Netsanet: ለመሆኑ የቀረች እንጥፍጣፊ ዕንባ አላችሁን? ነውስ አለቀባችሁ – ተለቃለቀ?

Sonntag, 7. Februar 2016

ለመሆኑ የቀረች እንጥፍጣፊ ዕንባ አላችሁን? ነውስ አለቀባችሁ – ተለቃለቀ?

ከዕንባ ብዛት የተነሳ ዓይንም መሲና አንዲሆን ተፈረደበት … እህህ!  … እም!
ከሥርጉተ ሥላሴ 24.11.12
“ሰቆቃው ጴጥሮስ”
„አየ፣ ምነው እመ ብርሃን? ኢትዮጵያን ጨከንሽባት?
ምነው ቀኝሽን እረሳሻት?
እስከ መቼ ድረስ እንዲህ፣  መቀነትሽን ታጠብቂባት?
ልቦናሽን ታዞሪባት?
ፈተናዋን፣ ሰቀቀኗን፣ ጣሯን ይበቃል ሳትያት?
አላንቺ እኮ ማንም የላት …
አውሮፓ እንደሆን ትነጋዋን በፋሽስት ነቀርሳ
ታርሳ፣ ታምሳ፣ በስብሳ
ሂትለራዊ እባጭ ጫንቃዋን፣ እንደ ኮረብታ ተጭኗት፣
ቀና ብላ እውነት እንዳታይ፣ አንገቷን ቁልቅል ጠምዝዟት
ነፍሷን ድጦ ያስበረከካት
ሥልጡን ብኩን መፃጉዕ ናት፤ … „
እሳት ወይ አባባ – ከብላቴ ሎሬት ጸጋዬ ገ/መድህን መግቢያው ላይ  ከ 1ኛው እስከ 12ኛው ስንኝ ገጽ 131)
ዓይን ዕንባ ብቻ አይደለም ደምም … ያምጣል። እንዲህ ታሪክን  – ትውልድን አነጣጥሮና አቅዶ የሚገድል ዘመነ ጉዲት …. የሞቱትን ሳይቀር ከመቃብር አላስቀምጥ ብሎ በበቀል የሚያንገረግብ አማሽ ግበረ – አይሁድ ስታፈራ  ያቺ መከረኛ እናት ሀገር … ። ምን አላችሁ? ዓለም ዓቀፍ የታሪክ ጠበብትስ ከቶ ምን ይሉ ይሆን?!
አልበቃው አለ እኮ! ሀገር ምድሩ … ሜዳው መስኩ። ሁሉንም እንዳሻው ከተከተ – አፈለሰ። ይህም አላሰከነውም – የጤፍ ጠላውን። የበቀል ቀፈቱ አልሞላም። በሰማዕትነት ያለፉትንም ቋሳ የታጠቀው የህሊናው ባሩድ ወደ እነሱ አነጣጥሮ ትናንትን ነሰተ፤ በሰላም የረፉት ሳይቀር አላስተኛም አለ። አትንት ተቀጠቀጠጠ – ተፈጨ። እነሱንም አጽማቸውንም፤ ውዳሴያቸውንም- ድርሳናቸውንም  በፋስ ሊተረትር … ሊበታታትን … ። አዎን! ለጥፋት፤ ለድርመሳ ታጥቆ ተነሳ ወያኔ። ማህከነ! ዬሂትለር ግልባጭ ….
