- በክሱ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋና አቶ ጀዋር መሐመድ ተካተዋል
የአውሮፓ ኅብረት ፓርላማ ባደረገላቸው ጥሪ ቤልጂየም ብራሰልስ ደርሰው ሲመለሱ ከመስከረም 28 ቀን 2009 ዓ.ም. ጀምሮ ተግባራዊ የሆነውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅን በመጣስ ተጠርጥረው በእስር ላይ የሚገኙት ዶ/ር መረራ ጉዲና፣ በኦሮሚያ ክልል በተለያዩ አካባቢዎች ተከስቶ የነበረውን ብጥብጥና ሁከት ሲያባብሱ እንደነበር የሚገልጽ ክስ ሐሙስ የካቲት 16 ቀን 2009 ዓ.ም. እንደ ተመሠረተባቸው ሪፖርተር ዘግቧል፡፡
የወንጀል ሕግ አንቀጽ 32 (1ሀናለ)፣ 38(1)ን፣ 27(1)ን እና አንቀጽ 238 (1 እና 2)ን ተላልፈዋል ተብለው የመጀመሪያ ክስ የተመሠረተባቸው ዶ/ር መረራ የአርበኞች ግንቦት ሰባት ሊቀመንበር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋና አቶ ጀዋር መሐመድ ናቸው፡፡ በፌዴራልና በክልል ሕገ መንግሥት የተቋቋመን ሥርዓት በሕገወጥ መንገድ ለማፍረስ መንቀሳቀሳቸውን፣ የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ የመሠረተው ክስ ያስረዳል፡፡
የፖለቲካ፣ የሃይማኖት ወይም የአይዲዮሎጂ ዓላማን ለማራመድ፣ በመንግሥት ላይ ጫና ለመፍጠርና ኅብረተሰቡን ለማስፈራራት፣ ከ2008 ዓ.ም. ጀምሮ የሁከትና የብጥብጥ ጥሪ በማስተላለፍ በአንዳንድ የአማራና ኦሮሚያ ክልሎች ኅብረተሰቡ ወደ ሁከትና ብጥብጥ እንዲገባ ማድረጋቸውን ዓቃቤ ሕግ ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 19ኛ ወንጀል ችሎት ባቀረበው ክስ ገልጿል ሲል ፡፡ዓቃቤ ሕግ በክሱ እንዳብራራው ዶ/ር መረራ የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) አመራርነትን እንደ ሽፋን ተጠቅመው፣ የአዲስ አበባ ከተማና የፊንፊኔ ዙሪያ ልዩ ዞን የጋራ ማስተር ፕላን ተቃውሞን እንደ መነሻ በማድረግ ሁከትና ብጥብጥ በተለያዩ የኦሮሚያ አካባቢዎች እንዲቀጥል አድርገዋል፡፡
በ2006 ዓ.ም. ለኦፌኮ አባላት የሥራ ክፍፍል በማድረግ በመንግሥትና በሕዝብ ተቋማት መንግሥታዊና መንግሥታዊ ባልሆኑ ተቋማት ላይ የንብረት ውድመት እንዲደርስ ማድረጋቸውን ክሱ ያስረዳል፡፡ በኢንቨስትመንት ላይ በተሰማሩ ባለሀብቶች ንብረቶች ላይም ውድመት መድረሱንም አክሏል፡፡ በሰውም ላይ ከባድ የአካል መጉደልና ሞት መከሰቱንም ጠቁሟል፡፡
ዶ/ር መረራ በ2008 ዓ.ም. በአንዳንድ የኦሮሚያ ከተሞች በተለይም በምዕራብ ሸዋ ዞን አምቦ አካባቢ የሚገኙ ፕሮጀክቶችን ማለትም የአምቦ-ካራ የመንገድ ግንባታን በመቆራረጥ፣ ካምፕ በማቃጠል፣ በተሽከርካሪዎችና በማሽነሪዎች ላይ የ2,957,661 ብር ንብረት እንዲወድም ማድረጋቸውን ዓቃቤ ሕግ በክሱ ገልጿል፡፡
