Netsanet: ይድረስ ለወዳጄ… (6ኛው ተከሳሽ ዘላለም ክብረት – ከቂልንጦ እስር ቤት – ክፍል ሁለት)

Samstag, 30. August 2014

ይድረስ ለወዳጄ… (6ኛው ተከሳሽ ዘላለም ክብረት – ከቂልንጦ እስር ቤት – ክፍል ሁለት)

August30,2014

የኔ ፅጌረዳ ሰላም ላንች ይሁን! እንዴት ነሽልኝ? ባለፈው የፃፍኩልሽን ቧልታይ የበዛበት ደብዳቤ አነበብሽው ይሆን? ዛሬ ደግሞ ስለክሴ፣ ስለከሳሼና ስለአጠቃላይ ሁኔታዎች ልጽፍልሽ አሰብኩ፡፡ እንግዲህ በዚህ ደብዳቤ ትንሽ ኮስተር ሳልል አልቀርምና ከወዲሁ ይቅርታን እለምናለሁ፡፡
ዘላለም ክብረት
ዘላለም ክብረት
ግርምቴ
ከታሰርኩበት ሚያዝያ 17/2006 ጀምሮ በጣም ሲገርመኝ የነበረው ነገር የፖሊስ/የመንግስትና የሕግ ታላቅ እኩያ ነው፡፡ መንግስት ሁሌም ሕግን ለማሸነፍ በሙሉ ድል ‹ተጠርጣሪዎ› ለመክሰስ ችሏል፡፡ ከተያዝኩበት ደቂቃ ጀምሮ አውቆ በሚመስል መልኩ የተለያዩ የፍትሕ አካላት እያንዳንዱን የሕግ አንቀፆች በተግባር ሊጥሏቸው ማየቴ ነበር የመገረሜ ምክንያት፡፡
ለሕጎቹና ለሕግ አካላቱ ቅርብ በመሆኔ ምክንያት የመንግስት አካላቱ ይወስዷቸው የነበሩትን የተለያዩ ርምጃዎች በሕጉ አይን በማየቴ ሊሆን ይችላል የሕግ ጥሰቱ እጅግ ጎልቶ የታየኝ፡፡
የፍተሸ ፈቃድ (Search Warrant) ከእሰር ማዘዣ (Arrest Warrant) ጋር በአንድ ወረቀት ላይ ተደባልቆ በመምጣቱ ገና ከመታሰሬ ነው የሕጉ ነገር ያሳሰበኝ የጀመረው፡፡ ሕግ ስንማር የፍተሻ ፈቃድ ከእስር ማዘዣ ተለይቶ እንደሚመጣ፣ በፍተሻ ፈቃዱ ላይ ሊፈተሸ የተፈለገው ነገር በግልፅ ሊቀመጥ እንደሚገባ፣ ፍተሻ ከጠዋቱ 12 ሰዓት እስከ ምሽቱ 12 ሰዓት መከናወን እንዳለበት …ብንማርም ‹ፖሊስ› በታሰርኩበት ወቅት አንዱንም የሕግ አንቀፅ ላለማክበር ያሰበ በሚመስል መልኩ የፍተሻ ፈቃድን ከእስር ፈቃድ ሳይለይ፣ ፍተሻውን ከምሽቱ 12 ሰዓት በኋላ በመጀመር፣ በፍተሻው ምን ማግኘት እንደሚፈልግ የማይገልፅ የፍተሸ ፈቃድ በማሳየትና እኔ ስጠይቅም ለመናገር ፍቃደኛ ባለመሆን… ሕጉን‹ንዶ ንዶ› የኔን የግለሰቡን መብቶች በዜሮ በማባዛት ‹ወንጀልን የመከላከል ርምጃውን› ጀመረው፡፡ በፍተሻ ወቅት የሚፈለገው ነገር ምንነት አለመገለፁም ፖሊስ ‹ለጠረጠረኝ› ሕገ-መንግሥቱንና ሕገ-መንግሥታዊ ስርዓቱን በኃይል፣ በዛቻና በአድማ የመናድ ወንጀል እንደ ኤግዚቢት የያዛቸው ‹ማስረጃዎች› ምንነት ይገልጣቸዋል፡፡
