Netsanet: የጎሳ ፖለቲካና የኢሳት ፈተና (ከአንተነህ መርዕድ) ከአንተነህ መርዕድ

Donnerstag, 9. Februar 2017

የጎሳ ፖለቲካና የኢሳት ፈተና (ከአንተነህ መርዕድ) ከአንተነህ መርዕድ

የጎሳ ፖለቲካና የኢሳት ፈተና (ከአንተነህ መርዕድ)
ከአንተነህ መርዕድ
ከደርግ መውደቅ ማግስት የህዝብን ብሶትና የእለት ተእለት ውሎውን የሚዳስሱ በርካታ ጋዜጦችና መፅሄቶችን ከዳር ዳር ባይዳረሱም በአዲስ አበባና በትልልቅ ከተሞች ህዝቡ እየገዛና ከእጅ እጅ እየተቀባበለ በማንበብ ይከታተል ነበር። ወያኔዎች ገበናቸው እየተጋለጠ መግዛት እንደማይችሉ ሲገነዘቡ፤ ጋዜጠኞችን በማሰር፣ በማሰደድ፣ ብሎም በመግደል (አሰፋ ማሩና ተስፋዬ ታደሰን ሳንረሳ)፣ አዟሪዎችንም በመቀጥቀጥ የነፃ ሚድያን ህልውና እንዲያከትም አድርገዋል።
በዚህ የጨለመ ድባብና ተስፋ አስቆራጭ ሁኔታ ነበር። ፀሃይ ከምስራቅ እንደምትወጣ ሁሉ ተስፋና ብርሃን ይዞ ኢሳት በአድማስ ላይ ብቅ ያለው። የኢሳት መፈጠር በጨለማ ማደግ ለሚመቻቸው እኩያን ሞት ስለሆነ ለማዳፈን ከየአቅጣጫው ሩጫ ተጀመረ። እውነቱን እያፍረጠረጠ ማውጣቱ መጥፊያቸው እንደሚሆን ያወቁት ወያኔዎች ብቻ ሳይሆኑ እውነተኛ ባህሪያቸውን ህዝብ እንዳያውቅባቸው የፈሩ የነገ መሳፍንት ጽንፈኞችም ሁሉንም ዓይነት ጦር ወርውረዋል። አሁንም ተስፋ ባለመቁረጥ የተቻላቸውን ያህል እያደረጉ ቢሆንም፤ ኢሳት ለህዝብ ነፃነት እውነት ላይ ተመስርቶ እስከሠራ ድረስ የሚያቆመው ኃይል አይኖርም። ለዚህም ነው ባለፉት ስድስት ዓመታት ውስጥ ከሁሉም አቅጣጫ የሚሰነዘርበትን ፈተና ተቋቁሞ እዚህ ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሰው። ወያኔ ኢሳትን ለማጥፋት ብዙ ሚሊዮን የህዝብ ገንዘብ አፍስሶ፣ የዲፕሎማሲና የስለላ ሥራ ሁሉ ሠርቶ ለስድስት ዓመት ያልተሳካለትን ተግባር በውክልና ይሁን በምቀኝነት በእውነት ፊት መቆም የማይችሉ ድንክ “ፖለቲከኞች” ወይም የፌስቡክ ጀግኖች የሚሰነዝሩት ብኩን ሃሳብ የበለጠ እያጋልጣቸው መሆኑን የተረዱ አይመስልም።
ኢሳት በጠንካራ የንዋይ መሰረትና በልምድ ፍፁም ብቃት ባላቸው ጋዜጠኞች የተገነባ ነው ማለት ከእውነት መራቅ ይሆናል። ጉልሁ እውነት ግን የወጣትነት እድሜአቸውን ለእውነተኛ አገራዊ ጉዳይ በሙያቸው ለማገዝ እየተሳሳቱም ቢሆን በቅንነት እየተማሩ ለመሥራት የቆረጡ ብዙ ተስፋ የሚጣልባቸው እንቁ ልጆች ያሉበት መሆኑ ነው። ሙያቸውን በሚገባ እያዳበሩ መሄዳቸውን ላለፉት ጥቂት ዓመታት ኢሳትን የተከታተለ ሁሉ ይገነዘበዋል። ኢትዮጵያ በሌለ አንጡራ ሃብቷ አስተምራ ዛሬ ከወደቀችበት የሚያነሳት ዜጋ በመብራት ስትፈልግ፤ በውጭም፣ በአገርም ውስጥ ያሉ አቅም ያላቸው ምሁራን ከፊሎችም በፍርሃት አንገታቸውን ደፍተው ህሊናቸውን ለድሎት ሲቸበችቡ፣ ጥቂቶችም ለሚያልሙት የነገ ስልጣን ሲሉ ጥልቅ ገደል እንድትገባ አንገቷ ላይ ደንጋይ ሲቋጥሩና በመንደር ሸንሽነው ተበተኝ ሲሏት በዚህ ማዕበል መሃል ትክክለኛ አቅጣጫ እንድትይዝ የኢሳት ጋዜጠኞች የሚያደርጉት መዋደቅ የተሸከሙትን የሃላፊነት ክብደት ያሳያል። የሚያሳዝነው ይህንን ብቸኛ ተቋምና ብርቅ የህዝብ ልጆች ኢላማ ያደረጉ እየተበራከቱ መምጣታቸው ነው። ቢሆንም የነዚህ እኩያን መንፈራገጥና መንጫጫት ኢሳት በትክክል እየሠራ ለመሆኑ አመላካች ቴርሞሜትር ነው። አንድ ዐይን ያለው በአፈር አይጫወትም የሚለው የአባቶቻችን አስተዋይ አባባል የተረሳን ይመስላል። አምባገነን ስርዓቶች እየተፈራረቁ ለአደቀቁት የኢትዮጵያ ህዝብ ለመከራው መወገድ ፈርቀዳጅ የሚሆን ተስፋ ሲፈነጥቅለት ያንን ተስፋውን እንደሾተላይ ደርሰው የሚቀጩ ልጆች ከአብራኩ ማፍራቱን አላቆመም።