መሰረቱ ነው – የተፈጠረበት። መነሻው ነው – የተጠነሰሰበት። መዳረሻው ነው የተወለደበት …. ወያኔ ሲፈጠር ለማጥፋት ነው። ሲፈጠር ለመደምሰስ ነው። ሲፈጠር ለማፈረስ ነው። ታውቃላችሁን? ወያኔ ጫካ በነበረበት ጊዜ ያው የካቲት ላይ ዘመቻ ነበረው – የሚበላውን ለመስረቅ። ያን ጊዜ በጊዜያዊነት የሚይዛቸው ትናንሽ ከተሞች ወይንም ወረዳዎች ነበሩ። ታዲያላችሁ የደርግ ሰራዊት ሲያስለቅቅው … ት/ቤቶችን አፍርሶ፤ ድልድዮችን ንዶ፤ የውሃ ቧንቧዎችን ነቅሎ። ክሊነኮችን ባንኮች ዘርፎ ይሄዳል።
… ማለት እነዚህ ሁሉ የህዝብ የልማት ተቋማት ሆነው ወያኔ ግን የህዝብ ልማት አጥፊ የጎሳ ድርጅ ፤ የህዝብን ሁለገብ ጥቅም በቀጥታ ተጻራሪ በመሆኑ ካለምንም ርህራሄ ድብዛቸውን አጥፍቶ ይሄድ ነበር። እና አሁን … አሁን እኔ  „ ¡የልማት መንግስት¡“ እዬተባለ የሚደለቀው ቅራቅንቦ የወሬ ማሟያ  ተረት ተረት ከዛ በአካል ተገኝቼ ከአየሁት ተጨባጭ ሃቅ ጋር ሳንፃጽረው  የተሰነጠቀ ብርጭቆ ያደርገዋል።  ልማት እዬተባለ የሚደሰኮረውን ነገር …። ቀድሞ ነገር ወያኔ መገንባት ተፈጥሮው አይደለም። ለብዙኃኑ ኢትዮጵውያን መቆም ዕጣ ፈንተው አይደለም። ፍለጎ የፋቀው ነው። ካለ ተፍጥሮው ደግሞ ሊሆን የሚችል ከቶ አንዳችም ነገር የለም። በስተጀርባው የሚከውነው የፍልሰት ትዕይንት ካልኖረ በስተቀር … ወያኔ ወያኔ ነው። አራት ነጥብ በቀላለአጋኖ።!
ትክክለኛ የወያኔ ተፈጥሮ ማጥፋት ነው። አንድ ቀን የህዝብ ክሊንክ ቢዘጋ ስንት ሰው ይሞታል? ስንት ነፍሰጡር እናቶች ሊያልፉ ይችላሉ? ስነት ህጻነት ለጉዳት ይዳረጋሉ? የህን የሚያስተውልበት ህሊና ወያኔ አልነበረውም። አሁንም። በዚያን ጊዜ ለመሥራት ወይንም እንደ ገና ለመገንባት ደግሞ የሀገራችን አቅምን እሰቡት። … በተገለበጠ እውነት ተሸብሽቦ ነው እኮ ወያኔ ይህን ያህል 21 ዓመት ኧረ ለእኔስ እንደ 60 ዓመት የመከራና የሀዘን ዘመን ነው የምቆጥረው … በሦስት እጥፍ አባዙት … ወያኔ ሥልጣን ላይ የቆዬበትን …
ሲወድቅ እንኳን የሚኖርበን የቤት ሥራ ስታሰሉት … እንዴት እንዴት አድርጌ ልግለጸው  ይሆን? እንዲህ ይሻላል። … “ ከማህጸን ውስጥ ሲጠነሰስ ዓይኑ ያጣውን ዕንቡጥ ሲወለድ ዓይናማ ማደርግ ነው። „ ትውልዱን የሚጠብቀው የነጠረ ኃላፊነት። ከምን ዓይነት የብረት ቁርጥራጭ ብንሠራ ነው ይህን ትውልዳዊ ኃላፊነት በብቃት ተወጥተን ባለ አደረነታችን በተግባር የምናቀልመው … ?! እስከዚህ ድረስ ጥልቅ የፊት ለፊት የድርጊት የቤት ሥራ ዘመን ይጠብቃናል። ወያኔ ሲወድቅ እንኳን ዕዳው … እና የቆዬበት ዘመን በቀላል ስሌት 21 ዓመት ብቻ አይባልምና ነው … በሉ ስምምነት ላይ እንድረስ እሺ … የእኔ ክብሮች።
