በመጪው ግንቦት ወር የሚካሄደውን አምስተኛ ዙር አገር አቅፍ ምርጫ ጠቅላላ የምርጫ ጊዜ ሰሌዳን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ጽሕፈት ቤት ይፋ አደረገ፡፡
ሐሙስ ዕለት በሒልተን ሆቴል በቦርዱ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች አቶ መርጋ በቀና (ፕሮፌሰር) በሚኒስትር ማዕረግ የቦርዱ ሰብሳቢ፣ አቶ አዲሱ ገብረ እግዚአብሔር (ዶ/ር) የቦርዱ ምክትል ሰብሳቢና አቶ ነጋ ዱፌሳ የቦርዱ ጸሐፊና የጽሕፈት ቤት ኃላፊ በጋራ በሰጡት መግለጫ፣ ዘንድሮ የሚካሄደውን አገር አቀፍ ምርጫ የተመለከቱ ዝርዝር የጊዜ ሰሌዳን አብራርተዋል፡፡
የቦርዱ ሰብሳቢ በወቅቱ እንደገለጹት፣ የፊታችን ግንቦት የሚካሄውን አገር አቀፍ ምርጫ በስኬት ለማከናወን የሚያስፈልጉ ቅድመ ዝግጅቶች በመጠናቀቅ ላይ ናቸው፡፡ ከፖስተርና ከኮሮጆ ማዘጀት ጋር የተያያዙ ጉዳዮች 90 በመቶ መጠናቀቃናቸውን አክለው ገልጸዋል፡፡
በዚህም መሠረት የዘንድሮ አምስተኛው ዙር ምርጫ የዕጩዎች የምርጫ ውድድር እንቅስቃሴ የካቲት 7 ቀን 2007 ዓ.ም. በይፋ ተጀምሮ ግንቦት 13 ቀን ከምሽቱ 12 ሰዓት ላይ እንደሚጠናቀቅ ቦርዱ ባወጣው የጊዜ ሰሌዳ ተገልጿል፡፡ የምርጫው ዕለት ደግሞ ግንቦት 16 ቀን 2007 ዓ.ም. እንደሚሆንና የምርጫው አጠቃላይ ውጤት በብሔራዊ ደረጃ በይፋ ለሕዝብ የሚገለጽበት ዕለት ደግሞ ሰኔ 15 ቀን 2007 ዓ.ም. ይሆናል በማለት ቦርዱ ይፋ አድርጓል፡፡
ቦርዱ ይፋ ያደረገው ዝርዝር የጊዜ ሰሌዳ 30 የሚሆኑ ዝርዝር ጉዳዮች የቀረቡበትና እስከ ምርጫው ፍጻሜ ድረስ የሚከናወኑ ክንውኖችን ያካተተ ሲሆን፣ በዚህም መሠረት በምርጫ የሚወዳደሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች የመወዳደሪያ ምልክታቸውን የሚመረጥበት ዕለት ከኅዳር 15 እስከ ኅዳር 30 ቀን 2007 ዓ.ም.፣ የምርጫ ጣቢያዎች ተከፍተው ሥራቸውን በይፋ የሚጀምሩበት ዕለት ታኅሳስ 30 ቀን 2007 ዓ.ም.፣ የመራጮች ምዝገባ በየምርጫ ጣቢያው የሚካሄድበት ጊዜ ደግሞ ከጥር 1 ቀን እስከ የካቲት 12 ቀን 2007 ዓ.ም. እንደሚሆን ተገልጿል፡፡
ከሁለት ሳምንት በፊት ከፓርቲዎች ጋር በተደረገ የውይይት መድረክ ላይ የተሳተፉ ፖለቲካ ፓርቲዎች ያላቸውን አስተያየት በምርጫ ቦርዱ ያስገባሉ መባሉንና የፓርቲዎቹ አስተያየት በዚህ የጊዜ ሰሌዳ ላይ ምን አስተዋጽኦ አበርክቷል በሚል ከሪፖርተር ለቀረበ ጥያቄ፣ የቦርዱ ሰብሳቢ ‹‹ከፓርቲዎቹ ባገኘነው አስተያየት መሠረት የእጩ ምዝገባ ጊዜና የመራጮች ምዝገባ ጊዜ ተስተካክለዋል፤›› በማለት ምላሻቸውን ሰጥተዋል፡፡
Keine Kommentare:
Kommentar veröffentlichen