ከጌታቸው ሽፈራው
ባለፈው ሶስትና አራት ወር ውስጥ ብቻ 17 ያህል ጋዜጠኞች አገር ጥለው ተሰድደዋል፡፡ በተለይ ባለፈው ሳምንት 12 ያህል ጋዜጠኞች ሲሰደዱ በርካታ ኢትዮጵያውያን ‹‹ለምን ተሰደዱ?›› የሚለውን በደንብ ሳያጤኑ ለመውቀስ ሲጥሩ ተመልክቻለሁ፡፡ በእርግጥ ጋዜጠኞቹ መሰደዳቸውን አልደግፍም፡፡ ነገር ግን እነዚህ ጋዜጠኞች ለምን ተሰደዱ ብለን ሳናጤን መውቀስም ተገቢ መስሎ ስላልታየኝ ነው፡፡
ከተሰደዱት መካከል ሁለቱን ብቻ ልጥቀስ፡፡ ተሰማ ደሳለኝ ይባላል፡፡ ኢቦኒ የተሰኘች መጽሄት ነበረችው፡፡ ተሰማ ፌስ ቡክና ኢንተርኔት ለቅሞ ከማሳተም ይልቅ ጋዜጠኛ ቀጥሮ ያሰራ ነበር፡፡ መጽሄቷ የሙያውን ስነ ምግባር የጠበቀች እንድትሆንም ጥሯል፡፡ ነገር ግን የመንግስት ስውር እጆች በሚቃኙት ማከፋፈያ (በተለይም ሁለተኛ ደረጃ አከፋፋዮች)፣ የህትመት ዋጋ አንዱ ፈተና ነበር፡፡ ተሰማ ስፖርትና ፋሽን ላይ የሚሰሩ መጽሔቶች ማስታወቂያ እንደሚያገኙ፣ የመንግስት ጫና እንደማይደርስባቸው ያውቃል፡፡ እሱ ግን የመረጠው ለአገሬ ህዝብ ይጠቅማል ያለውን ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮችን ማንሳት ነው፡፡ በእነዚህ ጉዳዮች የሚያጠነጥኑት ደግሞ ማስታወቂያ አያገኙም፡፡ ይታፈናሉ፣ ማተሚያ ቤት አያገኙም፡፡ እናም ኢቦኒ ገበያውን መቋቋም አልቻለችም፡፡ እንዲያውም እዳ አለብህ ተባለ፡፡ ተሰማ ልጅና ቤተሰብ አለው፡፡ ተቋሙ ግን ተዘግቷል፡፡ እንዲህም ሆኖ እዳውን ካልከፈለ የሚጠብቀው እስራት ነው፡፡ አሊያም ጎዳና፡፡ በዚህን ወቅት አንድም ሰው ሊያግዘው አልቻለም፡፡ በህትመት ላይ እያለም ለዴሞክራሲያዊ ግንባታ በሚያደርገው አስተዋጽኦ ይህ ነው የሚባል ማስታወቂያ አያገኝም ነበር፡፡ እናም ለአገሩ ሰርቶ መኖር ብቻ ሳይሆን በአገሩ ሰርቶ መኖር ሲያቅተው ከሁለት ወር በፊት አገሩን ጥሎ ተሰደደ፡፡
ሌላኛው አስናቀ ልባዊ ነው፡፡ አስናቀ የጃኖ መጽሄት ባለቤት ነው፡፡ መጻፍ አደገኛ መሆኑን እያወቀም ቢሆን ሲጽፍ ቆይቷል፡፡ ስርዓቱ የማይፈልጋቸውን ጉዳዮች ላይ ዜናዎችን ሲሰራ ‹‹አለቀለት!›› ተብሏል፡፡ ይህን ስራ በድፍረት እየሰራን ቢሆን መሰረታዊ የሆነ የሚዲያው ችግሮች እሱንም አልለቀቁትም፡፡ ማስታወቂያ ማግኘት እጅጉን ፈታኝ ነው፡፡ ከዚህ አለፍ ሲል ደግሞ ተከሰሰ፡፡ በትንሹ 50 ሺህ ብር ቢቀጣ የት አምጥቶ ይከፍላል? እሱም ለአገሩ ሰርቶ መኖር ይቅልና ሰርቶ መኖርም ፈታኝ ሆነብኝ ብሎ ተሰደደ፡፡