ሌላው ወያኔ የተፈጠረበትን ሚስጢር እሰቡት። ቁልጭ ያለ ነው። ጸረ ታሪክ ነው። አዎን ደፍረን እንናገረው። እራሱ ኢትዮጵያ የሚለው የወል መጠሪያ ቢለወጥ ደስታውን አይችለውም። ወያኔ  እኮ … ቱርኮች፤ ፖርቹጊዞች፤ ጣለያኖች፤ እንግሊዞች ቀብረውት ዬሄዱትን ፈንጅ ነው ጊዜ እዬጠበቀ እያፈነዳ ያለው …። አፄ ሚኒሊክና ኢትዮጵያን … አቡነ ጴጥሮስና እና ኢትዮጵያን እሰቧቸው። እንኝህ ቀደምት የሁሉም ነገር ዓርማችን፤ ሰንደቃችን፤ ማንነታችን፤ ታሪካችን፤ ትውፊታችን- አድህኗዊ እኛነታችን ናቸው።
አፄ ሚኒሊክ የኢትዮጵያ መሪ ብቻ አልነበሩም። የአፍሪካ መሪ ብቻ አይደሉም። የዓለም ጥቁሮች የነፃነት መሪ ናቸው። ከኒልሰን ማንዴላ በጣም እጅግ የቀደሙ።  የቅኝ ግዛትን ድህረ ፣ ማዕከለ፣ ቅድመ ራዕይ ከመሰረቱ ብትንትኑ የወጣው በአጤ ሚኒሊክ ነው። አጤ ሚኒሊክ አፍሪካን ሲቀረማት ለነበረው ኃይል ሁሉ የቀስተ ዳመና መቅሰፍት ናቸው። የቅኝ ግዛት አከርካሪን ብትንትኑን ያወጡ የጀግና ውጽፈተ ወርቅ ናቸው፤ የቅኝ ግዛት ዘመን እንዲያከትም ቅስሙን እንኩትኩት እንዲል ዓዋጅን በድል ያስጎሰሙ  ዬዓለም ዬጥቁሮች – ጥቁር አብነታዊ ምልክት – ዕንቁ ናቸው።  የ ሆ ን በ ት! የተፈለፈለ ድንቅነት የታተመበት። ኪናዊ የአርበኝነት ውሎ የተከተበበት። ፈዋሽ  – መድህን ዕሴት ናቸው አጤ ሚኒሊክ። ግርማቸው – ክብራቸው – እውነት አሁንም እዬት ይጣራል … በቃና!
„ዋ! … ያቺ ዓድዋ“
„ዋ!
ዓድዋ ሩቅዋ
የዓለት ምሰሶ አድመስ ጥግዋ
ሰማይ ጠቀስ ጭጋግ ዳስዋ
ዓድዋ ..
ባንቺ ብቻ ሕልውና
በትዝታሽ ብፅናና
በመስዋዕት ክንድሽ ዜና
አበው ታደሙ እንደ ገና …
ዋ!
ዓድዋ የዘር ዐፅመ ርስትዋ
የደም ትቢያ መቀነትዋ
በሞት ከባርነተ ሥርየት
በደም ለነፃነት ስለት
አበው የተሰውብሽ ለት፤
ዓድዋ
የኩሩ ትውልድ ቅርስዋ
የ ኢትዮጵያነተት ምስክርዋ
ዓድዋ
***
ዋ … ዓድዋ …
… ዓድዋ የትላንትናዋ
ይኽው ባንቺ ሕልውና
በትዝታሽ ብፅዕና
በመስዋዕት ክንድሽ ዝና
በነፃነት ቅርስሽ ዜና
አበው ተነሡ እንደ ጋና።
… ዋ … ያቺ አድዋ
ዓድዋ ሩቅዋ
የአለት ምሰሶ አድማስ ጥግዋ
ሰማይ ጠቀስ ጭጋግ  ዳስዋ
ዓድዋ … „
( እሳት ወይ አባባ ከብላቴ ሎሬት ጸጋዬ የግጥም መድብል ገጽ 56 ከሥንኝ 1 እስከ 19 በተጨማሪም ገጽ 58 ከ41 እስከ  52)
„ዋ! አድዋ“ ይህ ታሪክ ነው የኢትዮጵያን ተፈሪነትን ያመነጨው። የፈጠረው። ያፈለቀው። የደረሰው። የቃኘው። ይህ ለወያኔ ውጋቱ ነው። መጋኛው ነው። ስለዚህ ጊዜ ጠብቆ ወቅትን አጥንቶ በቀሉን ይፈጽማል። የወያኔ የ5 ዓመት በሉት የ10 ዓመት ዕቅድ ይኽው ነው የበቀል ዋንጫ …
ትንሽ ስለ ዕቅድ ልበል መሰል … መልክ እንዲኖረው አገላለጼ ..
