Netsanet: ” ዲሞክራሲ -101″…”መካሪ አያሳጣህ!” ተጳፈ ለሀይሌ ገ/ስላሴ በኤርምያስ ለገሰ

Freitag, 12. Februar 2016

” ዲሞክራሲ -101″…”መካሪ አያሳጣህ!” ተጳፈ ለሀይሌ ገ/ስላሴ በኤርምያስ ለገሰ

” ዲሞክራሲ -101″…”መካሪ አያሳጣህ!”
ተጳፈ ለሀይሌ ገ/ስላሴ
በኤርምያስ ለገሰ12743851_1068360716554981_1821910993132103980_n
ይቺን አጭር ፅሁፍ ለመጫር የገፋፋኝ በዛሬው እለት አትሌት ሐይሌ ለአንድ የውጭ ሚዲያ የሰጠውን አስተያየት በማዳመጤ ምክንያት ነው። አላማዬ ሐይሌ የተናገረውን ሁሉ ለመቃወም አይደለም። ወይም አንዳንድ ” ልወደድ ባይ ደካማ” ሰዎች እንደሚያስቡት አትሌቱ የተጐናፀፈውን ዝና ለማጉደፍ አስቤ አይደለም።
ለእኔም ሆነ ለመላው ኢትዬጲያውያን ሐይሌ በአለም አቀፍ መድረክ ኢትዮጵያዊ አርማችን ነው። አርማን ማቆሸሽ ደግሞ ሐገርን ከመክዳት የሚተናነስ አይደለም። ሀይሌ የማይቻል የሚመስል ነገርን በአለም አቀፍ መድረክ እንደሚቻል ያሳየልን በአርአያነት የምናወድሰው ብሔራዊ ሃብታችን ነው። ሐይሌ ሃይላችን ነው። በስደት አለም እንኳን አንዳንድ ሰዎች ሀገራችንን ጠይቀውን ማወቅ ከተሳናቸው ለማስረዳት ከምናነሳቸው ብርቅዬ ስሞች አንዱ ሐይሌ ገ/ሥላሴ የሚለውን ነው።
ይሔ ማለት ግን አትሌት ሐይሌ ተራራ የሚያካክሉ ስህተቶችን እየሰራ እያየን እና እያዳመጥን ዝምታን እንመርጣለን ማለት አይደለም። አንፃራዊ ትምህርት እና ንቃት የሚጠይቅ ቦታ ላይ እየገባ ” አላዋቂ ሳሚ” ሲሆን በአርምሞ አንመለከተውም ።…አካፋን አካፋ ማለት ይኖርብናል ። አስተውሎ ለተመለከተው የሀይሌ መውረድ የእኛም መውረድ ነው፣…የሀይሌ አልቦነት የእኛም አልቦነት ነው፣… የሀይሌ መካሪ ማጣት ሀገሪቷ አዋቂ ሽማግሌ የላትም ወይ የሚያስብል ነው። እንደዚህ አይነት ግድፈቶች በእንጭጩ ካልተስተካከሉ ደግሞ ውርደቱ ከግለሰብ ተሻግሮ አገራዊ ይሆናል። አይበለውና አትሌቱ አሁን የሰጠውን አስተያየት “የአውሮፓ ህብረት” ስብሰባ ላይ በእንግድነት ተገኝቶ ቢናገረው ምን ይውጠን ነበር?…በማርቲን ሉተር ኪንግ ግዛት የሆነችው አትላንታ ተገኝቶ የደሰኮራት ቢሆን ምን ያህል ያሸማቅቀን ነበር?…
( ወግን ወግ አነሳውና አንድ ነገር ትዝ አለኝ ። ወጉን ያጫወቱኝ በአትላንታ የሚኖሩ ኢትዬጲያውያን ናቸው። በተመሳሳይ መንገድ እንደራሴ የማምነው የኢሳት ባልደረባም በቦታው በአካል ተገኝቶ ስለነበር ይህንኑ አውገቶኛል።
