Netsanet: ተጠያቂነት የማያረጋግጥ የመልካም አስተዳደር ንቅናቄ (ግርማ ሠይፉ ማሩ)

Sonntag, 21. September 2014

ተጠያቂነት የማያረጋግጥ የመልካም አስተዳደር ንቅናቄ (ግርማ ሠይፉ ማሩ)

ግርማ ሠይፉ ማሩ
Girma Seifu
ግርማ ሠይፉ ማሩ
ባለፈው ሳምንት ማጠናቀቂያ በክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪያም ደሳለኝ ሰብሳቢነት የመንግሰት ከፍተኛ ባለስልጣኖች የ2006 የመልካም አስተዳደር ማሻሻያ አፈፃፀም ሪፖርት አቅርበዋል፡፡ ሁሉም ሪፖርት አቅራቢዎች “ፖወር ፖይንት” በሚባል የማይክሮ ሶፍት ፕሮግራም የተጠቀሙ ሲሆን አብዛኞቹ ይህን ፕሮግራም በቅጡ ለመጠቀም በግል ያላቸውን ዝቅተኛ ችሎታ ያሳየ ብቻ ሳይሆን በየመስሪያ ቤታቸው ሞያ ያላቸውን ሰዎች መጠቀም ያለመቻልና ያለመፈለግን ቁልጭ አድርጎ ያሳየ ነበር፡፡ የተፈቀደላቸውን አጭር ጊዜ ያመጣጠነ ዝግጅት ማድረግ ሳይችሉ ቀርተው ያዘጋጁትን የፅሁፍ ሪፖርት ሲያነቡ ጊዜ አለቀ እየተባሉ ማስተላለፍ የሚፈልጉትን ቁም ነገር (ካለቸው ማለቴ ነው) ትተው በመግቢያና በሪፖርት ይዘት ጊዜ ሲያባክኑ መታዘብ አሰገራሚ ነበር፡፡ ከዚህ አንፃር የውሃ መስኖ ኢነርጂ ሚኒስትሩ አቶ አለማየሁ ተገኑ በንፅፅር የተሻሉ ነበሩ ማለት ይቻላል፡፡ ቴክኖሎጂ የመጠቀም አስፈላጊነቱም ሰዓትን በአግባቡ በመጠቅም ተገቢውን መልዕክት ለማስተላለፍ ነው፡፡ ረፖርት አቅራቢዎች ስዓት በአግባቡ መጠቀም ባለመቻላቸው ሊያቀርቡ ያሰቡትን በሙሉ ካለማቅረባቸው በተጨማሪ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ላይ የሰዓት ቁጥጥር ስራ ጨምረውባቸው ነው የዋሉት፡፡ እርግጠኛ ነኝ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ቢሆኑ ኖሮ እንዴት ሊበሳጩባቸው እንደሚችሉ፡፡
የሲቪል ሰርቪስ ሚኒሰቴር ሚኒስትሯ ወ/ሮ አስቴር ማሞ ድርጅታቸው ኢህአዴግ ንቅናቄውን እንደ ፓርቲ የምርጫ ቅስቀሳ ግብዓት ለመጠቀም መወሰኑን በሚያሳብቅ ሁኔታ መሪ ድርጅታችን ኢህአዴግ አና መንግስታችን በሰጡት ትኩረት በሚል ነበር ንግግራቸውን የጀመሩት፡፡ የመሪ ድርጅታችን ኢህአዴግ በንግግሩ መግባት መልዕክት ለተሰበሰቡት የመንግስት ሹሞች ሳይሆን ጥሪ ለተደረገላቸው እና በአዳራሹ በብዛት ለታደሙት በኢህአዴግ አጣራር “የህዝብ አደረጃጀት” በመባል ለሚታወቁት የኢህአዴግ አፍቃሪዎች ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩም