Netsanet

Dienstag, 5. August 2014

“ስለእኔ አታልቅሱ!”(ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ )

August 5, 2014


“ዋይ ዋይ ከሚሉና ሙሾ ከሚያወጡ ሴቶችና ከሕዝቡ እጅግ ብዙዎች ተከተሉት፡፡ ኢየሱስ ግን ወደ እነርሱ ዘወር ብሎ እንዲህ አለ፡- እናንተ የኢየሩሳሌም ልጆች ለእኔስ አታልቅሱልኝ፤ ዳሩ ግን፡- መካኖችና ያልወለዱ ማኀፀኖች፣ ያላጠቡ ጡቶችም ብፁአን ናቸው የሚሉበት ጊዜ እነሆ ይመጣልና ለራሳችሁና ለልጆቻችሁ አልቅሱ፡፡” (የሉቃስ ወንጌል ም. 23 ቁ. 27-30) ከቅዱስ መጽሐፉ ይህን የመሲሁ የመጨረሻ ምክር የመረጥኩት (ምንም እንኳ ረቢው የተናገረው ስለመለኮታዊው ትምህርት ቢሆንም) ዓለማዊው ፍች የኢትዮጵያችንን የወቅቱን መንፈስ ለመረዳት ከማስቻሉም በዘለለ፤ በየጊዜው እያየን፣ እየሰማን ያለነውን የፖለቲካ ተቃውሞው የጥምዝምዞሽ መንገድ በአርምሞ ለመመርመር መልካም ምሳሌ ይሆናል በሚል እሳቤም ነው፡፡

የሠላማዊ ትግሉ መቀልበሻ ስልቶች

እፍኝ በማይሞሉ ፋኖዎች ከአርባ ዓመታት በፊት “ደደቢት” በተሰኘ የሰሜን በርሃ የተመሰረተው ህወሓት ከተራዘመ የትግል ጉዙ በኋላ፤ ታጋይ ሕላዊ ዮሴፍ “እልፍ ሆነናል” እንዲል፤ ራሱን አጠናክሮ “እልፍ” በመሆን ሥልጣን ይዞ፣ የሀገሪቷን አንጡራ-ሀብት አመራሩ መምነሽነሺያው ካደረገ፣ እነሆ ሃያ ሶስት ዓመታት እንደዘበት ነጎዱ፡፡ ርግጥ ነው ይህች የዳንኪራ እና ፌሽታ ዘመን እውን ትሆን ዘንድ፣ የቡድኑ ዋና ዋና መሪዎችም ሆኑ መላው ታጋይ (የበረከቱ ተቋዳሽ ባይሆንም) በቃላት ሊገለፅ የማይችል የመከራ ዓመታትን በቆራጥነት ማሳለፋቸው የሚስተባበል ታሪክ አይደለም፡፡ ሥልጣን እጃቸው ከገባ በኋላም የአገር ጥቅም መገበርን ጨምሮ እየገደሉ፣ እያሰሩና እያሰደዱ… በሕዝብ ላይ ወደር የለሽ ጭካኔን በመፈፀም ዘላቂነቱን እንዲህ ስለማስረገጣቸውም ተወርቶ የተዘጋ አጀንዳ ከሆነ ሰነባብቷል፡፡ ይሁንና ከዕለት ዕለት እየመረረና እየከፋ የመጣው ይህ ኩነት፣ ምድሪቷ የአንድ እውነት መዝጊያና የአዲስ ዓመት ምዕራፍ መክፈቻ ላይ መድረሷን ስለማመላከቱ ለመመስከር ጠቢብነትን አይጠይቅም፤ የዘመኑ መንፈስ እያሰማን ያለው “ፋኖ ተሰማራ”ም የሶስተኛው አብዮት ደውል ስለመሆኑ ለመረዳት የቀደሙ ነብያቶችን ትንበያ መጠበቅ አያሻም፡፡

ገዥዎቻችን፣ መግደልና ማሰርን ሱፍ ለብሶ፣ ከረባት አስሮ፤ ጠዋት ወደ ቢሮ ተገብቶ፣ ማታ የሚወጣበት መደበኛ ሥራ ከማድረጋቸውም ባለፈ፣ የሥልጣን ግዛታቸውን እንዲህ ነቅተው (ታጥበውና ታጥነው) ባይጠብቁት ኖሮ፣ ለሃያ ሶስት ዓመት ቀርቶ፣ ለሃያ ሶስት ሰዓት እንኳን በቤተ-መንግስቱ መቆየት እንደማይችሉ አብጠርጥረው ያውቁታል፡፡ የዚህ ጽሑፍ ፍሬ-ሃሳብም በዚህ መልኩ የሥልጣን ዕድሜውን ገና የማቱሳላን ያህል ማራዘም የሚፈልገው ኢህአዴግ፣ ተቃዋሚ ድርጅቶች የሚያቀነቅኑት የሠላማዊ ትግል አቅጣጫን የሚቀይስበትን እና የሚወስንበትን የሴራ ፖለቲካ፣ ለውጥ ፈላጊው ኢትዮጵያዊ ነቅቶ እንዲያከሽፈው መቀስቀስ ነው፡፡

ዛሬ በርካቶች በቁጭት እንደሚብሰለሰሉት ኢህአዴግ በመንበሩ ላይ ከሁለት አስርታት በላይ ተደላድሎ የመቆየቱ ምስጢር በውስጣዊ ጥንካሬው፣ አሊያም ሲቪል ጀግኖች በመጥፋታቸው ሳቢያ አይደለም (ወላድ በድባብ ትሂድና፤ ሀገሪቱ የሚሞትላት ጀግና ትውልድ ከመፍጠር መክና አታውቅም)፡፡ የግንባሩ ዋነኛ የጥንካሬ ምንጭ የተቃዋሚውንም ወገን የቤት ሥራ ጠቅልሎ እየሰራ በመሆኑ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ ወደኋላ ሄደን በአደረጃጀትም ሆነ በድጋፍ መሰረታቸው ‹‹የተሻሉ›› ሊባሉ የሚችሉ ተቀናቃኝ ፓርቲዎችን ሂደት ብንመረምር፣ መራራውን እውነታ እየጎመዘዘንም ቢሆን መጋታችን አያጠራጥርም፡፡ ለማሳያ ያህልም በአገዛዙ የማስቀየሻ እርምጃ ተጠልፈው ከከሸፉ ሕዝባዊ ንቅናቄዎች መካከል ጥቂቶቹን በአዲስ መስመር እንመልከት፡፡

ኦነግ

የኦሮሞ ነፃ አውጪ ግንባር፣ መለስ ዜናዊና ጓዶቹ ቆንጥረው ከሰጡት የሽግግር መንግስት ሥልጣኑ ተገፍቶ ከወጣ በኋላ ወደለመደው በርሃ በገባበት ወቅት፣ በአንፃራዊነት ቀድሞ መገንባት ከቻለው ጥንካሬ ባሻገር፣ በኦሮምኛ ተናጋሪው ማሕበረሰብ ዘንድ የሚሊዮኖችን ልብ ይበልጥ ማማለል ችሎ እንደነበረ የአደባባይ ሐቅ ነው፡፡ ወቅታዊውን የኃይል አሰላለፍ ጠንቅቆ የተረዳው “አባ መላ”ው ኢህአዴግም የጠብ-መንጃ ግብግቡ ከመጀመሩ አስቀድሞ፣ ከተማውን ለቆ ያልወጣውን የአመራር አባሉን ኢብሳ ጉተማን ወደ እስር ቤት ወረወረ፤ ይህንን ተከትሎም ኦነግ ከመቼውም ጊዜ በላይ በእልህና በቁጭት ተነሳስቶ አርሲና ሐረርን አስተባብሮ፣ ወለጋን በታንክ አቋርጦ፣ ባቱ ተራራን በመድፍ ጩኸት አንቀጥቅጦ፣ በባሌ ተሻግሮ ፊንፊኔ ላይ በድል ሊንጎማለል ነው ተብሎ ሲጠበቅ፤ በግልባጩ ዋና ፀሀፊው ሌንጮ ለታ እና የተወሰኑ መሪዎቹ በቦሌ በኩል በመመለስ “ወይ እኛንም አብራችሁ እሰሩን፤ አሊያም ጓደኛችንን መልሱልን?” በማለት ከመረጡት የኃይል ትግል ጋር የማይጣጣም ስልት ተግብረው አረፉት፤ በዚህም የልብ ልብ የተሰማው ኢህአዴግ፣ የድርጅቱን አባላትም ሆነ ኦሮምኛ ተናጋሪውን በጅምላ በ “ስመ-ኦነግ” እየወነጀለ ለአስከፊ እስር መዳረጉ፣ በክልሉ ላይ ከባድ ፍርሃት አነበረ፡፡ ይህ ፖለቲካዊ ስህተትም ለዛሬው ሽንፈቱ ዋነኛ ተጠቃሽ ሲሆን፤ የተቃውሞ ጎራ ትግሉንም ከሥርዓት ለውጥ ወደ እስረኛ ማስፈታት ያወረደ ቀዳሚ ኩነት ሆኖ በታሪክ ተከትቧል፡፡

መአሕድ

የፕ/ር አስራት ወልደየስ የመላው አማራ ሕዝብ ድርጅት (መአሕድ) ውድቀትም ከኦነግ ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡ መአሕድ በምስረታው ማግስት ያገኘው መጠነ-ሰፊ የሕዝብ ድጋፍ፣ ህወሓት/ኢህአዴግ በ17 ዓመታት ከሰበሰበው ሁሉ ይልቅ እንደነበረ አይዘነጋም፡፡ ይህ አይነቱ ፈጣን ግስጋሴም ሊያስከትለው የሚችለውን የቁጣ ናዳ አስቀድሞ የተረዳው ‹‹ብልጣ-ብልጡ›› ኢህአዴግ፣ ሊቀ-መንበሩን ጉምቱ የሕክምና ሊቅ ጨምሮ ጥቂት የአመራር አባላቱን እስር ቤት ወረወረ፡፡ ከዚያማ ድርጅቱ ‹‹እታገልለታለሁ›› የሚለውን የፖለቲካ ሥልጣን የመቆጣጠር ዓላማውን ‹‹መሪዎቻችን ይፈቱ!›› ወደሚል አኮስሶ ባለበት ሲረግጥና ሲዳክር ለ13 ዓመታት ከቆየ በኋላ፣ በስተመጨረሻ ህላዊነቱ አክትሞ ወደ ሕብረ-ብሔር (መኢአድ) ድርጅትነት መሸጋገሩ ታወጀ፡፡ ክስተቱም አብዮታዊው ግንባሩ የተቃውሞ ጎራውን እንቅስቃሴ ወደፈለገው አቅጣጫ መዘወሩን በሚገባ እንደተካነበት ያስረገጠ ሆኖ አልፏል፡፡

ቅንጅት

ዛሬ ዛሬ እንደ ንግስት ሳባ ዘመን የሩቅ ጊዜ ታሪክ ያህል ይሰማኝ የጀመረው ምርጫ 97ም ሌላኛው የነገረ-አውዱ አስረጂ ነው፡፡ በጥቂት ወራት ውስጥ ከጫፍ ጫፍ ሀገራዊ ንቅናቄ መፍጠር የቻለው ግዙፉ ቅንጅት በአብዛኞቹ የምርጫ ጣቢያዎች በይበልጥ ደግሞ በገጠር አካባቢዎች አሸናፊ መሆኑ በተለያዩ አጣሪ አካላት በመረጋገጡ፤ የኢህአዴግን‹‹መንግስት ለመመስረት የሚያስችለኝ ድምፅ አግኝቻለሁ›› ጨዋታን ከውስጥም ከውጭም አምኖ የተቀበለ አንድም እንኳ አልነበረም፡፡ በአዲስ አበባ አንዳንድ አካባቢዎች ይህንንዓይን ያወጣ ስርቆት በሠላማዊ መንገድ ለመቃወም በሞከሩ ዜጎች ላይ በተወሰደው ርህራሄ አልባ የኃይል እርምጃ በርካታ ንፁሀን ለህልፈት እና ለአካል ጉዳት ሲዳረጉ፣ በተወሰኑየክልል ከተሞች ደግሞ ከፍተኛ ሕዝባዊ ማጉረምረም ተፈጥሮ እንደነበረ ይታወሳል፡፡ ግና፣ ‹‹ብልሆቹ›› የኢህአዴግ ኤጲስ ቆጶሳት በተካኑት ስልት የቅንጅቱን መሪዎች ከያሉበትሰብስበው እስር ቤት ከተቱ፤ ትግሉም ከተነሳበት ‹‹የገጠሩ ወገኖቻችን ድምፅ ይመለስ!›› ወደ ‹‹መሪዎቻችን ይፈቱ!›› ቀኝ ኋላ ዞሮ፣ የሥርዓቱ ዕድሜ እንዲቀጥል ስለመፍቀዱ የእኔ ትውልድ የአይን ምስክር መሆኑ ርግጥ ነው፡፡

ሕዝበ-ሙስሊሙ

ለሶስት ዓመት ተመንፈቅ (ከ‹‹እፎይታ ጊዜ››ው በቀር) ካለማቋረጥ በተቀጣጠለው የሙስሊሙ ኃይማኖታዊ ነፃነትን የማስከበር ትግልም፣ የንቅናቄው አስተባባሪዎች ‹ቃሊቲ የታጎሩትን መሪዎች የማስፈታት ዓላማ በአራተኛነት የተያዘ ነው› ቢሉም (‹‹አህባሽን በግዴታ ማጥመቅ ይቁም››፣ ‹‹መጅሊሱ ወደ ሕዝቡ ይመለስ›› እና ‹‹ነፃ ሕዝባዊ ምርጫ ይካሄድ›› የሚሉት ሶስቱ መሪ ጥያቄዎች የተቃውሞ መነሾ እንደሆኑ ልብ ይሏል)፤ የሕዝበ-ሙስሊሙ በተለይም የቅርብ ጊዜዎቹ የመስጂዶቹ እምቢ-ባይነቶች፣ ሥርዓቱ ለማደነቃቀፍ (ዓላማውን ለማስቀየስ) ባዘጋጀው የ‹‹ይፈቱ›› ማዕቀፍ ስር የተገደበ የመምሰል አዝማሚያው ነው በዚህ አውድ እንድጠቅሰው ያስገደደኝ፡፡ በርግጥ የሁለት አስርታቱን የተቃውሞ ልምድ በቅጡ የመረመሩ የሚመስሉት የ‹‹ድምፃችን ይሰማ›› ወጣቶች፣ በዚህ የተለመደ የትግል ቅልበሳ ላለመጠለፍ የሚያደርጉት ብርቱ ሙከራ እንዳለ ብገነዘብም፣ ከቀደመው ‹‹ጥቁር ሽብር›› ወዲህ በቀጣይ በሚኖሩት የትግል ወቅቶች ዋነኛ የትግል ጥያቄያቸውን ነፃነታቸውን በማስከበር ማዕቀፍ ስር እንደሚያደራጁት አምናለሁ፡፡

ማልቀስስ ለማን?