እንዲህ ነበር የሆነው፣
በአትላንታ የሚኖሩ ኢትዬጲያውያን ክብር ለሚገባው ክብር ለመስጠት ሰፊ ፕሮግራም ያዘጋጃሉ። ከእነዚህ ታላቅ ኢትዬጲያውያን መካከል አትሌት ሐይሌ ገ/ሥላሴ ይገኝበታል። ፕሮግራሙ ሲጀመር ከነሙሉ ክብሩ ወደ መድረክ የተጠራው አትሌት ሐይሌ ሙቀቱ በፈጠረለት ወኔ ተነሳስቶ ታሪካዊ ንግግር አደረገ። ንግግሩ በከፍተኛ ጭብጨባ በመታጀቡ ሐይሌ ማቆም አልቻለም። በማሳረጊያውም በረጅሙ ተንፍሶ ” ኢትዬጲያ ብሆን ይሔን አልናገርም ነበር፣ የሚደርስብኝን ስለማውቅ !” በማለት ሀገሪቱ ያለችበትን ሁኔታ ለሕዝቡ በቁጭት አስረዳ ።በድጋሚ ከአዳራሹ የተሰማው ጭብጨባ፣ ፊሽካና ሳቅ ከአትላንታ ተነስቶ፣ አትላንቲክን አቋርጦ የሚኒሊክ ቤተመንግሥት ተሰማ።)
ወደቀደመው ጉዳያችን ስንመለስ አትሌት ሐይሌ በተደጋጋሚ ጊዜ የሚፎርሸው በምን ምክንያት ነው?… የሚናገረውን ነገር በጥልቀት ያውቀዋል ወይ?…ከጀርባ ሌሎች ምክንያቶች ይኖሩት ይሆን?…ወዘተ የሚሉትን ጥያቄዎች ማቅረብ ተገቢ ይሆናል። በእኔ እምነት አምስት መሰረታዊ ምክንያቶች ያሉ ይመስለኛል፣
1• ” የእውነተኛ ዲሞክራሲን” ትርጉም ያለማወቅ
2• የኢትዮጵያ ችግሮች ሁሉ ማጠንጠኛ ” የእውነተኛ ዲሞክራሲ እጦት” መሆኑን ያለመገንዘብ
3• “ፓለቲካ ሳይንስም ጥበብም” መሆኑን ያለማወቅ
4• ለከት የለሽ የሀብት ማሰባሰብ ፍላጐት እና
5• አገዛዙ የደረሰበት ( በድብቅ ሳያውቅ ያስፈፀመው) ከባድ ወንጀል መኖር
ለዚህ አጭር ማስታወሻ በመጀመሪያዎቹ ሶስት ነጥቦች ላይ ትዝብቴን ማስፈር እፈልጋለሁ ።
1• “የእውነተኛ ዲሞክራሲን” ትርጉም ያለማወቅ
እንኳን ለሀይሌ የተለያዩ የፓለቲካል ኢኮኖሚ መጵሀፍቶችን ላገላበጡ ምሁራን የዴሞክራሲ ትርጉም ግልፅ አይደለም። በቃሉ ትርጉም መግባባት ሳይደረስ ” ዲሞክራሲ ያስፈልጋል /አያስፈልግም?…አለ ወይስ የለም? ” በሚለው እሰጣገባ ውስጥ የተገባበት አጋጣሚዎች አሉ። በዛ ላይ “ዲሞክራሲ” የሚለው ቃል እንደ ቃልኪዳን ቀለበት የስም ማስጌጫ ጣቱ ላይ ያላጠለቀ አለመገኘት ትርጓሜውን አደናጋሪ ያደርገዋል። እስቲ ይታያችሁ ባለፋት ሁለት ወራት ከ150 በላይ ኢትዬጲያውያንን በጠራራ ፀሐይ የገደለው ህውሀት የለበሰው ” ኢሕአዴግ” የሚባል ጭምብል በውስጡ “ዲሞክራሲ” የሚል ቃል አለው።