ያለፉትን ስድስት ዓመታት በህሊናችን ስንቃኝ ኢሳት ያልዳሰሰው አገራዊ ጉዳይ፣ያላጋለጠው የዘረኝነት ተንኮልና ዘረፋ፣ ያልቃኘው ኢትዮጵያዊ የህብረተሰብ ክፍል፣ ያላመላከተው የነገ ብሩህ ተስፋ ቢኖር በጣም ትንሽ ነው። ዛሬ እየተቀጣጠለ ላለው ህዝባዊ አመፅና ለወያኔ መፍረክረክ ኢሳት ከፍተኛ ድርሻ አለው። ለአምባገነቡ ስርዓት ፍፃሜ የመጨረሻዋን የመቃብር ላይ ቢስማር የሚመታውም ኢሳት እንደሚሆን ተስፋ አደርጋለሁ። ከዚያም አልፎ በሚፈጠረው አዲስ ስርዓት ኢትዮጵያ ዳግም በአምባገነን ስርዓትና በዘረኝነት ማዕበል እንዳትመታ ጠባቂ መልዐኳ ከሚሆኑት ተቋማት ኢሳት አንዱ እንዲሆን ዜጎች ሁሉ ተግተው ሊሠሩ ይገባል።
ባለፉት አርባ ዓመታት ኢትዮጵያ ለምትዳክርበት የፖለቲካና የድህነት አረንቋ ድርሻ የነበራቸው ወገኖች እንዲሁም ለተሻለ ነገ ገንቢ ሃሳብ አለኝ ያሉትን ኢትዮጵያውያን እንደ ኢሳት መድረክ ሰጥቶ ይደመጡና ይታዩ ዘንድ እድል ያመቻቸ ማንም የለም። በኢትዮጵያ ሁኔታ ቀላል የማይባል ሚና ካላቸው ያለስኬት ካረጁት እስከ አዲሶቹ ፖለቲከኞች በኢሳት ተስተናግደዋል። መኢሶኖች፣ ኢህአፓዎች፣ ኢሰፓዎች፣ ሻዕብያዎች፣ ከፖለቲካው የተለዩትና አሁን ያሉት ወያኔዎች፣ ብአዴኖች፣ ኦህዴዶች፣ ኦነጎች (የተለያዩ አንጃዎች ሳይቀሩ)፣ የቅንጅት ሰዎች፣ የመድረክ አባላት፣ መኢአዶች፣አረናዎች፣ ሰማያዊዎች፣ኦጋዴኖች፣ ሲዳማዎች፣ ጋምቤላዎች፣ አፋሮች እንዲሁም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የፅንፉን ፖለቲካ ጠርዝና ጠርዝ ይዘው የሚጎትቱ የሞረሹ ተክሌ የሻውና ጁአር ሞሃመድ ሳይቀሩ ላንቃቸውን የከፈቱትና መታወቅን ያገኙት በኢሳት መድረክነት መሆኑን ቢክዱ እንታዘባቸዋለን። በነገራችን ላይ ኢሳት ቢጋብዛቸው እንኳ ሊቀርቡ የማይልፈጉት የትናንት ወንጀላቸውና የዛሬ ሸማቂ ልቦናቸው ውስጥስር የሰደደ ዘረኝነት ድፍረት የነፈጋቸው ገብሩ አስራት፣ ስዬ አብርሃ፣ ፍስሃ ደስታን፣ ሃሰን አሊን የመሳሰሉ ናቸው።
ከፖለቲካው ውጭ ከያኒያን፣ ፈላስፎች፣ የታሪክ ሰዎች፣ ሃኪሞች፣ ኢኮኖሚስቶች፣ ወታደራዊ ጠበብቶች፣ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች፣ አክቲቢስቶች በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ያለምንም ገደብ ሃሳባቸውን ለህዝባቸው ያሰሙበት መድረክ ቢኖር በኢሳት ነው።
በጋምቤላዎች ላይ የተካሄደውን የዘር ፍጅት፣ በሳውዲ፣ በየመንና በሊብያ በኢትዮጵያውያን ላይ የተፈፀመን ሰቆቃ ከእስር ቤት ውስጥ ሳይቀር የሚሰማውን ጩኸት፣ የአማራውን ከየክልሉ እየተመነጠረ መገደል፣ መዘረፍና መፈናቀል፣ የወልቃይትን እልቂትና አፈና ከትናንት እስከዛሬ፣ የኦጋዴንን ፍጅት በቪድዮና በቃለመጠይቅ አስደግፎ አቅርቧል፤ የሙስሊሙን ድምፃችን ይሰማ እንቅስቃሴ፣ የኦሮሞን ህዝባዊ ትግል፣ የአማራውን ተጋድሎ በመረጃ እያስደገፈ ከባለሙያ ትንተና ጋር በማቅረብ ኢሳት የሄደበትን ርቀት የተከተለው ሚድያ የለም ለማለት ያስደፍራል። የዘር