በ1983ቱ የመንግስት ለውጥ ዓለም አቀፋዊው አውድ፣ ለሽፍቶቹ ስብስብ እርግማንም በረከትም ይዞ ነበር፡፡ እርግማኑ፣ በቀደመ-ፖለቲካዊ ዝማሜያቸው ዝግ ሶሻሊስት ሥርዓት መመስረት አለመቻላቸው ሲሆን፤ በረከቱ ደግሞ በረዥሙ የእርስ በእርስ ጦርነት ክፉኛ የተመታችውን አገር በተለይም ተቋሞቿን ለመገንባት ከሚያስፈልገው ጊዜ አኳያ የምዕራባውያኑን ‹‹ዕድል እንስጣቸው›› የድጋፍ ልብ ማግኘታቸው ነው፡፡ በእነ ሳሙኤል ሀንቲንግተን ‹‹መድበለ-ፓርቲ ሥርዓትን እርሱት፤ አውራ ፓርቲነት ያዋጣችኋል›› ምክረ- ሐሳብ አማካኝነት የወቅቱ ምዕራባውያን አለቆቻቸውን መንፈስ መረዳታቸውን ወደኋላ ስንገነዘብ፤ ቢያንስ እስከ 97 ድህረ-ምርጫ ውጥንቅጥ ድረስ በተጓዙበት የአምባ-ገነንነት መንገድ በጥብቅ አለመወገዛቸውን እንረዳለን፡፡ በአናቱም በህወሓትና መሰል ነፍጥ አንጋቢ የድህረ-ቀዝቃዛው ጦርነት ቡድኖች ላይ ተስፋ የነበራቸው ዓለም አቀፍ ተቋማት እና ምሁራንም ዘግይተውም ቢሆን ቡድኖቹ ወደ ቋሚ ሽፍትነት መቀየራቸውን ከመመልከት አልዳኑም፡፡ የዚህ አይነት ስብስብ ቋሚ መለዮ፣ በመሰረተ ልማት ግንባታዎች ላይ ሙሉ ሀገራዊ ሀብት ማፍሰስ ነው፤ መግፍኤውም ግልፅ ነው፤ የሕብረተሰቡ የአምራችነት ማሕበረ-ኢኮኖሚያዊ አቅም ሲጎለብት፣ እነርሱም የሚያግበሰብሱት ሀብት እየሰፋና እየበዛ እንዲሄድ የማስቻሉ ሀቅ ነው፤ እንደ ህወሓት ያሉ የነፃ-አውጪነት የኋላ ታሪክ ያላቸው ገዢ ቡድኖች፣ በምርጫ ፖለቲካ የማይነቀነቁባቸው ምክንያቶችም ከዚሁ ጋር ይተሳሰራል፤ ከሰላማዊ ሕዝባዊ ዓመፅ ውጪ ይህን ነውረኛ ቡድን ማስቆም እንደማይቻል በ‹‹ሕዳሴ አብዮት›› ርዕሰ-ጉዳይ ለመከራከር የሞከርኩትም ለዚሁ ነው፡፡ እንግዲህ ከእስክንድር ነጋ እስከ ርዕዮት አለሙ፤ ከውብሸት ታዬ እስከ የሱፍ ጌታቸው፤ ከአንዱአለም አራጌ እስከ በቀለ ገርባ፤ ከጦማሪያኑ እስከ እነ ሐብታሙ አያሌው… ድረስ ዘርዝረን የማንጨርሳቸው የእልፍ አእላፍ ለውጥ ፈላጊ ኢትዮጵያውያን መታሰር አሳዛኝ ቢሆንም፤ ለእነርሱም ሆነ ለሀገር የሚበጀው ‹‹ታጋይ እንጂ ትግል አይሞትም!›› የሚለውን የጊዜውን አስገዳጅ ሕዝባዊ ጥሪ በመቀበል አደባባዩን በቁጣ ማጥለቅለቅ ብቻ ነው፡፡ ከዚህ ውጪ ዛሬ እያየነው እንዳለው የግፉአኑን መፈክር አንግቦ መነሳትን ገሸሽ አድርጎ፣ የ‹‹ይፈቱ›› ጥያቄ የትግሉን መንፈስ ይመራው ዘንድ መፍቀድ ሂደቱን ለሥርዓቱ ሴራ አሳልፎ እንደመስጠት የሚቆጠር ይመስለኛል፡፡

መግቢያዬ ላይ የጠቀስኩት የመምህሩ ቃል የሚነግረንም ለእነሱ ከማልቀስ ይልቅ፣ የአምባ-ገነኑን ሥርዓት ቀንበር ተሸክመን በአሳረ-ፍዳ ኑሮአችንን ስለምንገፋው ስለራሳችን ብናለቅስ የተሻለ መሆኑን ነው፡፡ ከዚህ ጎን ለጎንም አብዝተን ነፃነታቸውን የምንሻላቸው ጀግኖቻችን እንደምኞታችን ቢፈቱና መፃኢ ዕድላቸው ምን ሊሆን እንደሚችል ራሳችንን ብንጠይቅ፣ የምንፋጠጠው ‹ተመልሰው በኢህአዴግ የብረት ጫማ ስር ለጥ-ሰጥ ብሎ ማደር› ከሚል እውነታ ጋር ብቻ ነው፡፡የተለመደውን ‹‹የይቅርታ ቃጭል›› አጥልቀው፣ በተሰበረ መንፈስ ከትግሉ ርቀው አንደበታቸውን ሸብበው አሊያም ከሀገር ወጥተው ቀሪውን ህይወታቸውን በስደት እንዲያሳልፉ ከማድረግ ያለፈ የምንፈጥርላቸው ወይም የምናመቻችላቸው ምንም ነገር አለመኖሩ ርግጥ ነውና፡፡ ያውም ብርቱካን ሜደቅሳን ለቅቆ፤ ርእዮት ዓለሙን የሚያስርበትን የቆየ የፖለቲካ ጨዋታውን ሳንዘነጋ፡፡ ይህም ነው ሕዝብን የማዳመጥ አንዳችም ልምድ ለሌለው ሥርዓት ‹‹ይፈቱ!››፣ ‹‹ይለቀቁ!›› እያልን ከመጮኽ በመቆጠብ፣ ታሳሪዎቹ ስለተዋደቁባቸው የነፃነት እሴቶች መተግበር መታገልን ግድ ያደርገው፡፡

በጥቅሉ በመከራው ዳገት ላይ ያሉት ወገኖቻችን የገጠማቸውን ሁነት ያስነሳው፣ ማናችንም በነፃነትና በእኩልነት ልንኖርባት የምትገባዋን አገር የመናፈቅ እንደሆነ ከተስማማን ዘንዳ፣ በየእስር እርምጃው የተፈጠሩትን ክፍተቶች እየደፈንን፣ የነፃነቱን ቀን ለማቅረብ መታተር የወቅቱ አስገዳጅ ጉዳይ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ በቀድሞው የቅንጅት አመራሮች የገፍ እስር ማግስት፣ የከተሞቹን ንቅናቄዎች ከ‹‹ይፈቱልን›› ይልቅ፣ ‹‹ድምፃችን ይመለስልን!›› በሚለው መሠረታዊ ጥያቄ አጥብቀን ይዘን ትግላችንን ብናራዝመው ኖሮ፣ ፖለቲካዊ ለውጦችን መጨበጥ እንችል እንደነበር ማናችንም ብንሆን የምንጠራጠር አይመስለኝም፡፡ ከዚህ አኳያም የሚያስማማን ዋነኛ ጭብጥ፣ ቢያንስ የ2002ቱ ምርጫ በተካሄደበት አስቂኝ ድራማ ልክ ተከናውኖ እና ተቀልዶብን የማለፉ ዕድል እጅጉን ያነሰ የመሆኑ ጉዳይ ነበር፡፡

ባለፉት ጥቂት ወራት ውስጥ ያየናቸው የጦማሪያኑና የሶስቱ ፓርቲዎች ወጣት አመራሮች እስር፣ በተለመደው የ‹‹ይፈቱ›› ደካማ የትግል ስልት የመሄድ ዳርዳርታውን ገርተን፣ ከአደባባዩ መራቃቸውን ተከትሎ እየተፈጠረ ያለ የሚመስለውን (ከማሕበራዊ ድረ-ገፆች እስከ የዕለት ተዕለት የፓርቲዎቹ እንቅስቃሴ ድረስ) ክፍተት መሻገሩ፣ የተሻለ ብቻም ሳይሆን ገዢዎቻችን እንድንሰምጥበት ከሚሹት የሽንፈት ማጥ ውስጥ ከመነከርም የሚገታ አማራጭ ነው፡፡

