባራትንም ያከናውናል። ሰልፎች ታግደዋል። በአስቸኳይ አዋጁ ገደብ የተጣለባቸው መብቶች በተዘዋዋሪ በዚህኛው ዕቅድም ተግባራዊ ይሆናሉ። ዕቅዱ በስም እንጂ በይዘት ከአስቸኳይ አዋጁ ጋር አንድ ነው። የዕቅዱ ሌሎች ግቦች ከፉከራ ያለፉ አይደሉም። መሳሪያ መንጠቅ፡ ጸረ ሰላም ሃይሎችን መደምሰስ እና የመሳሰሉት ግቦች አሁን ህወሀት ካለበት ቁመና አንጻር የሚሳኩ አይመስሉም።
ማጠቃለያ
የመቀሌው ስብሰባ አልተጠናቀቀም። ህወሀት ሪፎርም ማድረጉንና ከስልጣን የሚያሰናብታቸው አመራሮች እንደሚኖሩ እየተነገረ ነው። It is too late. ምን ዓይነት ሪፎርም? ህወሀት አፈጣጠሩ ለዚህ የሚፈቅድለት አይደለም። ያረጠ ድርጅት ነው። ከተቸነከረበት የስታሊን መስመር ዝንፍ ካለ መጥፊያው ነው። ደግሞም 11ኛው ሰዓት ላይ ሪፎርም አያድነውም። የኢትዮጵያ ህዝብ ህወሀትን ሊሰናበት ተዘጋጅቷል። ይህ ዕቅድም የስንብት እንጂ የሪፎርም አይደለም። ከመቀሌ የሚጠበቅ ለውጥ አይኖርም። ህወሀት በዕቅዱ እንዳስቀመጠው ህዝቡ መንግስት ይቀጥላል ብሎ አያምንም። ተስፋ ቆርጧል። ስለዚህ ዕቅዱን የስንብት ደብዳቤ ነው ቢባል ያስኬዳል። ኑዛዜም ነው። ይህን ተቀብሎ የማሰናበትና ህወሀትን ከነጥቁር ገጽታው

Freitag, 1. September 2017

ጊዜው "የእምቢ አልገዛም! " "የእምቢ አልከፍልም! " ነው። (በ ዶ/ር ታደሰ ብሩ)

ህወሓት፣ በቀን ገቢ ግምት ግብር ከፋዮች ላይ  ያሰበው መጠነ ሰፊ ዘረፋ ላይ በደረሰበት ሰፊ ተቃውሞ ሳቢያ ቀላል የማይባል ኪሳራ ደርሶበታል። በዚህም ምክንያት የማፈግፈግ ምልክቶችን አሳይቷል። ማፈግፈግ የሥርዓቱ ጊዜዓዊ ማምለጫ ነው፤ ሁኔታዎች ሲረጋጉ ተመልሶ መምጣቱ አይቀርም። እንዲያውም ሌሎች ተጨማሪ የዝርፊያ መስሮችን መክፈቱን የማይቀር ነው። 

አሁን ተግባራዊ መሆን የጀመረ ድሆችን ይበልጥ የማደህያ አንድ መጠነ ሰፊ ፕሮጀክት እነሆ። በወሊሶ ከተማ የቀበሌ ቤቶች ኪራይ በአንድ ጊዜ ከ 40  - 50 ጊዜ እጥፍ መጨመሩ ኢሳት ገልፆ ነበር።

እንዲህ ዓይቱ ጭማሪ በወሊሶ ብቻ ሳይሆን በሁሉም የኦሮሚያ ከተሞች ወስጥ ተግባራዊ እንዲደረግ ተወስኗል።. ለምሳል፣ በወር 10 ብር ይከፈልበት የነበረ ዛኒጋባ ብር 500 እንዲከፈልበት፤ መክፈል  የማይችሉ ቤቶቹን እንዲለቁ እንዲደረግ ተወስኗል።

ይህ ውሳኔ በኦሮሚያ ላይ ተወስኖ የሚቀር አይደለም፤ የኦሮሚያው አፈፃፀም ታይቶ ወደሌሎች ክልሎችም መዛመቱ የማይቀር ነው። ስለሆነም ካሁኑ ተቃውሞዓችን አገራዊ መሆን ይኖርበታል።

መጪው 2010 "ለማይወክለን አገዛዝ ግብር ብቻ ሳይሆን ማናቸውንም ክፍያ አንፈፅምም" የሚባልበት ዓመት መሆን ይኖርበታል።

መምህራን፣ ተማሪዎች፣ የመንግሥት ሠራተኞች፣ ወታደሮችና ፓሊሶች "አንገዛም፣ አንታዘዝም፣ አንከፍልም፣ አንሠራም……" ለማለት ይዘጋጁ።

ጊዜው "የእምቢ አልገዛም! " "የእምቢ አልከፍልም! " ነው።