በፍተሻ ወቅት ፖሊስ ከቤቴ በኤግዚቢትነት ከያዛቸው ‹እቃዎች› መካከል 90 በመቶው ገበያ ላይ ያሉ መጽሐፍት ሲሆኑ ከነዚሀም መካከል የPaulo Coelho “By the river paedra I set down and wept’ PV.I.Lenin ‘what is to be done’ የአፄ ሱስንዮስ ዜና መዋዕል፣ የፍቅረስላሴ ወግደረስ ‹እኛና አብዮቱ›… ጨምሮ ሌሎች መፅሀፍት የሚገኝበት ሲሆን፤ የተለያዩ የሙዚቃ ሲዲዎችም በኤግዚቢትነት ተይዘዋል፡፡
(የሚገርመው ፍተሻው ሕገወጥ መሆኑን ‹ለፖሊስ› በተደጋጋሚ ብናገርም ‹ብርበራ ከጀመርን በኋላ ልናቋርጥ አንችልም›፣ የሚያስፈልገንን ነገር አንተ ልትነግረን አትችልም… የሚሉ መልሶች በመስጠት ‹አዲዮስ ሕግ› የሚል አሰራር ከመከተላቸውም በላይ በቤቴ የተገኘ እንደ ‹አዲስ ራእይ› አይነት መፅሄቶችን የብርበራው መሪ የሆኑ ግለሰብ ለበታች መርማሪዎች ‹ተዉት እሱ የኛ ነው› የሚል አመራር እየሰጡ ግርምቴን አብዝተውት ነበር፡፡ ጉዳዩን አስቂኝ የሚያደርገው ደግሞ በፍተሸው ወቅት ቤቴ ውስጥ ከተያዙት ‹ኤግዚቢቶች› መካከል አንዱም እንኳን ለክስ ማስረጃ ሁነው አለመቅረባቸው ነው፡፡ ይህ ነው እንግዲህ ለህግ ት/ቤት ‹search is not a fishing expedition in which the police grabs every thing › ተብለን የተማርነው፡፡)
የእስርና የምርመራ ጊዜ ደግሞ ፖሊስ ሕጉን ለመጣስ ሆን ብሎ የተጋ በሚያስመስለው መልኩ ሕጉ ግድ ሳየሰጠው የፈለገውን ሲያደርግ የከረመበት ወቅት ነው፡፡ በዚህ ወቅት ነው ‹እኛ የሚያሳስበን የአንተ የአንድ ግለሰብ መብት ሳይሆን፣የሰማኒያ ሚሊዮን ሕዝብ ደህንነት ነው› የተባልኩት(ውዴ! Ayn Rand እንኳንም ይሔን ሳትሰማ ሞተች አላልሽም?)፡፡ በዚህ ወቅት ነው ‹የሽብር ሕጉን ጥርስ አውልቃችሁ አምጡ የሚለን ከሆነ ጥርስ ከማውለቅ ወደኋላ አንልም› ብሎ ፖሊስ ሕገ-መንግስቱንና የዜጎች መብትን በአንድ ላይ ሲቀብራቸው የተመለከትኩት፡፡ (‹ሕገ -መንግስቱ የሀገሩ ህጎች በሙሉ የበላይ ሕግ ነው› የሚለው የህገ መንግስቱ አንቀፅ በምድረ በጋ የተደነገገ እንደሆነ ግንዛቤ ለመጨበጥ ችያለሁ)፡፡ በዚህ ወቅት ነው፡ የፍርድ ቤቱ ትእዛዝ እንዲፈፀምልኝ ለጠየኩት ጥያቄ ‹ሂድ ከዚህ!የማነው?! ፍርድ ቤት ማነው እኛን የሚያዘው? ከፈለገች ዳኛዋ ራሷ ትፈፅምልህ…› የሚል መልስ ‹ከህግ አስከባሪ ፖሊስ› የተሰጠኝ፡፡
‹‹ምን አይነት ዘመን ነው ፣ የተገላቢጦሽ፤
አህያ ወደ ቤት፣ ውሻ ወደግጦሽ፡፡