ስለዚህ እንደ አትሌት ሐይሌ ያሉ ሰዎች በትርጉም እና አስፈላጊነት ላይ ተደናግረው ብንመለከት ሊገርመን አይገባም። አብዛኛውን ጊዜ እነ ሐይሌ አዲስ እውቀት የሚጨምሩት በቃላት ትርጉም ላይ ልሂቃን እና ድርጅቶች ተስማምተው ተመሳሳይ ንግግር ሲናገሩ ካዳመጡ ብቻ ነው። ድፍረት ባይሆንብኝ የእነ ሐይሌ የእውቀት መጨበጫ ስልቱ በአይን የሚታይ የተግባር እንቅስቃሴ እንጂ በንባብ እና ምርመራ የሚገኝ አይደለም ።
በንባብ የሚገኝ ቢሆንማ ኖሮ አንጋፋው ፕሮፌሰር መስፍን ” ዴሞክራሲ ወይም ስልጣነ ሕዝብ ምንድነው? ” በሚለው ፅሁፋቸው ያሰፈሩትን በመመልከት ብቻ ግንዛቤ መጨበጥ በተቻለ ነበር። ፕሮፌሰር እንዲህ ይላሉ ፣
” ዴሞክራሲ ማለት የስልጣን ባለቤት ሕዝብ የሆነበት ስርአት ማለት ነው። መነሻው እና መድረሻው ይህ የህዝብ የሥልጣን ባለቤትነት ነው። የሥልጣን ኮርቻው ላይ መውጣትም ሆነ ከዚያ ኮርቻ ላይ መውረድ የሚቻለው በሕዝብ ፍቃድ ብቻ ነው” በማለት ይገልፁታል።
ፕሮፌሰሩ የዲሞክራሲን ትርጉም ብቻ አልሰጡንም። ዲሞክራሲን በራሳቸው መነጵር ሲመለከቱት ምን እንደሚሰማቸው እንደሚከተለው ገልጸዋል ፣
” እኔ ዴሞክራሲን የማየው ምንግዜም ደማቅ ብርሐን ያለበት ለጥ ያለ ሜዳ ላይ እንደተንጣለለና መጨረሻው እንደማይታይ ጥሩ የአስፋልት መንገድ ነው። ቁም ነገሩ እዚያ መንገድ ውስጥ መግባቱ ነው። ብርሃኑ ማንኛውንም ነገር አጋልጦ የሚያሳይ ሲሆን ለጥ ያለው የአስፓልት መንገድ ደግሞ እንደልብ የሚያስጋልብ ነው።”
2• የኢትዬጲያ ችግር ማጠንጠኛ ” የዲሞክራሲ እጦት” መሆኑን ያለመረዳት
ዛሬ አገራችን ኢትዬጲያ የምትገኝበት ሁኔታ ከመቼውም በባሰ አስቸጋሪ ሆኗል። በተለይም ባለፏት ሩብ ምዕተ አመት በኢትየጵያ ህዝብ ላይ ተንሰራፍቶ የተቀመጠው አገዛዝ ሀገራችን የመኖር እና ያለመኖር የህልውና ጥያቄ ውስጥ እንድትገባ አድርጓል። ስርአቱ በዚህ መልኩ ከቀጠለ እና ስር ነቀል ለውጥ ካልመጣ ይቺ በነጥቆ በራሪ ( roving bandits) የተወረወረች ምስኪን ሀገር ወዴት ልታመራ እንደምትችል መገመት አያዳግትም።
ከአንድ ሳምንት በፊት የአርበኞች ግንቦት ሰባት ሊ/መንበር በአሜሪካ ሀገር ሜሪላንድ ግዛት ለህዝብ ንግግር ሲያደርግ ተገኝቼ ነበር። ፕሮፌሰር ብርሃኑ ባደረገው ንግግር ሀገራችን የገባችበት አዘቅት መሰረታዊ ምንጩ ” ዲሞክራሲያዊ ስርአት” ባለመኖሩ እንደሆነ በቀይ ብእር አስምሮበታል። የሕዝብ ከመኖሪያው መፈናቀል፣ የህዝቡ በስርአቱ መማረር፣ የመንግስት በህዝብ ተቀባይነት ማጣት፣ አድሎአዊ የሆነ ስርአት መስፈን፣ የወጣቶች ስደት፣ ረሐብ እና የኢኮኖሚ ድቀት መንስኤው የእውነተኛ ዲሞክራሲ አለመኖሮ መሆኑን አስረድቷል። የሟሸሸና ጭንጋፍ መንግሥት ባለበት ሁኔታ ዲሞክራሲ ሊመጣ እንደማይችል አስገንዝቧል ። በዚህ አባባል ሙሉ በሙሉ እስማማለሁ ።