የኢትዮ ምህዳሩ ኤፍሬም ያ በደል የደረሰበት ሲሰርቅ ተይዞ አይደለም፡፡ እስክንድር፣ ርዕዮትና ውብሸት የታሰሩት ሲጽፉ ነው፡፡ በጣም የሚያሳዝነው 90 ሚሊዮን ህዝብ ባላት ኢትዮጵያ 80ና 90 ሺህ ብር ለማውጣት አልተቻለም ነበር፡፡ ውብሸት ታየን በትንሹም ቢሆን ያስታወስነው ፈረንጆቹ ከሸለሙት በኋላ ነው፡፡ የዚህ ትንታግ ጋዜጠኛ ልጅ ትምህርቱን ለማቋረጥ ምንም አልቀረውም ነበር፡፡ ሚስቱ ብዙ ተቸግራለች፡፡ እስክንድር ነጋን የምንጠይቀው ስንቶቻችን ነን? እጅግ በጣም ጥቂቶቹ! ጋዜጠኛ ሲሰደድ ግን አብዛኛው ኢትዮጵያዊ ወቀሳችንን እናዥጎደጉዳለን፡፡ አስናቀና ተሰማ ኤፍሬም ተጎድቶ አብዛኛው ባለሃብት፣ ዲያፖራ፣ ምሁር……ፀጥ ሲል የአይን እማኞች ነበሩ፡፡ የውብሸት ታዬ ልጅና ሚስት መቸገራቸውንና እሱም አስታዋሽ ማጣቱን ከእነሱ በላይ የታዘበ የለም፡፡ ወደድንም ጠላንም ጋዜጠኛም ሰው ነውና አለኝታ ይፈልጋል፡፡ ይህን ሲያጣ ደግሞ ስደትን ሊመርጥ ይችላል፡፡
እነዚህ ሚዲያዎች እየሰሩ በነበረበት ወቅት ማስታወቂያ ሲጠይቋችሁ ‹‹አይ ፖለቲካ ነው የምትጽፈው!›› ብላችሁ ፊታችሁን ያላጠቆራችሁ (ካላችሁ)፣ ስህተት ስታዩበት እንዲሻሻል ደውላችሁ የጠየቃችሁ፣ አንድም መረጃ አገኝበታላሁ ብላችሁ፣ አሊያም በመግዛታችሁ ሚዲያው ይጠናከራል ብላችሁ የገዛችሁ ‹‹ጥለውን ሄዱ!›› ብላችሁ ብታማርሩ ምክንያት ይኖራችኋል፡፡ ይገባችኋልም!
ነገር ግን ለስፖርትና ፋሽን ማስታወቂያ እየሰጠህ እነዚህ መጽሄቶች ማስታወቂያ ሲጠይቁ ‹‹ፖለቲካ ነው የምታሳትሙት!›› ብለህ መልሰህ አሁን ሲሰደዱ ‹‹አይ የእኛ አገር ጋዜጠኞች!›› ያልክ ነጋዴ ለመፍረድ ሞራል የለህምና አትፍረድ! ቃለ መጠይቅ ለማድረግ ሲደወልልህ ‹‹አይ ይህ መንግስት እኮ…ቅብጥርጥስ›› ብለህ የሸሸህ ‹‹ምሁር›› ጋዜጠኞቹ ተሰደዱ ብለህ እንዳትፈርድ፣ አንተም ድሮም የኢትዮጵያውያን ጉዳይ አያገባኝም ብለሃል አሁን እንዳትፈርድ! ያኔ እነዚህ መጽሄቶችን እንዲሁ አይተህ ያለፍክ ‹‹አንባቢ›› አታውቃቸውምና ተሰደዱ ብለህ እርር ድብን እንዳትል፣ እንዳትፈርድ!
