Netsanet: በእስር ቆይታቸው 100 ቀናት ለደፈኑት ጦማርያን የተማጽኖ ደብዳቤ ለጠቅላይ ሚኒስተሩ ተላከ፡፡

Samstag, 2. August 2014

በእስር ቆይታቸው 100 ቀናት ለደፈኑት ጦማርያን የተማጽኖ ደብዳቤ ለጠቅላይ ሚኒስተሩ ተላከ፡፡

Augest2/2014

‹‹ዞን ዘጠኝ››  የጦማሪያን ቡድን አባላት ዘለዓለም ክብረት፣ ናትናኤል ፈለቀ፣ ማህሌት ፋንታሁን፣ በፍቃዱ ኃይሉ፣ አቤል ዋበላና ሶልያና ሺመልስ ሲሆኑ፣ ተስፋለም ወልደየሱስ፣ አስማማው ኃይለ ጊዮርጊስና ኤዶም ካሳዬ ደግሞ ጋዜጠኞች ናቸው፡፡ ሶልያና የተከሰሰችው በሌለችበት ነው፡፡
በቅርቡም ቀደም ሲል መንግሥት በአሸባሪነት የፈረጀው የግንቦት ሰባት ዋና ጸሐፊ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ከየመን ዋና ከተማ ሰነዓ በቁጥጥር ሥር ውለው ይገኛሉ፡፡ እንዲሁም ደግሞ በተመሳሳይ ጊዜ በሽብርተኝነት ተጠርጥረው አራት የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች አመራሮችን (አብርሃ ደስታ፣ ሀብታሙ አያሌው፣ ዳንኤል ሺበሺና ስለሺ አሰፋ) መንግሥት በቁጥጥር አውሏል፡፡
ethopia-bloggersመንግሥት የፀረ ሽብርተኝነት አዋጅ ካፀደቀ ጊዜ ጀምሮ በርካቶች በዚህ ሕግ እየጠየቀ ይገኛል፡፡ ይህንን ሕግ፣ የሲቪል ማኅበራት አዋጅ፣ እንዲሁም የፕሬሱ አዋጅ ከዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ ትችት ሲቀርብበት የቆየ መሆኑም አይዘነጋም፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ሰሞኑን በርካታ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ለጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ የተማፅኖ ደብዳቤ ልከዋል፡፡ ከደብዳቤው ፈራሚዎች መካከል ሂዩማን ራይትስ ዎችና አምነስቲ ኢንተርናሽናል በግንባር ቀደምትነት የሚገኙበት ሲሆን፣ እነዚህ ድርጅቶች ኢትዮጵያ ውስጥ ባለው የሰብዓዊ መብት አያያዝና የፕሬስ ነፃነት ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ተስማምተው አያውቁም፡፡
እነዚህ ድርጅቶች በየጊዜው በሚያወጡዋቸው ሪፖርቶች ከመንግሥት ጋር ሲጋጩ የቆዩ ሲሆን፣ በተለይ የኢትዮጵያ የፀጥታ ኃይሎች በሶማሊያና በኦጋዴን ተፈጸመ ባሉት የሰብዓዊ መብት ጥሰት ምክንያት ግንኙነታቸው እጅግ እንዲሻክር ምክንያት ሆኖ ነበር፡፡
አምነስቲ ኢንተርናሽናልና ሂዩማን ራይትስ ዎች አንዳንዴም የአሜሪካ ስቴት ዲፓርትመንት በዓመታዊ ሪፖርታቸው በኢትዮጵያ መንግሥት የሰብዓዊ መብት አያያዝ ላይ ከፍተኛ ትችት የሚሰነዝሩ ሲሆን፣ መንግሥትም አንዳንዴ ዘጋቢ ፊልሞችን በመሥራት የአፀፋ ምላሽ ሲሰጥ ይስተዋላል፡፡
ሰሞኑን ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የተላከው ደብዳቤም አርቲክል 19 እና እነዚህ ሁለት ድርጅቶች በግንባር ቀደምትነት ያሉበት ሲሆን፣ በአጠቃላይ ደብዳቤው ላይ ፊርማቸውን ያሳረፉ ግን ቁጥራቸው አርባ አንድ ነው፡፡
መንግሥት የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችንም ሆነ ጋዜጠኞችን ወይም  የፖለቲካ ተሟጋቾች በእስር ሲያውል እንዲህ ዓይነት ደብዳቤ መጻፍና የታቃውሞ መግለጫ ማውጣት የተለመደ ቢሆንም፣ በዚህ ደረጃ በዓለም ዙሪያ ያሉት የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች (ብዙዎቹም አፍሪካ ውስጥ የሚገኙ ናቸው) በአንድ ላይ መንግሥትን ሲቃወሙ ለመጀመርያ ጊዜ ነው፡፡
