ምጧ የተራዘመባት- ኢትዮጵያ! (ጋዜጠኛ ኤልያስ ገብሩ)
ምጧ የተራዘመባት- ኢትዮጵያ! (ጋዜጠኛ ኤልያስ ገብሩ)
ሀገረ ኢትዮጵያ፡- ከአገዛዝ፣ አገዛዝ ስትሻገር በጭቆና በትር ተቀጥቅጣ፤ ስትማቅቅ በርካታ ዓመታትን አስቆጥራለች፡፡ የህዝቦቿ መከራም ቅርፁን እየቀያየረ፤ ሲያሻውም እየተመላለሰ ትናንትን አቋርጦ ዛሬ ላይ ደርሷል፡፡ ለጭቆና በትሩ ተግባር ወለድ መፍትሔዎች ካልተበጀላቸው መከራው ነገም ይቀጥላል አገዛዙ አለና!
ሀገር በጉልበት ሲገዛ ፣ ወረቀት ላይ በደማቁ አምሮ የተጻፈ ሕግ በመርህ መተግበር ሲሳነው፤ ህዝብና ገዢ ኃይል የአይጥና የድመት ኑሮን ለመኖር ሲገደዱ፣ የነቃ፣ የተማረ በሚባለው የህብረተሰብ ክፍል ዘንድ የሀገርን ሳይሆን የግል ጥቅምን ማስቀደም እንደ አዋቂነት ሲቆጠር፣ ሲተገበር፣ ለቁስ መንሰፍሰፍና “ለእኔ ብቻ!” የሚል የስግብግበነት መንፈስ አይን አውጥቶ በገሃድ ሲታይ፤ የጤናማ ይሉኝታ ባህል ተሸርሽሮ ገደል ሲገባ፣ ሀገር በቀል ባህላዊ እሴቶችን ይዞ መኖር ኃላ ቀርነት ሲያስብለን፣ ፖለቲካ በሀሳብ ሙግት ሳይሆን በጥላቻ ፣ በጠልፎ መጣል፣ በጉልበትና በፍረጃ ሲሰራ፣ የእራስን ዜጋ ንቆ ፈረንጅን ማምለክ ዘመናዊነት ሲመስል፣ እውነትን መጋፋጥ ሞኝነት፣ በውሸት /በሀሰት/ ውስጥ መኖርና ማምለጥ እንደ ብልጠት ሲወሰድ፣ አድርባይነት፣ ሆድ አደርነትና ጥቅመኝነት የህብረተሱ ዋነኛ መገለጫ መሆናቸው ሲያመዝን ጉቦ፣ ሌብነትና ዘመናዊ ሙስና እንደክብር መግለጫ ሲቆጠሩ፣ “እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል!” ከሚል የመነጨ ጥልቅ የሥልጣን ጥም ሰፊውን ህዝብ ሲያሰቃይ፣ ባለሥልጣናት በየረገጡበት የውጭ ሀገራት ክብርን ሳይሆን ውርደትን ሲከናነቡ፣ ገዢ ኃይል፡- ሀገርን ወደፊት ማራመድ ሲሳነው ሀገር የቁልቆለት መንገድ ላይ መሆኗን በጥቂቱ ያመላክታል ብዬ አምናለሁ፡፡
ቀደምት ስልጡን ሀገር መሆኗ በታሪክ ተደጋግሞ የሚወሳላት ኢትዮጵያለ፡- በህወሃት/ኢህአዴግ የጉልበት የሥልጣን ዘመንም በርካታና ስፍር ቁጥር የሌላቸው ችግሮችን ፀንሳለች፣ መከራዎችንም አርግዛለች፣ ዛሬም በእነኚህ ችግሮችና መከራዎች እየዳከረች ነው፡፡
የህወሃት አገዛዝ፣ ከደርግ ውድቀት ማግስት በኃላ “ሰላምና መረጋጋት”፣ “ተሃድሶ” የሚሉ ሃሳቦችን ሲያቀነቅን ነበር፡፡ በተራዛሚ ሂደትም “ህዳሴ፣ ትራንስፎርሜሽን“ ሲል ከርሞ አሁን ደግሞ፡- “በጥልቀት መታደስ!” የሚል ወቅታዊ ነጠላ ዜማ በመልቀቅ የሀሰት ነጋሪት ጉሰማውን ተያይዞታል፡፡
ከሩብ ምዕተ ዓመት በላይ በሥልጣን ማማ ላይ ያሳለፈው ይህ አምባገነናዊ አገዛዝ፣ ብዙ ያወራላቸውና በፕሮፖጋንዳ ማሽኖችም ብዙ ያስነገረላቸው ተንኮል – ወለድ ዕቅዶቹ በሙሉ በክሽፈት አዙሪት ውስጥ የሚናውዙ ናቸው፡፡ ይህንን ለመረዳት ነገሮችን በአንክሮ መከታተልና ማጤን ወሳኝነቱ አሻሚ አይሆንም፤ እንደማሳያም ከላይ የጠቀስኳቸው ቃላቶች መካከል ሦስቱን በምሳሌነት ላስቀምጥ፡-