ይሏል እንዲህ ነው፡፡ በዚህ ወቅት ነው፤ ምንም አይነት ሕጋዊ መብቶቼ ሳይነገሩኝ ‹ለምርመራ የተቀመጥኩበትና ብሎግ ላይ የተፃፉ ፅሁፎች የእኔ ‹የእምነት ክህደት ›ቃል እንደሆኑ ተደርገው መፃፍ እንዳለባቸው ትእዛዝ የተሰዘጠኝና በእምነት ክህደት ቃሌ ውስጥ ወይ ‹ጥፋተኛ ነኝ› ማለት አለያም ባዶውን መተው እንጂ ‹ጥፋተኛ አይደለሁም› የሚል ነገር መስፈር እንደማይችል የተረዳሁትና ‹ለምን?› ብዬ ስጠይቅም ‹ከበላይ አካል የመጣ ትዕዛዝ› እንደሆነ የተነገረኝ፡፡ (ማሬ፣ ዕድለኛ ባልሆን ኖሮ እንደ ‹አንድ› አባሪዬ ‹ህገ መንግስቱ ተከብሮ እያለ፣ ሕገ-መንግስቱ ይከበር ‹በማለቴ ጥፋተኛ ነኝ› ብለህ ፈርም ተብዬ መከራዬን አይ ነበር፡፡)በዚህ ወቅት ነው፤ መንግስቴ በመጀመሪያ ‹በሽብር ወንጀል› ባይጠረጥረኝም የፀረ-ሽብር ሕጉ አንቀፅ 14 በሚያዘው መሰረት ስልኬን ከግንቦት 2005 ዓ.ም ጀምሮ በመጥለፍ ንግግሬን ሁሉ ሊያደምጥ እንደነበር የተረዳሁትና ‹‹እንዴ ‹የሽብር ተግባራትን ለመፈፀም የማሴር ወንጀል› የተጠረጠርኩት ከታሰርኩ ከ23 ቀናት በኋላ ነው፤ ይሄም ፖሊስ እስከታሰርኩበት 23ኛ ቀን ድረስ በሽብር ጉዳይ ምንም አይነት ጥርጣሬ ያልነበረው ሲሆን ታዲያ ስልኬን አንድ አመት ለሚሆን ጊዜ እንዴት የፀረ ሽብር-ሕጉን ጠቅሶ ሊጠልፍ ቻለ?›› ብዬ ለጠየኩት ጥያቄ መልሱ ዝምታ እንደሆነ የተረዳሁት፡፡ (በነገራችን ላይ ስልኬ ለረጅም ጊዜ ቢጠለፍም ለማስረጃነት የቀረበብኝ ከአባሪዎቼ ጋር ‹ሻይ-ቡና እንበል እስኪ ብለን ያወራናቸው ወሬዎች ሲሆኑ፤ካንቺ ጋር ያውራናቸው ወሬዎች በማስረጃነት ባለመምጣታቸው ቅር መሰኘቴን በዚህ አጋጣሚ እገልፃለሁ፡፡)
ግርምቴ ብዙ ቢሆንም እንዳይሰለችሽ በማሰብ አንድ የመጨረሻ ግርምቴን ልንገርሽና ሌላ ጉዳይ ላይ እናልፋለን፡፡ የእስር፣ የምርመራ፣ የብርበራ … ሁሉ ዓላማ ተጠርጥረው የተጠረጠረበትን ወንጀል የሚያረጋግጥ መረጃ ለማግኘት ቢሆንም ከሁለት ወራት ለሚበልጥ ጊዜ፣ እጅግ የተራዘመ ምርመራ ተደርጎብኝ የቀረበብኝን ክስ ስመለከት ብዙ ነገሮች አስገረሙኝ፡፡ ቀዳሚው ጉዳይ የተከሰስኩበትን ‹የሽብር ተግባር ለመፈፀም የማሴር ወንጀል› በሚመለከት በምርመራ ወቅት አንድም ጥያቄ ያልቀረበልኝ ሲሆን፤ ይሄም ነገር ታዲያ የምርመራው አላማ ምን ነበር? እንድል አድርጎኛል፡፡ ሌላው ገራሚው ጉዳይ የሀገሪቱ ከፍተኛ የምርመራ ሂደት እንዲህ ቧልትና እያንዳንዱን እንቅስቃሴውን ከሕጉ ጋር በመላተም እንደሚያከናውን መገንዘቤ ነው፡፡ ታዲያ ‹ፖሊስ› ህግን ለመጣስ ካለው ትጋት የበለጠ ምን አስገራሚ ነገር አለ ውዴ?!