እነሆም ለማንስ ማልቀስ ይገባል? የሚለውን ጥያቄ መመለስ የሚያስፈልገን እንግዲህ በዚህ ከባድ ወቅት ላይ ነው፡፡ …እንደየተነሱበት አውድ ለሚያምኑባቸው ክቡድ ዕሴቶች ዘብጥያ ለተጣሉት ዜጎች መብሰልሰልን በመምረጥ ከጎናቸው መሰለፍን ላንገራገርነው ለኛ ማዘን የበለጠ የተገባ ነውና፣ እነርሱ ድርሻቸውን ስለመወጣታቸው እያመሰገንን፣ ፍትሃዊ አቋሞቻቸውን በገዘፈ ጉልበት ወደፊት መውሰድ ብቸኛው ምርጫችን መሆን ይኖርበታል፡፡ የ‹‹ሕዳሴው አብዮት›› ተግባሮትም አስፈላጊው ሥነ-ልቦና ይኸው ነው ብዬ አምናለሁ፡፡

ድል ለግፉአን ኢትዮጵያውያን

Montag, 4. August 2014

“እኛ አባቶች ከእንግዲህ ሀላፊነት ለወጣቶች በመስጠት በምክርና የተለያየ ተሞክሯችን በመስጠት ከጎናቸው መቆም አለብን፣

Augest 4/2014
hqdefault
በቅርቡ ኢንጂነር ግዛቸው ሽፈራው የአንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ ሊቀመንበር ለመሆን በዕጩነት ቀዳሚ ሆነው ማለፋቸው የፓርቲው ልሳን የሆነው ፍኖተ ነጻነት አስታውቋል፡ ፡በዚህ ጉዳያ ያልተናደደና ያልተበሳጨ ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያዊ ይኖራል ብሎ መገመት ይከብዳል፡፡ በተለይ ያእቆብ ሀ/ማሪያም በግንቦት 25/2005 በሰማያዊ ፓርቲ ሰልፍ ላይ በኩባ አደባባይ ለሰልፈኛው አቅርበውት በነበረው ንግግቸው ላይ “እኛ አባቶች ከእንግዲህ ሀላፊነት ለወጣቶች በመስጠት በምክርና የተለያየ ተሞክሯችን በመስጠት ከጎናቸው መቆም አለብን፣ከእንግዲህ የእኛ ሀላፊነት ወንበሩን ለወጣቱ ለአዲሱ ተውልድ መልቀቅ ነው፣ “ብለው ነበር፡፡ ኢንጂነር ግዛቸው ግን እንዲህ ቅዱስ ነገር ለመስማት ፍላጎትም ያላቸው አይመስልም፡፡ ኢህአዴግም የእሳቸው ወደ ፊት መምጣት እንደ ሰማይ መና የሚቆጥረው ነገር ነው፡፡ ለምን? ፣ሰውዬው ታሰረው ከነበሩትና በኋላም በይቅርታ ከተለቀቁት የቅንጅት አመራሮች አንዱ ነበሩ፡፡እና ምን አለበት ሊባል ይችላል፡፡በጣም ከባድ ችግር ነው ያለበት፡፡ዋናው ነገር ምን አይነት ይቅርታ ጠይቀው ነው የወጡት የሚለው ነው፣ እንዲህ የሚል ነው
….ህገ መንግስቱንና ህገመንግስታዊ ስርአቱን በሀይልና በአመጽ ለመናድ በህገወጥ መንገድ ተንቀሳሰናል በዚህም ምክንት ብዙ ጥፋትና ውድመት ተከስቷል፤እንዲህ አይነት ነገሩ ውስጥ በማድረግ ህዝባችንና መንገስታችንን በመበደላችን አጥፍተኛል ተጸጽተናል፣ከእንግዲህም አይለመደንም ይቅርታ ይደረግልን… የሚል አይነት ነበር፡፡
ኢህአዴግ በእንዲህ አይነት ሁኔታ ይቅርታ እንዲጠይቁ ያደረገው በትክክል የተባለው ነገር ስለፈጸሙ ሳይሆን፣፣ከእስር ትፈታላችሁ ነገር ግን ካሁን በኋላ እኔ ከምላችሁ አንዳች ፍንክች ብትሉ ተመልሳችሁ ትገቧታላችሁ ማለቱ እንደሆነ ትርጉሙ ግልጽነው፡፡ለዚህም የብርቱካን ሚደቅሳ ነገር ማየት ረዘም ተደርጋ እንዳተሰረች ዶሮ እንጂ እኝደወፍ እንድትበር አልተፈቀደላትም፡፡ስዊድን ሀገር ሄዳ ኢህአዴግ የማይፈቅደው ነገር ተናግራ ወደ ሀገር ቤት ስትመጣ ብዝብ ፊት ይቅርታ ጠይቂ አለበለዛ በተስማማስ መሰረት ወደነበርሽበት ትመለሻለሥ ጠባለች፡፡እምቢ አለች፡፡ተመለሰች፡፡በወቅቱ አብዛኛው የአንድነት አመራሮች በፊርማ የወጡ ስለነበሩ ለምን ብለው ሊከራከሩላት አልቻሉም፣እንዳውም የሚሉሽን አትሰሚምና የእጅሽን ነው ያገኘሽው በሚል አይነት ሁኔታ በብዙ መንገድ ሊኮንኗትና ሊያሳጧት ሞክረዋል፡፡
በወቅቱ ደግሞ ድርጅቱን በሀላፊነት ይመሩ የነበሩት ዛሬ ቲፎዞ አሰልፈው የመጡት ኢንጂነር ግዛቸው ሽፈራው ነበሩ፡፡እኚህ ሰው በወቅቱ ብርቱካን የታሰረችው እስርቤት የገባችውን የፊርማውን ቃል ስላቃለለች ነው የሚል በሚመስል የብርቱካንን ስም የሚያነሳ ሁል በድንጋይ ሳይቀር እስከማስደብበብ ደርሰዋል ውሸታም የሚለኝ ያ አይመስለኝም፡፡ከድርጅቱ አግደዋል አባረዋል፡፡ለዚህም የዛሬዎቹ የሰማያዊ ፓርቲ መሪዎችና አባላትን መጥቀስ ይቻላል፡፡ሰውዬው ድርጅቱን ይመሩት እስርቤት የፈረሙትንነገር በህልማቸውና በቅዠታቸው እየመጣባቸው ነበር፡፡ ለኢህአዴግ የገቡትን ቃል ለማክበር ብዙ የደርጅቱን ወጣቶችና ስም አባክነዋል፡፡ዘሬም ያ ፍርሀታቸው ደብቀው በፍርሀት ሊመሩት ከነቲፎዟቸው ብቅ ብለዋል፡፡በነገራችን ላይ ይህ ሰው በ97 ምርጫ ወቅት ፓርላማ እንግባ አንግባ በሚባልበት ወቅት እንግባ (ኢህአዴግ የሰጠንን ተቀብለን እንግባ) ብለው ይከራከሩ የነበሩ ከዚህም የሀገር ፍቅር ይኖራቸው ይሆናል እንጂ ወደፊት ገፍቶ ኢህአዴግን ለመታገል የሚጎላቸው ነገር እንዳለ ማወቅ ይቻላል፡፡ለጫማው በኋላ ይታሰብበታል ላሁኑ ማምለጥ ነው የሚሉ አይነት ሰው ናቸው፡፡
እና ምን ለማለት ነው ? ሰውዬ የአንድነት መሪ ቢሆኑ ድርጅቱን የሚመሩት ያኔ በፈረሙት ፊርማ ታስረውና ተሸብሽበው ነው፡፡አንዷል አተራጌ አፌን ሞልቼ ስለነጻነት አወራለሁ ሲል አትችል እንዲህ ማድረግ እንደማትችል እስርቤት ፈርመሀል ተብሎ ይኀው የትእንዳለ እናውቃለን፡፡ዶ/ር ብርሀኑ ነጋ የፈረው ፊርማ በሀገር ቤት የትም እንደማያደርሰው አውቆ ይኸውየት እንዳለ እናውቃለን፣እዛም አልቀረለትም የሞት ፍርድ ተፈርዶበታል፡፡ዶ/ር ያእቆብ ቃሊቲ እያለሁ የፈረምኩት ፊርማ እያሰብኩኝ የኢትዮጵያን ህዝብ ትግል ከምጎዳ አርፌ ብቀመጥ ይሻላል ብለው ይመስላል ይኸው መሪ አይደለም የየትኛውም የፖለቲካ ፓርቲ አባልም አይደሉም፡፡ብርቱካንም በውሸት ታስራችሁ በተጭበረበረ መንገድ የፈረማችሁት ፊርማ እፈራችሁ የምትኖሩ ከሆነና ሌላውም ሲታሰር ፍርዳችሁና ና ምላሻችሁ ይሄ ከሆነ ብላ ሀገሩም ትግሉም ጥላ ተደብቃ እየኖረች ነው፡፡
ኢንጂነር ሀይሉሻውል መለስን ጎንበስ ብለው እጅ ነስቻለሁ ያሉት ወደው አይደለም፣ የፈረሙት ፊርማ ምን ያህል ቀልባቸውና ቅስማቸውን እንደሰበራቸው መገመት ይቻላል፡፡ያኔ ታስረው የነበሩ ጋዜጠኞች ሀገር ጥለው ያሉት ቃሊትን ብቻ ሳይሆን የፈረሙትንም ፊርማ ስለሚፈሩ ጭምር ነው፡፡ኢህአዴግ ሰማያዊ ፓርቲ በአደረጃጀትም ሆነ በዐጣቃላይ ጥንካሬ ከአንድነት ስለሚበልጠው አይደለም እንዲህ ልቡ የተሸበረው፣የቀሊቲን ፊርማ እያሰቡ የሚመሩ ሰዎች ስላልሆኑ ጭምር ነው፡፡
ስለዚህ ኢንጂነር ግዛቸው ሽፈራው የአንድት መሪ ሆኑ ማለት ድርግቱ ክንፍ ብቻ ያለው የማይበር የታሰረ ዶሮ ከመሆን ውጪ ምንም አያመጡም፡፡ ስለዚህ በገዛ ፈቃዳቸው በቃኝ ብለው ከጎን ሆነው የትግል ልዳምቸውና ምክርብቻ ማካፈል አለባቸው፡፡ ደግሞም ባለፈው 22 ውስጥ ፖለቲካ ውስጥ ብዙ ጊዜጣቸውን ያሳለፉት እንደ በየነ ጴጥሮስና ዶ/ር መራራ ጉዲና በድርጅት አመራርነት በተለያየ ቦታ ተለጥፈው ተጣብቀው ነው ነው፡፡ለኢህአዴግ የጣሉት እንጂ ያስጣሉት ነገር የለም፡፡ሸክም መሆን ብቻ፡፡መአድ ውስጥ አመራር ውስጥ ነበሩ፣መኢአድ ውስጥ እንዲሁ፣ቅንጅት ውስጥ የታሰሩት አመራር ላይ ስለነበሩ ነው፣አንድነት እሰካሁን የሚያሳማውን ስም ያሰጡትም አመራር ላይ ስለነበሩ ነው፡፡አይተናቸዋል ፣በቃ አሁን ቦታውን ለሌላ ይልቀቁ!!በተለይ የእሳቸው ወደ ስልጣን መምጣት ድርጅቱን እንደእነ ቡልቻ ባሉ “የበራላቸው” ሰዎች በብሄር (በተለይ መዐአድ ውስጥ የነበሩ ሰው ከመሆናቸው አንጻር)በጣም የሚያሳማና ኢህዴግም የያኔው አንዳንድ የቅንጅት ስህተቶችን እያነሳ ህዝብ የሚያስትበት አጀንዳና የትግል መግደያ ከመሆን አያልፉም!