እነዚህ ጋዜጦች አትምልን ሲሉህ ‹‹መንግስት በተዘዋዋሪም ሆነ በቀጥታ ጫና ያደርስብኛል፣ ለምን ስፖርት አታሳትምም….›› ያልክ የማተሚያ ቤት ባለቤት አሁን ጋዜጠኞች ተሰደዱ ብለህ ከመፍረድህ በፊት የአንተን አስተዋጽኦም መርምር! ኢትዮጵያ ውስጥ ሚዲያዎች በእሳት ላይ መቀመጣቸውን እያወክ፣ ማገዝም እየቻልክ ሲሰደዱ ብቻ በመቆዘም፣ ሲታሰሩ የፌስ ቡክ ፎቶውን በመቀየር ብቻ ለውጥ የሚመጣ የሚመስለህ ዳያስፖራ ‹‹አይ ጋዜጠኛ!›› ከማለት በፊት ‹‹እኔ ምን አደረኩ?›› ብለህ መጠየቅ ይገባሃል፡፡
የኢትዮጵያውያንን መብት ለማስጠበቅ ተቋቁሞ ጋዜጠኞች ሲታሰሩ፣ ሚዲያዎች ሲዘጉ ሀሳብን በነጻነት ለመግለጽ ነጻነት ያልጮህክ ተቃዋሚና ፖለቲከኛ አሁን ሲወጡ ‹‹አቤት ፍርሃት!›› ከማለት በፊት የራሰህን አስተዋጽኦ መገምገም የግድ ነው፡፡ ለሚዲያውም ሆነ መረጃ አገኝበታለሁ ብለህ ሚዲያዎቹን በመግዛት የራስህን አስተዋጽኦ ያላደረክ ‹‹አንባቢ›› በስሚ ስሚ ‹‹ተሰደዱ!›› አደራህን እብዳትፈርድ!
የኢትዮጵያውያንን መብት ለማስጠበቅ ተቋቁሞ ጋዜጠኞች ሲታሰሩ፣ ሚዲያዎች ሲዘጉ ሀሳብን በነጻነት ለመግለጽ ነጻነት ያልጮህክ ተቃዋሚና ፖለቲከኛ አሁን ሲወጡ ‹‹አቤት ፍርሃት!›› ከማለት በፊት የራሰህን አስተዋጽኦ መገምገም የግድ ነው፡፡ ለሚዲያውም ሆነ መረጃ አገኝበታለሁ ብለህ ሚዲያዎቹን በመግዛት የራስህን አስተዋጽኦ ያላደረክ ‹‹አንባቢ›› በስሚ ስሚ ‹‹ተሰደዱ!›› አደራህን እብዳትፈርድ!
የትም ሁኑ የት፣ እናንተ! የጋዜጠኞችን መብት ይከበር ዘንድ ያለ ፍርሃት በድፍረት የጮኻችሁ ‹‹ለምን ተሰደዱ?›› ብላችሁ ብትወቅሱ ምክንያት ይኖራችኋል፡፡ ማስታወቂያ ሲጠይቋችሁ የሰጣችሁ፣ አንብባችሁ ገንቢ አስተያየት የለገሳችሁ፣ ያበረታታችሁ ብቻ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ጋዜጠኞች ለሚዲያ፣ ሚዲያው ለዴሞክራሲ፣ ዴሞክራሲው ለኢትዮጵያውያን ይጠቅማል ብላችሁ ይብዛም ይነስም የራሳችሁን አስተዋጽኦ ያደረጋችሁ ‹‹ለምን ተሰደዱ?›› ብትሉ ያምርባችኋል! ያገባናል ብላችሁ የቻላችሁትን ሁሉ አድርጋችኋልና!
Keine Kommentare:
Kommentar veröffentlichen