Netsanet: በእነ ጉርሜሳ አያኖ መዝገብ በአንደኛ ክስ ላይ የቀረበ ምስክር ተሰማ

Mittwoch, 28. Dezember 2016

በእነ ጉርሜሳ አያኖ መዝገብ በአንደኛ ክስ ላይ የቀረበ ምስክር ተሰማ

Ethiopia Human Rights Project
#FreeOFCleaders #OromoProtests #Ethiopia
በእነ ጉርሜሳ አያኖ መዝገብ በአንደኛ ክስ ላይ የቀረበ ምስክር ተሰማ
ምስክሮች በተከሳሾች ላይ ሳይሆን በክሱ ላይ ምስክርነት ሰጥተዋል፡፡
በነጉርሜሳ አያኖ ( በቀለ ገርባ) መዝገብ ከአንድ ወር በፊት የአቃቢ ህግ ምስክሮችን ለመስማት ቀጠሮ ተይዞ በነበረ ሲሆን የሁለት ሳምንት ጊዜ ውስጥ ሊመጡ ያልቻሉ የአቃቢ ህግ ምስክሮችን ለመስማት ለታህሳስ 18 መቀጠሩ ይታወሳል፡፡ በጠዋቱ ችሎት ምስክሮቹ በመንገድ ላይ እንደሆኑ እና ምስክሮቹ ከሰአት እንዲሰሙ አቃቢ ህጉ በመጠየቁ የምስክር ማሰማቱ ሂደት ለከሰአት ተዘዋውሮአል፡፡ የጠዋቱ ችሎት ከማለቁ በፊት የተከሳሽ ጠበቃ አቶ ወንድሙ ተከሳሾች ከቤተሰብ የሚቀርብላቸውን ምሳ እንዲበሉ እንዲፈቀድላቸው ጠይቀዋል፡፡ ዳኞችም ተከሳሾች በሚውሉበት ቀን ከቤተሰብ የሚቀርብላቸውን ምሳ እንዲበሉ በተደጋጋሚ ውሳኔ እንዳስተላለፉ አስታውሰው፡ ከማረሚያ ቤቱ ለመጡ ሃላፊዎች ምግብ ማግኘት መብት መሆኑን በመጥቀስ ለተከሳሾች ቤተሰብ የሚያቀርብላቸውን ምሳ በችሎት ውስጥ እንዲመገቡ በሃላፊነት እንዲያስፈፅሙ ነግረዋቸዋል፡፡
በከሰአቱ ችሎት አቃቤህግ ዘጠኝ ምስክሮች እንደቀረቡ ገልፆ በቅድሚያ በአንደኛ ክስ ላይ የሚመሰክሩለትን ሁለት ምስክሮች እንደሚያሰማ ተናግሮ የሚመሰክሩበትን ጭብጥ አስመዝግቧል፡፡
ሁለቱ ምስክሮች በመንግስት የሃላፊነት ቦታ ላይ የሚሰሩ ሲሆን በአቡነ ግንደበረት ወረዳ በኬ ቀላጤ ከተማ እና አጎራባች ወረዳዎች/ከተማዎች በ2008 ዓም ስለተነሳው ረብሻ እና የተከሰቱት ሁኔታዎችን በአጠቃላይ እንደሚያስረዱ እንዲሁም የሁከቱ እና የብጥብጡ ተሳታፊዎች ውስጥ የኦፌኮ አባላት እንዳሉበት የኦፊኮ አባላት ፓርቲያቸውን እንደሽፋን በመጠቀም የኦነግን ተልእኮ ለማስፈፀም እንደሚንቀሳቀሱ የደረሳቸውን መረጃ በተመለከተ ያስረዱልኛል በማለት ጭብጡን አስይዟል፡፡
የተከሳሽ ጠበቆች አቃቤ ህግ ያቀረበው ጭብጥ ላይ ያላቸውን ተቃውሞ አቅርበዋል፡፡ አቃቤ ህግ ያስመዘገበው ጭብጥ ጠቅለል/ሰፋ ያለ በመሆኑ ምስክሮቹ በማን ወይም በስንተኛ ተከሳሽ ላይ የቀረቡ መሆናቸውን እና የትኛውን ድርጊት ሲፈፅሙ የተመለከቱ እንደሆነ ዘርዘር ተደርጎ ጭብጡ እንዲቀርብላቸው ጠይቀዋል-የተከሳሽ ጠበቆች፡፡ ዳኞችም ተመካክረው የተከሳሾችን ሃሳብ ተቀብለው አቃቤ ህግ ጭብጡን ዘርዘር አድርጎ እንዲያቀርብ እንዲሁም ምስክሮች በስንተኛ ተከሳሽ ላይ የሚመሰክሩ መሆናቸውን በጭብጡ እንዲጠቅስ ውሳኔ ሰጥተው የነበረ ቢሆንም አቃቤ ህግ በበኩሉ ምስክሮች በየትኛው ተከሳሽ ላይ እንደሚመሰክሩ የመግለፅ ግዴታ እንደሌለበትና ያቀረበውን ክስ ያስረዱልኛል ብሎ ካመነ ማሰማት እንደሚችል ገልፇ፡ ከላይ የጠቀሰውን ጭብጥ ከ1-13ኛ የተጠቀሱ ተከሳሾች ላይ የቀረበውን 1ኛ ክስ ላይ የተገለፁ ድርጊቶችን የሚያስረዱ ምስክሮች እንደሆኑ ከዚህ በላይ ዘርዘር አድርጎ ማቅረብ እንደማይችል አስረድቷል፡፡ ዳኞችም የአቃቤ ህግ ግዴታ ክሱን ያስረዱልኛል ያላቸውን ምስክሮች ማሰማት እንጂ ጭብጥ ማስያዝ ግዴታ እንደሌለበት፤ ጭብጥ ማስያዝ በፍርድቤቶች በተለምዶ ሲሰራበት የመጣ አሰራር እንጂ ህግ ባለመሆኑ አቃቤህግ አንደኛ ክስን ያስረዱልኛል ያላቸውን ምስክሮች የምስክርነት ቃላቸውን እንዲሰጡ ወስነዋል፡፡
በአንደኛው ክስ ላይ የምስክርነት ቃላቸውን የሰጡት የመጀመሪያው ምስክር ኢንስፔክተር ደበሎ አበበ ይባላሉ፡፡ በ2008 ዓም የፓሊስ አዛዥ ሆነው ግንደበረት ወረዳ ይሰሩ እንደነበሩ የገለፁት ምስክሩ፤ በአዲስ አበባ ልዩ ዞን ፊንፊኔ ዙሪያ ማስተር ፕላንን እና የጭልሞ ጫካ ተጨፍጭፎ መሸጡን በመቃወም ሰበብ የግንደበረት አጎራባች ወረዳ በሆነችው ደንዲ ወረዳ ጊንጪ ከተማ ህዳር 30 ቀን 2008ዓም ረብሻ እና ሁከት መጀመሩን ተናግረዋል፡፡ በጊንጪ ከተማ የተከሰተው ረብሻም ወደ እንሱ ወረዳ ይመጣል ብለው ሰግተው ስለነበር መረጃ የማሰባሰብ ስራ ይሰሩ እንደነበር ገልፀዋል፡፡ ከታህሳስ 1-4/2008 በግንደበረት ወረዳ በኬ ቀላጤ ከተማ ሁከት እና ብጥብጥ ተነስቶ “ ወያኔ አይገዛንም”፣ “ኦነግ ነው የሚገዛን”፣ “ኦሮሚያን ነፃ እናወጣለን”፤ “ይሄ መንግስት አየገዛንም” የሚሉ መፈክሮች እንዲሁም ዘፈኖች ይሰሙ እንደነበረ ተናግረዋል፡፡ የሁከቱ ተሳታፊዎች ፓሊስን እና መንግስትን ይቃወሙ እንደነበር እንዲሁም እጅና እጅን በማጣመር ምልክት ያሳዩ እንደነበር ገልፀው በነዚህ ቀናት ውስጥ መሳሪያ ይተኮስ እና ቦንብ ይወረወር እንደነበረ፣ ድንጋይ ይወረወር እንደነበረ፣ የወረዳ አስተዳደር ቢሮዎች፣ ፍ/ቤቶች፣ መኖሪያ ቤቶች እና መኪና እንደተቃጠሉ ፣ንብረቶች እንደተዘረፉ፣ 3ት ፓሊሶች እና 3 ሲቪሎች እንደተገደሉ አስረድተዋል፡፡