በቡራዩ ከተማም በ42,598,204 ብር ንብረቶች ላይ ጉዳትና ውድመት ማድረሳቸውንም አክሏል፡፡ በደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን ወሊሶ፣ አመያ፣ ጎሮ፣ ቶሌ፣ ኢሉ፣ ቀርሳ፣ ወንጪ ወረዳዎችና ቀበሌ መስተዳድር የግለሰቦች መኖሪያ ቤቶችንና በኢንቨስትመንት የተሰማሩ ኢንቨስተሮችን የተለያዩ ንብረቶች ጉዳት በማድረስና በማውደም የ17,352,482 ብር ጉዳት እንዲደርስ ምክንያት መሆናቸውንም ክሱ ያብራራል፡፡
ሐምሌ 28 ቀን 2008 ዓ.ም. በኦሮሚያ ሚዲያ ኔትወርክ (OMN) ዶ/ር መረራ ባስተላለፉት የሁከት ጥሪ ሐምሌ 30 ቀን 2008 ዓ.ም. በመላ ኦሮሚያ ሕዝባዊ ተቃውሞ ለማካሄድ መታሰቡን በመግለጽና የሁከቱ ተካፋዮች እንዲሳተፉ ጥሪ ማቅረባቸውንም ዓቃቤ ሕግ በክሱ ገልጿል፡፡
ዶ/ር መረራ ለዚሁ መገናኛ ብዙኃን መስከረም 24 ቀን 2009 ዓ.ም. በቢሾፍቱ ኢሬቻ በዓል ላይ የተከሰተውን አደጋ አስመልክተው በሰጡት መግለጫ፣ የመንግሥት ታጣቂዎች በኦሮሚያ ሕዝብ ላይ በወሰዱት ግድያ 678 ሰዎችን እንደተገደሉ በመግለጽ ባስተላለፉት ጥሪ በክልሉ አንዳንድ ከተሞች ሁከትና ብጥብጡ እንዲቀጥል ማድረጋቸውን ክሱ ያብራራል፡፡
በተነሳውም ብጥብጥና ሁከት የሰላማዊ ሰዎች ሕይወት መጥፋቱን፣ ከባድ የአካል ጉዳት መድረሱን በመንግሥትና መንግሥታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች ላይ፣ እንዲሁም በኢንቨስትመንት ላይ በተሰማሩ ባለሀብቶች ንብረቶች ላይ ጥቃት እንዲደርስና እንዲወድሙ ማድረጋቸውን ዓቃቤ ሕግ በክሱ ገልጿል፡፡
በኦሮሚያ ክልል በኢሉአባቦራ፣ በምዕራብ ሸዋ፣ በምሥራቅ ሸዋ፣ በባሌ፣ በሰበታ ከተማ፣ በደቡብ ምዕራብ ሸዋ፣ በአርሲ፣ በምዕራብ አርሲ ዞን በመንግሥት ንብረት ላይ የ215,468,309 ብር ውድመት እንዲደርስ ማድረጋቸውንም ገልጿል፡፡ ዶ/ር መረራ መንግሥታዊ ባልሆኑ ተቋማት ንብረት ላይ የ1,168,293,498 ብር ንብረት እንዲወድም ምክንያት መሆናቸውንም በክሱ አብራርቷል፡፡
ሌላው ዶ/ር መረራ በቁጥጥር ሥር ውለው የታሰሩበት ምክንያት መስከረም 28 ቀን 2009 ዓ.ም. የታወጀውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅን በመጣስ ተብለው ነው፡፡ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሽብርተኝነት ከተፈረጀው የአርበኞች ግንቦት ሰባት ሊቀመንበር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ጋር በብራሰልስ በመገናኘታቸው ዓቃቤ ሕግ ክስ መሥርቶባቸዋል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ አዋጁን ለማስፈጸም በወጣው መመርያ በሽብርተኝነት ከተፈረጁ ድርጅቶች ጋር መገናኘት የተከለከለ መሆኑ ተገልጾ እያለ፣ ዶ/ር መረራ መመርያውን ጥሰው በመገናኘታቸውና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ቁጥር 01/2009 አንቀጽ 12(1)ን በመተላለፋቸው መሆኑን ክሱ ያብራራል፡፡