ደዌ የሚያሰቃያቸው ትንንሽ ህልመኛ መሳፍንት ሌት ተቀን አጥብቀው የሚፈሩትና በስውርና በግልፅ የሚተናኮሉት ኢሳትን መሆኑ አይገርምም። እንደ የዓመትባል በግ ሻጭ ነጋዴ ህዝብን ግንባሩ ላይ ከሌላው መለያ ቀለም እየቀቡ “አንተ የእኔ ነህ፣ ያኛው የእነከሌ ነው” የሚሉ የትርፍ ሰዓት ፖለቲከኖችና ነጋዴዎች ከቶውንም ኢሳትንና ጋዜጠኞቹን በአገር ጉዳይ ደፍረው መጋፈጥ አይችሉም። እንዴት ተብሎ? እንደሌላው መማር፣ ኑሮ ማደላደል፣ ውድ ጊዜአቸውን ከልጆቻቸውና ከቤተሰባቸው ጋር ማሳለፍ ሲችሉ፤ በለጋ እድሜአቸው፣ በሚያሳዝን የገቢ መጠን እየተዳደሩ ራሳቸውን ለአገር መስዋዕት ያቀረቡ የኢሳት ጋዜጠኞችን ማሽሟጠጥና ስም ጠርቶ መስደብ፣ ኢሳት ሊረዳ አይገባውም ብሎ በአደባባይ ከመፏለል የበለጠ ወያኔነት የለም።
ቆምንለት የሚሉትን ዘር መያዣነት (ሆስቴጅ) አድርገው በአንድ በረት ውስጥ እንደገባ ከብት ከሌላው እንዳይገናኝ “የእኔ ብቻ ነው”ን የሚያቅራሩ ጠባቦች በስደት በሚኖሩበት አገር ከወንድሞቻቸው ጋር ቡና መጠጣት ተስኗቸው “ግደለው፣ ፍጀው”ን በርቀት ሲያውጁ አገርቤት ህዝቡ በአንድነት ተቃቅፎ ሞትና መከራን እየተጋራ መኖሩን የሚያሳውቀውን ኢሳትን ቢጠሉ አያስገርምም። ከሁሉም የሚያስገርመው ኢሳትን የአንድ ዞግ (የአማራ ወይም የኦሮሞ) ብቻ አገልጋይ እንዲሆን እነሱ ትንሽ ሆነው ሊያሳንሱት ማለማቸው ነው።
የኦሮሞን ጉዳይ ለመሸፈን የተቋቋመው ኦ ኤም ኤን ስሙ እንደሚያመለክተው በኦሮሞ ጉድይ ላይ ብቻ አተኩሮ ቢሠራ የሚስደንቅ አይደለም። በእርግጥ የኦሮሞ ህዝብ ከቀሪው የኢትዮጵያ ህዝብ ጋር ጭቆናን ለማስወገድ ሆነ በዘላቂ የጋራ የሆነች አገር ለመገንባት የሚያግዝ ሃሳቦች ቢስተናገዱበት ራሳችውን ለትልቅ አላማ ማሰለፋቸውን ያረጋግጣሉ። ነገር ግን ፅንፈኛውን ሃሳብ የያዙ ብዙ ሰዎች ለኦሮሞውም ሆነ ለሌላው የማይጠቅም ሃሳባቸውን ያለምንም ገደብ ሲረጩ ይስተዋላል። ቀስ በቀስ የህዝቡ ፍላጎትና ያለው ተጨባጭ ሁኔታ ወደሰከነና ወደተሻለ አቅጣጫ ያመጣቸዋል ብለው ተስፋ ከሚያደርጉት አንዱ ነኝ።
በቅርብ ጊዜ ደግሞ የአማራ ድምፅ የሚል ሬድዮ ተቋቁሞ ፕሮግራሞቹን እያሰራጨ ነው። እንደ ኦ ኤም ኤን ሁሉ አማራውን በተመለከት ለመዘገብ አላማ እንዳለው ስሙ ይናገራል። የአማራውን ሰቆቃና ስቃይ በዜና በቃለ መጠይቅና በልዩ ልዩ ፕሮግራሞች በእውነት ላይ ተመስርቶ ከሰራ ጥቅሙ ከፍተኛ ይሆናል። ነገር ግን ብዙውን ጊዜ ኦ ኤም ኤን ላይ እንደሚታየው ሌላ ፅንፍ የረገጡ ለአማራውም ሆነ ለቀሪው የኢትዮጵያ ህዝብ የማይጠቅም ሃሳቦችን የሚረጩ ወገኖች ያለገደብ ከፏለሉበት ትልቅ አደጋ ይሆናል። እነዚህ ሁለቱ ተቋማት ቆምንለት ለሚሉት ህዝብ ከልባቸው በቅንነት ከሠሩ ትልቅ አማራጭና የዴሞራሲ ዋስትና ይሆናሉ። ወደሚፈለገው አቅጣጫም እንዲያድጉ ድጋፍ መቸር የሚገባ ሲሆን ሲሳሳቱም ገንቢ የሆነ ትችት ሊቀርብባቸው ይገባል።