ህወሃት ኢህአዴግ የጉልበት ሥልጣንን “ሀ” ብሎ ሲጀምር በህዝቡ ዘንድ እንዲሰርፅለት የታተረው ቃል “ሰላምና መረጋጋት” የሚል ነበር፡፡ ለአንዲት ሀገር ህልውና፣ ለህዝቦቿ በአንድነት መኖር ሰላምና መረጋጋት ወሳኝ ኹነቶች ናቸው፡፡ በወቅቱም የሚፈለገው እውነተኛ ሠላም መኖርና መረጋጋት መስፈን/አለመሸፈት ሀቅን የመመርመር ህሊና ላላቸው ባለአዕምሮ ዜጎች ልተወውና ወደ ዛሬው እውነታ እንለፍ፡፡
ከ2008ዓ.ም የመጀመሪያ ወራት ጀምሮ “በአዲስ አበባ ዙሪያ ያሉ ልዩ ዞኖች በአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ሥር ይካተቱ” የሚለውን የህወሃት/ኢህአዴግ እኩይ እቅድን በመቃወም በኦሮሚያ ክልል በሚገኙ የተለያዩ አካባቢዎች የተጀመረውን ህዝባዊ እምቢተኝነት ጠንካራና ተግባር ተኮር በመሆኑ የተነሳ አገዛዙን አንገዳግዶት ከባድ ስጋት ላይ ጥሎት እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትዝታችን ነው፣ አንዱም የታሪካችን አካል ነው፡፡
ከተጠቀሰው አመት አጋማሽ በኃላም በአማራ ክልል የወልቃይት ጠገዴ የማንነት ጥያቄን ተከትሎ የተነሳው ህዝባዊ ተቃውሞና ትግል የአገዛዙን ህልውና በብርቱ መፈተኑም ይታወቃል፡፡ በያዝነው ዓመት መስከረም ወር በደብረዘይት/ቢሾፍቱ ከተማ በየዓመቱ የሚከበረው የእሬቻ በዓል ላይ የደረሰው እጅግ አሳዛኝና ዘግናኝ የሞት አደጋ አይረሳም፤ በብዙ መቶዎች የሚቆጠሩ ንፁሃን ወንድምና እህቶቻችንን አጥተናል!
ይህ ዘግናኝ ኹኔታ በተለይ በኦሮሚያ ክልል ዳግም ህዝባዊ ቁጣን ቀስቅሶ በርካታ ፋብሪካዎች፣ ተሽከርካሪዎች፣ ንብረቶች…… በእሳት ቃጠሎ መውደም ጀመሩ፡፡ ተቃውሞ አድራጊዎችና የአገዛዙ የፀጥታ ኃይሎች ፊት ለፊት ሲላተሙ የበርካቶች ህይወት አለፏል፡፡ ወዲያውም የሀገሪቱ ሰላምና ደኅንነት ከባድ አደጋ ላይ መውደቁን ገዢው ኃይል አመነና ይህ አሁንም ድረስ ያለንበት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለስድስት ወራት ታወጀ፡፡ ከእዚህ በግልጽ መረዳት እንደሚቻለው ህወሃት/ኢህአዴግ ሥልጣን ከያዘ ጀምሮ አልፎ አልፎ አንጻራዊና ወቅታዊ ሰላምና መረጋጋትን በሀገሪቷ ከመፍጠር ባለፈ እውነተኛና ዘላቂነት ያለው ሰላምና ደኅንነትን እውን ማድረግ አለመቻሉን ነው፡፡ ከ25 ዓመታት በኃላም ሰላምና መረጋጋት በሀገሪቷ እና በዜጎቿ ዘንድ ሊረጋገጥ አልቻለም፡፡ ለእዚህ ደግሞ ዋናው ተጠያቂ “ሀገሪቷን እያስተዳደርኩ ነው” የሚለው ህወሃት/ኢህአዴግ ነው፡፡ የሀገርና የህዝብን ሰላምና ደኅንነት ማስጠበቅ አለመቻሉ የታላቅ ክሽፈቱ አንዱ ማሳያ ነው፡፡