  • የአጭር ጊዜ … ከቀናት እስከ አንድ ዓመት፤
  • የመካከለኛ ጊዜ ሊንክ ነው። ዬአጭር ጊዜውንና የረጅሙን ጊዜ የሚያይዝ፤
  • የረጅም ጊዜ ከ5 ዓመት ጀምሮ የሚኖሩትን ወቅታት … ንድፎችን ያካትታል …
በእነዚህ  የዕቅድ ጊዚያት ሁሉ  ወያኔ ሳይዘናጋ ቋሳም ቦታ አለው – ተመስጥሮ ይታቀዳል። አሁን ወያኔን በጣም የተዋጉት አካባቢዎች በሙሉ በወያኔ የሥልጣን ዘመናት ሁሉ አልተካተቱም። ናሙና …  ትሻላችሁን …. ? 21 ዓመት ሙሉ ጎንደር ውስጥ … ደብረታቦር … ጋይንት … አውራጃዎች እስከ ወረዳዎች ድረስ ተዘለዋል … ማለት ያው የአሽዋውና የስሚንቶ ድርድር ም ጸበለ ጻዲቅ አልደረሳቸውም ….
አንዲት የኢሰአት አድማጭ በቁጭት …. ከሐረር „የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ይባል የነበረው ት/ቤት ዛሬ ስሙ የለም ሲሉ“ አዳመጥኳቸው።  „ህዳሴ ግድበስ? ክፈለ – ከተማስ?“  ስም ጠፍቶ አይደለም  በአምሳላቸው የተሰዬሙት … ጥፋቱ መሰረት አለው። ጥፋቱ ዓላማ አለው። ጥፋቱ ታቅዶ ነው የሚከወነው።  ወ/ሮዋ  ከተገለጹት ውስጥ ደግሞ  … „አማራ መሆን ያሰፍራል ያስጠላል“ ብለዋል። አያስደንቅም። ወያኔ ለማጥፋትም የተፈጠረበት መሰረታዊ ዓላማ መቀመሚያው ይኽው ነው።
እንደ ወያኔ ውስጠ ተፍጥሮ ዕይታ … ዬኢትዮጵያ ታሪክ መሰረት አማራ ነው ብሎ ስለሚያምን – በቀዳሚ ጠላትነት ፈርጆታል። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሃይማኖትም የአማራ ብቻ ነው ብሎ ስለሚያምን ለወያኔ በቀል ባለ ድርሻ ነው። አማርኛ ቋንቋ የአማራ ብቻ ነው ብሎ ስለሚያምን በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ዓይናማው የኢትዮጵውያን ወላዊ ድርሻውን የተወጣ ድንቅ ባለውለታ ጀግናም ባለ ቤለ ኃይሉ ታግሎታል፤
ወያኔ ያደገ ታሪክ በጅራፍ መገረፉ፤ በመዶሻ ዓናቱን መቀጥቀጡ፤ በሳንጃ ደረቱን መሰንጠቁን፤ በመጋዝ አንገቱን መቅላቱን፤ በሳንጃ ሽንጡን መከትከቱ፤ ከተፈጠረበት ጊዜ ጀምሮ የሰራው የቤት ሥራው ነው። ከዚህ ጋር የተያያዙ የተሳሰሩ ሚስጢራዊ ነገሮች ደግሞ አሉ። የአማርኛ የሥነ  ጹሑፍ እድገት ደረጃ … ቅጥል ያደረገው፤ ያንገበገበው … አፍሪካዊው የቅኔው ልዑል ለዓለም አቀፉ ዬሎሬትነት ማዕረግነት