አንድ መቶ ሰባ አምስት ኪሎ ወርቅ ከሃገር ሊወጣ ሲል ቢያዝም በሳሞራ የኑስ ትእዛዝ እንዲያልፍ ተደርጓል።

Augest 4/2014

ምንሊክ ሳልሳዊ

  • 661
    Share
የጄኔራል ሳሞራ የኑስ እንደሆነ የሚጠረጠረው አንድ መቶ ሰባ አምስት ኪሎ ወርቅ ከአገር ሊወጣ ሲል ተይዞ የነበረ ቢሆንም በጄኔራሉ ትእዛዝ ከአገር እንዲወጣ መደረጉን የአየር መንገዱ የደህንነት ምንጮች ጠቁመዋል። ይህ በሁለት ካርቶን ታሽጎ በበረራ ቁጥር 600 እና 612 ወደ ዱባይ ሊሻገር ሲል በቁጥጥር ስር የዋለው ወርቅ በጊዜው ባለንብረቱ ተፈልገው ባለመገኘታቸው እንዲቆይ ቢደረግም ጄኔራል ሳሞራ የኑስ ቦታው ድረስ አሽከሮቹን በመላክ እንዲለቀቅ እና እንዲያልፍ/እንዲጫን የተደረገ መሆኑ ታውቋል።

ይህ የሃገር ሃብት የሆነን ወርቅ የወያኔ ባለስልጣናት ካለምንም ገደብ በማሸሽ እና በመዝረፍ ላይ የተሰማሩ ሲሆን ፒያሳ አከባቢ በሚገኘው በአፍሪካ ወርቅ ቤት ሽፋን እንዳልካቸው እና ዳንኤል በሚባሉ ስሞች በሚሊዮን ዶላሮች የሚገመት የወርቅ መጠን ከአገር በማስወጣት እና እንዲሁም የውጪ ወርቆችን ካለምንም የቀረጥ ክፍያ ወደ ሃገር ውስጥ በማስገባት ስራ ላይ መሰማራታቸው በተጨማሪም ሃገሪቷ የምታገኛቸው የውጪ ምንዛሬዎች በጥሬው እየታሸጉ ከሃገር እንደሚወጡ ታውቋል።

Sonntag, 3. August 2014

የጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ የፍ/ቤት ቀጠሮው ለመጪው ዓመት ተቀጠረ

August 3, 2014


በቀድሞው የ“ፍትህ” ጋዜጣ ላይ ዋና አዘጋጅ ሆኖ ሲሰራ ሶስት ክሶች የቀረቡበት ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ፤ በተደጋጋሚ ቀጠሮው ሲተላለፍበት ቆይቶ፣ ከትላንት በስቲያ ለመጪው ዓመት ተቀጠረ፡፡ የፌደራሉ ከፍተኛ ፍ/ቤት 16ኛ ወንጀል ችሎት፣ ሐምሌ 11 ቀን 2006 ዓ.ም ጋዜጠኛው የቀረቡበት ሶስት ክሶች ላይ ማስረጃዎችን መርምሮ ውሳኔ ይሰጣል ተብሎ ሲጠበቅ፣ዳኛው አዲስ ናቸው በሚል ተለዋጭ ቀጠሮ ለሐምሌ 24 መሰጠቱ ይታወሳል፡፡ ከትናንት በስቲያ ሃሙስ ከሰአት በኋላም በድጋሚ ዳኛው በመቀየራቸው መዝገቡን መርምሮ ውሳኔ ለመስጠት ለጥቅምት 3 ቀን 2007 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጥቷል፡፡ በጋዜጠኛው ላይ የቀረቡት ሶስት ክሶች በቀድሞው “ፍትህ” ጋዜጣ ላይ “መጅሊሱ፣ ሲኖዶሱና የአብዮታዊ ዲሞክራሲያዊ ማጥመቂያዎች”፣ “የፈራ ይመለስ” እና “የብሄረሰቦች መብት እስከ መጨፈር” በሚሉ ርእሶች በተለያዩ ጊዜያት በወጡት ፅሁፎች፤ መንግስትን በአመፅ ለመናድ ቀስቅሷል፣ የመንግስትን ስም አጥፍቷል፣ የህዝብን አስተሳሰብ ለማናወጥ ሰርቷል፤ የሚሉ መሆናቸው ይታወቃል፡፡ የፍ/ቤት የክርክር ሂደቱ ሁለት አመታትን መፍጀቱ ታውቋል፡፡