The Fridgegate Scandal እና ሌሎችም …
እኔ አሁን ደግሞ ወደ ክሴ ልውሰድሽ እስኪ ክሴን ባጭሩ ለማስረዳት ያክል (ምንም እንኳን ክሱ ግልፅ ባይሆንም፣ እኔ እንደመሰለኝ)፤ ‹የሽብር ቡድን በማቋቋም (ከሽብርተኛ ድርጅቶች ጋር ግንኙነት ለማድረግ የሚልም ‹ይመስላል›)በሀገር ውስጥ የተለያዩ የሽብር ድርጅቶችን (ሰውን ለመግደል የሕብረተሰቡን ጤና ለከፍተኛ አደጋ ለማጋለጥ፣ እገታ ወይም ጠለፋ ለመፈፀም፣ ንብረት ለማውደም፣ በተፈጥሮ፣ በታሪካዊና በባሕላዊ ቅርሶች ላይ ጉዳት ለማድረስ፣ የህዝብ አገልግሎቶችን ለአደጋ ለማጋለጥ ወይም በቁጥጥር ስር ለማዋልና ለማበላሸት) በመዘጋጀት፣ በማሴር፣ በማነሳሳትና በመሞከር የሚለው የመጀመሪያውና ዋነኛው ክሴ ሲሆን፤ሁለተኛው ክሴ ደግሞ ያች የፈረደባት ‹ሕገ-መንግስትንና ሕገ-መንግስታዊ ስርዓቱን የመናድ ወንጀል ነው፡፡
ሁለቱም ክሶቼ የቅጣት ጣሪያቸው እስከ ሞት ድረስ መሆኑን መግለፄም አያስከፋሽም ብዬ አስባለሁ፡፡ (ዘጠኝ ሞት መጥቶ ከደጅ ቁሟል ቢለው፣ ስምንቱን ተውና አንዱን ግባ በለው› አለ የሞት ዳኛ፡፡ እንደዳኛው ‹አንዱን ሞት ግባ› ብዬ ከመጋበዜ በፊት ብዙ የማጫውትሽ ጉዳይ አለኝና አስኪ ተከተይኝ ውቤ)
ከሳሼ ‹የሽብር ተግባራትን› ልፈፅም እንደተዘጋሁና እንዳሴርኩ እንዲሁም ‹ሕገ-መንግስቱንና ሕገ-መንግስታዊ ስርዓቱን በሀይል ለመናድ› እንደሞከርኩ ለማስረዳት ያቀረቡልኝ የማስረጃ ዝርዝርን ስመለከት ግን የአሳሪዎችን ፍላጎት ‹ወዲህ› መሆኑን የተረዳሁት፡፡
በምርመራ ወቅት አንድም ጥያቄ ያልቀረበልኝ ‹የሽብር ድርጊት› ዋና ‹ወንጀሌ› ሁኖ ሲመጣ አሳሪዬ ጋር ያለው ፍላጎት ሙሉ ለሙሉ የወንጀል እንዳልሆነ ያስረዳኝ ሲሆን፤ በሰነድ ማስረጃነት ከቀረቡብን ብዙ ገራሚና አስቂኝ ‹ማስረጃዎች› መካከል ‹የሽብር ተግባራትን ከሽብርተኛ ድርጅቶች ጋር በመሆን ለመፈፀም እንዳሴርን› ያስረዳል ተብሎ የቀረበው ዋነኛና ብቸኛ ማስረጃም ከጓደኛዬና አባሪዬ አንደኛ ተከሳሽ፣ ሶልያና ሽመልስ (ክሷ In Abesntia) እየታየ ያለችና በአንድ ቀጠሯችን ፖሊስ ከ Interpol ጋር በመሆን ለመያዝ ጥረት እያደረገ እንደሆነ የገለፁት በጥብቅ የምትፈለግ ‹አሸባሪ› ቤት በሌለችበት ፖሊስ ላደረገው ብርበራ ማቀዝቀዣ Fridge ዙሪያ ‹አገኘሁት› ያለው ግንቦት ሰባት የተባለ ፓርቲ በታህሳስ 2005 የወጣ የአባላት የውስጥ Newsletterና ቀኑ በሰነዱ ላይ ያልተመለከተ ሌላ የዚሁ ፓርቲ ሰነድ ነው፡፡
ውዴ ለመረጃ አንች ከእኔ ትቀርቢያለሽና ከላይ ስለጠቀስኩት ‹ሰነድ› ጉዳይ ብዙ ሰምተሻል የሚል ግምት አለኝ፡፡ እኔ ያለኝን መረጃ እና የዚህ ሰነድ ስለክስ ሒደቱ ሊኖረው ስለሚችለው አመላካችነት አንዳንድ ወሬዎችን እያመጣን እንተክዝ እስኪ፡፡