በሌላ ረገድ ከኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ማግስት ጀምሮ ባሉ ጥቂት ዓመታት “ተሃድሶ” የሚለው ቃል በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን በአሁኑ EBC በስፋት ይቀነቀን ነበር፡፡ የተሃድሶን ቃል ስንገልጠው “መታደስ” የሚል ፍቺን ይሰጠናል፡፡ መታደስ አንደ አዲስ መለወጥ ነው፡፡ በጎ ህሊና ያለው ሰው ተሃድሶን ይሻል፡፡ በመልካም መታደስ ለሰው ልጅ እፈላጊ ነውና ህወሃት/ኢህአዴግ፡- ሰፊው ህዝብና ሀገራችን በመታደስ ጎዳና ላይ ቢገኙ እጅግ ደስታና ሀሴት ነበር፡፡ ሆኖም፡- በ25ዓመታት ውስጥ “ተሃድሶን ውሃ በላት” በአገዛዙ በተግባር እውን ሊሆን አልቻለምና፤ ዛሬም “በጥልቀት” የሚል ተቀጽላ ቃል ተጨምሮባት በድጋሚ አፍአዊ ተግባር ላይ ውላለች፡፡ ‹‹ጥልቅ ተሃድሶ››ን በቃላት ማነብነብና በተግባር በጥልቀት ለየቅል ናቸው፡፡ ጥልቅ የሥልጣን ጥም ያለው ኃይል፣ በጥልቅ ሙስና የበሰበሰ አገዛዝ በጥልቅ ጥላቻ የገዛ ወንድምና እህቶቹን የሚያሰቃይ፣ የሚያስር፣ የሚያሳድድ፣ የሚገድል……. ቡድን በጥልቅ የገዛ ጥላውን ጭምር የሚፈራ ግለሰብ፣ ከቶ እንዴት በጥልቀትሊታደስ ይቻለዋልን???
ህወሃት/ኢህአዴግን ለ25 ዓመታት በአንክሮ ለተከታተለው፤ በጥልቀት ሊታደስ ቀርቶ በጥቂቱም ወደ መልካምነት ሊቀየር አለመቻሉን መረዳት ይቻላል፡፡ የመድብለ ፓርቲ ሥርዓትን አፈራርሶ፣ የግል ሚዲያን አንቆ ገድሎ፣ ነፃና ገለልተኛ የሲቪክ ማኅበራትን አክስሞ፣ ዜጎችን በፍርሃት እስር ቤት ውስጥ ከርችሞ ጠባብነትና ትምክተኝነትን አስፋፍቶ፣ ዘረኝነትን አንግሶ፣ ጥቅመኝነትን ፈልፍሎ………. ወዘተ “በጥልቀት መታደስ” ማለት ቧልት ይሆናል፡፡ “ከድጡ ወደ ማጡ” ነውና ነገሩ፤ መታደስ አለመቻል ሌላኛው የአገዛዙ መገለጫ ነው፡፡
በ2002ዓ.ም የተደረገውን “ሀገር አቀፍ ምርጫ”ን ተከትሎ 99.6% “ድል” ወደ አገዛዙ ሄደ፡፡ ከምርጫው በኃላም በስፋትና በ“ጥልቀት” የምትቀነቀነው ቃል “ትራንስፎርሜሽን” ሆነች፡፡ የአምስት ዓመቱ የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ በሚል እጅግ የተለጠጠውና በአማላይ ቃላቶች የተንቦረቀቀው የዕቅዱን ዝርዝር መለስ ብሎ ማየት ይቻላል፡፡ ዕቅዱና አፈፃፀሙ በአልተገናኝቶ መስመር ሲነጉዱም አይተናል፡፡ እቅዱ 2ኛ ዙር ቢኖረውም ፍሬያማ አልነበረም፡፡ እቅዱ 3ኛ፣4ኛ ዙር ቢኖረው እንኳን ህወሃት/ኢህአዴግና ትራንስፎርሜሽን በተግባር የሚታዩ፣ የሚነካ፣ የሚዳሰስ፣ የሚቆነጠር፣ ህልውና አይኖራቸውም፡፡ ለምን? እውነተኛ ትራንስፎርሜሽን ከቅንነት፣ ከህዝባዊነት፣ ከአርቆ አላሚነት፣ ከድፍረት፣ ከእውቀት፣ ከትጋት፣ ከቁርጠኝነት…….