ርግጥም ፕሮፌሰሩ እንደተገለፀው በኢትየጵያ “እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ስርአት” እስካልመጣ ድረስ የህግ የበላይነት ሊሰፍን አይችልም። ፀረ ዲሞክራሲ ዙፋኑን በጨበጠበት ሁኔታ ሁሉም ዜጐች በኢትዬጲያዊነታቸው ብቻ በህግ ፊት እኩል የማይታዩበት ፣ የዜግነት መብታቸው በተግባር የማይረጋገጥበት ሁኔታ ይፈጠራል። ተፈጥሯልም።
ዛሬ በህዝቦች መካከል በታቀደ መልኩ ጥርጣሬ እና ጥላቻ እንዲሰፍን እየተደረገ ነው። የወጣቱ የወደፊት ተስፋ ጨልሞ ስደትን እንደ አማራጭ ወስዷል። በጥቂት የሞራል ድህነት እና የበታችነት ስሜት በተጠናወታቸው ጠባብ ዘረኞች ሀገራችን ወደ መቀመቅ እየተገፋች ነው። የዜጐች የመናገር፣ የመጳፍ፣ የመደራጀትና ሌሎች መሰረታዊ መብቶች የ50ኛ አመቱን ” Golden Jubuilee” እያከበረ ካለው የኢቲቪ መስኮት ውጭ ማየት አልተቻለም።
3• “ፓለቲካ ሳይንስም ጥበብም” መሆኑን ያለመገንዘብ
የአሜሪካ ፕሬዝዳንት የነበሩት ጆን ኦፍ ኬኔዲ በበርካታ ድንቅ ንግግራቸው ይታወቃሉ። በተለይም ” ፓለቲካ ጥበብ (አርት) እና ሙያ… ያውም የተከበረ ሙያ ነው” በማለት አጠንክረው መግለጳቸው በብዙዎች ይታወሳል። ታዲያ ይህን ባህርዩን የተከበረ ሙያ እና ላቅ ያለ ማህበራዊ ሳይንስ መሆኑን ባለማወቅ አንዳንድ እንደ ሐይሌ ያሉ ታላላቅ ሰዎች ” አዳፋ ቃላትን” ሲናገሩ ይደመጣል።
ክፋቱ ደግሞ የሚናገሩት ከሕዝብ ፊት ስለሆነ ከንፈራቸው ተከፍቶ ሳይዘጋ ጉዳቱ በራሳቸው ላይ ይደርሳል።
እናም አትሌት ሐይሌ ፓለቲካና የዲሞክራሲ ጵንሰ ሐሳብ መረዳት በማለዳ ተነስቶ ” 84 ኪሎ ሜትር ልሩጥ” እንደ ማለት የቂል ድፍረት አይደለም። የአገር እና ህዝብን ሁለንተናዊ ሕይወት የሚመለከት እንደ አገር የመቀጠልና ያለመቀጠል የህልውና ጥያቄ ነው። የእውነተኛ ዲሞክራሲ መስፈን እና ያለመስፈን ጥያቄ በአሁን ሰአት ኢትዮጵያ የገባችበትን ቀውስ የመሻገር አሊያም ላታንሰራራ የመውደቅ ነው!!

Keine Kommentare:

Kommentar veröffentlichen