መቼም አሜሪካ ግሩም ሀገር ነው፡፡ ብዙ ነገሮች እንደቅሌት (Scandal) እየሆኑ ሲወጡ የምናይበት የቅሌቶች ሁሉ ቅሌት ድሞ የRichard Nixon ነው ‘The Watergatge scandal’ ይሉታል፤ ኒክሰን በ1972 ለተደረገው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ መረጃ ለማግኘት በማሰብ በ Washington DC የሚገኘውን የዲሞክራቲክ ፓርቲ ICT ዋና መሥሪያ ቤት Watergate የተባለው ሕንፃ ውስጥ) እንዲበዘበዝ በማስደረጋቸውና ይሄም ድርጊታቸው በፕሬሱ ይፋ በመሆኑ ኒክሰን ከስልጠናቸው ተዋርደው እንዲለቁ ሆነ፡፡
የWatergate ብዝበዛን ተከትሎ ብዙ ሐረጎች ለብዙ ሁነቶች መግለጫ በመሆን ይቀርቡም ጀመር ለምሳሌ ‘The Watergate Burglars’ ‘The Saturday Night Massacre:- ‘United States Vs Nixon’…. (የእያንዳንዷን ዝርዝር Google እያደረግሽ እንደምታይው ተስፋ አለኝ አበባዬ)፡፡ ከዛም በኋላ የተለያዩ ቅሌቶችን ከWatergate ጋር እያያያዙ መጥራት የተለመደ ነው፡፡ አሁንም ሌላ ምሳሌ ‘The Monicagate’ የፕሬዚዳንት ክሊንተንን የወሲብ ቅሌት ለመግለጽ)፣( ‘The Nipplegate’ (በ2003 ዓ.ም ጃኒት ጃክሰን በLive የቴሌቪዥን የሙዚቃ ዝግጅት ላይ ባልታሰበ ሁኔታ ያጋጠማትን የጡት ጫፍ (Nipple) መራቆትና በቴሌቪዥን የቀጥታ ስርጭት ታሪክን የቀየረ ሁነት ለመግለፅ)፤
ይሔን ሁሉ ማለቴ ወዴት ለመሔድ አስቤ እንደሆነ ሳትረጂው አትቀሪም ፍቅር፡፡ ከላይ ወደጠቀስኩልሽ ግንቦት 7 የተባለ ፓርቲ ሰነድ ጓደኛችን ቤት ተገኝ ስለመባሉ ጉዳይ ላስረዳሽ አስቤ ነው፡፡ ተገኘ የተባለው ሰነድ ላይ ጓደኛችን ወክለው ቤቷን ሲያስፈትሹ የነበሩት እናቷ ‹ይህ ሰነድ ፖሊስ ከፋይሉ ጋር ይዞት የመጣው ሰነድ ነው፡፡ እዚህ ቤት የተገኘ አይደለምና እዚህ ቤት ተገኘ ብዬ ልፈርም አልችልም› ማለታቸው በሰነዱ ላይ በግልጽ የተመለከተ ሲሆን፤ ሰነዱ ተገኘ የተባለበት ቦታ ደግሞ የጉዳዩን አስገራሚነት ያንረዋል- ማቀዝቀዣ (Fridge)! (በነገራችን ላይ ፖሊስ የወንጀል ‹ማስረጃ› ከውጪ ይዞ ቤት ውስጥ በመጣል ‘Eureka’ ‹ማስረጃ› አገኘሁ የሚልበት ልማድ አዲስ አይደለም፤ በኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) ጉዳይ የተከሰሱ ብዙ ሰዎች የዚህ ዓይነት ‹ፖሊስ አመጣሽ› ማስረጃዎች ሰለባ መሆናቸውን እያነበብን/እየሰማን ነው የጎለመስነው፡፡ ፖሊስን ወደቤታቸው ፈትሸው ከማስገባት ጀምሮ የተለያዩ ፖሊስን የመጠበቅ አስቂኝ ተግባራትን በቤት ብርበራ ወቅት እንደሚያከናውኑ ስንለውም ኖረናል፡፡ አስቢው እስኪ ውዴ፤ ሕዝብ ፖሊስን ሲጠብቀው የሚኖርበት ሀገር!)
