Netsanet: መኢአድ ሁሉን አቀፍ የሆነ የፖለቲካ ስርዓት እንዲሰፍን የማያቋርጥ ጥረት ያደርጋል፡፡

Freitag, 29. August 2014

መኢአድ ሁሉን አቀፍ የሆነ የፖለቲካ ስርዓት እንዲሰፍን የማያቋርጥ ጥረት ያደርጋል፡፡



የኢትዮጵያ ሕዝብ ሆይ!
ወያኔ/ኢህአዴግ እየተገበረው ያለው ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነን ማጥፋት ነው፡፡ 
ከዘመናት በፊት የሥልጣኔ ችቦ ከተቀጣጠለባቸው ጥቂት አገሮች መካከል አገራችን ኢትዮጵያ አንዷ ናት፡፡ በዚህ ረጅም የሥልጣኔና የታሪክ ዘመን ውስጥ የኢትዮጵያ ሕዝብ በተለያዩ መንገዶችና በማንኛውም ሁኔታ ነፃነቱን ለማስከበር ከውጭ ወራሪ ሐይሎች ጋር ሲታገል መኖሩ የዓለምን ቀልብ ከመሳቡ ባሻገር ለአፍሪካውያንና በዓለም ላይ ላሉ ጥቁር ሕዝቦች የነፃነት አርአያና ተምሳሌት በመሆን የጥቁርን ዘር ክንድ ብርታትና ፅኑነቱን አስመስክሯል፡፡ ይህ አስደናቂና ወደር የማይገኝለት ድል ዘወትር የሚከነክናቸው ባዕዳን የሀገር ውስጥ ባንዳዎች በማዘጋጀትና ግንባር ቀደም ተዋናይ በመሆን ብዙና ከባድ የችግር ቀንበር ሊጭኑብን ሲሞክሩ በዚህ ምክንያት ህዝባችን ዘርፈ ብዙ መሰዋዕትነትን እንዲከፍልም ሆኗል፡፡
Image
የኢትዮጵያ ህዝብ አንድነቱን፣ ታሪኩን፣ ሉዓላዊነቱንና ባህሉን ለሦስት ሺ ዓመታት ጠብቆ የኖረ መሆኑን ዓለም ይመሰክራል፡፡ ሕዝባችን በውስጥ አስተዳድር የደላውና የተመቸው ባይሆንም ቅሉ ብሶቱን አቻችሎ የአገሩን ዳር ድንበርና ሉዓላዊነት ለማስከበር በደሙ እያወጀ መተኪያ የሌላት ሕይወቱንም ሲሰጥ ቆይቷል፡
ወያኔ/ኢህአዴግ መንግሥት ሥልጣን ከያዘበት ቀን ጀምሮ ይህን በደምና በአጥንት የተገነባ ዳር ድንበር እንዲጣስ በማድረግ ለባዕድ ፈቅዶ በመሥጠት ወደብ አልባ ሲያደርገን፣ ዳር ድንበር፣ ሉዓላዊነትና ብሔራዊ ጥቅም እንዲሁም የሕዝቧን ነጻነትና ደህንነት በተገቢው መንገድ ማስጠበቅ ስላልቻለ ድርጊቱን በመቃወም ለመታገል የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት /መኢአድ/ በሕብረ-ብሔራዊና አገር አቀፍ ፓርቲነት በቁርጥ ቀን ልጆች ተመሰረተ፡፡
ኢህአዴግ የደርግን መንግሥት ተክቶ ሥልጣን ከያዘበት ቀን ጀምሮ ይመጣል ተብሎ ሲጠበቅ የነበረውን የአገር አንድነት፣ ሰባአዊ መብት መከበር፣ የዲሞክራሲ መጎልበት ሒደት ቀልብሶ የኢትዮጵያን ሕዝብ ዘርና ቋንቋን መስፈርት ባደረገ የክፍፍል ቀለበት ውስጥ አስገብቶ እርስ በእርሱ እንዲናቆር አድርጎታል፡፡ ሕዝባችንም በተወለደባት አገር ከቦታ ቦታ በመዘዋወር በነጻነት መሥራት እንዳይችል በተደረገበት ወቅት መኢአድ ይህን ለአገርና ለትውልድ የማይበጅ ድርጊት በመቃወም የኢትዮጵያን ሕዝብ አስተባብሮ ሉአላዊነቷ የተጠበቀ፣ እድገቷ የተፋጠነና የህግ የበላይነት የሰፈነባት ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን ለመገንባት የተቆቋመ አንጋፋ ድርጅት ነው፡፡
መኢአድ ይህን ለአገርና ለትውልድ የማይበጅ ሥርዓት ሲታገል ቆይቷል በመታገል ላይም ይገኛል፡፡ መኢአድ ይህን እንቅስቃሴ ያደርግ በነበረበት ወቅትም ትግሉ አልጋ በአልጋ እንዳልነበረና የገዥው ፓርቲ ካድሬዎችና አመራሮች በፓርቲው መሪዎች፣ አባላቶችና ደጋፊዎች ላይ ከፍተኛ የሆነና ግፍ የተሞላበት ድብደባ፣ መሰደድን፣ የመታሰርና የመገደል ዕጣ ሲያደርሱባቸው ቆይተዋል፡፡

