Netsanet: ማንነት በመሬት ላይ አይዘራም - ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ

Mittwoch, 10. Februar 2016

ማንነት በመሬት ላይ አይዘራም - ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ

ማንነት በመሬት ላይ አይዘራም - ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ

ባለፉት ጥቂት ሳምንታት ማንነት ዋና የመወያያ ርእስ ሆኖ ቈይቷል። የሥነ ልቡና ምሁራን identity crisis የሚሉት ነው እንዳልል ያተኰረው “እኔ ማነኝ” ከሚለው ላይ አይደለም። ያተኮረው “ማንነት ከመሬት ጋር ይያያዛል ወይስ አይያያዝም?” ከሚለው ጥያቄ ላይ ነው። ውይይቱን እንዳዳመጥኩትና እንደሰማሁት፥ እኔም አስተያየቴን እንድሰጥ ተጠይቄ እንደተቸሁት፥ ማንነትን ከመሬት ጋር የሚያያይዙ እምነታቸውን ከሃይማኖት እምነት ደረጃ አድርሰውታል። ስለዚህ እነሱን በማስረጃ ማሳመን ሃይማኖታችሁን ለውጡ እንደማለት ሆኗል። “እምነቱ አገር አጥፊ ነው፤ ተውት” ቢባሉም፥ ማንነታቸው ከያዙት መሬት ጋር ከተቆራኘ፥ ይህ አደገኛ አቋማቸው ለሚያስከትለው ሀገራዊ ችግር አንዳች ሥጋት አይታይባቸውም። ክልል ይዞ ኢትዮጵያዊ መሆን ይቻላል የሚሉም አይጠፉም። መሳሳታቸውን መስማት አይፈልጉም፤ ግን ማንነት የሚዘራበት መሬት የሚያስፈልገው ዳጉሳ አይደለም።

ይህ አቋም በተለየ በኦሮሞ ድርጅቶች ዘንድ በግላጭ የሚታይ ነው። ማንነትን ከመሬት ጋር የማያያዝ ጥያቄ የተነሣው የአዲስ አበባ መስፋፋት ገበሬዎቹን ከመሬታቸው ማፈናቀሉ ነው። (በነገራችን ላይ፥ “አማሮች የኦሮሞዎችን መሬት ነጥቀው ኦሮሞዎችን መሬት-አልባ አድርገዋቸዋል” ሲባል ቆይቶ፥ ድንገት ባለመሬት ሆነው የከተማ መስፋፋት ነጠቃቸው!)

በታሪክም ሆነ በአስተሳሰብ ማንነት ከመሬት ጋር ግንኙነት የሌለው የማኅበረ ሰብ ክሥተት። ማንነትን ከመሬት ጋር ማያያዝን የዲሞክራሲ አስተሳሰብ ነው ይሉናል። ግን እንኳን ዲሞክራሲ ሊሆን ከሰብአ ትካት አስተሳሰብ እንኳን ወደኋላ ርቆ መሄድ ነው። እስቲ የነገድን አጀማመርና እድገት እንመልከት። ነገድ፥ እንደ ነገደ እስራኤል፥ ከቤተሰብ ይጀምራል። እስራኤል የእስራኤላውያን አባቶች ስም ነው። ነገደ እስራኤል የሆኑት የሱ ልጆች ናቸው። በዚያን ጊዜ ቤተሰብ የሚኖረው እያደነና ወፍ-ዘራሽ ፍሬ እየለቀመ ስለነበረ፥ ኑሮው አደንና ፍሬ ወደሚገኝበት ቦታ እየተዘዋወረ እንጂ ለማንነቱ ሲል አንድ ቦታ ኖሮ አልነበረም። ይህ የተፈጥሮ ክሥተት ዛሬም በዱር አራዊትና በወፎች በአንበጣዎች ላይ ይታያል። ማንነታቸው የተመሠረተው አብሮነታቸው ላይ ነው እንጂ በሚያርፉበት መሬት ላይ አይደለም። የሚያርፉበትን መሬትማ ከበሉት በኋላ ወደሌላው ይሄዳሉ። አገር መያዝ የተጀመረው ሕዝብ እየበዛ ስለሄደና አደን ላይ ግጭት ስለተፈጠረ ነው። አንድ ሕዝብ አገሩ ያልሆነውን አገሬ ነው ካለ መሬትና ማንነት ያልተያያዙ መሆናቸውን መመስከሩ ነው።