ኢሳት የኢትዮጵያ ህዝብ ዐይን፣ ጀሮና አንደበት ነኝ ብሎ ከማወጁ አልፎ ለየትኛውም ሳይወግን ሁሉንም ህዝብ ያማከለ ሥራ በመስራት ላይ መሆኑን አስመስክሯል። ከሁሉም ኢትዮጵያውያን ድጋፍና አድናቆትም እያገኘ ነው። ኢሳትን ካለመበትና ቃል ከገባለት ኢትዮጵያዊ ሥራ ለማደናቀፍ የሚፈልጉ ወገኖች ከላይ ያየናቸውን ተቋማት እየተጠቀሙ የሚያደርጉት ዘመቻ ሁሉም በአንክሮ እየተመለከትነው ነው። ለዴሞክራሲ በመደጋገፍ መስራት ለድል ያበቃልና እነዚህን ተቋማት የሚያንቀሳቅሱና የሚደግፉ ወገኖች ሊያስቡት የሚገባ ጉዳይ ይመስለኛል። እርስ በእርስ በመጠላለፍ ተቃዋሚዎች ሽባ ሆነው እንደቀሩት ሁሉ በሽታው የሚድያ ተቋማት ላይ እንዳይገባ ያሳስበኛል። በኦህዴዶችና በብአዴኖች አማካኝነት ህወሃት እጁን እያስገባ እንድሆነ ያልታያችሁ ካላችሁ ዐይናችሁን ግለጡ እላለሁ። ኢሳት አማራውን አላገለገለም እያሉ በባዶ ጩኸት አየሩን የሚበክሉ ያሉትን ያህል የኦሮሞውን ጉዳይ ጉዳዩ አላደረገም የሚሉ ከሌላው ጎን አቧራ ያስነሳሉ። የሁለቱም ወገን መልዕክት ኢሳት በነሱ ደረጃ ወርዶና ጠብቦ የአንድ ወገን አቀንቃኝ እንዲሆን በመፈለጋቸው እንጂ እንደ ኢሳት ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል አማክሎ በሚዛናዊነት የሚሰራ ተቋም እስካሁን አልገነባንም።
በመንደርተኝነት ኢትዮጵያዊነትን መሸፈን አይቻልም። ጠባብና አጥፊ ነውና።
ሌላውን በመጥላትና በወገንተኝነት አገር እንደማይገነባ ሩቅ ሳንሄድ ከወያኔ ዘረኛ ስርዓት ተምረናል።
በትናንት አስከፊ ታሪካችን የዛሬ ህይወታችንና የነገ ተስፋችን ሊጨልም አይገባም። አገር የሚገነባው ከትናንት ተመክሮ ተነስቶ ወደ ፊት በማየት እንደሆነ ደቡብ አፍሪካ አስተምራናለች።
የትናንት ታሪካችን ሳይሸፋፈን እየተፈተሸ እውነቱ ቢወጣ መማርያችን እንጂ ለሸማቂና ሸፍጠኛ ፖለቲከኞች ሰለባ ሊያደርገን አይገባም። በመካሄድ ላይ ላለው ህዝባዊ ትግል መጠናከርና ለድል መብቃት ኢሳትና ሌሎችም ሚድያዎች የሚጫወቱት በጎ ሚና መበረታታት አለበት። መቶ ሚሊዮን ለተጠጋው የኢትዮጵያ ህዝብ ከአስር በላይ ኢሳትን የመሰሉ ጠንካራ ተቋማት ያስፈልጉታል። ማድረግ ያለብንም ይህንን እንጂ አንድና ብቸኛ ኢሳትን ማዳከም አይደለም።
ይህንን እንድፅፍ ወደ አስገደደኝ ጉዳይ ልመለስ። ሰሞኑን ኢሳት ከፕሮፌሰር ኃይሌ ላሬቦ ጋር ባደረገው ቃለመጠይቅ ምክንያት የተነሳው ጫጫታና ኢሳት ላይ ያነጣጠረው ዘመቻ ከሁሉም የፅንፍ ኃይሎች መሆኑ የአላማቸውን አንድነት የሚያመለክት ሆኗል። ኢሳት እንደሚድያ ተቋም ባለፉት ስድስት ዓመታት ከላይ በከፊል ለማሳየት የሞከርሁትን ፖለቲካዊና ማህበራዊ ጉዳይ ሁሉ ሽፋን ሲሰጥ ኖሯል። በተመሳሳይ ሁኔታ ከወዳጅም ድጋፍ፣ ከተቆርቋሪም እርማት፣ እንደጠላት ከሚቆጥሩትም ዘለፋና ጥቃት ደርሶበታል። ጋዜጠኛ ወንድማገኝ ጋሹ ከለንደን ፕሮፌሰር ኃይሌ ላሬቦን ከአቀረበ በኋላ በፕሮፌሰሩ፣ በኢሳትና በወንድማገኝ ላይ ከጽንፈኛ ወገኖች የተከፈተው ዘመቻ ስህተት ካለ በቀናነት እንዲታረም የሚጋብዝ እንቅስቃሴ ሳይሆን ፀጥ ለመሰኝት የታለመ ፀረ ዴሞክራሲ እንቅስቃሴ እንደሆነ ጎልቶ እየታየ ነው። ይህ አስተያየቴ በቅንነት ስህተቶች ኢንዲታረሙ የሚተጉ ኢትዮጵያውያንን አይመለከትም። እንዲያውም ሊበረታቱ ይገባል። ኃይሌ ላሬቦ ያቀረቧቸው ጭብጦች እውነትነት ከሌላቸው ሃሳባቸውን በሃሳብ ለመርታት ተዘጋጅቶ መቅረብ የእውነተኛ ምሁራን ስራ ይሆናል። ኢሳትም ለእንደዚህ ዓይነት ሁኔታ መድረኩን ክፍት አድርጎ ማስተናገድ የሚዲይው ስነምግባርና አገራዊ ኃላፊነቱ ያስገድደዋል። ከዚያ በዘለለ ኃይሌ ላሬቦን የመሰሉትን ምሁራንና ኢሳትን ዝም ለማሰኘት አልሞ መንቀሳቀስ ትልቅ ወንጀል ብቻ ሳይሆን የቡድኑን ተሸናፊነት የሚያሳይ ነው። ክሽፈትን።