ቢሆን የስብሰባ ታዳሚዎችን እንኳን ደህና መጣችሁ ለማለት “ውድ” የሚል ተቀፅላ ያገኙት እነዚሁ የህዝብ አደረጃጀቶች ናቸው፡፡ እርግጥ ነው በቀጣዩ ምርጫ በአሸናፊነት ለመውጣት የእነዚህ የህዝብ አደረጃጀቶች ሚና የላቀ ነው፡፡ በተለይ በአዲስ አበባ ተቃዋሚዎች ተጠናክረው ታዛቢ ካስቀመጡ ምርጫ ቦርድ ያለነዚህ የህዝብ አደረጃጀት ንቁ ተሳትፎ ቢሮ ቁጭ ብሎ ኢህአዴግን ብዙ ሊረዳው አይችልም፡፡ ጠቅላይ ሚኒሰትሩም ሆነ ፓርቲያቸው ይህ በቅጡ የገባቸው ይመስለኛል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የመልካም አስተዳደር ጉዳይ እዚህና እዚያ የጎደሉ አግልግሎቶችን በማስተካከል ብቻ የሚያበቃ እንዳልሆነ ይልቁንም የመልካም አስተዳደር ችግር በቀጣይ የሚያመጣው “መዘዝ” ብዙ መሆኑን አበክረው ገልፀዋል፡፡ እርሳቸው “መዘዝ” ያሉትን እኛ አብዮት ስንለው የመንግሰት ሚዲያዎች ደግሞ ተቀብለው “የቀለምና የፍራፍሬ አብዮት” ይሉታል፡፡ ተመስገን ደሳለኝ አብዮት ብቻውን የማይጥም ከሆነ ብሎ ይመስለኛል “የህዳሴው አብዮት” ብሎታል፡፡ ለማነኛውም በዚህች ሀገር የተንሰራፋው የመልካም አስተዳደር ችግር መዘዙ ብዙ መሆኑ በጠቅላይ ሚኒስትር ደረጃ ከታመነ ይህ መዘዝ የተባለው ነገር ስሙ ብዙ አያስጨንቀንም፡፡ የሚያስጨንቀን ይህ መዘዝ እንዳይከተል ምን ማድረግ ይኖርብናል ነው፡፡ በተለይ መንግሰት ይህን መዘዝ ለመከላከል ብሎ ለናይጄሪያ ሽብርተኝነትን ለመከላከል ልምድ ይሆናል ተብሎ የተነገረለትን “የፀረ ሽብር” ህግ እንደመፍትሔ አሰቦት ከሆነ ከመዘዙ እየራቀ ሳይሆን ወደ መዘዙ በፍጥነት እየተጠጋ መሆኑን መረዳት ይኖርበታል፡፡
ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩም ሆኖ ሌሎች ሚኒሰትሮች በተደጋጋሚ ያነሱት ሌላ አብይ ነገር የኪራይ ሰብሳቢነት የሚመለከት ሲሆን ይህን የኪራይ ሰብሳቢነት የገለፁት የኪራይ ስብሳቢነት መረብ በሚል ነበር፡፡ በዕለቱ ያነበብኩት ጋዜጣ ደግሞ በኮንትሮባንድ ሊገባ የነበረ ወተት በኬላ መያዙን የሚገልፅ ክፍል ነበረው፡፡ ታዲያስ ስብሰባ ላይ ቁጭ ብዬ “የሰው ለሰው ድራማ” አስናቀ እና ኢህአዴግ ቁልጭ ብለው ይታዩኝ ጀመር፡፡ ይህን መረብ ለመበጠስ እሰከ አሁን እንዳልተቻለ እና ከፍተኛ ትግል እንደሚያስፈልግ ጠቅላይ ሚኒሰትሩን ጨምሮ ሚኒስትሮቹ  እየገለፁ ኢቲቪ ደግሞ አሰናቀ ለፍርድ ሳይቀርብ ለምን ሞተ ብሎ ዶክመንተሪ ይሰራል፡፡ የኪራይ ስብሳቢነት መረብ እስኪበጣጠስ ድረስ አስናቀ መኖር እና ማጋለጥ ነበረበት የሚል አቋም አለኝ፡፡ እናንተስ ምን ትላላችሁ ጎበዝ? አሁን አንድ የቴሌቪዥን ድራማ አጨራረስ እንዴት መሆን እንዳለበት ዶክመንተሪ ያስፈልገዋል? ለማንኛውም የሰው ለሰው ድራማ ደራሲና አዘጋጆች የህዝቡን እንጂ “ባለሞያ” ተብዬዎች በኢቲቪ ያቀረቡትን አስተያየት እንደማትሰሙ እርግጠኛ ነኝ፡፡