ይህ ዘርፈ ብዙ ችግር እየተጋረጠበት ቢሆንም የሕዝብ ጥያቄ የሆነውን የነፃነት፣ የሕግ የበላይነት መስፈን የሰብአዊና የዲሞክራሲያዊ መብቶች መከበር ለሚደረገው ትግል የኢትዮጵያ ሕዝብ ለመምራት በግንባር ቀደምትነት ብቸኛውና ጥንካሬውን ያስመሰከረው የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት /መኢአድ/ በእሳት እንደተፈተነ ወርቅ ነጥሮ በመውጣት ላይ ይገኛል፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ተስፋ የሆነው መኢአድ ከተመሰረተበት ጊዜ ጀምሮ እስካሁን ድረስ ባደረገው ሕዝባዊ ትግል ሥራ ሁሉ የኢትዮጵያንን ብቻ ሳይሆን የዓለምን ሕብረተሰብ ትኩረት በመሳብ ላይ ይገኛል፡፡ መኢአድ ከስሙ መረዳት እንደሚቻለው ሕዝባችን በአንድነት በእኩልነትና በመፈቃቀር እንዲኖር አስተማማኝ ፖሊሲዎችን ነድፎ ተግባራዊ ለማድረግ በመላ አገሪቱ በመንቀሳቀስ ላይ ያለ የፖለቲካ ድርጅት ነው፡፡
መኢአድ ይህንን ታሪካዊና ህዝባዊ ኃላፊነት ለመወጣት ሲል በሚያደርገው ሁሉንተናዊ የሰላማዊ ትግል እንቅስቃሴ የገዥው ፓርቲ ወያኔ/ኢህአዴግ ከቅድመ ምርጫ 97 ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ በፓርቲው አባላት ላይ ከፍተኛ እንቅፋት መፍጠሩ የቀን ከቀን ትዕይንት ሆኖ ቀጥሎአል፡፡ ወያኔ/ኢህአዴግ ይህን ሁሉ ቢፈጽምም ሚስማር ሲመታ ይጠብቃል እንደሚባለው ሁሉ መኢአድ በአባላቱ ላይ የሚደርስበትን ዘርፈ ብዙ ተፅዕኖ፣ ችግርና ሰቆቃ በመቋቋም ለሕዝብና ለሀገር የሚጠቅም ሥራ በመሥራት የኢትዮጵያ ትንሳኤ ለማየት ህዝባዊና ሀገራዊ ኃላፊነቱን በመወጣት ላይ ይገኛል፡፡