ኢትዮጵያን እንኳ የምንፈልጋት አባቶቻችን ያወረሱን እናት ሀገራⶭን ስለሆነችና ስላደግንባት እንጂ፥ ማንነታችንን እንድንገልጽባት አይደለም። አንድ ኢትዮጵያዊ ማንነቱን ለመጠበቅ ከፈለገ፥ የሚያስፈልገው ኅብረተሰብ እንጂ፥ ኢትዮጵያ ውስጥ መኖር አይደለም። አሜሪካን አገር በኦሮሞነት እየኖሩ፥ “ለማንነቴ ኦሮማዊ መሬት ያስፈልገኛል” ማለት የአስተሳሰብ መዛባት ወይም ራሱን የቻለ የኦሮሞ አገር ለመፍጠር አቋራጭ መንገድ መያዝ ነው። አንድ ሕዝብ ከትልቁ አካል ተለይቶ ሌላ ሕዝብ ከሆነና፥ የራሱን መሬት ከያዘ በኋላ፥ ተመልሶ የዚያ ሀገር ሕዝብ አካል መሆን የትም ሀገር አልታየም። ወያኔዎች የጎሳ ፖለቲካ ያመጡብን አናሳ ነገድ ስለሆንን ሁል ጊዜ ተገዢዎች ሆነን እንቀራለን ብለው በመፍራት ነው። በነሱ አስተሳሰብ እንኳን ብንሄድ ከሁሉ አስቀድሞ የሚቃወሟቸው ኦሮሞዎች መሆን ነበረባቸው።

አንዳንድ ኦሮሞዎች ይኸንን ጽሑፍ ሲያነቡ፥ “ማንነታችንን መግለጫ መሬት ይሰጠን ማለት ኢትዮጵያዊነታችን መካዳችን አይደለም” ሊሉ ይችላሉ። አወቁትም አላወቁትም ኢትዮጵያዊነታቸውን መካዳቸው ነው። በቅን መንገድ እንኳን ብናየው ሁለት ዜግነት መያዝ ነው። ሁለት ዜግነት የሚያዘው ደግሞ የሁለት ነፃ ሀገሮች ዜጋ ከሆኑ በኋላ ነው። ይኸንን ነው የምትፈልጉት? እንዲያውም “ስለኦሮሞ ገበሬ ርስት መነጠቅ ስንጋደል ዝም ብላችሁ ታዩ ነበር” ሲሉ ተሰምተዋል። የኦሮሞዎች ነገር ባንድ ራስ ሰባት መላስ ሆነብን። ድርጅቶቹ ብዙዎች ናቸው፤ ስለኢትዮጵያ ያለቸው አስተያየትም በዚያው ልክ ብዙ ነው። የቱን እንመን? የቱንስ እንቀበል? ከኦሮሞ ክልል ያባረሯቸውን አማሮች “ኑ ለኛ ጉዳይ ከኛ ጋር ተሰለፉ” ማለት ፌዝ አይሆንም? የኢትዮጵያን ባንዲራ ለማውለብለብ የተጸየፉ ኦሮሞዎች አማሮችን “ከእኛ ጋራ የኦሮሞን ባንዲራ አጅባችሁ አልተሰለፋችሁም” የሚል ወቀሳን የሚቀበል የኦሮሞ ፖለቲከኞች አእምሮ ብቻ ነው። የትኛውን የአማራ የፖለቲካ ድርጅት ነው ደግፈን የሚሉት? አማራው ጎሳ ላይ በተመሠረተ የፖለቲካ ፓርቲ ስለማያምን አልደገፍክም ተብሎ የሚወቀስ እንኳን ሰባት አንድም ድርጅ የለውም። ወቀሳው ሞረሽ ወገኔን ከሆነ፥ ይህ ድርጅት የተቋቋመው ኦሮሞዎች ሀብታቸውን ዘርፈው፥ ቤታቸውን አቃጥለው ያፈናቀሏቸውን አማሮች ለመርዳት የተቋቋመ የበጎ አድራጎች ድርጅት ነው። ወቀሳው ግለሰብ አማሮችን ከሆነ፥ ይኸው ኢትዮጵያዊ ሀብቱ መዘረፍ የለበትም እያልን እየጮህን ነው።

