OPPOSITION PARTIES
Donnerstag, 31. Dezember 2015
ያሁኑ የኢትዮጵያ ሁነታ፤ ይመስላል የተምታታ – ፕ/ር ጌታቸው ኃይሌ
Dienstag, 29. Dezember 2015
በጋራ ከማልቀስ፣ በጋራ መታገል (አበበ ገላው)
በጋራ ከማልቀስ፣ በጋራ መታገል
ከ66ቱ አብዮት ወሳኝ ትምህርት መቅሰም አለብን። የኢትዮጵያ ተማሪዎች ንቅናቄ ሁለት መሰረታዊ ጥያቄዎች መሬት ላራሹ እና ዳቦ ለተራበው ነበሩ። የኢትዮጵያን ህዝብ መሬት አልባ አድርጎ ሲያስገብር የነበረው ፊውዳላዊ ስርአት የተንኮታኮተው እነዚህ መሰረታዊ ጥያቄዎች በመነሳታቸው ብቻ አልነበረም። ኢትዮጵያውያን ሁሉ በገዥዎችና በተገዢው ጭቁን ህዝብ ያለውን የመደብ ትግል ተረድተው ከዳር እስከዳር በአንድነት መነቃነቅ በመቻላቸው ነበር።
በርግጥ ያለመታደል ሆኖ ያ ህዝባዊ አብዮት በወታደራዊ ሃይል ተቀልብሶ ሌላ አስከፊ አንባገነናዊ ስርአት ተተካ።ከዛ ዘመን በከፋ መልኩ ዛሬ የኢዮጵያን ህዝብ ከመሬቱና ከቀዬው እያፈናቀለ በረሃብ የቀፈደደውን የህዝብ ደም እየመጠጠ በዘር ከፋፍሎ እየቀጠቀጠና እየገደለ የሚገዛ ዘረኛ የውስጥ ቅኝ ገዢ አስተሳሰብ ያለው የጥቂቶች ዘውጋዊ ስርአት በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ ተዘርዝሮ የማያልቅ ወንጀል እየፈጸመ ህዝብን በመግዛት ላይ ይገኛል።
ስለዚህም ነው የስርአቱ ሰለባ ሁሉ ልዩነቱን አቻችሎ በዘር ቆጠራ ላይ የተመሰረተውን የህወሃቶች ስርወ መንግስት ከስር መሰረቱ ለመጣል በጋራ መነሳትና መታገል የሚገባው። ሰሞኑን በኦሮሚያ የተነሳው ህዝባዊ አመጽም በድጋሚ ሊያስተምረን የሚገባው መሰረታዊ ጉዳይ ህወሃቶች የስልጣን እድሚያቸውን ለማራዘም የማይፈጽሙት ወንጀል የለም። የህዝብ ጥያቄ ከመመለስ ይልቅ፣ የኦሮሞን ህዝብ በአሸባሪነት ፈረጆ ጦርነት ማወጅ የስርአቱን ቀቢጽ ተስፋነት በግልጽ አጉልቶ ያሳየ እውነታ ነው።
የህወሃቶች ስርወ መንግስት በስልጣን ላይ እስካለ ድርስ የየትኛው ህዝብ የመብትና የፍትህ፣ የእኩልነትና የነጻነት፣ የመሬትና የዳቦ ጥያቄ ፈጽሞ ሊመለስ እንደማይችል ግልጽ ነው። በመሆኑም በየአቅጣጫውና በየክልሉ የሚደረገውን ትግል ከፍ አድርጎ ብሄራዊ ንቅናቄ መጀመር የግዜው አንገብጋቢ ጉዳይ በመሆኑ ከውጭም ከውስጥም በህብረት ለመታገል ሁላችንም ልዩነቶቻችንን አቻችለን በቅን ልቦና እንነሳ።
በተለይ ደግሞ አክቲቪስቶችና የፖሊቲካ ፓርቲ መሪዎች ለሚቀርቡላችሁ የጋራ የትግል ጥሪ ፈጣንና አወንታዊ መልስ እድትሰጡ በጭቁ ህዝባችን ስም እማጸናለሁ።
አንድነት ሃይል ነው!
http://wp.me/p5L3EG-96
Samstag, 26. Dezember 2015
ኢትዮጵያ የማን ናት? (ከአንተነህ መርዕድ)
ከአንተነህ መርዕድ
“ኦሮሞ ግንድ ነው አይገነጠልም” (ጄኔራል ጀጋማ ኬሎ)
Freitag, 25. Dezember 2015
የ11ኛው ሰዓት ጥሪ እያንዳንዱን ኢትዮጵያዊ ይመለከታል!
የ11ኛው ሰዓት ጥሪ እያንዳንዱን ኢትዮጵያዊ ይመለከታል!
December 25, 2015
የንቅናቄያችን መሪ ፕ/ር ብርሃኑ ነጋ ለኢትዮጵያ ህዝብ ባደረጉት የትግል ጥሪ በ11ኛው ሰዓት ላይ እንደምንገኝ ገልጸዋል ። የ 11ኛው ሰዓት መልዕክት፣ አንደኛ፣ ወደ 12ኛው ሰዓት ወይም ወደ ፍጻሜው እየተቃረብን መሆኑን የሚነገረን ነው። የ11ኛው ሰዓት የትግል ጥሪ የአንድን የትግል ምዕራፍ ለመዝጋት እና አዲስ የትግል ምዕራፍ ለመጀመር የመጨረሻ የሞት ሽረት ትግል የምናደርግበት ጊዜ ላይ መድረሳችንን የሚገልጽ ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ጥሪው ከትግሉ ፍጻሜ በሁዋላ ስለሚፈጠረው አዲስ ስርዓት ከአሁኑ ማሰብ መጀመር እንዳለብን የሚያነቃን ደወል ነው። 11ኛው ሰዓት ላይ ቆመን ከ12ኛው ሰዓት በሁዋላ ስለሚፈጠረው ነገር መጨነቅ ካልቻልንና በጊዜ ቤታችንን ካላሰናዳን ፣ ከትግሉ ፍጻሜ በሁዋላ ሊገጥሙን የሚችሉትን ተግዳሮቶች በጊዜና ብቃት ባለው መልኩ ለመፍታት መቸገራችን አይቀርም ። አንድ በእድሜ የገፋ ሰው 11ኛው ሰዓት ላይ መሆኑን ሲያውቅ ከህይወቱ ፍጻሜ በሁዋላ ስለሚኖረው ህይወት ማሰላሰሉ ተፈጥሯዊ ነው። የ11ኛው ሰዓት ጥሪም የአንድን አገዛዝ እርጅናና ፍጻሜ የሚያሳይ ብቻ ሳይሆን፣ በቦታው የሚወለደውን አዲስ ስርዓት ምንነትም የሚያሳይ ነው።
የ11ኛው ሰዓት ጥሪ ተደራሾች እነማን ናቸው? የጥሪው ተደራሾች በኢህአዴግ ዙሪያ የተሰባሰቡት እና እነዚህን ስብስቦች በማፍረስ አዲስ ስርዓት ለመገንባት የሚታገሉት የነጻነት ሃይሎች ሁሉ ናቸው። የ11ኛው ስዓት ጥሪ ለወያኔ ገዢዎች መገርጀፋቸውን የሚያረዳ የሞት ጥሪ ደወል ነው፤ ወደማትመለሱበት መቃብር ከመወርወራችሁ በፊት በቀራችሁ የአንድ ሰአት እድሜ አሟሟታችሁን አሳምሩ ብሎ የሚመክር ነው። በተለይ በጣት የሚቆጠሩ የሻገቱ ገዢዎችን ደግፋችሁ የቆማችሁ የመከላከያ፣የፖሊስና የደህነት አባላት አሰላለፋችሁን በጊዜ አስተካክሉ የሚል አርቆ ከማሰብ የመነጨ ምክር ነው ። የ11ኛው ሰዓት ጥሪ የሚመክር ብቻ ሳይሆን የሚያስጠነቅቅም ነው። ይህን የገረጀፈ አገዛዝ ደግፈው የቆሙ ሁሉ በጊዜ ከህዝብ ጋር እንዲታረቁ ይህ ካልሆነ ግን በመጨረሻው ሰዓት ከፍርድ እንደማያመልጡ የሚያስጠነቅቅ ነው። ካለፈው የሚመጣው ይበልጣል፤ ወያኔን ደግፋችሁ የቆማችሁ ሁሉ ያለፈ ጥፋታችሁን ለወደፊት በምትስሩት ስራ እንድትክሱ መልእክት ተላልፎላችሁዋል።
የ1ኛው ሰዓት ጥሪ የነጻነት ሃይሎች በአንድነት እንዲሰባሰቡና ትግሉን እንዲያቀጣጥሉም ያሳስባል። አገዛዙ 11ኛው ሰዓት ላይ ነው ማለት በራሱ ጊዜ ይወድቃል ማለት አይደለም። አገዛዙ ከደሃው በዘረፈው ገንዘብ ኪኒኖችን እየዋጠና ምርኩዞችን እየገዛ እድሜውን ሊያራዝም ይችላል። ከገፋነው በቀላሉ ተሰባብሮ ይወድቃል፤ ዝም ካልነው ግን ድዱ ረግፎም በህይወት መቆየቱና ስቃያችን ማራዘሙ አይቀርም። እኛ በዘር፣ በጾታ፣ በትምህርት ወይም በሌሎች ጥቃቅን ነገሮች ሳንለያይ አንድ ሆነን ይህን የሻገተ አገዛዝ እንድናስወግድ ግልጽ ጥሪ ተላልፏል።
የ11ኛው ሰዓት ጥሪ ያረጀውን ስርዓት ወደ መቃብሩ ከከተትነው በሁዋላ ስለሚፈጠረው አዲስ ስርዓት እንድናስብ የሚመክርም ነው። ዛሬ በመሰረታዊ ጉዳዮች ላይ ተቀራርበን እንድንነጋገርና የነገውን ትልም እንድንተልም የሚጠይቅ ነው። አስቀድሞ በጋራ መተለሙ ነገ ሊፈጠር የሚችለውን ችግር ከመቀነሱም በላይ፣ የሻገተውን አገዛዝ በህብበረት ለመጣል ከፍተኛ እገዛ ያደርጋል። በጭሩ የ11ኛው ሰዓት ጥሪ ወያኔን ተባብሮ ለመቅበር ብቻ ሳይሆን፣ በመቃብሩ ላይ ስለሚተከለው አዲስ ችግኝ ለመነጋገር ጥሪ የሚያቀርብ ነው።
ሁላችንም የ11ኛውን ሰዓት ጥሪ ተቀብለን ተግባራዊ ልናደርገው ይገባል። ድሉ የሁላችንም ነው!
