Netsanet: በስዊድን የኤርትራ ኤምባሲ አጣብቂኝ ውስጥ ገባ ኤምባሲው ዜጎቹን እንደሚሰልል ተረጋግጧል

Montag, 8. September 2014

በስዊድን የኤርትራ ኤምባሲ አጣብቂኝ ውስጥ ገባ ኤምባሲው ዜጎቹን እንደሚሰልል ተረጋግጧል

በስዊድን የኤርትራ ኤምባሲ በስደት አገራቸውን ጥለው የወጡ የኤርትራ ስደተኞችን እንደሚሰልል ተረጋገጠ። የስዊድን መንግሥት በደረሰው ጥቆማና ማስረጃ መሰረት ባደረገው ማጣራት ኤምባሲው በስለላ ስራ ተሰማርቶ ስዊድን ከለላ የሰጠቻቸውን የኤርትራ ተወላጆች አንደሚከታተልና እንደሚሰልል ማስረጃ ተይዞበታል።
ተቀማጭነታቸው ስዊድን የሆነ የጎልጉል ተባባሪዎች ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ክፍሎች ጋር በመነጋገር እንዳመለከቱት፣ የስዊድን ዜግነት ያላቸውንና ሻዕቢያን ለማስወገድ የሚንቀሳቀሱ ድርጅቶችን የሚደግፉ፣ አክቲቪስት የሆኑትን የኤርትራ አገዛዝ በኤምባሲው አማካይነት እንደሚስልላቸው የታወቀው በጥቆማ ነው።
ውስን ቁጥር ያላቸው በስዊድን የሚኖሩ የኤርትራ ተወላጆች ባቀረቡት ጥቆማ መሰረት የስዊድን መንግሥት ባካሄደው ማጣራት የኤርትራ ኤምባሲ የተከሰሰበትን ተግባር እንደሚፈጽም ተረጋግጧል። የመረጃው ባለቤቶች እንዳሉት ስደተን ሸሽተው የሚኖሩበት አገር ድረስ እየተከታተሉ መሰለል በህግ የተከለከለ በመሆኑ የኤርትራ ኤምባሲ ሊዘጋ እንደሚችል ፍንጭ ማግኘታቸውን አመልክተዋል።
ይህንኑ የተረዳው የሻዕቢያ አገዛዝ ከውሳኔው በፊት የምርመራውን ውጤት ለማስገልበጥ የበኩሉን እየሰራ መሆኑንን ከመረጃው አጠናካሪዎች ለመረዳት ተችሏል። የስዊድን መንግሥት በኤርትራ እስር ቤት ታስሮ ይሙት ይዳን በይፋ በማይታቀወቀው ጋዜጠኛ ዳዊት ይስሃቅ ጉዳይ ከፕሬዚዳንት ኢሳያስ ጋር ሲወዛገብ እንደነበርና ጉዳዩ እስካሁን እልባት እንዳላገኘ የመረጃው አቀባዮች አመልክተዋል።
በተለያዩ አገራት በትውልድ አገራቸው ያለውን አገዛዝ ኮንነው የጥገኛነት ማመልከቻ የሚያስገቡ፣ ከለላ ከተሰጣቸው በኋላ “በደለን” ለሚሉት አገዛዝ ሲላላኩና ሲሰሩ ባደባባይ እንደሚታይ በመጠቆም አስተያየት የሰጡ፣ ይህ የኤርትራ ተወላጆች መረጃ ላይ ያተኮረ ክስ ለኢትዮጵያዊያን ታላቅ ትምህርት እንደሚሆን ተናግረዋል።
በአሜሪካና በተለያዩ የአውሮጳ አገሮች ኢህአዴግ ዜጎችን እየተከታተለ እንደሚሰልል፣ በአፍሪካ ድንበር አቋርጦ የፈለገውን ከመሰለል አልፎ እንደሚያስርና እንደሚገድል ያስታወሱት አስተያያት ሰጪ “ተቃዋሚዎች የኢህአዴግ ኤምባሲዎች የስለላ ስራ እንደሚሰሩ ማስረጃ በመሰብሰብ ክስ ሊመሰርቱ ይገባል” ብለዋል።
ጋዜጠኛ ዳዊት የስዊድን ዜግነት ያለው ሲሆን 2001 ላይ ነበር የታሰረው። በኤርትራ የመጀመሪያዋ “ሴቲት” ጋዜጣ ሪፖርተርና ሸሪክ ባለቤት የነበረው ዳዊት በመስከረም 2001 ከመኖሪያ ቤቱ ታፍኖ ሲወሰድ በተመሳሳይ 10 የሚሆኑ ጋዜጠኞችም መታሰራቸው በወቅቱ ዓለምአቀፉ የጋዜጠኞች መብት ተከላካይ ድርጅት (ሲፒጄ) ዘግቦ ነበር። ከነሱም በተጨማሪ ተለምዶ G15 የሚባሉት የለውጥ አራማጅ ባለስልጣኖች አብረው ታስረዋል። ዳዊት የት እንደታሰረ ባለስልጣናት እንኳን እንደማያውቁ አቶ አሊ አብዶ የቀድሞው የማስታወቂያ ሚኒስትር ኢሳያስን ከድተው ከኮበለሉ በኋላ መግለጻቸውን በስዊድን የሚገኙ መገናኛዎች ወንድማቸውን ጠቅሰው መዘገባቸው ይታወሳል።
“የፕሬዚዳንት ኢሳያስ ልጅ” የሚባሉት አቶ አሊ፣ ዳዊት በህይወት እንደሌለ ፍንጭ በመስጠት ቀዳሚው ባለስልጣን ሆነዋል። የሆነ ሆኖ ሻዕቢያ በጋዜጠኛ ዳዊት ጉዳይ በግልጽ እምነት ክህደት አላካሄደም። ጋዜጣ ከኤርትራ ምድር እንዲታገድ መደረጉን በወቅቱ የወጡ መረጃዎች ያመለክታሉ። 
source: ጎልጉል

Keine Kommentare:

Kommentar veröffentlichen