ሀገር የሕዝቧ እናት ነች። ሀገር በእናት የምትመሰለው፥ ልጆቿ ሁሉ እኩል እናቴ እንዲሏትና እኩል አንድታሳድጋቸው ነው። የእናት ሆድ ዝንጉርጉር ነው እንደሚባለው፥ ኢትዮጵያ የተለያዩ ልጆች ወልዳለች። በዝንጉርጉር ልጆቿ ማህል አለመግባባት አይፈጠርም አይባልም፤ ይፈጠራል። ግን ካልጠፋ መፍትሔ (ምርቷን እኩል እንካፈል ማለት እያለ) ምን ዓይነት አለመግባባት ነው እናታችንን እንቀራመት የሚል መፍትሔ የሚያስፈልገው? መሬቱን መካለል እናት ሀገርን መቀራመት መሆኑን የማያምኑ ሊኖሩ ይችላሉ። እርግጥ ካሉ ሞኞች ናቸው፤ ወይም “ክልሉ አገራችሁ አይደለም” እየተባሉ የሚገደሉትን፥ የሚባረሩትን፥ የሚዘረፉትን የሺዎች ሥቃይ እንዳይሰሙ ጆሯቸውን የዘጉ፥ እንዳያዩ ዓይናቸውን የጨፈኑ ይሆናሉ።

ግን በምን ምክንያት ነው ይኸ መፍትሔ በተለየ በትግሬና በኦሮሞ ፖለቲከኞች ዘንድ የተወደደው፤ በሌሎች ዘንድ የተጠላው?

የክልል ፖለቲካ አራማጆች የሚሰጡት ምክንያት “አማሮች ጨቁነውናል፤ ርስታችንን ወስደውብናል፤ ባህላቸውን ጭነውብናል። ይኸንን ሁሉ ተጽዕኖ ከጫንቃችን ልናራግፍ የምንችለው የራሳችንን አገር ስንገዛ ነው” የሚል ነው። ይህን አስተሳሰብ ቢመረምሩት ልክ ለማፍረስ እንዲመች ሆኖ የተቀነባበረ ደካማ አስተሳሰብ ሆኖ ይገኛል። እስቲ አንድ በአንድ እንየው፤ ያልተያዘ የኢትዮጵያ ክልል ከየት ይመጣል? ወይስ ሌሎች ኢትዮጵያውያን የያዙትን አገር የማስለቀቅ ወንጀልን ከመጨረሻው ለማድረስ ክልሉን ከሌላ ጎሳ ለመጽዳት ነው? በዚህ ቦታ ላይ የጥንቶች (አናሳ ጎሳዎች)፥ ከትናንት ወዲያ የመጡ (ኦሮሞዎች)፥ ትናንት የመጡ (አማራዎች፥ ትግሬዎች፥ ወዘተ) ሰፍረውበታል። ኦሮሞዎች ይኸንን ቦታ የኛ የግል ግዛት ይሁን የሚሉት በየትኛው የተለየ መብት ነው? ማንነትን ከመሬት ጋር ካያያዙት፥ እንግዛው በሚሉት ምድር ላይ ከኦሮሞ ወረራ በፊት የነበሩ ኢትዮጵያውያን ማንነት እንዴት ሊሆን ነው? ወይስ እነሱ የጠሉትን የባህል ጭቆና ከሌሎቹ ላይ ለመጣል ነው?

“የማንን ርስት ማን ወሰደው” የሚለውን ጥያቄ ታሪክ አስተካክሎ መልሶታል። በዚያ ምድር ላይ በዓሥራ ስድስተኛው ምእት ዓመት በረይቱማና ቦረን እስኪወሩት ድረስ አንዳች ኦሮሞ ዝር አላለበትም ነበር። አሁን አብዛኛው የኦሮሞዎች ርስት ሆኖ ሳለ፥ ርስታችንን አማራ ቀማን ማለት ጩኸቴን ቀሙኝ ይሆናል።

ያልተራገፈ ጭቆና የትኛው ነው?