አርበኞች ግንቦት7!
http://wp.me/p5L3EG-8O
Donnerstag, 24. Dezember 2015
ከ “ናስ ማሰር – አፍ ማሰር” (ይገረም አለሙ) ይገረም አለሙ
ከ “ናስ ማሰር – አፍ ማሰር” (ይገረም አለሙ) ይገረም አለሙ
ጊዜው ድሮ ድሮ ነው፡፡ቦታው ደግሞ ዝናር ወይንም ጀበርና ታጥቆ ብረት/ጠብ -መንጃ ትከሻ ላይ ጣል አድርጎ መሄድ አንድም ለአቅመ ወንድነት መድረስ ሁለትም በሀብት ከሌላው የተሻሉ ተደርጎ የሚታይበት አካባቢ ነው፡፡ ደረስኩ ደረስኩ ያለ ጎረምሳ በወቅቱ ተወዳጅና ተመራጭ የነበረውን ናስ ማሰር የተባለ ብረት/ጠመንጃ ይገዛና በሀገር በሰፈሩ አንቱ የተባሉና የተከበሩ ሽምግሌ ጋር በመሄድ አባት እስቲ ይህችን ብረት እዩልኛ ይላቸዋል፡፡ ርሳቸውም እያገላበጡ እያዩ ቀዝቀዝ ባለ ስሜት ጥሩ ናት ሸጋ ብረት ናት ይሉታል፡፡ ከገጽታቸውና ከአነጋገራቸው ጥሩ ስሜት አንዳልተሰማቸው የተረዳው ጎረምሳ ምነው አባት ሆሳ ነች እንዴ ወጥ አይደለችም? ሲላቸው አረም ሸጋ የሆነች ወጥ ብረት ነች ይሉታል፡፡ አሁንም አነጋራቸው ስላላማረው ታዲያ ምነው አነጋገርዎ ቀዝቀዝ ቢላቸው አዎ ልጄ ከናስ ማሰር አፍ ማሰር ነው የሚበጀው ብየ ነው አሉት ይባላል፡፡
የህይወትም ሆነ የንብረት ደህንነት የሚጠበቀው በጠመንጃ ሳይሆን እጅ በሚሰራው መልካም ድርጊት ከአንደበት በሚወጡ የታረሙ ቃላት ነው፡፡ በጠመንጃ እየተማመኑና በጡንቻ እያሰቡ የሚሰሩትና የሚናገሩት ሁሉ ጠላት ስለሚያፈራ፡ የህይወትና የንብረት ደህንነት አይኖርም፡፡ ስነ ምግባር የገራውና በራሱ እንዲፈጸምበት የማይፈልገውን በሌሎች የማይፈጽም፤ ፈሪሀ እግዚአብሄርን የተላበሰና አንደበቱ የታረመ ለህሊናው የሚገዛ ሰው ግን ወዳጅ እንጂ ጠላት ስለማይኖረው በቀንም ሆነ በለሊት በሜዳም ሆነ በጫካ ብቻውን ቢጓዝ የሚያሰጋው ነገር አይኖርም፡፡
በጠመንጃ መተማመን ሲጀመር የማሰብንና የመወሰንን ስራ ጡንቻ ስለሚረከብ የሚሰራው ሁሉ የእብሪት የሚነገረው ሁሉ ለከት የለሽ ይሆንና ወዳጅ እያነሰ ጠላት እየበዛ ይሄዳል፡፡ ይህ አድራጎት በፖለቲከኞች ሲፈጸም ደግሞ የሚያስከትለው ጦስ ከድርጊቱ ፈጻሚዎች ይልቅ ሀገርንና ሕዝብን ይሆናል የሚጎዳው፡፡
ደርግን ማሸነፋቸው የፈጠረባቸው እብሪት ሀያ አራት አመት ሙሉ ሊበርድላቸው ያልቻለው የወያኔ ባለሥልጣናት የህዝብን አመኔታና ፍቅር ለማግኘት የሚያስችለውን መንገድ አያውቁትምና ዛሬም ህዝብን ማሰርና መግደሉን መሰብደብና ማፈናቀሉን ቀጥለውበታ፡፡ የንታቸው ብዛትም ይህን ሁሉ የሚያደርሱበትን ሕዝብ በለከት የለሽ አንደበታቸው ይሰድቡታል፡፡ ትግሉን የማያውቁት የባሩዱን ሽታ ያልቀመሱት አዳዲሶቹ ወያኔዎች ሳይቀሩ የጌቶቻቸውን ፈር እየተከተሉ ባልዋሉበት ተግባር ሲፎክሩ ባልተገራ አንደባተቸው ህዝብን ሲሳደቡ ሲዝቱና በህዘብ ሲያላግጡ እየሰማን ነው፡፡
ደርግን በማሸነፋቸው ሀያ አራት አመታት ሊበርድ ላልቻለ እብሪት የተዳረጉት ወያኔዎች የጠመንጃ ትምክህታቸው ህሊናቸውን ዘግቶ ማስተዋል ቢነሳቸው እንጂ በተቃራኒው ደርግ ለምንና እንዴት ሊሸነፍ በቃ ብለው ማሰብ ቢችሉና ከናስ ማሰር አፍ ማሰር ብሎ የሚመክር ሽማግሌም በአቅራቢያቸው ቢኖር ኖሮ በሀያ አራት አመታት ቆይታቸው ከጠመንጃ ትምክህት የህዝብን ፍቅር ወደ ማግኘት ሽግግር ባደረጉ ነበር፡፡
በጠመንጃ አምላኪነት የታበዩት ወያኔዎች በዘመነ ስልጣናቸው ከማናቸውም ወገን ለሚቀርቡ ማናቸውም ጥያቄዎች የሀይል ርምጃን ዘለፋ ስድብና ፍረጃን ምላሽ አድርገው ኖረዋል ፡፡ በውይይት ሊፈቱ ለሚችሉ ጥያቄዎች ተቃውሞዎችን ተከትሎ በሚያሰሙት የለሽ የለሽ የንቀት ንግግራቸው የበለጠ ህዝብን እያስቆጡ፣ ህዝቡ ቁጣውን በሰላማዊ ሰልፍ ሲገልጽ ለግድያ ያሰለጠኑትንና ሰዋዊ ባህርይውን አውልቀው የአውሬ ባህርይ ያለበሱትን ሰራዊት በማዝመት ያስደበድባሉ፣ ያስገድላሉ ያሳስራሉ፡፡ ሰሞኑን ኦሮምያ ውስጥ የተፈጸመውም ይሄው ከጠመንጃ አምላኪነት የተወለደው አረመኔያዊ ድርጊት ነው፡፡
ከአዲስ አበባ አልፎ አጎራባች የኦሮምያ ከተሞች መሬት አልበቃ ያላቸው ወያኔዎች ገደብ የለሽ የመሬት ፍላጎታቸውን ለማርካት የዋጡት ነው በሚል ከሁለት አመት በፊት የአዲስ አበባን ማስተር ፕላንን የተቃውሙ ዜጎችን በማሰር በመደብደብና በመግደል ተቃውሞውን ለማስቆም የቻለው ወያኔ ሁለት አመት አድፍጦ ከቆየ በኋላ አቶ አባይ ጸሀየ በአደባባይ ወጥተው ማስተር ፕላኑን ተግባራዊ እንደርገዋለን፤ እንቅፋት ለመፍጠር የሚያስብ ካለም ልክ እናስገባዋለን በማለት ለህዝብ ያላቸውን ንቀት አሳዩ ወያኔ ያቀደውን አይደለም ያሰበውን ተግባራዊ ከማድረግ ወደ ኃላ እንደማይልም አረጋገጡ፡፡
አቶ አባይ ጸሀዬ እንዲህ በእብሪትና በድፍረት ለመናገር የበቁበትን ምክንያት መገመት ይቻላል፡፡ የመጀመሪያው ጠመንጃ የወለደው ማንአለብኝነትና የህዝብ ንቀት ነው፡፡ ሌላው ደግሞ ኦህዴድን ጠፍጥፈው የሰሩት ወያኔዎች፤ መሪዎቹንም ከየምርኮ ሰፈር ሰብስበው ከምርኮኝነት ወደ ድርጅት መሪነት ያሸጋገሩዋቸው እነርሱ በመሆናቸው ለመቃወም ሞራልም አቅምም እንደሌላቸው ማወቃቸው ነው፡ ለሀያ አራት አመታትም ወያኔ በኦሮምያ ምድር ያሻውን ሲፈጽም ኦህዴድ የተሰጠውን ተልእኮ ከማስፈጸምና ሰጥ ለጥ ብሎ ከመታዘዝ ውጪ ትንፍሽ ያለው ነገር አለመኖሩም ለአባይ ጸሀዬ የእብሪት ዛቻና ድንፋታ አስተዋጽኦ አለው፡
ወያኔዎች ያልተረዱት ከባህሪያቸውም አንጻር ሊረዱት የማይችሉት ትናንት ወታደራዊ ምርኮኛ ዛሬ ደግሞ የስኳር ምርኮኛ ከሆኑትና ወዶ ገብ ሆነው ለወያኔ እጅ ከሰጡት የኦህዴድ አመራሮች ውጪ የሆኑ የኦህዴድ አመራሮች መኖራቸውን ፤እንዲሁም የኦህዴድን አመራሮች በምርኮ መያዝ ሕዝብን መያዝ አለመሆኑን ነው፡፡ይህን ደግሞ በአጭር ግዜ በመላ ኦሮምያ የተነሳው ተቃውሞ መማር ለሚችል በበቂ ያሳየ ነው፡፡
የአቶ አባይ ጸሀዬ ድንፋታ በተቃውሞ የቆመው ማስተር ፕላን ተግባራዊ ሊደረግ መሆኑን በማጋለጡ ምእራብ ሸዋ ላይ የተነሳው የደን መሸጥን ሰበብ ያደረገው የተማሪዎች ተቃውሞ ምክንያት ሆኖት ተዳፍኖ የቆየው ተቃውሞ ሲቀሰቀስ በኦህዴድ እና በወያኔ ሰፈር የተሰሙት ነገሮች መለያየት ምርኮኛም ቢሆን ጫናው ሲበዛበት አሻፈረኝ ሊል፤ሎሌም ቢሆን ንቀቱ ሲብስበት ሊያምጽ እንኳን ባይችል ሊያኮርፍ እንደሚችል ያሳየ ነው፡፡ ውሻ እንኳን በደል ከበዛበት ባይናከስ እንኳን ባለቤቱ ላይ ያጉረመርማል፡፡
ተቃውሞው ዳር እስከዳር ተቀጣጥሎ ኦህዴድን ከነመኖሩም የረሳው ወያኔ ገዳዮችን አሰማርቶ ተማሪዎችን በመግደል ተቃውሞውን አባባሰው፡፡ በቅርቡ የመንግሥት የህዝብ ግንኙነት ምኒስትር የሆነውና ከማን አንሼ በማለት በስድብና በዛቻ ከዋናዎቹ ወያኔዎች ጌቶቹ ጋር እየተፎካከረ ያለው ግልገሉ ወያኔ አቶ ጌታቸው ረዳ ደግሞ ሕዝቡን አጋንንት ሰይጣን ጠንቋይ እያለ በመሳደብ እሱም በአቅሙ የወያንን እብሪትና ንቀት በማሳየት በእሳት ላይ ቤኒዚን ጨመረ፡፡ ይህም ኦህዴድ ውስጥ ያሉትን ምርኮኞች፤ ወደ ገቦችና ነጻ ሰዎችን በአንድነት ከሕዝቡ እኩል አስቆጣ፡፡