በረብሻው ከተሳተፉት ውስጥ የተወሰኑት በፍተሻ ወቅት የኦብኮ መታወቂያ በኪሳቸው እንደተገኘ እንዳሉ የገለፁ ሲሆን አብዛኛዎቹ በምርጫ 2007 ወቅት የተቃዋሚ ፓርቲን ሲደግፉ የነበሩ መሆናቸውን እንደሚያስታውሱ እንዲሁም አንዳንድ ተቃዋሚዎች እና ፀረሰላም ሃይሎች እየተደራጁ ወጣቱን እና ህብረተሰቡን እንደሚያነሳሱ ከፀጥታ ሃይሎች መረጃ እንደሚደርሳቸው እንደነበር ተናግረዋል፡፡ ምን አይነት መረጃ እና መረጃውን ከማን እደሚያገኙት በተከሳሽ ጠበቆች ለቀረበላቸው ጥያቄ ሳይመልሱ ቀርተዋል፡፡ የኦብኮ መታወቂያ ከተያዘባቸው ውስጥ የሚዯስታውሱት ስም ካለ ተብለው ሲጠየቁ የሚያስታውሱት ስም እንደሌለ የተናገሩ ሲሆን የኦብኮ መታወቂያ ቢጫ ከለር እንደሆነ እና በወረዳው የሚገኝ ሃላፊ ቲተር እና የፓርቲው ማህተም እንዳለበት አስረድተዋል፡፡
ምስክሩ በመዝገቡ ተካተው በችሎት ከነበሩት 22 ተከሳሾች በግንደበረት ተከስቶ ነበር ባሉት ሁከት እና ብጥብጥ ሲሳተፉ አይተዋቸው ከሆነ ተብለው በተደጋጋሚ ሲጠየቁ ተከሳሾቹን ማናቸውንም እንደማያቋቸው የገለፁ ሲሆን በወቅቱ በረብሻው የተሳተፉ እና ንብረት ያወደሙትን ግለሰቦችን ጉዳይ ይመረምሩ ስለነበር፡ ጉዳዩ ተጣርቶም እዛው በወረዳቸው ፋይል የተከፈተባቸው በመሆኑ ቢያዩአቸው በቀላሉ መለየት ይችሉ እንደነበር ተናግረዋል፡፡
የመጀመሪያው መስካሪ የምስክርነት ቃላቸውን ሰጥተው ሲጨርሱ ሁለተኛውን ለመስማት ጊዜ ባለመኖሩ ምክንያት ነገ ጠዋት እንዲመሰክሩ ቀጠሮ ተይዟል፡፡
የትላንትናው የታህሳስ 18/2009 ችሎት መቅረፀ ድምፁ በመበላሸቱ ምክንያት እስከዛሬ 4ኛ ችሎት ይሰይምበት ከነበረው በተለምዶ አዳራሽ ከሚባለው እና ብዙ ታዳሚ ከሚይዘው ችሎት ተነስቶ ጠባብ ክፍል እና ጥቂት ታዳሚዎችን መያዝ የሚችል ችሎት ውስጥ ተሰይሟል፡፡ በርከት ያሉ የተከሳሽ ቤተሰቦች እና ችሎቱን ለመታደም መጥተው የነበሩም ቦታ ባለመብቃቱ ምክንያት ችሎት ሳይታደሙ ቀርተዋል፡፡ ችሎቱ ከማለቁ በፊትም የኦፊኮ ም/ፕሬዝዳንት የሆኑት አቶ በቀለ ገርባ በችሎቱ መለወጥ ላይ ያላቸውን አቤቱታ አቅርበው ነበር፡፡ መቅረፀ ድምፁ ተበላሽቶ ነው የሚለውን ምክንያት እንደ ሰበብ እንጂ ትክክለኛ ምክንያት ነው ብሎ እንደማያምኑ ገልፀው፣ በቀጣይ ቀናት 4ኛ ችሎት ይሰየምበት በነበረው ችሎት ተሰይሞ ችሎቱን መከታተል የሚፈልጉት ታዳሚዎች ሁሉ መስተናገድ እንዲችሉ አቶ በቀለ ገርባ አቤቱታቸውን ለችሎት አሰምተዋል፡፡
ዳኞችም በፊት ይሰየሙበት የነበረው ችሎት መቅረፀ ድምፅ ስለተበላሸ እንጂ ሌላ ምንም ምክንያት እንደሌላቸው በነገው እለት ተስተካክሎ ቀድሞ ይሰየሙበት ወደነበረው ችሎት እንደሚመለሱ አስረድተዋል፡፡
በአንደኛ ክስ ላይ እንዲመሰክሩ የቀረቡ ቀሪ ምስክርን እና ሌሎች የቀረቡ ምስክሮችን ለመስማት ለታህሳስ 19/4/2008 ተቀጥሯል፡፡

Keine Kommentare:

Kommentar veröffentlichen