“የጋማ ከብቶች” – ዲ/ን ዳንኤል ክብረት
ያንተ ታሪክ፣ ባህል፣ ማንነትና ቅርስ ስለሆነ ብቻ ዝም ብለህ አትዋጠው፤ አንጥረው፡
፡ ዕውቀት ወደሚባል፣ ማስረጃ ወደሚባል፣ መረጃ ወደሚባል፣ ክርክር ወደሚባል፣
ተጠየቅ ወደሚባል፣ ኅሊና ወደሚባል እሳት ላይ አውጣው፡፡ ይነጥራል፡፡
በቀደም ድሬዳዋ ላይ ዓሣ ዘነበ ብለን ከአንድ ወዳጄ ጋር ስናወራ፤“ባክህ ይሄ እንኳን የጋማ ከብቶች ወሬ ነው” አለኝ፡፡ እኔም አነጋገሩ ገርሞኝ፤“የጋማ ከብቶች ደግሞ እነማን ናቸው” ስል ጠየቅኩት፡፡
“የማያመነዥኩ ናቸዋ” አለና አሳጠረው፡፡
“እኮ ከድሬዳዋ ዓሣ ጋር ምን ያገናኘዋል?”
እኔ ድሬዳዋ እንኳን ዓሣ፣ የዓሣ ፋብሪካ ቢወርድላት ችግር የለብኝም፡፡ ለምን፣ እንዴት፣ መቼ፣ ማን፣ ፊትና ኋላ፣ ቀኝና ግራ የሚባሉ ነገሮች ፋሽናቸው አለፈ እንዴ? አንድ ሚዲያ፤ ‹ዓሣ ዘነበ› ከማለቱ በፊት በጋዜጠኛውና በሚዲያ ኃላፊዎች ላይ ‹ማመዛዘን› የሚባለው ነገር መዝነብ ነበረበት፡፡ ያንን የዘገበ ዘጋቢ ዓሣ ሊያዘንብ የሚችል ታሪካዊ፣ ሳይንሳዊ፣ ሃይማኖታዊ፣ አየር ንብረታዊ፣ ሌላም ምክንያት መኖር አለመኖሩን ሳያጣራ፣ በየቦታው ተዘዋውሮ ሳያረጋግጥ፣ ከሁሉም በላይ ደግሞ በኅሊናው መዝኖ ከግምት በላይ ሳያልፍ፣ እንዴት ለዘገባ ያበቃዋል፡፡ ይኼ የጋማ ከብትነት ይባላል፡፡
የጋማ ከብት ይበላል ግን አያመነዥክም፡፡ ያገኘውን መዋጥ ብቻ ነው፡፡ እስኪ የቀንድ ከብቶችን ተመልከት፤ቀን የበሉትን ማታ ጋደም ብለው በጽሞና ሲያመነዥኩት ታዳምጣለህ፡፡ ይፈጩታል፣ ይሰልቁታል፣ ያጣጥሙታል፣ ያወጡታል፣ ያወርዱታል፡፡ አንዴ ገባ ብለው እንዲሁ አይተውትም፡፡ ፊውዝ እንኳን የማይስማማው የኤሌክትሪክ ኃይል ሲመጣ አላሳልፍም ብሎ ራሱ ይቃጠላል፡፡ ብሬከር እንኳን በዐቅሙ የማይሆን ኤሌክትሪክ ሲመጣ ይዘጋል፡፡ እንዴት ሰው እንደ ጋማ ከብት የሰጡትን ሁሉ ይውጣል፡፡
አሁን በየስብሰባውና በየሚዲያው ‹የመለስ ራእይ› ሲባል እንሰማለን፡፡ የመለስ ራእይ ምን እንደሆነ አንድ፣ ሁለት፣ ሦስት ብለህ ግለጠው ቢባል ስንቱ ያውቀዋል? የሆነ ቦታ ሲባል ስለሰማ ሳያመነዥክ እርሱም ይለዋል እንጂ፤ እውነት ይሄ ሁሉ ሰው ራእዩን ዐውቆት፣ ከዚያ ገብቶት፣ ከዚያም ተስማምቶበት ነው እያወራ ያለው?