ሰው የሚናገረው ያደገበትን፣ የተማረውን፣ የኖረበትን ወይም እየኖረበት ያለውን ወዘተ ነው፡፡ በመሆኑም አቶ ጌታቸው በስም ከጠራቸው ነገሮች ጋር ትውውቅ የጀመረው መቼ የትና እንዴት አንደሆነና ስለ እነርሱ እንዲህ በጥልቀት ያወቀበትን ምክንያት ባናውቅም የቅርብ ግንኙነት ያለው መሆኑንን ግን ንግግሩ አሰረድቶናል፡፡ በርግጥም ሲናገር የሚጠቀማቸውን ቃላቶች ብቻ ሳይሆን የፊቱን ገጽታ ጭምር ላስተዋለ ከጠቀሳቸው ነገሮች ጋ የቅርብ ትውውቅ እንዳለው ያስታውቃል፡፡ ባይሆንማ ኖሮ የቱንም ያህል መታበይ ልቡን ቢደፍነው፣ የቱንም ያህል ጠመንጃ አምላኪነት ማስተዋልን ነስቶ በጡንቻው አንዲያስብ ቢያደርገው፣ የቱንም ያህል ለከት የለሽነት ቢጠናወተው ህዝብን አጋንንት ሰይጣን ብሎ አይሰደብም በጠንቋይነትም አይፈረጅም ነበር፡፡
እብሪት፣ የህዝብ ንቀት፣ ለከት የለሽነት ወዘተ የወያኔ ባህርይ በመሆናቸው አቶ አባይ ጸሀዬ በዛቻና ድንፋታቸው፣ አቶ ጌታቸው ረዳ በለከት የለሽ አንደበቱ በህውኃትዘንድ ሊመሰገኑና ሊወደሱ እንጂ ሊነቀፉ፣ ሊወገዙና ሊከሰሱ እንደማይችሉ ይታወቃል፡፡ነገር ግን ዘላለማዊ ምድራዊ ኃይል የለምና ጸሀይዋ መጥልቅ የጀመረች እለት ምላሴ ጠንቅ አተረፍሽ ለነፍሴ ማለታቸው አይቀሬ ነው፡፡
ተፈጥሮን ተመክሮ አይመልሰውምና ዋናዎቹ ወያኔዎች የተጠናወታቸው የህዝብ ንቀት እብሪትና ለከት የለሽነት(አፍ እንዳመጣ መናገር) መግደል መደብደብና ማሰር በውስጣቸው ስር ሰዶ የተዋሀዳቸውና ከዚህ ውጪ ሌላም ስለማያውቁ ይቅርብችሁ በሚል የሚሰጣቸውን ምክር መስሚያ የላቸውም፡፡ ሌሎቹ (መለስተኛና አዳዲሶቹ) እኛም እንደ ጌቶቻችን የሚሉ ካልሆኑ ሌላው ሌላው ቢቀር ከላይ የገለጽናቸው ሽማግሌ ለጎረምሳው እንደመከሩት ከናስ ማሰር አፍ ማሰር ይበጃል ልንላቸው እንወዳለን፡፡
ለኦህዴዶች ደግሞ የመጨረሻው መጨረሻ ሲመጣ ከሁለት ያጣ እንደምትሆኑ አስባችሁት ታውቃላችሁ? ወያኔዎች እስከቻሉና የእናንተ አገልጋይነት እስከቀጠለ ድረስ መላዋን ኢትዮጵያን ለመግዛት፣ ጀንበሯ ማዘቅዘቅ ስትጀምርና በአገዛዛቸው መቀጠል የማይችሉበት ደረጃ ላይ መድረሳቸውን ሲረዱ የሚገቡበት ምሽግ እንዳያጡ ሁለቱንም ጎን በጎን እየሰሩ ነው፡፡ የትግራይን ሕዝብ ከሌላው ለመነጠል ወገባቸውን ታጥቀው የሚሰሩትና ትግራይን በሁሉም ረገድ ከሌሎች የኢትዮጵ ክፍሎች የበለጠች ለማድረግ የሚጥሩት ለዚሁ ነው፡፡
እናንተ ግን ምን አላችሁ፣ መሬት ከመቀራመትና ፎቅ ከመገንባት ውጪ ምን በጎ ነገር ሰርታችኋል፡፡ እንደውም ለወያኔ አገላጋይነት አድራችሁ እንወክለዋለን ከምትሉት ህዝብ ጋር ተቆራርጣችኋል፣ ከዚህ አልፋችሁም ደም ተቃብታችኋል፤ የመጨረሻው መጨረሻ ሲመጣ ደግሞ ወያኔ ሜዳ ላይ ጥሎአችሁ ወደ ምሽጉ ሲገባ ህዝቡ እንዳለየ አይቶ ንቆ የሚተዋችሁ ሳይሆን ለበቀል ይፈልጋችኋል ለፍረድ ያቀርባችኋል፡፡ በዛን ወቅት ወያኔ በምንም እንዴትም ሊታደጋችሁ አይችልም፣ ይልቁንም በአገልጋይነት አድራችሁ በሕዝብ ላይ የሰራችሁትን ሁሉ በማጋለጥ ራሱን ነጣ ለማድረግ ነው ዪዳዳው፡፡ ስለሆነም ወያኔ በጠመንጃ አምላኪነት የሚፈጽመውን የመንግስት ሳይሆን የወራሪ ሀይል ተግባር እናንተ የህውሀት አምላኪ ሆናችሁ ማስፈጸሙን በመቀጠል መጪውን ለመቀበል መዘጋጀት ወይንም በቃን ብላችሁ ከህዝብ የሚያስታርቃችሁን ውሳኔ መወሰን ወቅቱ ዛሬ ነው፡፡ህዝብ እንደሁ ይቅር ባይ መሀሪ ነው፡፡
በዚህ መልኩ አንደ ኦህዴድ አቋም መያዝና ራሳችሁን ነጻ ማውጣት የማይቻል ከሆነ ሁለተኛው አማራጭና ምርጫ ስንዴው ከእንክርዳዱ ራሱን መለየት ነው፡፡ ከላይ እንደተገለጸው በኦህዴድ ውስጥ የጦርና የስኳር ምርኮኛ፤ ወዶ ገብ ( ለወያኔ ያደሩ) እና ነጻ ሰዎች መኖራችሁ ቢታወቅም ራሳችሁን በተግባር መግለጽ እስካልቻላችሁ ድረስ በኦህዴድ ላይ የሚቀርበው ተቃውሞና ክስ በጅምላ ሁላችሁንም ነው የሚመለከታችሁ፡፡ ስለሆነም በአንድ ቅርጫት ገብታችሁ ተንቃችሁ ህዝብን እያስናቃችሁ፤ ተባባሪ ሆናችሁ ህዝብን እያስፈጃችሁ መቀጠልና የሚመጣውን ለመቀበል መዘጋጀት አለያም በሌሎች ተጠቃሚነትና ጥፋት ተጠያቂ ላለመሆን ሚናችሁን መለየትና የህዝብ ወገን መሆናችሁን በተግባር ማሳየት ፡፡ ምርጫው የእናንተ የመወሰኛ ግዜአችሁም ዛሬ ነው፡፡
http://wp.me/p5L3EG-8L
Mittwoch, 23. Dezember 2015
አገር እንደዋዛ፤ ስትደርቅ እንደጤዛ (አቢቹ ነጋ)
አገር እንደዋዛ፤ ስትደርቅ እንደጤዛ (አቢቹ ነጋ)
አቢቹ ነጋ
ሁለት ሚሊዮን የሚሆኑ ኢትዮጵያዊያን ተሰደው ይገኛሉ። የስደታቸው ምክንያት ብዙና የተለያየ ስለሆነ መዘርዘር አያስፈልግም። ሁሉንም አንድ የሚአደርግ ነገር ግን አለ። ስደትን ደስ ብሎት የተቀበለ የለም። አንድ ቀን ወደ ሃገር ተመልሶ ሃገሩንና ሕዝቡን መርዳት ሁሉም ይፈለጋል።
ኢትዮጵያዊያኖች በየቀኑ በሚባል ደረጃ ይገናኛሉ። የግንኙነታቸው አድማስ በምንገድና በገበያ አዳራሽ ብቻ የተወሰን ሳይሆን በጸሎት ቤት፤ በድግስ፤ በበዓላት፤ በሐዘን፤ በግልና በመሳሰለው ይገናኛሉ። በምንም መድረክ ይገናኙ ስለሃገራቸው፤ ስለወገናቸው፤ ስለታሪካቸው፤ ባሕላቸው፤ ቀያቸው፤ የሃገራቸው መልካ ምድር፤ ሃይማኖታቸው፤ ኑሯቸው፤ የሃገር ናፍቆታቸው፤ ፖለቲካቸው መነጋገርን ያዘወትራሉ።
አንዳንዴ ብዙ ውይይቶች ጫፍ ደርሰው ሊበጠሱ የደረሱ እስኪመስል ድረስ ይጨቃጨቃሉ። ሁሉም ተወያይ በማንኛውም ጉዳይ ላይ ባለሙያ መስሎ ይታያል። ውይይታቸው ፊት ለፊት ብቻ ሳይወሰን ዘመኑ በወለደው የመገናኛ ብዙሃን፤ ማህበራዊ ድረ ገጾች፤ ቴሌ ኮንፈረንሶችን በመጠቀም ይደረጋል። አንዱ ሌላውን ግልሰበ ሲአብጠለጥል፤ አንዱ ቡድን ሌላውን ሲኮንንና ሲአወግዝ መስማትና ማየት ልምድና በሐሪ ሆኗል። ብዙውን ጊዜ እነዚህ ውይይቶችና ክርክሮች ለችግሩ መፍቴሄ ሳይሰጡ ጥፋትን፤ ስህተትንና ውግዘትን አጉልተው ይቋጫሉ።
ብዙዎች ይህ የኢትዮጵያዊያን መገለጫ የሆነውን ባሕሪ ያወግዛሉ። እንደዚህ ጸሐፊ እይታ ከሆነ እርር ትክን ያለ፤ እስከ መጣላት የሚአደርስ ውይይት የሚአደርጉት ሃገራቸውንና ሕዝባቸውን ከመውደዳቸው የተነሳ ብቻ ሳይሆን ጤናማና አዋቂነትም ነው ይላል። ሃገርን ከማፍቀር የተነሳ ለሕዝቧ ይበጃል የሚሉትን ሐሳብ መሰንዘራቸው ሊአስወግዛቸው አይገባም። አለመንጋገርና አለመወያየት ግን የጤናማ በሐሪ ምልክት አይደለም ሊሆንም አይችልም። መነጋገርና መወያየት ካለ ለችግሮች መፍትሔ ማግኘት ይቻላል።
ሰሞኑን የአዲስ አበባ ማስተር ፕላንን በመቃውም በተነሳው ሕዝባዊ ተቃውሞ ኢትዮጵያ እየታመሰች ትገኛለች። በሃገር ቤት በተከሰተው የፖለቲካ ቀውስ ዳያስፖራ ኢትዮጵያዊያን ልባቸው ተሰብሯል፤ ደንግጠዋል፤ ተጨንቀዋል፤ ሱባኤ ገብተዋል። አምላክ በቅዱስ እጁ ሃገራቸውን እንዲባርካትና እንዲቃኛት ፈጣሪያቸውን ተማጽነዋል። ምክንያቱ ግልጽ ነው-ቀውሱ ከቀጠለ የሚወዷት ሃገራችው ልትፈርስና ብትንትንዋ ሊወጣ በመሆኑ ሰግተዋል። ብዙዎችም የሚፈራው እንዳይሆን ምንመደረግ አለበት ብለው ሌት ተቀን ሲለፉ ይታያል። አገሪቱ ከፈረሰች መግቢያ ሊጠፋ ነው። በሶማሊያ፤ በሶሪያ፤ በአፈግሃኒስታን፤ በኢራክ፤ በሩዋንዳ፤ በሊቢያ፤ በማሊ ወዘት ከወደቁት አገሮች (Failed States) ጎራ ልትመደብ ነው የሚል ስጋት አላቸው። ይህ ከሆነ ደግሞ ባለሶስት ቀለሙ፤ ባለ ወርካው ፣ ባለመዶሻው ፣ የአማራው፣ የኦጋዴኑ፣ የደቡቡ፣ የጉራጌው፣ የቤንሻንጉሉ፣ የጋሞው፣ የቅማንቱ (ስንቱ ተዘርዝሮ ያልቃል) ባንዲራ የሚውለበለብበት መሬትና ወጋግራ አይኖርም። ያለ ሃገር የጎሳ ጥያቄ አይኖርም። ማፍረስና ማውደም ለሁሉም ቀላል ስራ ሲሆን መልሶ መግጠም ግን ይቸግራል። በዛ ጊዜ ቄሱም፤ ሸሁም፤ ፓስተሩም ዝም መጽሃፉም ጎሳውም ዝም ይሆናል።