ይህ እውነትን ለማፈን የሚደረግ እሩጫ፣ ጠባብና አደገኛ አካሄድ ዛሬ አልተጀመረም። ከአስራ ስምንት አመት በፊት በጦብያ መፅሄት ላይ ጽሁፉን እንድናወጣለት ከአውሮፓ ዛሬ ስሙን የረሳሁት ሰው ላከልን። ኢዲቶርያል ቦርዱ ለሳምንት ተወያየንበት። የኦሮሞን ጉዳይ ለፖለቲካ ዓላማ የሚጠቀሙ በርካታ ወገኖች ስለአሉ በተገቢውና ሚዛናዊ በሆነ መልክ ማስተናገድ የምንችል መሆኑን መገምገም ነበረብን። ከሰውየው የተለየ ሃሳብ ያላቸው ካሉ በተለይም ከኦሮሞዎች መካከል ስንጠይቅ ዶክተር መረራ ጉዲና ፈቃደኛ ሆኑ። የሰውየውን መጣጥፍ ለህትመት ካበቃነው በኋላ ከራሱ ከፀሃፊውና ከዘር ፖለቲካ አራማጆች ሳይቀር ድጋፉ ጎረፈልን። በቀጥዩ ወር የዶክተር መረራን ፅሁፍ ስናወጣ ድጋፉ ከሌሎች እንደቀጠለ ሆኖ በኦነግ ዙርያ ያሉና ሌሎችም የዘር ፖለቲካ አቀንቃኞች ዛሬ በፕሮፌሰር ኃይሌና በኢሳት ላይ እንደተከፈተው ዓይነት ዘመቻ አየሩን ሞሉት። ኃይሌ ላሬቦ ከስራቸው እንዲወጡ ፔቲሽን እንደተፈረመው ለጦቢያ ባልደረቦች በተለይም በጊዜው አዘጋጁ ለነበርሁት “እንገድልሃለን” ማስጠንቀቅያ በስልክ ሁለት ሳምንት ሙሉ ደርሶናል። “መግደል የፈሪና የተሸናፊ ስልት ነው፣ የተለየ እውነት ካላችሁ መድረኩ ክፍት ነው። ተጠቀሙበት። መሞት የሚገባን ከሆነ ደግሞ ወያኔም ለመግደል እያስፈራራንና እያሰረን ስለሆነ ለሙያውና ለአገራችን የምንከፍለው ክብር ያለው መስዋዕት ይሆናል” እያልን መልሰንላቸዋል። አንዳቸውም ደፍረው አልመጡም። ይልቁንስ ይመቸናል ባሉት ኡርጂ ጋዜጣ ይዘልፉን ነበር። መረራ ላይ የደረሰባቸውን ራሳቸው ቢናገሩት ይሻላል። የመረራ ትችት ግን ጊዜውን የጠበቀ በመሆኑ ብዙ ኢትዮጵያውያንን በተለይም ብዥታ የነበረባቸውን ጭፍን የኦነግ ደጋፊዎችን ሳይቀር አስተምሯል። ኦነግም እንደወትሮው በአባሎቹ ሆነ በሌላው ስሜት ላይ መጋለብ ሳይችል ቀረና ራሱን እንዲመረምር ተገደደ።
በፕሮፌሰር ኃይሌ ላሬቦ፣ በወንድማገኝ ጋሹና ኢሳት ላይ የሚደረገው ዘመቻ ዝም ለማሰኘት ከሆነ የከሸፈ የደካሞች መንገድ ነው። ኃይሌ ላሬቦ ባቀረቡት ኢንተርቪው የተሳሳተ መልዕክት ካለ ለማረም የሙያ ግዴታ አለባቸው። ሆነ ብለው የማይገባ ስህተት ተናግረው ከሆነ የኦሮሞውን ህብረተሰብ ሳይሆን ራሳቸውን ነው የሚጎዳው። ታሪክን የመሰለ የሰው ልጅ ትልቅ ሃብት ግለሰብ ሆነ ቡድን በባለቤትነት ሊይዘው አይችልምና። እውነቱን አደባባይ ማውጣት የሁሉም ግዴታ እንጂ የተወሰኑ ሰዎች ወይም ቡድኖች ብቻ ሃላፊነት አይደለም። ጋዜጠኛ ወንድማገኝና ኢሳት ድክመታቸውን እያረሙ የኢትዮጵያን ህዝብ ለማገልገል ትልቅ ኃላፊነት አለባቸው። ያንን ሃላፊነት ሲያጕድሉ የሚቀጣቸው ህዝቡ እንጂ ራሳቸውን የኮፈሱ ጋንጎች አይደሉም። ኢሳት ለኦሮሞ ህዝብ ትልቅ ከበሬታ እንዳለው በሥራው እያሳየ መሄዱ ያንገበገባቸው መንደርተኞች ጫጫታ ጊዜአዊ ነው። በርካታ የኦሮሞ ምሁራንና ፖለቲከኞች ከዚህ በፊት ኢትዮጵያዊ አግኝቷቸው በማያውቀው ደረጃ ሃሳባቸውን እንዲያካፍሉ በመደረጉ ትልቁ ብዥታ እየጠራ ኢትዮጵያን በጋራ የመገምባቱ ሃሳብ መሰረት እየጣለ መሄድ ላይ መሆኑ በጣም ፅንፈኛ ለሆኑና ለወያኔዎች አልተመቸም ስለሆነም ዘመቻው በጋራ የሚያደርጉት እየመሰለ ሄዷል። ፕሮፌሰር ህዝቅኤል ጋቢሳ የኢሳት ቤተኛ እንድሆኑ ደጋግመን አይተናቸዋል። በሚያቀርቡት የሳሳባቸው ግልፅነትና ድፍረት የማደንቃቸው ናቸው። የተሳሳተ ታሪክ ተነግሯል ካሉ እውነተኛ ታሪኩ ብለው የሚያውቁትን በመረጃ አስደግፈው ለመናገር ሙያውም ይፈቅድላቸዋል። ታሪኩ ባልተነገረበት ኦሮሞ ሚድያ ኔትወርክ ላይ አንድ አይነት ሃሳብ ካላቸው ሰዎች ጋር ብቻ ሄደው ያደረጉት ውይይት ዓላማውን የሳተ ይመስለኛል። ኢንተርቪውን የተከታተለው የኢሳት ታዳሚ እስከሆነ ድረስ ማስተባበል ሆነ ማሳረም የሚቻለው ከኢሳት የተከታተለውን ህብረተሰብ ነው። ሌላ አድማጭና ተመልካች ተፈልጎ የተሄደ ከሆነ ይህ ምሁራዊና ሙያዊ አካሄድ ሳይሆን ፕሮፓጋናዳ ነው የሚሆነው። ኢሳት መድረኩን ነፍጓቸው ከሆነ እንወቀውና ከስነምግባር አንፃር እንሞግተው። በዚህ ወቅት ኢሳት ላይ መቅረቡን የሸሹት “ኮሚኒቲያቸውን” ፈርተው ከሆነ ህዝብ የሚያከብራቸውና የሙያቸውን ስንምግባር የሚያስጠብቁት እውነትን ይዞ በመጋፈጥ መሆኑን መንገር ግድ ይለናል። ጦቢያ ላይ ለተስተናገደ ጉዳይ ኡርጂ ላይ እንደመሸገው ወንድማችን የኦሮሞ ሚድያ ኔትወክን ፈልጎ መሄድ እውነትን በእውቀት መሞገት አይደለም።
አንዳንድ የዋህ ወዳጆቼ ኢሳት ይህንን ለመዘገብ ጊዜው አይደለም ይላሉ። መቼ ነው ጊዜው? የሚዘራው እኩይ ፕሮፓጋንዳ ፍሬ እስኪያፈራና ዘረኞች እንደወያኔ በህዝብ ራስ ላይ ወጥተው እስኪጋልቡ ነው? ኢሳት ሆነ ሌላው ሚድያ ለነገ የሚያስቀምጡው እውነት ሊኖር አይገባም። በተለይም አገርንና ህዝብን በተመለከተ ጓዳ ውስጥ የሚውጠነጠንን ሁሉ አደባባይ ማውጣትና ማሳወቅ የሚድያ ትልቁና ዋና ሥራ ነው።
ኢትዮጵያን የመሰለች የረጂም ጊዜና ውስብስብ ታሪክ ያላት አገር ይቅርና በቅርቡ ብቅ ያሉ አገራት ባለፈ ታሪካቸው ይህ ነው ብለው የሚቋጩት፣ ያለቀ፣ ከስህተት ተፀዳ፣ ፍፁም የሆነ ታሪክ የላቸውም። በየጊዜው በምርምር የሚገኘውን እየፈተሹ እያዳበሩ አገር በመገንባት ላይ ነው የሚያተኮሩት።
የኛ የፖለቲካ ጋንግስተሮች ታሪክ ለጠባብ ፖለቲካ አላማቸው እስካልጠቀመ ድረስ ደንታ የላቸውም። ለመሆኑ የኢትዮጵያ ታሪክ ከምኒልክ ይጀምራል ያላቸው ማን ነው? እነሱ ተቀበሉትም አልተቀበሉት ኢትዮጵያ እንደበርካታ የዓለም ሃገራት ስትወድቅ ስትነሳ፤ ስትሰፋና ስትጠብብ፤ በዚህም ህልውናዋ ህዝቧ ሲጣላ ሲፋቀር፣ ሲጋባ ሲዋለድ፣ ሲፈልስና ሲዋሃድ የኖረ የብዙ ሺስ ዘመን ውጤት ነው። የሩቁን እንተውና ከክርስቶች ልደት ወዲህ ያለውን ብንመለከተው ንጉሥ ኢዛና ኑብያና መርዌ ድረስ ሲዘምትና ሲያስገብር እዚያ ደረጃ ያደረሰውን አቅም ያጎለበተው ዛሬ በየጎጡ ካለንበት ከተገኙ አባቶቻችን ጉልበትና ንብረት መሆኑን ማገናዘብ እንዴት ያቅተናል? ካሌብ ቀይባህርን ተሻግሮ የመን ድረስ ሲገዛ አፋር፣ ሶማሌ፣ ሲዳሞ፣ ጠቅላላ ደቡቡና ሰሜኑ ከእጁ አልነበሩም ብሎ የሚሞግት ሰው አለ? የአክሱምን ኃያልነት የተፈታተኑት የዮአዲት፣ የአገዎችና የሌሎችም ዘመቻዎች የህዝቡን ከታች ወደላይ፣ ከላይም ወደታች መቀላቀል እንዴት ያግደዋል? አምደፅዮን ዘርዐ ያዕቆብ ሶማሌን ይፋትን ደዋሮን ባሌ ድረስ ዘልቀው ግዛት ሊያሰፉ የዘመቱት የመደራቸውን ሰዎች ብቻ ይዘው ነው እንላለን? በኢትዮጵያ ጠረፍ ያሉት አሚሮች፣ ሱልጣኖች፣ አዳሎችና ሶማሌዎች ሲደክሙ በመገበር ሲጠነክሩ ደግሞ በመጋፋት መሃል ገብተው ሲያስገብሩና ሲቀላቀሉ የሚካሄደው የህዝብ ፍልሰትና ውህደት አይታየንም? ማንም ሊክደው የማይቻለው የአህመድ ኢቭን ኢብራሂም ኤል ቃዚ (የግራኝ መሃመድ) ዘመቻ መላ ኢትዮጵያን ሲያዳርስ የተፈፀመውን የህዝብ ውህደት እንዴት ነው የምናየው?