ዶ/ር መረራ ኅዳር 2 ቀን 2009 ዓ.ም. ከፕሮፌሰር ብርሃኑ ጋር በብራሰልስ የኦኤምኤን ሠራተኞችና የኦነግ አባላትና ደጋፊዎች ባዘጋጁት የስብሰባ መድረክ ላይ ባደረጉት ንግግር በኦሮሚያ አንዳንድ አካባቢዎች ስለነበረው ሁከትና ብጥብጥ በመግለጻቸው፣ ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጋር የተያያዙ ግዴታዎችን የመተላለፍ ወንጀል በመፈጸም ክስ ዓቃቤ ሕግ አቅርቦባቸዋል፡፡
ዶ/ር መረራ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 486(ለ)ን በመተላለፍ በ2006 ዓ.ም የኢትዮጵያና ናይጄሪያ ብሔራዊ ቡድኖች በአዲስ አበባ ስታዲየም በሚያደርጉት ጨዋታ የአልሸባብ አባላት የአጥፍቶ ማጥፋት ወንጀል ለመፈጸም ባለመቻላቸውና የታጠቁት ፈንጂ ፈንድቶ መሞታቸው እየታወቀ እሳቸው ግን ‹‹አሸባሪዎቹ አፈነዱ የተባለው የውሸትና የመንግሥት ድራማ ነው›› በማለት ሕዝቡ በመንግሥት ላይ እምነት እንዳይኖረው አድርገዋል ሲል ዓቃቤ ሕግ የሐሰት ወሬዎችን የማውራት ወንጀል ክስ መሥርቶባቸዋል፡፡
ከዶ/ር መረራ ጋር በአንደኛ ክስ ተካተው ክስ የተመሠረተባቸው ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋና አቶ ጀዋር መሐመድ ናቸው፡፡ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ከ2006 ዓ.ም. ጀምሮ በአማራ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች በህቡዕ አባላትን በመመልመል እንዲንቀሳቀሱ በማድረግ ሁከቱ እንዲቀጥል በኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቪዥን (ኢሳት) በተለይ በ2009 ዓ.ም. የሁከት ጥሪ ማድረጋቸውን የዓቃቤ ሕግ ክስ ያስረዳል፡፡ ‹‹የኢትዮጵያ አርሶ አደር ከእንግዲህ ግብርና የማዳበሪያ ዕዳ አይከፍልም፤›› በማለት አርሶ አደሩ በመንግሥት ላይ እንዲያምፅና ለፍትሕ ሥርዓቱ እንዳይገዛ የሁከት ጥሪ ማቅረባቸውንም አክሏል፡፡
እሳቸውም ሆኑ ድርጅቱ አርበኞች ግንቦት ሰባት እስከ መጨረሻው የደም ጠብታ ድረስ እንደሚታገሉ በመግለጽና በሰላማዊ መንገድ መታገል ሞኝነት መሆኑን በመስበክ በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል የሚገኘው ሕዝብ መሣሪያውን እየወለወለ ወደ በረሃ እንዲገባም በኢሳት ቴሌቪዥን ንግግር በማድረግ ሁከቱና ረብሻው በመላ አገሪቱ እንዲስፋፋ ጥሪ ማቅረባቸውንም ዓቃቤ ሕግ በክሱ ዘርዝሯል፡፡
ፕሮፌሰሩ በተለያዩ ጊዜያት በአገር ውስጥ በህቡዕ የሚንቀሳቀሱ ባሉበት ጥቃት እንዲያደርሱ በመንገር ከኤርትራ ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ የሽብር ቡድን አባላትም ተመሳሳይ ተግባር እንዲፈጽሙ ትዕዛዝ መስጠታቸውንም ክሱ ያብራራል፡፡