ሁል ጊዜ እናቶቻችን እንዲህ ሲሉ ይመክራሉ-አይሆንምን ትቶ ይሆናልን ማሰብ ይላሉ። ይህም የቅድሚያ ዝግጅት (Contingency Planning) ያስፈልጋል እንደማለት ይሆናል። ዕውነት አላቸው- ማሰባቸው ተገቢ የመስላል።
የኢትዮጵያዊያን ስጋትም እንዲሁ በአየር ላይ የተፈበረከ፤ መሰረተቢስ፤ ተራ መላምትና የናፋቂነት አስተሳሰብ አይደለም። የኢትዮጵያን ፖለቲካያዊ፤ ኢኮኖሚያዊ፤ ማሕበራዊ፤ አስተዳደራዊ፤ ሕጋዊ መስፈርቶች (Indicators) ለሚከታተልና ሰክን ብሎ ለሚአስብ ሰው ብዙ ጉዳዮች ዓይናቸውን ያፈጠጡ እውነታዎች ናቸው። ከወደቁት አገሮች ጋር ሊአስመድባት ወይም ወደዚያ እያንደረደሯት ያሉ ምልክቶች በገሃድ ይታያሉ። አሁን እዚህ ደረጃ አልደረስንም። ጉዞው ግን ፈጥኗል። እሩቅ አይደለም። ስለሆነም ለብዙዎቻችን ሁሉም ነገር ጨልሟል።
ጨለማውን ወደ ብርሃን መቀየር ይቻላል። አዎ እንችላለን (YES WE CAN) ብለን በአንድነት ከተነሳን ይቻላል። መፍትሔው በየአንዳንዳችን ቤትና ቡድን እጅ ይገኛል። ሩቅ መሄድ አይኖርብንም። ለብዙ ዓመታት ብዙ ተከራክረናል። ክርክሩ ይብቃ። መፍትሄው ላይ እንስራ። በእጃችን የሚገኝ መፍትሔ አለ። መፍትሔው ከየአንዳንዳችን የሚጠበቅበት ጊዜ ትላንት ወይም ነገ ሳይሆን ዛሬ ነው። በየለቅሶ ቤቱ፤ ጸሎት ቤቱ፤ በግብዣው፣ በአደባባይና በመንገድ ስናወጣና ስናወርዳት የነበረችውን ኢትዮጵያ በተግባር የምንታደግበት አስራ አንደኛው ስዓት ላይ ደርሰናል። ወደድንም ጠላንም የመጣንበት ጎሳ ሳይሆን የመጣንበት ሃገር ገላጫችን እንደሆነ አንዘንጋ።
ከሰሞኑ የሚታየው የሕዝብ እንቅስቃሴ ሁሉን አቀፍ መሆኑ ያስደስታል። ቀድሞ ነጻ አውጪ ነን እያሉ ይሰብኩ የነበሩት እንደ ሌንጮ ለታ ዓይነቶች በኢትዮጵያ ጥላ ስር ለመስራትና ለእርቀ ሰላም ጥሪ ሲአቀርቡ ማየትና መስማትን የመሰለ ትልቅ ተስፍ ሰጪ ነገር የለም። በእጃችን ያለው መፍትሔ የሚባለው ምሳሌም ይህ ነው። ሌሎችም ይህን ፈለግ ሊከተሉ ይገባል። በስልጣን ላይ ያለው መንግሥትም ከሕዝብ ጋር ለመነጋገር ዝግጁነቱን በአስቸኳይ ለሕዝብ ማብሰር አለበት። ይህን ካላደረገ ኪሳራው ይበልጥ የሚጎዳው እራሱን ነው።
በየስርቻወ ነጻ አውጪ እየመሰረቱ መናቆር ለማንም የሚበጅ አይሆንም። መገንጠልና ነፃነት መፍትሔ ቢሆን ኖሮ በኤርትራ፤ በደቡብ ሱዳን፤ በፓኪስታን ወዘተ ያለው ሁኔታ ባልታየ። ይህን የሚፈልግ ኢትዮጵያዊ ይኖርላ ብሎ ለማመን ይቸግራል። ካለም የሚወክለው ጥፋትን ነው። ስለዚህ ዓማራ፤ ኦረሞ፤ ትግሬ፤ ጉራጌ፤ ደቡብ ሕዝቦች፤ ኦጋዴን፤ አፋር፤ ቤንሻንጉል፤ ጉራጌ ወዘት ሳይባል መነሳት ያስፈልጋል። ለነገሩ ብዙዎቻችን የነጻ አውጪ መሪዎችን ጨምሮ የጎሶችን ክልል እንኳን ጠንቅቀን አናውቅም።
ይሀን ካላደረግን አገር አንደዋዛ ትጠፋና መጨረሻችን እንደ ጤዛ ተኖ በወጡበት መቅረት ይሆናል። በአገር ቤትም ሆነ በውጭ ያለው ኢትዮጵያዊ መንቃት አለበት። ቢረፍድም አልዘገየምና አገራችንን ከውድመት እንታደጋት። ሳይኖራት አስተምራ፤ አብልታና አጠጥታ አሳድጋናለች። ዓማረ አረጋዊ ‘መንግሥት እራሱን ይፈትሽ’፤ የሻቢያው ተስፋዬ ገብረአብ ‘ጎዳናው የት ያደርሳል’ ብለው ያስነበቡን መጣጥፎች’ ምክሮች ለሁላችንም የሚመቹ ናቸው። እናዳምጣቸው። አንዳንዴ ከምናምኑም የርግብ እንቁላል መጠበቅ ክፋት የለውም። መርዝም መድሐኒት ይሆናልና። መሬቱ ሰፊ አየሩ ምቹና ለሁላችንም በቂ ስለሆነ እንወቅበት። አመሰግናለሁ።
አቢቹ ነጋ (aneganega2013@gmail.com)
ታሕሳስ 12, 2008
Dienstag, 22. Dezember 2015
በሰሜን በጌምድር (ጎንደር) ወልቃይት ፀገዴ፣ ፀለምት በአማራው ላይ ተስፋፊው ተሓህት/ህወሓት የፈጸመው የዘር ማጽዳት ወንጄል (ገብረመድህን አርአያ)
በገብረመድህን አርአያ
ይህ ታሪካዊ መረጃ በተቀነባበረ መልኩ የሚጀምረው ገና ተጋድሎ ሓርነት ህዝቢ ትግራይ (ተሓህት) ሲፈጠር ጀምሮ አስቀድሞ ለማጥፋት ያነጣጠረው በአማራው ህዝብ ላይ እንደሆነ በማስገንዘብ ነው።
ከዚህ በመነሳት የተሓህት ፕሮግራም ገና ከ1967 ጀምሮ የረቀቀው በዲማ ኮንፈረንስ በየካቲት ወር 1968 ከ150 ያነሱ የተሓህት ታጋዮችን በማሰባሰብ ሕጋዊ ሆነ ተብሎ ቢነገርም፣ ሁሉም ታጋዮች ግን አልተቀበሉትም። በመጥፎ መልኩ የተዘጋጀውና አማራውን በማውገዝና ጠላት ብሎ የፈረጀ ነው። በኢትዮጵያና በህዝቧ፣ 1ኛ፣ የኢትዮጵያን ሉአላዊነት አውዳሚ፣ 2ኛ፣ አንድነቱን ጠብቆ ለዘመናት አብሮ የኖረውን የኢትዮጵያ ህዝብ በጎሳ በዘር ለመበታተን ተደምሮና ተቀንሶ የተቀነባበረ አደገኛ ፕሮግራም በማለት አውግዘውት ነበር። ከነዚህ ካወገዙት መካከል ለምሳሌ ለመጥቀስ፤ አስገደ ገብረሥላሴ፣ ካህሳይ በርሄ (ዶ/ር ግንጽል)፣ ተሾመ ጉዶ፣ ሲሆኑ እነዚህ በህይወት ያሉ ሲሆን፣ እቁባዝጊ በየነ፣ አሰፋ ገብረዋእድ፣ አጽብሃ ዳኘው፣ ዘርኡ ገሰሰ (አጋአዚ) ገሰሰው አየለ፣ ዶ/ር አታክልት ቀጸላ፣ ዘወንጀል በየነ፣ መሃረ ተክሌ ወዘተ እነዚህ ፕሮግራሙን በጠነከረ አቋም ስለተቃወሙ የተገደሉ ናቸው። [ሙሉውን ለማንበብ እዚህ ይጫኑ]
Samstag, 19. Dezember 2015
የኢትዮጵያዉያን አንድነት – ለወያኔ ግብዐተ መሬት (ይገረም አለሙ)
የኢትዮጵያዉያን አንድነት – ለወያኔ ግብዐተ መሬት (ይገረም አለሙ)
በኢትዮጵያ የነበሩት መንግስታት ዴሞክራሲያዊ አስተዳደርን ማስፈን ባይሆንላቸው ለሀገራቸው ቀናኢ ነበሩና ሱዳን ከኢትዮጵያ የምትመኘውን መሬት ለመወሰድ የነበራት የዘመናት ህልም ሳይሳካ ኖሯል፡፡ አሁን ግን በስም እንጂ በተግባር ኢትዮጵያ መንግሥት አልባ የሆነችበትን ይህን አጋጣሚ በመጠቀም የዘመናት ምኞቷን ለማሳካት ከወያኔ ጋር እየተሞዳመደች ነው፡፡ ይህን ድብቅ የአቶ መለስ ዜናዊ ሴራ የወያኔ ባለሥልጣኖች ለመደበቅ ቢጣጣሩም የሱዳን ጋዜጦች በደስታና በአሸናፊነት ስሜት እየዘገቡት ለማወቅ ተችሏል፡፡
ይህ የድብቅ ስምምነት ተግባራዊ ሆኖ ከኢትዮጵያ ሕዝብ እውቅናና ፍላጎት ውጪ ሱዳን መሬት ለመውሰድ ብትችል ሰላም የማታገኝበት ለትውልድም ግዜ እየጠበቀ የሚፈነዳ ፈንጂ ማቆየት መሆኑን በዋሽንግቶን ዲሲ በሚገኘው የሱዳን ኤንባሲ ሰላማዊ ሰልፍ የወጡ ኢትዮጵያውያን አስገንዝበዋል፡፡ የዚህ ሰልፍ ተካፋይ ለመሆን ከሌላ ከተማ የተገኙ የኦሮሞ ተወላጅ ኢትዮጵያውያን በቦታው ሲደርሱ መጣን ተቀበሉን ማለታቸውን ስሰማ የወያኔ የመቶ አመት የቤት ሴራ አበቃለት ይሆን! በማለት ሳላውቀው አይኔ በእንባ ተሞላ፡፡ ለካስ ከሀዘን ባላተናነሰ ደስታም ያስለቅሳል፡፡የአመታት ምኞት እውን ሲሆን ማየት አይንን አንባ ያስረግዛል!!
