የወያኔዋ ኢትዮጵያ — ደማቸውን ያፈሰሱላት የሚዋረዱባት፤ የሸጧት ግን የሚከበሩባት ምድር
የኢሉባቡር ጠቅላይ ግዛት አካል ከነበረው ከጋምቤላ በ1894 ዓ.ም. በተደረገው የኢትዮጵያና የእንግሊዝ ስምምነት መሰረት፤ከሱዳን ተነስቶ በነጭ ዐባይ አድርጎ የሚመጣው የንግድ መርከብ የሚቆምበት ወደብና የእንግሊዝ የቀረጥ አስተዳደር መስሪያ ቤት የሚያርፍበት ቦታ የሚሆን ከ2000 ሜትር ወይንም ከ40 ሄክታር የማይበልጥ መሬት፤ እንግሊዝ ሱዳንን ለቅቃ ስትወጣ ግን ወደ ኢትዮጵያ የሚመለስ የንግድ ማዕከል [Commercial Enclave] እግሊዞች እንዲያስተዳድሩት ተሰጥቶ ነበር።
እንግሊዝ ይህንን ቦታ እንደያዘች አስተዳደሩን እንዲጠብቁ የራሷን ዜጎች ትሾም ነበር። በኢትዮጵያ መንግስት በኩል ደግሞ ጋምቤላን እንዲያስተዳድርና ወሰኑን እንዲጠብቅ የተሾመው ከጋምቤላ ባላባቶች አንዱ ነበሩ። ኮሎኔል ጃክ ሞሪስ [Jack Maurice] የሚባለው እንግሊዛዊ አስተዳደሩን በተረከበበት ጊዜ ጀምሮ የጋምቤላውን ባላባትና አስተዳዳሪ እያታለለና በገንዘቡ እየገዛ በስምምነቱ ለእንግሊዝ ተለክቶ ከተሰጠው ወሰን እያለፈ ብዙ የጋምቤላን መሬት የሱዳን አካል ያደርግ ጀመር። ይህንን ወረራና የጋምቤላ መሬት ከኢትዮጵያ ተወስዶ ወደ ሱዳን መካለል የወቅቱ የኢትዮጵያ መሪ ልዑል አልጋ ወራሽ ተፈሪ መኮነን ይሰማሉ።
ዜናው እንደተሰማ ከተቻለ በሰላም፤ ካልሆነ ግን በጦር ኃይል ድንበር ታልፎ ወደ ሱዳን የተወሰደውን የጋምቤላ መሬት እንዲያስመልስ፤ ወደፊትም ድንበሩን እንዲጠብቁ በደጃዝማች ብሩ ወልደገብርኤል [ኋላ ላይ ራስ] የሚመራ ጦር ወደ አካባቢው ይላካል። ደጃዝማች ብሩ ወልደገብርኤል ወታደር አሰልፈው አካባቢው እንደደረሱ ጦርነት ከመክፈታቸው በፊት በዲፕሎማሲ መንገድ የጋምቤላው ባላባት የኢትዮጵያን ወሰን አልፈው ለሱዳን የሰጡትን መሬት እንግሊዝ እንዲለቅላቸው ኮሎኔል ጃክ ሞሪስን ጠየቁ። ኮሎኔል ጃክ ሞሪስም ድሮውን ቦታውን የያዘው ስምምነቱን ተላልፎ አውቆ ኖሮ፤ ኢትዮጵያና እንግሊዝ ወደ ጦርነት ሳያመሩ ወሰን አልፎ ወደ ሱዳን ያካለለውን ብዙ መሬት በሰላም ለኢትዮጵያ ለማስረከብ ተስማማ።
ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ራስ ብሩን ተከትሎ ዳር ድንብር ለማስከበር ከመሀል አገር ተነስቶ ወደ ጋምቤላ የዘመተው የኢትዮጵያ ወታደር በጋምቤላ በረሀ ያለውን በሽታ ችሎ እስከ ጥሊያን ወረራ ድረስ አንዲት ክንድ መሬት ሳያስወስድ እየጠበቀ ቆየ። ከጥሊያን ወረራም በኋላም የኢትዮጵያ ነጻነት ከተረጋገጠበው ዘመት ጀምሮ ሱዳን ነጻ እስክትወጣና በ1894 ዓ.ም. በተደረገው የኢትዮጵያና የእንግሊዝ ስምምነት መሰረት ሙሉው የጋምቤላ መሬት ወደ ኢትዮጵያ እስኪመለስ ድረስ ዳር ድንበር ሲጠብቅ እዚያው ኢሉባቦር ጠቅላይ ግዛት ጋምቤላ ኖሯል።
ሆኖም ግን ባላባት ተብሎ አካባቢውን እንዲያስተዳድርና ድንበሩን እንዲጠብቅ የተሾመው ፊት አውራሪ ጋምቤላ [ፊታውራሪ ጋምቤላ የአኙዋክ ተወላጅ ባላባት ናቸው] ለኮሎኔል ጃክ ሞሪስ እየተደለሉ የአስወሰዱትን መሬት ተዋግተው ለማስመለስ፤ ከዚያም በኋላ ድንበሩ እንዳይደፈር ወሰኑን ለመጠበቅ ከዳጃች ብሩ ወልደ ገብርዔል ጋር የዘመቱ ወታደሮች ልጆች ወያኔና ኦነግ ስልጣን በያዙ ማግስት «ነፍጠኛ» ተብለው ከኢሉባቦርና ጋምቤላ ተፈናቅለው አባቶቻቸው ደም ባፈሰሱበት ምድር ስደተኛ እንዲሆን ተደርገዋል።
አቶ ዮሀንስ መሸሻ በ1989 ዓ.ም. ባሳተሙት «የማውቃት ኢትዮጵያ» መጽሀፋቸው በዚያው አመት ከኢሉባቦር ጠቅላይ ግዛት «ነፍጠኛ» ተብለው «አገራችሁ ሂዱ!» በመባላቸው ተፈናቅለው አዲስ አበባ በስደት ሲንከራተቱ ካገጓቸው አማሮች መካከል ከደጃዝማች ብሩ ወልደገብርኤል ጋር የጋምቤላው ባላባት ለእንግሊዝ የሸጡትን መሬት ለማመለስ ከዘመቱና ድንበሩን ሲጠብቁ ከኖሩት አርበኞች የአንዱን አርበኛ የአገር ውስጥ ስደተኛ ታሪክ አስፍረዋል።
ኢትዮጵያ ደማቸውን ያፈሰሱላት የሚዋረዱባት፤ የሸጧት ግን የሚከበሩባት አገር ሆና ነው እንጂ እኒህ ነጻ ባወጡት ምድር የጦጣ ግንባር ያህል እንኳ የአንገት ማስገቢያ ተከልክለው በአማራነታቸው ብቻ ነፍጠኛ ተብለው ከኢሉባቦር በአገር ሻጮች እንዲፈናቀሉ የተደረጉት ኢትዮጵያዊ ጀግና፤ የእንግሊዙ ሞሪስ እያታለለ ወስዶ የሱዳን አካል አድርጎት እሳቸው ግን ባስመለሱት መሬት ላይ በስማቸው ትምህርት ቤትና መንገድ፤ ከተማና ተቋማት የሚሰየምላቸው፤ ሀውልትም የሚቆምላቸው አርበኛ ነበሩ።
Keine Kommentare:
Kommentar veröffentlichen