ትልቁ ጥያቄ፥ “ክልል ካልያዙ ባህል ማዳበር አይቻልም” የሚለው ነው። ይኸም አሸዋ ላይ የቆመ እፍ ቢሉት የሚገረሰስ ጥያቄ ነው። ባህል ማዳበር ማለት ቋንቋን ማዳበር፥ ሙዚቃን፣ ሃይማኖትን መኮትኮት ነው። ለዚህ ጥረት መሬት ከልሎ መያዝ አያስፈልገውም። የሚያስፈልገው ሙያተኞች ነው። ለምሳሌ፥ አሜሪካ ሆኖ የአማርኛ መጻሕፍት ማሳተምና ለገባያ ማዋል፥ ሙዚቃ በኦዲዮ ማሰራጨት እንደሚቻል ብዙዎች አሳይተዋል። ኢሉባቦር ሆኖ ወለጋ ውስጥ የሚነበብ መጽሐፍ መጻፍ ይቻላል። ሁለቱ አውራጃዎች አንድ ክልል ውስጥ ካልገቡ አይቻልም የሚያስብል ምክንያት የለም። እስፓኛ የተጻፉ መጻሕፍት ዋና ገበያቸው ላቲን አሜሪካ ነች። እንግሊዝ አገር የሚጻፉ መጻሕፍት ገበያቸው አሜሪካ፥ ካናዳ፥ አውስትራሊያ፥ ኒው ዚላንድ ነው።

ከሁሉም የሚገርመው፥ “በክልል ተከፋፍሎ መኖርን አለመቀበል ወያኔዎች የፈጠሩትንና ሥር የሰደደውን የጎሳ ወይም የነገድ ፖለቲካ አለመቀበልና ወደኋላ መሄድ ነው” የሚለው ፈሊጥ ነው። ይኸ የ “የወያኔዎችን ከፋፍለህ ግዛው እቀፉ” ጥሪ ነው። የተላከውም በግላጭ ለአማሮች ነው። ጎሰኝነት ይሰማኝ ቢሆን ኖሮ ጥሪው ያኮራኝ ነበር። ምስጢሩ፥ “የጎሳን ፖለቲካ የሚቃወሙ፥ በዲሞክራሲ የሚያምኑ አማሮች ናቸው” ማለት ነው። አማሮች ጎሰኝነትን የሚቃወሙት፥ ጎሰኝነት የአንድን ሀገር ሕዝብ ስለሚለያይ፥ በጠላትነት ስለሚያፋጥጥ፥ ጎሰኝነትና ዲሞክራሲ የማይታረቁ ሥርዓቶች ስለሆኑ ነው። ንጉሣዊውን ሥርዓት ለመጣል የታገሉት የአማራ ልጆች የዲሞክራሲን ሥርዓት ለማስፈን ነበር። የደርግን ሥርዓት ለመገርሰስ ደማቸውን ያፈሰሱት የአማራ ልጆች የዲሞክራሲን ሥርዓት ለማስፈን ነበር። የአማራ ልጆች አሁንም የሚታገሉት የጥንቱን ዓላማቸውን አንግበው ነው። የአማራ ልጆች ኢትዮጵያ ነፃ ሳትወጣ፥ በሀገራቸው የዲሞክራሲ ሥርዓት ሳይሰፍን እንቅልፍ አይወስዳቸውም። ዲሞክራሲ የነፃና የሠለጠነ ሕዝብ አስተሳሰብ ስለ ሆነ፥ ኋላ ቀር በሆነው የጎሳ አስተሳሰብ አእምሯችሁ የታሰረባችሁ ኢትዮጵያውያን መታሰሪያችሁን በጣጥሳችሁ በዲሞክራሲ ትግል እንድተተባበሯቸው የአማራ ልጆች የአክብሮት ጥሪ ያቀርቡላችኋል።

በብዙ ትግል ኢትዮጵያን እንደገና ያገነኗት ጀግኖች ከሁሉ ነገድ የተውጣጡ የኢትዮጵያ ሕዝብ አባቶችና እናቶች ናቸው። የአንዱን ነገድ አስተዋጽዖ በጎም ሆነ ክፉ ማጋነንና የሌላውን ማቃለል በአብሮ መኖር አለማመን ነው።

http://wp.me/s5L3EG-633

Keine Kommentare:

Kommentar veröffentlichen