በዚሁ ስብሰባ ላይ የተገኙት አቶ ገመቹ የተባሉ ሰው እኛ የኦሮሞ ተወላጆች የወያኔን የከፋፍለህ ግዛ አጥር ሰብረን ስንመጣ እናንተ አማራና ቅማንት ተባብላችሁ ተከፋፍላችሁ ጠበቃችሁን፤በጣም አዝነናል ይህን የወያኔን ሴራ በጥሳችሁ በአንድ ኢትጵያዊነት መንፈስ እንድትቆሙ ጥሪ እናስተላልፋለን በማለት የገለጹት ወቅታዊ መልእክትም ልብ የሚነካ ነበር፡፡ መለያየት በቃ እንበል!
ተደጋግሞ እንደተገለጸው ወያኔ በስልጣን መቆየት የሚችለው ኢትዮጵያውያንን ሰበብ እየፈጠረ ማለያየት፤ እሳት እየጫረ ማገዳደል የሀሰት ወሬ እየነዛ በጥርጣሬ እንዲተያዩ ማድረግ እስከቻለ ብቻ ነው፡፡ የኢትዮጵያውያን አንድነት የወያኔ ግብአተ መሬት መሆኑን ከማንም በላይ ቁንጮዎቹ ወያኔዎች በሚገባ ያውቃሉ፡፡ ሰለሆነም እንቅልፍ አጥተው የሚያልሙትና የሚሰሩት እንዴት በምን መንገድና ስልት እንዲሁም መቼና የት ኢትዮጵያዉያንን በተለይ አማራና ኦሮሞን ርስ በርስ እንደሚያበጣብጡ ነው፡፡
ሀያ አራት አመት ሙሉ በጽሁፍ፤ በንግግር ፤ በዘፈን ወዘተ የተላለፉ መልእክቶች የወያኔን የመከፋፈል ሴራ አክሽፈው አንድነትን ሊያመጡ አልቻሉም ነበር፡፡ ሎሬት ጸጋየ ገብረ መድህን በአንድ ግጥሙ የሰው ልጅ ሀ ብሎ ከፊደል ወይንም ዋ ብሎ ከመከራ ይማራል እንዳለው እነሆ ዛሬ ህዝቡ ከመከራ ተምሮ ከፖለቲከኞቹም ቀድሞ ወደ አንድነት እየመጣ ነው፡፡
ከህዝቡ ቀድመው የወያኔን ሴራ ሊያከሽፉ፣አርአያ ሆነው አንድነትን ሊያጠናክሩ፣ግንባር ቀደም ሆነው ትግሉን ሊመሩ ይገባቸው የነበሩ ብዙዎቹ ፖለቲከኞች ከገቡበት ህልም ሳይነቁ ሕዝቡ ቀደማቸው፡፡ መምራቱ ባይሆንላቸውም የህዝቡ ተነሳሽነት እያናቃቸው፤ እየተከፈለ ያለው መስዋዕትነትም ከየግል ጠባብ አመለካከትና የሥልጣን ጥም ተላቀው ለህዝብ ትግል ቅድሚያ እንዲሰጡና ስለ አንድነት እንዲያስቡ እያደረጋቸው መሆኑን እያን እየሰማ ነው፡፡ እሰየው፣ ይበል የሚያሰኝ ነው፡፡
ሎሬት ጸጋየ ገብረ መድህን የአባቶቻችንን ጥረት ሳስታውሰው ትዝ ሲለኝ ከሞከርነው ነገር ይልቅ ያልሞከርነው ነው የሚቆጨኝ እንዳለው ትናንት፣ ትናንት በስትያ በሆነው ባደረግነው የምናዝን የምንቆጭና በዚሁም የምንወቃቀስ ሳይሆን ልናደርገው ሲቻለን ያላደረግነውን ልናውቀውና ልንሄድበት ሲገባን ያላወቅነውንና ያልሄድንበትን መንገድ ለይተን (ይህም አንድነት ነው) የተጀመረው ትግል ከውጤቱ መስዋእትነቱ የማይከፋበትንና ለድል የሚበቃበትን ስራ መስራት ወቅታዊና አንገብጋቢ ጉዳይ ነው፡፡
ለዚህ ደግሞ ቀዳሚውና ዋናው በየግል ከምትሰጡት መግለጫና ከምታደርጉት እንቅስቃሴ አልፋችሁ ድምጻዊ ቴዲ አፍሮ ገና በ 97 ምርጫ ዋዜማ ጃ ያስተሰርያል ብሎ ባዜመው ዘፈኑ እስቲ ተባበሩ ይያዝ እጃችሁ አለበለዚያማ በምን ያስታውቃል እኛን መውደዳችሁ ያለውን ዛሬ ከአስር አመት በኋላ ተግባራዊ ማድረግ ነው፡፡ የትናንት ልዩነቶችን ወደ ጎን ብሎ እጅ ለእጅ ተያይዞ መታየትና በተግባርም በጋራ መንቀሳቀስ ነው፡፡ ፖለቲከኞቻችን በዚህ መልክ ብትታዩ ከምንም በላይ የወያኔን የከፋፋይነት ሴራና ስራ ታከሽፋላችሁ ብቻ ሳይሆን የመቶ አመት የቤት ስራ የሚለውን ከምንጩ ታደርቃላችሁ፡፡ ለተጀመረው ትግልም ብርታትና ቀጣይነት ሀይል ትሰጣላችሁ፤ በተግባር ደግሞ ኢትዮጵያ ወደ ዴሞክራሲያዊ ስርኣት የምታመራበትን ስልትና መንገድ በጋራ ትቀይሳላችሁ፤ድል ያለመስዋዕትነት ባይገኝም ከድሉ መስዋዕትነቱ እንዳይከፋ ማድረግ ትችላላችሁ፣ በጥቅሉ ድሉን ታቃርባላችሁ፡፡
በታላቁ መጽኃፍ ከፍሬያቸው ታውቋቸዋላችሁ ተብሎ እንደተጻፈው ይህ ወቅት ኢትዮጵያ ከወያኔ አገዛዝ ተላቃ ዴሞክራሲያዊት ሀገር እንድትሆን የሚሹና የሚታገሉ፣ በተቃራኒው በስመ ተቀዋሚ እያጭበረበሩ የኖሩና አሁንም በዚሁ መንገድ መቀጠል ዓላማቸው የሆኑ ፖለቲከኞችና ፓርቲዎች የሚለዩበት ነው፡፡ እስካሁንም መለየት እየተቻለ ነው፡፡ ለኢትዮጵያ ህዝብ ነጻነት ለሀገሪቱም ዴሞክራሲያዊነት ነው የምንታለው የምትሉ ወገኖች ህዝቡ እያሳየ ያለውን አንድነት እናንተ ተግባራዊ ማድረግ ተስኖአችሁ ይህ ህዝብ ከባድ መስዋዕትነት እየከፈለበት የሚገኘው ትግል በዚሁ መልኩ ብቻ ቀጥሎ በወያኔ ቢጨፈለቅ ከወያኔ ባልተናነሰ በታሪክና በትውልድ ትጠየቃላችሁ፡፡
መስዋእትነቱ ሊከብድ የድሉ ወቅት ሊረዝም ይችል ይሆናል እንጂ የኢትዮጵያ ሕዝብ እንደሆነ የትእግስቱን ያህል ሲያመር የሚያደርገውን ማወቅ የፈለገ ያውቀዋል፡፡ ሰሞኑን የሚታየውም ከበቂ በላይ ገላጭ ነው፡፡ ሕዝቡ ካመረረ መሪ ማጣት ለግዞት እንደማያንበረክከው የአምስት አመቱ የአርበኝነት ታሪኩም ያስረዳል፡፡ ዘር ሳይመነዝር የቋንቋም ሆነ የሀይማኖት ልዩነት ሳይፈጥር በአርበኞች እየተመራ እንዲያም ሲል ከመካከሉ የጎበዝ አለቆችን እየመረጠ በዱር በገደሉ ተዋግቶ ከፊሉም ከጣሊያን ጋር መስሎና ተመሳስሎ በውስጥ አርበኝነት ታግሎ ነው ለነጻነት የበቃው፡፡
በርካታ ፖለቲከኞችና የፖለቲካ ድርጅቶች ባሉበት በዚህ ዘመን ግን የህዝብ ትግል መሪ አጥቶ ወደ ጎበዝ አለቃ ምርጫ ሊደረስ አይታሰብም፡፡ እናም ለሥልጣኑ መቆየት ሲል ሕዝብ ቢያልቅ ሀገር ቢጠፋ ደንታ የሌለው ወያኔ ራሱም እየገደለ ርስ በርስም እያገዳደለ ዜጎች በየቀኑ እየሞቱ በመሆኑ ፖለቲከኞቻችን ሀላፊነታችሁ ከባድና ውስብስብ ነውና ፍጠኑ፤ እስከዛሬ የለበሳችሁትን ሱፍም ሆነ ገበርዲን አስቀምጡና ኢትዮጵያዊ ኩታ ለብሳችሁ ስለ ዴሞክራሲ እያዜማችሁ እጅ ለእጅ ተያይዛችሁ እናያችሁ፡፡ ፈጠናችሁ ሸንጎ ተቀመጡና ትግሉ ተጠናክሮና ሰፍቶ ስለሚቀጥልበት፤ መስዋእትነቱ ስለሚቀንስበትና ድሉ ስለሚቃረብበት ዘዴና መንገድ ተነጋገሩ አቅዱ ተንቀሳቀሱ፡፡
የኢትዮጵያውያን አንድነት ለወያኔ ግብዐተ መሬት ነው፡፡ በመሆኑም አንዱ የሌላውን ግብዣና ጥሪ መጠበቅና ይህን ላለመገናኘት ምክንያት ማድረግ አሁን ግዜው አልፎበታል፡፡ በዲሲው ሰልፍ ላይ ተገኝተው መጣን ተቀበሉን እንዳሉት የኦሮሞ ተወላጆች ሁሉም መጣን ተቀበሉን ማለት አንዱ ወደ ሌላው መሄድ ይኖርበታል፡፡ ርስ በርስ እየተጠራሩና አንዱ የሌላውን በር እያንኳኳ በአንድ መድረክ መገናኘትና መምከር ግዜ የሚሰጠው አይደለም፣ እናም ፍጠኑ፡፡ ይህን ማድረግ ደግሞ ህዝቡ እየከፈለው ካለው መስዋዕትነት አንጻር ሚዛን የሚደፋ አይደለም፡፡ታሪክ ለክብር ያጫቸው ኢትዮጵያዉያን የሚታዩበትም የሚፈተኑበትም ወቅት አሁን ነው፡፡