Samstag, 2. August 2014

በእስር ቆይታቸው 100 ቀናት ለደፈኑት ጦማርያን የተማጽኖ ደብዳቤ ለጠቅላይ ሚኒስተሩ ተላከ፡፡

Augest2/2014

‹‹ዞን ዘጠኝ››  የጦማሪያን ቡድን አባላት ዘለዓለም ክብረት፣ ናትናኤል ፈለቀ፣ ማህሌት ፋንታሁን፣ በፍቃዱ ኃይሉ፣ አቤል ዋበላና ሶልያና ሺመልስ ሲሆኑ፣ ተስፋለም ወልደየሱስ፣ አስማማው ኃይለ ጊዮርጊስና ኤዶም ካሳዬ ደግሞ ጋዜጠኞች ናቸው፡፡ ሶልያና የተከሰሰችው በሌለችበት ነው፡፡
በቅርቡም ቀደም ሲል መንግሥት በአሸባሪነት የፈረጀው የግንቦት ሰባት ዋና ጸሐፊ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ከየመን ዋና ከተማ ሰነዓ በቁጥጥር ሥር ውለው ይገኛሉ፡፡ እንዲሁም ደግሞ በተመሳሳይ ጊዜ በሽብርተኝነት ተጠርጥረው አራት የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች አመራሮችን (አብርሃ ደስታ፣ ሀብታሙ አያሌው፣ ዳንኤል ሺበሺና ስለሺ አሰፋ) መንግሥት በቁጥጥር አውሏል፡፡
ethopia-bloggersመንግሥት የፀረ ሽብርተኝነት አዋጅ ካፀደቀ ጊዜ ጀምሮ በርካቶች በዚህ ሕግ እየጠየቀ ይገኛል፡፡ ይህንን ሕግ፣ የሲቪል ማኅበራት አዋጅ፣ እንዲሁም የፕሬሱ አዋጅ ከዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ ትችት ሲቀርብበት የቆየ መሆኑም አይዘነጋም፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ሰሞኑን በርካታ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ለጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ የተማፅኖ ደብዳቤ ልከዋል፡፡ ከደብዳቤው ፈራሚዎች መካከል ሂዩማን ራይትስ ዎችና አምነስቲ ኢንተርናሽናል በግንባር ቀደምትነት የሚገኙበት ሲሆን፣ እነዚህ ድርጅቶች ኢትዮጵያ ውስጥ ባለው የሰብዓዊ መብት አያያዝና የፕሬስ ነፃነት ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ተስማምተው አያውቁም፡፡
እነዚህ ድርጅቶች በየጊዜው በሚያወጡዋቸው ሪፖርቶች ከመንግሥት ጋር ሲጋጩ የቆዩ ሲሆን፣ በተለይ የኢትዮጵያ የፀጥታ ኃይሎች በሶማሊያና በኦጋዴን ተፈጸመ ባሉት የሰብዓዊ መብት ጥሰት ምክንያት ግንኙነታቸው እጅግ እንዲሻክር ምክንያት ሆኖ ነበር፡፡
አምነስቲ ኢንተርናሽናልና ሂዩማን ራይትስ ዎች አንዳንዴም የአሜሪካ ስቴት ዲፓርትመንት በዓመታዊ ሪፖርታቸው በኢትዮጵያ መንግሥት የሰብዓዊ መብት አያያዝ ላይ ከፍተኛ ትችት የሚሰነዝሩ ሲሆን፣ መንግሥትም አንዳንዴ ዘጋቢ ፊልሞችን በመሥራት የአፀፋ ምላሽ ሲሰጥ ይስተዋላል፡፡
ሰሞኑን ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የተላከው ደብዳቤም አርቲክል 19 እና እነዚህ ሁለት ድርጅቶች በግንባር ቀደምትነት ያሉበት ሲሆን፣ በአጠቃላይ ደብዳቤው ላይ ፊርማቸውን ያሳረፉ ግን ቁጥራቸው አርባ አንድ ነው፡፡
መንግሥት የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችንም ሆነ ጋዜጠኞችን ወይም  የፖለቲካ ተሟጋቾች በእስር ሲያውል እንዲህ ዓይነት ደብዳቤ መጻፍና የታቃውሞ መግለጫ ማውጣት የተለመደ ቢሆንም፣ በዚህ ደረጃ በዓለም ዙሪያ ያሉት የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች (ብዙዎቹም አፍሪካ ውስጥ የሚገኙ ናቸው) በአንድ ላይ መንግሥትን ሲቃወሙ ለመጀመርያ ጊዜ ነው፡፡
የኢትዮጵያ መንግሥት እነዚህ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች፣ በተለይ የምዕራባዊያን የፖለቲካ አቋም ኒዮ ሊብራሊዝምን አራማጆች በሚል ምንም ዓይነት መለሳለስ የማያሳይ ሲሆን፣ የአገሪቱ የፖለቲካ ዕድል በራሷ ሕዝቦችና በራሷ መንግሥት ብቻ እንዲወሰን የፀና አቋም አለው፡፡
ጠንካራና ነፃ የሰብዓዊ መብት ተቋም በሌለበት በየትኛውም አካባቢ በሚኖር ሕዝብ የሚፈጸም የሰብዓዊ መብት ጥሰት ያገባኛል የሚል አቋም ያላቸው እነዚህ ድርጅቶች ግን፣ ሰብዓዊ መብት የዓለም አቀፋዊነት (ዩኒቨርሳል) ጉዳይ መሆኑን በመከራከሪያነት ያቀርባሉ፡፡
ደብዳቤው ክብደት ይኖረው ይሆን?
አርባ አንድ ድርጅቶች ፊርማቸውን ያሳረፉበትና “Detention of Bloggers is a Violation of International Law” [ጦማርያንን ማሰር ዓለም አቀፍ ሕግን መጣስ ነው] በሚል ለጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም የተላከው ይኸው ደብዳቤ፣ ዋና ይዘቱ ላለፉት ሦስት ወራት በእስር የቆዩትና በቅርቡ ክስ የተመሠረተባቸውን ጦማሪያን መንግሥት በነፃ እንዲለቃቸው የሚጠይቅ ሲሆን፣ ሌሎች ቀደም ሲል ሲያነሱዋቸው የነበሩት ቅሬታዎችም ተካተውበታል፡፡
በመጀመሪያ ኢትዮጵያ በርካታ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ስምምነቶችንና የአፍሪካ ቻርተሮችን ፈራሚ መሆኗ ተጠቅሶ፣ የኢትዮጵያ ፀረ ሽብርተኝነት ሕግ እነዚህን ዓለም አቀፍ ስምምነቶችና የአገሪቱ ሕገ መንግሥት ይጥሳል በሚል ነው፡፡ ለዚህም እንደ ማስረጃ ያቀረቡት፣ አንዳንድ የተመድ አጣሪ ቡድኖች ቀደም ሲል በሽብር የተፈረደባቸው የፖለቲካ አቀንቃኝ እስክንድር ነጋ፣ ጋዜጠኛ ውብሸት ታዬ፣ መምህርትና ዓምደኛ ርዕዮት አለሙና አንዱዓለም አራጌ ላይ ያቀረቡዋቸውን ሪፖርቶች ዋቢ በማድረግ ነው፡፡ በእነዚህ ግለሰቦች ላይ ተፈጸመ ያሉት የሰብዓዊ መብት ጥሰት፣ የፀረ ሽብርተኝነት አዋጅ መንግሥት ተቃዋሚዎችንና ጋዜጠኞችን ለማፈን እንደ መሣሪያ ተጠቅሞበታል የሚለውን ድምዳሜ ዓለም አቀፍ ተቀባይነት ያገኘ ሐሳብ እንደሆነ አቅርበዋል፡፡ የፀረ ሽብርተኝነት አዋጁ እንዲከለስም የደብዳቤው ሌላ ዋና ይዘት ነው፡፡