አንዱ፣ እገሌ የተባሉት ባለሥልጣን፣ ሥራ የሚቀጥሩት በዘመድ ነው ሲባል ይሰማል፡፡ ጓደኞቹ ደግሞ ‹የአንተ አገር ሰው’ኮ ናቸው› ይሉታል፡፡ ይሄ ነገር ሲደጋገምበት ‹ለምን አልጠይቃቸውም› ብሎ ቢሯቸው ሄደ፡፡ ምናለ ቢያንስ – የት ሀገር፣ የት ቀበሌ፣ የት መንደር ናቸው የሚለውን እንኳን ቢያጣራ፡፡ ቢሯቸው ገብቶ የሀገራቸው ሰው መሆኑን ይገልጥና ሥራ ይለምናል፡፡ እርሳቸውም በመንደርና በጎጥ የጠበቡ ነበሩና፤ ‹ለመሆኑ ሀገርህ የት ነው?› ይሉታል ‹ከእርስዎ ሀገር› ይላል፡፡ ‹የኔ ሀገር የት ነው?› ሲሉት ‹ከኛ ሀገር› አለ አሉ፡፡
አሁንማ የጋማ ከብቶች ወረሩን’ኮ፡፡ ኤሌክትሮኒክስ ሚዲያው፣ ማኅበራዊ ሚዲያው፣ ሥልጣኑ፣ ኪነ ጥበቡ፣ ቤተ እምነቱ፣ ምሁርነቱ፣ ንግዱ፣ ፓርቲው፣ ምኑ ቅጡ– በጋማ ከብቶች እየተሞላ ነው፡፡ እስኪ ከፈለግህ ‹እገሌ ሞተ› በልና ፌስ ቡክ ላይ ለጥፍ፡፡ ምንም ነገር ሳያጣራ ግማሹ ፕሮፋይል ፒክቸሩን ጥቁር ያደርጋል፣ ሌላው ‹አር. አይ. ፒ› ይላል፣ ሌላው ደግሞ ምናልባት ልቅሶ ተቀምጦ የዕድር ብር በልቶ ይሆናል፡፡ ‹በዓሉ ግርማ ዳጋ እስጢፋኖስ ተገኘ› ሲባል በአንድ ጀልባ ሮጦ ሊያጣራ የሚችለው የባሕር ዳር ነዋሪ፣ አብሮ ‹ሼር› እና ‹ላይክ› ካደረገ ከዚህ በላይ የጋማ ከብትነት ምን አለ?
ወዳጄ፣ማመን ማለት ፈጽሞ አእምሮን መነሣት አይደለም፡፡ አእምሮ የፈጠረልህን ፈጣሪ ከሆነ የምታምነው ማመዛዘንን እምነት አይቀማህም፡፡ የቅዱስ እስጢፋኖስን በዓል አከብራለሁ ብሎ የሄደ ምእመን፤‹ቅዱስ እስጢፋኖስ በድንጋይ ተወገረ› ሲሉት ‹እልልልልልል› ብሎ የሚያቀልጠው ከሆነ፣ ዐጸዱ በጋማ ከብቶች ተሞልቷል ማለት ነው፡፡ እንዲህ ያለው የጋማ ከብትነት ነው ፓስተሮቻችንና አስተማሪዎቻችን ልብሳችሁን አውልቁ፣ ሣር ብሉ፣ መሬት እንዳይነካን አጎንብሱና እንቁምባችሁ ሲሉን ያለማመንዠክ እንድንቀበላቸው ያደረገን፡፡
ኢየሱስ ክርስቶስ እንኳን እናቱ ትምህርት ቤት ባስገባቺው ጊዜ፣መምህሩ የእብራይስጥን ፊደል ሲያስቆጥረው፤ ‹አሌፍ› በል አለው፡፡ ‹አሌፍ› አለ፡፡ ቀጥሎ ደግሞ ‹ቤት› በል አለው፡፡ ዝም አለ፡፡ መምህሩ ተናደደና፤ ‹ለምን ቤት አትልም?› ሲል ተቆጣው፡፡ ሕጻኑ ክርስቶስም፤ ‹መጀመሪያ የአሌፍን ትርጉም ንገረኝና ከዚያ ቀጥዬ ቤት እላለሁ› አለው ይላል ተአምረ ኢየሱስ፡፡ ታዲያ ምነው የእርሱ ተከታዮች መጠየቅንና መመዘንን ፈሩ? ለምንስ የጋማ ከብትነት በዛ?