የበቃው በአማርኛ ቅኔዊ ግጥሙ ነው። ይህም የቆሽታቸው ማላታይን ነው ለወያኔ። እኛ ብቻ አይደለም ጋሼ ጸጋዬን የምናከብረው … ሶኔትን – እንግሊዞች፤ ሌሪክን – ጀርመኖች፤ ሃይኩን – ጃፓኖች ሲፈጥሩ የኛው ሃብት ብላቴ ሎሬት ጸጋዬ ገ/መድህን ደግሞ 8ዬሽን ፈጠረ … ይህ አዲስ ዓለም ዓቅፍ ግኝት በመሆኑ ሰፊ ተቀባይነትና ተደማጭነትን በሥነ – ጹሑፉ ዓለም አስገኘ። እኛ ብቻ አይደለም ጋሼ ጸጋዬን  የምንወደው የምናከብረው፤ በእውነትም የምንሳሳለትም። …… ጀርመኖች፤ እንዲሁም ቀስተኞች ሲዊዞች ሳይቀሩ አፍሪካዊው ባለ ቅኔ ነው የሚሉት።
„ጨዋታን ጫዋታ ያነሰዋል“ ይላሉ ጎንደሬዎችና… እዚህ ላይ አንዲት ደስ የምትል መረጃ ላቀርብላችሁ ወያኔዎችም ይቀጠሉ … እዚህ እኔ ከምኖርበት ሀገር በ2012 ዓለም ዓቀፍ የፊደላት ቀን ይከበር ነበር። ከፍላዬሩ ላይ ፊደላችን ነበር። ስለ ፊደላችን ልዩ ታሪካዊ ተፈጥሮም መግለጫ ነበር። ይህም ብቻ አይደለም ከ18 ሀገር ቋንቋዎች ጋር አማርኛ ቋንቋ በድምጽ ሳይቀር ቦክስ ተሰጥቶት ለአንድ ወር የዘለቀ ኤግዚቢሽን ነበር። ከፈለጋችሁ ፍላዬሩን እልክላችኋለሁ። … ደስ አይልም? … እንዲያው ነጮቹ „አማርኛ ቋንቋን ግጥም ማደመጥ የምሽት ማህሌት እንደ ማደመጥ ነው። መንፈስን በልዩ ሁኔታ የሚገዛ ልዩ ቃናዊ መንፈስ አለው ይላሉ!“ እና ወያኔ እንዳሰበው ሁለመናዋን ማጥፋት፤ መሰረ ታሪኳን የሚናገሩ ቅርሶቿን ለማፍለስ ሆነ ለማክሰል  የፈለገወን ያህል ቢፍጨረጨርም አይችልም … ያበራል ገና ታሪኳ … ወያኔም ግን ይከስማል … እስነ ጉቱ … ድሪቶው … ከሥሩ …
መቼም እኔ በጣም ስጋት አለብኝ። 21 ዓመት አዲስ ትውልድ በቅሏልና። በትውልዱ ላይ እቦታው ተገኝቶ ለመሥራት ብዙ ነገሮች ስለሚያግዱ ይጨንቀኛል። አብዝቼ የምጨነቅበት ጉዳይ ነው። እግዚአብሄር ይመስገን የደራሲ አቶ ምስባህከ ወርቆ „ዴርቶ ጋዳ“ ጭብጥ መሰረት „ ሰቆቃው ጴጥሮስ ነው“ አሁን ደግሞ ቴዲዬ ዕፁብ ታሪክ ሠራ። አፄ ሚኒሊከን፤ እቴጌ ጣይቱን … ብላቴን በሥነ ጥበብ ተክሊል አጋባቸው። … ይህ ምን ያህል ሚሊዮን እንዳሰለፈ ያላችሁበት ነው። … እኔ እንኳን በሕይወቴ ሙዚቃ አዳምጬ አላውቅም። አሁን አደብ ገዝቼ አዳምጠዋለሁ። … ሶስት ሙሉው ሲዲ አለኝ። … ዝክረ ታሪክ ስለሆነ በዬቦታው ወዳጆቼ ላኩልኝ። ታዲያ ግን ነቀዙ ወያኔ ደግሞ ተርመጠመጠበት። ስለዚህ በብዙኃኑ ታዳሚ አፍቅሮት፤ አክብሮት ያገኘውን የታሪክ ወርቃማ ልቅ … በትኩሱ በማለት  …. እንሆ ታጥቆ ተነሳ – የአጤ ሚኒሊክም ሆነ  የሰማዕቱ የአቡነ ጴጥሮስም ሐውልት … ለማፍረስ …