ዶክተር ደብረፅዮን በዕለቱ ሪፖርት ከሚያቀርቡት ሚኒስተሮች ቀዳሚውን ቦታ ያገኙ ነበሩ፡፡ ሪፖርት ያቀረቡት በዋነኝነት የቴሌኮሚኒኬሽን ሴክተሩን  በሚመለከትነው፡፡ ከሚመሩት መስሪያ ቤት አንፃር ሲታይም ቴክኖሎጂ በመጠቀም የተሻለ መሆን ሲጠበቅባቸው ማድረግ አልቻሉም፡፡ የቀረበው ሪፖርትም በፍፁም በመሬት ላይ ካላው የቴሌ ችግር ጋር የሚጣጣም አይደለም፡፡ በሪፖርቱ መስረት ሁሉም ችግሮች በእቅድ ከተያዘው ጊዜ ቀደም ብሎ የተተገበረ ሲሆን በአሁኑ ስዓት በተለይ በአዲስ አበባ ይህ ነው የሚባል ችግር እንደሌለ ነው ያበሰሩን፡፡ ይህ ግን በምንም መመዘኛ ተቀባይነት እንደሌለው ለመረዳት ከሪፖርታቸው በኋላ በሻይ እረፍት የተሰበሰቡት ሹመኞች ሳይቀሩ ሲያፌዙ እንደነበር ልነግራቸው እወዳለሁ፡፡ ዶክትር ደብረፅዩን ከአቀረቡት ሪፖርቱ ውስጥ የቴሌን ሰራ ለመስራት የፈጠሩት አደረጃጀት አንድ ጥሩ ነገር ጠቆም አድርጎን አልፏል፡፡ ይህም ፓርላማው ማፅደቅ የማያስፈልገው የቴሌን አገልግሎት በአሰራ ሦስት ክበቦች ወይም ክልሎች መከፋፈላቸው ነው፡፡ ይህም የተደረገው ለአሰራር ቅልጥፍና ሲባል እንደሆነ መረዳት ይቻላል፡፡ ይህ ተቀባይነት ያለው በጎ ጅምር ነው፡፡ በዚህ አደረጃጀት ሀረሪ ወይም ድሬዳዋ በምንም መለኪያ አንድ ክልል ሊሆን አይችሉም፡፡ አዲስ አበባ እንኳን አንድ ክልል ሊሆን አልቻለም፡፡ ሌሎችም በተመሳሳይ እንዲሁ፡፡ ይህ ለቴሌ አገልግሎት ምቹ የሆነ አደረጃጀት ለሌሎች የመልካም አስተዳደር እንዲሁም ማህበራዊ፣ ኤኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ጠቀሜታ በሚመች መልኩ የፌዴራል ስርዓቱ ይዋቀር ለምንል ሰዎች እንደ ጥሩ መግቢያ ሊያገለግል ይችላል የሚል እምነት አለኝ፡፡የፌዴሬሽን ምክር ቤት ይህን ሀሳብ ከዶክተር ደብረፅዮን ወስዶ የህዝቦችን ቋንቋ እና ስነ ልቦና መሰረት ባደረገ ሁኔታ ቢየጠናው ጥሩ ሀሳብ ይመስለኛል፡፡ እሰኪ አንዴ ከያዝነው አስተሳሰብ ወጣ ብለን በተለየ መንገድ ለማሰብ እንሞክር፡፡ ዶክተር ደብረፅዩን ያቀረቡት ሀሳብ በሌሎች ፌዴራል መስሪያ ቤቶችም ሊሞከር ይችላል፡፡ ይህ የምክር ቤት ውሳኔ አይጠይቀም ብለዋልና፡፡