እግዚአብሄር ኢትዮጵያን ይጠብቅ
http://wp.me/p5L3EG-8B
Dienstag, 15. Dezember 2015
ኦሮሞ እና እስልምና በ“ሕዳሴ አብዮት” መስመር (ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ)
ኦሮሞ እና እስልምና በ“ሕዳሴ አብዮት” መስመር (ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ)
በወርሃ-ግንቦት ላይ ለዘመናት የተንሰራፋውን ሀገራዊ ደዌ ይፈውሳል ብዬ ተስፋ ስለማደርግበት “የሕዳሴ አብዮት” በሶስት ተከታታይ ክፍሎች ለመዳሰስ መሞከሬ ይታወሳል፡፡ በወቅቱ መጪው የ “ሕዳሴ አብዮታችን” መፍትሔ ሊሰጥባቸው ከሚገቡ ጉዳዮች መሀል በዋነኝነት የኦሮምኛ ቋንቋ ተናጋሪው ማሕበረሰብ እና የእስልምና እምነት ተከታዮች የመብት ጥያቄን በተመለከተ በጥቅሉ ጠቃቅሼው አልፌ ነበር፡፡ ሆኖም ‘ሰፋ ብሎ ቢዳሰስ’ የሚሉ በተለያየ መንገድ የሚቀርቡ ጎትጓች ድምፆች መበራከታቸው የመነሻ ሃሳቡን ፈታ አድርጌ እንዳቀርብ አስገድዶኛል፤ እንግዲህ ይህ ጭብጥም የዛው ተከታይ መሆኑ ይሰመርልኝ፡፡
የኦሮሞ ጥያቄ
በኢትዮጵያችን ከሚገኙ በርካታ ብሔሮች መካከል አብላጫውን ቁጥር የሚይዘው ኦሮምኛ ተናጋሪው ቢሆንም፣ ለዘመናት ይደርሱበት ከነበሩ ሥርዓታዊ በደሎች እና የባሕል ጭፍለቃዎች ዛሬም በምልአት ነፃ እንዳልወጣ በቂ ማሳያዎች አሉ፡፡ በ1960ዎቹ አጋማሽ የአገሪቷ አደባባዮች የዘመኑን መንፈስ በተረዱ ቁጡ ወጣቶች መጥለቅለቁን ተከትሎ፣ ‹በንጉሣዊው አገዛዝ ግብዓተ-መሬት ላይ የመጨረሻዋን ድንጋይ ለማስቀመጥ› በሚል ሰበብ ቤተ-መንግስቱን መቆጣጠር የቻለው ወታደራዊው ደርግ፣ ህልቆ መሳፍርት በሌለው መስዋዕትነት የተገኘውን ወርቃማ ዕድል ከጅማሮው አጨናፍጎታል፡፡ በግልባጩ አብዮቱን ካጋሙት ገፊ-ምክንያቶች ዋንኞቹ ለሆኑት የብሔርና የሕዝባዊ መንግስት ምስረታ ጥያቄዎች፣ መፍትሄ ይስጥ አይስጥ እስኪረጋገጥ ድረስ መታገስ ያልፈለገው ህወሓት፣ ጉዳዩ በደም መፋሰስ ብቻ እንደሚፈታ አውጆ ጫካ ሲገባ አዲሱ መንግስት ገና የ6 ወር ጨቅላ እንደነበረ አይዘነጋም፡፡ ይሁንና ታሪክ በአስከፊ መልኩ ራሱን ሲደግም ያስተዋልነው ወታደራዊውን መንግስት መንፈቅ-ዓመት ያህል እንኳ መታገስ ያልፈቀደው ይህ ቡድን፣ ለጥያቄዎቹ መልስ ሳይሰጥ ከሁለት አስርታት በላይ ያለመንግራገጭ በሥልጣን ለመቆየት ባለመቸገሩ ነው፤ ርግጥ የእኔ ትውልድም የእድሜውን እኩሌታ በትግስት መጠበቁ የአደባባይ እውነታ ቢሆንም፣ ተጨማሪ የቻይነት ዓመታት ይኖራሉ ብዬ ግን አላስብም፤ አብዮቱን ምኩንያዊ የሚያደርገውም ይህ ነው፡፡ …እነሆም ከአራት አስርታት በላይ ሲንከባለሉ የቆዩት የኦሮሞ ጥያቄዎች በ“ሕዳሴ አብዮት” ይፈቱ ዘንዳ፣ ሊተኩርባቸው የሚገቡ አንኳር አጀንዳዎችን በሁለት አውድ ከፍለን እንመለከታለን፡፡
፩
ኢህአዴግ-መራሹ መንግስት ጥያቄዎቹን ከወረቀት ድንጋጌ (ከአፋዊነት) እና ከፕሮፓጋንዳ ሽንገላ ባለፈ፣ እውነተኛ መፍትሔ በሚያስገኝ መልኩ እልባት ሊያበጅላቸው አልፈቀደም፤ ባለፉት ሃያ ሶስት ዓመታት ‹‹አነበርኩት›› የሚለው ቋንቋ ተኮር ፌዴራሊዝም የይስሙላ ስለመሆኑ ለመገንዘብ፣ ዛሬም ከደርዝን በላይ የፖለቲካ ድርጅቶች የራስ አስተዳደር ጥያቄን አንግበው በትግል መድረክ መገኘታቸውን ማየቱ በቂ ነው፡፡ የክልሉ ‹‹ገዥ›› እንደሆነ የሚነገርለት ኦህዴድም ቢሆን፣ የህወሓቱ የአማርኛ ክንፍ እንደሆነው ብአዴን ሁሉ፣ የኦሮምኛ ክንፍ ከመሆን አለማለፉን፣ የብሔሩ ልሂቃንን ጨምሮ የፌደራል ሥርዓቱን አወቃቀር ያጠኑ በርካታ ምሁራን ማስረጃ እያጣቀሱ ያጋለጡት እውነታ ነው፡፡ ሕዝቡም በየጊዜውና በየአጋጣሚው የሚያነሳው ጥያቄ አሁንም ተግ አለማለቱ የልሂቃኑ ማስረጃ መሬት መርገጡን ያስረዳል፡፡ በቅርቡ አፈ-ጉባኤ አባዱላ ገመዳ ስለሕጋዊነቱ በድፍረት የደሰኮረለት የማስተር ፕላኑ ጥያቄ በኃይል መጨፍለቅም በገዥው በኩል ሕገ-መንግስቱ አፈር ለብሶ እንዳበቃለት ተናግሮ አልፏል፡፡በተጓዳኝ የክልሉ ነዋሪ በተፈጥሮ ሀብቱ ተጠቃሚ እንዳይሆንና ፍትሃዊ የሀብት ክፍፍል እንዳይኖር ከመደረጉ ባሻገር፤ ከሕዝቡ ቁጥር ብዛት አኳያ ኦሮምኛ በሁለተኛ ብሔራዊ የሥራ ቋንቋነት እንዲያገለግል ኦህዴድ ተፅእኖ የሚፈጥር አልሆነም፤ ሌላው ቀርቶ ጥያቄውን በሰላማዊ መንገድ ያነሱ ፖለቲከኞች ‹‹ኦነግ›› ተብለው የምድር ፍዳቸውን ሲቀበሉ የታደጋቸው የለም፡፡ የዚህ እኩይ ድርጊት ተጠያቂም ጉልበተኛው ህወሓት ብቻ ነው ማለት ገራገርነት ይመስለኛል፤ የገዛ ወገኑን አሳልፎ የሰጠው ኦህዴድም ጭምር የድርሻውን መውሰዱ አይቀሬ ነውና፡፡ ይህም ሆኖ ከአንዳንድ ምልክቶች በመነሳት ጥያቄዎቹ መልስ እስካላገኙ ድረስ፣ የቱንም ያህል የእስር ቤት ደጃፎች ከዚህም በላይ ቢጨናነቁ፣ የቱንም ያህል የእስረኞቹ ሰቆቃ እያደር ቢበረታ ከእንግዲህ በኦሮሚያ ምድር በፍርሃት ዝም-ጭጭ ብሎ የሚተኛ ሊኖር እንደማይችል ዛሬ ላይ ቆሞ መናገሩ ‹‹ሟርተኛ›› አያስብልም፡፡
፪
የኦሮምኛ ተናጋሪውን ያደረ ቅራኔ በመፍታት የአንድነት ዘብ ለማድረግ፣ የሀገሪቱ ታሪክ እና ባሕል በዳግም ብያኔ መታደሱ ግድ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ የክልሉ ማሕበረሰብ በዘመናዊው መንግስት ምስረታም ሆነ ከባእድ ወረራ መታደጉ ላይ ታላቅ አበርክቶ ቢኖረውም፣ በሀገሪቷ ታሪክ ውስጥ ሚናው ደብዝዞ መገለፁ ጎምዛዛ እውነት ነው፤ የቋንቋው ተናጋሪ ያልሆነው አብዛኛው ኢትዮጵያዊም ይህንን አምኖ ሊያርመው ቀርቶ፣ እውቅና ሊሰጠው እንኳ አለመፍቀዱ፣ ጉዳዩን ወደሰሞነኛው ‹‹ውጡ ከሀገራችን›› አይነቱ አስደንጋጭ ኩነት ገፍቶታል፡፡ ከዚህ በተቃራኒው በጥቂት የብሔሩ ልሂቃን የሚንፀባረቀው (ሀገርን ለፍርሰት ሊያጋልጥ የሚችለው) ሸውራራ የታሪክ አረዳድን እና የቅኝ አገዛዝ ትርክትን ማጥራት ሌላው ወሳኝ የቤት ሥራ ሆኗል፤ ምክንያቱም ከጥያቄው ጋር ተያይዘው የሚነሱ የተቃውሞ ድምፆች ማጠንጠኛ ‹ባሳለፍነው መቶ ዓመት ለቅኝ አገዛዝ ተዳርገናል፣ ሥርዓታዊ በሆነ መዋቅር የሥልጣን ባይተዋር ሆነን ቆይተናል፣ ከሌላው ሕዝብም በተለየ መልኩ ከሰብአዊ ፍጡር በታች ተቆጠረን ተረግጠናል…› የሚል መንፈስ እንዲይዝ እየተለጠጠ ነው፡፡ ይህ የታሪክ ትንተና ስሁት መሆኑን የምንረዳው በየትኛውም መንግስታዊ ሥልጣን ጊዜ (ሀገሪቱ በጦር መሪዎችም ሆነ በነገሥታቱ ጠንካራ መዳፍ ስር በተያዘችበት ዘመን) በግንባር ቀደምትነት በመንበሩ ላይ ይፈራረቁ ከነበሩት አማርኛና ትግርኛ ተናጋሪዎች የማይተናነስ እኩል ሚና እንደነበራቸው የቋንቋው ተናጋሪ ምሁራን በማስረጃ አስደግፈው ባዘጋጇቸው ድርሳኖቻቸው ያተቱትን ስናስተውል ነው፡፡