በግራኝ መሃመድ ዘመቻ የተዳከመውን ማዕከላዊ አስተዳደር ክፍተት በመጠቀም ከደቡብ የተንቀሳቀሰው የኦሮሞ ህዝብ ፍልሰትና መዋሃድ መላ ኢትዮጵያን አላዳረሰም ብሎ ማን ይክዳል? በዚህ ከባሌ ተነስቶ በተደረገ መስፋፋት ወቅት ደቡብ ውስጥ የነበሩት በርካታ ማህበረሰቦች ሲዳማ፣ወላይታ፣ ከምባታ፣ ሃድያ፣ ጉራጌ፣ ጃንጂሮ፣ ወዘተ ሳይዳጡ፤ ሰሜን ደግሞ ሸዋ ወለጋ፣ ጎጃም፣ ወሎ፣ ጎንደርና ትግራይ ዘልቆ የኦሮሞ ህዝብ ሲደርስ አማራው፣ አገው፣ ሽናሻው፣ ጉምዙ፣ ጋፋቱና ትግሬው ሳይጨፈለቅ፣ ሳይገደል፣ሳይገብርና ማንነቱን እንዲቀይር ሳይገደድ የተደረገ ዘመቻ ነው ብሎ ሊነግረን የሚደፍር ማን ነው? በዘመነ መሳፍንት ጊዜስ እያንዳንዱ መስፍን አቅሙ በፈቀደው ግዛቱን ሲያሰፋና ሲያጠብ ህዝብ ከቀየው አልተፋለሰም? አልሞተም? የነበረው እንዳልነበረ አልሆነም? የምኒልክ አያትና አባት ሳህለስላሴና ሃይለመለኮት በሁሉም አቅጣጫ ግዛታቸውን ለማስፋት እስከተቻላቸው ተግተዋል። ዘመነ መሳፍንት እንዲያከትም ፈር የቀደዱት አፄ ቴዎድሮስ ትግሬን ወሎን ጎጃምንና ሸዋን ያስገበሩት ሰይፍ ይዘው፣ እየቆረጡም፣ እየገደሉም፣ እየሞቱም ነው። አፄ ዮሃንስ ከአፄ ቴዎድሮስ የተለየ አላደረጉም። ንጉሥ ተክለሃይማኖት እስከ ከፋ ግዛቴ ነው ሲሉ፤ አፄ ምኒልክ ቀደምቶቻቸው የጀመሩትን ግዛት ያውም አፍሪካን ለመቀራመት ከዘመቱ የምዕራባውያን ወራሪ ኃይል ጋር እየተናነቁ፣ ሲጋፉ በታሪካችን እንዳሳለፍነው የጦርነት፣ የፍጅት ዘመቻ አድርገው አገር አቀኑ እንጂ ከአባቶቻቸው ተለይተው በዴሞክራሲ ገዙ ብሎ የሚሞግት አንድም ኢትዮጵያዊ የለም። በዘመነ ኃይለስላሴም በጣልያን ወረራና በተፈጥሮ አደጋ ሰፊ የህዝብ መፍለስ ተፈፅሟል። የትግራይና የወሎ ህዝብ በተደጋጋሚ ድርቅ ምክንያት ቀየውን ለቆ ጎጃም፣ ወለጋና ደቡብ በመስፈር ህይወቱን አትርፏል። በደርግ ጊዜ በሶማሌ ወረራ በአጭር ጊዜ ውስጥ ከሶስት መቶ ሺህ የበለጠ ገበሬ ከመላ አገሪቱ ተመልምሎ ሰልጥኖ ሲዘምት፣ ለበርካታ ዐመታትም በኤርትራና በትግራይም ሰፍሮ በጦርነቱ የተፈጠረውን ህዝባዊ ፍልሰትና መዋሃድ በዐይነ ህሊና ልንቃኝ ይገባል። በድርቁም የተጠቁትን የትግራይ፣ የወሎና የከምባታን ህዝብ በጎጃም ፓዌ በወለጋ በጋምቤላና በሌላም ለም መሬቶች አስፍሯል። በወያኔ ደግሞ ሰው በዘሩ እየተመነጠረ አማራ የተባለ ሁሉ ከበርካታ አካባቢዎች ሃብቱ እየተዘረፈና እየተገደለ እንዲፈናቀል ሲያደርግ ትግሬው ደግሞ ከተሞችንና ለም መሬቶችን እንዲቆጣጠር በሰፊው ተሰርቷል። ወልቃይት፣ ጋምቤላ፣ ደቡብ፣ ቤንሻንጉል፣ አዲስ አበባና ሌሎችም ቦታዎች የሚካሄደውን ወረራና ዘረፋ በየቀኑ የምንሰማው ነው።
ለብዙ ሺህ ዓመታት ነፋስ እንደሚገፋው ማዕበል ህዝቡ ከምስራቅ ወደ ምዕራብ፣ ከደቡብ ወደ ሰሜን፤ ከሰሜንም ወደ ደቡብና ምስራቅ በጦርነትና በሰላም ሲገማሸር፣ ሲቀላቀል፣ ሲዳዳጥና ሲጨፈላለቅ ብሎም ሲዋሃድ መኖሩ ይታወቃል። ከታሪካችን እንደምናስተውለው የኢዛናን፣ የካሌብን፣ የዮዲትን፣ የአምደፅዮንን፣ የግራኝን፣ የኦሮሞን መስፋፋት፣ የቴዎድሮስን፣ የዮሃንስን፣ የምኒልክን የኃይለስላሴን ኃይል እየተከተሉ በየቦታው የተዛነቁትን አያቶቻችንን ታሪክ ወደ ኋላ ብንቃኝ ማን በየትኛው ጊዜ ግፍ ፈፃሚ እንደነበር በትክክል ለማየት ከዘረኝነትና ከጠባብ የፖለቲካ ጥቅም ፀድቶ መገምገምን ይጠይቃል።