በደርግ ዘመን፤ ‹ጓድ መንግሥቱ እንዳሉት› እየተባሉ የሚነገሩት ጥቅሶች ሁሉ ብዙዎቹ መንግሥቱ ኃይለማርያም ራሳቸው የማያውቋቸው እንደሆኑ በኋላ ታውቋል፡፡ እንዲያውም በአንድ ስብሰባ ላይ ‹ሰውን ሰው ያደረገው ሥራ ነው› ብለዋል ጓድ መንግሥቱ ብሎ አንዱ ካድሬ ይጠቅሳል፡፡ ያውም ራሳቸው መንግሥቱ ኃይለ ማርያም ባሉበት፡፡ እርሳቸው ራሳቸው ገርሟቸው፤ ‹ኧረ ይሄን ነገር እኔ አልተናገርኩም› ይሉና ከስብሰባው በኋላ ያስጠሩታል፡፡ ‹ይህ ንግግር የኔ መሆኑን ከየት አገኘኸው?› ሲሉት ‹መቼም እንዲህ ያለ ንግግር ከእርስዎ አፍ ካልሆነ በቀር ከአድኃሪያን አፍ አይወጣም ብዬ ነው› አለ አሉ፡፡ ካድሬ ምን አለበት፤ ‹ነው› ከተባለ ነው፣ ‹አይደለም› ከተባለ፣ አይደለም ብሎ ይኖራል፡፡
በወዲህም ሆነ በወዲያ ቆመው ሚዲያውን የተቆጣጠሩት ወገኖቻችን ጥቂት ማመንዠክ ቢችሉ ኖሮ እኛን የአህያ ሆድ አድርገው አይቆጥሩንም ነበር፡፡ የሚበሉት እህል ይለያያል እንጂ ሁለቱም አያመነዥኩም፡፡ ሁለቱም ወዳጆቻቸው የነገሯቸውን ሳያመሰኩ ይውጣሉ፤ ሁለቱም ጠላት ከሚሏቸው የሚመጣውን አይቀበሉም፡፡ እነርሱን እስከ ደገፈና ጠላቶቻቸውን እስከ ተቃወመ ድረስ ሁለቱም ማንጠሪያ የላቸውም፡፡
በተለይ ደግሞ ዘረኝነትና ማይምነት ሲጨመሩበት፣የጋማ ከብትነት የከፋ ይሆናል፡፡ ዘረኞች ከራሳቸው ወገን የሚመጣውን ሁሉ እንዳለ ይውጡታል፡፡ ከዚያ ውጭ ያለው ሁሉ ሊያጠፋቸው፣ ሊቀማቸው፣ ሊያንቋሽሻቸው የሚመጣ አድርገው ስለሚመለከቱት ከወገናቸው ውጭ ማንንም አያምኑም፡፡ በባለሞያ ያልተቃኙ፣ በገለልተኝነት ያልተበየኑ፣ በማስረጃ የማይበጠሩ፣ ስሜትና እውነትን ያልለዩ፣ የታሪክ ድርሳናት በየቦታው ሲታተሙና ‹ለብሔረሰቡ› ሲሠራጩ ሃይ ባይ የላቸውም፡፡ ዘረኞች እውነትን በዘር መነጽር ነው የሚያዩዋት፡፡ ምን ተነገረ? ሳይሆን ማን ተናገረ? ነው ቁም ነገሩ? ቀጥሎ ደግሞ የኛ ወገን ነው ወይስ የነዚያ? ይባላል፡፡ የራስህ ወገን የነገረህን ዝም ብለህ መጋት ነው፡፡ ቢቻል ቢቻል ጀግና ነህ፣ ማራኪ ነህ፣ የሠለጠንክ ነህ፣ የዚህና የዚያ ምንጭ ነህ፣ ድንቅ ባህልና ምርጥ ታሪክ አለህ ይበልህ፡፡ ሳታመነዥክ ትጋተዋለህ፡፡ ይኼ ካልሆነ ደግሞ ተጨቁነህ፣ ተረግጠህ፣ ማንነትህ ተረስቶ፣ ከሰው በታች ሆነህ ነበር፤ እነ እገሌና እነ እገሊት ጠላቶችህ ናቸው ብሎ ሙሾ ያውርድልህ አሁንም ትጋተዋለህ፡፡ ማንጠር የሚባል ነገር የለም፡፡