ለማሳያም ‹‹የጎንደር ዘመን›› ተብሎ ከሚጠቀሰው (እ.ኤ.አ ከ1636-1769 ዓ.ም ድረስ የዘለቀው) ማዕከላዊ መንግስት ውድቀት በኋላ የተተካውና ‹‹ዘመነ መሳፍንት›› እየተባለ የሚጠራው አገራዊ የአስተዳደር ዘይቤ ጠንሳሽና ተግባሪ የኦሮምኛ ቋንቋ ተናጋሪዎች እንደነበሩ ማስታወሱ በቂ ነው፡፡ በወቅቱ የመንግስቱ መቀመጫ ከሰሜን ጎንደር ወደ ደብረታቦር የተዘዋወረ ሲሆን፣ የግዛት ወሰኑ ደግሞ ጎንደርን፣ ወሎን፣ ጎጃምን፣ ከፊል ሸዋንና ትግራይን የሚያካትት እንደነበር መዛግብቱ ያወሳሉ፡፡ በዘመኑ ሥልጣኑን የጠቀለሉትና ‹‹የጁ (ወራ-ሼክ) ስርወ-መንግስት›› በሚል ስም የሚጠሩት የአሮምኛ ቋንቋ ተናጋሪዎች እንደነበሩ የብሔሩ ምሁራን ነግረውናል፡፡ እያገባደድነው ባለው በዚህ ዓመት ‹‹የውገና ድርሰቶችና የታሪክ እውነቶች›› በሚል ርዕስ ዳጎስ ያለ ጥራዝ ያሳተሙት ታቦር ዋሚ ‹‹በኢትዮጵያ ታሪክ ዘገባዎች አላግባብ ዘመነ መሳፍንት ሲባል የቆየው የየጁ ዘመንና ታሪካዊ ሚና›› በሚለው ንዑስ ርዕስ ሥር በርካታ መጽሐፍትና የጥናት ጽሑፎችን በመጥቀስ ሥልጣኑ በኦሮምኛ ቋንቋ ተናጋሪዎች እጅ እንደነበረ በስፋት አብራርተዋል፡፡
ታቦር በትርክታቸው ‹‹የጁ ከሰሜን ኢትዮጵያ የኦሮሞ ነገዶች አንዱ እንደሆነና ቀስ በቀስም ይህ ስም የጎሳው ብቻ ሳይሆን ሕዝቡ የሰፈረበት አካባቢ ጭምር መጠሪያ እንደሆነ በርካታ ጸሐፍት ይመሰክራሉ›› (ገፅ 287) ሲሉ በአባሪ ማስረጃዎች አስደግፈው አቅርበዋል፡፡ ሥርወ-መንግስቱ በሥልጣን ላይ የቆየበት ጊዜያትንም ‹‹ከጎንደር ዘመነ-መንግስት ማብቂያ እስከ አፄ ቴዎድሮስ መነሳት ድረስ የነበሩትን ዓመታት ሁሉ ያካትታል›› (ገፅ 293) በማለት ገልፀውታል፤ ይህንን በአሃዝ እናስቀምጠው ብንል ደግሞ ወደ 86 ዓመት ገደማ ልንቆጥር እንገደዳለን፡፡
በተመሳሳይ መልኩ ‹‹የኦሮሞ ታሪክ›› የተሰኘው መጽሐፍ ጸሐፊ እሸቱ ኢረና ዲባባም መከራከሪያውን እንዲህ ሲሉ ያጠናክሩታል፡- ‹‹ጎንደር የሃበሻ መንግስት (አቢሲኒያ) ማዕከል በነበረችበት ወቅት የኦሮሞ ህዝብ በአካባቢው ሰፍሮ ይኖር እንደነበረና ወሳኝ ሚና ለረጅም ጊዜ ነበረው፤ እ.ኤ.አ. ከ1853-1854 በጎንደር በእስር ላይ የነበረው ጀርመናዊ ሰዓሊ በሰራቸው ምስሎች ኦሮሞ በወቅቱ በአካባቢው ገዢ እንደነበር እርሱም ከአካባቢው ኦሮሞ ሴት እንዳገባ፤ ምስልዋንም ሰርቶ እነዚህ የስዕል ስራዎቹ እ.ኤ.አ. በ1868 ዓ.ም በለንደን ከተማ በመጽሐፍ መልክ ታትሞ ወጥቶ ይገኛል፡፡ በአካባቢው ሰፍረው ይኖሩ ከነበሩት የኦሮሞ ጎሳዎች ውስጥ የቦረና ኦሮሞ አንዱ መሆኑን ኤች ሙሬይ በ1830ዎቹ ባሳተመው ጽሑፍ ውስጥ ከጠቀሰ በኋላ ኦሮሞ እንደ ሕዝብ በደንቢያ በጎጃም፣ በዳሞትና በአንጎት አካባቢዎች ሰፍሮ እንደሚገኝ ተጠቅሷል፡፡›› (ገፅ 83-84)
ራሱ የክልሉ መንግስትም፣ በባሕልና ቱሪዝም ቢሮው በኩል ‹‹የኦሮሞ ታሪክ እስከ አስራ ስድስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን›› በሚል ርዕስ ባሳተመው መጽሐፍ ‹‹…‹ወራ-ሼክ› የሚለው የቤተሰቡ መጠሪያ በየጁ ኦሮሞዎች ዘንድ ታላቅ ዝና ከማግኘቱም በላይ በአጠቃላይ የየጁ ኦሮሞዎች ቀደምት መንግስት መነሻ ወይም አባት ተደርጎ እስከመቆጠር ደረሰ ይባላል›› (ገፅ 281) ሲል ገልጿል፡፡
በግልባጩ የአፄ ምኒሊክ ፈረስ ሐረርና አርሲ መርገጡን ‹‹የቅኝ-ግዛት ወረራ›› አድርገው የሚያቀርቡ ዘመነኛ ‹‹ፖለቲከኞች››፣ ይህ አይነቱን ጥሬ ሀቅ ለመቀበል ቀርቶ ለመስማት አይፈቅዱም፡፡ የጠቀስኳቸው ድርሳናትም የሚነግሩን ኦሮሞ ከሌላው ብሔር ጋር ትንቅንቅ ገጥሞ በለስ ቀንቶት ድል ባደረገ ቁጥር መንግስታዊ ሥልጣን መጠቅለሉን ብቻ አይደለም፤ በሀገሪቱ ታሪክ ጭቆና እንጂ ቅኝ አገዛዝ የሚባል ነገር አለመኖሩንም ጭምር ነው፡፡ ከኤርትራ እስከ ሞያሌ፤ ከጋምቤላ እስከ ሶማሌ በተዘረጋው ሰፊ የኢትዮጵያ ግዛት ላይ በተደጋጋሚ ከተቃጡ የባዕዳን ወረራዎች በቀር፣ ቅኝ-ገዢም ሆነ ቅኝ-ተገዢዎች ስለመኖራቸው የሚያትት አንድም የታሪክ መረጃ ተፈልጎ ታጥቷል፡፡ መቼም ‹‹ድሮ ነፃ ሀገር ነበረን›› በሚል ዛሬ ላይ የመገንጠልን ጥያቄ ሲያነሱ፤ አሊያም አንድ ብሔርን በነፍጠኛነትና በወራሪነት ሲኮንኑ የምናደምጣቸው ጠርዘኛ ልሂቃን ‹የኦሮሚያ የግዛት ወሰን ጎንደርን እና ትግራይን ያጠቃልል ነበር› ስለማለታቸው ሰምተን አናውቅም፡፡ መቀመጫውን ደብረታቦር ላይ አድርጎ ከትግራይ እስከ ሸዋ ያስተዳድር የነበረ ሥርወ-መንግስት፣ የበለጠ ጉልበተኛ ተነስቶበት፣ በተራው ከመንበሩ በኃይል ሲገለበጥ ቅኝ-አገዛዝና ኢ-ሰብአዊ ብሎ ለመኮነን መሞከሩ ውሃ የሚያነሳ ሙግት ሊሆን አይችልም፡፡ እዚህ ጋ ሊዘነጋ የማይገባው ጉዳይ፣ በተለይም ከአፄ ምኒሊክ መንገሥ ወዲህ የኦሮሞ ማሕበረሰብ ቋንቋውን ጨምሮ የባሕል እሴቶቹ ተውጠው፣ የአገሪቱ ወካይ እንዳይሆኑ መጨፍለቃቸውን ነው፤ እንደምሳሌም የገዳ ሥርዓት ምንም እንኳ ሁሉንም የቋንቋው ተናጋሪ ያቀፈ ባይሆንም (የ‹‹ጊቤ ግዛት›› ተብለው የሚታወቁት፡- ጅማ፣ ሊሙ፣ ጎማ፣ ጉማ እና ጌራ ከገዳ ይልቅ በንጉሣዊ ሥርዓት ሲተዳደሩ፤ ወለጋና ኢሊባቡርን የመሳሰሉ አካባቢዎችም በ‹‹ሞቲ›› ይመሩ ስለነበር) የአክሱም