ለማንኛውም ይህ ‹ Fridge ማስረጃ› ‹አገኘሁ› የሚለው የፖሊስ ተግባር ነው… ‘The Fridgegate Scandal’ እንድል ያደረገኝ፡፡ እስርም፣ ክስም፣ ‹ማስረጃም›…. ከአሳሪዬ በኩል መምጣቱ ‹ፍርድም› ከአሳሪዬ በኩል ሊመጣ ይችላል የሚል ስጋት ውስጥ ቢከተኝም ተስፋ አልቆርጥም! ወዳጄ ‘The Fridgegate scandalን’ እንደ አንድ የክስ ሒደቱ ማሳያ ማቅረቤ ‘The Fridgegate Burgalrs’ ለፍትሕ ይቀርባሉ ብዬ በማሰብ አይደለም ወይም በባለስልጣኖቻችን መካከል ‘The Renaissance Massacre’ ተከስቶ ስልጣን ይለቃሉ የሚል ቅዠትም የለኝም፤ይልቁንም (በክርክሩ ሒደት የምናየው ቢሆንም) የቀረቡብን የሰነድ ማስረጃዎች አስቂኝነትና ምን እንደሚያስረዱ ካለመታወቃቸው አልፎ እንዲህ የአሳሪዎቻችን የቅሌት ተግባራት ውጤት መሆናቸውን ከ Alexander Hamilton የFederaliot Paper Number 78:
“The Judiciary is ‘beyond comparison the weakest of the three department of power”
ቃል ጋር አንድ ላይ ስመለከተው ‹ማስረጃ› ፈጣሪው› እና ጠንካራው አሳሪያችን ‹ደካማውን› ፍርድ ቤት እንዳይጫነው ብሰጋ ነው፡፡ ቢሆንም ግን ሁሌም ተስፈኛ ነኝ፡፡ ማሬ በሕግ ቋንቋ (በልሳን) ትንሽ አውርተን ወደ ሌላ ጉዳያችን እንሂድ፡፡ ያን ረጅም የምርመራ ሂደት አልፈንና ሕግ-አስፈፃሚው ሂደቱን እንዲያስጠብቁ በሕግ-አውጭው የወጡትን የስነ-ስርዓትና መሰረታዊ የመብት መጠበቂያ (Procedual and substantive) ሕጎችን አንድ በአንድ እየሰባበረ ለሕግ ተርጓሚው አካል ያቀረባቸውን ‹የወንጀል ድርጊት ማሳያ ማስረጃዎችን› በሕግ ትምህርት ቤት ‘The Fruits of Poisonous free’ የተባሉት ሲሆኑ፤ ተስፋዬም ከሶስቱ የመንግሥት አካላት ደካማ የተባው ሕግ ተርጓሚው አካል የቀረበለት ነገር በትክክል ‹ፍሬ› እንዳልሆነ ይገነዘባል የሚል ሲሆን፤ ያ ካልሆነም ‹ፍሬው› ከተመረዘ ዛፉ ለሕግ ተርጓሚው አካል በግድ ካልገመጥ አይለውም አይባልም፤ ዛፉን ለመመረዝ አካል ፍሬውን ለማስገመጥ አይሰንፉምና፡፡ ፍቅር! ለማንኛውም ተስፋ ጥሩ ነው፡፡
መንግስቱ ኃይለማርያም ደሳለኝን (MHD) አየኋችሁ
የኔ እመቤት! እውነት እውነት እልሻለሁ እንደ መታሰር ያለ አስተውሎትን የሚያሳድግ ነገር የለም፡፡ ምክንያቴን ከነማስረጃዬ አቀርባለሁ፡፡ ያኔ በዞን ዘጠኝ እያለሁ (ከመታሰሬ በፊት) ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝን አጠር አድርገን ‘HMD’ በሚል አፅርሆት እንጠራቸው ነበር፡፡ መታሰሬ ግን ዓይኔን አበራልኝና የእስከዛሬው አጠራራችን የፊደል መፋለስ እንዳለበት ለመረዳት ችያለሁ፡፡ እንዴት?