ዘረኝነት ማንጠር የሚባለውን ሞያ አጥፍቶብናል፡፡ ቅቤን ከአንጉላው የሚለየው ማንጠር ነው፡፡ ሲነጠር ቅቤው ለብቻው፣ አንጉላው ለብቻው ተለይቶ ቁጭ ይላል፡፡ ለአንጉላ ተብሎ ቅቤ አይጣልም፤ ለቅቤም ተብሎ አንጉላ አይበላም፡፡ ይነጠራል እንጂ፡፡ ያንተ ታሪክ፣ ባህል፣ ማንነትና ቅርስ ስለሆነ ብቻ ዝም ብለህ አትዋጠው፤ አንጥረው፡፡ ዕውቀት ወደሚባል፣ ማስረጃ ወደሚባል፣ መረጃ ወደሚባል፣ ክርክር ወደሚባል፣ ተጠየቅ ወደሚባል፣ ኅሊና ወደሚባል፣ እሳት ላይ አውጣው፡፡ ይነጥራል፡፡ አንጉላው ከቅቤው ይለያል፡፡ ካልሆነ ግን በተለይ የማያመነዥኩ ሰዎች ሆድ ውስጥ ከገባ አደጋ ነው፡፡
እንክርዳድ እክርደድ የተንከረደደ
ስንዴ መስሎ ገብቶ ስንቱን አሳበደ፤ የተባለው ለዚህ አይደል፡፡
ማይምነትን በእናቶቻችን ቋንቋ ለመተርጎም ‹የማይለቅም፣ የማያነፍስ፣ የማያበጥር፣ የማይነፋ፤ እንዲሁ የሚያስፈጭና የሚበላ› ማለት ነው፡፡ እናቶቻችን እህሉን ከቆሻሻው ለመለየት የቻሉትን በእጅ ይለቅማሉ፣ ያልተቻለውን በሰፌድ ያነፍሳሉ፣ የተረፈውን በማበጠሪያ ወንፊት ያበጥራሉ፡፡ ተፈጭቶ ከመጣ በኋላ ደግሞ በጥቅጥቅ ወንፊት ይነፉታል፡፡ ይኼ ሁሉ ልፋት ዓይነተኛውን እህል ለማግኘት ነው፡፡ ዓይነተኛውን እውነት ለማግኘትም በመረጃና በማስረጃ፣ በዕውቀትና በብስለት፣ በተጠየቅና በመጠንቀቅ መልቀም፣ ማንፈስ፣ ማበጠርና መንፋት ያስፈልጋል፡፡
ምሁራኑ እንኳን በየዐውደ ጥናቱ፣ ጥናታዊ ጽሑፍ ብለው የሚያቀርቡት ተዘጋጅቶና ተሰናድቶ የመጣውን ‹ዳታ›፣ ለበዓሉ የሚስማማውን ቀለም፣አየሩና ነፋሱ ሲለው የከረመውን እንጂ ዘወር ያለ፣ የተመዘነ፣የነጠረና፣የተመረመረ ነገር አይናገሩም፡፡ በዜና የሰማነውን በጥናታዊ ጽሑፍ ቅርጽ ያቀርቡታል፡፡ ሳያመነዥኩ ያቀርባሉ፤ ሳናመነዥክ እንበላለን፡፡
በድሬዳዋ የተጀመረውን ነገር ድሬዳዋ ላይ በተፈጸመ የጋማ ከብትነት እንዝጋው፡፡ መምህሩ ውጭ ቁጭ ብሎ ተማሪውን ይጠራውና፤ ‹እዚያ ክፍል ሄደህ እኔ መኖሬንና አለመኖሬን አይተህ ንገረኝ› ይለዋል፡፡ ተማሪውም ቀጥ ብሎ ሄዶ በመስኮት ያይና ተመልሶ መጥቶ ‹የሉም› ይለዋል፡፡ ይሄኔ መምህሩ በጥፊ ተማሪውን መታው፡፡ ተማሪው የደረሰበትን ይናገርና አባቱን ይዞት ይመጣል፡፡ አባትዬውም እንደመጡ፤ ‹እንዴት ልጄን ትመታለህ!› ብለው ይፎክራሉ፡፡ መምህሩም፤ ‹ታዲያ ለምን ከክፍል ውስጥ የለም ይለኛል› አላቸው፡፡ አባት መለስ ይሉና ልጃቸውን፤ ‹እንደዚህ ብለሃል› ይሉታል፡፡ ‹አዎ› ይላል ተማሪው፡፡ ‹መምህሩን ከክፍል ውስጥ የሉም አልክ› አባት አጽንተው ጠየቁ፡፡ ‹አዎ ብያለሁ› ይላል ልጅ፡፡ አባትም ተናድደው፤ ‹ታድያ እርሳቸው ከሌሉ ማን እያስተማረህ ነው ተምሬ መጣሁ የምትለው› ብለው ልጃቸውን ጥፊ ደገሙት ይባላል፡፡ እንዲህ ነው የጋማ ከብትነት የመጣልህን መዋጥ፡፡
http://wp.me/p5L3EG-an
Keine Kommentare:
Kommentar veröffentlichen