የገደለው ባልሽ
የሞተው ወንድምሽ፤
ሃዘንሽ ቅጥ አጣ
ከቤትሽም አልወጣ።
እንደተባለላት የአለፈ ታሪካችን ላይ ሲፈፀም የኖረው በጎና ክፉ ነገር የጋራችን መሆኑን መቀበልና ወደፊት መራመድን ይጠይቃል። ከዚያም፤
የተሻረው ባሌ ተሿሚው ወንድሜ፤
ምን እናገራለሁ ከዚህ መሃል ቁሜ።
እንዳለችው አልቃሽ ያለፈ ታሪክ ውጤታችንን በፀጋ ተቀብለን የቀደም ስህተቶች እንዳይደገሙ ተግቶ መሥራት መፍትሄ ይሆናል። ያለፈውን ታሪክ እዳ በቦታውና በጊዜው ያልነበረ ትውልድ እንዲከፍል በመጠየቅ የምናባክነውን ወርቃማ ጊዜና አቅማችንን አገርን ከአምባገነን ስርዓት ለማስወገድና ዴሞክራሲ ለማስፈን ብናውለው ይበጀናል።
“በሴት አያቶቻችን በር ማን እንዳለፈ እነሱ ብቻ ናቸው የሚያውቁት” የሚለውን እውነት ማን እንደተናገረ ረሳሁ። በየአንዳንዳችን ደም ሥር ውስጥ የብዙ ኢትዮጵያውያን ነገዶችን ዲ ኤን ኤ የያዘ ደም ነው በመላ ሰውነታችን የሚመላለሰው። ኢትዮጵያዊነት ብዝሃነትን በአንድነት ያካተተ ውበት ነው። ቋንቋ ዘርን እንደማያመለክት በስደት ዓለሙ ያላችሁ ቋንቋችሁን የማይችሉ ልጆቻችሁን ያሳደጋችሁ ሁሉ ጥሩ ምስክሬ ናችሁ። ለዚህም ይመስለኛል መጽሃፍ ቅዱስ በትንቢተ ኤርምያስ 13፡ 23 ላይ “በውኑ ኢትዮጵያዊ መልኩን ወይስ ነብር ዝንጉርጉርነትን ይለውጥ ዘንድ ይችላልን?” ያለው። አዎ የኢትዮጵያውያንን የዘር ብዝሃነት ክደው ስለዘር ንፅህና የሚሰብኩን እንደሂትለር ለክፉ ዓላማ ለማዋል እንጂ እናውቅለታለን ለሚሉት ህዝብ ደህንነት አለመሆኑ ግልፅ ነው።
በሶሻል ሚድያና በአየር ላይ አካፋና አዷማ ይዘው ታሪክ የሚቆፍሩ መናኛዎችን መምከር ካለብን ያለፉት አባቶቻችን በጊዜአቸው በመሰላቸው ኑረው አልፈዋል። ከሞቱበት አትቀስቅሷቸው። ልጆቻቸውን የሚገድል ስርዓት እንዲኖር እየደገፋቸሁ ለሞቱት አባቶቻችን ታሪክ ትቆረቆራላችሁ ብለን አናምንም። ራሳችሁ ከሞታችሁበትና ከገባችሁበት የዘረኝት አረንቋ ውጡና ዓለምን ተመልከቱ፣ ቤተሰቦቻችሁን ጠይቁ፣ የሚፈልጉት ፍትህ ነው፣ ሰላም ነው፣ ከጎረቤትና ከሃገሩ በሰላም በፍቀር መኖርን ነው። እያደቀቃቸው ያለው የዘረኝነት ጫማ ጥርሱ አልቆ ሊወገድ ትንሽ ሲቀረው የእናንተን አዲስ አንጓው የበዛ የዘረኝነት ጫማ ተክቶ እንዲረግጣቸው አይፈልጉም። ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና እንዳሉት የታሪክ ሂሳብ ማወራረድ ይቅር። ማንም አትራፊ አይሆንም። አሁን ላለንበት ውድቀት የሁላችንም ድርሻ አለበት። ታሪክን ለታሪክ ነቱ ትተን ህዝባችንና አገራችንን ወደፊት እናራምድ።
ከሁሉም በላይ ለሚደረገው ህዝባዊ ትግል ከፍተኛ ሚና እየተጫወቱ የሚገኙ የመገናኛ ብዙሃንን በተለይም ኢሳትን ኢላማ ያደረጉትን ኃይሎች መቋቋም ያስፈልጋል። ማንም ኢትዮጵያዊ ሃሳቡን በነፃነት በመግለፁ ጥቃት ሊደርስበት አይገባም። ምሁራንም በግላቸው ዘለፋ ይደርስብናል ብለው ለአገርና ለወገን የሚጠቅም እውቀታቸውን ከማካፈል ወደኋላ ማለት የለባቸውም። ሚድያዎችም ለህዝብ፣ ለአገርና ለእውነት መታመን እንጂ ለጠባብ ቡድኖች መጠቀሚያ እንዳይሆኑ ሁለንተናዊ ድጋፋችን አይለያቸው።

Keine Kommentare:

Kommentar veröffentlichen