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስለሽብር፣ ስለእስርና ስለመንግስታቸው አቋም በቅርቡ ተጠይቀው የሰጡትን ምላሽ በኢቲቪ ተመለከትኩ፡፡ ‹‹እነዚህ አሸባሪዎች ከአስመራ እስከ ሞቃዲሾ የተዘረጋው የሽብር ሰንሰለት አካላት ናቸው (በነገራችን ላይ በቅርቡ የቀድሞው የጋምቤላ ክልል ፕሬዚዳንት ከደቡብ ሱዳን ጁባ ተይዘው መምጣታቸውን ተከትሎ የሽብር ሰንሰለቱ ከአስመራ-ሞቃዲሾ-ጁባ ተለጥጦ ሶስት ማዕዘን መስራቱን መንግስት እየገለፀ ነው) ጋዜጠኛ ነኝ፣ ብሎገር ነኝ እያሉ የሽብር ዓላማን ማንገብ አይቻልም፡፡ እናንት ጋዜጠኞችም ተጠንቀቁ….›› አይነት ዱላ ቀረሽ ዛቻ ሲያሰሙ ተመልክቼ እንደሰውየው ‹ ኃይለማርያም አሁንስ መንግስቱን መንግስቱን መሰልከኝ ማለቴ አልቀረም፡፡ ለዛም ነው ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ መንግስቱ ኃይለማርያም ደሳለኝን (MHD) የሚለውን ስያሜ አፌ ላይ አልጠፋ ያለው፡፡
እንደዱሮው ‹ይሄ በፍርድ ቤት የተያዘ ጉዳይ ስለሆነ አስተያየት መስጠት አልፈልግም› ማለት ቀረና እንደዳኛ ግራና ቀኝ የተቀመጡትን ጋዜጠኞች እየገላመጡ ቢሯቸው ውስጥ ፍርድ ስጡኝ፡፡ ሌላው ሁሉ ይቅር በሕግ ፊት ነፃ ሆኖ የመገመት ሕገመንግስታዊ መብቴን ያክብሩ አላልኩም፡፡ ባይሆን የቀረበብኝን ‹ማስረጃ› ተመልክተው ፍርድዎችን ይስጡም አልልም፡፡ ግን ግን ‹ለባንዲራ ፕሮጀክታችን› (የሕዳሴው ግድብ) ማሰሪያ ይሆን ዘንድ የሁለት ወር ደመወዜን ለቦንድ መግዣ (ምንም እንኳን ለቦንድ ግዢ ጠቅላላ ክፍያ ሳልጨርስ ከስራ በመሰናበቴ ምክንያት ደመወዜ ቢቋረጥም) መስጠቴን እንደውለታ ቆጥረው በቤተ-መንግስት የዘረጉት ‹የፍርድ ችሎት› ላይ ምህረት ቢያደርጉልኝ ምን አለ? ‹ወርቅ ላበደረ ጠጠር፣ እህል ላበደረ አፈር› ይሰጡታልን?
ውቤ! ለማንኛውም በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተበየነብንን የሽብርተኝነት ካባ በፍርድ ቤት እንደማይፀናብን ተስፋ አደርጋለሁ፡፡
‹የነሲቡ ችሎት›
አፈ ንጉስ ነሲቡ መስቀሉ ከ1874 ዓ.ም ጀምሮ ወደ 30 ዓመት ለሚሆን ጊዜ በዳኝነት የተለያዩ የኢትዮጵያን ነገስታት ያገለገሉ ሲሆን ፍርዳቸው እጅግ ከባድና ጠንካራ ስለነበር በዘመኑ ‹እባክህ ከነሲቡ ፊት አታቁመኝ› እየተባለ ይለመን እንደነበር መርስኤ ሀዘን ወልደቂርቆስ በዓይን ያዩትን፤ በጆሮ የሰሙትን፤ ከትበው ይነግሩናል፡፡ በተመሳሳይ ጉዳይ በንጉሱ ዘመን አርሲ፣ አሰላ ላይ እጅግ ጨካኝ ደኛ ተሹመው ፍርዳቸው ከባድ ከመሆኑ የተነሳ ‹አቤት አቤት፤ የአሰላው ፍርድ ቤት› እስከመባል ደርሶ እንደነበር አሁንም ማስረጃችን ታሪክ ነው፡፡
