የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት መኢአድ የአዲስ አበባ ምክር ቤት አባልና የኮልፌ ቀራኑዮ ክ/ከተማ የፋይናንስ ሃላፊ የነበሩት አቶ ዳኜ አለሙ በ5/12/2006 ዓ.ም ባልታወቀ ምክንያት ሞተው ተገኝተዋል፡፡ እኚህ ጠንካራ አባል መኢአድ በሰላማዊና ህጋዊ ተጋድሎ ካጣቸው ቆራጥ ታጋይ ሰማእታት አንዱ ያደርጋቸዋል፡፡ በተለያየ ጊዜ ሞተው የሚገኙ የመኢአድ አመራርና አባላት ቁጥራቸው እየተበራከተ መጥቷል፡፡ መንግስት የዜጎችን በህይወት የመኖር ዋስትና ማረጋገጥ ቢኖርበትም ተግባራዊ ሊያደርግ ግን አልቻለም፡፡ በዚህ አመት በአዲስ አበባ ከተማ ብቻ አቶ አብይ ፅጌ የቂርቆስ ክፍለ ከተማ ሰብሳቢ አቶ ጥጋቡ ደበላ የአዲስ አበባ ድርጅት ጉዳይ ሃላፊ አቶ ዳኜ አለሙ የኮልፌ ቀራኒዬ ፋይናንስ ሃላፊ ሞተው ተገኝተዋል፡፡ እጅግ የሚያሳዝነው እና በህወአት/ኢህአዲግ ላይ ጥርጣሬያችን የሚያጎላው የሁሉም አባላቶቻችን አሟሟት በግልፅ አለመታወቁ ነው፡፡ አስክሬናቸው ወደ ሚሊኒክ ሆስፒታል የተወሰደ ቢሆንም የአንዱንም ውጤት ለመናገር ሆስፒታሉም ሆነ ፖሊስ ፈቃደኛ አልሆኑም፡፡ መኢአድ በሚያደርገው መራራና እልህ አስጨራሽ ትግል አመራሮቹና አባላቶቹ ከፍተኛ መስዋዕትነት ከፍለዋል፡፡ ትግላችን የኢትዮጵያ ህዝብ የዲሞክራሲያዊ ስርዓት ተጠቃሚ እስከሚሆን ድረስ ይቀጥላል፡፡ በመሆኑም በተለያየ ጊዜ መስዋዐት በሆኑ አባላቶቻችን ላይ ጥቃት መድረሱ ከፍተኛ ሀዘን ቢሰማንም ከትግላችን ለአፍታም ቢሆን አናፈገፍግም፡፡ መኢአድ በህወአት /ኢሕአዲግ ዘርፈ ብዙ የሆኑ በደሎች እየተፈፀመበት ቢገኝም ሁሉንም ተፅእኖ በድል ተወጥቶ የቆመለትን አላማ ከኢትዮጵያ ህዝብ ጋር ዳር እንደሚያደርስ አይጠራጠርም፡፡ መኢአድ በሰላማዊ መንገድና ፍጹም ኢትዮጵያዊ ጨዋነት በተላበሰ መልኩ የሚያደርገውን ትግል ለማደብዘዝና ቢቻለው ለማጥፋት ሌት ተቀን በሚያሴረው ህወአት ኢህአዲግ አምባገነናዊ እርምጃ መቼም ቢሆን አይምበረከክም፡፡ ከአሁን በፊት የተቃጡበትን የተለያዩ ህገ ወጥ እርምጃዎች ተቋቁሞ ቀጥሏል፡፡ አሁንም ቢሆን እየተቃጡበት ባሉ ጥቃቶች ከኢትዮጵያ ህዝብ ጋር በመሆን እንደሚወጣቸው ሙሉ እምነት አለው ፡፡ በአጠቃላይ ህወአት/ኢህአዲግ ምርጫ በደረሰ ቁጥር በተለያዩ መንገድ በሚወስዳቸው እርምጃዎች ህልውናችንን ጨርሶ ለማጥፋት እንደሚሰራ ቢታወቅም በሰላማዊ መንገድ ድል እንደምናደርግ እምነታችን የፀና ነው፡፡ ማንኛውንም የሰላማዊ ትግል የሚፈቅደውን ስልት በመጠቀም በቅርቡ ከመቼውም በበለጠ መንገድ በማከናወን የኢትዮጵያን ህዝብ የዲሞክራሲያዊና የፍትህ ተጠቃሚ ለማድረግ የሚከፈለውን ዋጋ ሁሉ ለመክፈል ተጠናክረን እንገኛለን፡፡ በመጨረሻም ለምናደርገው የትግል ጥሪ ሁሉ መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ዝግጅት እንዲያደርግ ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡ መስዋዐት ለሆኑ የጓዶቻችን ቤተሰቦች እና የትግል አጋሮቻቸው መፅናናትን እንመኛለን፡፡ አንዲት ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር! ነሐሴ 08/12006
Keine Kommentare:
Kommentar veröffentlichen