ወዘተ የሚወለድ ሲኾን በአንጻሩ ጠባብነት፣ ትምክህተኝነት፣ ወገንተኘነት፣ ሙሰኝነት፣ ሴሰኝነት፣ የሥልጣን ጥመኝነትና ክፋት ባለበት ቦታ እውን አይሆንም፡፡ ሀገርን “ከአንድ ዝቅ ካለ ደረጃ ወደ ላቀው ሌላኛው ከፍታ አሸጋግራለሁ!” የሚል ኃይል በተቃራኒው የአዘቅት መንገድ ላይ አይገኝም ነበር፡፡ ግን ይህ በሀገራችን ሆነ! በመሆኑም አገዛዙ በብዙ ረገድ ሀገርን ወደ ከፍታ ሳይሆን ወደ አዘቅት ውስጥ ከቶታል፣ እየከተተም ይገኛል፡፡
…….“በ25 ዓመታት ውስጥ መታደስ አልቻልኩምና አሁን ገና በጥልቀት መታደስ አለብኝ!” የሚል ቡድን እንዴት የአንድን ሀገር የትራንስፎርሜሽን እቅድ እውን ሊያደርግስ ይቻለዋል?! ይህም ያልዘሩትን ዘር አዝመራ እንደማጨድ ይቆጠራልና ሌላኛውን የአገዛዙ ክሽፈት ነው፡፡
ከላይ በመግቢያዬ እንገለፅኩት፤ ኢትዮጵያ በዘመነ ህወሃት/ኢህአዴግ በርካታና ስፍር ቁጥር የሌላቸው ችግሮችን ፀንሳለች፤ መከራዎችንም አርግዛለች፤ እነኚህ ችግሮችና መከራዎች፡- ምጧ እንዲረዝም ስቃይዋም እንዲበረታ አደርገዋታል፡፡ ከምጧ እና ከስቃይዋም በሌላም መንገድ ለመገላገል በተፈጥሯዊ መንገድ አምጣ እውነተኛ ሰላምን፣ ነፃነትን፣ ዴሞክራሲን፣ ፍትህን፣ እኩልነትን፣……… መውለድ ይጠበቅባታል፡፡ አልያም የምጥ ማፍጠኛ መርፌ መውጋት ከቀላል እስከ ከፍተኛ የሚደርስ ቀዶ ጥገና ማድረግ የግዷ ሊሆን ነው፡፡ እኒዚህም ካልተሳኩ አሳዛኙን እውነታ መቀበል የዜጎቿ እጣ ፈንታ ይሆናል፡፡ ውስብስብና አስቸጋሪ ነገሮች ካልተፈጠሩ በቀር አንዲት እርጉዝ ሴት በተፈጥሯዊ መንገድ አምጣ ብትወልድ ጥሩ መሆኑን የዘርፉ የህክምና ባለሙያዎች እንደሚመክሩት ሁሉ፤ ሀገራችንም እውነተኛ ሰላምን፣ ነፃነትን፣ ዴሞክራሲን፣ ፍትህን፣ እኩልነትን፣…… በተፈጥሯዊ መንገድ አምጣ ብትወልድ ለዜጎቿም እፎይታ ነው፡፡ ይህ እውን እንዲሆን ግን ዴሞክራሲያዊ ለውጥን የሚሹ ዜጎች (በሀገር ውስጥና ከሀገር ውጭ ያሉ) ከመቼውም ጊዜ በላይ ስለሀገራቸው ቀጣይ ፖለቲካዊ እጣ ፈንታ በአንክሮና በስክነት ማሰብ፣ ማሰላሰል ይጠብቅባቸዋል፡፡ የሀሳብ ልዩነት የትም ቦታ አይጠፋምና ልዩነትን ችሎ አንድነት ላይ ግን ይበልጥ ጠንክሮ መቆም የውዴታ ግዴታቸው መሆኑን አሻሚ አይሆንም፡፡
የልዩነት መንገዶች ላይ ትኩረት ተሰጥቶ ለዓመታት መሰራቱ ወደታች ሲያወርዱን እንጂ ወደ ከፍታ ሲያወጡን በተግባር አልታየምና እያቃረንም፣ ውስጣችንን እየተፈታተነንም ቢሆን የልዩነት ድንበርን በድፍረት ተሻግረን ለተሻለ የሀገር ስሪትና ምስረታ አንድ እንሁን!
ለዴሞክራሲያዊ የለውጥ እንቅስቃሴ እንተባበር!
Keine Kommentare:
Kommentar veröffentlichen