የአጤ ሚኒሊክን ሀውልት ወያኔ መጀመሪያ እንደ ገባ  ዓይኑ ያረፈበት ጽኑ ጠላቱ … ነበር። ተንደርድሮ እንደገባ ገንባሌውን ሳይቀይር ያፈጠጠበት።  … የኦሮሞ ብሄረሰብ ወገኖቻችንም ከጥፋት ዓላማው ጋር ለማሰለፍ ብዙ የህሊና ሥራ ሰርቶበታል …።  እኔ እንጃ ሄሮድስም በዛች ግድም ዝር ሳይሉ እንደሆነ ነው አፈር የቀመሰቱ የሚመስለኝ … አንጡራ ጠላታቸው … ናቸውና ሁለቱም …።
ያው አባ ጳውሎስም ቢሆኑ … ሰማዕቱን ቅዱስ ጴጥሮስ ሲያዩ  በሸታቸው ይቀሰቀሳል …። የማህል ልባቸው ረመጥ ነበርና አይቅርብኝ እኔም ብለው ድቡሽታቸውን ከምረው አልፈዋል። ያው …  አንድ ቀን ዋጋውን ያገኛል። ወያኔንና የጥፋት ተልዕኮውን ምንም የዴሞክራሲ ቀመር ሳይታከክ ህዝብ ቀን የሰጠው ዕለት ብትንትኑን ያወጣዋል … ። ውሳኔ ህዝብንም አይጠብቅም። በዚያ ዕለት ህግ ጥሰት ነው።  … ወዮ! በሰላም ጊዜ እንዲህ እንዳሻህ ብሎ ትክሻውን ለማናቸውም ዓይነት የበቀል ክምር የደለደለ ትእግስት … የቆረጠ ዕለት።  ነገና እነሱን ያዬቸው ሰው …
እኔ እምሳበው ሆድ አደሩ ሁሉ ቁጭ ብሎ እራሱን ገዝቶ የሚመረምርበት ወቅት በራሱ ጊዜ- ጊዜ እዬሰጠው ነውና ከወያኔ ጋር መማዳሞዱን አቁሞ ከሚሊዮን ጋር ቢሰለፍ መልካም ነው። በስተቀር ግን „በሰፈሩት ቁና … „  …  እራሱ ወያኔ ከነ አካሉ ይፈርሳል። እንደ ቀደመው ጊዜ በሰው ሰውኛ አንሰበው … መንፈሳችነን  ከእዮር ጋር … ይሁን እሺ የእኔ ውዶች …  ባለቤቱ በትጋት አለና ለቤቱ ….
ይህ በራሱ መንፈሳችን በሃዲድ እርስ በእርሱ እንዲተሳሰር፤ በውል በኪዳን አንዲሰግር፤ ለስምረት በትጋት እንደንገሰግስ ኃይልና ጉልበት፤ ጥንካሬና ብርታት፤ መጽናነትና ፅናትን በስፋት የሚመግብ የህሊና ብቁ ስንቅ ነው። በደል ሲባዘ ይፈሳል። ሲከርም ይበጣሳል።
አንተ መዳህኒዓለም ዝምታህ በዛ! ቅጣቱን ቀጥል! አነባብር! እጅግ የናፈቀንን ንጹሕ አዬር እባክህን ለግሰን። ምን ሲሳንህ ሁሉ በእጅህ አይደለምን?!
እግዚአብሄር ይስጥልኝ።

Keine Kommentare:

Kommentar veröffentlichen