የኢትዮጵያ መንግሥት እነዚህ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች፣ በተለይ የምዕራባዊያን የፖለቲካ አቋም ኒዮ ሊብራሊዝምን አራማጆች በሚል ምንም ዓይነት መለሳለስ የማያሳይ ሲሆን፣ የአገሪቱ የፖለቲካ ዕድል በራሷ ሕዝቦችና በራሷ መንግሥት ብቻ እንዲወሰን የፀና አቋም አለው፡፡
ጠንካራና ነፃ የሰብዓዊ መብት ተቋም በሌለበት በየትኛውም አካባቢ በሚኖር ሕዝብ የሚፈጸም የሰብዓዊ መብት ጥሰት ያገባኛል የሚል አቋም ያላቸው እነዚህ ድርጅቶች ግን፣ ሰብዓዊ መብት የዓለም አቀፋዊነት (ዩኒቨርሳል) ጉዳይ መሆኑን በመከራከሪያነት ያቀርባሉ፡፡
ደብዳቤው ክብደት ይኖረው ይሆን?
አርባ አንድ ድርጅቶች ፊርማቸውን ያሳረፉበትና “Detention of Bloggers is a Violation of International Law” [ጦማርያንን ማሰር ዓለም አቀፍ ሕግን መጣስ ነው] በሚል ለጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም የተላከው ይኸው ደብዳቤ፣ ዋና ይዘቱ ላለፉት ሦስት ወራት በእስር የቆዩትና በቅርቡ ክስ የተመሠረተባቸውን ጦማሪያን መንግሥት በነፃ እንዲለቃቸው የሚጠይቅ ሲሆን፣ ሌሎች ቀደም ሲል ሲያነሱዋቸው የነበሩት ቅሬታዎችም ተካተውበታል፡፡
በመጀመሪያ ኢትዮጵያ በርካታ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ስምምነቶችንና የአፍሪካ ቻርተሮችን ፈራሚ መሆኗ ተጠቅሶ፣ የኢትዮጵያ ፀረ ሽብርተኝነት ሕግ እነዚህን ዓለም አቀፍ ስምምነቶችና የአገሪቱ ሕገ መንግሥት ይጥሳል በሚል ነው፡፡ ለዚህም እንደ ማስረጃ ያቀረቡት፣ አንዳንድ የተመድ አጣሪ ቡድኖች ቀደም ሲል በሽብር የተፈረደባቸው የፖለቲካ አቀንቃኝ እስክንድር ነጋ፣ ጋዜጠኛ ውብሸት ታዬ፣ መምህርትና ዓምደኛ ርዕዮት አለሙና አንዱዓለም አራጌ ላይ ያቀረቡዋቸውን ሪፖርቶች ዋቢ በማድረግ ነው፡፡ በእነዚህ ግለሰቦች ላይ ተፈጸመ ያሉት የሰብዓዊ መብት ጥሰት፣ የፀረ ሽብርተኝነት አዋጅ መንግሥት ተቃዋሚዎችንና ጋዜጠኞችን ለማፈን እንደ መሣሪያ ተጠቅሞበታል የሚለውን ድምዳሜ ዓለም አቀፍ ተቀባይነት ያገኘ ሐሳብ እንደሆነ አቅርበዋል፡፡ የፀረ ሽብርተኝነት አዋጁ እንዲከለስም የደብዳቤው ሌላ ዋና ይዘት ነው፡፡
በደብዳቤው ፊርማቸውን ካሳረፉት ድርጅቶች መካከል የአራቱ ተቀማጭነታቸው በናይጄሪያ፣ የሦስቱ በደቡብ ሱዳን፣ የሁለቱ በግብፅ፣ የሁለቱ ደግሞ በብሩንዲ ሲሆኑ የተቀሩት ማዕከላዊ አፍሪካ፣ ታንዛኒያ፣ ዛምቢያ፣ ዚምባቡዌ፣ ጋምቢያ፣ ምዕራብ አፍሪካና ኬንያ ውስጥ ነው፡፡ የተቀሩት ደግሞ ከዞን ዘጠኝ ጋር በተያያዘ ስሙ ተደጋግሞ ሲነሳ የነበረው አርቲክል 19ን ጨምሮ ተቀማጭነታቸው በአውሮፓና በአሜሪካ ነው፡፡
ደብዳቤው በተመድ፣ በአውሮፓ ኅብረትና በአፍሪካ ኅብረት ድርጅቶች ውስጥ በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ ተፅዕኖ ለመፍጠር ዓላማ ያደረገ ይመስላል፡፡
‹‹መንግሥት አቋሙ መመርመር አለበት›› 
የኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) የቀድሞ ሊቀመንበር አቶ ሙሼ ሰሙ፣ የደብዳቤውን ተፅዕኖ ፈጣሪነት በሁለት አቅጣጫ አይተውታል፡፡ ቀደም ሲል በተመሳሳይ የተለያዩ የተቃውሞ ሪፖርቶች ቢወጡም እዚህ ግባ የሚባል ለውጥ በመንግሥት አሠራር ላይ አለማምጣታቸውን ያስታውሳሉ፡፡ መንግሥትም በራሱ መንገድ ድርጅቶችን መፈረጁን እንደቀጠለ ያስረዳሉ፡፡ እነዚህ ዓይነት ሪፖርቶች ተፅዕኖ ያልነበራቸው አንድም በመንግሥት ቀድመው የተፈረጁ በመሆናቸው ለመቀበል የሚያሳየው ባህሪ አነስተኛ መሆኑን፣ እንዲሁም ድርጅቶቹ የሪፖርት እወጃቸው በመንግሥት ተቀባይነት ሲያጣ ቀጥለው የሚሠሩት ሥራ አለመኖሩ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ ‹‹እስከምን ድረስ ይሄዳሉ?›› የሚል ጥያቄም ሰንዝረዋል፡፡