አቶ ጀዋር መሐመድም የአዲስ አበባ ከተማና የፊንፊኔ ዙሪያ ኦሮሚያ ልዩ ዞን የጋራ ማስተር ፕላንን ለሁከት መቀስቀሻ ምክንያት በማድረግ፣ በአገር ውስጥ ለሚገኙ የኦነግ የሽብር ቡድን አባላት ጥሪ ሲያቀርቡ እንደነበር የዓቃቤ ሕግ ክስ ያስረዳል፡፡ በኦሮሚያ ክልል የነበረውን ብጥብጥና ሁከት በኦኤምኤን በማስተላለፍ ሁከትና ብጥብጡ እንዲቀጥል ጥሪ ሲያደርጉ እንደነበር በክሱ ተጠቅሷል፡፡
ከወቅቱ ሁኔታ ጋር ተያይዞ ነጋዴዎች ለሕዝቡ የተለያዩ ቁሳቁሶችን እንዳይሸጡ እንዳያቀርቡና እንዳይገዙ የትራንስፖርት አቅርቦት እንዳይኖር በማለት የሁከት ጥሪ መግለጫዎችን ሲያስተላልፉ እንደነበር በክሱ ተብራርቷል፡፡ አቶ ጀዋር ከላይ በዶ/ር መረራ ክስ ላይ የተገለጹ የንብረት ውድመቶች (በገንዘብ የተገለጹት) እንዲደርሱ ምክንያት መሆናቸውንም ክሱ ይጠቁማል፡፡
በመሆኑም ሦስቱም ተከሳሾች በፈጸሙት በሕገ መንግሥቱና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን በኃይል ለማስወገድ ሙከራ ወንጀል መከሰሳቸውን የዓቃቤ ሕግ ክስ ያስረዳል፡፡ ዓቃቤ ሕግ የጠቀሰውን የወንጀል ሕግ አንቀጽ 238 (1 እና 2)ን ተላልፈው ፈጽመውታል የተባለው ወንጀል በሰውና በሰነድ ማስረጃዎች ከተረጋገጠ፣ ከሦስት ዓመታት እስከ ሞት ሊያስቀጣቸው እንደሚችል ሕጉ ይገልጻል፡፡
በክሱ ውስጥ በሁለተኛ ክስ ላይ የተካተቱት ድርጅቶች ደግሞ የኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቪዥን (ኢሳት) እና ኦሮሚያ ሚዲያ ኔትወርክ (ኦኤምኤን) ናቸው፡፡ ድርጅቶቹ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 32 (1)ሀ እና ለ፣ 38፣ 34 (1)እና የሽብርተኝነት አዋጅ ቁጥር 652/2001 አንቀጽ 5 (1) ለን በመተላለፍ፣ ዶ/ር መረራ፣ ፕሮፌሰር ብርሃኑና አቶ ጀዋር ደግሞ ‹‹ሕገ መንግሥቱንና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን በሁከትና ብጥብጥ እናስወግዳለን፤›› በማለት ያቀረቡትን ጥሪ በማስተላለፍ ድጋፍ ማድረጋቸውን ዓቃቤ ሕግ በክሱ አብራርቷል፡፡
መገናኛ ብዙኃኑ በተለያዩ ጊዜያት ያስተላለፉትን ጥሪ ዓቃቤ ሕግ በዝርዝር በክሱ አካቶ አብራርቷል፡፡ በአጠቃላይ ድርጅቶቹ የኦነግና የአርበኞች ግንቦት ሰባት ልሳን በመሆንና ሚዲያንና ሙያን ሽፋን በማድረግ፣ ሦስቱ ግለሰቦች የሚያስተላልፉትን የብጥብጥ ጥሪ በመቀበልና የሽብር ቡድን ድጋፍ በማድረግ በዋና ወንጀል ላይ ተካፋይ በመሆናቸው፣ የሽብር ተግባር ወንጀል ክስ እንደተመሠረተባቸው ዓቃቤ ሕግ በክሱ ገልጿል፡፡
ክሱ የቀረበለት የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 19ኛ ወንጀል ችሎት ለዶ/ር መረራ ጉዲና ክሱን በመስጠት ለማንበብና ተከሳሹ በጠበቃ ተወክለው እንዲቀርቡ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ከስድስት ዓመታት በፊት ክስ ተመሥርቶባቸው በሌሉበት በሞት እንዲቀጡ ፍርድ መሰጠቱ ይታወሳል፡፡
Keine Kommentare:
Kommentar veröffentlichen