የኢትዮጵያ ሕዝብ ሆይ!
የኢትዮጵያ ሕዝብ ከብዙ ሺህ ዓመታት የነፃነት ታሪካችን ባልተናነሰ ሁኔታ በዘር በቋንቋና በጉሳ ሳይለያይ በፍፁም ወንድማማችነት፣ መከባበር፣ መፈቃቀርና መቻቻል አብሮ መኖሩን ታሪክ ይመሰክራል፡፡ ዛሬ የሕዝባችን ችግር ወያኔ/ኢህአዴግ እንደሚያራግበው የክልል፣ የቋንቋ፣ የሀይማኖትና የዘር ልዩነት አይደለም፣ ችግሩ ዳር ድንበራችንን አስጠብቆና አንድነታችንን አጠናክሮ ከድህነት ማጥ ውስጥ በማውጣት ለተሻለ ሕይወት ሊያቃና የሚችል ሕዝብ የመረጠውና የሕዝብን አመኔታ ያገኘ መንግሥት አለማግኘት ነው፡፡
የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት /መኢአድ/ ይህን ክፍተት በመሙላት የኢትዮጵያን ሕዝብ በአንድነት፣ በእኩልነትና ፍትህ በተሞላበት ሁኔታ በመምራት ለነጻነት ለማብቃት በመታገል ላይ ይገኛል፡፡ በመሆኑም መኢአድ በ1997 በቅንጅት ከሌሎች ጋር በተሰለፈበት ወቅት በደረሰበት በደልና ግፍ ተስፋ ሳይቆርጥ ባለው ከፍተኛ ህዝባዊ ተቀባይነት የተነሳ በአሁኑ ሰዓት በመላ ሀገሪቱ በመቶዎች የሚቆጠሩ ቢሮዎችን በመክፈት ሁሉንም ኢትዮጵያዊ በዕኩልነት በማሳተፍ ላይ ነው፡፡ በዚህ የአንድነትና የነጻነት ትግል እንቅስቃሴ የሁሉንም ኢትዮጵያዊ መብት ለማስከበር ከሁሉም ጋር ጥብቅ የሆነ ግንኙነት ፈጥሮ ተስፋ የተጣለበት ሥራ በመስራት ላይ ይገኛል፡፡
በመላ ሀገሪቱ ከሰሜን እስከ ደቡብ ከምስራቅ እስከ ምዕራብ ከርዕስ ከተማ እስከ ቀበሌ ድረስ በመውረድ ህብረተሰቡን በማደራጀትና በማንቃት፣ ህዝቡ ስለሀገሩ አንድነት፣ ነፃነትና የዲሞክራሲ ፅንሰ ሀሳብን ግንዛቤ እንዲያዳብር በማድረግ ከፍተኛ ሚና በመጫወት ላይ ይገኛል፡፡ የፓርቲው እንቅስቃሴ በሀገር ውስጥ ብቻ የተወሰነ ባለመሆኑ በተለያዩ ምክንያቶችና መንገድ ሀገራቸውን ጥለው በባዕድ ሀገር በስደት የሚኖሩትን ኢትዮጵያውያን ጭምር ስለሀገራቸውና ህዝባቸውን ጥለው በባዕድ ሀገር በስደት የሚኖሩትን ኢትዮጵያን ጭምር ስለሀገራቸውና ህዝባቸው ማድረግ ያለባቸውን ሁሉ ሀላፊነት በመፈጸም የነፃነት ትግሉ ተሳታፊዎች ከመሆን አልፈው ባለቤት ጭምር እንደሆኑ አድርጓል በማድረግ ላይም ነው፡፡
መኢአድ የሌሎች ድርጅቶችን ሕጋዊ ህልውና የሚያከብር ሲሆን በተለያዩ አስገዳጅ ምክንያቶች በትጥቅ ትግልና በስደት ላይ የሚገኙ የፖለቲካ ቡድኖችና ሌሎች ወገኖቻችን በህዝባዊ ፖለቲካ የሚሳተፉበት ሀገራዊ የድርድር መድረክ እንዲመቻች ሁሉን አቀፍ የሆነ የፖለቲካ ስርዓት እንዲሰፍን የማያቋርጥ ጥረት ያደርጋል፡፡
አንዲት ኢትዮጵያ ለዘዓለም ትኑር!!!

Keine Kommentare:

Kommentar veröffentlichen