ሐውልትን ወይም የጎንደር ግንብን ያህል በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ቦታ አለማግኘቱ አይካድም፡፡ እንዲሁም በሌላ ቋንቋ ተናጋሪው ዘንድ ‹‹ጣኦት ማምለክ›› ተደርጎ የሚቆጠረው የኢሬቻ ክብረ-በዓል አረዳድ ስሁት ስለመሆኑ ቢረፍድም የመስከሩ ጠቀሜታ የጎላ ነው፡፡ ይህ የምስጋና ሥነ-ስርዓት በአገሪቱ ታሪክ ተገቢውን የክብር ስፍራ ሳያገኝ መገፋቱን በማመን፣ ሚዛንን ማስተካከል ግድ ይላል፡፡ በጥቅሉ ምግቡ፣ አለባበሱ፣ ሙዚቃውና መሰል እሴቶቹ በትልቁ የታሪካችን ገፅ በበቂ ደረጃ አለመወከላቸውን ዛሬም ለማድበስበስ መሞከሩ መፍትሔውን ከማራቅ፤ አሊያም ልዩነትን ከማስፋት ያለፈ ፋይዳ አይኖረውም፡፡ መቼም በዛሬይቱ ኢትዮጵያ፣ የመገንጠል ጥያቄ ያነሱ ቡድኖች መኖራቸው ደብቀን የምናስቀረው ሚስጥር አይደለም፤ ከኦሮሚያ እስኪ ኦጋዴን፤ ከጋምቤላ እስከ ቤንሻንጉል ድረስ ይህን ለማስፈፀም የሚተጉ የታጠቁ ኃይሎች ተፈጥረዋልና፡፡ በርግጥ እነዚህ ኃይሎች የቆሙበት መሰረት ማሕበረሰቡን የሚወክል ነው ወይስ የራሳቸውን የሥልጣን ጥማት ብቻ የሚያረካ? የሚለው ገና ያልጠራ፣ አሁንም አጥጋቢ መልስ ያላገኘ ጥያቄ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ፖለቲካዊው ፍላጎት ማሕበራዊ ውሉን የዋጠው ይመስላል፡፡ ኤርትራን ያጣንበት ምክንያትም ከዚህ ብዙም እንደማይርቅ ጥርጥር የለውም፡፡ አሁንም የዚህን ጥያቄ ውል ከሳትን ሌላ የምናጣው ክፍለ-አካል መኖሩ አይቀሬ ነው፡፡ ስለዚህም ነው በ‹‹ሕዳሴው አብዮት›› እንደ አዲስ በምትገነባው ኢትዮጵያችን ጥያቄዎቹ በቀዳሚነት ምላሽ ሊያገኙ ይገባል ብዬ የምከራከረው፡፡ በለውጡም፣ እነዚህ ጎታች የፖለቲካ አቋሞች እና አቀንቃኞቹ ዘላቂ መፍትሔ አግኝተው የአንድነት ዘመን አብሳሪ እንደሚሆኑ አልጠራጠርም፡፡
በተቀረ በኦሮሞ ላይ አንድ ብሔር በተለየ መልኩ በደል አድርሷል፣ ዘግናኝ ጭፍጨፋ ፈፅሟል… መሰል ትርክቶች ጭራና ቀንድ ተሰክቶባቸው ግብረ-ሂትለርና ፋሽስታዊ ድርጊቶች ተመስለው የሚቀርቡበት አውድ ከተራ ጊዜያዊ የፖለቲካ ፕሮፓጋንዳነት ያለፈ፣ በዕውን ለመፈፀማቸው ምንም አይነት የታሪክ ሰነድ አልተገኘም፡፡ ከጥቂት ሳምንት ቀደም ብሎ በዚህ ርዕሰ-ጉዳይ ዙሪያ ከታሪክ ምሁሩ ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ ጋር ስንወያይ ‹‹ወደ አኖሌ (አርሲ) ከዘመተው የአፄ ምኒሊክ ሠራዊት መካከል አብላጫው ኦሮሞ ነው›› ሲሉ መግለፃቸውም፣ ከዶ/ሩ የትምህርት ደረጃ፣ ከረዥም ዓመት የሥራ ልምዳቸው እና ከቋንቋው ተናጋሪ አብራክ የተገኙ ከመሆናቸው አኳያ ችግሩን ወደ አንድ ብሔር ማላከኩ ስህተት ለመሆኑ ሁሉንም የሚያስማማ ይመስለኛል፡፡ ታቦር ዋሚም ከላይ በጠቀስኩት መጽሐፍ (ከገፅ 275-278) ከአማራው ነገስታቶች ጋር ጋብቻ የፈፀሙ ኦሮሞ ንጉስና ንግስት በማለት በስዕላዊ መግለጫ አስደግፈው ያቀረቡት የቋንቋው ተናጋሪ ንጉሦችና ነገስታት ስም ዝርዝር እንደተጨማሪ ማስረጃ ሊወሰድ ይችላል፡፡ ጸሐፊው ለማሳያነት ከጠቀሷቸው ውስጥ የአፄ ቴዎድሮስ-እቴጌ ተዋበች፣ የአፄ ምኒሊክ-ጣይቱ ብጡል፣ የንግስት ዘውዲቱ-ወሌ ብጡል፣ የአፄ ኃይለስላሴ-እቴጌ መነን፣ የምኒልክን እህት ያገቡት-ንጉስ ሚካኤል… የኦሮሞ ብሔረሰብ አባላት እንደነበሩ አትተዋል፡፡ ከዚሁ ጋርም አያይዘው በተለያየ ጊዜ በሀገሪቷ የተከሰቱት የኃይል ግጭቶች አሰላለፍ በብሔር ከመቧደን ይልቅ፣ በሥልጣንና በጥቅመኝነት ላይ የተመሰረቱ እንደነበረ ፈራ-ተባ እያሉም ቢሆን እንዲህ ሲሉ ገልፀውታል፡-
‹‹በጣም የሚገርመው ከሣህለ ሥላሴ ጊዜ ጀምሮ እስከ አፄ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግስት ድረስ በኦሮሞው ላይ ሲካሄዱ ለነበሩት ዘመቻዎች ሁሉ ግንባር ቀደም ተዋናዮቹ በተለያዩ ምክንያቶች ከነገሥታቶቹ ጋር ጊዜያዊና ዘላቂ ዝምድና የፈጠሩ እራሳቸው ኦሮሞዎች መሆናቸው ነው፡፡ …(ራስ ጎበና) እኚህ የኦሮሞ መስፍን የታወቁ ፈረሰኛ፣ ጀግና፣ ተዋጊና ወታደራዊ ስትራቴጂስት ከመሆናቸው በላይ በኦሮሞ የውጊያ ስልትና በኦሮሞ ሥነ-ልቡና ላይ የጠለቀ እውቀት ነበራቸው፡፡ ይህንን ብቃት ሙሉ በሙሉ ለምኒሊክ አገልግሎት አውለውታል፡፡ ከሁሉም በፊት ምኒልክ ሳይሆኑ የኦሮሞን ግዛት ያሸነፉት ራስ ጎበና ነበሩ፡፡›› (ገፅ 499-500 እና 503)፡፡
ይህን መሰሉ የኃይል ትንቅንቅ ከአርሲና ባሌ በፊት ቤጌምድርና ትግራይ ውስጥ በተከሰተበት ወቅት ኦሮምኛ ተናጋሪው በአሸናፊነት በመውጣቱ ለ86 ዓመት ያህል ሥልጣን ይዞ መቆየቱን ከላይ አይተናል፡፡ መቼም የጁዎች፣ ጎንደሮችን ድል አድርገው ሥርወ-መንግስታቸውን ደብረ ታቦር ላይ የመሰረቱት በምርጫ ካርድ (ያለነፍጥ) ነበር ካልተባለ በቀር፣ አንዱን ወገን ለይቶ በሂትለርነት መኮነኑ ፍትሃዊ ካለመሆኑም ባለፈ፤ የሚጠቅመው ከመከራ ነፃ እንዲወጣ የምንዋትትለትን ሕዝብ ሳይሆን፣ የአገዛዙን ዕድሜ ለማራዘም ነው፡፡ በተጨማሪም በራሱ በቋንቋው ተናጋሪዎች ብቻ ከተዘጋጁ ድርሳናት የጠቀስኳቸው እነዚህ ሁነቶች፣ በማስረጃ ያልተደገፈውን (አፈ-ታሪኩን) የአኖሌ ጡት ቆረጣ ትርክት ተአማኒነት ያሳጡታል፡፡ ከዚህ ባለፈ የተሸነፈ ሠራዊትን እጅ-እግር መቁረጥ ምኒሊክም ሆኑ ከእርሳቸው በፊት የነበሩ ገዥዎች ይፈፅሙት የነበረ ጭካኔ መሆኑ አይስተባበልም፤ እንዲያውም በአንድ ወቅት አፄ ቴዎድሮስ፣ በሸዋ ላይ ሾመውት የነበረው የምኒሊክ አጎት አቤቶ ሠይፈ ‹‹ሸፍቶብኛል›› በሚል አንኮበር ድረስ መጥተው ወግተው ድል ካደረጉት በኋላ ሠራዊቱ በሙሉ አንድ እጅና አንድ እግሩ እንዲቆረጥ ማድረጋቸውን ተከትሎ፡-
“አፄ ቴዎድሮስ እጅግ ተዋረዱ
የሸዋን ሰው ሁሉ እጅ ነስተው ሄዱ”
ተብሎ መገጠሙ የጉዳዩን እውነታነት ለማሳየት በቂ ነው፡፡
(የእስልምና እምነት እና የኦሮምኛ ተናጋሪው ማሕበረሰብ ጥያቄዎች፣ በ‹‹ሕዳሴ አብዮት›› የሚኖራቸውን የመፍትሔ ሃሳብ በተመለከተ ሳምንት እመለስበታለሁ)
http://wp.me/p5L3EG-8o