አቶ ሙሼ በተጨማሪ የትም ቢሄዱ ‹‹ምን ያህል ተፅዕኖ መፍጠር ይችላሉ?›› የሚል ሌላ ጥያቄ ያነሳሉ፡፡ ‹‹ድርጅቶቹ ቀጥተኛ ተፅዕኖ መፍጠር አይችሉም፡፡ የተቀመጡባቸው አገሮች መንግሥታት ኢትዮጵያ ላይ አንዳንድ የዕርዳታና የብድር ማዕቀብ እንዲጥሉ የሚወተውቱ ቢሆንም፣ እስካሁን ተግባራዊነቱ አልታየም፤›› ሲሉም አክለዋል፡፡
መንግሥታት በእነዚህ ድርጅቶች ከሚቀርብላቸው ጥያቄ የበለጠ አቋማቸውን የሚመለከቱት ከአጠቃላይ የሕዝብ ፍላጎትና የአገር ለአገር ግንኙነት አንፃር መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
አቶ ሙሼ እንደሚሉት ደብዳቤው ሌላ ፋይዳ ግን አለው፡፡ በዚህ ደረጃ ለኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር የቅሬታ ደብዳቤ ሲጻፍ ለመጀመሪያ ጊዜ መሆኑን የጠቆሙት አቶ ሙሼ፣ ለድርጅቶቹ ቁጥር ትልቅ ሥፍራ ሰጥተውታል፡፡ ‹‹በያሉበት የራሳቸውን ተፅዕኖ ይፈጥራሉ፤›› ብለዋል፡፡
እሳቸው እንደሚሉት፣ መንግሥት ጥያቄው ከእነሱ ስለመጣ ሳይሆን የተጻፈውን በትዕግሥት አይቶ ክፍተቱን ለመሙላት አቋሙን በመፈተሽ ቢጠቀምበት መልካም ነው፡፡ ዋናው ተፅዕኖ አገር ውስጥ ከሚገኙት ከሕዝብና ከተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች መሆን እንዳለበትም መክረዋል፡፡ ‹‹ሰው በአስተሳሰቡ ምክንያት መታሰር የለበትም፤›› በማለት በፍርድ ቤት በተያዘ ጉዳይ ላይ ከዚህ የዘለለ አስተያየት ከመስጠት አቶ ሙሼ ተቆጥበዋል፡፡
ቀደም ሲል እንዲህ ዓይነት ሪፖርት ከሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ሲወጣ መንግሥት አፋጣኝ ምላሽ የሚሰጥ ሲሆን፣ ለዚህኛው ደብዳቤ መልስ በሚመስል ሁኔታ ስለድርጅቶቹ ሪፖርት እንከንና ስለኢትዮጵያ አቋም የሚያሳይ ዶክመንተሪ በኢቲቪ ማክሰኞ ምሽት ቀርቧል፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በሰጡት አጭር ምላሽ የመማር፣ የመጻፍና የማሰብ ነፃነት የመሳሰሉ የሰብዓዊ መብት ጉዳዮች የኢትዮጵያ መንግሥት የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ አካል መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡ ከዚህም በመነሳት፣ ‹‹ሰብዓዊ መብት የኢትዮጵያ ፖሊሲ እምብርት ነው፣ የህልውናችን ጥያቄ ነው፤›› በማለትም፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ግልጽ የሆነ የሕግ ጥሰት ካልተፈጸመ በስተቀር ሰዎች የመሰላቸውን በመጻፋቸው እንደማይታሰሩ አስረድተው፣ የውጭ ድርጅቶችን የሚመለከት ጉዳይ እንዳልሆነም ገልጸዋል፡፡ ‹‹በአንድ ሉዓላዊ አገር ፖለቲካ ውስጥ እየገቡ እገሌን ፍቱ፣ እገሌን እሰሩ የማለት መብት የላቸውም፣ በእነሱ ጥያቄ የሚመጣ ለውጥ አይኖርም፤›› ብለዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ለተማፅኖው ደብዳቤ ግልጽ ምላሽ ያልሰጡ ቢሆንም፣ ቀደም ሲል ለእስር የተዳረጉ ጋዜጠኞችንና ጦማሪያንን አስመልክቶ ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱ፣ ‹‹አንድም በሙያው የታሰረ ሰው የለም፡፡ ኢትዮጵያን ለማናጋት የተዘረጋው የሽብር መረብ እስኪበጣጠስ ግን ከዚህ መረብ ጋር የተገናኘ ማናቸውም ሰው ላይ ዕርምጃ መውሰዳችን እንቀጥላለን፤›› በማለት የመንግሥታቸውን አቋም ግልጽ አድርገዋል፡፡

Keine Kommentare:

Kommentar veröffentlichen