በደብዳቤው ፊርማቸውን ካሳረፉት ድርጅቶች መካከል የአራቱ ተቀማጭነታቸው በናይጄሪያ፣ የሦስቱ በደቡብ ሱዳን፣ የሁለቱ በግብፅ፣ የሁለቱ ደግሞ በብሩንዲ ሲሆኑ የተቀሩት ማዕከላዊ አፍሪካ፣ ታንዛኒያ፣ ዛምቢያ፣ ዚምባቡዌ፣ ጋምቢያ፣ ምዕራብ አፍሪካና ኬንያ ውስጥ ነው፡፡ የተቀሩት ደግሞ ከዞን ዘጠኝ ጋር በተያያዘ ስሙ ተደጋግሞ ሲነሳ የነበረው አርቲክል 19ን ጨምሮ ተቀማጭነታቸው በአውሮፓና በአሜሪካ ነው፡፡
ደብዳቤው በተመድ፣ በአውሮፓ ኅብረትና በአፍሪካ ኅብረት ድርጅቶች ውስጥ በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ ተፅዕኖ ለመፍጠር ዓላማ ያደረገ ይመስላል፡፡
‹‹መንግሥት አቋሙ መመርመር አለበት›› 
የኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) የቀድሞ ሊቀመንበር አቶ ሙሼ ሰሙ፣ የደብዳቤውን ተፅዕኖ ፈጣሪነት በሁለት አቅጣጫ አይተውታል፡፡ ቀደም ሲል በተመሳሳይ የተለያዩ የተቃውሞ ሪፖርቶች ቢወጡም እዚህ ግባ የሚባል ለውጥ በመንግሥት አሠራር ላይ አለማምጣታቸውን ያስታውሳሉ፡፡ መንግሥትም በራሱ መንገድ ድርጅቶችን መፈረጁን እንደቀጠለ ያስረዳሉ፡፡ እነዚህ ዓይነት ሪፖርቶች ተፅዕኖ ያልነበራቸው አንድም በመንግሥት ቀድመው የተፈረጁ በመሆናቸው ለመቀበል የሚያሳየው ባህሪ አነስተኛ መሆኑን፣ እንዲሁም ድርጅቶቹ የሪፖርት እወጃቸው በመንግሥት ተቀባይነት ሲያጣ ቀጥለው የሚሠሩት ሥራ አለመኖሩ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ ‹‹እስከምን ድረስ ይሄዳሉ?›› የሚል ጥያቄም ሰንዝረዋል፡፡
አቶ ሙሼ በተጨማሪ የትም ቢሄዱ ‹‹ምን ያህል ተፅዕኖ መፍጠር ይችላሉ?›› የሚል ሌላ ጥያቄ ያነሳሉ፡፡ ‹‹ድርጅቶቹ ቀጥተኛ ተፅዕኖ መፍጠር አይችሉም፡፡ የተቀመጡባቸው አገሮች መንግሥታት ኢትዮጵያ ላይ አንዳንድ የዕርዳታና የብድር ማዕቀብ እንዲጥሉ የሚወተውቱ ቢሆንም፣ እስካሁን ተግባራዊነቱ አልታየም፤›› ሲሉም አክለዋል፡፡
መንግሥታት በእነዚህ ድርጅቶች ከሚቀርብላቸው ጥያቄ የበለጠ አቋማቸውን የሚመለከቱት ከአጠቃላይ የሕዝብ ፍላጎትና የአገር ለአገር ግንኙነት አንፃር መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
አቶ ሙሼ እንደሚሉት ደብዳቤው ሌላ ፋይዳ ግን አለው፡፡ በዚህ ደረጃ ለኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር የቅሬታ ደብዳቤ ሲጻፍ ለመጀመሪያ ጊዜ መሆኑን የጠቆሙት አቶ ሙሼ፣ ለድርጅቶቹ ቁጥር ትልቅ ሥፍራ ሰጥተውታል፡፡ ‹‹በያሉበት የራሳቸውን ተፅዕኖ ይፈጥራሉ፤›› ብለዋል፡፡
እሳቸው እንደሚሉት፣ መንግሥት ጥያቄው ከእነሱ ስለመጣ ሳይሆን የተጻፈውን በትዕግሥት አይቶ ክፍተቱን ለመሙላት አቋሙን በመፈተሽ ቢጠቀምበት መልካም ነው፡፡ ዋናው ተፅዕኖ አገር ውስጥ ከሚገኙት ከሕዝብና ከተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች መሆን እንዳለበትም መክረዋል፡፡ ‹‹ሰው በአስተሳሰቡ ምክንያት መታሰር የለበትም፤›› በማለት በፍርድ ቤት በተያዘ ጉዳይ ላይ ከዚህ የዘለለ አስተያየት ከመስጠት አቶ ሙሼ ተቆጥበዋል፡፡
ቀደም ሲል እንዲህ ዓይነት ሪፖርት ከሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ሲወጣ መንግሥት አፋጣኝ ምላሽ የሚሰጥ ሲሆን፣ ለዚህኛው ደብዳቤ መልስ በሚመስል ሁኔታ ስለድርጅቶቹ ሪፖርት እንከንና ስለኢትዮጵያ አቋም የሚያሳይ ዶክመንተሪ በኢቲቪ ማክሰኞ ምሽት ቀርቧል፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በሰጡት አጭር ምላሽ የመማር፣ የመጻፍና የማሰብ ነፃነት የመሳሰሉ የሰብዓዊ መብት ጉዳዮች የኢትዮጵያ መንግሥት የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ አካል መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡ ከዚህም በመነሳት፣ ‹‹ሰብዓዊ መብት የኢትዮጵያ ፖሊሲ እምብርት ነው፣ የህልውናችን ጥያቄ ነው፤›› በማለትም፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ግልጽ የሆነ የሕግ ጥሰት ካልተፈጸመ በስተቀር ሰዎች የመሰላቸውን በመጻፋቸው እንደማይታሰሩ አስረድተው፣ የውጭ ድርጅቶችን የሚመለከት ጉዳይ እንዳልሆነም ገልጸዋል፡፡ ‹‹በአንድ ሉዓላዊ አገር ፖለቲካ ውስጥ እየገቡ እገሌን ፍቱ፣ እገሌን እሰሩ የማለት መብት የላቸውም፣ በእነሱ ጥያቄ የሚመጣ ለውጥ አይኖርም፤›› ብለዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ለተማፅኖው ደብዳቤ ግልጽ ምላሽ ያልሰጡ ቢሆንም፣ ቀደም ሲል ለእስር የተዳረጉ ጋዜጠኞችንና ጦማሪያንን አስመልክቶ ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱ፣ ‹‹አንድም በሙያው የታሰረ ሰው የለም፡፡ ኢትዮጵያን ለማናጋት የተዘረጋው የሽብር መረብ እስኪበጣጠስ ግን ከዚህ መረብ ጋር የተገናኘ ማናቸውም ሰው ላይ ዕርምጃ መውሰዳችን እንቀጥላለን፤›› በማለት የመንግሥታቸውን አቋም ግልጽ አድርገዋል፡፡