ውዴ! ይሔን የምፅፍልሽ የእኛው ዘመንን ‹የነሲቡ ችሎት› አስመለክቶ ትንሽ ነገር ብዬሽ ደብዳቤዬን ልቋጭልሽ በማሰብ ነው፡፡ አዋጅ ቁጥር 652/2001 (የፀረ-ሽብር አዋጅ) ከወጣበት ጊዜ ጀምሮ በሽብር ጉዳዮች ላይ ስልጣን (Juridiction) ያለው የፌዴራል ከፍተኛው ፍርድ ቤት እንደሆነ በመደንገጉ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 4ተኛ ወንጀል ችሎት የተለያዩ በፀረ-ሽብር ሕጉ የተከሰሱ ግለሰቦችንና ቡድኖችን ጉዳይ እያየ የቆየ ሲሆን፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ‹የፀረ-ሽብር ሕጉ ሰለባዎች› እየተበራከቱ በመሔዳቸው ምክንያት 4ተኛውን ወንጀል ችሎ ለማገዝ በማሰብ 19ኛ ወንጀል ችሎ የሽብር ጉዳዮችን በማዬት ላይ ይገኛል፡፡
በፀረ ሽብር ሕጉ ተከሰውኖ 4ተኛ ወንጀል ችሎት ቀርበው ነፃ የወጡ (Acquit) ሰዎች ብዛት ለጊዜው ለማወቅ ባልችልም እጅግ በጣም ትንሽ እንደሆኑ ግን እርግጠኛ ነኝ፡፡ ይህ የሆነው ችሎቱ ከሌሎች ችሎቶች የተለየ በመሆኑ እንዳልሆነም አስባለሁ፡፡ ይልቁንም ችሎቱ የሚይዛቸው ጉዳዮች በፀረ-ሽብር ሕጉ አግባብ ለማየት ስለሚገደድ ነው፡፡ መቼም የፀረ-ሽብር ሕጉን አሳፋሪነትና ጅምላ ጨራሽነት ላንች እንዳዲስ በመንገር ጊዜሽን አላባክንብሽም፡፡ ለዛም ነው በዚህ ዘመን ‹እባክህ ከ4ተኛ ወንጀል ችሎት ፊት አታቁመኝ› ወይም ‹አቤት አቤት፣ 4ተኛው ወንጀል ችሎት› ብንል ብዙም የማያስገርመው፡፡ የፀረ-ሽብር ሕጉ ከሚሰጠው ሰፊና ጠቅላይ የሆነ የወንጀል ትርጉም አንፃር ከልብ ወለዳዊው ‘Moratorium on the Brain’ አዋጅ ጋር በተነፃፃሪ መቆም የሚችል ከመሆኑም በላይ በሽብር ጉዳይ የተሰየወን ችሎትም እጅግ አሳፋሪ ያደርገዋል፡፡
እንግዲህ የእኛም ጉዳይ የ4ተኛ ወንጀል ችሎት እህት ከሆነው 19ነኛ ወንጀል ችሎት እየታዬ የሚገኝ ሲሆን የፀረ-ሽብር ሕጉም ‹ሰለባ› ፍለጋ በችሎታችን ተገኝቷል፡፡ እንግዲህ አበባዬ ጉዳያችን በፀረ-ሽብር ሕጉ ከመታየቱ ጋር ተያይዞ ስራ አስፈፃሚው አካል ‹ማስረጃ› ፈጥሮ የከሰስን መሆኑ ነው ችሎቱን ‹የነሲቡ ችሎት› ያደረገው፡፡ ለማንኛውም ግን ይሄን ስታነቢ ታዲያ ‹ከአንበሳ መንጋጋ፣ ማን ያወጣል ስጋ› ብለሽ ተስፋ እንደማትቆርጪ አምናለሁ፡፡ እኔና አንች እኮ ተሸንፈን አናውቅም ውዴ፡፡ ሁሌም ማሸነፍ፣ ሁሌም ሌላ ተስፋ ማድረግ፣ ሁሌም ደስተኛ መሆን፣ ሁሌም መዋደድ የሕይወት ግባችን አይደለምን ? ታዲያ ይችን ክስ በድል እንዳንወጣት ማን ያግደናል? ምን አልባት አሳሪያችን፡፡ Hamilton በድጋሚ ጠቅሼልሽ ተስፋችንን አለምልመን እንለያይ፡
‘The Judiciary (…) has no influence over either the sword or the purse (…) It may truly be said to have neither force nor will, but merely judgement’
Amen!

ያንችው ዘላለም
ከብዙ ፍቅር ጋር!

Keine Kommentare:

Kommentar veröffentlichen