የንግድ ሚኒስትሩ አቶ ከበደ ጫኔ ባለፈው ዓመት ሰኳር እና ስንዴ እጥረት እንደነበረ በይፋ አምነዋል፡፡ ያቀረቡት ምክንያትም ሰኳር ይደርሳል ተብሎ ተገምቶ በፊንጫ እና ተንዳሆ ሰኳር ፋብሪካ በእቅዱ መሰረት ባለመድረሱ ችግር መከሰቱን ነው፡፡ እኛም ሰንል የነበረው ችግር አለ በእቅድ መስራት አልቻላችሁም እንዲሁም አትችሉም ነው፡፡ የሰንዴም የሰኳርም እጥረት የለም ሲሉን እንዳልነበር አሁን ችግር መኖሩን አምነው ከውጭ ግዥ እየተፈፀመ እንደሆነ ነግረውናል፡፡ ይህች ሀገር በሌላት የውጭ ምንዛሪ በሀገር ውስጥ ሊመረት የሚችልን ምርት ከውጭ እንድታሰገባ እያደረገ ያለን ፖሊሲና ፈፃሚዎቹ ተጠያቂ ሊያደርግ አልቻለም፡፡ ሰኳርና ስንዴ ማቅረብ ያልቻለ የሃያ ዓመት አገዛዝ መዘዝ ሊመጣበት እንደሚችል ቢፈራ ተገቢ ነው፡፡ አንድ በግብርና ላይ የተሰማሩ ባለሀብት ፈራ ተባ አያሉ “ስንዴ ከውጭ ታዞ የሚመጣበት ገዜ እና በሀገር ውስጥ ቢመረት የሚወሰደው ጊዜ ተቀራራቢ ነው፡፡” ብለዋል፡፡ አስከትለውም “ኢትዮጵያ ሰንዴና ሰኳር ኤክስፖርት የምታደርግ ሀገር እንጂ ከውጭ የምታስገባ መሆን የላባትም፡፡” በማለት ድጋፍ እንዲደረግላቸው ጠይቀዋል፡፡ ግብርና ግን መሬት ይፈልጋል መሬት ደግሞ በመንግሰት እጅ ሆኖ እንደልብ የሚገኝ አይደለም፡፡ የመሬት ፖሊሲያችን ይፈተሸ ስንል ለምን ጫጫታ ይበዛል?
የፍትሕ ሚኒሰትር ሪፖርት በጥቅምት ወር ባቀረቡት እቅድ በግርፊያ ምርመራ ያደርጋሉ ያሉዋቸውን ፖሊሶች እንዴት እንደተቆጣጠሩ ሳይነግሩን ቢጫ ታክሲ ማህበራት ጋር ስብሰባ አድርገናል እና የመሳሰሉትን ሪፖርት ማድረግ ምን ፋይዳ እንዳለው መረዳት ከባድ ነው፡፡ አስገራሚው ደግሞ ፍትህ ሚኒስትር የሚያዘጋጀው የዜጎች ቻርተር ነው፡፡ በእኔ እምነት ፍትህ ሚኒስትር ከህገ መንግሰቱ የተሻለ ሌላ የዜጎች ቻርተር የሚያስፈልገው አይመስለኝም፡፡ በፍትህ ሰርዓቱ እምነት እንዲኖረን ህገ መንግሰቱን ማስከበር ላይ ትኩረት መስጠት ይኖርበታል ብዬ አምናለሁ፡፡ ከሌሎች የመንግሰት አካላት ጋር ተባብሮ የህገ መንግስቱን መስረታዊ ድንጋጌዎች መናድ ማቆም አለበት፡፡ ለዚህም ማሳያው በቅርቡ በመፅሔቶች እና ጋዜጦች ላይ በመንግሰት ሚዲያ የተጀመረውን ስም ማጥፋት ተከትሎ በፍትህ ሚኒስትር መሪነት ወደ ፍርድ ቤት ማምራቱ ነው፡፡ ዘጠና ሚሊዮን ለሚሆን ህዝብ ቢበዛ 20 ሺ ኮፒ ለሚያትም  አንድ መፅሔት ሀገር ሊያጠፉ ነው የሚል መዓት ማውራት ምን አመጣው? ለነገሩ የፈሪ ዱላ የሚባለው ብዒል አንደሆነ መገመት አያሰቸግረም፡፡ ግለሰቦችን እያሳደዱ በማሰር እና አሰሮ ማሰረጃ እያፈላለኩ ነው ከሚል ፌዝ  መውጣት ይኖርብናል፡፡ መንግሰት “የፀረ ሸብር ህግ” ያሰፈልገናል ሲል የነበረው ሰዎችን ሳይዝ በቂ ማሰረጃ ለመሰብሰብ ይጠቅመኛል በሚል እንደነበር እናስታውሳለን፡፡
የከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስትሩ አቶ መኩሪያ ኃይሌ ይህ ነው የሚባል ነገር ሳያቀርቡ ሰዓት ሰዓት አልቋል ቢባሉም በከተማው የተንሰራፈውን የቤት ችግር ለመቅረፍ በተለይ በማሕበር ለመገንባት ገንዘባቸውን ባንክ ላስገቡ፣ ቅድሚያ ታገኛላችሁ ተግለው ከሚፈለገው 40 ከመቶ በላይ ባንክ ያስገቡ በ40/60 የተመዘገቡ እና በውጭ በሚኖሩ ኢትዮጵያዊየን በጉጉት ሲጠበቅ የነበረውን የቤት አቅርቦት ማሳካት አለመቻል አንድም ነጥብ ሊያነሱ አልቻሉም፡፡ ዜጎች ቤት እናገኛለኝ ብለው ተብደረው ባንክ ያሰቀመጡትን ገንዘብ የመንግሰት ባንክ እየነገደበት ትርፍ በትርፍ ሲሆን ዜጎች ቀጣይ ተሰፋቸው ምን እንደሆነ እንኳን ማሰረዳት አልቻሉም፡፡ አዲሱ የኮንዶሚኒየም ቤቶች ምዝገባ የተጀመረ ሰሞን አንድ ፅሁፍ አቅርቤ እንደ ነበር ይታወሳል፡፡ በሚቀጥለው ዓመት የቤቶች ግንባታን አስመልክቶ ሂሳብ ማውራረድ ስለሚኖር ለዛሬው በዚሁ ማለፍ ይሻላል፡፡ ዜጎች ግን አሁንም ተሰፋ እያደረጉ ነው?
በመጨረሻ ሁሉም ሪፖርት አድራጊ መስሪያ ቤቶች እንደ ችግር ያነሱት “የከፍተኛ አመራር እና ፈፃሚዎች የአመለካከት ችግር መኖር” የሚለው ይገኘበታል፡፡ ይህ ችግር ሁሌም በኢህአዴግ ሰፈር እንዳለ የምንረዳው ስለሆነ መፍትሔው በየአዳራሹ እየመሸጉ ሰልጣና፣ ስልጣና እየተባለ የሀገር ሀብትና ንብረት ከማባከን ተጠያቂነት የሚያሰፍን ሰርዓት በመዘርጋት ኃላፊነቱን ብቃት ላለው ዜጋ ማስረከብ ነው፡፡ አሁን በኢህአዴግ አባልነት በመንግሰት ስልጣን ላይ የሚገኙት በአብዛኛው ከዝቅተኛ ደረጃ እስከ ማስተርስ እና ከዚያም በላይ በርቀትም ሆነ በመደበኛ ይህች ሀገር አስተምራለች፡፡ እነዚህ ኃለፊዎች ባለፉት ሃያ ዓመታት የሰለጠኑ ቢሆንም ለህዝብ መልካም አስተዳደር ለማስፈን የሚያስችል አመለካከትና ክዕሎት ማደበር አልቻሉም፡፡ ስለዚህ ቦታውን መልቀቅ ግድ ይላቸዋል ብንል ድፍረት ሊሆን አይችልም፡፡ ቦታውን የማስለቀቅ ኃለፊነት ደግሞ የህዝብ ነው፡፡ የህዝብ ድምፅ ይከበር ዘንድ ሁሉም የድርሻውን መወጣት አለበት፡፡ ማንም የማንም ነፃ አውጪ አይደለም፡፡

ቸር ይግጠመን!!!

Keine Kommentare:

Kommentar veröffentlichen