Freitag, 1. August 2014

ጋዛ-ተኩስ አቁምና ዉጊያ

‪#‎DW‬
እሥራኤልና የፍልስጤም ደፈጣ ተዋጊዎች ተስማምተዉበታል የተባለዉ ተኩስ አቁም ታዉጆ ሳያበቃ ተኩሱ ቀጥሏል።የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትና የዩናይትድ ስቴትስ ባለሥልጣናት እንዳስታወቁት ሁለቱ ወገኖች ለጋዛ ሕዝብ ሠብአዊ ርዳታ እንዲደርስ ለሰባ-ሁለት ሰዓታት ተኩስ ለማቆም ተስማምተዉ ነበር።ዋና ፀሐፊ ፓን ጊ ሙን በቃል አቀባያቸዉ በኩል ባስተላለፉት መልዕክት እንዳሉት ተኩስ አቁሙ ለተጨማሪ ድርድር በር ይከፍታል የሚል ተስፋም ነበር።
«ይሕ ለሠብአዊ ርዳታ ሲባል የተደረገዉ ተኩስ አቁም በሐገሬዉ አቆጣጠር አርብ ነሐሴ 1 2014 ከጠዋቱ ሁለት ሰዓት ጀምሮ እስካልተራዘመ ድረስ ለ72 ሠዓታት የሚቆይ ነዉ።በዚሕ ጊዜ ዉስጥ ተዋጊዎች በያሉበት ይቆያሉ።የእስራኤልና የፍልስጤም መልዕክተኞች በግብፅ መንግሥት ጋባዥነት ዘላቂ ተኩስ አቁም ለማድረግ ለድርድር ባስቸኳይ ወደ ካይሮ ይጓዛሉ።በዚሕ ድርድር የሚካፈሉት ወገኖች ሁሉንም ጉዳይ ያነሳሉ።»
የዓለም አቀፉ ድርጅት መገለጫ ተሠራጭቶ ሳያበቃ ተኩስ አቁሙ ተጥሶ ጋዛ እንደመሰንበቻዉ መንደድ ይዛለች።ለተኩስ አቁሙ መጣስ እሥራኤልና የፍልስጤም ደፈጣ ተዋጊዎች አንዳቸዉ ሌላቸዉን እያወገዙ ነዉ። የእስራኤል ጦር ራፋሕ በተባለችዉ ከተማ አጠገብ በፈፀመዉ ድብደባ ብቻ ሐምሳ ሰዎችን ገድሏል።ከሁለት መቶ በላይ አቁስሏል።የፍልስጤም ደፈጣ ተዋጊዎች ደግሞ ሁለት የእስራኤል ወታደሮች ገድለዋል፤ አንድ ማርከዋል።የእስራኤል ጦር ጋዛን መደብደብ ከጀመረበት ካለፈዉ ሐምሌ አንድ ጀምሮ የገደላቸዉ ፍልስጤማዉያን ቁጥር 1500 ደርሷል።አብዛኞቹ ሠላማዊ ሰዎች ናቸዉ።የፍልስ ጤም ደፈጣ ተዋጊዎች ስልሳ-ስድስት እስራኤላዉያን ገድለዋል።ሠላማዊ ሰዎቹ ሰወስት ብቻ ናቸዉ።

የህወሃት ሽብር መቆም አለበት!

August 1, 2014
ዛሬ በኢትዮጵያ መሬት ላይ ያለ አሸባሪ ወያኔና ወያኔ ብቻ ነው። በኢትዮጵያ ውስጥ ሰዎችን በፖለቲካ አመለካከታቸው፣ መንግስት በመተቸታቸው በግልጽ በመጻፋቸውና በአደባባይ በመናገራቸው ከዚህም አልፎ በጥርጣሬ በተለይም በብሄረሰብ ማንነታቸው እያሳደደ የሚያፍን የሚያሰቃይና የሚገል የሽብር ተቋም ካለ ወያኔ ብቻ ነው። በኢትዮጵያ መሬት ላይ ሰላማዊ ዜጎችን ኢላማ ያደረገ የተቃውሞ ሃይል በተግባርም ሆነ በአስተሳሰብ ከወያኔ ውጪ አንዳች ሃይል የለም።
አፋኙ የወያኔ ስርአት በተለየም የህዝቡን ሀብትና ንብረት እየዘረፉ የሚቀማጠሉት የህወሃት መሪዎችና ሎሌዎቻቸው የተቃውሞ ድምጽ በሰሙ ቁጥር እንደሚሸበሩና እንቅልፍ አጥተው እንደሚያድሩ ይታወቃል። አፍነውና ዘርፈው ገለው የሚገዙት ህዝብ ግፍ በዛብኝ ብሎ በተናገረ ቁጥር የሚሸበሩት እነሱ ብቻ እንጂ ህዝቡ አይደለም።
በኢትዮጵያ ምድር ያለው አሸባሪ ወያኔ ብቻ መሆኑን ሺ ምሳሌዎችን ጠቅሶ ማስረዳት ይቻላል። ሶስት አመት ሙሉ የሰላም እጃቸውን እየዘረጉ ከልመና ባልተለየ ሁኔታ መብታቸውን የጠየቁና ድምጻችን ይሰማ ያሉት የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ማንንም ዜጋ አላሸበሩም። የተገላቢጦሽ እነሱ አሸባሪ ተብለው የግፍ ሰቆቃ ይፈጸምባቸዋል። ጋዜጠኞችና ጦማሪዎቹ መንግስት ያወጣውን ህግ እንዲያከብር ስለጠየቁ በአደባባይ ስለጻፉ ግፍ ይፈጸምባቸዋል። እነሱ ያሸበሩት ሀገርና ህዝብ የለም። ከመንገድ ላይ ጎትተው እንደ እባብ ቀጥቅጠውና ፈነካክተው በማግስቱ ፍርድ ቤት ያቀረቧት ወየንሸት ሞላ የተባለች ባለ ተስፋ ወጣት የወያኔ አረመኔዎች በሙስሊሙ ህዝብ ላይ የሚሰሩትን ጭፍጨፋ እግር ጥሏት ከማየትና ከመታዘብ ውጪ ያሸበረችው ሰው፣ ሀገር የለም። በየወህኒ ቤቱ እና አፈና ጣቢያው ታስረው የሚቀጠቀጡት የኦሮሞ ልጆች ለጥያቄያቸው መልስ ሲጠብቁ ከመጨፍጨፍ ያለፈ የፈጸሙት እብሪት የለም። በየክልሉ ቀና ብለህ ባለስልጣን ተናገርክ፣ ጥያቄ ጠየቅክ፣ ባለስልጣን ደፈርክ፣ ተሰብስበህ አየንህ ወዘተ እየተባለ የሚገረፈው እንደ እንስሳ እየተገደለ የሚጣለው ገበሬ የሰራው ወንጀል የለም። አሸባሪም አይደለም! በየቦታው ቦንብ እየቀበረ አፈንድቶ ንጹሃንን ገድሎ ሊያፈነዱ ሲሉ ፈንድቶባቸው ራሳቸውን ገደሉ ብሎ በአደባባይ የሚሳለቀው አሸባሪው ህወሃት እንጂ ንጹሃኑ አይደለም።
የኛ መሪ አንዳርጋቸው ከልጅነት እድሜው ጀምሮ ራሱን ለህዝብ ነጻነት የሰጠ አርበኛ እንጂ አሸባሪ አይደለም። በተመሳሳይ ውንብድና ከጎረቤት ሀገር ድረስ በአለም አቀፍ የወረበሎች ውንብድና መንገድ ወያኔ እያፈነ የገደላቸው አሮሞዎችና፣ ሱማሌዎች፣ አኙዋኮች፣ አማሮችና ሌሎችም ነጻነት ከመፈለግ ውጪ ያሸበሩት ህዝብና ሀገር የለም።
በኢትዮጵያ ምድር የነጻነት ድምጽና ኮሽታ በሰማ ቁጥር የሚሸበረው ህወሃትና በለሟሎች ብቻ ናቸው። ይህ የነጻነት ድምጽ ደግሞ እየጎላ መሄዱ የማይቀር ነውና ወያኔ ሰፈር ሽብር ይሆናል።
የኢትዮጵያ ህዝብ ሆይ! ወጣት፣ ሴት፣ ሽማግሌ፣ ገበሬ እና በየቦታው ያላችሁ የኢትዮጵያ ልጆች ሁሉ! አሸባሪህ ወያኔና ወያኔ ብቻ መሆኑን አውቀህ በገዛ ሀገርህ ላይ ነጻነት በተመኘህና በጠየቅህ ጊዜ ሁሉ ለሽብር ጥቃቱ ኢላማ ያደረጉህን ወያኔ ተባብረን ከላያችን ለማውረድ ተነስ! በያለህበት እምቢ በል! ለወያኔ የሚጠቅም የመሰለህን ነገር ሁሉ አታድርግ! አትተባበር! ሸቀጣቸውን አትግዛ! ወያኔዎችን ከማህበራዊ ሂወትህ አግል! የቻልክ ሁሉ ደግሞ የነጻነት አርበኞችን ዛሬ ነገ ሳትል አሁን ተቀላቀል!!! ነጻነታችን ያለው በእጃችን ላይ መሆኑን አትዘንጋ። ግንቦት 7 ሁልጊዜም ከመቼውም ጠንክሮ ከጎንህ ነው።
የወያኔን ሽብር በተባበረ ሃይል እናቁመው!
ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ!!!